የሕይወት አስትንፋስ :- ለእናት አገራችን ለኢትዮጵያ
የሕይወት አስትንፋስ :- ለእናት አገራችን ለኢትዮጵያ
አዲሱ ( የቆየ) ርዕዮተ ኢትዮጵያ
“…የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔደን ገነትን ተከለ፣ የፈጠረውንም ሰው ከዚያ አኖረው። በዚያ አካባቢ…የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው። የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው። እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከባል። የሦስተኛው ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው። አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። …ሰውን ወስዶ ያበጃትም ፣ ይጠብቃትም ዘንድ በዔደን ገነት አኖረው።…ሰውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው:–ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፣ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፣ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። በሁዋላ ከጥበብ ፍሬ የበላውን ….እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ ወዴት ነህ ? አለው።…” ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት።
ግሩም ታሪክ ! የየትኛው አገር ስም ነው እንደ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ገጽ ላይ ያውም መጽሐፍ ቅድስ ላይ የሰፈረው?
ግሩም ጥያቄ! “…ወዴት ነህ? አለው!”…እንግዲህ ጥበብና ፍልስፍና ፤ ዕውቀት ፍለጋም በዚህ ጥያቄ ይጀምራል። የት ነው ያለኸው? ከአዚሁ ጋር ሦስት ጥያቄዎች አብረው ዓለምን አስጨንቀው ብዙ ሐሳቦች ወረቀት ላይ እንዲሰፍሩ ምክንያት ሁነዋል።
“ከየት መጣን?” ይላል የመጀመሪያው ጥያቄ።
“ወዴት እንሄዳለን?” ይላል ሌላው አስቸጋሪ የሰው ልጆች ሁሉ ጥያቄ ። በሕይወትም ዘመንም ሆነ ወደ ሞትም ሲወረድ።
“እንዴትስ እንኑር?” ይላል ሦስተኛው ከባድ (ዓለምን ያተራመስው) ጥያቄ። ሁሉም ድርሰቶች በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ የተደረሱ ናቸው።
፩
አንድን ሕዝብ የሚያሰባስብ ፣ አንድ የሚያደርግ የሚያስሰተሳስርና የሚያቀራርብ ነገር ፈልጎ እነደማግኘት ያለ ከባድ ነገር፣ በዚህቺ ዓለም ላይ የለም። ግን ደግሞ እንደሱ አዚያና እዚህ በአገሪቱ ምድር ላይ “ወድቆና ተበትኖ” (በቀላሉ አይታይም እንጂ) የሚገኝ አስደናቂ “እንቁ” ነገር የለም።
ጀርመኖች ፈልገው ቁልፉን አግኝተውታል። ፈረንሳዮች ገና ዱሮ ደርሰውበታል። አሜሪካኖች ጠይቀውና ተመራምረው መልሱን እጃቸው ውስጥ አስገብተዋል። ሩሲያ ከስንት መቶ አመታት መንከራተት በሁዋላ “ነፍሱዋንና አገራቸው የተመሰረተችበትን ቋሚ መንፈሱዋን” በመከራ ፈልጋ፣ አሁን አግኝታለች። እንግሊዞች ደግሞ ይህን ከአወቁትና ከጨበጡት ጊዜው ቆየት ብሎአል።
ቻይና እሩቅ ሆነን፣ እዚህ ተቀምጠን እንደሰማነው፣ ፈልጋና አፈላልጋ የኮንፊስዮስ ትምህርት ላይ ዓይነዋን አሁን ጥላለች። ጃፓን በእጁዋ የያዘቺውን ወርቅ ለማንም አልሰጥም ብላ፣ ይኸው ዘመናዊ ሥልጣኔውን ፣ ከጥንታዊ ባህሉዋ ጋር አዳቅላ ደህና አድርጋ ተራምዳለች። ምሲኪኖቹ ጣሊያንና ግሪክ ግን፣ ዞሮባቸው ስንት ወርቅማ ነገር መሬታቸው ውስጥ ተቀብሮ እያለ ቆፍሮ እነደማውጣት ፣ ነገሩ ጠፍቶአቸው ግራ ተጋብተዋል። እሥራኤል ብቻ ከሦስት ሺህ አመት በሁዋላ ታሪኩዋን፣ ባህሉዋን ፈልጋ አግኝታ መልሳ ልትቋቋም ችላለች።
