ምድራዊ ገሓነም- መጥፎ መናፍስትና አጋንንቶች

ምድራዊ ገሓነም
መጥፎ መናፍስትና አጋንንቶች

ሰይጣን ሰው ነው ሰውም ሰይጣን ነው

ምድራዊ ገሓነም መጥፎ መናፍስትና አጋንንቶች

…ገሓነም ባዶ ነው። አጋንንቶች ሁሉ ከዚያ አምልጠው ሸሽተው የሚገኙት እኛው መካከል ነው። አንዳንዶቹ አታላይ መሲህሆች ናቸው።ሌላው በነብይ ስም ቆሞአል። ነጻ-አውጪ አለ።ከችግር ጠባቂ ዘበኛ።እራሱን ከመሬት ተነስቶ የነፍስ አባት ያደረገ አለ።መንገድ መሪ።የጦር አዛዥ ፊታውራሪ።አርበኛ መሳይ። ከባውን የቀየረ ቄስ። ሰባኪ።

ግማሹ ብድግ ብሎ ከመሬት ተነስቶ እራሱን የሾመ አገረ ገዢም ወጥቶታል።

ዕውነተኛውን ከአታላዩ ዱሮም ዛሬም እንዴት ማወቅ እንዴት መለየት ይቻላል?

በሥራው!

የሮሙ ቄሣር ኔሮ በዕብሪት ልቡ አብጦ – እሱ እራሱን አምላክ አድርጎ አይቶም ሊሆን ይችላል – እሳት ለኩሶ ከተማይቱን ሲያጋይ ሠገነቱ ላይ ቁጭ ብሎ ሙዚቃ እየሰማ እና ክራሩን እየተጫወተ ሰው ሁሉ ነፍሱን በዚያን ሰዓት ለማዳን ብድግ ብሎ ሲያመልጥ ከተማይቱዋም በዚያን ዘመን ያኔ ፈርሳ አመድ ሲትለብስ ትርምሱን እግሩን ዘርግቶ – በዘመኑ የነበሩት እንደጻፉት እና እንዳስተላለፉልን እሱ ከላይ ሁኖ እሱ እየሳቀ ግርግሩን ይመለከት ነበር።

ለቀናት ለተራቡ አንበሳና ነብር ክርስቲያኖችን ወርውሮ እሱ በሌላ ጊዚያቶች እዚያው ኮለሲዩም ስታዲዮም ውስጥ -ዳቦና ጨዋታ ለተራው ሕዝብ በሚባለው ፍልስፍና- በአውሬዎች እነሱ ሲቦጫጨቁ እሱ ቄሣሩ ከትዳር ጓደኛዋ ጋር ወይኑን እየተዝናና ይጎነጭ ነበር ።christenverfolgung-nero

ሳይናገር በአውራ ጣቱ ብቻ ይወስናል። ደስ እንዳለው አንዴ ወደ ላይ ወይም ወደ ታች በማሳየት በግላዲያተሮች ሕይወት እዚያው (ጠበቃ የለ) ፍርዱን ይሰጣል። አጃቢዎችም የእሱን ፊት እያዩ -ደስ ለማሰኘት አብረው ይስቁ ይሳለቁም ነበር።
በአረመኔነቱ በታሪክ የሚታወቀው ኔሮ ብቻ አይደለም። አነጣጣሪ ተኳሾች አሉ። እሥረኛ ሲገርፉና ሲያሰቃዩ የማይከብዳቸው ሰዎች ብዙ ናቸው።ሲያዋክቡ ሲቆጡ የሚረኩ አሉ። አብዮታዊ እርምጃ ሌላው አስገራሚ ውሳኔ ነው።
አንዱ የሮማው ቄሣር በእብሪት መንፈስ ተነሳስቶ ጥቁር ፈረሱን የሕዝብ እንደራሴ አድረጎ ሾሞታል። ቄሣሩም ካሊ ጉላ ይባላል።

ይህን ለመረዳት ጨርሶ ጥንታዊ ሮም ላይ መቆየት አያስፈልግም።


በመካከለኛው አፍሪካ በቅርቡ አንዱ ጎረቤቱን ገድሎ ታፋውን ቆርጦ እዚያው የፈረንሣይ ወታደሮች እያዩት በያዝነው 21ኛው ክፍለ ዘመን በልቶአል። ሌሎቹ ቤንዚን አርከፍክፈው የወደቁትን ጎረቤቶቻቸውን ተመልካቹ እያጨበጨበ አቃጥለዋል።
አይሁዶችን ሒትለር ሰብስቦ ፈጅቶአል። ስታሊን „ጸረ-ሶዣሊዝም „ የሚላቸውን ለየት በአለ መንገድ ሳቤሪያ አድርሶ እነሱን ጓደኞቸን ወደ ሞት ሽንቶአል።
በቀበሌ እጅ በአብዮታዊ እርምጃ በጫካና በጦር ሜዳ …ኢትዮጵያኖች ከዳተኛ ተባብለው እርስ በእራሳቸው ተጨራርሰዋል። በኡጋንዳ ስምንት መቶ ሺህ ሰው አልቆአል። በሱማሌ ቅጥራቸው አይታወቅም።
ለምንድነው የሰው ልጆች/ የሰው ልጅ የሌላውን ሰው ደም የወንድሙን ከመሬት ተነስቶ በከንቱ የሚያፈሰው?
ሰይጣን ስለተጠጋቸው? አእምሮአቸውን አጋንንት ሰለ አሸነፈው? በመናፍስቶች ስለተከበቡ? ልባቸው በሳጥናኤል ስለ ተሰለበ? ጋኔን ስለሚጋልባቸው? ወይስ እነሱ ወደው ጋኔን ስለሚጋልቡ?

መልሱ መልሶቸ ቀላል አይደሉም።

“..እኛን ጥለህ አነተ መሄድህ ነው።… እንዴት ብለን እንጸልይ ብለው ክርስቶስን ሲጠየቁት:-
„…አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ…ከክፉ! ከክፉ ሁሉ አድነን ብላችሁ…ጸልዩ አላቸው።“


በአገራችን ኦርቶዶክስ ኢትዮጵያኖች „…እመቤታችን ሆይ…“ የሚለውን የጸሎት መስመሮች ከካቶሊኮቹ ጋር ሁነው ጨምረውበታል።nero-book
ከዚያ ወዲህ ወይም ከዚያም በፊት „…ክፋት እና መጥፎ ሥራን በደልንና ጭቃኔን መዋሸት እና ማታላልን“ አንድን ልጅ አባቶች ሲመክሩ ከዚህ ራቅ ከዚህም ተጠንቀቅ ይህን ከልብህ አውጣ …ተው“ ብለው ያስተምራሉ።
ከክፋትና ከክፉ ሰው ከአረመኔና ከቀመኛ ከመጥፎ ሥራና ሃሳብ ከአጸያፊ ተግባሮች…ወላጆች ይህን ከሚያደርጉና ከሚመክሩ ሰዎች ቢቻላችሁ ራቁ እናንተም አታድርጉ በእንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የተበከሉትን አጠገባችሁ አታድርሱ ብለውም ያስጠነቅቃሉ።
„…ይመክራሉ ያስተምራሉ“ የሚለው ቃል የሰውን ልጅ ወደ ሚገራው ወደ ትምህርትና ወደ መልካም አስተዳደግ ወደ ወግና ወደ ሥርዓት ወደ ጥበብና ወደ ዕውቀት አንድን ሰው – በሕይወት ዘመኑ ኮትኮቶ የሚወስድ ተጨማሪ መንገድ እንዳለ ያሳያል።

ይህን ተገንዝቦ ፕላቶ በሰው ልጆች ታሪክ (የአይሁዶች ትምህርት ቤት ነበር) የመጀመሪያውን አካዳሚ መሰረተ።
በግሸን አምባ ሌላው የኢትዮጵያ መሣፍንት ልጆች ትምህርት የሚቀስሙበት አዳሪ ትምህርት ቤት -ይህን አንዳዶቹ እሥር ቤት ይሉታል- ተከፍቶ እዚያ ወጣቶች አስተዳደርና አነጋገር ነገር ማየትና ማገናዘብ ይማሩበት ነበር።
ከዚህ ጋር-ቀደም ሲል- በርካታ ጥንታዊ ገዳሞች ትላልቅ በሁዋላ አገሪቱን የሚመሩና የመሩ ሰዎች የፈለቁበት ትምህርት ቤቶች ተቆርቁረው ተከፍተዋል ።


በአክሱም ቤተ- መንግሥት በጥንታዊት ኢትዮጵያ የግሪክ አስተማሪዎች ያኔ መጥተው ፍልስፍና እና አስተዳደር፣ ክርክርና ሪቶሪክ ሎጆክና ታሪክ በሚያስተምሩበት ዘመን የቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢና የመሣፍንቶቹ ቪላ የወጣቶች መኮትኮቻ ትምህርት ቤት እንደ ነበር ተጸፎአል።
ግሪኮች „ክፋትና የኃጢአት ሥራ“ ከአለማወቅ የሚመጣ ባህሪ ነው ይላሉ። ይህ አነጋገር ዕውነት ይሆን?


