ለ አእምሮ (PDF)
ለ አ እ ም ሮ (ርዕስ አንቀጽ/Editorial)
ለማን ነው ይሄ ሁሉ ጥረትና ድካም?…..ለመጪው ትውልድ ገና ለአልተወለደው? …ለአሁኑ ትውልድ? ወይስ…ለተበታተነው? …ለአበደው ትውልድ?…ወይስ በነገር ለተሳከረው?…ኢትየጵያዊነቱን ለከዳው …ወይስ አሁንም በኢትየጵያዊነቱ ለሚኮራው ትውልድ ? ?
እረ…አእምሮ…እረ ! ለመሆኑ ይህ „ለአእምሮ „ የሚባለው መጽሔት ለማን ነው? …. ለጥበብ፣… ወይስ ለጠብ?…. ለአንድነት? ወይስ መጨረሻ ለሌለው ክፍፍል?
ቢያንስ- በዚህኛው መጽሔትና በዱሮው መካከል – የአንድ መቶ አመት፣ ልዩነት አለ።
ያኛው በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ፣ በአጤ ምንልክ ጊዜ:- በሃያኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ብቅ ያለ ጋዜጣ ነው። ይህኛው፣ አርፍዶ የወጣው፣የዛሬው መጽሔት ደግሞ፣ አሁን በያዝነው፣ በሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።
በሁለቱ ጊዜያት መካከል:- ጥንታዊ ግሪኮች እንደሚሉት- ብዙ ወሃ ፣ በድልድዩ ሥር፣ ፈሶአል።
የሰገሌ ጦርነት፣ አንደኛው ነው። የጣሊያን ወረራና የአምስት ሚሊዮን ወገኖቻችን እልቂት ሁለተኛው ነው። ከዚያ በፊት በዋድላ አውራጃ አንቺም በሚባለው ሜዳ የራስ ጉግሣ ወሌ ጦር ድል ይመታል። አብዛኛው፣ታሪካችን በጦርና በጦርነት ላይ ያተኮረ ነው? ለምን?
አርበኝነትና ስደት፣ ድልና ነጻነት፣ መልሶ መቋቋምና፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት፣ የነዋይ ወንድማማቾች፣ የገርማሜምና የመንግሥቱ ነዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራና፣ በዚያ ሳቢያ እነዚያ ጣሊያንን የመከቱ የአዛውንት አርበኞች ሞት፣ ሌሎቹ፣ በአገሪቱ ላይ የተፈራረቁ ክስተቶች ናቸው። የመንግሥት ግልበጣ ሙከራም አንድ ጊዜ ብቻ አልነበረም!
ንጉሡ ይወርዳሉ። ደርግና ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማሪያም:- ወደ አንድ መቶ ሃያ የሚሆኑ ሰዎች ቤተ መንግሥት ገብተው፣ ሥልጣን ይዘው፣ ሶሻሊዝምን አውጀው፣ የአንድ ፓሪቲ አምባገነን አገዛዝን :- ብዙዎቹ እያጨበጨቡ ጥቂቶቹ እየተቃወሙ ፣ በኢትዮጵያ፣ላይ ይመሰርታሉ። ለምን?
ከዚያ በፊት!
