አስተሳሳሪው መንፈስ

አስተሳሳሪው መንፈስ

Phoenix_by_WhiteRaven90

አንድን ሕብረተሰብ ምንድነው አንድ አድርጎ የሚያስተሳስረው ?

በአንድ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ እያንዳንዱ የአሜሪካ ዜጋ ፈረንሣይና ጀርመን ኬንያና ናይጄሪያ ቻይና እና ሕንድ ኢትዮጵያዊውና አረቡ እርስ በእራሱ አይተዋወቅም። ያም ሆኖ ግን አንድ የሚያደርጋቸው ነገር በመካከላቸው አለ።

ምንድነው ታዲያ ያ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር?

ክፋትና ቅናት ጥላቻና ንቀት የተደበቁ አጀንዳዎች ሰዎችን እንደማያሰበስቡ እናውቃለን።

አለጥርጥር በአንደኛ ደረጃ መጠቀስ የሚገባው ነገር ቢኖር ሃይማኖት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ አንድን ሕብረተሰብ የሚያስተሳስረው ነገር የጋራ ቋንቋቸውና ፊደላቸው ነው። በጋራ ያሳለፉት ታሪካቸውም ሌላው በሦስተኛው ረድፍ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ ያለፈውን „በደንብ የማናውቀውን „ የአያት ቅድመ አያቶችን ዘመንንም ያካትታል።

ሃይማኖት ነው እንዳይባል ኢትዮጵያ በሦስት ትላልቅ ሃይማኖቶች ስለተከፋፈለች „እኛ እንደ አረቡና እንደ ቻይናው እንደ ሕንዱና እንደ ቱርኩ አንድ ወጥ ሃይማኖት ሁሉንም ያሚያያይዝ እምነት የለንም „ ስለዚህ „አንድ የሚያደርገን መንፈስ በመካከላችን የለም“ የሚሉ ሰዎች አይጠፉም።

ይህ አባባል በትክክሉ ለመፍረድ ዕውነት ነው?

ለመሆኑ ሕንዶችና ቻይናዎች አረቦችና እሥራኤሎች አሜሪካና ጀርመን… እነሱስ ቢሆኑ …አንድ ሃይማኖት ብቻ ነው ያላቸው?

አይመስለንም።

የተለያዩ ቋንቋዎች ሕዝቡ በኢትዮጵያ ሰለሚናገር እኛን እንደ ጀርመንና እንደ አሜሪካን እንደ ሩሲያና እንደ ስዊስ „የሚያስተሳስር አንድ ቋንቋ በመካከላችን የለንም ።ስለዚህ ይህ እሰከ ሌለን ድረስ የጋራ ቋንቋ አለን ብለን መናገር እንችልም“ የሚሉ ሰዎች በየአለበት ይደመጣል።

እሱስ ቢሆን (እንደዚህ ዓይነቱ አባባል) ዕውነት አለው ?

ታሪካችን በብዙ መካራና ደስታ በክፉና በደጉ በውድቀትና በመነሳት በረሃብና በችግር በጥፋትና በልማት „የታጠረ“ ነው። ስለዚህ በዚህ መንገድም እኛን „….ታሪካችን አንድ ሊያደርግ አይችልም „ የሚሉ ሰዎች በመካከላችን አሉ።

በደም ላይ ያልተገነባ በሠይፍና በጦር ያልተዋቀረ የአገር አንድነት፣የመንግሥት አመሰራረት እንዲያው ዝም ብሎ የተሰባሰበ ግዛት በዚህች ዓለም ላይ አለ?

መልሳችን አጭር ነው። የትም ቦታ የለም።ሁሉም -ተዘዋወሩና ተመልከቱ- በኃይል ነው የተዋቀረው።

የኢትዮጵያ ታሪክ አነሳስና አካሄድ ከአሜሪካኑና ከእንግሊዙ ከጀርመኑና ከሩሲያው ከፈረንሣዩና ከጃፓኑ ከኬንያኑና ከደቡብ አፍሪካው አመሰራረትና አመጣጥ ፈጽሞ የተለየ አይደለም።

ለጋና እና ለናይጄሪያ ለሕንድና ለታላቁዋ ብርታኒያ ለአሜሪካና ለአውስትራሊያ የጋራ ቋንቋቸው እንግሊዘኛ ነው።

ይህ ስለተባለ ግን ሌላ ቋንቋ የእነዚህ አገር ኑዋሪዎች አይናገሩም ማለት አይደለም። በዘልማድ እንግሊዝ በሚባለውም ታላቁዋ ብርታኒያ እዚያ አገር አየር ላንድ ዌልስ ስኮትላንድ የሚባሉ አካባቢና የተለያዩ ቋንቋዎች እናያለን፣ እንሰማለን። ግን ሁሉም የሚግባቡበት ቋንቋ አንድ ነው።እሱም ከሌላ ቦታ የመጣው እንግሊዘኛ ነው።የእንግሊዘኛ ቋንቋ ዕድሜው ደግሞ ረጅም አይደለም። እራሳቸው እንግሊዞች ፈረንሣይኛ ይናገሩ ነበር።