ፈላስፋው ሆብስ ነው – ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን ሌሎቹን ከእሱ በፊት የነበሩትን አሰተማሪዎቹን ተከትሎ „…የሰው ልጅ አውሬ ነው። እንደ አውሬ እንድን ሰው እንድ ተኩላ አንድ ቀን አረሳስቶት ቦጭቆት የሚሄደው ያ ሰው እሱን የሚመስል ሌላ ሰው ነው።“ ከእሱና ከእነሱ እነሱንም ከሚመስሉ ተጠንቀቁ ብሎ ሌቪታን በመባል የሚታወቀውን መጽሓፉን እሱ ደርሶአል።


ለጆን ሎክ ይህ መቦጫጫቅ እንዳይመጣ እሱ የሰጠው መልስ አጭር ነው።

መቻቻልና የሌላውን አመለካከት አክብሮ ማዳመጥ መደማመጥ ዋና የመግባባት መነሻ ነው ይላል። እሱም ብቻውን በቂ እንዳልሆነም ያነሳል። አልፎም ሄዶ ሎክ ቁጥጥር እንደ ሌሎች ምሁሮች በሰው ላይ ማካሄድ ያስፈልጋል ይላል።
በአራተኛው ክፍለ-ዘመን የተነሳው የክርስቲያና ሃይማኖት የሃዋሪያትን ወንጌል አስተማሪ የሰሜን አፍሪካው ተወላጅ አጉስቲኖስ ኢንስቲትውሽን -ተቋማት መዘርጋት አለበት ይላል። ለእሱ ለአጉስቲኖስ የሰው ልጅ በአውሬና በአምላክ መካከል የሚገኝ ሳይሆን በተፈጥሮና በአምላክ መካከል የሚገኝ ፍጡር ነው ይለናል።augistinus
የሰውን ልጅ በአራዊትና በአምላክ መካከል በባህሪው የመደበው ሌላው ሰው የጀርመኑ ፈላስ ሼልንግ ነው። እሱም ተመራምሮ በደረሰበት ዕውቀቱ ይህን ፍጡር ሰውን ዝም ብለን አንየው እንቆጣጠረው ብሎ ተጣርቶአል። ምክንያት አለው ምክንያቱም ሰው ክፉም ደግም ነገር ለመሥራት ችሎታ ስለአለው ያለውም በመሆኑ ይህን እሱ ሼልንግ ተገንዝቦ አደገኛነቱን በዘመኑ ጠቁሞአል። ማሠሪያው ደግሞ ፍቅርና ሃይማኖት እንደሆነም አያይዞ ጽፎአል።
ቶማስ ጄፈርሰን ነው የሰውን ልጆች ጎትቶ በመላእክቶችና በአጋንንቶች መካከል ያስቀመጠው።
በአንድ በኩል የሰው ልጆች በእሱ ዓይን -ምንም እንኳን ጥሩ ሰው ለመሆን እንደ መላአክ በሥራቸው ለመምሰል ጥረት ቢያደርጉም- ሰዎች በምንም ዓይነት ቅዱሳን አይደሉም ይለናል። እትመኑአቸው ብሎም ያስጠነቅቃል።
በሌላ በኩል የሰው ልጆች እንደ ከይሲው እርኩሱ ፍጡሮች ሰይጣኖች እንዳልሆኑም አንስቶ መልሶ ያጽናናል።
እንግዲህ ሰይጣን አይደለንም ። ግን ለምን የሰይጣን ሥራ በወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጎረቤትና በዘመዶቻችን ላይ እንጠነስሳለን?
ፈላስፋዎች እና ሳይኮሎጂስቶች „ሰዎች ሰይጣን አይደሉም „ስለዚህ የሰውን ልጆች ሁሉ ዝም ብለን በጭፍኑ ከማመን እጅና እግራቸውን በሕግና በሥልጣን ክፍፍል በትምህርትና በቅጣት ተብትበን እንያዝ አለበለዚያ አይቻሉም ይሉናአል።
ጄፈርሰን ከቢጤዎቹ ጋር በዚያ የግለሰብን ነጻ-መብትን የሚያውቀውን የአሜሪካንን ሕገ-መንግሥት ሁለቱን „ቁጥጥርና ነጻነትን“ አጥምሮ አብሮ ነድፎአል ።
ክፉና መጥፎ ሰው አለ። ለምንድነው አንዱ ሰው ክፉ ሌላው ርሕሩህ የሚሆነው? ክፉና መጥፎ ሰው ምንድነው?ምንድናቸው?
ለምንድነው ክፋትና ጥፋት በእንስሶችና በልጆች ዘንድ ሳይሆን በሰው ልጆች ዘንድ ነፍሳቸውን በአወቁና ነገር በገባቸው ሰዎች ዘንድ በብዛት የምናየው?
ክርስቶሰ እንደ ልጆች „ንጹሕ“ ሁኑ ብሎ ያስተምራል።

ለምንድነው ሕጻናት ክፋትን አያውቁም የሚባለው?
ሰይጣን እነሱን (ሕጻናትን) ፈርቶ ሰለማይጠጋቸው ይሆን? አጋንንቶችና መናፍስቶች ልጆችን አይተው ሰለሚሸሹአቸው ይመስለናል?
ሰይጣን ወይም መጋኛ ወይም አጋንንት.. ዲያብሎስ አተላ ይወዳል ይባላል። አመድ የሚፈስ ቦታ ይገኛል። በቀትር እየተዘዋወረ አላፊ አግዳሚውን ጫካ ውስጥ ይለክፋል ይባልለታል። ደም መጠጣት ይወዳል። ወንዝ ዳር ተኝቶ ድልድይ ሥር ተጋድሞ አድፍጦ ለቀም ለማድረግ ይጠብቃል ተብሎም ይነገርለታል። መብረቅ ሲመጣ ደንግጦ ሰው ላይ ይለጠፋል የሚሉ አሉ። …ፈሱም ኃይለኛ ሽታ አለው ይገማል ይባላል።
የቬኑዙዌላ መሪ ሁጎ ቻንሰስ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ሚስትር ጆርጅ ደብሊዩ ቡሽን (ታናሹ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገው ሲወርዱ ተራውን ተቀብለው አትራኖሱ ጋ ሲጠጉ „ስለ ሰይጣን አንስተው አንድ ነገር ይሸተኛል…እሱ እዚህ ነበር። ጠረኑ የእሱ ነው ይሸታል…“ የሚለውን ቃላታቸውን ለመንግሥታት መሪዎች ወርውረው እኚህ ሰው አንዳንዶቹን ደጋፊዎቻቸውን እዚያው አስቀዋል። ሌሎቹን ደግሞ አስቆጥቶአል።

ሰይጣን የሚባል ነገር ለመሆኑ አለ?ከአለስ የትነው ያለው? ወይስ ለማስደንገጥ ብቻ የሚነሳ ስም ነው?
ለመሆኑ ሰይጣን ማን ነው?


አዲስ ኪዳን „…ከከፉ ሁሉ ጠብቀን“ በሚለው አረፍተ-ነገር እንደጀመረው ሁሉ ብሉይ ኪዳንም ላይ ደግሞ „ ከዚህች ፍሬ አትብሉ …አለበለዚያ ክፉና ደጉን አውቃችሁ ትሞታላችሁ“ በተባለው የጥበብና የሕይወት ዛፍ ታሪክ የሰውን ልጆች ድራማ ይጀምራል።
„…ዝምታው ምንድነው በጥሳችሁ ብሉ እንጅ! „ ብላ በመጀመሪያ ሔዋንን በሁዋላ አዳምን በተንኮል ምክርዋ ባታለለቺው በዚያች እባብ ታሪክ ይቀጥላል።

Ethiodragon


አለ ምክንያት አይደለም የኢትዮጵያ ታሪክም በአንድ ዘንዶ ታሪክ የሚጀምረው። በዚያ እንደ መስዋዕት በየጊዜው በሚቀርቡለት ሴቶችም ወንዶችም ልጆች በመብላት በአስቸገረው ዘንዶ ትረካ የሚጀምረው ታሪክ በንግሥና ይቀጥላል።
በደፋሩ በአጋቦስ ብልሃትና ዘዴArk of the covenant Israel Ethiopia Solomon Sheba ያ ወጣት ልጆችን በየወሩ የሚበላው ዘንዶው ይገደላል። አጋቦስ ሕዝቡ ቃል በገባለት ውል እሱ በኢትዮጵያ ላይ ይነግሣል። ልጁ ማክዳም ንግሥት ሳባ ተብላ አልጋውን ትወርሳለች።

 

