..ለሁሉም! (ከ ስነ፥ምግባር / ከሞራል ፍልስፍና)

The Garden of Eden

Advertisements

እኩል መብት ለሁሉም ዜጋ

…ለሁሉም!

(ከስነ፥ምግባር / የሞራል ፍልስፍና)

„ጥያቄው ትልቁ ጥያቄ ! እንስሶች ያስባሉ ወይም አያስቡም የሚለው አይደለም? ወይም እንደ ሰዎች እነሱ ይናገራሉ መናገርስ ይችላሉ? የሚለውም ጥያቄ ወሳኝ አይደለም። ትልቁ ጥያቄ እንስሶችን ሲጎዱአቸው ሲወጉአቸው ያማቸዋል ወይስ አያማቸውም?… ውጋትስ ይሰማቸዋል ወይስ አይሰማቸውም ? የሚለው ነገር እሱ ወሳኝ ነው።“

Jeremy Bentham (1748-1832)

መገመት እንደሚቻለው የቤት እንስሳም የዱር አራዊትም ወፍና ትላትሎችም የወሃ ውስጥ ነፍሳትም ጭምር ሲወጉአቸው ነፍስ ነውና እነሱም የያዙት አለጥርጥር ያማቸዋል። በአምላክ አምሳል የተፈጠረውን ሰው ደግሞ እነኳን መብቱን ረገጠውበት በነገር ስያዋክትም የባሰ ያነገበግበዋል። (ከማስታወሻ ደብተሬ)

A

ቀጥሎ የምናነበው ታሪክና የምንከታተለው ፍልስፍና ቀልድም ፌዝም የመድረክ ላይ ጨዋታ ሰው ማየት የሚፈልገውም ቲያትርም አይደለም።

ነገሩ-ጉዳን ለአልተከታተለው ሰው እንደሚመስለው – የአሽሟጦች ቀልድም ሳይሆን በዕውነት ላይ የተመሰረተ የሞራል ፍልስፍና እና ጥያቄም ነው።

እዚህ ከሰው መብት አልፈው ስለ እንስሶች መብት ማውራት ከጀመሩ -አንዳዶቻችሁ በአካባቢአችሁ እንደሰማችሁት- ጊዜው ረዘም ይላል።

እንደምናውቀው እዚያ በአፍሪካ በአጠቃላይ ስለ ሰው ልጆች መብት እንዳይነሳ በብዙ አካባቢ ከተከለከለ ቆይቶአል። እንዲያውም እንደምናየውና እንደምናነበው ይህን ነገር አንስቶ መከራከር ይሰጠኝ ብሎ መጠየቅ ያስቀጣል።

እዚህ ከአትላንቲክ ወዲህና ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲያ ለምንገኘው ሰዎች ደግሞ ከእንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ „…ለጋማና ለቀንድ ከብቶች ሙሉ የዜጋ መብታቸው በሕግ ይታወቅ“ ይባልላቸዋል።

እዚያ በአፍሪካ ዝም ብለህ አፍህን ይዘህ ተቀመጥ በየጊዜው ይባላል። ቀደም ሲል ቅኝ ገዢዎች በሁዋላ እነሱን በተኩት አምባገነኖች ተደጋግሞ እነደዚህ ዓይነቱን ነገር እንዳታነሱ ተብሎ ለብዙ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአል።

እዚህ ለቤት ድመትና ለውሻ፣ ለቤት ወፍና የሳሎን ዓሣ በተቃራኒው „ሰበአዊ የፍጡር መብታቸው“ – አትደነግጡ-„ ይከበር“ የሚሉ ሰዎች ተነስተዋል።

እዚያ በአምላክ አምሳል የተፈጠረውን አንድን ሰው የመናገር መብቱን ልበተኛ የታጠቀ ባለሥልጣን እንደ ጥጃ አለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝና አለ ዳኛ ፍርድ የፈለገውን ያህል አመት ሊጠፍረው ይችላል።

አዳኞች ጫካ ወርድው አንድም ጥንቸል፣ አንዲት ወፍ ቀበሮና ተኩላ አንበሳና አነር ዝሆንና አውራሪስ እንዳይገድሉ እዚህ „ይህን የሚያደርጉ ግለሰቦች ይቀጡ ይታገዱ“ ይባላል።

እዚያ ! በጥላቻ ላይ ተመስርቶ ትላንትና የሚተዋወቅ ጎረቤት በጎረቤቱ ላይ ጦር ሲመዝ አንዳንድ መንግሥታት ዝም ብለው ይመለከታሉ ይባላል። በርቱ የሚሉም እንዳአሉ እዚህ ይጻፋል።

አይጦች ከላብራቶሪ እዚህ ነጻ ወጥተው ተለቀው „በሰላም እንደሌሎቹ ፍጡሮች ይኑሩ“ ይባላል። እዚያ… በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ሰበአዊ መብቶች አምኒስት እንተርናሺናል ሂውመን ራይት ወች በየጊዜው እንደሚጽፉት „የሰው ልጆች መብት በእግር በደንብ ይረገጣል።“

ምን ዓይነት ዓለም ውስጥ ነው ያለነው?