ለአረቦች ከአወቁበት፣ እንደዚያው ለእነሱም ማን እንደሆኑ ፈልጎ ማግኘት ቀላል ነው። ግን ከመስማማት እነሱ መበጣበጥን፣ ከመነጋገር እነሱ እንደ እኛ መጣላትን ይወዳሉ። ለፋርስ እንደዚሁ መንገዱ ቀላል ነው። ግን “አዛውንት ቀሳውስት” ጸሎቱን ትተው ፖለቲከኛ ሁነው ፣ የሰማዩንም የምድሩንም አንድ ላይ ፣ ሳያገባቸው ጨፍልቀው፣ ሰውን ሁሉ እዚያ ግራ አጋብተዋል። ቱርክ አንድ የሚያደርጋትን “ታሪክና መንፈስ” እየፈለገች ነው፣ ይባላል።
ግን የጥያቄዎቹ ሁሉ ዋና ጥያቄ ፣ “እኛን”፣ ይህ ነገር ፣ ይህ ቃል….እንደገና መደገም አለበት፣ “እኛን ኢትዮጵያኖችን” እንደ ገና የሚያሰባስበን ፣ እንደገና እኛን አንድ የሚደርገን ነገር ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ነው።
፪
አንድ ሰው ፣ ነጭ ይሁን ጥቁር ፣….ከአንድ የበለጠ፣ …አራትም ይሁን አምስትም ፣ ከዚይም በላይ ሊሆን ይችላል፣ “አይደንቲቲ”/Identity/፥ ልዩ “መለዮ ቆብ” እንዳለው ሁላችንም እናውቃለን። ይህ ልዩ “መለዮ ቆብ” ደግሞ ፣ “ቁጥሩ” እንደ ጊዜውና እንደ ዘመኑ “ሊጨምርም ሊቀንሲም፣ ሊበዛም ሊያንስም” እንደሁኔታው ይችላል። አንድ ቋሚ ግን፣ በምንም ዓይነት ማንም ሊቀይረውና ሊለውጠው የማይችለው፤ እሱነቱን እስከ የሕይወቱ መጨረሻ ድረስ ፣ እረ.. ይህ ነገር ከዚያም አልፎ ይሄዳል፣ የሚገልጽ “አይደንቲት” ሁሉም ሰው አለው።
ምንድነው እሱ?
አንድ ሰው፣ ለምሳሌ እንውሰድ። ይህ ሰው … ሰፖርተኛም ፣ ወታደርም፣ ወይም ጸሃፊና ዘፋኝ፣ ቲያቲር ተጫዋችና አይሮፕላን አብራሪም ሊሆን ይችላል። ዜግነቱን ቀይሮም ፣ ይህ ሰው እንደወላጆቹ አፍሪካዊ ሳይሆን በሕጉ መሰረት ዜግነቱን ቀይሮ…. አሜሪካዊም፣ ወይም ፈረንሳዊ፣… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፣ በጅምላ አውሮፓዊም ሊሆን ይችላል።” በዚያ ላይ፣ ይኸው ሰው እንደ ጾታው የወንድ ወይም የሴት፣ ባህሪ ሊኖረው ይችላል ።
የተላያዩ አመለካከቶችም ይህ ሰው፣ ወይም ይህች ሴትዮ ፣ በተለያዩ ጥያቄዎች ላይ ሊኖራትም /ሊኖረውም ይችላል።
በዚህ ምሳሌ፣ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ወይም አሜሪካዊ በአንድ ወገኑ ለሆን ይችላል። በሌላ ወገኑ ይኸው ሰው … ሐማሴን ፣ ወሎዬና መንዜ፣ የሸዋና የሆሮ ጉድሩም ሰው ሊሆን ይችላል። ከጥንት ጀምሮ “……ዘ-ብሔረ ጽጌ፣ ዘ- ብሔረ ቡልጋ ….” የሚባለው አነጋገር በኢትዮጵያችን የተለመደ ነው። ይህ አዲስ አይደለም።
አዲሱ ነገር፣ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን፣ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በዚህ “የዘር -ልዩነት” (ሁላችንም እንደምናውቀው) በአገሪቱ የፖለቲካ ትግል ማካሄድ ይቻላል? ወይስ አይቻልም የሚለው የጥቂት ሰዎች፣ወይም ቡድኖች ጉዞ፣ በአገራችን ያመጣው ትርምስ ነው። እሱም እስከ አሁን አጠያያቂ ጉዳይ ነው።ጥሩነቱ ደግሞ “ርዕዮተ-ዓለሙን ” ንፋስ መቶት አሁን በያለበት እንደደምናየው ተከታዮች አጥቶል።
እንደምናውቀው (ይህ ሚስጢር አይደለም )፣ እኛ ኢትዮጵያውያኖች የተካለስስንና የተደበላለቅን ፣ የአንዱ እናት ከሰሜን የአንዱ አባት ከደቡብ፣ የአንዱ ከምዕራብ የሌላው ከመሓል አገር የመጡ ናቸው። እንግዲህ ከእነሱ የሚወለደው ልጅ የየትኛው “ነገድና ጎሣ ፣ ወገን ነው?” ማለት እንችላለን።
እርግጥ ይህ ሰው፣ እንደፈለገው …ያንንም ነኝ ፣ …ይህንም ነኝ ብሎ የመሸበት “ማደር “ይችላል ልንል እንችላለን። ይህም፣ ዕውነቱን ለመናገር መብቱ ና የእራሱ ውሳኔ ነው። ግን በደንብ ለመረዳት ፣ በእንደዚህ ዓይነት ተካልሰው ጅርመንና ፈረንሣይ፣ አሜሪካና ካናዳ፣ አውስትራሊያና ጃፓን ወይም ቻይና ወይም ከየመን የተወለዱ የኢትዮጵያ ልጆች (ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም) ዘራቸው ምንድነው? የዘር ጥያቄን ፖለቲካ ውስጥ ምን አመጣው? ለምን ተነሳ?
