ጊዜና ሰው የአዛውንት ጉባዔ

ጊዜና ሰው
የአዛውንት ጉባዔ

ጊዜና ሰው የአዛውንት ጉባዔ-7

ማሳረጊያ ከምግብ በሁዋላ በዚያ በበጋ ወራት ወደ ማምሻው ላይ ከቡና ጋር የቀረበው ጣፋጩ ዲሰርት መንጋጋን ብቻ ሳይሆን ዓይንንም ከሩቁ ማርኮ ምራቅ የሚያስውጥ ነው። ማነው ኢትዮጵያ ዲሰርት የላትም? እሱንም አታውቅም የምለውን ጥያቄ አንዴ ያነሳው? ይህን ቢያይ እሱ ደንግጦ አፉን ይይዛል።

ከዓሣና ከጎድን ጥብስ ከዶሮ መረቅና ከቀይ ወጥ ከአልጫና ከአታክልት ከምስርና ከሽሮ ከክ ወጥና ከሽቡራ ዓሣ ከክትፎና ከቁርጥ ከአይብና ጎመን ከፍርፍርና… ከቅልጥም ከፍትፍትና – የአገራችን ምግብ ከቻይና ቀጥሎ በዓይነቱም በብዛቱም ሁለተኛ ነው ይባላል – የግሪክ አማልክቶች ታላቁ የመጀመሪያው ደራሲ ሆሜር እነደ ጻፈው ግሩም ምግብ ንጹህ አየር ደስ የሚል አስተናግዶ ሲያምራቸው ወደ ኢትዮጵያ ይወርዱ ነበር ይላል – ከእነዚህ ሁሉ ግሩም ጠረጴዛው ላይ ከተዘረጉት የባህል ምግቦችና የቀቃይ ጥበቦች በሁዋላ ለማሳረጊያ ከቡና ጋር የቀረብልን ዲሰርት ጣፋጩ የነጮች አይስ ክሬም አልነበረም።

food

ጠረጴዛው ላይ ከለተለያዩ አበባዎች ጋር የተለያዩ ፍራ ፍሬዎች መሶቡ ላይ በመልክ በመልካቸው ተቀምጠዋል። ብርቱካን ሎሚ ፓፓያ ማንጎ አናናስ መደሪን የወይን ዘለላ ሙዝ ፕላም ሸሪ ሮማንና …ከየት እንደመጣ አይታወቅም ትርንጎ ተዘርግተዋል። በፈላ ዘይት-ድስት ውስጥ የተጠበሱት ከዚያ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ክብ የአናናስ ቀለበቶችና ለሁለት ከመሓከሉ የተሰነጠቁ ሙዞች የፈላው ዘይት ውስጥ ገብተው ቀለማቸውን ቀይረዋል። በሁዋላ የማር ወለላ ፈሶባቸዋል። ከርሸም ሲሉና ከሞቀው ማሩ ጋር አፍ ውስጥ ሲፈሱ ግሩም ናቸው።

fruits


ይህን ቀምሶ ነው አንዱ „ይህማ ያስኮራል! በአገራችን „የጠፋው ዲሰርት አለ እንዴ?“ ያለው።
ትንሽ እሳት የመታው ሽንኮራም ሞቅ ብሎ ተቆራርጦ ቢመጣ አልጠላም አለ ሌላው።ጥርስ ቢኖር አይደለ? …ከሳቅ ጋር አለ- ሦስተኛው።
„ጥንቅሽ ብትል አይሻልም?“ አለ ሌላው።
አይስክሪም ለሚፈገልጉት በሞቀ እንጆሪና ቀይ የቡና ፍሬ የሚመስል ሸሪ በተገመሰ ሮማንና በመንደሪን በኮክና በጥቁር ወይን ፍራ ፍሬዎች አንድ ላይ (እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ ይበቅላሉ) በጎድጓዳ ሳህኖች ተዘጋጅተውና አሸብርቀው ከላዩ ላይ ክሬም እንደ አክሊሊ ጣል ተደርጎ ቀርቦላቸዋል።
ይህን ሲቀምሱት አንዳዶቹ „አበዱ“።

