ቀ.ኃ. ሥ. “የመጨረሻው የአፍሪቃ ንጉሠ-ነገሥት”

HSI-Book-review

ቀ. ኃ. ሥ.

“የመጨረሻው የአፍሪቃ ንጉሠ-ነገሥት”

ወደ ማምሻው ላይ በአይሮፕላን ጣቢያው አካባቢ ግርግር ይታይ ነበር። ሁሉም እዚያ ቦታ የካኪ ኮትና የቡሽ ባርኔጣ ስለደፉ ማን ምን እንደሆነ ለማወቅና ለመለየት ያስቸግራል።
ሦስት አራት ሰዎች ከወታደር መኪና ላይ ዘለው ወርደው ታጅበው ወደ እንግዳ ማረፊያው ክፍል ዘልቀው ይገባሉ። ከጥቂት ደቂቃ በፊት መኪናው ኬላውን ሲያቋርጥ ሚስተር ስሚዝ የሚባል መታወቂያ ወረቀት አንድ ወታደር አገላብጦ አይቶ መልሶላቸዋል።
ስሚዝ በእንግሊዝ አገር ጥቂት አመታት ያሳለፈ አንድ ትልቅ ሰው ነው።
ከእንግሊዝ አገር ከአንዱ የአየር ኃይል አይሮፕላን ጣቢያ ማምሻውን ተነስቶ ሌሊቱን በፈረንሣይ አገር ላይ በሮ ማልታ የምትባለው ደሴት ላይ ያረፈው የጦር አይሮፕላን ሚሰተር ስሚዝን ይዞአል።

ስሚዝን አጅበው ሦስት ኢትዮጵያኖች አብረው ከእንግሊዝ አገር ተነስተዋል።
የሐረሩ መሥፍን ልዑል መኮንን አንደኛው ናቸው። ጸሓፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ እና እንዲሁም አማካሪአቸው ብላታ ሎሬንሶ ከአጃቢዎቹ መካከል ይገኙበታል።


ባሕር ላይ ማረፍ በምትችለው አይሮፕላን ከንፈው አራቱም ካይሮ በተከታዩ ቀን ይገባሉ።ከካይሮ ወደ ሱዳን ከሱዳን ወደ ጎጃም ወደ ኦሜድላ ሜዳ ከዚያም ዘልቀው ቀስ እያሉ ወደ መሓል አገር ይደርሳሉ።
መንገድ ላይ ብዙ ነገር ያጋጥማቸዋል። …ይህንና ይህን የመሰሉ ማስረጃዎችን ሰብስቦ እዚህ የሚተርክልን ጀርመን አገር በቅርቡ ታትሞ የወጣው የዶክተር ልጅ አስፋ ወሰን አሥራተ መጽሓፍ ነው።
ሚስተር ስሚዝ የአጼ ኃይለ ሥላሴ የሽፋን ስም መሆኑን- መቼም ይህን ስሚዝ የሚባለው ነገር ያመጡት እነቸርችርል መሆን አለባቸው- አንባቢው የሚረዳው ቢያንስ አንድ መቶ ሰማንያ ገጽ ከአገላበጠ በሁዋላ ነው።


ከዚያ በፊትና ከዚያ በሁዋላ ያለው የንጉሠ ነገሥቱ ታሪክ እሳቸው ያሳለፉት ውጣ ውረድ የተቀበሉት ፈተናና መከራ -ሌሎቹም ጽፈውታል- ቀላል አይደለም።


የልጅ አሥራተን መጽሓፍ ልዩ የሚያደርገው ወደ መጨረሻው ላይ አንስተው የሚተርኩልን ጉዳዮች ናቸው። „…ባዶ ነበር !“ የሚለውን ቃል ጸሓፊው ወርውረዋል።

ምኑ ነበር ባዶ?


ልጅ አስፋ ወስን „የመጨረሻው የአፍሪካ ንጉሠ ነገሥት „ ብለው ሰይመው ያወጡት መጽሓፍ የንጉሠ-ነገሥቱን እርምጃ በተለይ ከእነ መንግሥቱና ከእነ ገርማሜ ነዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ በሁዋላ ሥርዓቱን ለማሻሻል ምንም ዓይነት የለውጥ እርምጃ በአለመውሰዳቸው እሳቸውን ይተቻቸዋል።
ግን ደግሞ እንደ እሳቸው እንደ አጼ ኃይለ ሥላሴ “በፎርቱና” -በአልታሰቡ ግሩም ዕድሎች የታደሉ መሪ በአገራችን በቅለው እነዳልነበሩ-አለጥርጥር ንጉሡ ዕድለኛ ነበሩ- ከሕይወት ታሪካቸው በደንብ ማንበብ ይቻላል።
ፎርቱና! ትቀርባቸዋለች። ይህቺም ዕድል ትወዳቸዋለች። ይህቺም ዕድል ትሸሻቸዋለች።… ከጥይት በተአምር አምልጠዋል። ወሃ ሊበላቸው ሲል ሌሎቹ ነፍሳቸውን ሰውተውላቸው እሳቸው ተረፈዋል። ዘጠኝ ወይም አሥር የሚደርሱ ወንድሞቻቸው/ እህቶቻቸው ሲሞቱ እሳቸው ብቻቸውን ተርፈው ዙፋኑን ጨብጠዋል።