ሰይጣን አንዴ- በመጽሓፍ ቅዱስ- እባብ ተመስላ ብቅ ትላለች። ሌላ ጊዜ ሰይጣን ተቀይራ በአለሰባት አንገት አውሬ ትሆናለች።
ሔዋንን በመጀመሪያ ነጥላ የሸነገለቺው እባብ በሁዋላ በተጻፈው መጽሓፍ ላይ እንደምናነበው „…ሳጥናኤልን የዋጠቺው እሱም እራሱ ዋጪኝ ብሎ እባቡዋን አታሎ ሸንግሎ በግንቡ ላይ በእሱዋ ብርታት ከገሃነም ተስቦ አጥሩን ዘሎ ተንሸራቶ ገነት የገባው በእሱዋም አፍ „…ዝምታው ምንድነው ከጥበብ ዛፍ ብሉ“ ብሎ የታናገረው ሰይጣን ነው።
ተመሳሳይ ትረካ በቅዱስ ቁርኣን መግቢያም ላይ እናገኛለን።
መከራና ኃጢያአት ሞትና ጭንቀት ከዚያ ከበለሱ ፍሬ በሁዋላ በሰው ልጆች ላይ የመጣ „መዓት“ ነው ብለው የሃይማኖት አባቶችም ይህን ያስተምራሉ። እንግዲህ የሰይጣንም መነሻ የሰው ልጆችም መከራ -በትንሹ ሲተረክ -እንደዚህ ነው።
ምድራዊ ፈላስፋዎች ግን ይህን ታሪክ እግዚአብሔር አውቆ ሰዎችን ለመፈተን ያስቀመጠው „ግሩም ፈተና“ ነው ብለው በተራቸው በሌላ መልክ ነገሩን ተርጉመው ያቀርቡልናል።nero-muse


… እንዴት እንደምንኖር? እንዴትስ መኖር እንደአለብን? ለመኖርና በሕይወት ዘመናችን ምን ምን መሥራት እንደሚያስፈልገን? የትኛው ሥርዓት ውስጥ ብንኖር መንፈሳዊና ምድራዊ ደስታ እናገኛለን ብለን በጭንቅላታችን ተመራምረን እንድንደርስበትና አእምሮአችን እንድንጠቀምበት „…የምርጫ ነጻነት“ አምላክ የሰጠበት ሰዓት ነው ብለው እርምጃውን ብዙ ፈላስፋዎች (ሰለ ሰይጣን ሳይጨነቁ) ይህን ጉዳይ አንስተው በእግዚአብሄር ሥራ ይደነቃሉ።


በገነት መናፈሻ ውስጥ ከአሉት ብዙ ዛፎች ውስጥ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን „…ከዚህች ከጥበብ ዛፍ አንዲት ፍሬ እንዳትበሉ ከበላችሁ ደግሞ ክፉና ደጉን ታውቃላችሁ…ትሞታላችሁ “ ማለቱ በአንድ በኩል „ ትዕዛዙና ሕጉ እዲከበር“ ማስጠንቀቁ ቢሆንም
ይህን ባታደርጉ ደግሞ በሌላ በኩል ትዕዛዙን ከአልሰሙ „ እራሳችሁን ችላችሁ“ አእምሮአችሁን ተጠቅማችሁ በዚህች ምድር ላይ ጥራችሁ ግራችሁ ላባችሁን አንጠፍጥፋችሁ ትኖራላችሁ ብሎ እሱ እራሱ (ገና ከመጀመሪያው) አስጠንቅቆ መልቀቁ ተገቢ ምርጫና የመምረጥ መብት ነው ይላሉ ። እንግዲህ በየትኛው ሥርዓት ውስጥ ለመኖር እንደምንፈልግ ወሳኙ እኛ ነን።

የሆነውና የተከሰተው የሁለተኛው መንገድ ነው።The Garden of Eden

ከፍሬው በልተው ዓይናቸው ተከፈተ። እራቁታቸው መሆኑንም አወቁት። ይህ ደግሞ በሌላ ቋንቋ የሥልጣኔ መጀመሪያ ነው።
በመጀመሪያ ቅጠል በጥሰው -መጽሓፉ እንደሚለው- ሓፍረታቸውን ሸፈኑ። ቀጥለው ወደ እርሻና ከብት እርባታ ተሰማሩ። ደበሎና ሱፍ ደረቡ። ቆይተው ጥጥ ዘርተው ለቅመው ፈትለው ሸማ ሠርተው አጌጡ።
ለምንድነው ሌሎቹ ሲጌጡ የተቀሩት ራቁታቸውን አሁን ድረስ የሚሄዱት? ለምንድነው ከልብስም በዘመናዊ ልብስ አጊጦ ተኳኩሎ መውጣት በአውሮፓ እየተስፋፋ የሄደው? ለምንድነው በሌላው አካባቢ መሸፋፈን የነገሰው?
ለምንድነው ሌሎቹ ከአፈርና ከጭቃ ቤት ሲሰሩ የድንጋይ ቤቶች ጥበብ ቪላና ትላልቅ ቤተ-መንግሥት መሥራት ሌላ አካባቢ የተጀመረው?
ለምንድነው የሮምና የፓሪስ የበረሊንና የሊሳቦን ሕንጻዎችና ቪላዎች ከአፍሪካውያኖቹ በአሰራራቸው በውበታቸው በአቀማመጣቸው የሚያማመምሩት?

ለምንድነው ነጮች ተከባብረው ተቻችለው አብረው ተስማምተው ሲኖሩ አፍሪካ እርስ በእራሱ የሚጣበሰው?


ቆየት ብለን ወደ በሁዋላ እንደምናየው ገበሬው ቃዬል ከብት አርቢ ወንድሙን አቤልን „በቅናት“ ተነሳስቶ ደብድቦት ይገድለዋል። ትንሽ ዘግይቶ በሰው ልጆች ሥራ -አሁንም መጽሓፉ እንደሚለው-እግዚአብሔር አዝኖ የወሃ ጥፋት ይከተላል። በአባቱ እርቃንነት ያላገጠ ልጁን ኖህ ካምን ይረግመዋል። ሰዶምና ጎሞራ በእሳት ይቃጠላል። የባቢሎን ግንብ ይፈርሳል።
„ከእንግዲህ አላጠፋችሁም“ የሚለው የመጀመሪያው ውልና ቃል-ኪዳን ቀስተ-ደመና በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል ይደረጋል።

በሁዋላ እንደምናውቀው ብዙ ፈላስፋዎች ይህን ሓሳብ መሠረት አድርገው „ሶሻል ኮንትራት“ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተቻችለውና ተከባብረው በጋራ የሚኖሩበት „የጋራ ቃል-ኪዳን“ ብለው የፖለቲካ ቲዎሪአቸውን ነድፈዋል።


ይህ እንደዚህ አሁን እንደ ዋዛና ፈዛዛ እዚህ የሚተረከው ታሪክ አንድ ሰው ከመሬት ተነስቶ ወንድሙን ወይም ጎረቤቱን ጠላቱንም ቢሆን እንኳን „ አርዶ እንዳይበላው“ አጥብቆ ያግዳል። በዚህም…አትግደል አትስረቅ አትዋሽ በሃሰት አትመስክር እናትህና አባትህን አክብር …የሚሉ የሞራልና የኤትክ ሕግጋት ጋር የሰው ልጅ ይተዋወቃል። ያ ሕግ እነዚህ ሕግጋት የሠፈሩበት የሙሴ ጽላትም የመጀመሪያው መተዳደሪያ ደንብ ኢትዮጵያ በቀጥታ እንደ ደረሰም በታሪካችን ላይ እንመለከታለን። እሱን ተከትሎ የክርስትና ሃይማኖት አገራችን ይገባል። ለመጀመሪያ ጊዜም በዓለም ላይ የአንድ መንግሥት ሃይማኖት ሁኖ የክርስትና ሃይማኖት በአገሪቱ ይታወጃል።


ባህላችን ታሪካችን ሥርዓትና ደንቡ ባህሪያችን በአገራችን የተመሠረበት በአይሁድ በክርስቲያና ሃይማኖት ላይ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።

