ላቢሪንት/ፈሩ ሲጠፋ – ርዕሰ አንቀጽ

ላቢሪንት/ፈሩ ሲጠፋ – ርዕሰ አንቀጽ

labyrinth3

በሪንት – የአዙሪት መናፈሻ ውስጥ ገብቶ መዝናናት -ውድ አንባባቢ- ቀላል ነው። ከዚያ ሳይረፍድ ወይም ሳይመሽ በቀላሉ መውጣት ደግሞ ከባድ ነው። አይቻልም።
የገቡበት በር ይጠፋል።ያቋረጡት መንገድ አንድ ይመስላል። ግራ ቀኙ ተመሳስሎ ያደናግራል። የመውጫ በሩ እንደ መግቢያው አንድ ብቻ ነው።

ታዲያ ከተገባበት መከራ መውጫ መንገዱ ብልሃቱ ምንድን ነው?
ግንቡን በመሰላል መዝለል? ወይስ ወደ ላይ መንጠልጠል? ጫካ ውስጥ ቆሞ መጮህ?… በድፍረት መፏጨት? …መጸለይ? አንድ ተአምር ከላይ እሰከ ሚወርድ ቁጭ ብሎ መጠበቅ? ወይስ….?
ደራሲዎች አእምሮአቸው ክፍት ስለሆነና ብዙ ነገር እነሱ በአንዴ ማየት ስለሚችሉ ቀላል መልስ መሰንዘር ይችሉበታል።

der_name_der_rose_spielplan

ኡምቤርቶ ኢኮ ያ „…በጽጌረዳ ስም..“ ብሎ ስለ አንድ የመካከለኛ ክፍለ-ዘመን የገዳም መጽሓፍት ቤት ታሪክና የአርስጣጥለስ የፍልስፍና ትምህርቶቹ ተማሪዎች እጅ ገብቶ (በአውሮፓ) ከመንፈሳዊ ትምህርትና ከመልካም ሥራ ወጣት ልጆቹን አርቆ „እንዳያበላሻቸው“ እነሱን ስለሚጠብቀው አይነ ስውር ሊቀ ካህን በተረከው ትልቁ የልብ ወለድ ድርሰቱ ላይ አንድ ሰው የላበሪንት ገዳም- ሕንጻ ውስጥ ገብቶ እንዴት እንደሚወጣ በቀላሉ ያሳየናል።
ብርድ የሚመክት ሹራብ ግን መልበስን ይጠይቃል። ደራሲው ይህንኑ ለወጣቱ አልብሶታል።
ከአስተማሪው ጋር የአርስጣጥለስን መጽሓፍ የሚፈልገው ወጣቱ ልጅ የገባበት ሕንጻና እግሩ የረገጠው ክፍሎች ከነመስተዋቱ እያነጸባረቁበት ደረጃዎቹ መውጫና መግቢያውን ስለአዞሩበት ሽራቡን ሳያወልቅ ቀስ እያለ ተርትሮ እንደ መንገድ ቀያሽ መሓንዲስ በእሱ እየተመራ የት የት እንደ ነበረ ምንን እንዳለፈ በሚቀጥለው እርምጃ ምን ማድረግ እንደ አለበት ያ ልጅ በዚያች በለበሰው ሹራብ ጉዞውን ሊረዳ ችሎአል።
መሓል ላይ የሹራቡ ክርስ ቢያልቅበትስ?
የአዙሪት መናፈሻ ውስጥ ተገብቶ በቀላሉ የማይወጣበትን ጫካ እንደ ምሳሌ የወሰድነው አለ ምክንያት አይደለም። ውቅያኖስ ውስጥ ገብቶም ወዴት እንደሚዋኝ (ደሴትም መሬትም ተራራም በማይታይበት ወሃ)ግራ የተጋባውን ሰው እንደ ምሳሌም ልንወስድ እንችላለን።

ዓሣ ነባሪዎቹ ብቅ ቢሉበትስ!

አሁንም ከዚያ ከተገባበት ችግርና መከራ ለመውጣት እንደ ጫካው ጉዞ መውጫ በሩ ማምለጫ መንገዱ ድፍንፍን ብሎ ጨልሞ ጠፍቶናል።

ይህን የማይመለከቱ አሉ።

እስቲ እራሳችንን አንድ ጥያቄ ብቻ እንጠይቅ። ከዚህ ሁሉ ግርግርና ትርምስ በሁዋላ ምን አተረፍን?
ለመሆኑ አሁን ማን ምን አተረፈ? ምንም ማለት እንችላለን!