B

ሦስት መጽሓፍት የእንስሳትን መብት አስመልክተው ገበያ ላይ በዚህ በያዝነው ወር ወጥተዋል።ይህን ከሚሉት ሰዎች መካከል ፈላስፋዋና ጋዜጠኛዋ የጀርመኑ ተወላጅ Hilal Sezgin (Artgerecht ist nur die Freiheit. Eine Ethik für Tiere 301 Seiten.16,95 €)[i] በአንደኛ ደረጃ ትገኝበታለች። ሁለቱ የአሜሪካን ፈላስፋዎችና ደራሲ Sue Donaldson & Will Kymlicka[ii] በሁለተኛ ደረጃ አብረው እነሱም ግሩም ሓሳባቸውን ይዘው ገባያ ላይ ቀርበዋል።

ሦስተኛው በFriederike Schmitz ተሰብስቦ የቀረበው „የእንስሳት ኤቲክ“ የሚለው በአለ 589 ገጹ ወፍራም መጽሓፍ ነው።[iii]

Animal Liberation የተባለው በPeter Singer ቀደም ሲል በ1975 ዓ.ም. የወጣው ተጨማሪ መጽሓፍ በአራተኛ ደረጃ ይጠቀሳል።

ሁሉም በአንድነት „…ከብቶችን ማሰር እነሱን አሥሮ ማሰቃየት፣ መግረፍ ማደለብና አንድ ቀን ጎትቶ እነሱን ማረድ አርዶም መብላት ይህ ተገቢ ሥራ ነው ወይ? ለመሆኑ ይህን ለማድረግ ማን ፈቀደልን? በምን ምክንያት እኛ የሰው ልጆች እንደዚህ ዓይነቱን ` ፍጅት` በእንስሶች ላይ ለማካሄድ የተነሳነው? ይህንንስ ማድረግ እንችላለን ወይ?… ሕሊናችንስ አይወቀሰንም ወይ? ሞራላችን ይህን ይፈቅዳል? ኤትኩስ አያግደንም ወይ? ይህን ሁሉ ለማድረግ የሞራል በላይነታችን ይፈቅድልናል ወይ? „ብለው እራሳቸውን ጠይቀው በሺህ በሚቆጠሩ ገጾች ላይ መልሳውቸን አስፍረው እሱን ይዘውልን ቀርበዋል።

…. ያለነውና አሁን የምንገኝበት ቦታም ይህን ግልጽ ለማድረግ የሞራልና የኤቲክ አንደኛው የፍልስፍና ዓለም ውስጥ ነው።

C

የቤት ሠራተኛን በጥፊ፣ አሽከርን በካልቾ፣ልጆችን በአርጩሜ፣ ተማሪን በአለንጋና በመጥረጊያ፣ሚስትን በቀበቶ መግረፍ መምታት መቅጣት እሷንም ሚስቴ ናት ብሎ አስገድዶ መተኛት በሕግ እዚህ የሚታወቀውን ለመድገም የተከለከለው ትላንትና ነው።

ጊዜው እሩቅ አይደለም- ይህን የከለከለው ሕግ የወጣው- ያለፈው ክፍለ ዘመን በ20ኛው ላይ ነው።

አሁን ደግሞ በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ-ዘመን -ነጮች ጠግበው የሚሰሩትን አጡ አይባል እንጂ- አንድ ሰው፣የቤት እንስሳውን የጋማና የቀንድ ከብቱን የውሻና የዶሮ ላባውን ጫፉን እንዳይነካ፣-ቢያንስ በጽሑፍ ደረጃ ኃይለኛ አስተያየቶች ተመራምረው ሰብስበው አሳትመው ጠርዘው ብቅ ብለዋል።

በእንስሳና በሰው ልጆች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት የሚፈልግ አንድ ሰው በምንም ዓይነት ሳያነሳ ዘሎ ማለፍ የማይገባው ነገር/ነገሮች አሉ።

