አንዳንድ ግንዛቤ (ርዕስ አንቀጽ/ Editorial)
እንደ ጀመርነው በየወሩ አንዳንድ ጉዳዮችን- ውድ አንባቢ- እናነሳለን። ዛሬም እንደገና ኢትዮጵያ የማን ናት? ብለን እናንተንም እንጠይቃልን።
ዩናይትድ እስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ሆነች ወይም ፈረንሣይ ወይም ደግሞ ደቡብ አፍሪካ የአሸናፊው ፓርቲ „ የግል ንብረትና የግል ሐብት“ እንዳልሆነች ሁላችንም እናውቃለን።
በተቃራኒው ቻይና ወይም ሰሜን ኮሪያ ወይም ደግሞ ኪዩባ የአሸናፊው ድርጅት ያውም የመሪው ቁንጮ „የግል ንብረት“- እነሱ በቃላት ጨዋታ „የጭቁኑ ሕዝብ“ ጥዋት ማታ ይበሉ እንጂ–መሆናቸውን በደንብ ይህንንም ጉዳይ ለይተን እናውቃለን። እንረዳለን።
….ኢትዮጵያ የማን ናት? ኤርትራስ ? ኦሮሞና… አማራስ? የሚለውንም ጥያቄ የምንሰነዝረው -ዘለቅ ብላችሁ አንደምትመለከቱት- ከዚሁ አንጻር ነው።
አንዳንዴ ይህ የስታሊን ቲዎሪና ትምህርት ኢትዮጵያ ባይገባና ባይስፋፋ ኑሮ ሰው ሳያልቅ ትውልዱ በነገር ሳይሳከር ይህች አገር በሥልጣኔዋ እንደ ሌሎቹ መንግሥታትና ሕዝብ የትና የት በደረሰች ነበር እንላለን። … ደርግም ነጻ-አውጪም ጦርነትም ስደትም ክትትልም አምባገነነንትም አለመደማመጥና አለመግባባትም የሚባለውም ነገር በልጆቹዋ መካከል ፈጽሞ በአልተፈጠረም ነበር ብለን እንገምታለን።
ይህን የምንልበት ምክንያትም አለን።
ሌላው ዓለም እንደ እኛ „በነገር አብዶና ተሳክሮ ተዋግቶና ተጨራርሾ በመጨረሻው ለስደት ተዳርጎና ተበትኖ ሲንከራተት አልታየም። ይህ በቂ ማስረጃ ነው።
ምናልባት ሱማሌ ናት። ምናልባት አፍጋኒስታን። ምናልባት ግብጽና ሞዛቢክ ኮንጎና…እነሱም የተበጣበጡት – መለስ ብሎ ታሪክን መመልከትን ይጠይቃል – በዚሁ አፍሪካና እሲያ ቀስ ብሎ ሰተት ብሎ በገባው „ የተለያዩ ትምህርቶችና በእነሱም ፍልስፍና “ነው። ከዚያም ለመውጣት በሚያደርጉት መፍጨርጨር መንገዱ ጠፍቶአቸዋል ።
የሚደንቀው እኛ ሁኔታ ነው። እኛ ገና „…ዲሞክራሲ በገደብ፣ የለም ዲሞክራሲ ያለ-ገደብ፣ ዲሞክራሲ ለሁሉም፣ የለም ዲሞክራሲ ለጭቁኑ… ከነአካቴው ገና አርባ አመት ጠብቅ „ ስንባባል፤ የሞራል ፍልስፍናን መሠረት አድርገው „ለጋማና ለቀንድ ከብት ለለማዳ ውሾችና ለሰለጠኑ ድመቶች…ሙሉ የዜግነት መብት ይሰጣቸው“ የሚሉ ጸሓፊዎችና ፈላስፋዎች እዚህ አውሮፓና እዚያ አሜሪካ ብቅ ማለታቸውና መነሳታቸው ደግሞ እጅግ አስደስቶናል።
ይባስ ብለው አንዳንዶቹማ „ …ለቀበሮና ለተኩላ ለርግብና ለአሞራም የመኖር መብታቸው ተከብሮ ተጠብቆ በእኩል ዓይን እንደ ጎረቤት ዜጋ ከእንግዲህ እንዲታዩ „ -ይህ አንጀት ያርሣል – እሰከ መጠየቅ ድረስ ዘልቀዋል።
እኛም ይህን ጉዳይ እንድታዩት የአነሳነው የሰው ልጆች በአስተሳሰባቸውና በአመለካከታቸው የትና የት -እኛ እዚያው ነገር ውስጥ ስንዳክርና ስንከባለል- ጥለውን እንደሄዱ ለማሳየት ብቻ ነው።
ተመልከቱአቸው አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮች ስለ ተረሳው ስለ ሞራልና ስለ ኤትክ ፍልስፍናዎች ታገኙበታላችሁ።
እኛም ደግሞ፤…. ስለ አንድ በዓለም ታሪክ ስለሚታወቅ ከሰጎን የሚበልጥ ግርማ ሞገስ ስለ አለው ግሩም “የኢትዮጵያ” ትልቅ አሞራ፣ „የማታውቁት እንድታውቁ“ የምታውቁም እንድታስቡበት፣ ስለ እሱ የሕይወት ታሪክ በጥቂቱ አንስተናል።
ይህንንና ሌሎቹን ዝግጅቶቻችንን ገጹን ገልበጥ ስታደርጉት ታገኛላችሁ።
ሽፋኑን ያጌጠው አሞራም „በየአምሰት መቶ አመቱ ሞቶ የሚነሳው“ ይኸው የኢትዮጵያ ልዩ ወፍ አንደኛው የላባ ዘር ሥዕል – ደራሲዎች ገጽታውን ግሩም አድርገው አድንቀው ጽፈውልናል- የእሱ ነው። ወረድ ብለን ስለዚሁ አንድ ሌላ አርዕስትም አንስተናል።
„የሚያስተሳስረን መንፈስ…“ በሚል አርዕስት ሥር „ኢትዮጵያን አትዮጵያ የሚደርጋትን እኛንም የሚያስተሳስር መንፈስ“ አብረን አንስተን አንዳንድ ነጥቦችን ዳሰስናል። ለመሆኑ እነሱ …
….ምንድን ናቸው እነሱ እኛን የሚያስሰተሳስሩ ነገሮች?
በመጨረሻም ምን ጊዜም ከልባችን የማይፋቀውን የጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነውን የአድዋን ድል 118ኛ ዓመት አስበነዋል!
_
መልካም ንባብ….
_
ዋና አዘጋጁ
ይልማ ኃይለ ሚካኤል
—