የአፍሪቃው የፖለቲካ እንቆቅልሽ / ርዕስ አንቀጽ

አሁንም በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ያልተፈታው

ትልቁ የአፍሪቃ የፖለቲካ እንቆቅልሽ

ነጻነት ወይስ ባርነት ?


ለጥቂት ደቂቃ ለአንድ ሰከንድ ስለ የባህር በርና ስለ አሰብ ስለ ኤርትራም መገንጠል እንርሣ። ስለ ገዳ ሥርዓትና ስለ ኦሮሞ ጉዳይ ስለ ኦጋዴን ልጆች ጥያቄ በአጠቃላይ ከሩሲያ ተነስቶ ኢትዮጵያ ስለ ገባው „ስለ ብሔር/ብሔረሰብ መብት እሰከ መገንጠል ድረስ…“ ስለ እሱም የስታሊንን ድረሰት ማሰብ ለጊዜው ለትንሽ ደቂቃ እናቁም።
ትልቁ የአፍሪቃ እንቆቅልሽ ከባድ ይመስላል እንጅ አንዲት በጣም ትንሽ ነገር ናት።


ሳይታወቀን ግን ይህን ነገር ደህና ነው ብለን ተሸክመነው ስንከራተት ከርመናል። ብዙዎቹ ሕይወታቸውን እሰከ መሰዋት ድረስ ሄደዋል። ሌሎቹ ሐብታቸውን የተቀሩት ጉልበታቸውን አብዛኛው ጊዜአቸውን በእሱ ላይ አሳልፈዋል።


ይህ „ነጻነት“ አንድ ቀን ይመጣል ብለው ሁሉም ተስፋ አድርገው ነበር። ፋታ ስለማይሰጠው ስለ ዳቦና እንጀራ ጥያቄ (ይህን ማንሳቱን የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ረስቶታል) ስለ የሥራ ዕድልና የጡረታ ገንዘብ ስለ ሕክምናና ስለ ጤና ጉዳዮች ለጊዜው እነሱንም ወደ ጎን እንተው።

በእነሱ ፋንታ ስለ ሥልጣን አያያዝና ሥልጣን ላይ መውጣት ሥልጣንም ላይ መሰንበትና ከእሱም አልወርድም ማለት ምን እንደሆነ እናሰላስል።

*

ጊዜውን በደንብ ማስታወስ ያስቸግራል እንጂ ይህን ዛሬ ሳነሳ አንድ ሁኔታ ትዝ ይለኛል።

በአንዱ የጥቅምት ሃያ ሦስት „የዘውድ በዓል ቀን“ አጼ ኃይለ ሥላሴ በዚያ በአንዱ በቀዩ ሮልስ ግልጽ መኪናቸው ውስጥ ከእቴጌይቱ ጋር ተቀምጠው በነጫጭ ፈረሶችና የደመቀ ልብስ በለበሱ ፈረሰኞች ታጅበው ሲሄዱ መንገድ ዳር የሰማሁት ነገር አሁን ስለ ሥልጣን በማነሳበት ሰዓት – አይረሳምና- እንደገና በአእምሮዬ ብቅ ይላል።

በእጅ መኪናውን መንካት ነው እንጂ የሚቀረው በዚያ ጠባብ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎዳና (ንጉሡ አይፈሩም) ክቡራን ልዑላንና ልዕልቶች የአገሪቱን ትላልቅ መሣፍንቶችን መኳንንቶች የጦር ጄነራሎችና ሚኒስትሮች የፓርላማ አባሎችና አገረ ገዢዎች…በአጠገባችን ሲያልፉ የሚቀልጠው እልልታ የሚሰማው ጭብጨባና ሁካታ ለንጉሡ „ታቦት“ የወጣ ይመስላል።

ለጥ ብለው እጅ የሚነሱ አሉ። የጠቅል አሽከር ብለው የሚፎክሩ።…ዕድሜህን ያርዝመው ብለው የሚመርቁ።
በዚያ ትርምስ የካበው ቀለም ዓይን ይስባል የልዕልቶቹ የአልማዝ አክሊል ይማርካል አንዲት ትንሽ ልጅ እዚያ መንገዱ ላይ በሚታየው ግርግርና ተአምር በዚያ ትርምስ በውበቱም ተደንቃ የእናቱዋን ቀሚስ ጎትታ „…ለእኔም አንድ ቀን አንደዚህ ይደረግልኛል?… እኔም እንደነሱ መሆን እፈልጋለሁ…አይደለም እማዬ…እማዬ!“ ስትል እንደ እስዋ እንደ እህቱ የፈነደቀው ታናሽ ወንድሙዋ ቀበል አድርጎ „…እኔ ግን እነደዚያ ሰውዬ -ንጉሡን እያሳየ – በትልቁ መኪና ውስጥ ተቀምጬ መሄድ እፈልጋለሁ…“ሲል አባትዬው ደንግጦ „…ዝም በል! ቀዥቃዣ…“ ብሎ ሲቆጣው ልጁ -ጥፋቱ ስለ አልገባው ማልቀስ ጀመረ።

