ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ

በጉግስ ጨዋታ ክንዳቸው ጠንካራ አይደለም፣ ስስ ነው። ሜዳውን ግን በቀላሉ ደክመው አይለቁም። እዚያ ላይ ጠንካራ ናቸው። ማንም እንደሚያስታውሳቸው ወፍራም አይደሉም ። ቀጭንና ሸንቃጣ ናቸው። ምግብ ፣ ጥሬ ሥጋና ቅልጥም፣ ቅቅልና ጥብስ ብዙ ጀግና እንደሚያደርገው እሳቸው እይወዱም። ብዙዎቹ እንደሚመሰክሩት ጠንካራ መጠጥ እንደሌሎቹ ውሲክና ኮኛክ፣ ጠጅና ነጭ አረቄ አይደፍሩም። አይጠጡም። ከዚህ ሁሉ ይልቅ ግፋ ቢል ሻፓኛና ካቪያ:- የዓሣ እንቁላል፣ ትንሽ የአታክልትና የጠቦት በግ ሾርባ ይመርጣሉ።አደን ይወርዳሉ። ፈረስ ይወዳሉ። ከስው ይልቅ –ይህ በእሳቸው አልተጀመረም–ውሻ ያቀርባሉ።
በፎቶ ግራፍ እነደምናውቃቸው ግዙፍና ረጅም አያደሉም ። አጭር ናቸው። ነገር ግን በአዚያ ቁመታቸውና ግርማ ሞገሳቸው አዳራሹን ብቻቸውን እኝህ ንጉሥ ይሞላሉ።
ናፖሊዮን አንዴ አጃቢ ፣ልብስ አልባሽ ወታደሩን — (አጭር ነው እሱ) ናፖሊዮን ባርኔጣውን ከቁም ሳጥኑ ላይ ለማውርድ መከራውን እጁን ሰዶ ሲያይ ፣ ወታደሩ ደርሶ ተመልክቶ በጌታው በንጉሱ ተደንቆ ማንነቱን ግን ለማሳየት “…እኔ ትልቅ ነኝ እስቲ ልርዳዎት ዞር ይበሉ” ሲለው “…አንተማ ረጅም ነህ እንጂ፣ ትልቅ አይደለህም ።ትልቅ ማለት እኔ ነኘ ፣ አንተ ግን ረጅም፣ሰው ነህ…”እንዳለው ሁሉ ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ገና ልጅ ሁነው ፣ ትምህርት ቤት ሲሄዱ በተፈሪ ዘመናቸው፣ “ትልቅና አስተዋይ ሰው” ነበሩ። አምባሳደር ዘውዴ ይህን የትምህርት ጊዜአቸውን ሳይበዛ አንስተዋል።
የፕሩሲያው ንጉሥ ዳግማዊ ቪሊሔልም ወደ አጼ ምኒልክ የላኩት የጀርመኑ ልዑካን ቡድን፣ ጅቡቲ አርፎ ፣ ሐረር ድንበር ላይ ራስ መኮንን አነጋግሮ- እሳቸው ያኔ የአገር ድንበር ጥበቃ ላይ ነበሩ- በድሬደዋ አቆራርጦ ይኸው ቡድን ወደ አዲስ አበባ ከመድረሱ በፊት ፣ ራስ መኮንን ልጃቸውን ፣ “ወጣቱን ተፈሪን አይተው እንዲሄዱ ጠይቀዋቸው” ነበር።
እንደ ደረስንም ይላል የቡድኑ መሪ ቮን ሮዝን ፣ ያኔ ይወጣ በነበረው ዕለታዊ ጋዜጣ ላይ ከአዲስ አበባ ሁኖ ወደ በርሊን በላከው ጽሑፉ”…ገና የዘጠኝና የአሥር አመቱ የራስ መኮንን ልጅ እንደትልቅ አዋቂ ሰው ተቀብሎን እኛን በሥነ-ሥርዓቱ እንድንቀመጥም ቦታ ሰጥቶን፣ የቤት የእልፍኝ አሽከሮቹን እያዘዘ፣ ይህን አቅርቡላቸው፣ ያን አድረጉ፣እያለ እንደ አባቱ እያዘዘ፣ ይህ ነው የማይባል መስተናግዶ፣ ይገርማል!ወጣቱ ልጅ አደረግልን። ይህ ልጅ በአነጋገሩ፣ በጥያቄና መልሱ፣ በአስተያየቱና በአስተዳደጉ ወደፊት በምኒልክ ቤተ-መንግሥቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚኖረው ሰው መሆኑ ከአሁኑ ያስታውቃል።” ብሎ የተመለከተውን ሁኔታ ወደዚህ ልኮ ያኔ የነበሩት የጀርመን አንባቢዋችን፣ ነገሩ አስገርሞ ነበር።

“የሸዋ መኳንንት (እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌላውም የኢትዮጵያ) በልቶ ተለያየ፣
መኮንን ብቻ ነው ለልጁ ያቆየ…”