ም ማንም ሰው እንደሚያውቀው በከብቶች ላይ የሚደረገውን በደልና ጭካኔ ነው። ነገሩ ከኢትዮጵያ ለመጣ ሰው አዲስ አይደለም።

ከብቶች በፍልጥና በጅራፍ፣ በድንጋይና በዱላ በሽመልና በአለንጋ ይገረፋሉ። ይደበደባሉ። አለፍላጎታቸው ከብት በመሆናቸው ይታሰራሉ እንዲያርሱም ይደረጋል። ከአቅማቸው በላይ ይሸከማሉ ይህን ሁሉ ፍዳ ከአዩ በሁዋላ ደግሞ አንድ ቀን እንደ አሮጌ ጫማ አንዳንዶቹ (ቆዳው የእነሱ ነው) ከቤታቸው ተባረው ሜዳ ላይ ይጣላሉ።

የተቀሩት ደልበው ቋቅ እስከሚላቸው ድረስ በግድ ተቀልበው በሁዋላ ተሸጠው እንዲታረዱ ይደረጋሉ።

ይሀ ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ጥያቄ ጸሓፊዎቹን አንገብግቦአል። በመጀመሪያ ግልጽ እንዲሆን „ይህን ለማድረግ ተንቀሳቃሽ ነፍስ በአለው በአንድ ከብት ላይ ለእኛ ለሰው ልጆች ማን ፈቀደልን?“ የሚሉ ሰዎች እዚህ ተነስተዋል።

D

ሁለቱም ሦስቱም ጸሓፊዎች በዓለም ላይ 56 ቢሊዮን ከብቶች በዓለም ላይ ታርደው – ይህ ቁጥር ከባህርና ከውቅያኖስ ከጫካና ከወንዝ ተለቅመው የሚወጡትን ትናንሽ ነፍሳትናንና ዓሣን ሌሎቹ ሕዝቦች እያጣፈጡ የሚበሉትን ቅንቡርስንና እንቁራሪቶችን ትሎችንና ጉንዳኖችን አያካትትም- ለምግብ ይቀርባሉ ብለው ይከሳሉ።

ለሒላል ሴስጊን ይህ ድርጊት ደር ሽፒግል ለሚባለው የጀርመን መጽሔት ተጠይቃ ስትመልስ እንዳለቺው „…በእንስሳትና በከብት ላይ የታወጀ ርህራሄ የሌለው ፍጅት ነው“ ብላ ሥጋ በላተኛውና አቅራቢ የቄራ ሰዎችን ከሳለች።

ዶሮና አሣማ ላምና በግ ጥንቸልና ዳኪዬ በሰው ሰራሽ ዘዴ እንዲራቡ ቶሎ እንዲደልቡ ተደርገው ታርደው ለገበያ ይቀርባሉ…ይህን ለማድረግ የሰው ልጅ የሞራል መብቱን ማን ሰጠው ይላሉ?

ሦስቱም ጸሓፊዎች የሚጠቀሙበት መንገድና የሚከተሉት ጎዳና የሞራል ፍልስፍና ነው።

እሱንም አንስተው ወደ ፖለቲካ ዓላማቸውና ጥያቄአቸው እሱን ለማስተዋወቅ ይቸኩላሉ። ለሆዳችን ሲባል ይህን ያህል ሕይወት እንዴት ይጥፋ? ለምን?በምን ምክንያት? ብለው እራሳቸውንም አንባቢውንም ይጠይቃሉ።

ሂላል ሴስዝጊን የእራሱዋ መልስ አላት። „ ምህረት የተደረገላቸው የእንስሶች ገነት„ በሚለው መንደሩዋ ሰፊ የገበሬ ቤትና ሜዳ ገዝታ በጉንም ላሙዋንም ዶሮ እና ፍየል ውሻና ድመቶችን ሰብስባ „ነጻነት ሰጥቼአቸዋለሁ „ብላ እነሱን „ሳትበላ“ ሴትዮዋ እነሱን ትቀልባቸዋለች።

የጀርመን ቀሳውስቶችና ካህናት አንድ ጊዜ ተሰብስበው የክርስቶስን ልደት ሲያከብሩ „እነሱም ከብቶቹ አምላካቸውን ማመስገን አለባቸው በሚለው የጸሎት ሥነ ስርዓታቸው ላይ“ዶሮና ላም አህያና በግ ሰብስበው ጸሎት በቅዳሴ ሲያደርሱ – ዶሮ እየጮኸ በሬው እያመጀገ በጉ ሣሩን እየበላ በቴሌቭዝን ለተመልካቾች ተላልፎአል።

አበዱ ማለት እንችላለን?