ይህን ሰምተው ፈገግ ያሉ አርበኞች አጠገቤ ነበሩ። እናቱ እጅ ላይ ሁኖ -እንዳያለቅስ አባብለው- ይህ ልጅ ትርምሱን ዓይኑን ከፍቶ መከታተሉን ቀጠለበት።

ይህን ያለፈ ገጠመኝ እኔ እዚህ የማነሳው፣ አንዳንዱ ቸኩሎ ስም እንደሚያወጣው፣ የለፈው ስርዓትና ወግ ናፍቆኝ ሳይሆን፣ ስረ መሰረት ያለው ጉዳይ ላይ አእምሮዋችንን ለማሳረፍ እንድንችል ያህል ነው!

ስለ ትልቁ የዛሬው የአፍሪቃ እንቆ ቅልሽ፤ ስለ ሥልጣን አያያዝና ሥልጣን ላይ መውጣት፣ ሥልጣንም ላይ መሰንበትና ከእሱም አልወርድም ማለት ምን እንደሆነ እንድናስብ እንድንመረምር ነው።


ያ ልጅ ምን ታይቶት ይሆን? ይህ የልጆች ምኞት ከየት መጣ?… ይህ ብዙው ሰው የሚመኘው ግን ለመናገር የሚከብደው „የሥልጣን ጥማት“ ምንድነው? …ይህንንስ ለማሰብ ከጀርባው የሚገፋፋው ምክንያት ምንድነው?

ወጣቱ ቦካሣ፣ ተማሪው ሙጋቤ በሁዋላ ወታደር የሆነው መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ኢሳያስ አፈወርቂ እና መለሰ ዜናዊ ወይም ጆን ኤፍ ኬነዲና ቶማስ ጄፈርሰን ወይም ሙሴ ወይም ደግሞ በግ ጠባቂው (ንጉሥ) ዳዊት ማኦ ሴቱንግ ስታሊንና ሒትለር ካስትሮና ኬንያታ ማንዴላና ሑፌት ቧኜ…እነ አንጌላ ሜርክልና እነ ማርግሬት ቴቸርና ደጃች ተፈሪ መኮንን እና አጤ ቴዎድርስ ናፖሊዮንና… ሌሎቹ በልጅነት ዘመናቸው እላይ እንደተጠቀሱት ሁለቱ ልጆች „ሥልጣንን ተመኝተው የእናታቸውን ቀሚስ ይጎትቱ አይጎትቱ -ተጽፎ የተላለፈልን ነገር ስለ ሌለ ምንም የምናውቀው ነገር የለም።

በደንብ የምናውቀው ነገር ቢኖር እነዚህ እላይ ዝም ተብሎ ስማቸው የተጠቀሰ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መንገዶችና ዘዴዎች… ሥልጣን ላይ ወጥተው „ሥራቸውን ሰርተው“ አልፈዋል። ጥቂቶቹ አሁንም ሥልጣን ላይ ናቸው።
አንዳንዱ ለረዥም አመታት ገዝቶአል።

ሌላው ለጥቂት አመታት ኃላፊነቱን ተቀብሎ መልሶ ሥልጣኑን ለሕዝቡ አስረክቦአል። አብዛኛው በሰላም በምርጫ ተሸንፎ ተተኪውን ጨብጦ ጠረጴዛውን በገዛ ፈቃዱ ጠርጎ ወንበሩንና የቢሮ ቁልፉን ለተከታዩ ሰጥቶአል።
ሌላው አምባገነን የሚጠረጥራቸውን „ተቀናቃኞቹን“ ፈጅቶ አልለቅም ብሎ ተቀምጦአል።

ማናቸው እነዚህ የተለያዩ የሥልጣን ሰዎች? ምንድናቸው እነዚህ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች? ምን ዓይነት የፖለቲካ ዓላማ ነው የሚከተሉት? ድርጅታቸው የተገነባበት የርዕዮተ- ዓለሙ ሕንጻቸው ምን ይመስላል? ተከታዮቻቸውስ ምን ያስባሉ? እነሱን መቆጣጠር ይቻላል ወይ? ይህ ከሆነስ…እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?