ተብሎ በሁዋላ በየአለበት ሲነገርላቸው፣ ተፈሪ መኮንን፣ ያኔ! ስንት መሰናክል አቋርጠው “ልዑል ራስ” ተብለው” የአልጋ ወራሽነቱን ቦታ ቀስ እያሉ በብልሃት ይዘዋል። ትንሽ ቆይተውም የጎንደር ንጉሥ ተብለው፣ እኝህ መስፍን ዘውዱን ከንግሥት ዘውዲቱ እጅ ተቀብለዋል።
ምናልባት ቀጭንና ሸንቃጣ፣ ክንዳቸውም “ጠንካራ” በአለመሆኑ፣ አንዱ እንደጻፈው፣ ወደ ፖሊቲካ ጥበብና ወደ ዲፕሎማሲ አዘንብለው ፣ ልጅ ተፈሪ መኮንን፣ ቀስ እያሉ እየተጠነቀቁ ሌሎቹን ጨዋታና ፌዝ፣ ዝሙትና ሴሰኛነትን፣ ጉራና ፉከራን የሚወዱትን መኳንንትና መሳፍንቱን ፣ ሁሉ ጉድ አድርገዋል።
ነጻነቱዋን ለማስመለስ ከጦር ሜዳ ይልቅ ወደ ጄኔቫና ወደ እንግሊዝ የተንቀሳቀሱበት ምክንያት፣ ከዚሁ የመነጨም ሊሆን ይችላል።
ይህም እርማጃቸው በወኔ በሚያምነው የኢትዮጵያ ጀግኖች ዘንድ የማይገባ ስም አትርፎላቸዋል። ትክክለኛ እንደነበር ያመጡት ውጤትም መስክሮላቸዋል። እንደሳቸው አደጋ ላይ ወድቆ የነበረ የቻይና ንጉሥ የጃፓኖች “መቀለጃ” ሲሆን፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ በስንት ብልሃት ከጣሊያንና እኛን ከረዱን እንግሊዞች እጅ አምልጠው የኢትዮጵያን አንድነትና ነጻነቱዋን አስመልሰዋል።

በአንዴም እንደ ቀጥታ መስመር ጉዞ፣ ከወረዳና ከአውራጃ ገዢነት፣ ወደ ጠቅላይ ግዛት፣…ከደጃዝማችነት ወደ ራስ፣ ከዚያ ወደ ልዑል ራስ ፣ቆይቶም ንጉሥ፣… ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴና አልጋ ወራሽ፣ በመጨረሻም ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሰ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ፣ ተብለው ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ ም (የኢት. ዘመን አ.)፣ የዓለም ተወካዮች በተገኙበት ሊነግሱም፣ ወጣቱ መስፍን ችለዋል። ማን ነው በንግሥ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኘው? ማነው ያልተገኘው?
ሁሉም መጥተዋል።
ኤቨሊን ዋግ (Evelyn Waugh)ያ እሽሟጣጭ ጋዜጠኛ፣ ” የአንድ አስገራሚ ሕዝብና ወጉ” በሚለው መጽሓፉ፣ እራሱ ወገኛ ሁኖ “በአንድ የእንግሊዝ ጨዋ ሰው (ጄንትልማን) “በሚለው ጽሑፉ (ሰውዬው አለጥርጥር ግሩም የብዕር ሰው ነው) ብቻ! አሽሟጦ የኃይለ ሥለሴን የንግሥ ሥነ-ስርዓት ለእንግሊዝ አንባቢዎች በአቀረበው ጽሑፉ ስንት ትላልቅ የአውሮፓ ነገሥታት ተወካዮች እንደመጡ ይህ ሰው ዘርዝሮአል።
ኢትዮጵያ በዓለም ፖለቲካ ልዩ ቦታ ነበራት።
በዚያን ዘመን የነበረውንም የዕድገት ሁኔታም ምን ደረጃ ላይ እንደነበርም ማወቁ ይጠቅማል። ግን በማንኛውም የባህል ታሪክ ወሳኙ፣ ኤቨሊን አዲስ አበባ ወርዶ ያጣው ልብስ፣ ጫማና፣ ፎቅ ቤቶች አይደሉም። ሮም አቴነም ያኔ ዓለምን ሲያንቀጠቅጡ እነሱም ፎቅ ቤቶች፣… አልነበራቸውም።
…..
ከየት አገኙት ተፈሪ መኮንን ይህን ሁሉ ጥበብ?… የእግዚአብሔር ጸጋ ነው?… ጊዜው አመች ስለሆነ ነው? በጥሩ የጀሲዊቶቸ አስተማሪዎች እጅ በማደጋቸውና በመማራቸው ነው? የሰው ምክር በማዳመጣቸው? በቂ ገንዘብ ስለነበራቸው? ዕጣ ዕድሉ በእሳቸው ላይ ስለወደቀ?
ኢትዮጵያ ተቸግራ፣ በመከራ ጊዜ ያገኘቻቸው አንድ ሰው በመሆናቸው ነው?