ይህ አንደኛውን የሥልጣኔ በዚያውም የሰይጣን አመጣጥ መነሻ ታሪክ ነው።-ቅዱስ ቁርኣንም ይህን ቦታ በቅጠሎቹ ላይ ይጠቅሳል ።


ሌላው አካባቢ ሌላው ባህልና ሥልጣኔ ሌላ እራሱን የቻለ አተራረክ አለው። ከእኛ ባልራቁት በግብጻዊያን ቤት ከዚህ ለየት ያለ አቀራረብ እንዳለ እናነባለን።
በግሪክ አማልክቶችና በጃፓኖች ዘንድ የፍጥረት አጀማመር በሌላ ዓይነት ቀርቦአል።
የነፋሱ ንጉሥ ሹ በጥንታዊ ግብጾች አመለካከት እንደ አክንባሎ አናታችን ላይ የተዘረጋው ሰማይ አንድ ቀን ተንኮታኩቶ ወድቆ ዓለምንና የሰውን ልጆች እንዳይጨርስ እሱን ቀጥ አድረጎ እንደ ምሶሶ የያዘው ጀግናው ንጉሥ „ንፋሱ ሹ“ ነው ብለው ያኔ እነሱ ያምኑ ነበር።nero-aksum-demol
ሰማይና መሬትም ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩም የእሱ ፈቃድ ብቻውን ወሳኝ ነበር።
ሳት ብሎት ይህ ንጉሥ ወይም ተቆጥቶ ወይም ጀርባውን ለማከክ አንድ እጁን መሸከሙን ትቶ ለቀቅ ከአደረገው ሰማዩ ተንኮታኩቶ ወርዶ የሰውን ልጆች ሁሉ -መናገር አያስፈልግም- ያጠፋዋል ብለው ይህ እንዳይሆን እነሱ ይሰግዱለት ነበር።
ተንዶ ሰማዩ ከተሰበረ አማልክቶቹ ከሰማይ ላይ ተንሸራተው ወርደው ከሰዎች ጋር ተደባልቀው ያልታወቀ ችግር በሁለቱ መካከል ይፈጥራሉ ብለውም ይፈሩ ነበር።
ከዚያ በፊትስ ምን ነበር?
የፈርዖኖቹ ታሪክ እንደሚለው ቀደም ሲል አማልክቶቹና የሰው ልጆች በንፋሱ ንጉሥ ሳይለያዩ አንድ ላይ በዚህች ምድር ላይ ተደበላልቀው ይኖሩ ነበር። በዚያም ዘመን የሰው ልጆች እየረበሹ የአምልክቶቹን ጸጥታ ነስተው ረብሻ እዚህም እዚም ተነስቶ ግርግር ጩኸትን ትርምስ በአገሪቱ ነግሦም ነበር። አማልክቶቹም ተቸግረው ሰዎችን ዝም ለማሰኘት እነሱን እያሳደዱ ይቀጡ በጦራቸውም ይዋጉ ነበር።
ለጃፓኖች ሥርዓቱንና ደንቡን በሰው ልጆች መካከል ሳያዳለ እየዘረጋ እንዲፈርድም እየፈረደም እንዲገዛ የጸሓይ ልጅ ንጉሥ ሁኖ እነሱን እየተቆጣና እየቀጣ እንዲያስተዳድር ከሰማይ ለእነሱ -ታሪካቸው እንደሚለው- ተልኮላቸዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እሰከ አሁን ድረስ ሲወርድ ሲዋረድ ንጉሥ አኩሂቶ ላይ ደርሶአል።

በግሪክ አገር የአማልክቶች ጦርነት እኔ እበልጥ እኔ እሻል በሚባል ፉክክር ገብተው ሶይስ የተባለው የአማልክቶች አለቃ (ተወልዶ) እስከሚነሳ ድረስ በመካከላቸው ረብሻ ነግሶ በጦር እንደተፈላለጉ ጊዜውን ገፍተው ነበር።
ሶይስ ከመምጣቱ በፊት በምድርም በሰማይም ላይ ይህ ነው የማያባል ረብሻና ትርምስ ብቻ ሳይሆን ግዲያና ፍጅት ጋብቻና ቅሚያ ድፍረትና አመንዝራነት በአማልክት ልጆችና በወላጆቻቸው በወንድምና በእህት (እንደ ሰው ልጆች እነሱም ይጋቡና ይዋለዱ ነበር) ዝብርቅርቁ የወጣ የተጨማለቀ ልማድ በመካከላቸው ሰፍኖ አንዱ ሌላውን ጭምር ይበላውም ነበር። (i


ሶይስ ብቻ አፈ-ታሪኩ እንደሚለው እናቱ አንድ አማልክት ሊደርሱበት ከማይችሉበት ዋሻ ውስጥ ደብቃው እሱ ከሞት ይተርፋል።
አድጎ ጉልበት ገዝቶ ከዋሻው ሲወጣ ጦርነት በአባቱና በእህቶቹ በወንድሞቹም ላይ ይከፋታል። አሽናፊ ሁኖ ወጥቶ ድል አድራጊው ሶይስ- አፈ ታሪካቸው እንደሚለው- በቂም በቀል አባቱንም እህቶቹንም ሳያጠፋ ምህረት አድርጎላቸው አባቱን በግዞት የእንድ ደሴት ንጉሥ እህቶቹንና ከሞት የተረፉትን ወንድሞቹን ደግሞ የባህር ንጉሥ የውቅያኖስ ንጉሥ የፍቅር የጦርነት የሐዘን …ንጉሥ እያለና እየሾመ እሱ የሰማይ ንጉሥ ሁኖ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ሰማይና ምድርን ይገዛል።
የሥልጣን ክፍፍል በማድረጉ ሰላምና ጸጥታ በምድርም በሰማይም ላይ ሰፈነ። ይህ ሁሉ ሲሆን የሰው ልጆች ቦታ የት ነበር? በግሪክ ትረካ የሰው ልጆች ከየት መጡ? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ የአመጣጥ ታሪክ እንደ አላቸው ይነገራል። (ii
ጥንታዊ ግሪኮች ሰይጣንን እኛ በምናውቀው ዓይነት እነሱ አያውቁትም። „ክፋትን“ ግን ምን እነደሆነ በደንብ አድርገው ያውቃሉ።
እንዲያውም „ክፋትን መክቶ የሚከላከል አምላክ/አማልክት“ አለ ይላሉ።The-Engel-and-dragon
ይህ ደግሞ ለምን እኛን የሰው ልጆችን የሚፈታተን ሰይጣን እግዚአብሔር ላከብን? ለምን ሰይጣንን ከእኛ አያርቅም? ለምን እንደዚያ እየተፈራረቁ ሲያስቸግሩን ዝም ብሎ ያያል? እጁን ዘርግቶ ለምን አያድነንም? የሚሉትን አቤቱታዎች ያስነሳል።

እናሳጥረው።
…ሰው ሰይጣን ነው። ሰይጣንም ሰው ነው። ይህ አባባል ዕውነት ይሆን?

ወይስ ሰይጣን/ሰይጣኖች በአየር ላይ ከንፈው/ከንፎ ሳይታሰብ ሰውን ወይም አንድን አገር አንድን ሕዝብ የሚያሰቃዩ መናፍስት/መናፍሰቶች ናቸው?

ይህንና ይህን የመሰሉ ጥያቄዎች…ከቃዬልና አቤል ከዳዊት እና ከጎሊያድ ከዩሊዮስ ቄሣር እስከ ኔሮ እስከ ካሊ ጉላና እስከ ከኢቫን ጨፍጫፊው ከስታሊን እሰከ ሒትለር ያሉትን ሰዎች የምንረዳውና የምንመልሰው አእምሮአችንን ከፍተን ነገሮችን በትክክል ለማየት ስንችል ነው።


ሕጻናትን የሚዳፈሩ የከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቄሶች አሉ። በኮሙንዝም ስም እነ ኪም ኢል ሱንግ ሥልጣን ላይ ወጥተው ውርርሱን ወደ ንጉሣዊ አገዛዝ ወደ አልጋ ወራሾች ሥርዓት ቀይረውታል።

ትላንት ጫካ አንድ ላይ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ጠላት ሁነዋል። ትላንት „ዲሞክራሲና እኩልነት“ ይል የነበረው ሰው ዛሬ ጊዜው አይደለም ይላል።
„…ሰው ሰይጣን ነው ሰይጣንም ሰው ነው“ የሚለውን አነጋገር የምንረዳው አንዴ ብቻ ሳይሆን አራት አምስት ጊዜ አገላብጠን ስናየው ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ በአሜሪካንና በአውሮፓ በአረብ አገሮችና በቻይና በሕንድ በሩሲያና በጀርመን… በአንድ ዘመን „ጨዋ“ የነበረ ሰው በሌላ ዘመን እንደዚያ አስፈሪ የሆነ “አረመኔ ጦረኛ“ ይወጣዋል። ለምን? በምን ምክንያት?
ለምንድነው በአስተሳሰብ የማይስማሙ ሰዎች ብዙ ቦታ በጭካኔ ተነሳስተው የሚጋደሉት? ለምንድነው በሌላ አካባቢ ሌሎቹ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖራቸውም የሚስማሙት?
ምናልባት በአንዳንዱ አካባቢ ሰይጣኖች ስለጠፉ? በሌላው አካባቢ ሰይጣኖች አለቅጥ ስለ ተራቡ? አንዱ አካባቢ በእግዚአብሔር ስለ ተረገመ? ሌላው አካባቢ በእሱ ስለተቀደሰ?
አንዳዶቹን እግዚአብሔር በጣም ስለሚወዳቸው? ሌሎቹን በተቃራኒ ሰይጣን ስለሚያፈቅራቸው? ወይስ ለእነሱ አሳልፎ ስለሰጣቸው? ወይስ እግዚአብሄር እኛን ለመቅጣት ፈልጎ?