ሁሉም ባዶ እጁን ነው የወጣው።

ንጉሣዊ ቤተሰቦች -ይህ አያነጋግርም- ምንም ያተረፉት ነገር የለም። ..አላተረፉም። መሣፍንቱና መኳንንቱ እንደዚሁ ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል።
ያ የሚፈራውና ግርማ ሞገስ የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊትና ፖሊስም በመጨረሻው ወይ ሞተዋል ወይ ተበትኖአል። ደርግ ከአለ ኮ.መንግሥቱና ከፍቅረ ሥላሴ ድርስቶች ሌላ ምንም ከእነሱ የተረፈና የቀረ ነገር የለም።ጨፍረው ጨፍረው የት ደረሱ? ስደት እሥራት ሞት።

ብዙ የሚነገርለትና የሚወደስለት የተማሪው እንቅስቃሴ እና ከእነሱ አብራክ የወጡት የፖለቲካ ደርጅቶች -እጭኣት ኢህአፓ መኢሶን ወዝ ማሌሪድ …ዛሬ የት ናቸው?

ከጥቂት አመታት በፊት ጊዜው ለኢትዮጵያ „ነጻ-አውጪዎች ነው“ ተብሎ በሰፊው ተነግሮ አላስቀምጥ አላስቆም ብለውን ነበር።

ግን እነ ኦነግ እና እነ የደቡብ ሕዝቦች መላ አማራና አማራጭ ኃይሎች…እራሳቸው አንዳንዶቹ የእህዴግ ተከታዮች ጭምር አሁን የት ናቸው? የት ነው ያሉት?

ሻብዕያና ጀበሃ ሕዝባዊ ወያኔና ኦጋዴን አፋርና …እነሱ አሸናፊ ሁነው ወጡ ሊባል ይችላል። ግን ምን አዲስ ነገር ለአገሪቱ ለሕዝቡ ለተከታዮቻቸው አመጡ?
ምን ያህል ሰው ነው እነሱን አሁን የሚከተላቸው? ምን ተአምር ሰሩ? በእነሱ የሚያለቅስ የለም?


ምናልባት በኢትዮጵያ ውስጥ በተነሳው ትርምስ ያተረፉት ቻይና እና ሕንድ አረቦችና አሰፍስፈው መሬቱዋን ለመግዛት የሚጠብቁ የውጭ ኃይሎችና መንግሥታት ናቸው ልንል እንችላለን። አሁን ጥሩ ጨዋታ ተጀመረ!


ሌላው እላይ የተባለውን እንደገና ለመድገም ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ እሰከ ተማሪው ድረስ ባዶ እጁን ነው የወጣው።
ለዚህ ደግሞ የስደተኛው ቁጥር ምስክር ነው። የደሃው ብዛት፣ የሚያማርረው ገበሬ፣ ልጆቻቸውን እያስታወሱ የሚያለቅሱ ወላጆች በቂ ማስረጃ ናቸው።


ኤርትራ ተገነጠለች ተባለ። ያ የተባለውንና የተወራለትን ገነትን/ፓራዲይዝን አገኙ?

በአለፉት ሃምሳ አመታት ….ኦሮሞ ትግሬ አማራ ተባለ። ለመሆኑ„አዲሲቱዋ ኢትዮጵያ ተመስርታ“ አንዲት የምታኮራ መርፌ ብጤ እንኳን አገሪቱዋ ሰርታ የዓለም ገበያ ላይ አወጣች?

ትርፉ በሁሉም አቅጣጫ ኪሳራና ቢበዛ ደግሞ አለመደማመጥ ነው።


መደማመጥ እንኳን (እንደ አረቦቹ በአለመንጫጫታችን በጨዋነታችን የምንታወቀው) ጠፍቶ (በኢትዮጵያኖች መካከል) በያለበት አሁን መደናቆር ነው።

ቀደም ተብሎ የተሰማው እንደ አዲስ ነገር ዛሬ ተነስቶ ይደገማል። ጊዜና ታሪክ መልስ ሰጥቶበት የታለፈው ነገር እንደ አዲስ ተአምር ይነሳል።

ሰው የሰለቸው መፈክር እንደ ገና ይወረወራል። በዘመናቸው በጊዜአቸው ቁም ነገር ያልሰሩ ሰዎች ምንም ነገር እንዳልሆነና እንዳልተደረገ „እንደገና እድሉን ስጡን“ ይላሉ። ችግሩ (የኢትዮጵያ) ችግር ያለው ተራው ሰው ጋ አይደለም።

ችግሩ ያለው ፊደል የቆጠረው ሰው ጋ ነው። ችግሩ ያለው እነሱ ያስተመሩአቸው የሰበሰቡአቸው ልጆችም ጋ ነው።
አገሪቱ ከገባችበት ችግርና ቀውስ የምትወጣው ደግሞ በተያዘው የስህተት ጉዞ ዝም ተብሎ በጭፍኑ ወደፊት ሲራመዱ አይደለም።


