ታምረኛው „ፎንቅስ“ /Phoenix/

„ፎንቅስ“ /Phoenix

„ፎንቅስ“ /Phoenix

በቁመናው ከሰጎን ይበልጣል። በጥንካሬው የዱር አራዊቶችን ያስፈራራል። በፍጥነቱ በምድር ላይ ማንም አይደርስበትም። አስፈላጊም ከሆነ እንደ መንኮራኩር አጓርቶ መሬቱን በሁለት የእግር ጥፍሮቹ ደብድቦ አንዴ ከተነሳ ጠፈርን በክንፉ ሸፍኖ በአንዴ ውቅያኖሱን አቋርጦ ሌላም አህጉርም በቀላሉ ይገባል ።

አሉ ከሚባሉት ከአንደኛው የላባ ዘር ውስጥ ቢቆጠርም እንደ ሰጎኑ ይህን ፍጡር ከወፍ ወይም ከዶሮ ወይም ደግሞ ትልቅ ክንፍ ከአለው ከዱር አሞራ ዘር መድቦ እሱን መቁጠር ያዳግታል።

በተፈጥሮው እሱን የሚያክልና የሚወዳደር በላባ ውበቱና በግርማ ሞገሱ በደማቃ የተለያዩ ቀለሞቹ ቅንብር -ተፈጥሮ በለገሰው ገጽታው ማንም ወፍ አይስተካከለውም። ቢደመሩም አይደርሱበትም።

ይህ „ፎንቅስ“ የተባለውን ልዩ ስም ይዞ እዚህና እዚያ ታይቶ በተለያዩ አካባቢ የሚገኙትን ተመልካቾቹን ከተፍ ሲል በውበቱ አስደንግጦ አፍ የሚያስከፍተው ትልቁ አሞራ የጥንታዊ ዘመን ደራሲ ላክታንዝ የተባለው ጸሓፊ[i] – ሌሎቹም ስለ እሱ በዘመናቸው ጽፈዋል- እንደ እሱ ግን ተገርሞ በግሩም ቃላቶቹ አሳምሮ የጻፈ ሰው የለም።

„…እንደ እብነበረድ የነጣ ነው“ ይለናል። „… ቢሆንም እነደ ግሩም አዕዋፋት ገጽታ በተለያዩ ቀለማት በሚያብረቀርቁ አንዴ ቀይ አንዴ አረንጓዴ አንዴ ቢጫ አልፎ አልፎም ቀጭን ሰማያዊና ጥቁር ላባዎች ሰውነቱ ተሸፍኖአል። አፍንጫው እንደ ውድ ንቁ ከንጹህ የሚያምር ቀንድ የተሰራ ይመስላል። ሁለቱ እንደ ፈርጥ የሚያማምሩ ክብ ዓይኖቹ እሳት የሚተፉ ናቸው።አናቱ ላይ እንደ አክሊል የተቀመጠው ቀይ ቁንጮው እንደ ጸሓይ ከሩቁ ጨረር ይፈነጥቃል። ይህ ልዩና ትልቁ አሞራ እንደ ሌሎቹ ወፎች ጥራጥሬ ፈልጎ አይለቅምም። ወይም ደግሞ የወደቀ ሥጋ አይመገብም።

የሕይወት ምግቡ የጸሓይ ብርሃንና ጸሓይ የምትፈነጥቀውን ሞቃት ጨረር ነው።….ይህን የመሰለ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቀው በልዩ የላባ ቀለማት ያሸበረቀው አሞራ የመጣውና የተወለደውየቃጠሎ እሰት ደኑን ከአልበላው የውሃ ጥፋት ግሩም መናፈሻ ገነቱን ከአልመታውና ከአላጠፋው ከኢትዮጵያ ምድር ነው። የትውልድ አገሩም ደስ የሚለው የኢትዮጵያ መዝናኛ ሜዳና ሸለቆ ተራራና ዱር ነው።“

ስለዚህ አሞራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው በጥንታዊ የግሪኮች የአተራረክ ዘመን ነው። እኔ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁትና ያወኩት ግሪክ አገርን ስጎበኝ ሳይሆን ጥንታዊዋን የንግድ ከተማ ባህር ላይ ደስ በሚል አርችቴክቶች የተሰራቺውን ቬኒስያን ለሁለተኛ ጊዜ ወርጄ እዚያ በሰነበትኩበት ቀናት ነው።

በመጀመሪያው ጉብኝቴ የማርቆስ ቤተክርስቲያን እና ከተማይቱ የያዘቺውን ደስ የሚሉ የባህር ዳር መናፈሻ ቦታዎችን- የጀልባ ሽርሽሩ አይነሳበተለይ የቅዱስ ማርቆስ ታሪክና ከዚያም በላይ የጣሊያን ሠዓሊዎች የሠሩትን ድንቅ ሥራ እየተዘዋወርኩ(ልቤን ማርከው ነበር) እነሱን ሳደንቅና ስመለከት የቆይታ ጊዜዬን በእነሱ ላይ አጥፍቼ ሌሎቹን ቦታዎች ሳላዳርስ ተመልሼ ነበር።