Sue Donaldson & Will Kymlicka ለጋማና ለቀንድ ከብቶች ለቤት ውስጥ እንስሳና ወፎች ለይስሙላ የችሮታ እውቅና ሳይሆን በትክክል „የዜግነት እኩልነት መብታቸው ይታወቅላቸው“ ብለው ተነስተዋል።

እሰከዚህ ድረስ ጥሩ ነው።

ለማዳ የቤት እንስሶች ብቻ ሳይሆኑ „ከተማው ውስጥ ያሉ የአደባይ እርግቦች አሞራና ቁራ ተኩላና ቀበሮ …እነሱም እንደ ማንኛውም የከተማው ኑዋሪ“ ይህ ነው የእነሱ ጥያቄ „እኩል መብት ይሰጣቸው „ ብለው አስተያየታቸውን ወርውረዋል።

ይህም እንግዲህ አንድ ቀን ሕገ-መንግሥቱ ላይ ይሰፈርልን ብለዋል። ዋና ክሳቸው እንስሶች እንደ ሰው ልጆች እነሱ ውጋትን ስለሚያማቸው አይወዱም አይችሉም -ይህ መቆም አለበት ባይ ናቸው።

E

ይህን በ21ኛው ክፍለ-ዘመን መስማት በጣም አይገርምም?

የት ነው ያለነው?

በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም እንደ አለፉት አመታትና ጊዜያት (እኛ ገና)„…ዲሞክራሲ በገደብ!… የለም ዲሞክራሲ አለገደብ፣ ዲሞክራሲ ለጭቁኑ ሕዝብ ብቻ… ዲሞክራሲ ለቡርጃውም!… የለም ለእነሱ መሰጠት የለበትም / …ለአንተም አይገባህም፣ለእሱ ጓደኛዬ ይገባዋል፣… ለዚያ ግን ጨርሶ አይሰጠውም !“ በሚባልበት ጊዜ እነደዚህ ዓይነቱ ጉዳይ እዚህ አውሮፓና እዚያ አሜሪካ የምዕራቡ ዓለም መነሳቱ በጣም አስደንቆናል። አስገርሞናል።

ለመሆኑ እንደገና ለመጠየቅ የት ነው ያለነው? በየትኛው የአስሰተሳሰብ ክፍለ-ዘመን ውስጥ ነው እኛ የምንገኘው?

“…. ጠባይህ…ታይቶ ትንሽ እንደ ሁኔታው ለአንተም ለእሱም ዲሞክራሲ ረጋ በል አንድ ቀን ይሰጠኻል/አይሰጥም„ በሚለው ንትርክ ዙሪያ ገብተን እንደ ዓይነ ስውር ሰዎች በዚህች ዓለም ውስጥ ስወናበድና ስንከራተት „…የከብቶች መብት“ ይባስ ብለው „የእነሱ መብት አለአንዳች ጥያቄ ይጠበቅ…ይከበር „ እዚህ አውሮፓ እዚያም አሜሪካም በሚባልበት ጊዜ ጥያቄው ዛሬ መነሳቱ እኛንም በአንድ በኩል አስደስቶናአል፣ በሌላ በኩል ዕውነቱን ለመናገር ግራ አጋብቶናል።

እሱ ብቻ አይደለም!

ሌሎች ሓሳቦችም ከዚሁ ጋር እዚህ ይሰማሉ።

F

„…ሰበአዊ መብትን አስመልክቶ – ግልጽ ለማድረግ- በመጽሓፍ ቅዱስ ላይ ምንም ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የተጻፈ ነገር አናገኝም።በእስላም ሃይማኖት ውስጥም ይህን ጉዳይ የሚያነሳ መልዕክት እንደዚሁ ፈልገን አናይም። ምን ጊዜም የትም ቦታ የሰበአዊ መብት መከበር ጉዳይ ላይ ላቲን አሜሪካ ይኖሩ በነበሩት በኢንካ ሥልጣኔ ዘመን ይህ ጥያቄ ትልቅ ሚና በምንም ዓይነት አልተጫወተም። እዚያው አካባቢ ሰፍረው በነበሩት በቶልቴክን ወይም በአስቴክን ወይም ደግሞ በጥንታዊ ግብጾች ሥልጣኔ ጊዜ ከእናካቴው በግልጽ ለመናገር በጥንታዊ ግሪኮችም አልፈን ሄደንም በሮማዉያኖችም ዘንድ ይህ የሰበአዊ መብት ጥያቄ የትም ቦታ እንደ ትልቅ ቁም ነገር ተቆጥሮ እንዲከበር አልተጠየቀም ።… ስለዚህ ሞስኮና ፔክንግ የተቀመጡትን የቻይና እና የሩሲያን መንግሥታትን መሪዎች -ይህን ቢያንስ ማለት እንችላለን – „ – ደር ሽፕግል የተባለው የጀርመኑ መጽሔት የቀድሞውን ቻንስለር ሔልሙት ሽሚትን ጠቅሶ እንደጻፈው[iv]– „በዚህ ሰበአዊ መብት መከበር አለበት በሚባለው አጉል ቀልድ እነሱን አናሰልቻቸው አናስጨንቃቸው ።“

ምን ዓይነት ዓለም ውስጥ ነው እኛ ለመሆኑ ያለነው? እነሱስ ነጮቹ ምንስ ዓይነት ሕይወት ውስጥ ነው የገቡት?… ይህን ለማለት ምን ነካቸው? ምን አሳሰባቸው?