በሩሲያና በኬንያ በሕንድና በኮንጎ በደቡብ አፍሪካም ብዙ የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩ ዘሮች አሉ። ግን አንድ የመማሪያና የመግባቢያ የገበያ ላይ መለዋወጫና መነጋገሪያ ቋንቋ ከመጠቀም እነሱን የሚያግዳቸው ነገር የለም።

አማርኛ ከግዕዝ በሁዋላ ለኢትዮጵያ እንደሆነው ሁሉ ለቻድና ለሴንጋል ለአይቮሪ ኮስትና ለኮንጎ ለግብጽና … ለእነሱ ደግሞ የአውሮፓው ፈረንሣይኛ ስፓንሽና ፖርቱጋል…ከመካለኛው ምሥራቅ ጠመጣው አረብኛም እንደ አካባቢው የጋራ ቋንቋቸው ሁኖ እነሱን ከጥቂት አመታት ወዲህ ያገለግሉአቸዋል።

ቀደም ሲል ሃይማኖትን አንስተን በኢትዮጵያ ሦስት ትላልቅ ሃይማኖቶች እንዳሉ ጠቀስን እንጂ አንድ የሚያደርጋቸውን ስለ አንድ „አሃዱ አምላካቸው“ ሳናነሳ አልፈናል።

አይሁዱም ክርስቲያኑም እስላሙም የሚያምነውና የሚጸየው -ይህ ደግሞ አቴኢስቱን አይጨምርም- ለአንድ ፈጣሪው አምላኩ ለእግዚአብሔር ነው። ይህ ነው እንግዲህ ዋናው ነጥብ እነሱን አማኞቹን በኢትዮጵያ አንድ የሚያደርጋቸው መንፈስ ነው። አንድ አድርጎአቸውም ያቆያቸው።

አንድ ቦታ ላይ ስለ ኢትዮጵያኖች የምግብ አሰራር፣ስለ የጋራ ሸማ ልብሳቸው፣ ስለጥልፍ ቀሚሳቸውና ቡሉኮአቸው የቤት ቁሳቁሳቸውና የጋራ በዓላቸው ሠርግና ሐዘናቸው ቀብራቸውና ለቅሶአቸው ጭፈራና ድግሳቸው ደቦና አፈርሳታ አንስተን አልፈን ነበር።

ከዚሁ ጋር ስለልማድና ስለባህላችን ስለተትሩፋትና ስለትውፈታችን ስለሥነ ምግባራችንና ስለእሴታችን ስለ ግብረ ገብ ትምህርትና ስለ አስተዳደጋችን ስለ እነዚህ ሁሉ እኛን ከጎረቤትም አገር ከሌላው ዓለም ልዩ ከሚያደርጉን ነገሮች ከብዙ በጥቂቱ በአለፈው ጊዜ እንደዚሁ አንስተን ጽፈናል።

ድርሰቶቻችንና ጽሑፎቻችን አሉ። ታሪክና ምሴሌዎቻን አሉ። ተረትና ጨዋታዎች። ዘፈንና ጭፈራዎች። የሙዚቃ መሣሪያዎቻችን ዋሽንትና መለከት ከበሮና ድቤ ጦርና ጋሻ ቀረርቶና እንጉርጉሮ…

በዚያ ላይ አንድ የሚያደርገን የስፖትር ጨዋታም አለ። ማን ነው ለመሆኑ የአገሩ ልጅ ማራቶን ሮጦ ሲያሸንፍ ሳይዘል ቁጭ ብሎ የሚያየው?… አሥር እና አምስት ሺህ ስምንት መቶና ሦስት ሺህ…ተከታትለው ሲገቡ የማይፈነድቀው? ኳስ ሲጫወቱ አብሮ የማይጨነቀው?

ግን ደግሞ የአበሻ ልብስ የማይለብሰውን ቴሌቭዢንና ኮሚፒውተር ሞባይል የሌለውን ባዶ እግሩን የሚሄደውንና መጻፍ ማንበብ የማይችለውን የገጠር ሰው እሱን „ኢትዮጵያዊ አይደለም“ ልንል እንችላለን?

የደቡቡ የዶሮ ወጥ አሰራር ከሰሜኑ ይለያል? የሸክላ ድስት ምጣድና አኩንባሎ ቡናውና ዕጣኑ ጠላና ጠጁ እንጀራና ዳቦው እነዚህ ሁሉ ምንድናቸው?

ሌላም መነሳት ያለበት ጉዳይ አለ!