ከዚያ በፊት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ አንድ ሕንጻ፣ አባቶቻችን ድንጋይ ተሸክመው እንዲሰራ ይደረጋል። የሕዝብ እንደራሴዎች መሰብሰቢያ አዳራሽ ፤ ሸንጎ፣ በዘልማድ ፓርላማ ፣ የሚባለው ሕንጻ፣ በታላቁ ቤተ መንግሥትና በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን መካከል ተሰርቶም ይመረቃል። ሁለት ክፍሎችም:- የሕግ መወሰኛ እና የዘውድ ምክር ቤት- እነደ እንግሊዙ ፓርላማም እንዲኖረውም- ይደረጋል።
ኢትዮጵያም፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፣ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ትሆናለች።
ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች እና ሐኪም ቤቶች ፣በአገራችን ይከፈታሉ። መንገድ እና ድልድይ ይዘረጋሉ። ባንክ ቤቶች፣ ማተሚያ ቤቶች፣ የቲያትርና የሲኒማ አዳራሾች፣ ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች፣ ሆቴልና አልቤርጎ ቤቶች፣ መሸታ ና ዳኒኪራ ቤቶች፣ የኳስና የስፖርት ቤቶች፣ የአይሮፕላንና የባቡር ጣበያዎች ይከፈታሉ። የአየርና የባህር ኃይል፣ የምድር ጦርና የፖለሲ ሠራዊት፣ የክብር ዘበኛም ጦር፣ ይመሰረታል።
ሙዚቃው ይደራል። አለባበስና አካሄድ፣ አነጋገርና አመለካከት፣ ወግና ሥርዓት፣ ባህልና ልማድ፣ ቀስ እያለም በትንሹ፣ ይቀየራል። ቀሰ እያለም፣ ይህ አዲስ ሁኔታ፣ በከተማ ውስጥ፣ ሌላ መልክ ይይዛል። ነገሮች ይናጋሉ።
ሁለት ትውልዶች፣ አባትና ልጅ የማይግባቡበት ደረጃም ላይ በቀላሉ ይደረሳል። አንደኛው ቀስ እያለ እያዘገመ፣ እንዲያውም እየፈዘዘ እዚያው የነበረበት ቦታ ላይ ቆሞ፣ መቆየቱን ይመርጣል። ሌላው፣ ወጣቱ ትውልድ፣ ትንሽ ፊደል የቆጠረው፣ እየተጣደፈ፣ እንዲያውም ሳያስበው፣ „በጭፍን ዓይኑ፣ ሰተት ብሎ አብዮት የሚባለው እሳት“ ውሰጥ፣ ዘሎም ይገባል።
….ማርክሲዝም፣ ሌንንዝም፣ ስታሊንዝም፣ ኮሙኒዝም፣….መገንጠል፣ የጦር ትግልና የመደብ ትግል፣ በተወሰነው ክፍል አሸናፊ ሁኖ ይወጣል። ኤርትራ ! በስንት የዲፕሎማቲክ ትግል ከእናት አገሩዋ ከኢትዮጵያ ጋር የተባበሩት መንግሥታት ተቀብለው፣ ትዋሃዳለች።
መልሳም፣ይህች አገር፣ እንደገና እንድትገነጠል ትደረጋለች። ሌሎቹም እንገንጠል ይላሉ።
ከዚያ በሁዋላ በአገሪቱ ላይ የወረደውን የለውጥ መዓት፣ “ጥሩውንም መጥፎውንም“ መለስ ብለን ወደፊት በዚሁ መጽሔት ላይ እናነሳለን።
ዛሬም ያለንበትንና የገባንበትንም ሁኔታ፣ ቀስ ብለን ረጋ ብለን ሳንቸኩል፣ እሱንም እንስተን በጋራ እንመለከታልን።
ይህ ሁሉ ሲሆን ሌላው ዓለም ቆሞ አልጠበቀንም። እኛን ጥሎ፣ ፈትለክ ብሎ ሄዶአል። እኛ ፣ ከነበርንበትና ከገባንበት ጣጣ መንጣጣ ሳንወጣና እዚያው ውስጥ ተዘፍቀን፣ ወዲያና ወዲህ ስንገላበጥና ስንወናበድ፣ ሌላው ዓለም ፣ በአንዴ ከእኛሁዋላ ተነስቶ አፈትልኮ ያመለጠበትንና የደረሰበትን የዕውቀትና የሥልጣኔ ደረጃ ለማነጻጽረው፣ በጎን አስቀምጠን፣ ማንም እነዲመለከተው፣ ወደፊት እናደርጋለን። ሌሎቹ፣ በምን ብልሃት ተስማምተው ኖሩ? … ኖረውም፣ አተኩሮአቸውን፣ በሥልጣኔና በቴክኒክ፣ በደሰታ ና በሰላም ፣ በሥነ-ጽሑፍና በጥበብ ላይ ብቻ ጣሉ? ብለንም እንጠይቃለን። መልሱንም፣ ሚሥጢሩንም ወደፊት ፈልገን እዚሁ መጽሔት ላይ እናሰፍራለን።