…ከልጅ ወደ ደጃዠማችነት ከዚያ ወደ ራስና ልዑል ራስ ከዚያም የጎንደር ንጉሥ አልጋ ወራሽና ትንሽ ቆይተው በሁዋላ ንጉሠ-ነገሥትም ሁነዋል።
ይህቺ ፎርቱና ስትከዳቸው „ቀልባቸው ተገፎ ትከሻቸው ወድቆ አንገታቸውን ደፍተው ምስኪን መስለው ለመሄድም ተገደዋል።“

በስደት ላይ ገንዘብ አጥተው ንብረታቸውንና የምግብ ማቅረቢያ ሳህናቸውንና ሹካቸውን ሳይቀር ለመሸጥ ተገደዋል። መቸገራቸውን ያየ አንድ ኩባንያ „ …ፊልም በአንድ መቶ ሺህ ዶላር እንዲጫወቱም „ ጠይቆአቸዋል።

እሳቸውም (የቻይናው “የመጨረሻ ንጉሠ-ነገሥት” መቀለጃ ሁኖ ፊልም ሲጫወት በየመዝናኛ መሸታ ቤት ለጃፓኖች ሲዘፍን …) አላደርገውም ብለው እምቢ ብለዋል።
ይህቺ ለጥቂት አመታት የተደበቀችባቸው ፎርቱና -እሳቸው ይህን የሰማይ መላዕክት የምድር ሠራዊት በአላወቀበትና በአልገመተበት ሰዓት ብለው ይተረጉሙታል- እንደገና ብቅ ብላ ፈልጋ ትክሳቸዋለች።
የሁለተኛ ዓለም ጦርነት በአፍሪካ ሌላ መልክ ይይዛል ። ረስቶአቸው የነበረው ጎበዙ ዊኒስተን ቸርችርልም ያኔ -ይህ የአውሮፓ ሊበርቲና የጸረ- አምባገነኖች አርቺቴክት- የአጼ ኃይለሥላሴን ሚና መምጣቱን ይረዳል።
ብድግ ብለው “ስሚዝ” ተብለው ይመለሳሉ።

አገሪቱን ከውጭ ኃይል መንጋጋም ያወጣሉ።

ከዚያ በፊት በስንት ተአምር አልጋ ወራሽ እንደሆኑና ሌሎችን “ተቀናቃኞቻቸውን” በፖለቲካ ጥበብና ብልሃት ከጨዋታ ውጭ እንደ አደረጉ መጽሓፉን ማገላበጥ ይጠቅማል።

ከስደት ተመልሰው ትምህርትን አስፋፍተዋል። ለጥበብና ዕውቀት ቅድሚያ ሰጥተዋል። የጦር ሠራዊቱን ገንብተዋል። ይኸው ሠራዊት/ሠራዊታቸው ከድቶአቸው ተነስቶባቸዋል።

አጼ ኃይለ ሥላሴ ግን „… አባቴ እግራቸው ላይ ወድቀው ሥልጣኑን ለአልጋ ወራሹ ይስጡ ቢሉአቸው እምቢ…አሉ“ የሚለውንም ሁኔታ ልጅ አስፋ ወሰን አንሰተዋል። በዚህ ጥያቄ ላይም በርካታ ባይባል አንዳንድ ሰዎች ጽፈዋል።

እንደ ታላቁዋ ብርታኒያ እንደ ስዊዲንና እንደ ዴንማርክ ስፔን እነደ …ልንሆን እንችል ነበር? ለምን አይቻልም?


በአርግጥ ፓርላማውን አሻሽለውና ሥልጣኑን አሳልፈው ሰጥተው ( በ1924 እ.አ.እ. የተመሰረተ በአፍሪካ የመጀመሪያው ፓርላማ ነው) ከእሱ ጋር ሳንሱርን አንስተው የፕሬስ ነጻነትን ንጉሡ አብረው ቢያውጁልን ኑሮ ያቺ አገር „:..ኮሚኒዝም ማርክሲዝም… ደርግና ሶሻሊዝም …የጠበንጃ ትግልና…መገንጠል…. ነጻ አወጪ ወይም ….የላብ አደሩ አምባገነን መንግሥት…“ ከሚባለው / ከሚባሉት ቅዠቶች አምልጣ አሁን ያለችበት ሁኔታ ውስጥ በአልገባችም ነበር።


ምን ይደረጋል- እንደ ገና ፎርቱና ንጉሡን ትክዳለች። ወይስ „…ደርግ የሚባለው ፍጡር የሚሽከረክርበት አድማና አላማ ሌላ ዕድል ያመጣልኛል… „ ብለው ንጉሱ አስበው ይሆን? …ወይስ እንደ ሚባለው ዕድሜ ተጫጭኖአቸው ደክመው ?