ለመሆኑ መካለስ በኢትዮጵያ የተጀመረው መቼ ነው?… ትላንት?… ዛሬ? ….ወይስ ጥንት “በአብዬና በስብስቴ ዘመን”? ወይስ ከአዳም ና ሔዋን ጊዜ ጀምሮ?
በአጭሩ ለመናገር ፣ አንድ ሰው ( ሕይወት እንደዚህ ግሩም ናት) ብዙ “አይድነቲቲ” አለው። ግን አንድ የባየርን ፣ ወይም የፕሩሲያ ወይም ደግሞ የፍራንክ፣ …ወይም የኤልዛስ ሎትሪንግ ፣ የሳክሰን አንሃልት ወይም የባድን ሰው እኔ፣ ባየርን እንጂ… እኔ … ጀርመን አይደለሁም ብሎ ቢከራከር ” አበደ ” እንዴ የሚለው ሰው ቁጠር ትንሽ አይደለም።
፫
ስንት “የውጭ አገር ሰው ከዓለም ዙሪያ ” ተሰባስቦ አሜሪካን ደርሶ ” አሜሪካዊ ነኝ ” ብሎ ልክ እንደ ዱሮው ዘመን ሰው ሁሉ ሮም ደርሶ “….ሮማዊ ነኝ ” ብሎ እንደሚኮራው ሁሉ፣ አሁንም አሜሪካ ደርሶ ሰው ሁሉ፣….እንቁጠር ከተባለ… ኦሮሞውም ፣ ትግሬውም ፣ ኤርትራውም፣ አፋሩም፣ አማራውም ፣ እንደ ጃፓኑና፣ ትላንት አሜሪካን ደርሶ፣ ዜግነቱን እንደቀየረው ቻይናዊ፣ እሱም አሜሪካዊ ነኝ ብሎ ይኮራል። …..ለምንድ ነው ሰው ሁሉ ዛሬ እዚያ እንደዚህ የሚለው?
በተቃራኒው ግን ለምንድነው ተማርኩ የሚለው አንድ ኢትዮጵያዊ…”እኔ እኮ ኤርትራዊ እንጂ፣ ኦ …እንጂ … ኢትዮጵያዊ አይደለሁም …” ብሎ ኢትዮጵያዊነቱን “የሚክደው?”። …ተክዶስ የት ሊደረስ? ነቢዩ ኤርምያስ ብዙዎቻችን የምናውቀውን ጥሩ ነገር እሱ አንስቶአል። ” …ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ፣…..ኢትዮጵያዊነቱን…” ይላል።
መጽሐፉም ገና ዱሮ “አትዋሽ በሐሰትም አትመስክር…” ይላል። ከዚህ ተነስተን አንድን ሰው “አትካድ” ማለት እንችላልን? ። አዎን ይቻላል። ጥያቄው ግን በአሁኑ ሰዓት እሱ ሳይሆን ፣ ጥያቄው እነዚህ “… እኔ ወይም እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም !” ብለው የሚክዱ ሰዎች ቁጥራቸው፣ ለመሆኑ ስንት ነው? ብሎ መጠየቁ ላይ ነው። መጠየቅ ደግሞ ያስፈልጋል። ለመሆኑ እነሱስ ….. ሲደመር ሲቀነስ አሁን ከቁጥር ውስጥ ይገባሉ ወይስ አይገቡም ? ብሎም መምከር ያስፈልጋል። እንደ ትልቅ ቁም ነገር፣ “እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ” የሚለውን ሰው፣ አሱን/እነሱን ማየት ግን ስህተት ነው። …. ለምን? ….ወሳኙ ጥያቄም ይህ ነው።
በደንብ ከአየነው ፣ አንደኛ ቁጥራቸው ብዙ አይደለም። በጣም ትንሽ ነው። ሁለተኛ፣ አክራሪዎች ብድግ ብለው በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ሰውን የሚሰበስቡበት ዘመን አልፎአል። ሦስተኛ፣ በቀላሉ የሚታለል ትውልድ እንደዱሮ አሁን የለም። ቢጣሩም ፣ ቢጮሁም የሚሰማቸው ወጣት የለም። አራተኛ ይህ ጉዞ “ትርፍ “የማያመጣ ሥራ እንደሆነ ሁሉም ገብቶታል።
ይህ ከሆነ ደግሞ አብዛኛው ሰው በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ምን እንዲመጣለት ይፈልጋል? ….ምንድነው እሱን በአሁኑ ሰዓት የሚያሳስበው ነገር? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። ከዚሁ ጋር ሌላም ጥያቄ አብረን እናንሳ። የኢትዮጵያን ልጆች የሚያሰባስብ የቆየ፣ ያለ፣ ያልጠፋ፣ ያልተዳፈነ ” ፍም፣ የሚንቀለቀል እሳትና መንፈስ” ምንድነው ብለን እንመራመር። እራሳችንንም እንጠይቅ። ጠይቀንም መልሱንም ወደ መፈለጉ አሁን እንሸጋገር።