ከሠላሣ አመት በሁዋላ ጓደኞቼን ለማየት ጓጉቼ ነበር የገባሁት ። የቀመስኩት ድግስ የሚገርም ነው።

ስነሳ ከቤቴ ተቀይረው ይሆን? አርጅተው? ደክመው? ወይስ አስተሳሰቦቻቸውን ለውጠው? ምን ያህል ዕውቀት ሰበሰቡ? ምን ያደርጋሉ? ልጆችስ አሉአቸው? ተጋብተዋል? ተፋተዋል? ልክ አውሮፓ ያኔ ገብቼ አካባብዬን መጽሓፍቶችን ሰውን ሴቱን ታሪኩን ለማወቅ የጓጓሁትን ያህል አሁን በእስተእርጅና ስለ የቀድሞ ጓደኞቼ -ከአየሁዋአቸው ብዙ ዘመን ነውና ተቿኩዬአለሁ።

በተለይ ያን የተማሪዎች መሰባሰቢያ አዳራሽ/አዳራሶች ከሁሉም በ1974 ዓ.ም (እአአ) የተሰበሰብንበት ሂትለር ያኔ ያሰራው ምናልባት ወደ አንድ ሺህ የምንሆን ወጣት የአውሮፓ ተማሪዎች ከየትነውየመጡት ከሞስኮ እስከ ፓሪስ ከለንደን እሰከ ስቶክሆልም ከለንደን እሰከ ሮም አምስተርዳም ካርቱም የተሰበሰብንበት የኦሎምፒክ ስታዲዮም(የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ሲተላለፍ አንዴ አይቼአለሁ) እሱን እንደገና በሚቀጥሉት ቀናት ለማየት በጣም ጓጉቼ ነበር።

ከዲዘርት በሁዋላ ነው የደፈረው ኮኟኩን ሌላው ውስኪውንና ጂንቶኒኩን አረቄውንና ኡዞውን የተቀሩት በዚያ ሙቀት የተቃጠሉት ደግሞ ወሃና ነጭ ወይናቸውን ከሲጋራቸው ጋር ይዘው ወደ ሳሎኑ ዘለቁ።
ከብት የሚረባበት ወተት ያለበት አገር – እኛ እኮ ቻይና ወይም ጃፓን አይደለንም- ጣፋጩን አይስክርም መሥራት (ማቀዝቀዣውና የስኳር መሥሪያው ሸንኮራ እስካለ ድረስ ማንም የሚሰራው ነው።
(ጣፋጭ ነገርን ከምግብ በሁዋላ- እንዲያው ታሪክን ለመጥቀስ- መቅመስን አውሮፓን ያስተማሩት ያስተዋወቁት ደግሞ -አያውቁትም ነበር ቱርኮች ናቸው። ስለዚህ የሰው ልጆች ሥራ ነው።)
መለኪያዬን ይዤ እኔም አጥንቴ በዚያ የከተማ ዙረት መድከሙ የታወቀኝ ሶፋው ላይ ዝርግፍ ብዬ የተቀመጥኩ ሰዓት ነው።wein

ድካም የጨመረብኝ የቤቱ ደረጃ ነው።
ያን ረጅም ደረጃ -ከተማይቱዋን ስቃኝ ረፍዶ ስለነበር- በዚህ ዕድሜዬ ረስቼው ነው እንጅ – ይህን አሁን ሳየው ማድረግ አይገባኝም ነበር – አንዴ ሮጬ ቁና ቁና መተንፈስ የጀመርኩት ከምግብ በፊት ነው።
በሩን በፈገግታ የከፈቱልኝ ልጆች አስደንግጠውኛል።

