ለአእምሮ ለውጥ …

ለአእምሮ ለውጥ ...ለአመለካከትና ለሥነ-ምግባር ተኅድሶ

ለአእምሮ ለውጥ …

Advertisements

ለአእምሮ ለውጥ …

ለአመለካከትና ለስነ-ምግባር ትንሣዔ

“እንደ ኢትዮጵያኖች ለነጻነታቸው ተቆርቁረው የሚነሱ ሕዝቦች በአፍሪካ ውስጥ-እንዲውያም በዓለም ላይ የለም ብዬ ብናገር መዋሽት አይደለም። ታሪካቸውም መስክራል። አንድ የማያውቁትና የተሰወረባቸው ነገር ቢኖር `ማንም ሰው አንድ የአገሪቱ ዜጋ እኔም አንተም እሱዋም እሱም ሙሉ የመናገርና የመቃወም የመተቸትና የመደገፍ የመጻፍና የማረም የመመራመርና የመጠየቅ ነጻነትና መብት ከሌላው ጋር እኩል አለው… ` የሚባለው ነገር ሲነሳ እሰከዚህም እምብዛም ምን እንደሆን አይታወቅም እነሱን አይጨንቃቸውም። እንድያውም ለምን ይህን ነገር አንስተህ የቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ ትቃወማለህ ብለው የሚቆጡ ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም። ግን ደግሞ እንደነሱ ዲሞክራሲ በአገሪቱ ጠፋ ብለው ተቃዋሚ በነበሩበት ዘመን ያልጮሁበት ጊዜ የለም። ይህን ተማሪዎች በንጉሱ ዘመን ብለዋል። ወታደሩም ተመሣሣይ ድምፅ አሰምቶአል። ነጻ-አውጪዎቹ በጊዜአቸው ብለውታል። ሥልጣን ላይ ሲወጡና ወደ ሥልጣኑ ቀረብ ሲሉ ሁሉም ይህን ጥያቄ- ጴጥሮስ እንደአደረገው – ከድተውታል። …..ለምን?” ከማስታወሻ ደብተር ።

…እንዴት ልኑር?…

እንዴት እንኑር?…

ዛሬ ምን ልብላ?

ነገስ ምን ልልበስ?

…ልጆቼን እንዴት ላሳድግ?

ምንስ ..ያጋጥመኛል?

በመካከሉስ በድንገት ያ ቢሆን?

…ያኛው መዓት ከተፍ ቢል?…

ብሞትስ? ብለው እንስሳትና አራዊቶች አያስቡም። ለዛሬውም ሆነ ለነገውም እነሱ አይጨነቁም። በመካከላችን ሥነ-ስርዓት ይኑር? ብለው ጉባዔ ጠርተው አይመካከሩም። አይመክሩም። ለየትኛው ሕይወታቸው?
የሰው ልጆችን ግን -አዲስ አይደለም ይህ አመለካከት- ከእነሱ ይለያሉ።
የላይኛው የዱር አራዊት ግፋ ቢሊ ጎጆ አለበለዚያም ዋሻ ፈልጎ ይጋደማል እንጅ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቋሚ ቤት ሠርቶ ለልጆቹ አያወርስም። የጋማና የቀንድ ከብቶች በተቃራኒው ነገ ከአሚአርደውና ከገራፊው ጌታው ጋር አብሮ እየተጋፋ ቀኑን ያሳልፋል። እሱም በሰራለት በረት ውስጥ ተነድቶ ይገባል። ቢላው ደግሞ አንድ ቀን አንገቱ ላይ መቼ እንደሚያርፍበት ሁሉም፥አያንዳንዱ ከብት አያውቅም። ይህን ባአለማወቁ ግን በምንም አይፈረድበትም።


ከፊሉ ይበቃዋል፣ ሣር ግጦ ያድራል። ሌላው እንስሳ በአንዱ አውሬ ታድኖ ይበላል። ዛሬ የበላው ነገ በሌላው ይበላል። የሚኖሩት እነሱ በኢንስቲክትና እናታቸው ለጥቂት ጊዜያት ባሳየቻቸው ብልሃት ነው። የሰው ልጅ ግን ልዩ ፍጡር ነው። የተለያየን እያንዳዳችን ፍጹም ዩኒክ ነን። ሰው በተሰጠው አእምሮው አርቆ ያስባል።እራሱን ይጠይቃል። የተጓዘበት መንገድ ወደ ገደል የሚወስደው ከሆነ በጊዜው ጠምዘዝ ብሎ አዲሱን ይሞክራል። ያሰላስላል። ያመዛዝናል። ሐሳቡን ከሌላው ጋር ይካፈላል። ካልተስማማውም አንድ ሰው የራሱን መንገድ ብቻውን ማንንም ፈቃድ ሳይጠይቅ መርጦ ወስኖ ይሄዳል። ተፈጥሮ እግዚአብሔር የሰጠው የግል መብቱ ነው።
እንደምናውቀው ሰው ሁሉ ደግሞ በጅምላ ብድግ ብሎ አዲስ ነገር አይሞክርም። ሁሉም ሰው ሌላው ምን አደረገ ብሎ ተንጠራርቶ ከሌላው ብልሃትንና ጥበቦችን ጥሩውንም ነገር ሰብስቦ ይጠቅመኛል ብሎ አይቀስምም። በዓለም ዙሪያ የሚታዩ ዘላኖች ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ለምን እንከራተታለን ብለው እራሳቸውንና ወላጆቻቸውን አይጠይቁም። በጥንታዊ የአኗኗር ዘዴና ልማድ በአሉበት የቀሩት እሰከ አሁን ድረስ እሰከ 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የምናያቸው ሰዎች ሌላ ትምህርት የሚሰጡን ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። የተፈጥሮ አየር ሳይታሰብ ቢቀየርባቸው? የከብትና የወረርሺን በሽታ ብቅ ቢል? ምን እናድርግ ብላው አይጨነቁም። እንደነዚህ ዓይነቶቹ በመጨረሻው…ይተርፋሉ ወይስ ይጠፋሉ? እንደምናውቀው ብዙዎቹ ከጥንታዊ የአኟኗር ዘዴ አንላቀቅም ያሉት ሕዝቦች ጠፍተዋል ። ለአለመቀየራቸው ደግሞ በቂ ምክንያት አላቸው።