ወይስ ብልሃቱ ጠፍቶአቸው? ወይስ ከእኔ በሁዋላ ሰርዶ አይብቀል ብለው? ወይም ደግሞ እስቲ ቅመሱአትና ተቀጡ! ይህ አይታወቅም።
ግን ጊዜው የእሳቸው አልነበረም።ይመስላል እንጂ ጊዜው አሁንም ድሮም የተማሪዎችም የወታደሮችም አልነበረም። እንዲያው ሙከራ ተደረገ እንጂ ጊዜው የሶሻሊዝምና የኮሚኒቶቹም አልነበረም።

ጊዜው አሁንም ሆነ ዱሮም „የነጻ- አውጪዎችም „ አይደለም።


የልጅ አስፋ ወስን መጽሓፍ ከሦስት ሺህ አመት በላይ የኖረው የአገሪቱ ምልክት „ዘውዱ“ በንጉሠ ነገሥቱ „ግትርነት ወደቀ „ በተዘዋዋሪ ይላሉ።

ለምን ግን መሣፍንቱና መኳንንቱ ተሰብስቦ መላ- አንድ ሁለት ሦስት አራት አማረጮች… ብሎ እንዳልመታ? ለመረዳት ያስቸግራል። “ታማኝነትና …ባዶ ነበር” የሚሉ አረፍተ ነገሮች ገጹ ላይ ተወርውረዋል። ማለት የሚቻለው ሁሉም ተያይዞ ቦታውን ለአዲስ ተወናዋኒያኖች አስረክቦ ተሰናብቶአል። ማነው አዲሱ ተወናዋይ?

መጽሓፉን የታሪክ ምሁሩ „…መጪው ትውልድ የንጉሡን ሥራ ከአሁኑ (ትውልድ) በተሻለ ዓይን አይቶ ፍርዱን ይሰጣል።“ ብለው ትረካቸውን በዚህቺ አረፍተ ነገር ይዘጋሉ።
„…እረኛውን-ማለት መሪውን አናቱን ብለህ ጣለው ከዚያ በሁዋላ በጎቹ ይበተናሉ።“ የተባለው አነጋገር በኢትዮጵያ ደርሶአል።


ለአገሪቱ ጥፋት ተጠያቂው ግን በእኔ ግምት አንድ ሰው ብቻ አይደለም። ተጠያቂዎቹ ብዙ ናቸው። እሱ ደግሞ ሌላ ቦታ ይወስደናል።

ማለት የሚቻለው ነገር ንጉሠ -ነገሥቱ ይህቺን አገር እኛን ጭምር ከብዙ መንጋጋዎች አውጥተውናል። ትምህርት ሰጥተውን “ከጨለማ ኑሮ”…ከፋሽሽትና ከቅኝ ገዢዎች ቀንበር አላቀውናል።.. ከሥልጣኔና ከዘመናዊ ሕይወት ጋር በትንሹም ከግለሰብ ከዜጋ ነጻነትና ፍርድና ፍትሕ ጋርም አለ ጥርጥር በደንብ አስተዋዉቀውናል። ነጻ-ሓሳብ እና የሕግ በላይነት የምንለውም ከዚያ ዘመን የመጣ አመለካከት ነው።

ያምሆኖ ሊበራል ጭንቅላትና ሪፓብሊካን ዲሞክራቶች በዚያች ምድር በገፍ መወለድ ሲገባቸው በእነሱ ፋንታ “ቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ ያላቸው አምባገነን ሥርዓት” የሚሉ ወታደሮቸም ነጻ አውጪ ተማሪዎችም ብቅ ብለው ሜዳውን መያዙ በጣም ያሳዝናል።

ታሪክ ጸሓፊው ልጅ አስፋ ወስን አሥራተ” መጪው ትውልድለየት ያለ ፍርድ ይሰጥ ይሆናል…” ብለው ለመድገም ትረካቸውን ዘግተዋል። ጸሓፊው ሞናርኪስት ሳይሆኑ ሪፓብሊካን መሆናቸውን በተዘዋዋሪ ገልጸዋል። ወይስ ?

….

መጽሓፉ በእንግሊዘኛ ና በአማርኛ እንደሚተረጎም ጸሓፊው ለደቸ ቬለ ሰሞኑን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ አንስተዋል። መልካም ነው። በተለይም ሰፋ ያለው ወጣቱ ትውልድ አንብቦት ከትውልድ ሀገሩ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጋር በሚያመዛዝን አእምሮ ቢተዋወቅና፣ ቢነጋገርበት ደግ ነው። ብዙ የአውሬ መንጋጋ አድፍጦና አሰፍስፎ ሊቦጫጭቀን በዝግጅት ላይ የሚገኝበት ዘመን ነው። በየት እንደሚመጡብን መገመት እንጂ ምኑም አይታወቅም። በፎርቱና- በዕድል ላይ ብቻ የተገነባ ፖለቲካ መጨረሻው አያምርም።

ፖለቲካ ሌላ ዕውቀቶችን ያጠቃልላል።

ለ አእምሮ ሰኔ 2006 / June 2014/ እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 10

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s