ከያዙት ሰታቴ ሳህን ላይ ይህን? ወይስ ይህን? ይውሰዱ ! ብለው ከማስተናገዳቸው በላይ ኮረዳዎቹ -አንዱዋ ነጭ ጠጉር አላት ሌላዋ ቀይ አንደኛዋ ጥቁርና አራተኛዋ በአለ ቡና ቀለም- በዕድሜአቸውም በቁንጅናቸውም በግልጽነታቸውም በአነጋገራቸው የቀድሞውን የወጣትነት ዘመኔን የሰባውን አመተ ምህርት የበርሊን ኑሮ እንዳለ አስታወሱኝ።ጊዜና ሰው የአዛውንት ጉባዔ


ገጽታቸውና ፊታቸው በየዩኒቨርስቲው የምግብና የሌክቸር አዳራሽ በየሰላማዊ ሠልፉና በየቲች ኢኑ በ የመናፈሻውና በየቡና ቤቱ በተማሪዎች መኖሪያ ቤትና እነሱ በነበራቸው ቢራ ቤቶቹ በየመንገዱና ሱቁ ያኔ የማውቃቸው አብረውኝ ያኔ የነበሩ ተማሪዎች መሰለኝ። ዛሬ እነሱ የት እንዳሉ? ምን እንደሚሰሩ ጓደኛዬን እጠይቃለሁ ነገሩን አሳደርኩኝ።


የጀርመኑን የቀዘቀዘ ነጭ ወይን ጠጅ „አመሰግናለሁ“ ብዬ በአልተረሳኝ ጀርመንኛዬ ከአንዱዋ ተቀብዬ አንድ ሁለት በረዶ እንዳይመታኝ ጣል አድርጌበት አምቦ ወሃ በላዩ ላይ ከልሼበት ወደ ውስጥ ጓደኞቼ ወደ ተቀመጡበት ሳሎን በሁለቱ ኮረዳዎች ታጅቤ እየተመራሁ ወደ ውስጥ ገባሁ።


በ1999 ዓ.ም. (እ.አ.አ) ስድሳኛውን አመቱን ያከበረው እኛ ሁላችንን እንደገና የጋበዘን ወዳጄ መሓል ቆሞ ሰውን በሙሉ ከተለያዩ ቦታ የመጡ ስለሆነ እገሌ ሙያው… እንደዚህ ነው። እገሌ ደግሞ…የተማረው ይህን ነው…. እያለ ያስተዋውቃል።

የደረስኩበት „…ይህ አሁን ሸብቶ ጨዋ ሰው መስሎ ዝም ብሎ መሓላችሁ ተቀምጦ የምታዩት ሰው በዘመኑ ቢያገኛችሁ ይሻጣችሁ ነበር። የፖለቲካ ዝንባሌው አትርሱት በዚያ በስድሳው መጨረሻና በሰባው አመተ ምህረት ሰው ሁሉ ጸረ-አሜሪካን በነበረበት ዘመን እሱ የአሜሪካንና የሆሊውድ የቴክስና የዘናጮች ወዳጅ ነበር። በሁዋላ ምናልባት ሶሻል ዲሞክራት እንኳን ብትሆኑ ይሻላል ይለን ነበር።“ እያለ የሚያስተዋውቀው ሰው ላይ ነው።

„ይህኛው ደግሞ ከአራት ጓደኞቹ ጋር ፔኪንግ ሪቪውን የሚያነቡ ማኦኢሰቶችና እነ ቹኤንላይንና እነ ሁዋ ኩዋ ፌንግን የሚያመልኩ ነበሩ።“ ብሎ ይቀልዳል።


