Category Archives: ርዕስ አነቀጽ / Editorial

ዳግማዊ ምኒልክ (ርዕስ አንቀጽ)

ዳግማዊ ምኒልክ (ርዕስ አንቀጽ)

ዳግማዊ ምኒልክ

ዳግማዊ ምኒልክ

 

እኛ ኢትዮጵያኖች ሙታንን በማስታወስ „ዘለዓለማዊ“ ማድረግ ቀርቶ የሰባት አመቱ  -ጥቂቱ ይህን ቀን ይጠብቃል- ተዝካር ሳይወጣ እንኳን አብዛኛዎቻችን ንዳልነበሩ እንረሳቸዋለን።

አፈር ሰውዬው አንዴ ከለበሰ ማን አስታውሶት የእሱን መቃብር መልሶ መላልሶ ይጎበኛል? ማን አታክልት መቃብሩ ላይ ተክሎ አልፎ አልፎ እየወረደ እሱን ይኮተኩታል? አበባውንስ ጥዋት ማታ ወሃ እየቀዳ ማን ያጠጣል? ሜዳውንና አካባቢውንስ ማን ዞር ብሎ ይጠርጋል?

ይህን የሙታን ቀን የሚባለውን ነገር ቤተ- ክርስቲያናችንም  አታውቅም። የሞስሊሙም ማህበረ ሰቡም  እንደዚሁ አያውቀውም። አይንከባከበውም። 

 ለአገራቸው ዳር ድንበር ወይም ለነጻነታቸውና  ለባንዲራቸው የሞቱትንና የወደቁትን ልጆቹዋን የመከላከያ የጦር ሠራዊቱም የጦር ኃይሉም ይህን ቀን በአመት አንዴ የሚያስታውስበት ቀን  እንኳን – ሐውልት መሥራቱን እንተወው የለውም።

ያለውንና የኖረውን ማጥፋት የነበረውን ማቃጠል ከዚያም አልፎ በእሱ ቦታ ደግሞ ለአዲሱ ትውልድ „…እኔም እኮ አዲስ ታሪክ መጻፍ እችላለሁ እንችላለን“ በሚለው ከንቱ ውዳሴ ብቻ ብዙ ትርዕይቶች ማቅረቡን የፖለቲካ መደቡ በተቃራኒው ያውቅበታል። በአለፉት አመታት እነደዚህ ዓይነቱን ቲያትሮች – የተመዘገቡ ናቸው- በተደጋጋሚ አይተናል።

…ምን ለመሆን? ብሎ እነሱን የሚኮረኩር፣ የት ለመድረስ ?…ብሎ እነሱን በጥያቄ የሚያጣድፋቸው፣እሩጫው ወዴት ብሎ እነሱን የሚወቅሳቸው፣ የራሳቸው ሒሊናም ሆነ ሌላ ሰው የለም። በእርሱ ፋንታ በርቱ የሚል ድምጽ ግን እንደገደል ማሚቶ ከሁሉም ቦታ ይሰማል።

ስንቱ ነው የእናቱንና የአባቱን መቃብር የሚጎበኘው? አልፎ አልፎስ ብቅ ብሎ የሚጠርገው? የሚንከባከበው?

ምኒልክ ከሞተ አንድ መቶ አመቱ ነው። ይህን ምክንያት በማድረግ በስሙ የተዘከረበት ስሙ የተነሳበት ፣ጉባዔ በሥነስርዓቱ የተካሄደበት ጊዜ የለም። ቢኖርም ብዙበቦታ አልተሰማም።   

ለቴዎድሮስም፣…ለዮሐንስም፣…ለዘውዲቱም ፣ለኃይለ ሥላሴም …ለንጉሥ ….እገሌና እገሊት ….ጥቂቱን ብቻ ለመቁጠር እነቁጠር ለእነሱም -ይህ ነው የአብዛኛው አስተሳሰብ- ምንም ስለ አልተደረገ „ለምን ለምኒልክ ብቻ ይህን ይህል ቦታ ከአልጠፋ ነገር ትሰጣላችሁ ?“ የሚለን ሰው አይጠፋም።          

ምኒልክ የሚለው ስም በኢትዮጵያ የነገሥታትና የአገሪቱ ታሪክ -የሌሎቹ ስም ይደጋገማል – በአለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት ምክንያቱ ምን እነደሆን በግልጽ አይታወቅም እንጂ-  ሁለት ጊዜ ብቻ ነው በታሪክ ላይ ብቅ ያለው።