የምናወራው ስለ አስተሳሰብና አመለካከት አመጣጣ ና ጅመራ ነው። እሱንም ለምን አንዳዶቹ በጊዜው ሁኔታውን አይተው መጪውን ችግር ተመልክተው አካሄዳቸውን ቀየሩ? ሌሎቹ ደግሞ ሳይለውጡት ይዘውት ቀሩት?…ለምን አንዳዶቹ ባህሎችና ሥልጣኔዎች ሳያስቡበት በድንገት ጠፉ? ለምን ደግሞ ሌሎቹ ቶለው ብለው ተመክረው እራሳቸውን አስተካክለው ወደፊት ተራምደው አምልጠው መሪ ለመሆን ቻሉ?… የሚሉትን ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል በአጭሩ ለመመለስም ነወ። ጥረታችንም ይህንኑ ለማሰየት ነው።
በተለይ በአንድ ዘመን „ትክክል“ ነው ተብሎ የተያዘው ጉዞ ሳያውቁት ወደ ገደል አፋፍ ሊወስድ ይችላል። የሚወስድ ከሆነ ደግሞ (በዓይን ይታያል) ያለው ምርጫ ለዚያ መንገደኛ ሁለት ብቻ ነው።leaimero-9-lalibela
ወይ በያዙት መንገድ ቀጥሎ ገደል መግባት ነው። ወይም ደግሞ መለስ ብሎ አዲስ መውጫ መንገድ መፈለግ ነው። ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች አዲስ አይደልም። የሥርዓት ምሥረታን ሙከራን በ20ኛው ክፍለ-ዘመን እንውሰድ።


በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከንጉሣዊ አገዛዝ እስከ አማራጩ የፋሽሽቶችና የኮሚኒስቶች ሥርዓት ድረስ በአውሮፓ ብቅ ብለው አይተናል። ግን ሥስቱም ተሞክረው ሳይሳካ ተቀባይና ተከታይ አጥተው ተራ በተራ ወድቀዋል። አሽናፊ ሁኖ የወጣው ከእነሱ አንዱም አይደለም።
አሽናፊ ሁኖ የወጣው የሕግ በላይነት የሰፈነበት ሰበአዊ መብቶች የታወቁበትና የተረጋገጡበት የግል ሐብት የተፈቀደበት ነጻ – የዲሞክራቲክ ሥርዓትና ሕብረተሰብ ነው። እዚያም ውስጥ ሁላችንም እንደምናውቀው መናገርና መጻፍ ይቻላል። መተቸትና መቃወም ይፈቀዳል።። የፈለጉትን ፓርቲ መምረጥ።… ለምን እዚህ አውሮፓና አሜሪካ እንደዚህ ዓይነቱ መንገድ ተመረጠ? ለምን እዚያ አፍሪካና አረብ አገሮች „…እኔ ብቻ“ አውቃለሁ/አውቅልኻለሁ ተባለ?
ጥረታችን ይህንንንም ለማሳየት ነው።


የውድቀት አፋፍ ላይ ደርሰናል የሚሉ ጥቂት አይደሉም።ይህች አገር ያ ሕዝብ ይህች ለዘመናት ተፈርታና ተከብራ የቆየች ኢትየጵያ ከእንግዲህ አሁንስ „አትተርፍም በቃ አለቀላት „ ብለው የሚሰጉ -የሚያዳምጣቸው ቢኖር- ጥቂት አይደሉም።እንደሚገመተው እጅግ ብዙ ናቸው።
„…ነገር ሲያመልጥ ጠጉር ሲመለጥ አይታወቅም „ ይባላል። ይህኛው ግን ስውር ሳይሆን ወለል ብሎ „…የጥፋት መንገዱ ላይ እንደሆን በደንብ ይታየናል“ ሲሉ አልፎ አልፎ ከእነሱ አፍ ይሰማል።
“እንኳን እኛ እራሱዋ አውሮፓም ተጠንቅቃ ችግሮቹዋን ተነጋግራ ተመካክራ በጋራ ከአልፈታች የሚፈራው ጦርነት አይቀርላትም“ ስለዚህ ቡራ ከረዩን ትተን ከገባንበት ለመውጣት „እናስብበት „ ሰዎች ይላሉ።
የሚያዳምጣቸው የለም እንጂ በዚህ ግምታቸው ዕውነት አላቸው።
ለመሆኑ ግን ያልተሞከረ?ያልተሰማ አዲስ መፍትሔ ለአገራችን አለ?
ሁሉም ነገር በአለፉት አመታት አልተባለም?


ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከመውደቃቸው ከአምስት አመት በፊት በስዳስው ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ „ደርግ“ ያውም አንድ ሰው መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም የሚባል አንድ ሻለቃ እሳቸውን ተክቶ ከቤተ-መንግሥታቸው እሳቸውንና ልጆቻቸውን አባሮ መንበራቸው ላይ ተቀምጦ ያን-እሳቸው ዘወትር እንደሚሉት „..የሚወዱትንና የሚወዳቸውን ሕዝባቸውን“ ያተረማምሳል ብለው እሳቸው ፈጽሞ አላሰቡም ነበር።(1)
እንኳን እሳቸው አጠገባቸው የነበሩትም የቆዩ አማካሪዎቻቸው በውኑም በሕልማቸውም „ደርግ“ የሚባለውን ፍጡር ብዙዎቹ ይመጣል በአገሪቱ ላይ ይነግሣል ይፈጠራል እነሱንም አንድ ቀን „አለፍርድ ለቃቅሞ ይፈጃቸዋል“ ብለው አላዩም አላሰቡም ነበር።2
እንኳን እነሱ ተማርን ያሉትም ያኔ መፍትሔውን እናውቃለን ብለው የተነሱትም ቡድኖች መጪውን አደጋ እነሱ በደንብ አላዩትም።