“ ካላቸራል ሪቮሉሽንን የሚያደንቁ ቴንግ ሲያዮ ፒንግን የማይወዱ በሁዋላ ደግሞ እሱ አሸናፊ ሁኖ ሴንትራል ኮሚቴውን ሲመራ ፊታቸውን አዙረው የማኦን ሚስት ዓይኑዋ አፈር ይብላ ያሉም ነበር…“ የሌሎቹን ስም ይጠራል።

protest-and-age


„እሱ ደግሞ በቀኝ በኩል የተቀመጠው ወዳጄ -ምንም እንኳን አብሮ አደጌ ቢሆንም ልቡን ያኔ የሳበው ቻይና ሳይሆን ሞስኮ ነበር።“ ይላል።


ቤቱ መቼም ሰፋፊና ረዣዥም ክፍል አለው። በቆሙበት ሁሉ ሁለት በር በግራና በቀኝ ይታያል። ጣራው ሦስት ተኩል ወይም አራት ሜትር ይሆናል።

እራስህን እወቅ (ርዕስ አንቀጽ/Editorial)

ክፍሎቹን ጥንታዊ የግሪክና የሮማ ቅርጾች ሥዕሎችና መጽሃፍቶች ሞልተውታል። እኔን ትዝ የሚለኝ ከአእምሮዬ በርሊን ስደርስ ያልወጣው የዱሮ የተማሪዎች መኖሪያ ቤታችን ነበር።

ከነበሩት ሴቶች ውስጥ ለአንዱዋ ዕድል ሰጥቶ እነሱን በማስተዋወቁ ቀጠለ።


እነደገና አንደኛዋን እሷ አጠገብ የተቀመጠቺውን ዘሎ እንግዳ አስተናጋጁ „…ያ ደግሞ „ በጣቱ እያሳየ „…የቀድሞውን የዘውድ አገዛዝ የኃይለ ሥላሴን መንግሥት አልጋውን የኢትዮጵያ መፍትሔ እሱ ነው እያለ ፊት ለፊት ይደግፍ ነበር…“ የሚለውን ሰው ጠቆመ። „የተማሪዎች ስብሰባም ስንሄድ ቆይ `ዋጋሽን` አንድ ቀን ታገኚአለሽ እያለ ይዝትብን ነበር…“ እያለ የጠረጴዛው ግራና ቀኝ የተቀመጡትን በስማቸው እየጠራ ሲያስተዋውቅ በመካከሉ አንድት ቁንጅናዋ በምንም ዓይነት ከዚህ ሁሉ ዘመን በሁዋላ ያልከዳት ሳቂታዋ ወይዘሮ…ሴት ልጅዋን አስከትላ ሳሎን ውስጥ ገብታ ጠቅላላ አተኩሮውን በሁለት ደቂቃ ስባ እሱዋ እራሱዋ እንግዳ ሳትሆን ቤተኛ ሆና ያ ጎደለ ይሄ ቀረ ማለት ጀመረች።


ዱሮውንም በቀልጣፋነቱዋ እወዳት ነበር። በፈገግታዋና በጥቅሻ ያኔ በርሊን ስትመጣ አንገታችንን የምታዞረው ልጅ አሁን ቤቱን በአንዴ ተቆጣጠረች።


ይዛት የመጣች ልጅዋ ከመቅላቱዋ ሌላ (አባቱዋ ፈረንጅ መሆን አለበት)ቁርጥ እናቱዋን ነው።
እሱዋን ማስተዋወቅ አያስፈልገኝም ብሎ ወደ“ አናርኪስቶቹ“ ወደ ሰሜን ኮሪያኖቹ ወደ ቼና ወደ ካስትሮ „ተከታዮች „ ከእነሱም ጋር ወደ ሁለቱ „አልባኒስቶቹ“ ፊቱን አዞረ።


እንጂነሮችና መሓንዲሶች ነበሩ።ቄሶችና ዲያቆኖች ተገኝተው ነበር ። እነሱ ዝም ብለው ይህን ጉድ ይህን ታሪክ እየጠጡ ያዳምጣሉ።


„እሱ አቶ…የማሪያምና የክርስቶስን ሥዕል ግድግዳው ላይ ሰቅሎ ሲጸልይ እነ እገሌ የማርክስና የሌኒን የስታሊንና የ…ፎቶዎች የቤት ግድግዳቸው ላይ ይሰቅሉ ነበር“ አለ።