ምንስ አቅብጦአቸው ነው? እንደዚህ ዓይነቱ የክርክር ውስጥና ደረጃ ላይ እነሱ የደርሱት? ለመሆኑ እኛንስ ምን ነካን? በዚህ አቀራረባቸውና አመለካከታቸው ለመሆኑ ምን ይህል ጥለውን ሄደዋል ?

በአንድ በኩል የከብቶችን ነጻነት! በሌላ በኩል በመጽሓፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁራን በግሪክ ፍልፍስና እና…በሌሎቹ ሥልጣኔዎች „…ሰበአዊ መብት የሚባል ነገር የለም…“ የሚባልበት ነገር?

እንደዚህ ዓይነቱን አሰተያየት በመስማታችንና በማየታችን እጅግ በጣም ተደንቀናል!

ጉዳዩን ዛሬ የምናነሳውም -ግልጽ ለመሆን – ለዚህና በነዚሁ ምክንያት ብቻ ነው።

G

በአውሮፓ ሆነ ወይም በሌላም ቦታና አካባቢ በዚህ ዓለም ስለ እንስሳና ስለ ከብት ስለ አውሬና ስለ አዕወፋት ስለ እነሱ መናገር የጀመረ አንድ ሰው ምንም ነገር ሳያነሳ ምንም እንዳልሆነና እንዳልተደረገ ዝም ብሎ አፉን ዘግቶና ይዞ ማለፍ የማይችለው ጉዳይ አለ።

እሱም እንናገር ከተባለ -እነሱ እንደሚሉት- ዝም ብሎ ማለፍም የማይችለው ዝም ተብሎ ሊያልፍም ቢሞክር የማይቻለው ነገር አለ።

እሱም እነሱ እንደጻፉት ብዙዎቹም የእንስሳት መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት – የሰው ልጆች በእንስሳትና በከብት በእነሱ ላይ እንደፈለጉት የሚያወርዱት በደል ከዚያም በላይ ደስ እንዳላቸው የሚጠቀሙት ኃይልና ጉልበት በመጨረሻም የሚያሳዩት „ጭካኔ ዝም ተብሎ አይታለፍም „ ባይ ናቸው።

ጸሓፊዎቹ እንደሚሉት (በመጀመሪያ ረጋ ለን እናዳምጣቸው) የሰው ልጆች የበላይነት ቦታ በዚህቺ ዓለም ላይ መያዝና መወሰን- ይህ ቀጥለን የምናነሳው ጉዳይ – አጠያያቂ ነው ባይ ናቸው።

እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ደግሞ በእንስሳ ላይ ብቻ ሳይሆን „ ሕግና ሥርዓት በሌለበት አካባቢም“ በሰው ልጆችም ላይ ሌሎች ሰዎች የሚደርጉት በደል እንደዚሁ ጎልቶ የሚታይ ጉዳይ ነው።

አንድ ሰው ሓብቱን ወይም ጠበንጃውን መከታ አድርጎ ወይም ወታደር አሰልፎ ወይም ደግሞ አስፈራሪና አጃቢ ደጋፊ ጋሻ ጃግሬዎቹን አሰልፎ በገዛ ወንድሙ ላይ ከሚያሳየው ባህሪ ጋእኩል በእንስሳት ላይ የሚወርደው ፍጅት -በእነሱ ዓይን – እነሱ እነደሚሉት አንድ ነው ባይ ናቸው።

እሱም ሌላ ነገር ሳይሆን ኃይልና ጉልበት ነው። ጸሓፊዎቹ ኃይልና ጉልበትን „በደካማ ፍጡሮች ላይ መጠቀም ይቁም“ ባይናቸው።

ሥልጣኑንም መከታ አድርጎ አንዱ በአንደኛው ላይ ኃይልና ጉልበቱን መከታ በማድረግ ያ ሰው የሚወስደው ኢሰበአዊ እርምጃ ደግሞ „ማን ፈቀደለት?“ የሚለውን ትልቁን የህግ -የሌጋሲ ጥያቄ ያስነሳል።