አንደኛው በኢትዮጵያ መንግሥትና ግዛት የምሥረታ ሚቶሎጂ [1]፣ የቀዳማዊ ምኒልክ ታሪክ ሲሆን

ሁለተኛው ደግሞ ከስንት ሺህ አመት በሁዋላ ብቅ ያለው የዳግማዊ ምኒልክ ሥራና ገድል ነው።

እኛዚህን ትልቅ ጥቁር ሰው፣ የምኒልክን ታሪክ ዛሬ የምናነሳው መቶኛውን የሙት አመት ለማስታወስ ነው።

የእሳቸውን ታሪክ በጥቂቱ  አስቀምጠን  እንዳለፍን ምኒልክ ከሞቱ ከአምስት አመት በሁዋላ በደቡብ አፍሪካ የተወለዱት የሚስተር ኔልሰን ማንዴላ ዕረፍት –  እኛም በዝግጅት ላይ እንዳለን ደርሶን- ይህ ዜና እኛንም እነደ ሌሎቹ አስደነግጦአል።

በሁለቱም የአፍሪካ መሪዎች መካከል የአንድ መቶ አመት ልዩነት አለ።

አንደኛው ንጉሥ „…አገሬን ሕዝቤን ነጻነቴን ለባዕድ ለቅኝ ገዢ ወራሪ ኃይል አልሰጥም“ ብሎ በዲፕሎማሲውም መንገድ በሁዋላም ወረድ ብለን እንደምናየው፣እሱም አልሆን ሲል  በጦር ሜዳም አደዋ ላይ ተዋግቶ የኢትዮጵያን ስም ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝብን መብት- አሁን የእሱ ሐውልት ይፍረስ የሚሉትንም ሰዎች መብት ጭምር ተከራክሮ- ይህ ጀግና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንድ ላይ አስተባብሮ ከእነሱም ጋር አብሮ አንድ ላይ  ቆሞ  ነጸነታቸውን፣ነጻነታችንን እሱ አስከብሮአል።

አለ ምክንያት አይደልም ኔልሰን ማንዴላ በሁዋላ የመሩት „የደቡብ አፍሪካ ናሺናል ኮንግሬስ ድርጅት „…ሃይማኖቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣…የነጻነት ጥማቱን እንደ ኢትዮጵያ፣… የማንነታቸውን ኩራታቸውንና አርበኝነታቸውን፣ ….ከነጮች ጋር የእኩልነትና መብታቸውን ትግል እንደ ኢትዮጵያ አድርገው…“ (-ለዚህ ደግሞ የማንዴላን ባዮግራፊ ተመልከት-) „ ለመታገል እነሱ አውጥተው አውርደው የተነሱት።

ኔልሰን ማንዴላ በብዙ ትላልቅ የሽንጎ አዳራሽ፣ የፓርላማ  ሕንጻ ውስጥ በበርካታ የዓለም ከተማዎች ተጋብዘው ግሩም ንግግር ስለ የሰው ልጆች እኩልነት፣ስለ ነጻነትና ስለ ሰባአዊ መብቶች ስለ ዲሞክራሲና ስለ ዘረኛነት መጥፎ ጠንቅነት ንግግር እንዳደረጉ ሁላችንም እናስታውሳለን።

በኢትዮጵያ እንኚህ ሰውንና ድርጅታቸውን በረዳው  በዋና ከተማው በአዲስ አበባው የሸንጎ መድረክ ላይ ግን ብቅ ብለው አንድ ጊዜም ንግግር እኚህ ሰው አላደረጉም። ለምን አዲስ አበባ የሽንጎ አዳራሽ ውስጥ ንግግር ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ  ምክንያቱ – እኚህ ሰው ኪዩባ ሳይቀር እዚያ ድረስ ወርደዋል- ለእኛ ግልጽ አይደለም። ለምን አሥመራ ሄደው እዚያም የሽንጎው አዳራሽ ውስጥ ሌላ ቦታዎች እንደአደረጉት እንደአልተናገሩ ምንም የምናውቀው ነገር የለም።

በተባለው ግል የታሪካቸው በባዮግራፊአቸውወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የኢትዮጵያን የአይሮፕላን አስተናጋጆች ተመልክተው እንደተገረሙ ጽፈዋል።ቆየት ብለው አይሮፕላን አብራሪውን ሲመለከቱና ጥቁር ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያኔ በዓይናቸው ሲያዩ መደነቃቸውን እኝህ ሰው ጠቅሰዋል።

„ፖሊሱን፣የክብር ዘበኛውን፣ንጉሡን….ሲቃኙ ደግሞ  „ለካስ ይህም አለ ወይ…“  ብለው ሳይደብቁ በመጸሓፋቸው ላይ አሥፍረዋል። በሁዋላም  „በጦር ትግል ሥልት“  በኢትዮጵያኖች እንዲሰለጥኑ በንጉሡ ትዕዛዝ ተደርጎአል።