ታሪክ ” የኣቦ ሰጡኝ ልጆች የሕልም እሩጫ ወይም የዕብዶች ሥራ” ሳይሆን የብዙ ነገሮች መገጣጠም ውጤት ነው። በእርግጥ ማለት የምንችለው፣ አጼ ምኒልክ፣ አንድ ጎናቸውን በ”ስትሮክ” /በአደንዛዥ በሽታ/ ተመተው፣ በድንገት ታመው ባይሞቱ ኑሮ፣ ከዚያ በፊት አልጋወራሽ ልጃቸው ልዑል ወሰን ሰገድ እንደዚሁ በድንገት በሃያ አመቱ እሳቸውን ቀድሞ ባይሄድ ኑሮ፣ ራስ መኮንን እነደዚሁ ባያርፉ፣ ልጅ ኢያሱ በልጅነት ዕድሜአቸው ባይቀብጡ፣ ጣይቱ ብጡል አንድ ልጅ ለምኒልክ ቢወልዱ፣ “የሪፓብሊካኖች ክለብ” በአገሪቱ ቢኖር …ወዘተ፣ ወዘተ፣…. የወጣቱ መስፍን ፣ የተፈሪ መኮንን ዕጣ ዕድል ሌላ መንገድ በያዘ ነበር።
ሐረርንም ተሹመው ያገኙት፣ ታላቅ ወንድማቸው ደጃች ይልማ መኮንን አባታቸውን ተከትለው በማረፋቸው እንጂ፣ እሱንም፣ ግዛት ታላቃቸው እያሉ፣ ወጣቱ ተፈሪ፣ አያገኙትም ነበር።
የጄሲዊቶቸ ትምህርት አለጥርጥር ረድቶአቸዋል። ጀሲዊቶች ደግሞ ለወጣት ተማሪዎች የሚሰጡት ትምህርት የሚያስተላልፉት ኤቲክና ሞራል ቀላል አይደለም። እዚህ የእነሱን ትምህርት የቀመሰ የሚሰራውን ያውቃል።
ንጉሠ-ነገሥቱ አልፎ አልፎ ወይም አዘውትረው የሚየናቡዋቸውን መጽሓፍቶች ጽሕፈት ቤታቸው ኢዮቤሊው ቤተ መንግሥት ገብቼ ለማየት ፈልጌ ነበር። ግን ይህ አልሆነልኝም። አልተሳካም። እዚያ ላይ የኒኮሎ ማኪያቬሊን መጽሐፍ ሲያነቡ ምን ቦታ ላይ አስተያየታቸውን ጥለው እንደሄዱ፣ ሼክስፒርን ሲያገላብጡ ምን እንደተገነዘቡ፣ የወዳጃቸውን የዳንቴን ግጥሞች ሲከታተሉ ምን እንደታያቸው ለመከታተል ፈልጌ ነበር። ግን ይህ አልተሳካልኝም።
መጽሓፍቶቹስ አሁን የቀድሞ ቢሮዋቸው ቢኖሩ አይደል?
ስንት መዝገብ ማገላበጥ በቻልን ነበር። ግን እነሱስ ሳይቃጠሉ እስከ አሁን ድረስ አሉ? እግዚአብሔር ይወቀው።
ምናልባት በዚያን ዘመን አጠገባቸው የነበሩ አማካሪዎቻቸው፣ ጸሐፊዎቻቸው፣ ሚኒስትሮቻቸው አንዳንድ ነገሮችን ጫርጫር አድርገውልን ጠረጴዛዎቻቸው ውስጥ አስቀምጠውልን፣ ዞር ብለው ይሆናል። ከልዑል ራስ እምሩ ብዙ ነገር እኔም እንደሌሎቹ ጠብቄ ነበር ። ግን ልብ ሳልል አልፌ ይሆናል እንጂ፣ ምንም ነገር አላገኘሁም። ደጃች ከበደ ተሰማ ሌላው ሰው ነበሩ። እሳቸውም የጻፉት ነገር ይኑር አይኑር ምንም አይታወቅም። የንጉሡ የልጅ ልጆች ስለ አያታቸው ቢጽፉ ጥሩ ነበር። ሌሎቹስ?
ነጮች የጻፉአቸው አሉ። ከሁሉም አምባሳደር ዘውዴ ረታ በተከታታይ ያቀረቡልን ሁለቱ መጽሓፍቶች ግሩም ናቸው።

ቀኃሥ በ20ኛው ክፍለ ዘመን፣ በረጅሙ የግዛት ዘመናቸው ብዙ ነገር ለአገሪቱ ኢትዮጵያ አድርገዋል። ነጻ የመንግሥት ትምህርት ቤት ከፍተው ትምህርትን አስፋፍተዋል።ዘመናዊ ሥልጣኔን ከአገሪቱ ጋር አስተዋውቀዋል። ሐኪም ቤት፣ መጽሓፍት ቤት፣ የቲያትር አዳራሾችን፣ የሙዚቃ ትምህርት ቤትና የኦርኬስትራ ቡድኖችን፣ ስፖርት፣ የኩዋስ ሜዳዎችና የተለያዩ ቡድኖችንን፣ የኪነ ጥበብ ትምህርት ቤትንና ሰዓሊዎችን፣ ድርሰትና ደራሲዎችን፣ አየር መንገዱን፣ የባህርና የጦር ኃይሉን ፣ ተግባረዕድ ትምህርት ቤቶችን አቋቁመዋል። አበረታተዋል። አፍርተዋል።
ከስድሳ አመት በላይ በወሰደው የፖለቲካ ዘመናቸው ብዙ ነገሮች ደግሞ ለአገሪቱ ለማድረግ ፣ ምንም የሚያግዳቸው ነገር ስለአልነበር በቀላሉ ይችሉ ነበር። በቀላሉ?