ይህን ጥያቄ ማንሳት ደግሞ በቀጥታ የፖለቲካ ፈላስፋዎች እንደሚሉት -የዚህዓለምን ችግር በትክክል ለመረዳት- ይጠቅማል።

በሌላ አነጋገር ብዙዎቹ እዚህ ተስማምተው እንደሚሉት በእንስሰና በከብቶች ላይ የሚወርደው የሚዘንበው ኃይልና ጉልበት ዱላና ድብደባ እሥራትና ሰንሰለት ሸክምና ጭካኔና ቆይቶም በአንዳንዱ ላይ በመጨረሻ የሚደርሰው የቢላ እርድ…ይህን ሁሉ -ጸሓፊዎቹ እነሱ እንደሚሉት እያዩ ሳይናገሩ ዝም ብሎ ዘሎ ማለፍ በሞራል ደረጃ እንደማይቻል በጻፉት ጽሑፎቻቸው ላይ እነሱ አንስተዋል።

ግን እንዲሚባለው ና እንደሚገመተው- አንዳንድ አንባቢም ሰው በዚህች ደቂቃ እየሳቃ እንደሚያስበውና እንደሚናገረው ከብዙ ቦታም እንደሚሰማው – አብዛኛዎቹ እላይ የተጠቀሱት ነጥቦችና ጥያቄዎች- ፈላስፋዎቹም ያነሱት ፍሬ ሐሳቦችም ዝም ተብለው የሚታለፉ ቀላል ጉዳዮችና ነገሮች አይደሉም።

H

በከብቶችና በእንስሳ ላይ ምን ማድርግ እንደሚቻል በሕግ ወይም በሃይማኖት ወይም በዘልማድ የተፈቀዱና የተከለከሉ-እንደምናውቀው ሕግጋትና ደንቦች አሉ።

አንዱ እንደ ጻፈውና ማንም አእምሮ ያለው ሰው እንደሚገምተው የጎረቤትን ዶሮ ሠርቆ ወይም ቀምቶ አርዶ በጀርመን አገር ሆነ ወይም በሌላ ቦታ መብላት ያስቀጣል።

እንደዚሁ የጎረቤትን ውሻን ወይም ድመቱን ጠልፎ ወስዶ ይዞ የእሱን ጆሮ ወይም ጭራውን ወይም ደግሞ እግሩን መቁረጥ ክልክል ስለሆነ ይህም ያስቀጣል።

ይህን ያደረገ ሰው እዚህ ሆነ ሌላ ቦታ ይቀጣል። ምናልባት እነደዚህ ዓይነቱ የከብት ስርቆት ድፍረት ሌላ ቦታ ጦር እሰከ ማማዘዝ ድረስም ያስኬዳል።

በሌላ በኩል ሕግ አውጪው እራሱ ዝም ብሎ አይቶ የሚያለፋቸውም ነገሮች አሉ።

በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ጀርመን አገር -እዚህ እንደተጻፈው-ከሚፈለፈሉት ከብዙ ሚሊዮን ጫጩቶች ውስጥ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉትን ወንድ ጫጩቶች ከሴቶቹ ለይቶ ለቅሞ እነሱን (እንቁላል ስለማይጥሉ ወይም እነሱ ቶሎ እንቁላል በየቀኑ እየጣሉ በቀላሉ ሰለማይደልቡ )በመርዝ ጢስ መፍጀት የዶሮ አርቢ ከበርቴውንም ገበሬውንም ይህን በማድረጉ ፈጽሞ አያስቀጣውም።

የድመት ግልገሎችንም ሰብስቦ ወሃ ውስጥ ዘፍቆ መግደል በሕግ ይህ እርምጃ እንደወንጀል ታይቶ ሰውዬውን ወይም ሴትዮዋን አያስቀጣም። በሌላ ቋንቋ ይፈቀዳል።

አይጦችን በመርዝ አሳዶ እነሱን በየጊዜው የማይፈጅ ወሃ አጠራቃሚና ወሃ አቅራቢ ድርጅትና ግለሰብ እሱ ደግሞ ኃላፊነቱን አልተወጣም ተብሎ ተከሶ በሌላ በኩል በአገሪቱ ሕግ ይቀጣል።

እንደዚህ ዓይነቱን እርምጃና ኃይል ጉልበት መጠቀም በሠለጠነው ዓለም የግድ (ዲክታተሮች የማንንም ፈቃድ የፓርላማን አባሎች ውሳኔ እንኳን አይጠብቁም) ሌጋሲውን ይህን የሚፈቅድለት ልዩ – ፈቃድ ከተሰየመው ክፍል ማግኘት ይኖርበታል።