 ማንዴላ ከንጉሡ የተሸለሙት ሽጉጥ በሁዋላ ጋርዲያን እንደ ጻፈው (ለኃይሌ ቦታ የሰጠው አንድም ትውልድ የለም) ሁለት ሚሊዮን ፓውንድ እሰከ ማውጣት ድረስ እነደሄደ ጋዜጣው ተገርሞ ጽፎአል።

ምኒልክ በነጻነት ትግል፣ማንዴላም በነጻነት ትግል ሕያው ሁነው ሁለቱም ይኖራሉ። አንደኛው የተረሳውን ለመድገም የቅኝ ግዛት ወራሪዎችን በመከላከል ነው። ሌላው የቅኝ ገዢዎችን የበላይነት በመቃወም ነው።

ምኒልክ ነጻነታችንአስክብሮ መንግሥቱን አመቻችቶ ለአጼ ኃይለሥላሴ እና ለእኛ ለአለነው ትውልድ አገሪቱን አስተላልፎ ሄዶአል። ማንዴላም ኢትዮጵያን አረአያ አድርጎ ሁሉም የደቡብ አፍሪካ ኑዋሪዎችና ተወላጆች ነጩም ጥቁሩም፣ክልሱም ሕንዱም …ቻይናው አረቡም… የአገሪቱ ዜጎቹ ሁሉ እኩል በነጻ  የሚኖሩበት ዲሞክራቲክ  ሕብረተሰብ መሥርቶ አልፎአል።

በሁለቱ ሰዎች መካከል የአንድ መቶ አመት ልዩነት አለ። ለምን ምኒልክ የዲሞክራቲክ ሥርዓት ለኢትዮጵያ አላመጣም ብለን ልንከሰው አንችልም።

የምኒልክን የነጻነት ትግልና የፖለቲካ ጥበብ ከእሱም ጋር  የኔልሰን ማንዴላን „ለዲሞክራሲና ለሰበአዊ መብቶች መከበር- ጥቁር ይሁን ነጭ፣ክልስ ይሁን ሕንድ- የእነሱን የዜጎች መብት መጠበቅና ማወቅ ማክበርም“…  እነዚህን ሁለቱን አስተሳሰቦች አጣምሮ፣አዳቅሎ ለአገሬ እሰራለሁ፣ እንደዚህ  ዓይነቱን ፖለቲካም በኢትዮጵያ አራምዳለሁ ለሚል ሰው፣ ሁለቱ የሰሩት ሥራ ሕያው ሁኖ የሚቆም ግሩምና መልካም፣እጅግም ደስ የሚያሰኝ  ጥሩ ትምህርት  ነው።  ከዚህ ውጭ መጀመሪያ ልማት በሁዋላ ዲምክራሲና ሰበአዊ መበት  የሚለው ራዕይ „ …ዕብደትና ምኞት“ ነው።

በ„ዕብደት“ ደግሞ የሚመጣውና የሚሆነው ነገር ስለ ማይታወቅ ይህም ነገር አደገኛ ስለሆነ ከዚህ ነገር ራቁ ይባላል። “…ምኞት“ ግን ምኞትደግሞ የሌላውን መብት እስከአልተጋፈ ድረስ „ይፈቀዳል።“ 

 መድሓኒት ቀማሚ ነጋዴዎች እንደሚሉት”…ከዚህ ለየት ያለ ሓሳብ ያላችሁ ሰዎች ….ብዙ ቦታ ሳትደርሱ ሐኪማችሁን ለማንኛውም ነገር ጥርጣሬ ከአላችሁ እነሱን እባካችሁ አነጋግሩ…።“ 

እኛም ይህን ማለቱን ለዛሬ – ይቅርታ አድርጉልን-እንመርጣለን።

መልካም ንባብ! መልካም ትካዜ! መልካም ግንዛቤና ምናልባት ደግሞ መልካም  ጥያቄና አስተያየት !

እንደ ምኒልክ በዓለም ላይ የተከበረ፣ እንደ እሱም በአንዳንድ በገዛ ልጆቹ አልአግባብ የተጠላ – ሰው የለም!