ግን ደግሞ ወደፊት እናነሰዋለን እንጂ በገጠማቸው መሰናክሎች ምክንያት፣ እንዳሰቡት ሊያደርጉት አልቻሉም።
ምንድነው አስበው፣ አቅደው የነበሩዋቸው ነገሮች?
እንደ ዓለም ታላላቅ ሰዎች፣ እንደ ትልቁ እስክንድር፣ እንደ የሩሲያው ትልቁ ጴጥሮስ፣ እንደ ቀዳማዊ ናፖሊዮን፣ እንደ ዩሊዮስ ሴዛር ቋሚ ሥራ ሰርተው ለመሄድ አስበው እንደ ነበር ጥርጥር የለንም። ይህን ጉዳይ ግን “የሕይወት ታሪካቸውን “ኢንዲጽፉ የተመደቡት ሰው፣ አቶ ከበደ ሚካኤል ምናልባት “አዳምጠው” ሊሆን ይችላል። የሚታወቅ ነገር ቢኖር “በጊዜው ሳያደርሱ”ቀርተው፣ ያ የባዮግራፊ ሐሳብ (ደጃች ዘውዴ ገብረ-ሥላሴ እንዳሉት) ሜዳ ላይ ወድቆአል።
እራሳቸው ንጉሡ የጻፉት መጽሐፍ (ስለ የተወሰነ ዘመን ነው የሚያትተው) ብዙም ነገር አላዘለም።

ኢትዮጵያን ግን ቀኃሥ በግዛት ዘመናቸው የበለጠ አንድ አድርገዋታል። በቅኝ ገዢዎች እጅ ትማቅቅ የነበረችውን ኤርትራን በስንት የዲፕሎማቲክ ትግል መልስው ከኢትዮጵያ ጋር አዋህደዋታል። እንኩዋን ኤርትራን ፣ ሌሎቸም የአፍሪካ መንግሥታት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ ኢንዲወጡ ትልቅ አስተዋዕጾ አድርገዋል። አልፈው ተርፈው ጠላት ያፈሩበትን “የገለልተኛ መንግሥታትን ማህበርን ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጋር ” አቋቁመዋል።
ግን ምን ይደረጋል ብዙ መስራት የሚገባቸውን ጊዜ፣ እሳቸው”… ጊዜን ሥሩበት እንጂ አይሥራባችሁ!” እያሉ ሲያስጠነቅቁን፣ ሳይሰሩበት፣ እራሳቸው ባአስተማሩአቸው ልጆች “ተቀድመው”፣ በእነሱ እጅ ንጉሡ ወድቀዋል።
በእሳቸው ላይ ብቻ ሁሉን ነገር መለጠፍ አይቻልም።
አሁን ከዚህ ሁሉ አመት በሁዋላ መለስ ብለን ያለፈውን ጊዜያት ስንመለከተው፣ ንጉሡ ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላው “የፖለቲካው መደብ በሙሉ” ያኔ ሥልጣኑን ይዞ የነበረው ክፍል፣ ይህም አማካሪዎቹን ይጨምራል፣ ለመጪው ትውልድ፣ ለአገሪቱ ለኢትዮጵያ ምንም ቋሚ ነገር፣ ለክፉ ቀን አዘጋጅቶና ነድፎ በአለማስቀመጡ፣ ሁሉም በጅምላ ሊወቀሱበት ይገባል።
እነሱን ብቻ መውቀስ ተገቢ አይደለም።
እንደ ጌጥ፣ እንደ የትግል ስልትና ፕሮግራም “መሰረታዊ ለውጥ፣ የምን ሪፎርም፣ ሥር ነቀል አብዮት፣ ሥር ነቀል፣ ሹምሽር…እስከ መገንጠል” ፤ ይሉ የነበሩ ወጣት ትውልዶችም፣ እነሱም አብሮ ተጠያቂዎች ናቸው። ከአንዳንድ ተባራሪ መጽሐፍቶች ከተለቀሙ የኮሚኒዝምና የሶሻሊዝም፣ ቃላቶች ሌላ ምንም ዓይነት መፍትሔ፣ ለአገሪቱ በጊዜአቸው በአለማቅረባቸው እነሱንም ይህ ጉዞአቸው ይስጠይቃቸዋል።
እንግዲህ የዚህ ሁሉ ትርምስና አለመዘጋጀት ደግሞ፣ ውጤቱ ይኸው አሁን የምናየው ነገር ውስጥ ሁላችንንም ወርውሮ ሄዶአል።
መሬት ለአራሹ ተባለ። ይህ የመሬት ጥያቄ ግን በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን መልስ ለማግኘት በአለመቻሉ መሬት “የሕዝብ ነው” ተብሎ ፖለቲካ በማያውቀው ወታደር በአወጅ ተወረሰ። ለመሆኑ ዛሬ የዚያ የኢትዮጵያ መሬት ባለቤት ማን ነው?