„…ንጉሡ ይውረዱ፣ መሬት ለአራሹ፣ የብሔር ትግል እሰከ መገንጠል ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥትና ሶሻሊዚም ለኢትዮጵያ የተደራጀ የነቃ የታጠቀ…ኃይል „ ይሉ የነበሩት ተማሪዎችም አንድ ፍጡር „ደርግንም ሆነ ቀይ ሽብርን ቀበሌን ሆነ የእርስ በእርስ ፍጅትን“ በስድሳው አመተ ምህረት ይህን የመሰለ ነገር ጥያቄአቸው በአገሪቱ ላይ „ያምጣል ያወርዳል“ ብለው ሐሳቦቹን ሲወረውሩ ምንም ነገር እነሱ አልታያቸውም ነበር።3
እንደተጠየቀው ንጉሡም ወረዱ። ሥርዓቱም ፈረሰ።ተማሪውም „ዕድገት በሕብረት“ ብሎ ዘመተ። ሙዚቃ በራዲዮ እና የወለዱትን ልጅ ክርስትና ማስነሳት ተከለከለ። ሰው ከጦጣ ነው የመጣው/የተፈጠረው ተባለ። ሠፈራ ቀጠለ። የሕብረት እርሻ ተባለ።
ደርግና ካድሬዎቹ ብቻቸውን አሥራ ሰባቱን አመት በአገሪቱ ላይ ጨፈሩ። „ኢሠፓን የሚቃወም በሞት ቅጣት ወይም በ20 አመት እሥራት“ ብሎ አወጆ ተደላድሎ ሽጉጡን ታጥቆ ወንበሩ ላይ ተቀመጠ።

አሥረኛ አመቱን ሲያከብር ከጥቂት አመት በሁዋላ ደርግ ይበተናል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ዚምባቦዌ ይወርዳል የደርግ አባሎች ይታሰራሉ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ የኢሠፓ አባሎች ከእነ ጦር ሠራዊቱ ይወገዳሉ ብሎ የገመተ ያሰበ ሰው አልነበረም።
አሁን -ብዞዎቹ ይህን ጠቅሰው – በቅርቡ ከፊታችን ምን ቆሞ እንደሚጠብቀን አናውቅም? ስለዚህ ይታሰብበት ይላሉ።lalibela-inside3
መጪው ጊዜ „መጥፎ ይሁን“ ወይም በአንዳንዶቹ ዘንድ እንደሚባለው „ጥሩ የዕድገት ዘመን“ የትኛው ይሁን ማንም ሰው አያውቅም። አብዛኛዎቹ ግን አለጥርጥር „መጥፎ ነው“ ይላሉ። ደግሞ መጪው ጊዜ „የመከራ ይሁን የደስታ የፈንጠዚያ ይሁን የለቅሶ“ ማንም -እንደ አለፉት ገዢዎች – አሁን የሚያውቅ የለም።
ዕውነት?


ይህንንም ሲሉ- እነሱ በአለፉት አርባ አመታት ጊዜ ውስጥ በአገሪቱዋ ላይ የተካሄደውንና የወረደውን መዓት አንድ በአንድ እንደገና ይቆጥራሉ።
ኤርትራ ከነወደቡዋ ከእሱም ጋር አንድ ሺህ ስድስት መቶ ኪሎ ሜትር የሚሆነውን የባህር በር ይዛ እንደሄደች ያነሳሉ። በዚያ ሳቢያ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ያስታውሳሉ። ትዳር በሁለቱም በኩል እንደ ፈረሰ፣ቤተሰብና ጎረቤቶች አንዱ ልጅ እዚህ ሌላው እዚያ እንደቀረ ሁሉም እንደ ተበተኑ ይዘረዝራሉ።
አለቀለት የተባለውም ጦርነት በኢህአዴግን በሻዕብያ መካከል እንደገና ተከፍቶ ከሁለቱም ወገን በጥቂት ቀናት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአንድ መቶ ሺህ ወጣቶች በላይ ባድሜ ረግፈዋል።
ቤተ-ክርስቲያናትና ገዳም መስጊድ ምዕምናንም ለሁለት ተሰንጥቀዋል። የንግድ ድርጅቶች በዚሁ ክፍፍልና መገንጠል ተዘግተዋል።
የህግ -መንግሥቱም ጉዳይ አለ። ሕግ-መንግሥቱ „…ብሔር/ብሔረሰቦች እንዲገነጠሉ ይፈቅዳል…“ ይህም አገሪቱ እንደ ዩጎዝላቪያ አንድ ቀን እንድትበታተን መጋበዙ አይቀርም ይላሉ። ይኸው ሕገ-መንግሥት መናገር መጻፍ መቃወም መተቸትና መደራጀት መምርጥና መመረጥ በኢትዮጵያ „ይቻላል“ እንደሚል ይጠቅሳሉ።
በተግባር ግን አይታይም ብለው ያማርራሉ።


ከዚሁ ጋር ቀደም ሲል አገሪቱን አተረማምሶ የሄደውን ደርግንና የኮነሬል መንግሥቱን ስምና ድርጊቶች አብረው አንዳዶቹ ይጠቅሳሉ። የቀበሌን ጭፈራ በአገሪቱ ዜጎች ላይ፣ የካድሬን ቁጣ የቀይ ሽብር/ነጭ ሽብር የጥይት እሩምታ ሠፈራ ዘመቻና አለ ክስ አለፍርድ የተገደሉትን ሰዎች ጉዳይ አብረው ይተርካሉ።
ዛሬም እንደ ዱሮው ስደት ክትትል እሥራትና ማስፈራራት በአገሪቱ አለ ይላሉ። ለዚህም በየጊዜው እዚህ ይፋ ሁኖ የሚወጣውን የአምኒስት እንተርናሽናል ዘገባና የሒውማን ራይት ወችን መግለጫ ለምስክርነት ከፍ አድርገው ያነሳሉ።
በኦነግ በኦጋዴንና በእህአዴግ በነዚህ መካከል የተካሄደውንና አልፎ አልፎ የሚካሄደውን ጦርንት እንደ ምሳሌም አንስተው እነዚህ ሰዎች ይጠቀሳል።
ይህን ሁሉ አይተው -ለማሳመን ኢትዮጵያ አለቀላት የሚለው መደምደሚያቸው ላይ ይደርሳሉ።
እንደገና ለመጠየቅ ይህን የሚሉ ሰዎች ዕውነት አላቸው? ወይስ ዝም ብለው ያጋንናሉ?