፬
አንድ ትምህርታዊ አነጋገር በአውሮፓ አለ። እሱም፣ አንድ ወጣት ጎረምሳ በልጅነት ዘመኑ እንደ “አናርኪስት” ዞር ብሎበት፣ በማንም ላይ:- በወላጆቸም ላይ ሊሆን ይችላል፤ አምጾ “ከእንግዲህ አበዛችሁት በቃ “ብሎ ከአልሸፈተ፣ ይህን ልጅህን ፣ እዚህ ሁሉም ሰው፣ ችላ ሳትል ጠርጥረው ይላል። ነገር አይቶ በጎልማሣ ዘመኑ ደግሞ -ይህ ልጅ ኮሚኒስት ከአልሆነ ፣ …ትንሽ ቆይቶ አለምን ተመልክቶ ከአምባገነን አስተሳሰቡ ትንሽ ፈንጠር ብሎ ቢያንስ ወደ ሶሻል ዲሞክራቶች ከአልተጠጋ ፣ አካሄዱ አደገኛ ስለሆነ በዓይነ ቁራኛ ጠብቀው ይላል።
ልብ ገዝቶ ግን ትዳር ይዞ ቤት መስርቶ ልጆች ውልዶ ቢያንስ “የሊበራሎቹ መንደር” ከአልተደባለቀ ደግሞ ይህን ሰው፣ እዚህ አትመነው ይባላል። ዕድሜው ገፍቶ ዓለምን ተመልክቶ ደግሞ ኮንሰርቫቲቭ/conservative/ ከአልሆነ ፣ ይህን ሰው አውሮፓውያኖች፣ አንድ ነገር የጎደለው፣ “የሚያጠያይቅ ሰው ነው ” ይሉታል።
ዱሮ፣ እንዲያው ይህ አባባል ዕውነት ሁኖ ፣ የአገሬን ልጆች እንደዚህ በአደረጋቸው እላለሁ። ምነው እንደዚህ በሆኑልኝ ብዬም እጸልይ ነበር። ግን እንደምናውቀው እኛ ጋ እኮ ወጣቱ ሰይሆን ሽማግሌው፣ የስድሳውና የሰባው፣…የሰማንያ አመቱ ሽማግሌ ፣እላይ እንደተባለው ኮንሸርቫቲቭ ሳይሆን የተገላቢጦሹን (የጃጁ ናቸው እንዳትሉኝ እንጂ) “ኢትዮጵያ ትበታተን፣ ትጥፋ” የሚሉ ጭልጥ ያሉ በተግባር “አናርኪስቶች” አሁንም ናቸው ።
ስም ጥራ ብላችሁ ከጓደኞቼ፣ ከእነ እገሌ ….ከእነ እንትናና ….፣ ከእነ ….እገሊት አታጣሉኝ እንጂ፣ የስም ዝርዝራቸው ረጅም ነው። አሁን ይክበር ይመስገን፣ እነሱ አቋማቸውን ባይቀይሩም፣ ወጣቱ ትውልድ ጆሮውን ላለመስጠት አትድረሱብኝ ብሎአቸዋል። ይህ ነገር ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ የሚታይ ነው።
“ኮንሰርቫቲቭ” አልኩ?
ኮንሰርቫተቪ የሚለው ቃል አለአግባብ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ ቦታ፣ ይህን ቃል ሰዎች “ከአደሃሪ፣ ከሁዋላ ቀርነት፣ ከበዝባዥና ከጸረ አብዮት ጋር …” ሆን ብለው፣ በተለይ ግራዎች ያያያዙት ቃል ነው። ኮንሰርቭ ማለት በትክክል ትርጉሙ፣ አንድን ነገር “…መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ ማቆየት፣ አቆይቶም ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ” ከሚለው ቃል ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።
ይህ ከሆነ እና ሌላ ትርጉም ከአልተሰጠው እኛ ” ኮንስረቫተቪ” “… የአገራችን ባህልና ሥልጣኔ ሳይበተን እንደ ሌሎች አገሮችና ሕዝቦች እንዲቆይ የምንከራከር፣ አዲሱ ኮንሰርቫቲቭ ነን። “አዲሱንና ዘመናዊ ሥልጣኔን ከቀድሞ ባህላችንና ወጋችን ጋር አብረን፣ ልክ እንደ ጃፓኖቹ፣ ልክ እንደ አሜሪካኖቹ ና ፈረንሣዮቸቹ፣ ልክ እንደ ጀርመኖቹ …ሁለቱን አዛምደን አያይዘን፣ ማንነታችንን ሳንረሳ መጓዝ እንችላለን ባይ ነን።
ታዲያ ምንድነው እሱ?