መሬት በአሁኑ ጊዜ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው መንግሥትና ከውጭ የመጡ የእነ ካራቱሪ፣ የእነ ሳውዲ፣ የእነ አላሙዲ፣ የእነ… ሐብት ነው።
መሬት ለአራሹ የተባለለት ገበሬ ዛሬ በእጁ፣ በደጁ ምንም የለውም። በእሱ ፋንታ 300 ሺህ ሔክታር ለካራቱሪ፣ 200 ሺህ ሔክታር ለሳውዲ፣ 40 በ60 ኪሎ ሜትር ለሱዳን፣ ለግብጽ፣ ለብራዚል…ይባላል።
የኢትዮጵያ ፓርላማ ያኔ፣ ለዚህ የተማሪም ይሁን የገበሬው የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፣ ማሰርያ መልስ ቢሰጥ ኑሮ ያ ትርምስ ሁሉ አሁን በቀረልን ነበር።
ግን ጥፋቱን ሁሉ በቀኃሥ ላይ ብቻ መለጠፍ ትክክል አይደለም።
እሳቸው አይደሉም ዛሬ የኢትዮጵያን መሬት ለ50፣ ለ70 እና 90 አመታት ለውጭ ቱጃሮች አሳልፈው ያስረከቡት። የኢትዮጵያ ነገሥታት ግዛት ያሰፋሉ፣ ድንበር ያጠነክራሉ እንጂ፣ መሬት ለውጭ ነጋዴ፣ ቱጃሮች አሳልፈው፣ አይሸጡም። እንዲያውም ነገር ያልገባቸው፣ የአውሮፓን የቅኝ ገዢዎችን ተንኮል አርቀው ያላዩ የአፍሪካ ባላባቶች፣ በአንድ ጠርሙስ አረቄ፣ በአንድ ጠበንጃ (በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን እንደታየው) ተታለው መሬታቸውን ለነጮቹ ሲሸሊሙና፣ በሁዋላ ሲነጠቁ፣ ቆይተውም የቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ገብተው ባሪያም ሆነው ሲሸጡ፣ ኢትዮጵያን አልደፈሩም። ሞክረው ግን ነበር። የአሰብ ወደብ ጥሩ ምሳሌ ናት። አደዋና ማይጨው ሌላው ነው።
ዱሮ በፈረስ ነበር ይባላል መሬት፣ ለአንዱ የሚሸለመው። ዛሬ በጀርመን ቴሌቪዥን ተቀርጾ እንዳየነው፣ ሞተር ብስክሌቶች በግራ ና በቀኝ ተለቀው “…የቻልከኸውን ያህል መሬት ውሰድ! ነው የተባልኩት። ምናልባት ” ሕንዱ እጁን እየመተረ፣” ምናልባት ግዛቴ እዚያ ተራራ ድረስ ሊሆን ይችላል…ምናልባት አዚያም አልፎ ይሄዳል” የሚባልበት አገር ሁኖአል።
በሁዋላ ሲታይ ያ ለውጭ ቱጃሮች፣ በሊዚ ለረጅም አመታት የተሰጠው መሬት፣ ቤልጅግን ፣ጋዜጠኛዋ እንዳለቺው ያካክላል።/1
/2
ተፈሪ መኮንን የተነጠቀውን አስመለሱ እንጂ ለማንም አሳልፈው አልሰጡም።
ነጻ-ምርጫ ንጉሡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ አስተዋውቀው፣ ፓርላማው ውስጥ ፣ ሁለት ድርጅቶች ፣ ሶስት አራት አምስት ፓርቲዎች፣ ተመርጠው ቢገቡ ኑሮ ጥሩ ነበር። እንዲያው አሳቸውን ቢያደርጉልን ኑሮ እንላለን እንጂ ከእሳቸውም በሁዋላ የመጡትም፣ ይህን ነገር፣ “እኛ እናደርጋለን” ብለው ይፎክሩ የነበሩ “ልጆች”፣ እንኳን ማድረግ ቀርቶ፣ ጨርሶም፣ ቃላቸውን አክብረው አልሞከሩትም ። መሞከር ብቻ ሳይሆን ፕሮግራማቸው ላይ እንኳን አላሰፈሩም።
የት አሉ ሽንጎ ውስጥ ዛሬ የተቃዋሚ ፓርቲዎች? አንድ ተቃዋሚ ሰው ብቻ አይደለም ፓርላማ ውስጥ ያለው?