ፈጽሞ አይመስለንም።

ለነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው ስለ ልቦና ስለ አእምሮ ስለ ነፍስና ስለ ሥጋ…ስለ መንፈስ ደስታና ስለ ሓዘን ስለ ሰው ልጆች ባህሪ „ጠለቅ „ ብለን „ጠጋ“ ብለን ለመመልከት ጥረት ስናደርግ ብቻ ነው።

ጥንታዊ ግሪኮች ከዕውቀታቸው ሲያካፍሉን መልሱ ይህን ይመስላል።

ሁለት አዛውንቶች ለብዙ አመታት ተለያይተውና ተራርቀው ከሰነበቱ በሁዋላ አንድ ቀን ተገናኝተው ስለ የባጥ የቆጡ ስለ ዓለምና ስለ እግዚአብሔር ስለ መንፈሳዊ ኑሮና ስለ ዓለማዊ ችግሮች ይጫወታሉ።philodialogue


ሁለቱም በሁለት የተለያዩ ነገሮች የታደሉ ናቸው።
አንደኛው በስምና በዝና በአካበተው ሐብትና ንብረቱ በመንደሩና በአካባቢው የተከበረ ጥሩ ስም ያተረፈ ትልቅ ሰው ነው። ሁለተኛው ጥበብና በዕቀውት በብሩህ አእምሮው ከአገር ድንበር አልፎ የሚሄድ እሱም እንደ ጓደኛው ትልቅ ስም ያተረፈ አዛውንት ነው። ከዚያም በላይ ሁለቱም የእድሜ ባለጸጎች ናቸው።
ሊቀ ሊቃውንቱ የልጅነት ጓደኟውን ከስንት አመት በሁዋላ ሊጎበኘው በሩን አንኳኩቶ ገብቶ መጠጥም ምግብ ቀርቦለታል።
ሁለቱም ስለሚያሳስባቸው ስለ ፍርድና ፍትህ ስለ መልካም አስተዳደር የቀረበላቸውን የወይን ጠጃቸውን እየቀመሱ ግሩም ጨዋታ ይዘው ሐሳቦቻቸውን ይለዋወጣሉ።
„…እርጅናው እንዴት ያደርገኻል? እባክህን እስቲ ንገረኝ አጫውተኝ ወንድሜ።… እንደያው እንደ ዱሮ እንደ ወጣትነት ዘመንህና ዕድሜ ወዲያ ወዲህ በእግርህም በፈረስህም እንደልብህ አለማለትህ ትንሽ ቅር አያሰኘህም…ወይ “ ሊቁ ይለዋል።


ዕድሜም ገንዘብም የተሰጠው ሓብታሙ „…አይ አንተ ደግሞ! እሱማ እየደከሙ መሄድ የተፈጥሮ ሕግ ነው። በዚህ ዕድሜአችን የማይመጣ ነገር የለም። እንደ አመጣጡ ከተቀበልነው ደግሞ አይቆረቁረንም።“

ሊቁ:- „የፍቅር ነገር፣ የስሜት ዓለምህስ እንዴት ነው? ስሜትህ በመብረዱ አታዝንም?“


ቱጃሩ „…ይገርመኻል አታምነኝም እሱን መገላገሌ አንደ ከባድ ነገር ከትከሻዬ ላይ አራግፌ እንደጣልኩት ሽክም ይህል ነው። ተገላግዬ አለሁ።“


ሊቁ:- „…ሰላምና ጸጥታ ዕረፍትም ጭምር እድሜ ከፍ ሲል ለእንደእኛ ዓይነት ሰዎች ሰውነታችን የሚሻው ነገር ነው። እጅግ ደስ ይላል። ግን ካለሓብትና ከአለንብረት ሁሉ ነገር ይጨንቃል። …ለእነሱስ -ገንዘብ አስፈላጊ አይደለም?“


ቱጃሩ:- „ በእርግጥ ንብረትና ሓብት ብዙ ነገሮችን ያቃልሉልናል። ከዚያ በላይ ግን አስፈላጊ አይደለም። በሓብት መካበት የሚደሰት ሰው ጥቂት ነው። ሁሉም ሰው አይደሰትም። ለእኔ ንብረት ማለት የሚገባኝን ሠርቼ ማግኘት እንጂ ሰዎችን መክፈል ከሚገባቸው በላይ ጠይቄ ሓብትን በማይሆን መንገድ ማካበት አልፈልግም። እንደ ደንቡ ሰዎች የሚፈለጉትን አቀርብላቸዋለሁ። የሚገባውንም ሒሳብ እጠይቃለሁ። የቸገረውንም እረዳለሁ። ለአምላክም ተገቢውን አሥራትና መስዋዕት አቀርባለሁ። አገባለሁ። በሐብት ብዙ ጥሩ ነገሮችን ማድረግም ይቻላል። „

ሶቅራጠስና ሓብታሙ ጓደኛው ኬፋሎስ ይህን የመሰለ ውይይት ሲያደርጉ አጅበውት የነበሩት ተማሪዎቹ ከባዱን የፍልስፍና ውይይት አስተማሪአቸው እገረ መንገዱን ይከፍታል ብለው ተስፋ አድርገው ይጠባበቁ ነበር።
ሶቅራጠስ ግን ጓደኛው በሕይወት ዘመኑ ሠርቶ ጥሮ ግሮ በደረሰበት ደስተኛ ውጤቱና የሕይወት ልምምዱ ከእሱም በሰበሰበው ተመክሮው በውይይቱ ላይ በማዳመጡ እጅግ ተደስቶአል። የተደሰተበትም ምክንያት አለው።


ይህ ሰው በትውፈት የተደገፈ የተስተካከለ ሕይወት በመምራቱ ነው። ኬፋሎስ የተማሪዎቹን መቁነጥነጥ አይቶ “ከእንግዲህ የተቀረውን እናንተው ተፈላሰፉበት እኔ ግን ለአማልክቶቼ መስዋዕቶቼን ለማደርስ እወጣለሁ” ብሎ ሜዳውን ለፈላስፋዎቹ ለአስተማሪውና ለተማሪዎቹ ለቆ ይወጣል።


መልካም ሥራ አንግዲህ -ከንግግሩ ላይ እንደምናየው ፖለቲያም የተባለው መጽሓፍም ላይ ተጽፎ እንደምናነበው- እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ነው። ተቃራኒው ደግሞ „ክፋት“ ነው።

ethical-brain
ክፋትና አጥፊ እርምጃ ምንድናቸው?

ኪፋሎስ ሜዳውን ለቆ እንደወጣ የሶፊስቱ ቁንጮ ዋና መሪ ትራሲማኮስ የሚባለው ፖለቲከኛ መድረኩን ተረክ፣

„…ጥሩ ነገር መሥራት ማለት እኔን የሚጠቅም ሥራ መሥራት ነው።“ ብሎ ንግግሩን ለተማሪዎች ይከፍታል። „.. በተፈጥሮ ሁሉም የሰው ልጅ እኩል አይደለም። ስለዚህ ጠንካራው ጊዜው የሰጠውን ሓብትና ሥልጣንም ከሌሎቹ ተከላክሎ ለእራሱ ሕልውና መቆየት ሲል ጥዋት ማታ መሥራት አለበት። ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ በእጁ ሲያስገባ ብቻ ነው እሱ አርፎ መተኛት የሚችለው። አስፈላጊ ከሆነም ቢቻለው ፈላጭ ቆራጭ -ታይረን መሆን አለበት። ከጠንካራ አመራርና ከጠንካራ ሕብረት አንጻር ስንመለከተውና ስናየው እንደዚህ ዓይነቱ ሥርዓት መኖር ደግሞ ተገቢና ትክክል ነው።“ የሚለውን አስተያየቱን ይሠነዝራል።