፭
ሃምሰ ሺህ “የላብ አደር መደብ” በሌለበትና በአልነበረበት አገር በኢትዮጵያ ፣ “የላብ አደሩ ወይም የወዝ አደሩ….ፓርቲ” አቋቁሞ መስርቶ ምንም ቢኮን ምንም ቢደረግ ሊመጣ ለማይችለው ለሶሻሊዝም /ኮሚኒስት ሥርዓት” (ይህ ሥርዓት ምን እንደሚመስል ሞስኮና ፔኪንግ፣ ምሥራቅ በርሊንና ካምቦጂያ፣ አዲስ አበባና አሥመራ … ላይ ታይቶአል) ያኔም አሁን መታገሉ ከንቱ እንደሆነ ታሪክ ምስክር ሁኖ ፍርዱን ኢትዮጵያ ላይ ሰጥቶአል። አሁን እዚያ ላይ መለስ ብሎ መነታረኩ ከንቱ ሙከራም እንደሆንም ማንም ሰው ያውቀዋል።
በዘር፣ በጎሣ አንዳዶቸ እንደሚሉት፣ “በብሔርና /በብሔረሰብ እስከ መገንጠል ድረስ….” ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የጥቂት ቡድኖች ሥራ፣ እነሱም የመሰረቱት “ዓሣ አይሉት ሥጋ ፣… የሶሻሊዝም/ ወይም የኮሚኒዚም ርዕዮተ ዓለምና ሥርዓት”፣ በዚህ ጉዞ የትም መድረስ እንደማይቻል፣ አሁንም ታሪክ ምስክር ሁኖ ፣ ሙከራውና አካሄዱ ስህተት እንደሆነ በግልጽ በኢትዮጵያ አይተናል። የሚገርመው ወይም የሚደንቀው ኢትዮጵያ በአለፉት አርባ አመታት የሄደችበትን የጎሣና የነገድ ጎዳና እና መንገድ አንድም አገር በዓለም ደረጃ ያልሞከረው ድርጊት ነበር።
አሁን ይህን የተሳሳተ መንገድ በጅምላ ፣ በጭፍን የሚከተል ሰው -ይክበር ይመስገን- የለም።ትርፉ በአሥመራና በአዲስ አበባ እንደምናየው ፣ ዲሞክራሲ የሰፈነበት፣የሰበአዊ መብቶች የተጠበቁበት ነጻ-ሕብረተሰብ ሳይሆን ፣ አንድ ቡድን፣አንድ ድርጅት ለአለፉት ሃያ ሁለት አመታት፣አገሪቱን ተከፋፍለው የነገሱበት ሥርዓት ነው እንጂ። እኛ ብቻ ሳንሆን ይህን የሚሉት፣ በየአመቱ እዚህ ተጠርዘው የሚወጡ የአምኒሰት ኢንተርናሽናልና የሂመን ራይት ዘጋባዎች ናቸው።
ታዲያ መፍትሔ መንገዱ ምን ይመስላል?
አሁን ደግሞ “የሴቶች “ድረጅት መሥርቶ (ከፊሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንስታይ ጾታ ስለሆነ) በሴቶች አመራር ሥር፣ አንድ መንግሥት ፣ በኢትዮጵያ ቢቋቋም አገሪቱ ፣ ሌላውም የአፍሪካ ክፍል ሰላም ያገኛል የሚሉ አስተሳሰቦች መናፈስ ከጀመሩም ጊዜው ሰንበት ብሎአል። ሴቶች ጦረኞች አይደሉም ።ሴቶች ርህሩህ ናቸው። ሴቶች ለልጆቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው መልካም ነገር ይመኛሉ። ስለዚህ ወንዶቹ ስለአላወቁበትና ማስተዳደር ስለ አልቻሉበት “ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ችግርና ችግሮች እነሱ ብቻ ናቸው መፍትሔዎቹ” የሚሉ ጹሑፎች ተበራክተዋል። በእነሱ፣ በሴቶች በላይነትና በእነሱ ሥልጣን መጨበጥ፣ የአንድ አገር ችግር በቀላሉ እንደማይፈተው ሁሉ፣ በ “ወጣቶች ድርጅትም” ሆነ ወይም በ”መለዮ ለባሽ ወታደሮች” አገር አልተገነባም። ሊገነባም አልተቻለም። እንግዲህ ነጮቹ አሁን እንደሚመኙልን “..በሴቶች መሪነት፣ በወታደሮች ወይም በወጣት ተማሪዎች አመራር ሥር መንግሥት አቋቁሞ ሕዝብን መምራት መርቶም ከረሃብ መላቀቅ ፈጽሞ አይቻልም። ይህንንም በአገራችን በተለይ በወታደሩ መንግሥት ሥር አይተናል። “ተማሪውም “ሥልጣን ላይ ወጥቶ ይኸው እንደምናየው ምንም አዲስ ነገር አልተፈጠረም። መናገር አይቻልም። መጻፍ አይፈቀድም። …
በአጭሩ በኢትዮጵያና በሕዝቡ ላይ ልምምድ/ኤክስፐርመንት የሚደረግበት ጊዜ፣ ነገሮች ግልጽ እየሆኑ ስለመጡ አክትሞአል። የም ሆኖ ግን መንገዱ አሁንም ለብዙዎቹ “ጨልሞአል”
ታዲያ መፍትሔ መንገዱ፣ እኛን አንድ አድርጎ በፍቅር ወደ ቀናው የዲሞክራቲክ ሥርዓት የሚወስደን ብልሃት ምንድነው?