ሌላው ቀርቶ “የፕሬስ ነጻነትን” አጼ ኃይለ ሥላሴ ለአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ዕድል የተለያዩ ሐሳቦች፣ በአገሪቱ ውስጥ እንዲንሸረሸሩ፣ ከዚያም ጥሩ ነገር ነጥሮ እንዲወጣ ብለው ፣ ይህን ነጻነት ቢያውጁልን ኑሮ፣ ዛሬ ፣ (አርባውን አመት) የትና የት እኛም እንደሌሎቸ ዕድሉን አግኝተን በደረስን ነበር።
ግን እንኳን እሳቸው፣ “የፕሬስ ነጻነት፣ መምጣት የግድ ያስፈልጋል! ” ይሉ የነበሩነት እስቸውን የተኩት ቡድኖችም፣ እስከ አሁን ድረስ ይህን መብት፣ ሳይፈቅዱ አፍነው ይዘውታል።
እንግዲህ ችግሩ ያለው በትውልዱ ላይ ነው። አለጥርጥር አጼ ኃይለ ሥላሴና ባለሙያዎቻቸው ደግሞ የ20ኛው ክፍለ-ዘመን ሰዎች ናቸው።
ያካሄዱትም ፖለቲካ በዚያ ዘመን የነበረውን የእራሳቸውን ፖለቲካ ነው። ያ ፖለቲካ ግን አገር የሚያጠናክር እንጂ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ አልነበረም።
የሚገርመው “የንጉሠ-ነገሥቱን ፖለቲካ ቀይረን፣ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ / በሲሻሊዚም አዲስቱዋን ኢትዮጵያ እንመሰርታለን” የሚሉ የ20ኛው ክፍለ- ዘመን “ታጋዮች” (ያ የሚሉት ነገር ምን እነደሆን በመጨረሻው አይተናል! ተገንዝበናል!) እዚያው የምናውቀውና ወደሁዋላ ወደቀረው የጨለማ ዘመን (አለ ነጻ -ፕሬስ) ውስጥ ጥለውን፣ በእኛ ላይ ይቀልዱብናል።
እሳቸውን የተኩና ቤተ-መንግሥት የገቡ ደርጎቸም ሆነ፣ሌሎቸ ነጻ አውጪዎቹም፣ ምን አዲስ ነገር፣ ከዱሮው የተለየ አመጡልን?ብሎ እራሱን የሚጠይቅ ሰው የሚያገኘው መልስ አሳዛኝ ነው። ጠያቂውም እራሱ፣ እነሱም ገዢዎቸም በደንብ ያውቁታል።
ለመድገም፣ “ንጉሡ ይውረዱ እንጂ ያን እናመጣለን፣ ይህን እናደርጋለን…” ያልተባለ፣ ያልተጠየቀ ነገር የለም። ሁሉም ተብሏል። …መሬት ለአራሹ ዱሮ፣ በተማሪው ተባለ። ነጻ- የፓርላማ ምርጫ ከአልሆነ ተባለ። የዜጎች መብት ይከበር ተባለ።… ሳንሱር ተነስቶ ልብ ወለድ ድርሰት እንደልብ አትመን እናውጣ ተባለ። የምርምር ነጻነት፣ የመናገር ነጻነት…ተባለ። በእነዚህ ሁሉ ፣ ጥያቄዎች ደግሞ እንደምናውቀው ንጉሠ ነገሥቱ፣ ይከሰሱበት ነበር። በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያም ሁሉም ሰው ተሰለፎአል። ታዲያ ውጤቱ የት አለ? መልሱ የትደረሰ? ምን ይታያል? የት ነው ያለነው?
አሥመራ እንዴት ናት? አዲስ አበባስ? ጎንደር? ወለጋ? በሐረር ምን ይታያል፣ ምንስ ይሰማል?
ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና አቶ ገርማሜ ነዋይ በዘመናቸው “ለውጥ” ብለው ተነስተው፣ አርበኛ ሳይቀር አብረው ፈጅተዋል? ቢሳካላቸው ኑሮ ፣ አዲስ ነገር፣ ከኮነሬል ሞአመር አል ጋዳፊ፣ ከገማል እብደል ናስር፣ ከሻለቃ ምንግሥቱ ኃይለ ማሪያም የተለየ ሥርዓት፣ የነዋይ ወንድማማቾች ያመጡልን ነበር? አይመስለንም።
ደርግን ተክተን “ነጻና ዲሞክራቲክ መንግሥት በኢትዮጵያ እናመጣለን “ብለው በጫካ ሁሉም ተሰማርቶ ነበር። እነሱስ ሥልጣኑን ሲረከቡ ምን አመጡልን?
በአጭሩ የዲሞክራሲ መብት የሌለበት አገር ምንም አዲስ ነገር አይመጣም።
አጼ ኃይለ ሥላሴ ከገርማሜና ከመንግሥቱ ንዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተረፉ። ለምንድን ነው ግን፣ ይህን እንደ ማስጠንቀቂያ ቆጥረው፣ ከግንዛቤአቸው ውስጥ አስገብተው የአገሪቱን ፖለቲካ ለማስተካከል የአልሞከሩት?