 

 ዋናው አዘጋጅ ይልማ ኃይለ ሚካኤል    

 


[1](ይህን ደግሞ በሌሎች ትላልቅ የዓለም ሕዝብ ታሪክ የምናየው ነው- ሌላው ቀርቶ በተኩላ ሞግዚትነትና ከእሱዋም  „የእናት ወተት“( እርቦአት ልትበላቸው፣አውሬ ስለሆነች ትችላለችግን ታሪካቸው ላይ ይህን አላደረገችም) የእሱዋን ወተት ጠብተው ያደጉት- ይህን አልነበረም ብሎ መከራከር የአንባቢው ፋንታ ነው- ሁለቱ የሮም መንግሥት መሥራች ወንድማማቾች ሮሚውሲና ሮሙሎስ፣  እዚህ ላይ ይህን ማስታወሱ በቂ ነው፣…. ግሪኮችም፣ጀርመኖችም፣…ሩሲያና ቻይናዎችም ጃፓኖችም በየፊናቸው እረ ስንቱ ሥልጣኔ… ተመሣሣይ ታሪክ አሉአቸው)

 

*ዕ ን ቁ ጣ ጣ ሽ *(ርዕሰ አንቀጽ)

*ዕ ን ቁ ጣ ጣ ሽ*

 newyearjpg

አንድ የሚያደርገንና አንድ ያደረጉን ነገሮች ብዙ ናቸው።

አንደኛው አለጥርጥር ዕንቁጣጣሽ ነው። ይህን የሚክድ ሰው ከአለ ኢትዮጵየዊ እሱ/እሱዋ አይደሉም። ቀልዱ እዚህ ላይ ያቆማል። 

ኢትዮጵያን በዚያውም እኛን አንድ የሚያደርግ ነገር ቢኖር ይህ ዛሬ ሁላችንም የምናከብረው አዲሱ አመት ነው።  

ሁለተኛው የሰዓት አቆጣጠራችን ነው።  ሶስተኛው ልዩ የሆነው የምግብ አሰራራችን ነው። አራተኛው የዘመን መቁጠሪያችን ነው።  ቅርጫና በመሶብ ዙሪያ አብሮ መብላትም አለ።  

አምስተኛው ምርቃቱም ነው።  ከሁሉም የምናምንበት አሃዱ አምላከችንም አንደኛውና መዚጊያው ነው።  

ስድሰተኛውና ሰባተኛው፣ ስምንተኛውና….ዘጠነኛው….

የቡሄና የገና ጫዋታ፣ …አበባዬ ሆይ፣ ሙዚቃው፣  ትዝታና ሰርጋችን፣ ዕድር ዕቁባችን (…በአንዳንድ ነገር የተበሳጩ ልጆች፣ ሌላ ጊዜ ፈልገው በአገኙት ነገር ተደስተው ያናደዱአቸውን ጓደኞቻቸውን መልስው በተራቸው ሲያበሽቁ „ኤቺ ቤቺ…ይኸው እየው፣ ተመልከተው፣ … እኔም አለኝ…“ ልጆች ተንኮለኛ ናቸው እዚህ ይላሉ) እነዚህ ሁሉ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ናቸው።  በዚህ አያቆምም ሌሎቹም አሉ።  

የሆነው ሁኖ፣ እነዚህ ሁሉ ባህሎቻችን እኛን ከሌሎቹ እንደለ „ፍጹም ልዩ“ ያደርጉናል።

አዋቅረው አያይዘው አንድ አድርገው የያዙን ብዙ ናቸው።  ይህ ደግሞ ቢሉት ቢገፉት፣ ለመፋቅ ቢሞክሩት  አይፈቅም። ይህ በቀላሉ አይሰረዝም። ይህ ከአእምሮ አይጠፋም። ይህ ወደዱም ጠሉም ሕያው ሁኖ ለመጪው ትውልድም የሚተላለፍ ባህል ነው።

አንድ ጊዜ ከጸሎት በሁዋላ አዲሱን አመት ለማክረበር ወደ አንድ አዳራሽ ተያይዘን ስነገባ አንድ እንግዳ ፈረንጅ እኛን አይቶ የማያውቅ (ይመስለኛል ከሴት ጓደኛው ጋር አብሮ የመጣ) ሲተዋወቀን የአንዱን ጓደኛችንን ስም መሓመድ መሆኑን ሰምቶ ተገርሞ „…እንዴ እርሶም እዚህ ይመጣሉ እንዴ?“ ብሎ ሲጠይቀው“ እኔ እኮ ጌታዬ ሞስሊም እንጂ አረብ አይደለሁም „ ያለው መልሱ አይረሳም።

በሁዋላ በደመራ በመስቀል በዓል ላይ ይኸው ሰው፣  ሌላውን „ሐሰን“ የሚባለውን አንዱን ኢትዮጵያዊ ያገኘዋል።  ምን እንደተባባሉ መገመት ለአንባቢው መተው በቂ ነው።  