በቅርቡ እዚሁ ጀርመን አገር „…አደራ የተሰጠህን የሰው ውሻ በመስኮት ወርውረህ ገድለኻል“ ተብሎ አንድ ሰው ፍርድ ቤት ተከሶ ቀርቦ -አቃቤ ሕጉ የስድስት ወር እሥራት ጠይቆአል- ሰውዬው ተሟግቶ ከስድስት ወር እሥራት እንደምንም ብሎ ሊያመልጥ ችሎአል።

„…አብሮ ለሚኖር ለማንም የአገሪቱ ዜጋ“ እነሱ -በዚህ አቀራረባቸው ማንኛውንም ተንቀሳቃሽ ፍጡር ይጨምሩበታል ይህ ነው እኛንም ነገሩን እንድናነሳ የገፋፋን- „ …በሰላም በዚህች ምድር ላይ ለመኖር የሚገባውንም መብቱን ለእያንዳንዱ – ለጋማና ለቀንድ ከብት ለሚጋልቡት ፈረስ፣ ለልጆቻቸው ለሸለሙት እንስሳ ጭምር አለ ገደብ መብታቸው ይከበር “ የሚለውን ጥያቄ ሌሎቹ ፈላስፋዎች እንደ Peter Carruthers ያሉ ሰዎች ከብቶች እንደ ሰው ልጆች አርቆ ማሰብና ለመጪና ለወደፊቱ ጊዜያቶችና ችግሮች ፕላን አውጥተው እቅዶች ዘርግተው አንዳች ነገር በዚህች ዓለም ላይ መሥራት ስለማይችሉ ይህ „የእኩልነት መብት ይሰጣቸው“ የሚባለው ነገር ቦታ የለውም ባይ ናቸው። ያም ሆኖ በእነሱ ላይ የሚካሄደውን ጭካኔ ይቃወማሉ።

I

የት ሊወስዱን ፈልገው ነው ? ምን እኛ የማናውቀውን ነገር ሊያስተምሩን አስበው ነው ይህን የመሰለ ጉዳይ አሁን የሚያነሱት?… ቅንጦት ነው ወይስ ጥጋብ ? ለመሆኑ ይህን…የእንስሳን መብት ማወቅ ከአልጠፋ ነገር በአሁኑ ዘመን ማንሳት ተገቢ ጥያቄ ነው? ወይስ አይደለም?…ሥራ ከመፍታት የመጣ ፍልስፍና ነው ወይስ…ሊቀልዱብን ?

ይህንንና ይህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን መጽሓፉን ፈጽሞ ያላገላበጠ ሰው በስህተት እንዲወረውር የተነሱት ጉዳዮቹ ሊገፋፉት ይችላሉ።

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እዚህ ጀርመን አገር ታትመው ገበያ ላይ የወጡት ሦስቱ መጻሕፍቶች በበርካታ ቃለ-ምልልሶችና አስተያቶችም በጋዜጣና በቴሌቪዥንና በራዲዮም ሪፖርታጅ ተደግፈውና ታጅበው የሰሚን ጆሮም አስደንቀዋል።

አንዱ አዳኝ „እኔ መኖር እፈልጋለሁ። በጥይት መትቼ ገድዬ ጫካ ውስጥ የጣልኩትን የዱር እንስሳ ማታ ጠብሼ ስበላው ደግሞ ይህ ተፈጥሮ ነው ደስ ይለኛል።“ ሲል አንድ አታክልት ብቻ የሚበላ ሰው ደግሞ „የሰው ልጆች አውሬነት አይገባኝም…“ ብሎ ለአዳኙ ዓይነት ሰው መልሱን ጭንቅላቱን በመነቅነቅ ሰጥቶአል።

መስመር የለቀቀ ውይይት የተከፈተ ይመስላል።

አንዳንዱ በሃይማኖቱ -ሕንድን ወይም ኢትዮጵያን ውሰድ- ሌላው በተፈጥሮው የተወሰነ ነገር ይበላል።የተቀረው ተጠይፎም ይሁን ነፍስ ያለው ነገር አልበላም ብሎ ከነገሩ ይርቃል።

እነዚህ ጸሓፊዎቹ የወሰዱትና የሚከተሉት ፍልስፍና የወንድማማችነት የአብሮ አንዱ አንዱን ሳይበላ በሰላም ጉርብትና ላይ የተመሰረተ የፍቅር ኤቲክን ነው። ከዚያም አልፎ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከብቶችን ማራባት ማደለብ በጫጩቶቹ ላይ እንዳየነው እነሱ አያስፈልጉም ብሎ በመርዝ ጢስ መፍጀት ከእንደዚህ ዓይነቱ እርምጃ እንቆጠብ የሚለውንም ትችት ጽሑፎቻቸው ያነሳል።