እንግዲህ እሱን መልስ ፣ የጥያቄውን መልስ መስማት የምንፈልግ ከሆነ ፣….እኛን አንድ የሚያደርግ ነገር ምንድነው ብሎ መጠየቅ ትክክል ነው። አንድ የሚያደርጉን ነገሮች በብዛት አሉ። ሁለቱን ብቻ ለጊዜው ጎትተን እንውሰድ።
አንደኛው ፣ ከዚህ ዓለም ያልሆነው፣ የቆየው የአገራችን መንፈሳዊ ትምህርት ነው።
ሁለተኛው ፣ የሰበሰብነው ምድራዊ ዕውቀትና ጥበብ ነው።
እነዚህ ሁለቱ ምድራዊና መንፈሳዊ ትምህርቶች በ18ተኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተነሱት ጭንቅላቶች እንደ አስተማሩን “የሚቃረኑና የሚጻረሩ፣ የማይጣጣሙ ትምህርቶች” ሳይሆኑ አንዱ ሌላውን የሚያግዝና የሚደጋገፉ የጥበብ ዓለሞች ናቸው።
በእርግጥ “መንግሥትና ሃይማኖት” በሕግ ሊለዩ ያገባቸዋል፤ በብዙ አገሮችም ተለይተዋል። ችግሩ እሱ አይደለም ። ችግሩ፣ በዚህ እኛ እራሳችን ኢምኒት አካል ሁነን በምንገኝበት “ዩኒቨርሱም”:- በሰማ-ሰማዕታት ውስጥ፣ የአንዲት ሚስማር ጭነቅላት እንኳን ሳይሆን (ከጠቅላላው ኮከቦችን እና ጸሐይ፣ እንዲሁም ፕላኔቶች ጋር ሲነጻጸር) የትንሹዋን እስፒል አንገት እንኳን በማታክለው ” ምድረ-ዓለም” የምንኖር ሰዎች ፣ በአለችን አንስተኛ አንጎል “ሁሉን ነገር እናውቃለን፣…. ስለዚህ እግዚአብሔር የለም፣ እሱ ከሌለ ደግሞ እኔና ብጤዎች የፈለግነውን ለማደረግ ተራው ጊዜው የእኛ ስለሆነ እንችላለን” ብሎ መነሳትና ማስተማር፣ ተጠንቅቆ ለመናገር ፣ ዕብደትም ፥ ቅዠትም ነው። እንደዚህ ዓይነቱ አመለካከት ደግሞ የት እንዳደረሰን የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ምስክር ነው።በሃያኛው ክፍለ-ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዋች በዚህ ትምህርት ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ምንድነው ፣ እዚህ ቁጭ ብለን ስለ ሌላው ፕላኔቶች እኛ የምናውቃቸው ነገሮች? …እነሱ ከየት መጡ? እኛስ የሰው ልጆችስ ከየት መጣን? …ከሕይወት በሁዋላ ወዴት ነው የምንሄደው? ነፍስና መንፈስ ምንድናቸው?