„ እሱ ድርሳነ ሚካኤልን ሲያነብ እኛ ማርክስ …“ ሲባል ሁሉም ይስቃሉ።


አንድ ወጥት ወንድ ልጅ እግሩን አጣምሮ አባቱ አጠገብ ቁጭ ብሎ ይህን ሁሉ ጉድ በሚችለው አማርኛ ለመረዳት ይሞክራል። ከእሱ አጠገብ የግሪክ ሐውልቶች አሉ። ግድግዳው ላይ የንግሥት ሳባ ጉዞ ግሩም ተደርጎ ተስሎ ተሰቅሎአል።


በሁዋላ ስሰማ በሩ ላይ ከተቀበሉኝ ሴቶች ውስጥ አንደኛዋ የእሱ የተቀመጠው ጎልማሣ እህት ስድሳኛውን አመቱን ያኔ ያከበረው ጓደኛዬ ልጅ/ልጆች ናቸው።


እኛም ያኔ በእነሱ ዕድሜ በነበርንበት ዘመን- በስድሳውና በሳባው አመተ ምህርት „ያዙኝ ልቀቁኝ“ እንል ነበር። እነሱ ግን ረጋ ያሉ ናቸው።“ እያልኩ እራሴንም ትውልዴን እታዘባለሁ።Axum Art

ትንሽ ቆይተው „…ሁላችሁም ጥቁር ናችሁ። ለምንድነው እኔ ትግሬ እኔ ኦሮሞ አፋር ሱማሌ ሓማሴን እያላችሁ የምትጣሉት ?“ ብለው ሰውን ሁሉ ይጠይቃሉ።


ለዚህ መልስ የለም። ዝም ብሎ ታለፈ። ሌላም አርዕስት ተነሳ።


„የፕሮሌታሪያን ያኔእንደሚባለው የላብ አደሩ/ወዝ አደሩ አምባገነን መንግሥት…“ምን ታይቶን ነው ይህን ሐሳብ ርዕዮተ ዓለም የተቀበልነው? አለ አንደኛው።
ቤቱ ሳቀ። -ዱሮ ይህ ቢሆን መግቢያም ቦታ የለም።…ትወገዛለህ! ትኮነናለህ!

 

redflag


ለእነሱ -ለወጣቱ ትውልድ እንደዚህ ዓይነቱ ፖለቲካ ምናቸውም አይደለም። „ለመሆኑ ለዚህ አመለካከት ለመሞት ዝግጁ ነህ ወይ ? ተብለው ቢጠየቁ …ምን አልክ?“ ብለው የሚቀልዱ ናቸው።
ወደ ሰባው መጨረሻ ላይ ቀስ እያለ ብቅ ያለው ከሰማንያው ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የተደራጁበትን ቤት እየጣሉ ወደ „ነጻ-አውጪዎቹ „ እየፈለሱ የገቡትን ሰዎች ሰውዬው እንደጀመረው በቦታው ላይ ነበሩ ማስተዋወቁን ቀጠለበት።


ቆይቶ በአርባ አመት ውስጥ ስንት ጎዳና ያ የተማረ ሰው ሁሉ እንደተጓዘ ይተረክ ጀመር።


ለመሆኑ ከዚህ ሁሉ ድካም በሁዋላ… ምን አገኘን? ተባለ። ….ምን አተረፍን? ለመሆኑ ለአገራችን ምን ሰራን? የትስ ደረስን? የት ነው ቀልጠን የቀረነው? …ስንቱ ሞተ? ለምንስ ሞቱ?… እገሌ አሁን የት ነው ያለው? የሚሉ ጥያቄዎች ተነሱ።