አንድ ቡድን ወይም አንድ ድርጅት ወይም ደግሞ አንድ ሰው ብቻውን ወይም „ማዕከላዊ ኮሚቴው“ እንደሚባለው በሚሰጠው ውሳኔና መልስ ላይ ብቻ ተመስርቶ አገር አይገነባም። መልሱ ለተገባው ችግር እሱ አይደለም ።


እንደዚህማ ቢሆን ኑሮ ሶቭየት ኅብረት ምሥራቅ ጀርመን ሓንጋሪና ፖላንድ ሩሜንያና ቡልጋሪያ…ደርግና ኢዲ አሚን ቦካሳና ቦታ ኢያን ስሚዝ …እነዚህ ሁሉ ተንኮታኩተው በአልወደቁም ነበር።

ታዲያ ምንድነው ከተገባበት ላበሪንት- ከአዙሪት ጫካና ከዞረበት መናፈሻ ለመውጣት መንገዱ? መድሓኒቱ? ብልሃቱ? ዘዴው የት ነው ያለው?


በዚህ እትማችንም እንደ አለፈው ጊዜ ይህን ጥያቄ ቀስ እያልን እያነሳን ለመመለስ እንሞክራለን።


ስለ ሰው ልጆች ባሕሪ እናነሳለን። …ክፋትና መጥፎ መናፍስቶችና አጋንንቶች ከየት እንደመጡ እነሱን እንዴት መቆጣጠር እንደሚገባን ከብዙ በጥቂቱ በጉዳዩ ላይ እንመላለስበታለን።


ስለታሪክ እናነሳለን። ስለ ፍልስፍና እንጠቅሳልን። ስለ መንግሥትና አስተዳደር (እነዚህ ነገሮች አንድ አይደሉም) ስለ የፖለቲካ ሰዎች ኃላፊነት ነካ ነካ አድርገን እናልፋለን።


ስለ ታሪክና ስለ ፖለቲካ ፍልስፍና ሲነሳ የሚናደዱና የሚቆጡ የሚያላግጡና የሚያሾፉ፣ አለፈው ተርፈውም „ደማቸው የሚፈላ ሰዎች“ እንዳሉ እናውቃለን።


ግን ደግሞ አለ ታሪክና አለ ፍልስፍና አለ ሃይማኖትና አለ ሞራል አለ ምርምርና አለ ጥናት የኢትዮጵያን ባህልና ኢትዮጵያዊነትን መረዳት አይቻልም።

እንዲያውም አውጥተን አውርደን የደረስንበት አንድ ነገር ቢኖር የአገራችን በሽታ ያለው አንድ ቦታ ላይ ነው።
እሱም „መንግሥት“ የሚባለው ጽንሰ ሓሳብ ላይ ነው። ከእሱ ለየት የሚለው „አስተዳደር“ የሚባለውም ነገር ላይ ነው። „አገር“ የምባለውም ቃል ትክክለኛ ትርጉም ተፈልጎ በአለመገኘቱና መልስ ስለአልተሰጠውም እንላለን።

እነዚህ ሦስቱ (ስቴት ኔሽን ገቨርንመንት) የሰው ልጆችን አሰባስበው በተለያዩ ባህሎችና በተለያዩ ትውፈት በተለያዩ ትሩፋትና እሴቶች …ሥነ -ምግባር እንዲኖሩ ያደረጉ ኮንሰፕቶች (የቻይናው ከሕንድ ይለያል የጀርመኑ ከፈረንሣይ…) በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዘንድ „አንድ“ ተደርገው ተጨፍልቀው በመታየታቸው ነው።

ይህ ደግሞ ሁሉም ሕዝቡም አገሩም መንግሥትም አስተዳደርም „የኔ ነው“ ወደሚለው የአንድ ቡድን„ጠለፋ ይወስደናል።
ዕውነቱን ከተናገርን ከዚያም አልፎ ይሄዳል።
…አገርም ብቻ ሳይሆን የአገር ንብረትም መሬቱም ባንኩም ሠራዊቱም ጦሩም የጸጥታ ፓሊሱም ትምህርት ቤቱም ዩኒቨርስቲውም ንግዱም ሕንጻውም መንገዱም እርሻውም „የአንድ ፓርቲ የአንድ ቡድን …“ ተደርጎ ይታያል። ከዚያም አልፎ “አንተ አታስብ እኔ ነኝ ለአንተ የማውቀውም” ወደሚለው ዛቻና ጥላቻም ተሸጋግሮአል።

ምን ይደረግ ነገሥታቱም እንደዚህ አድርገው አገሪቱዋን ቀደም ሲል ስለአዩ ወጣቱ ትውልድም “ለእሱ ብቻ” በየፊናው „አደራ ተብሎ የተሰጠው“ ይመስለዋል።