እስከ አሁን ድረስ የምናውቃቸውና የምንሰማቸው መልሶች “እግዚአብሔር የለም” የሚለውን መልስ ነው። እሱን ደግሞ ፣ ፎየር ባህክ፣ ማርክስ፣ ሌኒን፣ ኒቼ…ዳርዊንና ሌሎቹም አንስተውልን በቂ መልስ ስይሰጡን ፣እነሱም ተወናብደው እኛንም አወናብደውን ሄደዋል። ምንም መልስ እነሱ አላቀረቡልንም። አልሰጡንም።ሊሰጡንም አልቻሉም።
አሁን ያለንበትና የደረስንበት ዕውቀት፣ ከዚህ ሁሉ አመት በሁዋላ፣ አሁንም ቢሆን ጠቅላላውን የሰው ልጆች ጥያቄዎች ሁሉ (ይህ የሰው ልጆች ጥያቄ ደግሞ ገደብ የለውም ) የአልመለስንበት፣ ልንመልስም የማንችልበት ደረጃ ላይ ነው። ምን ይታወቃል ለጥያቄዎቻችን አንድ ቀን መልስ እናጘኝም ይሆናል። መልሱም የዚያኑ ያህል ላይገኝም ይችላል። በአሥራ ስምንተኛውና በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ተነስተው፣ በእግዚአብሔርና በቤተክርስቲያን የቀለዱት ምሁሮች ትምህርት ዛሬ ፣መለስ ብለን ስንመለከተው ተከታይ የለውም። ይህ ትምህርት ግን ኢትዮጵያ ሰርጎ ገብቶአል።
በሃያኛው ክፍለ-ዘመን፣ በተለይ በኢትዮጵያ፣ ለዚህ ደግሞ ያኔም አሁንም ታትመው ይወጡ የነበሩ ጽሑፎች ምስክር ናቸው፣ ሃይማኖታችንን እና ፈጣሪ አምላክችንን የሚጋፋው፣ የኮሚኒስት ርዕዮተ ዓለም፣ በወጣቱ ትውልድ ዘንድ ተስፋፍቶ እንደነበር አይዘነጋም። ቁጥራቸው ምን ያህል እንደነበሩም ባይታወቅም፣ ከደረግ እስከ የዩነቨረስቲ ተማሪና እስከ አስተማሪዎች ድረስ፣ …ከቀበሌ ዳኛ እስከ የቀበሌ ዘበኛ፣ ከገበሬ እስከ የሰራተኛ ማህበር ተጠሪዎች፣ ከነጻ-አውጪዎች እስከ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት ተከታዮች፣ ሁሉም አዎ ! ያኔ እንደትክክለኛ ” የዓለም ራዕይ” ይህን ትምህርትና ይህን ፍልስፍና “የኮሙኒዝም ርዕዮተ ዓለም” ተቀብሎ፣ አንዲት የጥርጣሬ ጥያቄ እንኳን ሳያነሳ፣ በሌሎች አገሮችና ሕዝቦች ላይ ያ ሥርዓት ምን አመጣ ብሎም ሳይጠይቅና ሳይመራመር በድፍኑ ኢትዮጵያ መሬት ላይ ዘርተዋል። በሁዋላም እንደአየነው ትምህርቱ አገሪቱንም ፣ ሕዝቡንም አዋክቦ፣ “ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ” እዚያ ላይ ሰቅሎ አሥራ ሰባት አመት ፍዳዋን አሳያቶአት፣ ተሰውሮአል ።ሄዶአል። ሄደ?
ያ ፍልስፍና ደግሞ የትም አልሄደም። ቦታውን “ያ ! የመደብ ትግሉ” “ለብሔር ትግል ” በሌላ ቋነቋ ያው ለኮሚኒዝም ለቆ ገጠር ገብቶአል። አሁን ያ አመለካከት በዓለም ደረጃ “ታሪካዊ ግቡን ሳይመታ”ተሰናብቶአል። ግን ያ ፍልስፍና ማንም እንደሚያውቀውና እንደሚረዳው በኢትዮጵያም በኤርትራም ፣ አሁንም “በሥልጣን” ላይ ጉብ ብሎ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ይንሸራሸራል።
እሱ ብቻ አይደለም። ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚፈልጉትም (ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆን አይታወቅም እንጂ) እነሱም ከዚህ አስተሳሰብ ጨርሶ “አልተላቀቁም።” “…ለምንድነው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የማይስማሙት?” ለሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄም መልሱ ያለው እዚሁ ላይ ነው።
እንግዲህ አሁን ለእኛ ያ “ትምህርትና ያ ፍልስፍና ” የት እንዳደረሰን አይተን፣ ተገንዝበን በቂ ተመክሮም ሰብስበን አንድ ደረጃ ላይ ደርሰናል።
በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል፣ ይባላል። ይህ ዓይናችንን የከለለውን ነገር በቃ ብለ አሁን ወደ አገራችን ጥንታዊና ቋሚ እሴቶች ተመለሱ እንላለን። መመለስም ይኖርብናል።
ከንቱ ሃሳብ ፍለጋ በዓለም ዙሪያ ከመንከራተት በእኛው በኢትዮጵያውያን እጅ፣ የነበረውን እንቁ ፈልጎ ማግኘትና እሱን ማየት- እንዳንጠፋ ከፈለግን- አስፈላጊ ነው። ። በቂ የሚያኮሩን እሴቶችና በቂ ትምህርቶች በእጃችን ላይ አሉን። እነሱም ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈው፣ ጥንታዊው የኢትዮጵዊነት መንፈስና ጥንታዊው እሴቶቻችን (ቫሊዩስ) ናቸው።
ምንድን ነው ይህ የኢትዮጵያ መንፈስ? ምንድነው በሌላ ቋንቋ፣ ርዕዮተ፥ኢትዮጵያ ? ምንድን ነው ርዕዮተ፥ኢትዮጵያ ፣ የተመሰረተበት መሰረቱ?