ክርስቲያኑም እስላሙም፣ አይሁዱም ጭምር (እነሱ ቤተ-እሥራኤሎቹ አሁን ወጥተው አልቀዋል ይባላል) አዲሱን አመት አብረው አንድ ላይ ያከብራሉ።  የዶሮ ወጡ አንድ ነው።  የቡና አፈላል ሥርዓቱ ( ሌላ ሳይሆን ) አይለያይም ያው አንድ ነው።  Coffee_Ceremony_1_Ethiopia

 የጠላ አጠማመቁ፣  የጤፍ እንጀራው፣ ፍትፍቱ፣ አገልግሉ፣  (ልጆች ምን ይላሉ እንደዚህ ዓይነቱን ነገር ብለናል…ኤች ቤች!) ድፎ ዳቦው፣ ሽሮው፣ በርበሬው፣ … የሸማ-ልብሱ፣ ጥጡ(ቀለሙ ይለያይ እንጂ) ነጠላው፣ ጋቢው፣ ቡሉኮው፣ ፈትሉና ሸማኔው ያው አንድ ነው።  ቅመሙም አንድ ነው። ኢትዮጵያም የተቀመመችበት ቅመም፣  ምሥጢሩም ይኸው ነው።  ግን ደግሞ የአንድነታችን ምሥጢሩ  ከዚህም አልፎ ይሄዳል።

 

የቤተ-ክርስቲያኑን ቁልፍ እስላሙ በታመኝነት ተረክቦ ይጠብቃል።  አጎቱና አክስቱ እስላም ወይም ክርስቲያኑ የሆኑ ጥቂት አይደሉም።  በጋራ የጉልበት ሥራ በደቦ ድሮም አሁንም ኢትዮጵያኖች ይገናኛሉ። ይረዳዳሉ።  

አብረው ያጭዳሉ።   በጋራ መንገድ ይጠርጋሉ።  በአማርኛ ቋንቋ ይነጋገራሉ።  ይገበያያሉ።  እንቅፋት ሲመታቸው የማይተዋወቁ ሰዎች መንገድ ላይ „ወንድሜን“ ይባባሉ።  ሲያስነጥሰው „ይማርህ/ይማርሽ „መንገድ ላይ ሰላምታ ይለዋወጣሉ።  ይህ የት ቦታ አለ?

በዛሬው ዕለት ደግሞ ልጆች ተሰብስበው፣ ዘር ሳይቆጥሩ ፣ ሐብት ሳያራርቃቸው፣ ሃይማኖት ሳይሉ፣  በአንድነት „አበባዬ ሆይ“ ይላሉ።  

ጎረቤት ጎረቤቱን ያምናል። ጓደኛ በአብሮ አደጉ ይተማመናል።  …በፍቅር ላይ የተመሰረተ የተደበላለቀ ትዳር በብዛት አለ።  ከእነሱም የወጡ ልጆች በያአለበት በየመንደሩና በየአገሩ ተሰማርተዋል።  ተበትነዋል።  

እንግዲህ ኢትዮጵያና ልጆቹዋ ድሮም እነደዚህ ነበሩ።   ዛሬም እንደዚህ ናቸው።  ይህ ነው እኛን ኢትዮጵያቾችን ከሌሎቹ ለይቶ „ልዩ“ የሚያደርገን ነገር።  ቢያንስ በዚህ በመስከረም ወር አዲሱን አመት (2006ዓ.ም)የሚያከብር ሕዝብ እኛ ነን።  

ይህ የት ይገኛል?

ሌሎች እኛን አንድ የሚያደርጉን ነገሮችም አሉ።  

እሱም ለሰበአዊ መብትና ለነጻነት ያለን፣  ወራሪ ነጮች ግን ሊረዱት የማይችሉት፣  የቆየ ጥማታችን እንዳለ ነው።  ለዚህ በማይሸጠውና በማይለወጠው ቀናተኛ የተፈጥሮ ነጻነታችንና መብታችን፣  አገራችንን ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ፣  ከቱርክና አረቦች ሴራ፣  ከፖርቱጋል ሙከራ፣  …አባቶቻችን አድነዋል።  

አሁን የሚቀረው ደግሞ  (ደግመን ደጋግመን የምናነሳው) ዕውነተኛው የግለሰብ መብቶች እንደገና፣  ለመናገር ያ! አምላክ  የሰጠንን የተፈጥሮ ጸጋ ሙሉ ሰበአዊ መብታችንና ነጻነታችንን አለአንዳች አምባገነን ፍርሃቻ እሱን ማስከበር ነው።  

ይህ ደግሞ አንዱን ከሌላው ሳይል አንድ የሚደርገን የ21ኛው ክፍለ-ዘመን፣  ግዳጅም ኃላፊነትም፣  መድረሻናግብም፣  የጉዞ መንገድም፣ የጋራ እሴትም ነው።  