እንኳን ኢትዮጵያ የብርትሺና የፈረንሣይ ኢምፓየሮች የዛሬ ሃምሣና ስድሳ አመት አንዳዶቻችን ደርሰንበታል ተንኮታኩተው ወድቀዋል።… ቦታውንም አሜሪካን ሶቪየት ተሻምተው ተከፋፍለዋል።
የሮምና የግሪክ ከጥንቱ የሶቪየትና የኦስትሪያ/ሐንጋሪ የጀርመንና የጣሊያን በተለያዩ ዘመናት ተነስተው አብጠው ሰፍተው እንደገና ተፈረካክሰው ተበታትነው ወድቀዋል።
የፈረዖኖቹ ግብጽም የኦቶማን ኢምፓየርም እነዚህ ሁሉ ተበትነዋል።
ለምንና በምን ምክንያት?
አንደኛው ምክንያት ከጊዜው ጋር አብረው የአስተሳብ ለውጥ አድርገው መሄድ ስለ አልቻሉም ነው። ሁለተኛው በውስጥ ውዝግብ በውጭ ጦርነት ተወጥረው ሰለተያዙ ነው። ሦስተኛው የላይኛው መደብ በሥልጣን እና በባህሪአቸው የማይሆን ዓለም ውስጥ ገብተው በመጨማለቃቸው ነው። አራተኛው እነሱን ለመተካት የተነሳው አዲስ አስተሳሰብ ጊዜውን ለመጠቀም በመቻሉ ነው።

አህጉሪቱዋ አፍሪካ ደግሞ እንደምናየውና እንደምንሰማው ለጦርነትና ለፍጅት ለክፍፍልና ለትርምስ አዲስ አይደለችም።
ሩዋንዳ አንደኛዋ ናት። ሱዳን ሁለተኛዋ ናት። ሦስተኛዋ ደግሞ ማን ትሆን?
በሩዋንዳ የተካሄደው ፍጅት ሲጀምር እንደዚሁ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ጥላቻ በዚያ አካባቢ ሰፍኖ ነበር ይባልለታል።ሰሞኑን የሚታየው የደቡብ ሱዳን ውስጣዊ ወዝግብና ጦርነት ተመሳሳይ ነው።መካከለኛው አፍሪካን እና ኮንጎን ዞር ብለን ስንቃኝ አዝማሚያው -እነሱ እንደሚሉት- አንድ ነው። ከዚያ በፊት በአልጄሪያ የዛሬ ሃያ አመት ገደማ ….በቻድ።በማሊ።በጎረቤት አገር በኬንያ ኩኩዩና በሌሎቹ መካከል ምርጫውን አስመልክቶ በተጫረው ግጭት በቆንጨራ ተናንቀው በሺህና በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አልፎአል።
እግሩን ያጣ እጁን የተቆረጠ ዓይኑ የጠፋ ከንፈሩና አፍንጫው …የተበጠሰ የተደፈሩ ሴቶች …የተቃጠሉ መንደሮች ብዙ ናቸው።
በሱማሌ የተጀመረው መፈረካከስ የዚሁ የተሳሳተ ፖለቲካ አካሄድና ከእሱም የተወለደ ችግር እንደሆነ ይጠቀሳል። ሁሉም ቦታ በአፍሪካ የሚታየው ሥዕል አንድ ነው።…. ጦርነት ስደት ረሃብ እሥራትና ክትትል…የዘር ጥላቻ ግድያ እርሻና ቤት ማቃጠል ከብት መንዳት…
በደቡብ አፍሪካና በኬንያ በጋና እና በቦትስዋና በታንዛኒያ ሌላ ሁኔታ በተቃራኒው ልዩ ሥልጣኔ እዚያ እናያለን። በናየረጄሪያ ደግሞ በቅርቡ ሃይማኖትን አስታኮ የሚታየው አዝማሚያ ያስፈራል።


ይህች አገር – ኢትዮጵያ እንደሚባለው በእርግጥ ለመበታተን የሚያስፈራ ሁኔታ ላይ ደርሳለች? ይህ ከሆነ…ምን እናርግ? ምን ይደረግ?…ዝም ብለን እንተኛ ?… ጦር አንዳዶቹ እንደሚሉት አንስተን እንታገል? ወይስ አዳዲስ እሰከ ዛሬ ድረስ ያልተሰሙ ናቸው የተባሉትን መፍትሔዎችን አንስተን እንሰንዝር? …ወይስ የተባሉትን መልሰን እንድገም?…መጪው ምርጫ ውስጥ ዘለን እንግባ? አደባባይ እንውጣ? ብሔራዊ እርቅ እንበል? …በተያዘው መንጫጫት እንቀጥል?
ለመሆኑ ከዚህ ሁሉ የተለየ ምን ዓይነት ከዚህ በፊት ያልተሰማ አዲስ መፍትሔ በኪሳችን አለ?leaimero-9-new-buecher_mit_kerze_kurzg
ረሃብና ችግር፣ የዋጋ መወደድና ሙስና በሥልጣን መባለግና የዘመድ ሥራ…እነዚህ ሁሉ ዝም ተብለው የሚታለፉ ነገሮች አያደሉም።
እዚሁ ላይ ከትምህርት ቤት ተመርቀው ወጥተው ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች ቁጥር ብዙ ነው። የጡረታ ገንዘብ አይበቃም። የሕክምና መድሓኒት የለም። ቤንዚን ተወዶአል።መብራት አንድ ቀን ይበራል በሚቀጥለው ቀን ይጠፋል። የስልክና የኢንተርኔት ቁጥጥር ከባድ ነው።
በግብጽና በቱኒዚያ በሊቢያና በሶሪያ በየመንና በዮርዳኖስ…በምሥራቅ አውሮፓም የወጣቱ እንቅስቃሴ የተቀጣጠለው በእነዚሁ እላይ በተጠቀሱት ችግሮችና ምክንያቶች ነው።

መልሱ ታዲያ ለኢትዮጵያ አሁን ምንድነው?