በመጨረሻውስ ኢትዮጵያ ምን አገኝች? ተባለ።…ለዚህ ሁሉ ጥያቄና መልስ ፍለጋ ምሽቱ እንዳለ በውይይት ፉት ብሎ አለቀ።


አንድ ፈረንጅ ሲቀልድ „ኢትዮጵያ- ኤርትራ በመገንጠሉዋ- በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ሁለት ድምጽ ያላት አገር በአሁኑ ጊዜ እሱዋ ብቻ ናት“ ብሎ የቀለደብን ነገር ተነሳ። እነሱም ይህ በተባለላቸው ማግስት ማንም እንደሚያውቀው ጦር ተማዘው ተዋጉ። ይህ ደግሞ ሌላ እራሱን የቻለ አርእስት ሁኖ ተከፈተ። መቼም እንደ ኢትዮጵያኖች “ክርክር” የሚወድ ሕዝብ የለም። የቆየ ባህላችን ነው። ዱሮ ሥርዓት ነበረው። አሁን…


ነገ የመርከብ ሽርሽር እና የበርሊን አጥር ጉብኝት ዝነኛው የኦለምፒክ ስታዲዮም አዳራሽ… ፕሮግራም ስለአለን በጊዜ ብንተኛ ሲባል ሰው ሁሉ ተቃወመ። ከዚህ ሁሉ አመት በሁዋላ ወይኑ እየተቀዳ ማን ይተኛል!


ቀልዱ መጣ። ዘፈን ተዘፈነ። ግጥሙ ወረደ። የዱሮ ታሪክ ተነሳ።አለ ጣጣመንጣጣ የምንሄድባቸው ዳንስ ቤቶች የተማሪ ማህበር ጉባዔ በበርሊን ከተማ በትልቁ ስታዲዮም በዚያን ጊዜ በተለኮሰው የክፍፍሉ ዘመን የነበሩ ነገሮች ሁሉ ተጠቀሱ። የፌደረሼሽን መቋቋም የአውሮፓ ማህበር ለሁለት መሰነጠቅ የደርግ ደጋፊዎች መሰባሰብ…ወዘተ …ወዘተ… ታሪክ ቀጠለ።


እንደገና የዚህ ሁሉ ጉዞ ድካም ለአገሪቱ ምን አመጣ ተባለ?
ቁም ነገሩ እሱ ሳይሆን አንደኛዋ ዝም ብላ የምታዳምጠን ጓደኛችን እንዳለችው „…ቁም ነገሩ ወንድሞቼ ያለው፣ ያለፈው ታሪክ ላይ መነታረክ ሳይሆን ቁም ነገሩ ያለው እኛ የቀረነውና የተረፍነው ሰዎች እንደዚህ ተገናኝተን ስንጫወትና ያለፈውን ዘመን ግንዛቤአችን ውስጥ አስገብተን አንዳንዴ የሚያከራክር ቢሆንም መነጋገር አብረን መቻላችን ነው።….መነጋገር በመካከላችን እሰከ አለ ድረስ ደግሞ ኢትዮጵያ አለች ማለት እንችላለን። ዱሮ ተለያይቶ ተበታትኖ የነበረ ሰው አሁን እኛ እንደምናደርገው በየአለበት መነጋገር ከጀመረ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው። ዘመኑ ተቀይሮአል።enlightenment

ይህ ደግሞ ተቀራርቦ መነጋገሩ የአገሪቱ የኢትዮጵያ ተስፋ ነው።እንደዚህ ዓይነቱ ነገር መኖር ደግሞ አዲስ አመለካከትን በሰው ልጆች ዘንድ የሚፈጥረው ነው። በእኔ ግምት“ ቀጥላ እንዳለቺው“ የዕብደት ዘመን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ትውልድ ያለ ነገር ነው።“