ይህን አስመልክተን ስለ ፓርላማ ሥርዓት (ስለ ሸንጎ) አንድ ጽሑፍ እንድትመለከቱት አቅርበናል።  እዚያም ላይ ስለ ሶሰት ሥርዓቶች አንስተናል።

ስለ ሃይማኖት አክራሪዎች መንግሥት፣  ስለጠበንጃ አንጋቢዎች ሥርዓትና ስለ ዲሞክራቲክ ሕብረተሰብ፣  ከብዙ በጥቂቱ ዘርዝረን አልፈናል።  

 „አንድ ሕልም አለን“ ያ የእኛ የዘንድሮው ምኞትና ሕልማችን (እሱን እንናገር ከተባለ) እዚያ የሸንጎ አዳራሽ ውስጥ የተለያዩ ስምና ቀለም ያላቸው ድርጅት ተወካዮች ወንበሮቹን በምርጫ በአገኙት ድምጽ ተከፋፍለው ቦታቸውን ሲይዙና፣  ተዝናንተው አዳራሹ ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ ማየት ነው።

የተለያዩ ድርጅት ተወካዮች ከተከራከሩ በሁዋላ ቢራቸውንና ቡናቸውን አብረው ተገባብዘው ሲጠጡ ማየት ነው።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ወረድ ብላችሁ ደግሞ ሌላውን ጽሑፋችንን ተመልከቱት።

እንደምናውቀው ፣  ሃይማኖትና ባህል፣  ልማዶችና የኑሮ ዘይቤዎች፣  ታሪክና ምሳሌዎች….አንድን ሕዝብ አንድ የሚያደርጉ ክስተቶች ናቸው።  ከእነሱ ጋር የጋራ እሴትም/እሴቶችም የሰውን ልጆች አንድ ያደርጋሉ።  አለበለዚያ የአውሮፓን አንድነት፣  የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት፣  የሰሜን አትላንቲኩን የጦር ቃል-ኪዳን…ወዘተ መረዳት አይቻልም።

ከዚያ ውስጥ አንዱ እሴት ፓርላማና የነጻ ሰው መብት የሚለው ፍልስፍና ነው።

እንግዲህ ይህን እሴት አንስተን መልካም አዲስ አመት እንመኝላችሁዋለን።  መልካም አዲስ አመት ለእናንተም 364 ቀናቱን በሙሉ  በተከታታይ „እኛ“ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ለምትሉትም ወገኖቻችን ሁሉ አብረን እንመኛለን።  

ምክንያቱም ቢያንስ-ይህ ነው መነሻ ሐሳባችን- የዛሬው የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ቀን ሁላችንንም አንድ ያደርገናል።

አንድ ሕልም አለን ያ ሕልምም ለመድገም „ማንም…ፖለቲከኛ „ነን የሚለው ሰው ሁሉ አደባባይ ወጥቶ ተወዳድሮ በአገኘው ውጤት ፓርላማ ገብቶ ወንበሩን ሲይዝ ማየት ነው።  

ጠበንጃ እና ድርጅት ግን ከሁሉ በፊት፣  በመጀመሪያ፣  ልክ እንደ መንግሥትና ሃይማኖት፣ ሁለቱ መለያየት ይኖርባቸዋል።  መለያየትም አለባቸው።

 

የሰላም የጤና እና የዲሞክራሲ መት።

 

——

የመከረም 2006/September 2013 ልዩ እትም * ዕንቁጣጣሽ *

 

 

  

ፀጋ፥ብርሃን

spiritual-light

                             ፀጋብር

ሲያይዋት ትንሽ ናት።ጠጋ ብለው ሲተነትንዋት ይህ ነው የማይባል ትልቅ ነገር ነች።

ሳይታሰብ ብቅ ትላለች።ቆይታም ሳትወድ ትጠፋለች። ወዳጆቹዋ በነፍስ ግቢና በነፍስ ውጪ ሰዓት ብዙ ናቸው።የልባቸውን ያደርሱ ቀን ግን ተራ በተራ እነሱ እሱዋን እነደማያውቁዋት ጨርሶ ይከዱዋታል።

ከመሣፍንቶች ጋር አንድ ጊዜ አብራ ትቆማለች። „አብዮተኞችም“በጣም አድርገው ያስጠጉአታል።አክራሪዎቹም ያቅፉአታል። ፋሽሽቶቹም እነደ ኮሚኒስቶቹ አላማቸውና ፕሮግራሞቻቸው ላይ ከፍ አድረገው ያስቀምጡአታል።