„ይህማ!… ይህን ማድረግና ይህን እንደ ትክክለኛ አማራጭ ማየት መጪውን የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት በሕዝብ መካከል በቀጠሮ እንደ ማሳደር ነው። ይህ ከሆነ በገዢና በተገዢዎች መካከል ያለው ጥላቻና ለመተናነቅ መፈለለግ አንድ ቀን መምጣቱ የማይቀር ጉዳይ ነው።“
ተገዢው ክፍል ዝም ቢል እነሱን መርተው ሥልጣኑን ለመንጠቅ የሚፈልጉት ክፍሎች እሳት ከመለኮስ አይመለሱም። ገዢውም ደህና እንቅልፍ ሳይወስደው ሁሌ እንደቃዣ -ከአሁን አሁን መጥተው አነቁኝ ብሎ በሰቀቀን የሚኖር ነው። እንደዚህ ዓይነቱ አስተዳደር መገላመጥ ያበዛል። የእራሱን ጥላ እንኳ ሲያይ ይደነግጣል። እንደ ተደበቀ እንተቅበዘበዘ እንደ ተጣደፈና ከሰው እንደራቀ አንድ ቀን ሳይደላው እፎይ ብሎ ሳያርፍና የሰበሰበውን እንኳን ሳይበላ ልጆቹም ምንም ሳያገኙ ጠላቶቹ እጅ ይወድቃል።
መልካም አስተዳደር አመጣለሁ ብሎ የተነሳው ሰው ወደ ጭቆና ይሸጋገራል። እገነባለሁ ያለውን ሕብረተሰብ በዚህ መንገድ ያፈርሳል። እረዳለሁ ብሎ የተናገረውን ቃሉን ወደ ጭቃኔ ይቀየራል።
ሥልጣን ለእሱ ለገዢው ጣፋጭ እንደሆነቺው ሁሉ ለተራ ሰው ለተገዢው ቋቅ የሚል መራራ ሬት ትሆናለች።”


ሶቅራጠስ ይህን ዘርዝሮ እስቲ እንደ ሐኪም ለአንድ ሕብረተስብ አንድ መፍትሔ ዝም ብለን ከመወርወራችን በፊትና ተቀበሉት ብለን ከማስጨነቃችን በፊት እንደ እነሱ እንደ ሓኪሞቹ ረጋ ብለን እናስብ”ይላል። ሐኪሙ መራራ መድሓኒቱም ለበሽተኛ ከመስጠቱ በፊት ምን ዓይነት መድሓኒት በሽተኛው እንደሚስፈልገው ጠጋ ብሎ ጊዜ ወስዶ መመርመር ይኖርበታል። መርምሮ ከዚያ በሁዋላ ተገቢውን መድሓኒትና ሕክምናም ያዝለታል። እሱንም ያደርግለታል።

ብዙ ሰዎች አንድ ላይ ተሰባስበው ለዘመናት በሚኖሩበት ሕብረተሰብም ውስጥ አንድ መፍትሔ አንድ ሰው ወይም ሁለት ሰዎች ከማቅረባቸው በፊት እንደ ሓኪሙ እነሱ በመጀመሪያ በዘመናዊ አነጋገር ለመናገር ያን አካባቢ የግድ መመርመር ይኖርባቸዋል። ሶቅራጠስ እነዚህ ሰዎች መፍትሔ መድሓኒት ለአንድ ሕብረተሰብ ከማዘዛቸውና ከመስጠታቸው በፊት የሰዎችን /የሰውን ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ በመጀመሪያ መመርመር ይኖርባቸዋል ይላል።

ምንድነው የሰው ልጆች ከእንሰሳ የሚለያቸው የተፈጥሮ ባህሪ? ይህን ባህሪ ለመረዳት ሁለት መንገዶች አሉ።

አንደኛው የፕላቶ ተማሪ የታላቁ እስክንድር አስተማሪ የሆነው አርስጣጥለስ የነደፈው ዘመናዊ ሳይንስም አሁን የሚከተለው ኢምፔሪካል ጥናት ነው።

ሁለተኛው መንገድ ፕላቶና አስተማሪው ሶቅራጠስ የሚሉት የሰው ልጅ እራሱን ከፍ አድርጎ አስተካክሎ ሊደርስባቸው የሚፈልጋቸው የመኖር ዘይቤ ናቸው። ይህን ለማስረዳት
ፕላቶ ሙዚቃንና የከዋክብቶች አቀማመጥን እንደ ምሳሌ ይወስዳል።

መንፈስን የሚያድሰው እንደ የሂሳብ ትምህርት ሥርዓት የተቀነባበረው የሙዚቃ ድርሰትና ማታ ማታ አንገታችንን ከፍ አድረግን ሰማዩን ስንመለከት የምናያቸው የክዋክብቶች ቅንብር ቁንጅናቸው -ሓርሞኒ ይለዋል- አቀማመጥ ናቸው።
ፕላቶ ይህን ነገር በሌላ ምሳሌ ለማስረዳት ብዙ ፈረሶች በአንድነት የሚጎትቱን ሠረገላም አድርጎ ያቀርበዋል። ፈረሶቹ በአንድነት ካአልረገጡና ሠረገላውን በሶምሶማቸው አስተካክለው ከአልሳቡት ወይ ሠረገላውን ይገለበጡታል ወይም ይሰብሩታል ወይም ደግሞ ከቆሙበት ፈቀቅ አይሉም። ይህ „ይሰበራል“ የሚባለውን ነገር ደግሞ እንደ ፕላቶ እንደ እሱ የሚያስፈራው ነገር የለም። አንድ ሕብረተሰብ ተንኮታኩቶ ከወደቀ ደግሞ ከዚያ በሁዋላ ምን እንደሚመጣ? ማን እንደሚተካው? ምንም የሚታወቅ ነገር ስለሌለ አትንቀጅቀጁ ተማሪዎቹን ይላል ። ፕላቶ “አብዮት” የሚባላውን ነገር ከዚህ ተነስቶ አይወደውም። ይህም የክፋት ሥራ ከየት እንደሚመጣ መልስ እንድንፈልግ ይረዳናል።

ለምንድነው ሰዎች ክፉ መጥፎ ሥራ የሚሠሩት? ….አውቀው ነው ወይስ ሳያውቁ? እነሱ እራሳቸውን ገደል ለመክተት ፈልገው ነው ወይስ “ጥሩ” ሥራ እየሰራን ነው ብለው በማመናቸው ነው?

ለእነዚህ ጥያቄዎች አንደኛው ፈላስፋ ሶቅራጠስ ጥሩ መልስ የዛሬ ስንት ሸህ አመት መልስ ሲሰጥ „ሳያውቁ ምንም ነገር በአለማወቃቸው መሓይም በመሆናቸው ነው…“ ይላል።
በዚህ መልሱ ከጥፋታቸው እነሱን „ነጻ“ ሊያወጣቸው ፈልጎ አይደለም።nero-socrat
የማያውቁት ነገር ውስጥ ገብቶ ያውም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩትን የተለያዩ ሕዝቦችን ማስተዳደር ቀላል ነገር እንዳልሆነ ለማሳየት ብቻ ነው።
እሱ እራሱ „…እኔ የማውቀው አለማወቄን ነው“ ሲል አንድ ሰው በየቀኑና በየጊዜው እንደ ችሎታውና ዝንባሌው ማጥናት መመራመር ጥበብና ዕውቀትን መሻት እንጂ እንደ አራቱ መደብ አዋቂ የጨበጥኩት ዕውቀት „በቂ ነው“ ስለዚህ እኔም ጨረቃ ላይ ከንፎ የሚያስወጣውን መንኮራኩር እንዳው በደፈናው እንደ አሜሪካኖቹና እንደ ሩሲያኖቹ „እሠራለሁ“፣ የሚያግደኝ የለም ብሎ መፎከር እንደማይበቃ ለማሳየት ነው።
ሶቅራጠስ አልፎ ሄዶ „ለእራሱ ጥሩ ነገር እሠራለሁ“ ብሎ ግን ደግሞ ባለማወቅ „መጥፎና ክፉ ሥራ የሚሰራው ሰው እራሡን ጭምር የሁዋላ ሁዋላ እንደሚጎዳ እንኳን አያውቅም“ ይላል።
ለዚህ ነው ሁለቱ ፈላስፋዎች አስተማሪውና ተማሪው ፕላቶን ለዕውቀትና ለጥበብ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት።
ለመልካም ሕብረተስብ ለመልካም አስተዳደር ለሰው ልጆች አብሮ በሰላምና ደስታ መኖር ብዙም ቢያስቡም ከከተማ ግርግርና ከሰውነት ስሜት ” ባርነት” ከሁለቱም፣ ሁለቱም አዋቂዋች ተላቀውና ርቀው በመንፈሳዊ በኮንቴምፕላቲቭ ዓለም ውስጥ መኖርን የሚሹት። የፈለጉት። ይህ ደግሞ ጊዜ የሚሽረውን ሥራ ሳይሆን ዘለዓለማዊ ሁኖ የሚቆየውን ሥራ ሰርቶ ለማለፍ የተነሳሱበት ነው። እሱም ፍልስፍና ነው። እሱም ድርሰት ነው። እሱም ሙዚቃና የኪነት ጥበብ ነው። እሱም ጥናትና ምርምር ነው። እሱም-ወደ ቅጀት ዓለም ሳንሄድ በአንድ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ-ጊዜያዊ ሳይሆን ቋሚ ሁኖ የሚጠቀስ ሥራ ነው። መዓት “እብዶች” ከመሬት ተነስተው እዚህማ ላይ “እኛም አለንበት” ሊሉ ይችላሉ። ይህ ግን ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው እሳት በላሱት ጭንቅላቶች አንድ ቀን የሚፈተን ሥራ መሆን አለበት። ደግሞ የትኛው ሥራ ?