ይህን ለመረዳት ከመሶቡ ጠርዝ -አውሮፓውያኖች እንደሚሉት -ምግብ ከቀረበበት ሳህን ጫፍ ከዚያ ባሻግር ችግሮችንና ነገሮችን መመልከት ያስፈልጋል።
ለዚህም አንድ ጥያቄ ብቻ ማንሳቱ ይበቃል።
ለምንድነው አፍሪካ የምትተረማመሰው? ለምንድ ነው አውሮፓና አሜሪካ በልጽገው በሰላም ተመካክረውና ተቻችለው አንድ ላይ በጥሩ ጉርብትና የሚኖሩት? ለምንድነው እዚያ አህጉር ችግር በየአለበት የሚፈላው? ለምንድነው ነጮቹ ጋ ሁሉ ነገር መልክና ሥርዓት ያለው?
ተመሳሳይ ጥያቄ እናክልበት።
የነጮቹ ዓለም በምን ብልሃት ላይ ነው የተዋቀረው? የአፍሪካውያኖቹ „ዕብደት“ ደግሞ በምን መሠረት ላይ ነው የተገነባው?
እንዴት ነው እነሱ ነጮቹ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሳሰሩ እየተፋቀሩ የሚሄዱት ? ለምንድነው በዚያ አህጉር አንድ አፍሪካዊ ጎረቤቱን በቢላና በመጥረቢያ ጠብቆና ተጠባብቆ አንዱ ሌላውን የሚያባርረው? አሳዶም ወንድሙን አብሮ የኖረውን ጎረቤቱን በመጥረቢያ የሚፈልጠው?


በሦስት ብልሃቶች አውሮፓና አሜሪካ እነዚህ አህጉሮች አፍሪካን ጥለው ሄደዋል። አፍሪካን ብቻ አይደለም።ሌለውንም ዓለም!
ስንመለከተው:- እነሱም ሜዳዎች ይህን ይመስላሉ።
አንደኛው እነሱ የጨበጡትና የሚመሩበት አይዲኦሎጂ-አይዲኦሎጂ ርዕዮተ ዓለም ማለት አለብን (ሌላው አጥቶና ጠፍቶበት ይወናበዳል ወይም ጊዜ የጣለውን ታቅፎ ብቻውን ይንከራተታል ወይም ደግሞ በተስፋ ምናልባት ተመልሶ ይመጣ ይሆናል ብሎ እራሱን ያጽናናል) እነሱ የጨበጡት ትምህርት የመረጡት ሥርዓት „ነፃ- ሕብረተሰብ“ የሚለው አስደሳች አመለካከታቸው ነው። ወይም በሌላ ቋንቋ „ሊበርቲ“ የሚባለው የፖለቲካ ነጻነት ጥበብ ያ የእያንዳንዱን ዜጋ መብት/መብቶች የሚያውቀው ሥርዓታቸው መኖር ነው።
ይህ ደግሞ እጅግ ኃይለኛ ማንም የማይደርስበት አይዲኦሎጂ ሆኖ ወጥቶአል።። (ዕውነቱን ለመናገር እኔ/እኛ በምንም ዓይነት -ይህን የምንተነፍሰውን አየር በማንኛውም አልባሌ ነገር ጨርሶ የማንቀይረው የማንለውጠው መብታችንን የሚያውቅ ግሩምና ትልቅ እሴት ነው።)
ሁለተኛው ከዚሁ ከላይኛው ጋር አብሮ ተስታኮ የተወለደው የምርምርና የቴክኒክ ጥበብ ችሎታቸውነው።


ዓይናችን እያየ ጆሮአችን እየሰማ ከካሴት ማጫወቻ ከብርቄ ራዲዮ ተነስተው በአጭር ጊዜ ውስጥ „ዎክማን“ ፈልስፈው እሱን ጥለው ፋክስን ዘለው በአንዴ ታብሌትና ላፕ ቶብ ኮሚውተር አይ ቮንና አይጴድ ሁለ ገብ ቴሌቪዥንና ነቪ የንፋስ ስልክና ስካይፕና ፋይቨር…ገብተዋል። ሕክምናውን አናነሳም።የቤት ሥራቸውን አንጠቅስም።ወሃና የመብራት ኃይላቸውን ዘለን እናልፋለን። መኪና ሲሰሩ አይሮፕላን ሲፈጥሩና ሲገጣጥሙ መርከብ ሲያንሳፍፉ…ይህን ሁሉ እንተው። ይህም የማይናቅ ችሎታ የተገኘው ለምርምርና ለጥያቄ ሕብረተሰቡ ክፍት በመሆኑ ነው።
ሦስተኛው ብቃታቸው በየቀኑና በየሳምንቱ ታትመው የሚወጡት ጋዜጣዎቻቸውና መጋዚኖቻቸው …ፊልምና መጽሓፍቶቻቸው በአጠቃላይ „…የካልቸራል እንዲስትሪአቸው የሚባለው ምርታቸው“ እነሱን ጠንካራ አድርጎአል።
ሕንድም ቻይናም ራሺያም ናይጄሪያና ኢትዮጵያም ፊልም/ፊልሞች ያውም በብዙ መቶ የሚቄጠሩ ይሰራሉ። ጥያቄው ግን ምን ዓይነት ፊልም የሚለው ነው።
መጽሓፍት ጋዜጣና መጽሔት ፊደል ያላቸውና የሌላቸው አገሮች በየጊዜው አትመው ገበያ ላይ ያወጣሉ። አሁንም ጥያቄው ምን ዓይነት ጋዜጣ ነው? ማነው ስለምን መጻፍ የተፈቀደለት? ሳንሱር አለ ወይ?…ሕዝብ ወይም አንድ ተቃዋሚ አስተያየቱን መስጠት ይችላል ወይ?