ሥልጣን ላይ ሲወጡ ደግሞ ብዙዎቹ መልሰው እንደ የሚፋአጅ የፍም እሳት፣ እርግፍ አድረገው ሁሉም ይጥሉአታል። በእግራቸው ቢረግጥዋት -ይረግጡዋትል- ደስተኛ ናቸው።

ለወረጠላት መቼም እንደ ሱዋ „አመቺ“ ነገር የለም። በእሱዋ ስም ይዘምታል። በእሱዋም ስም ገንዘብ ይሰበሰባል። ሰውን ወደ ጦር ሜዳ መሰብሰብ ይቀላል።

ወጣቶች ልጆችም ዕውንት መስሎአቸው ሕይወታቸውን እሰከ መሰዋት ድረስ ይሄዳሉ። ተንኮልኛ አታላዩም፣ ይህን ሰለሚያውቅ እሱዋን ያስቀድማል። 

የዋሁም „ዕውነት“ ነው ብሎ ይህን የሚሉ ሰዎችን ሳይጠይቅና ሳይመራመር ዓይኑን ጨፍኖ ይከተላቸዋል። ሳያውቅ የገባበትን ጣጣና መንጣጣ አደገኛ መሆኑን የሚረዳው ግን ነገር ከእጁ ከአመለጠች በሁዋላ ላይ ነው።… ሲደርስበት ደግሞ ብዙ ነገር አልፎአል።

ልቡን አንዴ የሰጣቸው ደግሞ፣ ቢያታልሉትም „አሜን“ ብሎ ተቀብሎ ምንተ- ዕፍረቱን ሸፋፍኖ ውስጥ ውስጡን እየተቃጠለ፣ አንገቱን ደፍቶ ይከተላቸዋል።

የተቀረው ዓይኑን እሰከሚከፍት ድረስ በጭፍን መንገዱ አለጥያቄ አብሮ ይጓዛል። የደረሰበት ቀን ግን ወደ ሁዋላ ማለትም እሱንም ይከብደዋል።

ይህን ቀስቃሾቹ በደንብ ያውቃሉ።ይህን ተንኮለኛ አደራጆቹ በደንብ ይጠቀሙበታል።

ማናት ይህቺ፣ አንዳንዴ በሦስት አንዳንዴ በአራት ፊደል የምትጻፈው፣ ነገር ?

ከመሣፍንቱ እስከ ተራ አወናባጁ?… ከፋሽሽቱ እሰከ ኮሚኒስቱ ፣ ከአናርኪስቱ እሰከ ሽፍታው፣…ከቅኝ ገዢው እስከ…ባሪያ ነጋዴው ድረስ የሚያነሱዋት ቃል? 

ሊበርቲ ናት?… ወይስ አርነት?… ነጻነት ናት ወይስ ነጻ- ሰው?…ጥበብ? …ብርሃንና ዕውቀት? ወይስ ጨለማ?…

ሞሰሊን ኢትዮጵያን ሲወር ያስቀደመው ቃል ቢኖር „…የሥልጣኔ ሚሺን፣… ኢትዮጵያን ከባርንት ለማውጣት የታቀደ ዘመቻ… ሲቭላይዚንግ ሚሽን..“ የሚለውን ቃል:- ለማስታወስ ወርውሮ ነበር። የወረራ ዘመቻውንም ያ ፋሽሽት የሰየመውም በዚሁ ግሩም ቃልና ጥሪው ነበር።

ሌኒንና ስታሊን፣ ማኦና ካስትሮ፣ ከእነሱ በሁዋላ የተነሱት ስፍር ቁጥር የሌላቸው „ነጻ-አውጪዎች፣ እስከ መገንጠል የሚለውን ትግላቸውን“ የቀየሱት፣ ያራመዱት፣ የልባቸውን ያደረሱት፣ በዚህች „አርነት“ በምትባለው ቃል ነበር።

በሌላ በኩል በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ በሕዝቡም ላይ ተነስተው የጨፈሩት ወታደሮች ያራገቡት „ሥርዓትና ቃል…“ ሌላ ሳይሆን ይኸው፣„…አርንትን፣ ..ነጻነትን፣ እኩልነትን፣ ሰበአዊ መብት፣ …ዲሞክራሲን “ነበር። የወታደሩ መንግሥትደርግም ብሎታል።„እናመጣላችሁዋለን…“ በሚለው ውሸት ዙሪያ እስከ አሁን ድረስ ብዙዎች ቆመዋል።

የ20ኛው ክፍለ ዘመን የውሸት ፖለቲካም በብዙ አካባቢ የተመሰረተው ፣በዚሁ አታላይ ቃል ላይ ነው። እላይ ከተጠቀሱት ቡድኖችም ውስጥ አንዳቸውም የገቡበትን ቃላቸውን እስከ አሁን ድረስ አላከበሩም።