አሁን፣ ግን ለጊዜው፣ ከሁሉም ነገር፣ እኛ ለሁለት አርዕስቶች ብቻ ቅድሚያ ሰጥተን፣ በእነሱ ላይ እናተኩራለን።
አንደኛው የነጻነትና የነጻ ሕዝብ ሰብዓዊና ዲመክራሲያዊ መብቶቹ የመከበር ጉዳይ ላይ ነው። ሁለተኛው፣ ነጻና ሁሉንም ዜጋ እኩል የሚያስተናግድ ህብረተሰብ እንዴት፣ በአገራችን ይመሰረታል ? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ፣ በሰፊው እንወያያለን።
….መተቸት፣ ….መቃወም፣ የተለያዩ ሐሳቦችን ማራመድ፣ ….መደራጀት፣ ነጻ ምርጫ ውስጥ ገብቶ መምረጥና መመረጥ፣…. ነጻ-ጋዜጣ፣…. ነጻ -ራዲዮና ነጻ- ቴሌቢዠን፣ የሸንጎ ወንበር መያዝ፣ የሥልጣን ገደብና የሥልጣን ቁጥጥር፣ ….እነዚህን ሕገ-መንግሥቱ ላይ የሰፈሩትን መብቶች በሥራ ላይ ለማዋል፣ ምን መደረግ እንዳለበት ? እሱስ እንዴት እንደሆነ፣ እንመረምራለን።
ሕብረተሰቡን የሚበትኑና የሚከፋፍሉ፣ ነገሮች ምንድናቸው ብለን፣እራሳችንን ወደፊት እንጠይቃለን። ሕብረተሰቡንና አገሪቱን ኢትዮጵያን አንድ አድርገው የሚያስተሳስሩና የሚገነቡም ጉዳዮች ምንድን ናቸው ብለንም ጠይቀን ከእናንተም ጋር አብረን መልሱን በጋራ እንፈልጋለን።
እንደሚታወቀው፣ ለአለፉት አመታት „በልዩነቶቻችን ላይ ብቻ አተኩረን“፣ ወርቃማውን ጊዜ እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች ሳንጠቀምበት አሳልፈናል። እሱንም ሳንሸፋፍን አንስተን እንነጋገርበታለን።
በዚያው ልክ እኛም፣ እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች፣ እንደ አሜሪካና እንደ ቻይና፣ እንደ እነግሊዝና፣ ሩሲያ…. እኛንም ምንድነው አንድ የሚያደርገን ነገር? ብለን እራሳችንን ጠይቀን በመልሱ ላይ እንደ ሰለጠኑ ሕዝቦች፣ እኛም፣ ወደፊት እንከራከራለን።
በዚህ መንፈስ፣ በዚህ ዓላማ ሥር ይህን „ለአእምሮ“ የተባለውን መጽሔት፣ ለጊዜው በዚህ መልክ ለእናንተም ፣ ለእኛም፣ በተለይ፣ ለአዲሱ ትውልድ፣ በአገሩ በኢትዮጵያ፣ ጉዳይ እንዲወያይበት፣ እንዲትወያዩበት፣ …. እንድትከራከሩበት፣ አዳዲስ ሐሳቦችን እንድታሰራጩበት፣ ሜዳውንም ፈረሱንም ይኸውላችሁ ብለን እንድትጠቀሙበት ከፍተናል።
በግልጽ ለመናገር፣ ይህ መጽሔት፣ በአገራችን ነግሦ፣ እስከ ዛሬ ድርስ ወደፊት ወደሁዋላም፣ ወደ ግራም ወደቀኝም፣ እንዳንመለከት፣ ዓይናችንና አእምሮአችንን፣ ጨፍኖ፣ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰንን፣ „እኔ ብቻ አውቃለሁ፣ የሚለውን የአምባገነኖችን፣ አስሰተሳሰብ፣ የቶታሊቴሪያን፣ አስተሳሰብን“ ይቃወማል። አእምሮ:- ለአእምሮ፣ ለነጻ አስተሳሰብና ለነጻ ሕዝብ፣ ለነጻም ዜጋና የብዙ ፓርቲዎች፣ የፓርላማ ሥርዓት፣ የቆመም ነው።
*
*——————————መጀመሪያ ገጽ ለመመለስ—————————–
ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements > Le’Aimero’s Disclaimer