በሁለተኛው ጉብኝቴ በቂ ጊዜ አግኝቼ ወይዘሮ ማሪያ ካላስ በወጣትነት ዘመኑዋ ትጫወትበት የነበረውን የኦፔራ አዳራሽ – ድምጹዋ ግሩም ነው- እሱን ለመመልከት የተሰጠኝን በእጄ ላይ የሚገኘውን አጃቢ ቴፕ ገና በሩ ላይ ስከፍት በእንግሊዘኛ እና በጀርመንኛ ቋንቋ ስለ ኢትዮጵያው ወፍ ስለ ግሩሙ አሞራ ስለ ፎንቅስ – ሕንጻው አዳራሹ በእሱ ነው የተሰየመው – አንዴ በጆሮዬ ቀስ እያለ ሰውዬው ሲተርክልኝ ተገርሜ ቆሜ ስለ እሱ ከአዳመጥኩኝ ወዲህ ነው። ትዝ ይለኛል- ዞር ብዬ አጠገቤ የነበሩትን ሰዎች ሳይ -አንድ ዓይነት ነገር ነው ለካስ የምናዳምጠው- ጭንቅላታቸውን ሲነቀንቁ ስለ ምን እንደሆን ገብቶኛል።

በሁዋላ እሱንንና ሌሎቹን ከኢትዮጵያ ጋር የሚገናኙ ታሪኮችንና አፈ-ታሪኮች ንግርትና ድርሰቶችን ከግሪክና ከሮማውያን ጽሑፎች ከአረብ ጸሓፊዎች መሰብሰብ ጀመርኩኝ።

አንደኛው እንግዲህ ይህ ነው።

„…በተከታታይ ለአምስት መቶ አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከኖረ በሁዋላ ይህ አሞራ እንደ ንጉሣቸው የሚመለከቱትንና የሚያዩትን የተለያዩ የአገሪቱን አዕዋፋትን አስከትሎና በእነሱ ታጅቦ ወደ ግብጽ አገር „ ደራሲው ላክታንዝ ቀጥሎ እንደጻፈው“ …ዘልቆ ሒሊዮፖሊስ የሚባለው ከተማ ይገባል። አመጣጡ ከዚህቺ ዓለም ተሰናብቶ ለማለፍ ነው።“

የአሟሟቱ ሥነ-ሥርዓት ግን ልዩ ነው።

„…መልካም ሽታ ያለው እጣን እና ከርቤ ተነስንሶለት የወይራ እንጨት እና ጥሩ ማአዛ ያላቸው ቅጠሎች ተጎዝጉዞለት „ እዚያ የአደባባይ አልጋ ላይ ተጋድሞ በቀጠሎው የግብጽ ጸሓይ ጨረር በእሱ ተለኩሶ ነዶ ጋይቶ መልካሙ ጢስ ወደ ላይ እየተና አመዱ እዚያው ጠረኑን እየለቀቀ ነፍሱ ወደ ላይ እንድታርግ ፈልጎ ነው ይባላል።

ከተቃጠለው ላባው፣ሥጋውና አጥንቱ ከወደቀው አመዱ ውስጥ ግን -የታሪኩ ተአምር ይህ ነው– ነፍሱ ሳትሆን ወደ ላይ የወጣችው „…አዲስ እሱን የመሰለ አሞራ… „ ወይም ደግሞ እንደ ገና የዱሮው ታድሶና ተመልሶ ወጣት ሁኖ በእሳት ተፈትኖ „ተወልዶ“ ከዚያ አመድ ተራግፎ ብቅ ብሎ ወጥቶአል። ብቸኛ ስለሆነ እንደሌሎቹ ፍጡሮች የሚወለደውና የመጸነሰው ወይም የሚፈለፈለው ከወንድና ከሴት ጸታ አይደለም። እሱ የተወለደውና የሚወለደው ሁል ጊዜ በየአምስት መቶ አመቱ ከእሳትና በእሳት ነው።

„…እንዴት ያለህ የተባረክ አሞራ ነህ። ሞትን አትፈራም። አንተው እራስህ የእራስህ ፈጣሪ የእራስህ አዋላጅ የእራስህ ሞግዚት የእራስህ ጠባቂ ነህ…“ ብሎ ደራሲው ላክታንዝ ተደንቆ ይህን የመሰለ ቃላት ለእሱ መርጦ በዘመኑ በጻፈው ጽሑፉ ላይ አስቀምጦለታል።

ይህን የመሰለ ግሩም ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ አሞራ „ሞቶ በእሳት ተፈትኖ ከወደቀበት አመድ በየአምስት መቶ አመቱ በመነሳቱ“ ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋር አብዛኛዎቹ ጸሓፊዎች አያያይዘውታል።