እንግዲህ ነገሩ ያላው እነሱ ጋ ሳይሆን እኛው ጋ ነው። prosaune1

„ነጻነትን፣…በሌላው አካባቢ እንደሚባለው፣ ሊበርን፣…ጥብብን፣ ብርሃንና ዕውቀትን…“ እባካችሁ ስጡን፣ እባካችሁን አምጡልን ብለን፣ ማንንም የምንጠይቀው ነገር ሳይሆን ፣ እኛው ነጥቀን የምንወስደው ነገር ነው።

መሬት ላይ የወደቀውን ነገር ብድግ አድርጎ የእራሳችን ማድረጉ ደግሞ ወንጀል አይደለም። ለዚህ ደግሞ ዕውነቱን ለመናገር፣ „ግብ ግብም፣ጦርነትም” የሚባለው ነገር ውስጥ መሄድ አያስፈልግም ።

ማመዛዘናና ነገሮችመመልከት፣… ማሰብና ያሰቡትን ነገር መናገር፣… መጻፍና መወያየት፣ መከራከርና መተቸት፣ እኛ የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ወይም አቴኢስቶች እንደሚሉት „ከተፈጥሮ“ ያገኘነው ፀጋና ስጦታ ነው። ለምን አምባገነኖች ይህቺን መብት ይፈሩአታል?

አንድ አምባገነን ሥልጣኑን መከታ አድርጎ ብዙ ነገሮችን „አታድረጉ ብሎ አንድን ሕዝብ ሊከለክል“ ይችላል። ማሰብን ግን እሱ ጨርሶ መከልከል ይችላል? በምንም ዓይነት፣ ማሰብን መከልከል አይችልም። በምን አቅሙ ነው፣ የአንድ ሰው ጭንቅላት ውስጥ ገብቶ ሊከለክል የሚችለው? ይህማ አስቸጋሪ ነው።

ምሮ ያሰበውን፣ የታሰበውንስ ቀና ሐሳብ ከሌላው ጋር ለመነጋገር (ምንም ዓይነት ሥልጣን ቢኖረው) ማንም ሰው ማንንም ሊያግደው አይችልም ።

እንግዲህ አሁን ያለነው፣ በዚህ „ፀጋ-ብርሃን“/ዘመነ፥ብርሃን በሚለው ጽሑፋችን እሱን አንስቶ መመልከቱ ላይ ነው። አምባገነኖች የእያንዳንዱን ግለሰብ ነጻነት፣ ለምን እንደጦር እንደሚፈሩ በየጊዜው አንስተን እንመለከተዋለን። 

እንግዲህ ይህ አንደኛው  አርዕስት ነው።

ሁለተኛው ስለ ጋርዲያን ጋዜጣ ነው።የምዕራቡ ዓለም ስለ ሚኮራበት ስለ ፕሬስ ነጻነት፣ ስለዚያም አታሚዎች ፍተሻ ፣ስለ ጋርዲያን ጋዜጣ ነው። ቻይና በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንዳለች አስተያየቱዋን ፈልገን ለማውጣት አስበን ነበር። አልተሳካልንም። ግን አገላብጣችሁ እንደምታዩት የሌሎቹም አስተያየት ቀላል አይደለም።

ሦስተኛው  አርዕስት„ ….እኛ ጥቁሮች እራሳችንን በእራሳችን፣ ተመካክረንና ተቻችለን ተፈራርቀን መግዛት ስለ አልቻልን፣ የዱሮ ጌቶቻችን ነጮች መጥተው ይግዙን…“ በሚለው አዲስ ጥሪ ላይ ያተኩራል።

ይህ ደግሞ ምን እንበላው „…ያሳዝናልም። ያስቃልም። ያቃጥላልም። ይኮረኩራልም። ….“ ወቸ ጉድም ያሰኛልም።

በተጨማሪም አወዛጋቢ ሰለሆነው የግብፅ ጉዳይ ያለንን አስተያየትና፣ እንዲሁም ስለ ውርሰ፥ቅርስ ለመነሻ ያህል የደረሰንን ሰነደንና  የሰዓሊው የእስክንድር ቦጎስያን ማስታወሻችንንም ተመልከቱት።  

ዋና አዘጋጁ

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

 

————-

—————————————————-

https://leaimero.files.wordpress.com/2013/04/a_schreibfeder.gif

አስተያየት ለመስጠት / Comments

——————————–

——————–

leaimero-reg-logo © ለ አእምሮ 2005 / © Le’Aimero Copyright 2013

ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements

Le’Aimero’s Disclaimer

—–