በዚህ ግን እሳቸው ላይ አንፈርድባቸውም።
ሌሎቸም እሳቸውን የተኩት ዕውንት እንናገር ከአልን እላይ እንዳለነው እነሱም ፈጽሞ አልቻሉበትም። ቃላቸውንም እንኳን ማክበር አልቻሉም። ጥያቄው ዞሮ ዞሮ ምን አዲስ ነገር፣ ለአገሪቱ ፣ ለሕዝቡ እነሱ አመጡላት? ነው።
አጼ ኃይለ ሥላሴ ያሰሩት ፓርላማ አለ። ይህ ፓርላማ በነጻ ምርጫ የሁሉም ድርጅቶች ቤት እንዲሆን ተጠይቆአል። ከእንግዲህ ከእዚህ ሁሉ የትርምስ ዘመን በሁዋላ ይህን አዳራሽ፣ ይህን ሕንጻ፣ እሱን የተለያዩ በሕዝብ የተመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ ማድረግ የእኛ ፋንታ ነው።
አጼ ምኒልክ የጀመሩትን የህትምት ሥራና ማተሚያ ቤቶችን አጼ ኃይለ ሥላሴ አስፋፍተውታል። በፕሬስ ነጻነት እነሱን አጅቦ ወደፊት መጓዝ የትውልዱ ኃላፊነት ነው። ብዙ የቴሌቪዢንና የራዲዮው ጣቢያ አገሪቱም ማስተናገድ ትችላለች። እንግዲህ ይህን በሥራ መተርጎሙ የትውልዱ ፋንታ ነው።
ነጻ ትምህርትና ጥበብ እንዲስፋፋ ንጉሡ ብዙ ጥረዋል። ብዙ ነጻ ትምህርት ቤቶች እንዲሰሩ፣ ሁሉም እንዲማርበት፣ ማድረጉ ከእንግዲህ የአሁኑ ትውልድ ፋንታ ነው።
ንግድ እንዲስፋፋ፣ ኢትዮጵያ በአንድነቱዋ እንድትጠነክር፣ ባህሉዋና ታሪኩዋ እንዳይጠፋ፣ ሳይሆን ገኖ ከሌሎቹ እኩል በዓለም ላይ ለጥቁር ሕዝቦች አለኝታ እንዲሆን ንጉሡ ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እንግዲህ ይህን ኃላፊት ተቀብሎ ወደፊት መጓዙ ደግሞ፣ አሁንም የእኛ የትውልዱ ፋንታ ነው።
ሁለት ነገሮችን ቢያንስ ማንሳት ይቻላል።
በንጉሱ ዘመን ቤቱ (አለፍርድ ቤት ማዘዣ) ተሰበሮ ልጆቸ ተወስደው አለፍርድ፣ ሜዳ ላይ በጥይት አልተደበደቡም። በንጉሱ ዘመን ሰልፍ የወጣ ተማሪ ግፋ ቢል በሚያስለቅስ ጢስ እንጂ(ያውም በሁዋላ) በጥይትና በጩቤ መንገድ ላይ በገፍ አልቆሰለም። አልተገደለም።
ከሃያ አራት ሰዓት በላይ አንድ ሰው ዳኛ ፊት፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ስድስት ወር፣ አንድ አመት ሁለት፣ አሥር አመት አልማቀቀም።

ቢያንስ ይህ መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጆች መብት በንጉሡ፣ በቀ ኃሥ ዘመን እንደምናውቀው ይከበር ነበር።
ሁለተኛው፣ ማንም ሰው በገዛ አገሩ፣ እንደ ጣሊያን ዘመን” ዘርህ ምንድነው?” ተብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ በውጭ አገር ፣ በነጭም ይሁን በጥቁር፣ በአረብ ይሁን በቻይና፣ በሕንድ አንድም ሰው አይጠየቅም ነበር።
በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያዊነቱ፣ ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ ፓስፖርት፣ የሚጓዝ አንድ ኢትዮጵያዊ ሰው የትም ቦታ፣ የአውሮፓ የአይሮፕላን ጣቢያዎች ሆነ፣ የተለያዩ መንግሥታት ወደብ፣ የባቡር ጣቢያና አውራ ጎዳና ላይ ፣ የዛሬን አያድርገውና ኮርቶ ተከብሮ፣ ፍራንክፈርት ላይማ፣ ሰላምታ ፖሊስ እየሰጠው እንደ አምባሳደር አለ ቪዛ ሳይጠየቅ ይወጣም ይገባም ነበር።
ስንቱ በሁዋላ ” ነጸ -አውጪ” የሆነውም ይህን ዕድል ተጠቅሞ አገሩን ለቆ ወጥቶአል።
“…ተቀምጠን የሰቀልነውን” ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊሲ አንዴ እነዳሉት “ቆመን (ተፈሪ መኮንንን ) ማውረድ አቅቶናል” ያሉትን፣ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን) በሁዋላ ጥቂት ወታደሮችና ተማሪዎች፣አዋክበዋቸው፣ እሳቸውንና ሥርዓቱን ጥለዋል።