ይህ ደግሞ ወደ „…ይገባኛል …ለእኔ ብቻ ይገባኛል“ የሚል ቋንቋና አመለካከት ፍልስፍና የድርጅት መሪዎችንና ተከታዮቹን ወስዶ ኢትዮጵያን እዚህ አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ አድርሶአታል።

ይህ ብዙ ነገሮችን እንድንረዳ ይጠቅማል።

የኢህፓና የመኢሶን „ጠብ“ የምንረዳው የደርግና የሻብዕያ የጀበሃና የሻብዕያ የወያኔእና የኢዲዩን የኦነግና የወያኔን የደቡብና የኦጋዴን አንዱ ከአንዱ ጋር ግንባሩን እየቀየረ „መዋጋት“ የምንረዳው „አገሪቱን ለመግዛት ሕዝቡን ለመምራት መሬቱን ለመያዝ በትረ-መንግሥቱን ለመጨበጥ ሠራዊቱን ፓሊሱንና ፍርድ ቤቱን እሥር – ቤቱን ለመቆጣጠርና ለማዘዝ …እኔ ብቻ ታሪካዊ ኃላፊነት አለኝ ይገባኛል“ ከሚለው ፍልስፍና የመነጨ ነው። ችግራችን እሱ ነው።መኳንንቱም፣ መሣፍንቱም ይህን ብለው ይህ ከአልሆነ ብለው ተናንቀዋል። ነገሥታቶችም።

ይህን የሚቃወምና የሚተች ሌላም መፍትሔም አለ እኮ እስቲ እሱን እናሰላስል የሚል ሰው ወይ „ይደመሰሳል“ ወይ „ ይቀጣል“ ወይም አገሩን ጥሎ „እንዲሰደድ“ ይገረጋል። ወይም ደግሞ አፉን በጠበንጃ ፍረሃት ይዞ እንዲቀመጥ ይገደዳል። አልፎም የስም ማጥፋት ዘመቻ ይወርድበታል።


ነገሮችን ለመረዳት፣ ስለ እብሪተኛው ቄሣር ስለኔሮም ያነሳነው ለዚህ ነው።

እሱን ብቻ አይደለም።

ስለ እባብም አንስተናል።

ስለ ሰይጣናና ስለ ሳጥናኤል ተርከናል። የፕላቶና የሶቅራጥስንም ምክሮች ጎትተን የጠቆምነውም ከገባንበት ለመውጣት ማሰብ ማጥናት ማመዛዘን አለብን የሚለውን ጥበብ ለመጠቆም ነው።

ሰይጣን አለ ወይ ? ብለን እራሳችንን ጠይቀናል። ለመሆኑ እንደሚባለው እኛ ጥቁሮቹ ተረግመናል? ወይስ ነጮች ተመርቀዋል? የሚለውንም ጥያቄ ሰንዝረናል።


ጥፋተኛው ገዢው መደብ ብቻ ሳይሆን ሰዎችም „ጠንካራ ክንድ“ የማየት ድክመት እንዳላቸውም አብረን አንስተናል።


ወረድ ብለን ከስንት አመት በሁዋላ ተለያይተው ስለ ተገናኙት ስለ አዛውንቶች ጉባዔም -ከዚህ ሁሉ የትርምስ ዘመን በሁዋላ – ስለ እነሱም በዚሁ ጽሑፋችን አንስተናል። ተገናኝተው እነሱ ሰለካሄዱት ወጎችም ከብዙ በጥቂቱ ጠቅሰናል። ይህ ደግሞ ከገባንበት ላበሪንቱ ለመውጣት በሚደረገው ጥረትና ሙከራ ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል የሚያሳይ ይመስለናል።
ፖለቲካና የፖለቲካ መፍትሔዎች በንግግር እንጅ በጡንቻ አይፈቱም። ድል አድራጊውም ይመስለዋል እንጂ ድሉ ቋሚ አይደለም። ሁሉ ነገር ይቀየራል ። ይለወጣል። ይሻሻላል። ያልፋል። ሰውም ይሞታል አዲስ ነገርም ይበቅላል። ከጨለማ በሁዋላ የጸሃይ ብርሃን ቦግ ይላል። ጥያቄው ዱሮም አሁንም በምን አይነት ሥርዓት ውስጥ በእሱም ሥር እንኑር የሚል ነው?

ሰው ሰይጣን ነው። ሰይጣንም ሰው ነው። ሁሉ ሰው ግን ሰይጣን አይደለም። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ማንም መብቱን የማይረግጠው ነው።

መልካም ንባብ።
ይልማ ኃይለ ሚካኤል
ዋና አዘጋጅ

—-

logo-circ-reg

—-

ለ አእምሮ ሚያዝያ 2006 / April 2014 / እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 08

Advertisements

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s