“…ተበታትነን እንዳንጠፋ የምንፈልግ ከሆነ ” ( አንድ ቦታ ላይ አንዴ የተነሳውን ግንዛቤ ለመድገም) በሦስት ነገሮች ላይ፣ ዓይናችንን፣ (የሞትና የሽረት ጉዳይ ስለሆነ፣ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄም እየሆነ ስለመጣ) በእነሱ ላይ መጣል ይኖርብናል። ልባችን እና አእምሮአችንንም ከፍተን እነሱንም በጭፍን ሳይሆን በቀና መንገድ ፣ መመልከትም ይኖርብናል። እነሱም እንግዲህ እነዚህ ናቸው ። ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ልጆችን አንድ አድርገው፣ ይህቺን አገር በዚያውም እኛ እንዳንጠፋ ለዘለዓለም የሚጠብቁን ተመክሮዎች – አላንዛዛውም – ሦስት ናቸው።
አንደኛው – ይህን -አዲስ አይደለም ሐዋሪያው ጳውሎስ ቀደም ብሎ አሰተምሮአል- እምነት ነው። እምነት ስንል – ሁላችንንም አንድ የሚያደርገን ፣ አንድ አሃዱ አምላክ ማለት ነው። ሦስቱም፣ ለማስታወስ ፣ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆኑ የአገራችን ሃይማኖቶች ተከታዮች በዚህ በአሃዱ አምላክ ያምናሉ።
ሁለተኛው ፍቅር ነው።…እሱም በመጀመሪያ የቤተሰብ ፍቅር ነው። …የጎረቤት ፍቅር እና… ከዚያም አልፎ የአገር ፍቅር፣ የኢትዮጵያም አገራችን ፍቅር ነው።ማክያቬሊ ከእናት አገር ፍቅር ምንም የሚበልጥ ፍቅር በዚህ ዓለም ላይ የለም ይላል። ሰውዬው ስለምን እንደሚናገር ያውቃል። አለበለዚያ የማንም ባሪያ ትሆናለህ ማለቱ ነው።
ሦስተኛውና የመጨረሻው እሴት ደግሞ በሰበአዊ መብት መከበር ላይ የተመሰረተ ነው። … የግለሰብ፣ የዜጋ ነጻነት፣ የአንድ ሰው ሙሉ ሰበአዊ ክብሩና መብቶቹ በማንም ሳይረገጡና ሳይደፈሩ መጠበቅና መከበር ፣ እነዚህ ድርድር የማይደረግባቸው መሠረታዊ መብቶቹ ናቸው። ያለፈው ታሪካችንም እነዚህ መብቶች በአለመከበራቸው ያመጣብንን የአረመኔ ኢ-ሰበአዊ ድርጊቶች፣ በሰው ልጆች ላይ ምስክር ሁኖ የሚቀርብ ኽያው ማስረጃ ነው። እንግዲህ በእነዚህ ፍልስፍናዎችና እምነቶች፣ በእነዚህ “አዲስና የቆዩ ርዕዮተ ዓለሞች” እሴቶችና መንፈሶች፣ ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አቀነባብረን ፣ አዋቅረን እንደ ሌሎቹ፣ እኛም፣ …እንደ ጃፓኖቹ ወይም እንደ አሜሪካኖቹ ወይም እንደ ጀርመኖቹ…ተከባብረንና ተቻችለን ፣ በሕግ የበላይነት ተመርተን ፣ ተገቢውን ቦታ በዓለም መድረክ ላይ ይዘን፣ ንጽሁን የነጻነት አየር በእናት አገራችን፣ በኢትዮጵያ ከአወቅንበት ልንተነፍስ እንችላለን።
ይህ አመለካከት ፣ይህ ፍልስፍና አዲስ አይደለም። ፍልስፍናው የቆየና እላይ የተጠቀሱት አገሮች የጨበጡት ፣ አማራጭ የሌለው በመከራ የተገኘ ትክክለኛ ዓለም አቀፋዊ ተመክሮም ነው። ልዪነት ቢኖረው ምናልባት “በትንሹ” ነው። ይህኛውም! ያኛውም… አሜሪካዊ ወይም ጃፓናዊ፣ ወይም ጀርመናዊ … እንደሆነው ሁሉ፣ በትንሹ እኛም የምንለው “ኢትዮጵያዊ መንፈስ”አለው። ግን ይህ ስለተባለ “ዓለም አቀፋዊነቱን” ፈጽሞ አይሽረውም።
“አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፣ በእግዚአብሔር ስም አሸነፍኩአቸው ። መክበቡንስ ይክበቡኝ፣….በእግዚአብሔር ስም አሕዛቦቹን አሸነፍኩአቸው።”
መዝሙረ ዳዊት 117 ቁ.10-11 ሃሌ ሉያ …ሉያ!
የአወናባጁ የአምባገነኖች ዘመን -የፈለጉትን ስም እነዚህ ሰዎች ይያዙ፣ አክትሞአል። የሚሰማቸውም ሰው የለም፤ እየተንጠባጠቡ ደጋፊዎቻቸው ሳይቀሩ ጥለዋቸው ሄደዋል። ሃሌ ሉያ …ሉያ!