ግን ደግሞ ንጉሡ የሰሩትን ሥራ በሁዋላ ብቅ ያሉ ቡድኞች፣ የእራሳቸውንና የሌላውን ሕይወት ጭምር አበላሹት እንጅ ግማሹንም እንኳን ለመስራት አቅቶአቸዋል።
ንጉሡ ሲወርዱ “…አገር ማስተዳደር ቀላል አይደልም። ችግሩ የእኛ ስልጣን ላይ መቆየት አይደለም ። አገራችሁን ኢትዮጵያን ግን ጠብቁዋት ” ያሉትን የአደራ ቃል እንኳን ሰሚ አጥቶ ይኸው ” የተበተነ ንብ”አባቶች እንደሚሉት፣ ሁላችንም ሁነናል።
ፖለቲካ ማለት የአለፈውን ከግምት አስገብቶ፣ ለአሁኑም፣ ለመጪውም ትውልድ፣ ለረጅሙም ጊዜ፣ ለአገርና ለልጅ ልጆች፣ አብሮ ማሰብ ማለት ነው። ይህን የተገነዘበ ሰው የለም።
የሚጠፋ ባህልና ታሪክ መጀመሪያና መጨረሻው፣ መቼ እንደሆን አይታወቅም። ልክ “…ጠጉር ሲመለጥና” አባቶች እንደሞሉት “…ነገር ሲያመልጥ” አይነት ነው።” በኢትዮጵያ የሆነውም ይኸው ነው።
ወራሪ ጣሊያን ያልገደላቸውን፣ አርበኞች ብቅ ያሉ ኃይሎች ለሁለተኛ ጊዜ ገድለዋቸዋል። ሞሶሊኒ ያልቻለውን “የዘር ክፍፍል “፣ የፖለቲካው መደቡ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ጥሩ አድረጎ የሞሰሊኒን አላማ አቀነባብሮታል።
ለማሳጠር! ሐረር፣ ኤጄርሳ ጎሮ የዛሬ 121 ዓመት የተወለዱት (ተፈሪ መኮንን) አጼ ኃይለሥለሴ ፣… አማራም (አዲሱን ፈሊጥ ለመጠቀም) ኦሮሞም፣ ጉራጌም፣ ትግሬም ፣ ኦርቶዶክስ፣ የወሎ እስላምም፣ አፋሩም ወደሳባ ከሄድን ደግሞ፣ ትግሬም፣ ጎንደሬም፣… የሆኑ፣ የተደበላለቁ፣ የተካለሱ፣ እንደ እኔና እንደ አንተ፣ እንደ አንቺም፣ እንደ እሱም ንጹህ ኢትዮጵያዊ፣ ናቸው። “የአማራ ንጉሥ” የሚለውን ቃል የለጠፈባቸው ሞሶሊኒ ነው።

የወጣቱ መንፍን የተፈሪ መኮንን አለባበሳቸው፣ የጠጉር አቆራረጣቸው፣ መስቀላቸው፣ እንደ ማንኛውም፣ የኢትዮጵያ ልጆች ነበር። በሁዋላ አደባባይ ሲወጡም እንደማንኛውም ሰው ፣ እንደ እኔና እንደ አንተ፣ በዚያች ጠባብ የአዲሲ አበባ መንገድ እጃቸውን እያውለበለቡ በአመት ውስጥ፣ በአጠገባችን ስንት ጊዜ ደጋግመው ታይተዋል።
ቤተክርስቲያን ሄደው ያስቀድሳሉ። ሐኪም ቤት ሄደው በሽተኞች ይጎበኛሉ። አዳሪ ትምህርት ቤት ሄደው ተማሪው የሚበላውንና የሚተኛበትን ያያሉ። የሥዕልና የሙዚቃ ትምህርት ቤት፣ የቲያትር አዳራሾችን፣ የኳስ ሜዳ፣ የተማሪዎች የስፖርት ቀንን ይጎበኛሉ።
ከእሳቸው በሁዋላ ከመጣው፣ “ገዢ” ውስጥ ማነው በአደባባይ ወጥቶ በአውራው ጎዳና ላይ እንደሳቸው የታየው? እንኳን ኳስ ሜዳና ትምህርት ቤት ሄዶ መመረቁ ቀርቶ “ድል አድረጎ እንኳን አዲስ አበባ ሲገባና ሥልጣኑን ሲይዝ” በግልጽ መኪና የታየ አንድም ሰው የለም።
ለምን?
እንግዲህ ከቅዠት ዓለም ወደ ነጻ-ሕብረተስብ ትውልዱ መመለስ አለበት። እንዴት? በምን ብልሃት?
ለዚህ ደግሞ መልሱ ከባድ አይደለም። መልሱ “ነጻ ሰው ነኝ “ብሎ በይፋ መናገር ነው። ለነጻ ሰው ደግሞ መንገዱም፤ መልሱም፣ ግቡም፣ አንድ ነው።
ሁሉንም በእኩልነት በሚያሰተናግድ “ሕግ””ሕገ-ምንግሥት ያስፈልገናል።
በንጉሡ ጊዜ ጅምሩ ጥሩ ነበር። ውጤቱ ግን አላማረም።
እሳቸው አንድ ነገር ይሉ ነበር፣”…በአልተማረ ሕዝብ ላይ ገዢ ከመሆን በተማረ ሕዝብ ውስጥ ተገዢ መሆን የተሻለ ነው።”ይላሉ።
ይህ አነጋገር ደግሞ ጥራዝ ነጠቆችን ለነገር የሚጋብዝ ነው።
ለምንድነው የኢትያጵያ መሬት፣ ለአምባገነኖች በያለበት መፍለቅ አሁንም አመቺ የሆነው? ይህን ጥያቄ በንጉሡ የልደት ቀን ዛሬ መጠየቁ ተገቢ ነው።
0*/
—————————————-
0*/ Source of the Photos: Thanks (ከአክብሮት ምስጋና ጋር!)
1/– “በኢንቨስትመንት ስም የሚፈጸም የመሬት ነጠቃ፤ በኢትዮጵያ”
2/ Land-Grab-Deals -in-Africa
—————————————————-