„ልንገራችሁ“ አለች አየር ስባ። „የሓዘን ዘመን አለ። የአእምሮ ቀውስ ዘመን አለ። የኢኮኖሚና የፖለቲካ ክሪዝም ዘመን አለ። ኢትዮጵያን በአለፉት አርባና ሃምሣ አመታት የመታት ቀውስ አውሮፓን አንዴ በሃያኛው ክፍለ -ዘመን ከመታው የአእምሮ ቀውስ ጋር የሚነጻጻር ነው። ከማድሪድ እሰከ ሞስኮ ከባልካን አስከ ፓሌርሞና ኦስሎ የተለያዩ አይዲኦሎጂዎች ተነስተው ይህቺን አህጉር አተራምሰዋታል።“


„ታዲያ አሁን እኛ ከገባንበት ቀውስ ልንወጣ እንችላለን ነው የምትይው?“ አላት አንዱ።


አዎን አለ-ሌላው ጣልቃ ገብቶ።


እንዴት? የሚባለው ጥያቄ ተወረወረ።


„…ዘለዓለማዊ አስተሳሰብ፣ጊዜ የማይሽረውና ጊዜ የማይቀይረው አመለካከት፣ የለም። እራሱ የሳይንስ ምርምር እንኳን ቢሆን ከተወሰነ አመት በሁዋላ የሚቀየር የሚለወጥ የሚሻሻል ነው። ከዚያም በላይ ሁላችንም ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ -ሕይወት ገደብ አላት- ከዚህቺ ዓለም ሁላችንም ተሰናብተን የምንሄድ ነን። የበርሊን ግንብ ይፈርሳል።ሶቪየት ሕብረት ይወድቃል።ኮሚኒስቶች ሥልጣን በሕዝብ ድጋፍ እንደወጡት በሕዝብ አመጽ አንድ ቀን ወድቀው ሥልጣኑን ያስረክባሉ ብሎ የገመተ ሰው አልነበረም።ግን እንደምናየው እነሱም ሄደዋል።…“ አለች።

21stcentury


ዝምታ ለጊዜው ሰፈነ። ቀልደኛው ጓደኛችን ለሞቱትም ለተረፉትም ለአሉትም ለተወለዱትም መለኪያችንን አንስተን እንጠጣ አለ። ሁሉም መለኪያቸውን አነሱ።

አንደኛው ለእናት አገር ለኢትጵያ ቀስ ብሎ አለ።


የተሰበሰብንበት ምክንያት እላይ እንደተጠቀሰው ጓደኛችን ስድሳኛውን አመቱን ከእኛ ጋር ለማክበር ከስድስት ወር በፊት በ1999 ዓ.ም. (እአአ) በአደረገልን ጥሪ መሰረት ነው።ቀደም ብለው የደረሱት እንዳጫወቱኝ እነሱ ሲደርሱ ሽንኩርቱ ጅንጅብሉ ሥጋው ኳኳ እያለ ሰው ሁሉእ የተተረማመስ ሲከተፍ እነሱ ያዩትን ለአልነበረነው አጫውተዋል። ሰውዬው ፊውዳል ነው ብለው እሰከ መጠራጠር ድረስ እንደሄዱም ነግረውኛል።


ከአንድ ሳምንት በፊት ከፈረንጅ ጓደኞቹ ጋር በተመሳሳይ ድግስ አብሮ ከእነሱ ጋር አክብሮአል። የጥሪው ደብዳቤውና የስልክ ንግግሩ ማርኮኝ ነው የመጣሁት። ከዚያም በላይ ስንት አመት ያላየሁትን ጓደኞቼን ለማየት ነው።


ደብዳቤው እንደዚህ ይላል።….ይቀጥላል። ይቀጥላል።

ዘመነ፥ብርሃን / Enlightenment

ዘመነ፥ብርሃን / Enlightenment

LoveEthiopia

እስከ ነገው ብርሃን በትዝታ እንቆይ

ለ አእምሮ ሚያዝያ 2006 / April 2014 / እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 08

Advertisements

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s