በሦስቱም የሚሊተሪውን ከጨመርን በአራቱም መስኮች ምዕራቦቹን የሚደርስባቸው የለም።
አፍሪካን ብቻ ሳይሆን እነሱ ቻይናንም ሩሲያንም አረቦችንም ሕንድንም ይበልጣሉ።
በቻይናና እና በሆንኮንግ በታይዋንና በደቡብ ኮሪያ ብዙ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ተሠርተው የዓለም ገበያ ይቀርባሉ። እዚህም ላይ የሐሳቡ ባለቤት የፈጠራው አባት ማን ነው? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው።
ለምንና እንዴት በምንስ ተአምር እነሱ ነጩቹ ይህን የመሰለ ጥበብ ፈልገው ያገኙት ለብቻቸው የጨበጡት? እንዴትስ ተካናቸው? ለምንድ ነው ሌላው ሕዝብ ይህን ፈልጎ ለማግኘት ዓይኑ የታወረው?
ፊልም መሥራት ጋዜጣና መጽሓፍት መጻፍ መመራመርና መፈላሰፍ መጠየቅና መልስ መፈለግ ለምን በአውሮፓ ይቀላል ?ለምን በኢትዮጵያ ይከብዳል?
ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲት በየዓመቱ ፈልፍሎ ማውጣት እዚህ ይቀላል።እዚያ ግን ለምን ይቸግራል?… የውይይትና የክርክር ባህል የመተቸትና የመውቀስ ሥርዓት መዘርጋት እዚህ መንግሥት ያበረታታል። እዚያ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ያስፈራል? ወይም ያሳሥራል? ለምን?
እንዴት እነሱ ቻሉበት?እንዴትስ እኛ አቃተን?


መልሱ ከባድ አይደለም። ቀላል ነው።
በአውሮፓና በአሜሪካ ሕዝቡም ሆነ ገዢው በትክክል ለመናገር በሕዝብ የተመረጠው መንግሥት/አስተዳደር በነጻ አስተሳሰብ ያምናል። አገራቸውም የነጻ አስተሳሰብ መንሸራሸሪያ „ዓለም“ ነው። የማይክሮ ሶፍቱን ባለቤት የቢልጌትን አነሳስ፣ የአፕልን መሥራች የነፎርድንና ….የእነ…አመጣጥ ታሪክ መመልከት በቂ ነው።
የዚህንና የእንደዚህ ዓይነቱን ሁኔታ በአፍሪካ አመቻችቶ ማቅረብ ለምን ከባድ ሆነ?
አፍሪካ እንደምናውቀው „…እኔና ተከታዮቼ ብቻ እንናገር አንተ ግን ዝም በል! …እኔ ለአንተ የሚያስፈልግህንና የሚጎዳህን አውቅልኻለሁ…የምትለብሰውን ልብስ የምትናገራቸውን ቃላቶች የምትቀምሰውን ዳቦ እኔ አቀርብልሃለሁ…ስለዚህ አርፈህ ተቀመጥ አለበለዚያ ደግሞ …ዋ ዱላውን አለንጋውን ጥይቱም ሊከተል …ይችላል“ የሚባልበት ቦታ ነው። ለምን?
የላይኛው መንገድና ብልሃት ነጮቹ የተከተሉት ለእነሱ አዲስ አብሮ የመኖር መንፈስን በመካከላቸው እንዲኖር በሩን ከፍቶላቸዋል።
የታችኛው አፍሪካ በዘርና በነገድ በመደብና በሃይማኖት ልዩነትና ጥላቻ ላይ አተኩራ እንድትፋጭ መንገዱን አመቻችቶ ለቆላቸዋል።
መነጋገር ከተቻለ መተቸትና መወቃቀስ የተለየ ሓሳብ ማቅረብ በሕግና በይፋ ከታወቀ ማንም ሰው አዲስ ነገር -አንተም እሱም እሷም ጎረቤትህ… ነጩም ጥቁሩም ቢጫውም ቀዩም … መፍጠር መፈላሰፍ ያለውን አሻሽሎ ማቅረብ ይችላል።
ግን ያለንበት ሁኔታ በሁለት አብይ ምክንያቶች ነጻ ውይይትን ነጻ ሕብረተሰብንና ነጻ የግለሰቦችን አስተሳሰብ በሰዎች መካከል እንዲኖር አይፈቅድም።


አንደኛው ምክንያት:- በተለይ ይህ የአፍሪካን ገዢውን መደብ ይመለከታል- „ ሰው ሁሉ በነጻ መወያየት ከቻለ ነገ ሥልጣኑ ላይ ብቻዬን ተቀምጬ መግዛት የማልችልበት ደረጃ ላይ እደርሳለሁ“ ስለዚህ „አፉን ለጉሜ ልያዝ… „ወደሚለው ፍርሃቻ በዚያውም ወደ አምባገነንነት ገዢውን ክፍል ወስዶታል። ርዕዮተ ዓለሙም አስተዳደጋችንም ምኞቱም „እኔ ብቻ „ ለሚል ሰው አመቺ ነው።
ፍረሃቻው ከሥልጣን ከወረድኩ „…ይገዱሉኛል“ ወደ ሚለውም አመለካከት (መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምን ተመልከት) ተሸጋግሮአል። አንድ ሰው አለፍርድ አለ ዳኛ ና አለ ጠበቃ በጥይት ተደብድቦ የሚሞትበት አህጉር በአፍሪካ ነው።
የገዢ መደብ ልጆች አገራቸውን በገፍ ጥለው የሚሸሹበት አካባቢ ምሥራቅ አፍሪካ ነው። ወላጆች ሂድ ብለው ያላቸውን አሟጠው ልጆቻቸውን ወደ ውጭ የሚሸኙበት አህጉርም አፍሪካ ነው። እንደሚነበበው ከሰባት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ ወጣቶች አውሮፓ ለመግባት ቤታቸውን ለቀው ተነስተዋል።
ሁለተኛው ምክንያት -እላይ እንጠቆምነው- ከየትም በመጣው አይዲኦሎጂም ላይ የተመሰረተ ነው። አፍሪካ ተሽከርክረው በተለያዩ መንገዶች የገቡ ርዕዮተ ዓለሞች የግለሰብን ነጻነትን የሕግ በላይነትን ፈጽሞ አያውቁም። አይቀበሉም። እሱማ ቢሆን ኑሮ በዚህ ትምህርት የተጠመቁት ሰዎች ገና ዱሮ በሌላ መልክ በተደራጁ ነበር።
አናስረዝመው እንጅ ሌላም ሦስተኛም ምክንያት አለ።