እነዚያ ሁለቱ ልጆች „አንዱ ንጉሥ አንደኛዋ ንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ለመሆን…“ ገና አፍንጫቸውን ሳያብሱ የተመኙት ሚጢጢዎች በዚያ ሓሳባቸው የት እንደ ደረሱ አይታወቅም።

ምናልባት ኢህአፓና መኢሶን በሚባለው የተማሪዎች ክፍፍል ውስጥ ገብተው እነሱም ተከፋፍለው በባዶ ሜዳ ተናንቀው ይሆናል። ወይም አንዱ ኤርትራ ሄዶ ሌላው አዲስ አበባ ቀርቶ ይሆን?። ወይ ሁለቱም በስደት ላይ ናቸው?…ወይስ አንዱ የአባቱን ዘር ሌላው የእናቱን ወገን መርጦ ይሆን? ደርግ ጨርሶአቸውስ ቢሆን?…
በአለፈው እትማችን ስለ „ፖለቲካ እንደ ሙያ“ ስናነሳ ስለ ሦስት „የአስተዳደር ሥርዓቶች „ አንስተን – ሲውርድ ሲዋረድ ስለመጣው የዘውድ ውርሰ መንግሥት ትራዲሽና ሥርዓት ተርከናል።

በሕግ ላይ የተመሰረተ ራሽናል የሚባለውን በሁለተኛ ደረጃ ጠቅሰን ስለ ሦስተኛው „ጊዜ የሚወልደው ጊዜ የወለደው ባለ ግርማ ሞገሱ የታምራተኛው የካርስማቲክ ሰው ሥርዓትና አስተዳደር (ይህ የሃይማኖት መሪዎችን ነቢዮችንም ይጠቀልላ)- የጀርመኑን ማክስ ቬበርን ጥናትና አተናተን ተመልክተን እሱንም ተከትለን ስለ እነሱ ስለ ሦስቱ ሥርዓቶች ከብዙ በጥቂቱ እቅርበናል።

ዞሮ ዞሮ ሁሉም ሥርዓት በሕዝቡ ዘንድ „ተቀባይነት ሌጂትሜስ „ እንዲኖረው የግድ ያስፈልጋል። ተቀባይነት የሌለው „አስተዳደር“ ደግሞ ታሪክ እንደሚያሳየውና እንደሚያስተምረው መጨረሻው ያው የማይቀርለት ውድቀት ነው።

በአፍሪካ የምናየው የፖለቲካ እንቆቅልሽ አባት ለልጁ- ኮንጎን የካቢላን ሥራ ተመልከት- ሥልጣኑን በቀጥታ እንደ ዘውድ አገዛዝ የሚያወርስበት አካባቢና ቦታ ሁኖአል።
ሌላም አዲስና አዳዲስ ነገሮች ቢያንስ ከሃያ አመት ወዲህ ብቅ ብሎአል። እሱም„የነጻነትና የባርነት“ ትክክለኛ ትርጉሙ ተምታቶና ተቀያይሮ „ባርነት“ ማለት በአንድ ፓርቲ አምባገነን አገዛዝ ሥር እየተሰቃዩ መኖር እንደ „ነጻነት“ ተቆጥሮአል።

ለሰበአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ለእነሱም በሥራ ላይ እንዲውሉ መጠየቅና ለዜጋ ነጻነት ድምጽን ማሰማት ደግሞ እነደ “ወንጄል“ ተቆጥሮ የሚያስከስስ የሚያስወነጅል አህጉር ሁኖአል።
ነጻነት ምንድነው? ባርነትስ አሁን በያዝነው ዘመን እሱ ምንድነው?

ሰሙና ወርቁን „የነጻነትና የባርነትን“ ፈልፍሎ አውጥቶ ይህን እንቆቅልሽ የዛሬው እትም ለመፍታት ይሞክራል።
የሥልጣን ሰዎች ምንድናቸው?

መልካም ንባብ

ዋና አዘጋጁ
ይልማ ኃይለ ሚካኤል

—-

ለ አእምሮ ሰኔ 2006 / June 2014/ እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 10

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s