ፎንቅስ የሚባለው አሞራ ይኑር አይኑር -ይህ አያጠያይቅም ግልጽ ነው። የሚያጠያይቀው አንድ ጊዜ አርባ ሰባት አመት ከክርስቶስ ልደት በሁዋላ በዚህች ምድር ላይ ታየ የተባለው ፎንቅስ አሞራ ዕውነተኛው ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ጥያቄ ነው።

በዚያን ዘመን ታየ የተባለው አሞራ አምስት መቶ አመት ሳይሞላው ተቃጥሎ ከአመዱ በወጣ በግማሹ ላይ ማለት ከሁለት መቶ ሃምሣ አመት በሁዋላ ብቅ ያለ ወጣት አሞራ ነበር ይባላል።

ሁለት አማራጭ መፍትሔዎች መገመት ይቻላል። የትኛው ትክክለኛ እንደሆነ -የመጀመሪያው ይሁን ሁለተኛው- መልሱን ለማወቅ በጣም ያስቸጋራል።

እንደዚሁ ለማወቅ የሚያስቸግረው ነገር የሮማው ሊቃነ ጳጳስ ክሌመንስ ሰባተኛው ለኣይርላንዱ ተቃዋሚዎች ከቤተ- ክርስቲያኑዋ ተገንጥለው „በአፈነገጡት“ በእንግሊዞች ላይ እንዲነሱ ለማበረታቻ ላኩ የተባለው ባለወርቅማው የፎንቅስ ላባ ዕውነተኛ ታሪክ ይሁን አይሁን:-ስለ እሱም ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።

ኢትዮጵያ ግን ቢያንስ በየአምስት መቶ አመቱ በተከታታይ አደጋና መከራ ላይ ይህች አገር ወድቃ ትንሣኤዋን ሁሌ – በታሪኩዋ ላይ እንደታየው ከአመድ ወጥታ ብቅ ብላ እንደገና ታድሳ እንደተቋቋመች እናውቃለን።

ከአምስት መቶ አመት በፊት ከተካሄደባት የግራኝ መሓመድ ወረራ በስንት ብልሃት አምልጣለች።ይህ አንደኛው ነው። ከዚያ በፊት ከአምስት መቶ አመት በፊት የተካሄደው የዮዲት ጉዲት ሥራና ጥፋት እንደዚሁ ተርፋለች። ይህኛውም ሁለተኛው ነው። የኢትዮጵያ ግዛት ከፋርስ እሰከ ሕንድ ውቅያኖስ ከግብጽ እሰከ ደቡብ አፍሪካ የተስፋፋበት የአጼ ካሌብ ዘመን ሦስተኛው ነው። እሱም የውጭ ወረራን ከመከላከል የመጣ ነው።

አሁን ያለንበት አንዱ አንደኛውን የማይሰማበትና ሌላውን ጨርሶ የማያደምጥበት ዘመን ሌላው የፈተና ጊዜ ነው። ይህ ከሆነ ቢያንስ አርባ ሃምሣ ዓመት አይሆነውም? ከዚያ በፊት ማይጨውና አድዋ አሉ። በየአምስት መቶ አመት…

ዓለም እንዴት እንደተፈጠረችና ጠፈር -ዩኒቨርስ እንዴት መስመሩዋን ይዛ ሳትጋጭ እንደምትንቀሳቀስ የሕይወት እስትንፋስ- ነፍሳችን ምን እንደሆነች? ብዙዎቹ ነገሮች ከዕውቀታችን በላይና ውጭ ስለሆኑ ይህ ነው ይህ ነው ብለን አሁን መናገር አንችልም።

የሚደጋገመው የሰው ልጅ ሆነ የእህል ዘር…ግን መሬት ላይ ይወድቃል። ይበሰብሳል።እንደገናም ይበቅላል። ተመልሶም ይነሳል።ይህ ደግሞ አዲስ አይደለም። ዱሮም እንደዚህ ነበር። አሁንም ወደፊትም እንደዚሁ ይቀጥላል።

„የትንሣኤ“ ምልክት የሆነውን ፎንቅስን ታሪክ ዛሬ ያነሳነው ኢትዮጵያን ዘለዓላማዊ ከሚያደርጉአት ነገሮች ውስጥ አንዱ የሆነውን ንግርትእሱን ዛሬ ለማስታወስ ነው እንጂ ዕውነተኛው የትንሣኤ[ii] ቀን ፋሲካ ነው። ይህንንም ያንንም የኢትዮጵያ ስምና ታሪክ ደግሞ ማንም ሰው ይደክማል እንጂ አይፍቀውም።ሊፍቀውም ቢሞክር አይችልም።


[i] LaktanzLUCIUS CAECILIUS FIRMIANUS 240 ዓ.ም በሰሜን አፍሪካ የተወለደ

[ii] ሐዋሪያ ጳውሎስ ስለ ዘርና ፍሬ ስለ ትንሣኤ

አእምሮ የካቲት 2006 / February 2014/ እትም፣ቅጽ 2 ቁጥር-7

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s