ሁለት ነገሮች፣

አውሮፓ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ አመታት ፈጅቶባታል። ለምን ይህን ያህል ጊዜ ፈጀባት? ለምንስ ለእኛ ይህን ያህል ጊዜ ተሰውሮብን ግራ አጋባን?


አንደኛው የፍልስፍና የምርምርና -የሳይንስ ጥናት መንገድ ነው።

ሁለተኛው የመልካም አስተዳደር ዘይቤ ብልሃትና ዘዴ፣ በሌላ አነጋገር ተቻችሎና ተከባብሮ በዲሞክራቲክ ሕብረተሰብ ውስጥ አብሮ መኖር ነው። እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ለእኛም ለእነሱም ብዙ አመታት ፈጅቶብናል። ያለፈው ምሥጢር እነዲህ ነው።


አውሮፓውያኖች-ሮም ቀደም ብላ ከጥበቡ እንደ እኛው ቀምሳለች – ከእንቅልፋቸው የነቁት፣ የግሪኮች ትምህርት የአውሮፓ ገዳም ከገባ ወዲህና የገዳሙ ትምህርት ወደ ዩኒቨርስቲዎች፣ እዚሁ ገዳም ውስጥ ቀስ እያሉ ከተቀየሩ በሁዋላ ነው።
የሚታወቀውን ለመድገም- ግሪኮቹ አራት መቶ አመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ነጻ አስተሳሰብን ማራመድና መመራመርን እንዲሁም የሰው ልጆች ነጻነትን ማለት ዲሞክራሲን (ባሪያና ሴቶች ልጆችና የውጭ አገር ሰዎች እኩል መብት አልነበራቸውም እንጂ!) ፈልገው አግኝተው መዳፋቸው ውስጥ አስገብተው በሥልጣኔአቸው ሌሎቹን ቀድመው ለመሄድ ችለዋል።


እንዴት ነጻነትን አርነትን ዲሞክራሲን መራመርና መፈላሰፍን ሌሎቹን ቀድመው አገኙ? አግኝተውም በደንብ ሊጠቀሙ ቻሉ? አንዴትስ ግሪኮች ወደቁ? ሮም እንዴት ተነሳች? እሱዋስ እንዴት ወደቀች? ይህ ማደር የሚያስፈልገው አርዕስት ነው።

አንድ ግን ለማሳረጊያ ማንሳት የምንፈልገው ነገር ቢኖር፣ እኛ ተከባብረንና ተፋቅረን አብረን በሰላም ለመኖር ከአወቅንበት እንደሚባለው እንደ አውሮፓውያኖች ገና ብዙ አመታት መጠበቅ ሳይሆን ነገ ማድረግ የምንችለው ነገር ነው። ያገኘነው ልምምድ የቀመስናቸው መከራዎች በቂ ትምህርቶች ናቸው። ነጻነትና ነጻ አስተሳሰብ ማለት ደግሞ ማንኛውንም ዓይነት “ባርነትን” አልፈልግም ማለት ነው። እንደ ክርስትና ትምህርት ደግሞ “እኩልነትና ፍቅርን ነጻነትን ወንድማማችነትና … የሚያስተምር ትምህርት የለም።” ግን እሱንም ቢሆን ቫቲካን ሆነች የእኛ ቤተ-ክርስቲያን ወንጌላዊት ሆነች የአሜሪካ የተለያዩ ሴክቶች በደንብ አንስተው ሰውን አላስተማሩም። ቢያደርጉማ ኑሮ “ባርነት የዘር ጥላቻ…ለሁለት ሺህ አመታት በተከታታይ በአልነገሰ ነበር።

ሰው ሰይጣን ነው። ሰይጣን ሰው ነው። “ከክፉ ሁሉ አድነን የሚባለውም ለዚሁ ነው።

ሰው ሁሉ ግን ሰይጣን አይደለም።

————-

——————————–

i/ ሰማይና ምድር -ጋያና ኤሮስ – ወንድና ሴት ሁነው ይገናኛሉ።ልጃቸው ኡራኖስ ይወለዳል። እሱ ከእናቱ ከመሬት ከጋያ ጋር ተገናኝቶ ብዙ ልጆች ይወለዳሉ። የእሱ ልጅ አንዱ ክሮኖስ የሚባለው አባቱን ይሰልብና እሱ እረሱ የአባቱን ቦታ ወርሶ ገዢ ሁኖ በወንድሞቹና በእህቶቹ ላይ ይነሳል።
ክሮኖስ እንድ ግብጾቹ ፈርዖኖች ከእህቱ/ከእህቶቹ ጋር ተገናኝቶ ሦስተኛውን ትውልድ በሁዋላ ጠንካራ አማልክት የሚሆኑትን እነ ዴሜተርን እነሓዴስን እነ ፖሳይዶንን እና በመጨረሻው ሁሉንም አሸንፎ ንጉሥ የሚሆነውን ሶይስን በጠቅላላው በርካታ ልጆችን ይወልዳል።
በአንዱ ልጅህ እጅ አንድ ቀን ነፍስህ ታልፋለች የሚባል ንግርት ከአባቱ ሰምቶ ስለነበር ክሮኖስ ከመሬት ተነስቶ በፍረሃቻ የወላዳቸውን ሥጋውን ወንዶች ልጆቹን እንደተወለዱ እሱ እየያዘዛና እየለቀመ ይውጣቸው ጀመር።

ii/ ፕሮሜቴዎስ የሚባለው አምላክ ፈጠራቸው የሚለውን አተራረክ ከወሰድን የሰውን ልጆች ይህ አማልክት ከተቃጠሉት የ …ልጆች ከቲታን አመድ ጠፍጥፎ እሰኑን እንደፈጠራቸው ከግሪክ ታሪክ እናነባለን። ሶይስ የሰው ልጆች በፕሮሜቴዎስ እጅ ከአመድ ተጠፍጥፈው በመሠራታቸው እሱ ፈጽሞ እንደ አልተደሰተም ። እሱ በተራው ሶይስ ቀጥቃጩንና አንጣሪውን ሔፓኢስቶስን ከሸክል ድንጋይ አንዲት መልከ መልካም ሴት ልጅ ጠፍጥፎ ሠርቶ እንዲልክለት እንደአዘዘው እንመለከታለን።
ይህቺ ልጅ በሁዋላ ፓንዶራ የሚባለውን ስም የያዘቺው በሶይስ ትዕዛዝ ወደ ሰው ልጆች መኖሪያ መንደር ተልካ እዚያ ፕሮሜቴዎስ ቆልፎበት የነበረውን ሳጥን ሰርቃ እዚያ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ በሽታዎችን፣ እንደ ሞትና ሐዘንን ነገር መርሳትን መዣዠትን ጥላችን ምቀኝነትን… በሰው ልጆች መካከል ሳጥኑን ከፍታ እንድተረጨው ትደረጋለች።
በዚያም በዚህም የሰው ልጆች በአንድ በኩል ከውጭ ከሚመጣባቸው ችግሮች በሌላ በኩል እራሳቸው በእራሳቸው በማወቅም ሆነ በአለማወቅ በሚጠነስሱት ሥራዎቻቸው ተተብትበው ጦርነት በእራሳቸው ላይ ከፈቱ።
ሌላም ሦስተኛ በስንት መከራ በሁዋላ ተፈልጎ የተገኘም ችግር አለ። ይህም በእያንዳንዳችነ ደረትና አእምሮ በልቡና እና በጨኝቅላታችን ውስጥ ያሉ ሁለት ዓለሞች ናቸው ። ይህንንም በመንፈሳዊ ትምህርት የሥጋና የነፍስ ፉክክርና ትንቅንቅ ልንለው እንችላለን። ወይም ደግሞ በፍልስፍናው ዓለም ከሃይማኖት በተለየ ዓይን ፣ ሥጋና አእምሮ ወይም መንፈስ ወይም ደግሞ ነፍስ የሚባለው ነገር ነው። ነፍስ ወይም መንፈስ በግሪኮች ዘንድ በሦስት ይከፈላል። ማሰብና ማመዛዘን ፍቅርና ስሜት ጀግንነት ናቸው።

ሶቅራጠስ አልፎ ሄዶ „ለእራሱ ጥሩ ነገር እሠራለሁ“ ብሎ „መጥፎና ክፉ ሥራ የሚሰራው ሰው እራሡን ጭምር የሁዋላ ሁዋላ እንደሚጎዳ እንኳን አያውቅም“ ይላል።

ለዚህ ነው ሁለቱ ፈላስፋዎች ለዕውቀትና ለጥበብ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት።