ወተት አንጠጣም አይብ አንብላም እንቁላል አንነካም ሌለው ቀርቶ ከበግና ፍየል ጸጉር የተሰራ ሹራብ አንለብስም የሚሉም አሉ።

አርዕሰቱ የጋማና የቀንድ ከብቶች የአዕዋፍና የዶሮ የውሻና የድመት መብት-እነሱ የጎረቤት ዜጋ መብት የሚሉት ጥያቄ- የዚህ የፍልስፍና አቅጣጫዎች አለ ጥርጥር ብዙ ያነጋግራል።

የበለጠ የሚነጋግረው ለጥቁር አፍሪካ „ ሰበአዊና ዲሞክራሲያው መብቶቹ ገና እዚያ ላይ እነሱ ሰለአልደረሱ በአዳር ይያዝ „ የሚለው ጉዳይ ነው።

J

„መጽሓፍ ቅዱስ ስለ ሰበአዊ መብት አይናገርም። ቅዱስ ቁራን ይህን አያነሳም። በጥንታዊ ግሪክና በሮም ሥልጣኔ ስለ ሰበአዊ መብቶች ጉዳይ አልተነሳም። ፈርኦኖች አያውቁም ላቲናች አይቀበሉም….ስለዚህ እነዚህን የአፍሪካና የእስያ መንግሥታት በዚህ ጥያቄ አክብሩ ብለን አንወትውታቸው …..“ ወዘተረፈ የሚባለው ነገር ላይ ላዩን ሲያዩት „ትክክለኛ „ አነጋገር ይመስላ። ጠጋ ብለው ታሪኮቹን ሲያገላብጡት በቀላሉ የሐሰት ፕሮፓጋንድ እንደሆነ አንድ ሰው መረዳት ይችላል።

በአዲስ ክዳን ላይ የተጻፉትን የክርስቶስን ትምህርቶች የሓዋሪያትን-በተለይ የጳውሎስን- መልዕክቶች የተከታተለ ሰው እዚያ ላይ ስለ ነጻነትን ስለ አርነት ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለቅሞ ማግኘት ይችላል። እንዲያውም የሮም መንግሥት የወደቀበት አንደኛው ምክንያት በክርስቶስ ትምህርት ነው።

የአቴን ዲሞክራሲ ባይኖር ኖሮ (ያኔ ደግሞ እንዱስትሪም አልነበረም) አውሮፓና አሜሪካ የዲሞክራሲ ሥርዓት ምን እንደሚመስል በቀላሉ በአልተገነዘቡ ነበር። እራሱ ብሉይ ኪዳን (ባርነትንም ይፈቅዳል) ስለ „መልካም አስተዳደር“ ያነሳል።

ሐሳባችን እንሰብስበውና እንዝጋው ። አለአቴን ፍልስፍና አለ ሮም ሕግጋት አለ ክርስትና ትምህርት አለ የብርሃን ዕውቀት:-ኢንላይትመንት[v]

አውሮፓ የዛሬውን አውሮፓ ባልሆነች ነበር። አገር ያጠፋው ትምህርት ዲሞክራሲ አይደለም። አገራችን ዘልቆ የገባው የስታሊን ትምህርት እንጂ።

እርግጥ ቤተ ክርስቲያናችን „ባርነትን በመጥፋት ላይ“ ብታተኩሩ ኢትዮጵያ ገና ዱሮ የትና የት በደረሰች ነበር።

የሰው ልጆች ሥልጣኔ የተጀመረው በከብትና በቤት እንስሳ እርባታና በእነሱ ላይ በተጣለው ሞፈርና ቀንበር ነው። ውጤቱ የጤፍ ና የስንዴ የ…እርሻ ነው። ጋንዲ “አንድን ሕብረተሰብ የምትረዳው በከብቶቹ ላይ የሚያሰየውን ባህሪ በደንብ ከተመለከትክ በሁዋላ ነው።”

—–

ተፈሪ መኮንን

———


[i] Hilal Sezgin (Artgerecht ist nur die Freiheit. Eine Ethik für Tiere 301 Seiten.16,95 €)

[ii] Sue Donaldson & Will Kymlicka: Zoopolis A poltical Theory of Animal Kingdom ,Eine poltische Theorie der Tierrechte 608 pages 36€

[iii] Friederike Schmitz :Tierethik 589 Seiten 24 €

[iv] Der Spiegel Nr.51 16.12.13 on Helmuth Schmidt

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s