እሱ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ „…እኛም እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው ከኢንዱስትሪ አብዮት በሁዋላ ነው ስለዚህ አትቸኩሉ…ረጋ በሉ…“ የሚለው የአንዳንድ አማካሪ ነጮች የሐሰት ፕሮፓጋንዳና እሱም „ዕውነት ነው“ ብለው ከሚያምኑ ሰዎች የተንኮል ሥራም የመነጨ ነው።
…መናገርና መጻፍ መቃወምና መደገፍ መተቸትና ማረም ከእንዱስትሪ አብዮት ከፋብሪካ ሥራ በፊት የነበረ የቆየ የሰው ልጆች መሰረታዊ የሆነ ምንም ሰው -ንጉሥ ይሁን ወታደር ተማሪ ይሁን ተዋጊ ጦር የማይገፈው ቋሚ ሰበአዊ መብቱ ናቸው።lalibela-inside2
ግሪኮች ይህን ከክርስቶስ ልደት በፊት ደርሰውበት ለወገኖቻቸው ለቀዋል። ሮማውያን ሞክረውታል። እንግሊዞች ፋብሪካ ሳያቋቁሙ ተለማምደውታል። ብሉይ ኪዳን ላይ አለ። በአዲስ ኪዳንም ላይ ክርስቶስና ሐዋሪያት የሰው ልጆች ሁሉ እኩልና ነጻ ናቸው ብለው አስተምረዋል።4
ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው -ለዚህም ነው ከከብትና ከአውሬ የምንለየው- የመናገር የመተቸት የመጻፍ …አስተያየት መስጠት….ለመጪው ጊዜያቶች ለእራሱን ለልጆቹ ማሰብ፣ መጨነቅ እርማትን መጠየቅ… መብቱን/መብቶቹን በማንም የሚታገድ አይደለም።
„ላግደው“ ቢባልም ይህን ከአወቅንበት አይቻልም።


አለማንም ሰው ፈቃድና ችሮታ ሁላችንም ጥዋትና ማታ ምን ላድርግ? ምን ልሥራ ብለን እናስባልን፣ ከሂሊናችንና ከአእምሮአችን ጋር ብቻችን እንሟገታለን። በደረስንበት ሓሳብ እንስቃለን። እናሰላስላለን ። ይህኛውን ሓሳብ እንጥለዋለን። መልሰን እሱን እናነሳዋለን። እንደገና እንፈትሸዋለን።… የደረስንበትን ሐሳብም ከፈለግነው ሰው ጋር በፈለግነውን ሰዓት አንስተን እንለዋወጣለን?
በወረቀት ላይ መጻፍ ይቻላል። ጽፈን እናስቀምጣለን። ከፈለግን እናሰራጫለን። ምን ይመስለኻል? ይመስላችሁዋል? ብለን ከብጤዎቻችን ጋር እንወያያለን።
ለዚህ ነው የመናገር እና የማሰብ ነጻነት ከላይ እንደ መና ዳቦ ተወርዉሮ እንዲሰጠን በልመና የምንጠብቀው መብት ሳይሆን ሰው ሁሉ በእራሱ ቤት የሚያውጀው በሥራም እሱ እራሱ አለፈቃድ የሚተረጉመው ከእግዚአብሔር ወይም ከተፈጥሮ የተሰጠን መብታችን ነው።
ለዚህም ነው የአመለካከትና የሥነ- ምግባር ለውጥ በመካከላችን ውስጥ በመጀመሪያ እናድርግ ብለን አርዕስቱን የከፈትነው።
እንደዚህ ዓይነቱን እርማጃ የምሥራቅ አውሮፓ ሕዝቦች ወስደው -እርግጥ ሰባ አመት ፈጅቶባቸዋል- ሰበአዊ መብታቸውን የገፈፉትን አምባገነን ኮሚኒስቶቹን ከሥልጣናቸው አባረዋል። ሒትለር ከአሥራ ሁለት አመት ሞሶለኒ ከሃይ አመት በሁዋላ እነሱም ተሰናብተዋል።
ሙባራክ ከሠላሣ አመት በሁዋላ… ከቤን አሊና…ከጋዳፊ ጋር ሄደዋል።


የክርስቲያንም የእስልምናም ሃይማኖት የሰው ልጅ ሁሉ አንዱ ከአንዱ ሳይበልጥ እኩል ነው ይላሉ። የሰው ልጆች እኩል ከሆኑ ደግሞ አንዱ ተነስቶ አንዱን የግድ ይህን ልበስ ይህን አትልበስ ዛሬ ተናገር ነገ ዝም በል ያንን አትናገር… እኔን ብቻ ተከተል… የምፈቅድልህን ብቻ አንብብ… አትጠይቅ አትመልስ አትመራመር አትተች አትሳቅ ቀና ብለህ እትሂድ …ሊለው አይችልም።
library philo-pragሕገ መንግሥቱም ነጻነቱን በመስጠት ይህን ይከለክላል።
በሚሊዮን የሚቆጠረው ደግሞ አንድ ላይ ቆሞ ይህማ „ከእግዚአብሔር የተሰጠኝ የመናገር መብቴ ነው“ ከአለ ምንም ማድረግ አይቻልም። ዝም ብሎ መቀበል ብቻ ነው።
ይህን መሠረት አድርገን ሁለት ነገሮች ኢትዮጵያን በዚያውም ድፍን አፍሪካን አህጉሪቱን አሁን ከአለችበትና ከገባችበት ችግር ያወጣታል ብለን እናምናለን።
አንደኛው መናገርና መነጋገር መውቀስና መተቸት በመካከላችን አለ አንዳች ፍርሃቻ በግልጽነት ሲካሄድ ነው። ሁለተኛው ማንም ሰው በሕግ ፊት ያለው መብቱ እኩል እንደሆነ ሁሉም ሰውና ሁሉም ወገን ይህን ዓለማቀፋዊ ደንብ ሲቀበልና ሲረዳው በተግባርም በሥራ ሲተረጉመው ነው።

የግለሰብ ሰበአዊ መብት /መብቶቹ ከታወቁ ደግሞ የሕግ በላይነት በአንድ አገር አለ ማለት ይቻላል ። የሕግ በላይነት ከታወቀ ደግሞ ሰበአዊ መብቶች -እዚህ እንደምናየውና በየቀኑ እንደምንተነፍሰው ተከበሩ ማለት እንችላለን ።