ለመልካም ሕብረተስብ ለመልካም አስተዳደር ለሰው ልጆች አብሮ በሰላምና ደስታ መኖር ብዙም ቢያስቡም ከከተማ ግርግርና ከሰውነት ስሜት ባርነት ከሁለቱ ተላቀውና ርቀው በመንፈሳዊ በኮንቴምፕላቲቭ ዓለም ውስጥ መኖር ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ ጊዜ የሚሽረውን ሥራ ሳይሆን ዘለዓለማዊ ሥራ ሰርቶ ማለፍን ነው። እሱም ፍልስፍና ነው።እሱም መዚቃነን።እሱም ድርሰት ነው።እሱም ኪነት ነው። እሱም ሳይንስ ነው።

በግሪክ ላይ ከቆየን -በትክክል የአቴን ሥልጣኔ ላይ ትንሽ ጊዜ ወስደን አካሄዳቸውን ከተመለከትን- እነሱ ይህን አታድርግ ይህን አታስብ ይህ ክልክል ነው፣ይህ ደግሞ ለአንተ አይደለም የሚል እንደ ፋርስ አያቶላዎች ወይንም እነደ ግብጽ ፈርኦንች ዓይነት የሰውን ልጆች አእምሮና ሥራ የሚቄጣጠሩ „ካህናቶች“ በአናታቸው ላይ ተቀምጠው እነሱን አፋቸውን ለጉመው እግራቸውን አሥረው አልገዙአቸውም።

ይህ አንደኛው ምክንያት ነው።

ሁለተኛው ምክንያት አዲስ ነገር ለማወቅ ኃይለኛ ጉጉት ያላቸው ሰዎች ነበሩ።

ይህም ይከተሉት በነበረው ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ነው። አካባቢአቸውን ተንቀሳቅሰው ያጠኑ ነበር። የሌላውን አገርና ሕዝብ ዕውቀትና ጥበብ ተዘዋዉረዉ ይሰበስቡ ነበር።

ወደ ግብጽ ተጉዘዋል።ፋርስ ደርሰዋል። ሕንድን አይተዋል። ኢትዮጵያ ሔሮዶቱስ ወርዶ ሊጽፍ የቻለው በዚሁ ምክንያት ነው።

በሒሳብ በድርሰት በሕንጻ ሥራ በታሪክ ምርምር በመድሓኒት ቅመማ በሕክምና ጦር ቴክኒክና በመርከብ ሥራ በእርሻ ምርትና በከብት እርባታ በወይራ ዘይትና በምግብ ዓይነቶች በልብስና በቤት ቁሳቁሶች በቅኔ ውበትና በኢስቴትክ በቁንጃ…ከሁሉም ከሁሉም በፍልስፍና እና በፖለቲካ ዲሞክራሲ በምርጫና በውይይት በክርክርና በውድድር አምነው ከሌሎቹ የተሻላ ቋሚ የጋራ ቤታቸውን በጋራ ሊሠሩ የቻሉት -ይህ ነው ብልሃቱ- ለነጻነት በአላቸው ፍቅር ነው።

አሜሪካንና ጀርመን ፈረንሣይና ታላቁዋ ብሪታንያ… አሁን እነሱ ሌሎቹን ቀድመው የሄዱት ልክ የአቴኖቹን ፈለግ በመከተላቸው ነው። አቴኖች መፈላሰፍን መናገርን መከራከርን ውይይትን አዲስ ነገር ማየትና መስማት የማይፈልጉትን የሚቃወሙትን ፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖችን ታይረንን እንደ ዛሬ የምዕራብ አገሮች አጥብቀው የሚቃወሙ ናቸው። እንዲያውም በሕዝብ ላይ በእነሱ ላይ አምባገነን ሁኖ ፈላጭ ቆራጭ ሠርዓቱን ለመዘርጋት የሚሞክረውን ሰው „ግደሉት“ የሚል ሕግ አላቸው። ነበራቸው።

ውይይትና ክርክር ከመናገር ከመጻፍ ነጻነት ከመሰብሰብና ከመደራጀት እንዲሁም ከመንቀሳቀስ መብት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።

ግን ደግሞ መወያየት መከራከር ዝም ብሎ ተናታርኮ ተጣልቶ ለመለያየት ሳይሆን አንድ ሁሉንም ወገን ሊያሳምን የሚችል እውነትና ሓቅ ላይ ለመድረስ ነው።

እንዴት እንኑር? ችግሮቻችንን እንዴት እንፍታ? ረሃብን እንዴት እናስወግድ? በሽታን እንዴት እንከላከል? ነገ ምን ዓይነት ቀን ይመጣል?….ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች አንድ መልስ ብቻ የለም።

አንድ ሰው ወይም አንድ ድርጅት ብቻውን ትክክለኛ መልስ የለውም።

ወይም ደግሞ የተለያዩ ሰዎች በምሥጢር ተሰብስው „እኛ ብቻ እንውቃለን መልሱም እኛ ጋ ነው። እናንተ ግን ዝም በሉ…“ የሚባልበት አይደለም።

ትክክለኛው መልስ ለአንድ አገርና ለአንድ ሕዝብ ውስጣዊ ችግር ወይም ለሌሎች ችግሮች „ሁሉም የሚሉት ተጨምቆ አንድ ላይ ሲቀመጥ“ ሊሆን ይችላል።

ወይም እነሱ ፖለቲከኞቹ ያልታያቸው ሌላ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ጠበብቶች የሚሠነዝሩት ለየት ያለ አስተያየትና ሓሳብ ሊሆንም ይችላል።

ወይም ሰዎች ሳያዉቁ የሚከራከሩበት ጉዳይ ሌላ አገር ቀደም ሲል መልስ የተሰጠበትም ነገር ሊሆን ይችላል።

ወይም ደግሞ አገሪቱ ቀደም ሲል ከአሳለፈቺውም ታሪክ ጋር የበለጠ ሊቀራረብ ይችላል።

አዲስ ነው ተብሎ የሚነገርለት ነገር ቀደም ሲል ከተካሄደው ስህተትም ጋር አንድ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ የአንድ ፓርቲ አምባገነን ሥርዓት። ለምሳሌ „በቂ ዲሞክራሲና በቂ ነጻነት አገሪቱዋ ውስጥ አለ“ የሚለው አነጋገር። ለምሳሌ „ጊዜ ስጡን“ የሚለው ሽንገላ።

ከአስተሳሰብ ዓለም በምንም ዓይነት ልንወጣ አንችልም። ማንም ሰው ከተለያዩና ከማይጣጣሙ እርስ በእራሳቸው ከሚቃረኑ ወይም ከሚደጋገፉ አስተሳሰቦች ዓለም ፈጽሞ ሊያመልጥ አይችልም።

ግን እነዚህ የተለያዩ የማይጣጣሙ አስተያየቶችና አመለካከቶች ተበጥረውና ተለቅመው -ሁሉንም ወይም አብዛኛውን ሊያስማሙ የሚችሉ – የጥራት ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ።

እንዴት?

በሕዝብ ዘንድ በሰዎች ዘንድ ትክክለኛና ዕውነተኛ በመሆናቸው ተቀባይነት ሲያገኙ ብቻ ነው። ይህም ሥነ-ስርዓት በአለው ክርክርና ውይይት ከሓሳቦች መፋጨት በሁዋላ „…ክፋት ሳይኖረው በጥሩነቱና በደግነቱ በመልካም መፍትሔው ሰው ሁሉ የተቀበለው የሚቀበለው አስተሳሰብ ሲሆን ብቻ ነው።“

ብዙሃኖቹም ሊሳሳቱ ይችላሉ። ግን ብዙሃኖቹ ተቀበሉት ተብሎ የጥቂቶቹ ጩሀት ቦታ የለውም አይባልም። በሸንጎም ውስጥ ሆነ በአደባባይ በጋዜጣ ሆነ በራዲዮና ቴሌቪዥን በቡና ቤት ሆነ በትላልቅ ወይም ትናንሽ አዳራሶች ፊርማ በመሰብሰብ በሰላማዊ ሠልፍ ማንም ሰው እንደገና ለሓሳቡና ለአቋሙ መከራከር መሟገት ድምጽ መሰብሰብ ይችላል።

ለዚህ ዓይነቱ አካሄድና የአኗኗር ዘዴ ደግሞ ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ አመት በፊት የነበረውን ሁኔታ መለስ ብሎ መመልከት ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል።

ክፉና ደግ መልካም ሥራና አረመኔነት የሁለቱን ልዩነት ለማወቅ ይህን ያህል ከባድ አይደለም። እንደሚባለው ሰይጣን አይደለም ዓለምን በዚያውም ኢትዮጵያን የሚያተረማምሰው። ሰው እራሱ ነው። ሰው ደግሞ ሰይጣን ሰይጣንም ሰው ነው።

ሰው ሁሉ ግን እንደምናውቀው ሰይጣን አይደለም።

……

logo-circ-reg

—-

ለ አእምሮ ሚያዝያ 2006 / April 2014 / እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 08

Advertisements

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s