ቁልፉ ደግሞ ማንም ሰው ለፈለገውና ለሚያምነው አምላኩ የመጸለይ መብት እንዳለው ሁሉ „ማንም ሰው የፈለገውን የመናገር መብት አለው።“ ከእሱም ጋር … የመጻፍና የመተቸት። …የመምረጥና የመመረጥ።የመቃወምና የመደገፍ የመደራጀትና ከአልፈለገም ያለመደራጀት መብቱም የተከበረለት ነው።
ያኔ ደግሞ አማራጭ አስተያየቶች አደባባይ በግልጽ ይወጣሉ።
የፖለቲካ አማራጭ አስተሳሰቦች አደባባይ ይውጡ እንጂ „አንዱ ብቻውን ያለውና ያራመደው አቅዋም ትክክለኛ ነው።… ሌሎቹ ግን ተሳስተዋል“ ማለት አይቻልም።
በፖለቲካ ዓለም አንድ ትክክለኛ መልስ ለአንድ ጥያቄ የለም። ወይ የተለያዩ ሓሳቦች እንድ ላይ ተጨምቀው አንድ መልስ በጋራ ሊወጣቸው ይችላል። ወይም የተለያዩ አስተሳሰቦች ተቀራርበው ተሞርደውና ተስተካክለው ለተነሳው ችግር ምናልባት መልስ በጋራ ሊወረዉሩ ይችላሉ። ወይም አዲስ ሐሳብ ብቅ ሊል ሊወለድ ይችላል። እሱም ላይ ቢደረስ ደግሞ ይህም መልስ ቋሚ ላይሆን ይችላል። ከጊዜው ጋር አብሮ መሄድና መቀየር በአዲስ አስሰተሳሰብ መተካትም ይኖርበታል።


„….የአሽናፊ መደብ አመለካከት፣ የአሸናፊ ብሔር መፍትሔ፣ ትክክለኛው የማርክስ አይዲኦሎጂ ፣ ዕውነተኛው የስታሊን ቲዎሪ ፤የተራማጆች ትክክለኛ አቋም፣ ሶሻሊዚም ኮሙኒዚም ነጻ-አውጪ …“እነዚህ ሁሉ ቅጽሎች አንድን አገር አንድን ሕዝብ አንድን አህጉር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦችን ከገቡበበት ችግር የሚያወጡ „ጥበቦች“ ሳይሆኑ መልሰው ችግር የሚያባብሱ አመለካከቶች ናቸው።
ታሪክ -በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን- እነዚህ እላይ የተቆጠሩት አመለካከቶች ስህተት ናቸው ብሎ ደግሞ ገና ዱሮ ትክክለኛ ፍርዱን ሰጥቶአል። የአመለካከትና የአእምሮ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል።


ይህ ሲባል ግን „እኔ የሕይወቴን ደስታ ፈልጌ አግኝቼአለሁና እባክህን ተወኝ አትረብሸኝ/አትረብሹን“ የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።እነሱም ደራሲያንና ፊልም ቀራጮች ፈላስፋና ሙዚቀኞች ስፖርተኛና የኪነት ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
የአመለካከት ለውጥ ይደረግ ሲባል ዓለም በቃን ብለው ገዳም የገቡ ሰዎችም እባካችሁ ተውን ቢሉን መብታቸው ነው።ወይም እነዚህ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪ ጠበብቶች ሐኪምና ኢንጂነሮች አስተማሪና ተማሪዎች እባካችሁ አትድረሱብን ሊሉን ይችላሉ።
የአመለካከትና የአስተሳሰብ የሥነ-ምግባርም ለውጥ እናድርግ ሲባል „እኛ ኤርትራ ነን ወይም ኦሮሞ ወይም አማራና ሱማሌ ነን …የምንሰራውን እናውቃለን ተዉን …“ብለው አንዳዶቹ ወይም ብዙዎቹ ሊቆጡን ይችላሉ።
ዕድሜው የገፋም ሰው/ሰዎች ጊዜው የእኛ አይደለም የወጣቶቹ ነው „እንተው“ ሊሉ ይችላል።
ከሃይማኖት ተነስቶ ከድሮ አመለካከቱ አልላቀቅም የሚል ሰው ሊኖርም ይችላል። ሌሎችም ያልጠቀስናቸው አሉ።


በአጭሩ ግን ለማለት የምንፈልገው ይህ የአመለካከት ለውጥ ሌላ ነገር ሳይሆን ምንም ሰው በአገሩ ወይም በአለበት ቦታ -የሌላውን ሰው አፍንጫ እስካልነካ ድረስ- የፈለገውን ነገር ለማድረግ ሙሉ መብቱ አለአንዳች ገደብ ይታወቅለት ማለታችን ነው።
ይህን መሰረት ከአደረግን እኛም አንድ ቀን ጥበብና ዕውቀትን ጨብጠን በደስታና በሰላም ጎን ለጎን የምንኖርበት ጊዜ እሩቅ አይደለም።ይህን የሚል ይህን የሚመኝ ሰው ቁጥር በኢትዮጵያ ትንሽ አይደለም። ለመናገር ለማሰብ ለማመዛዘንና የሒሊና ፍርድ ለመስጠት ሁሉን ነገር አምላክ ሰጥቶናል። የሚቀረው እራስን ነጻ-አድርጎ እንደያውም ከዱሮ አስተሳሰብ ተገላግሎ እፎይ ብሎ የልብን መናገር ነው። ይህን እንደ ጦር የሚፈሩ ደግሞ ትንሽ አይደሉም። አይዞህ አትፍራ ይላል መጽሓፉ!

1) Der letzte Kaiser von Afrika -The Last Emperor from Africa -HSI

(Lij Dr.Asfa -Wossen Asserate)

2)The Quest for Socialist Utopia? (Prof.Bahru Zewede)

3) The Holy Bible & Koran


ይልማ ኃይለ ሚካኤል
ዋና አዘጋጅ

logo-circ-reg

ለ አእምሮ ግንቦት 2006 / May 2014/ እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 9

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s