በዚያ ኢትዮጵያ በሚባለው ክልልና ግዛት ውስጥ ብቻ መወለዱ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት አንድን ሰው ወደደው ጠላው ተቀበለው ወይም ይህን አውልቆ ጣለው እሱን ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ልክ እንደ አሜሪካኑና እንደ ግብፁ እንደ ሕንዱና ታንዛኒያው ሕዝብን ያስተሳስራል።

አንድን ሕዝብ የሚያስተሳስር ሌላው አሁን ወደ መጨረሻው ላይ መጠቀስ ያለበት ተጨማሪ ትልቅ ነጥብ ቢኖር በአዋቂዎች የተነደፈው „ሕገ-መንግሥቱ“ ነው።

ሕገ-መንግሥት/ቶች እንደ አገሩ ይለያሉ።

የነጻ ሰዎች የግለሰብ መብት የሚያውቀውና የሚያከብረው ዲሞክራቲክ ሕግ መንግሥት ሕዝብን አንድ አድረጎ እንደ ሃይማኖት የሚያስተሳስር ዘመናዊ ምሶሶና ግድግዳ ጣራና አጥር ነው።

ከሁሉም ግን ወይም እላይ ከተጠቀሱት ጉዳዮች ጋር በተጨማሪ አንድን ሕዝብ አንድን አገር -ከሃይማኖትና ከዘር ከመደብና ከሐብት ከዕድሜና ከጾታ ከጉልበትና ከጥንካሬ ከጤና ከደካማ በሽታኛ ከእነዚህ ሁሉ ባሻግር (የሰው ልጆች በሥራቸውም በችሎታቸውም የተለያዩ ናቸው) እነሱን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር እርስ በእርስ መተማመንና እሱ ላይ ተመስርቶ የሚገነባው የወንድማማችነት መንፈስና ፍቅር ነው።

ይህ በአንድ ሕብረተስብ ውስጥ በጣም ከፍተኛ ቦታ የአለው „የዜጎች ፍቅርና መፋቀር“ ከየት ይመጣል?

መተማመን የጠበቀ መተሳሰርንና አንድነትን ወንድማማችንነት በሰው ልጆች መካከል እንዴት ይፈጥራል?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ „ጥላቻ“ ከየት ይመጣል? ብሎ እራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።… ንቀት፣ቅናት፣ክፋት …እነዚህ ሁሉ ከየት ይመጣሉ ብሎ መመራመርን ይጠይቃል።

እንደዚህ ዓይነቱ መፈቃቀርና አንድነት መተማመን በሰዎች መካከል እንዳይመሰረት „ልዩነትን“ ብቻ ጥዋት ማታ የሚያስተምሩ ክፉ ሰዎች፣ አክራሪ በአገራችን እንደሚባለው „ቀስቃሽ ካድሬዎች“ በመካከላችን እንዳሉም መረዳት ያስፈልጋል።

እንደዚህ ዓይነት ሰዎችደግሞ-ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ቦታ አሉ። እኛ ጋ ግን ልቅ እያጣ መጥቶአል። መድሓኒቱ ታዲያ ምንድነው?

መድሓኒቱ አንድ ነገር ነው። በልዩነት ፋንታ አንድነትን ማስተማሩና የሰበአዊ መብቶችን ጥያቄ ከፍ አድርጎ ማንሳቱ ከፋፋዮችን – ይህ ነው ብልሃቱና ዘዴው እነሱን መቆሚያ ያሳጣቸዋል። በተለይ በጨለማ ሳይሆን በግልጽና ብርሃን በሚፈነጥቀው በጥበብና ዕውቀት ላይ ተመርኩዞ በጋዜጣ ላይ መወያየቱ።

የሰለጠነ ዘመናዊ ሕብረተሰብ ከሃይማኖትና ከዘር ልዩነት ከዚያም በአሻግር አንድ የሚያደርጉትን እሴቶች ፈልጎ አግኝቶ በእሱ ላይ ጠንክሮ በመሥራት ብዙውን የውስጥ ችግሮቹን (ያለህበትን አካባቢ ተመልከት)በቀላሉ እሱ ፈቶአል። አንደኛው መንገድ ነጻ ሰው መሆን ነው። ሁለተኛ ሳይንስና ምርምር ትምህርት ነው። የጥበብ ሰው ከብዙ የጥፋት መንገዶች ይቆጠባል።

እንግዲህ በትክክል እንደሚታየው እያንዳንዱ የአገሪቱ ዜጋ ኃላፊቱን አይቶና ተገንዝቦ ቆርጦ ለእራሱና ለቤተሰቦቹ ለጎረቤቱና ለእናት አገሩ የተቻለውን አስተዋዕጾ – በብዙ አገሮች እንደምናየው- ለማበርከት የቻለውም ነጻ ሕብረተሰብ ውስጥ ለመተንፈስ በመቻሉ ነው።

ያኔ ነው ሠራተኛውና ነጋዴው አስተማሪውና ሐኪሙ ተማሪና ገበሬው እንጂነሩና አናጢው…. አገሬ ሐብቴ መሬቴ አየሬ ብሎ ለእናት አገሩ ያለው ፍቅር የሚጠነክረው።

መተማመን በሰዎች መካከል የነገሮች ሁሉ መሰረት ነው። በነጻ ሕብረተሰብ ውስጥ ደግሞ ሁሉ ነገር ሳይሸፋፈን ግልጽ ስለሆነ ሰዎች እርስ በእራሳቸው በቀላሉ መተማመን ይችላሉ።እምነት ደግሞ አብሮ ለመኖር መሰረት ነው። ይህም በመሆኑ ነው በምሥራቁና በምዕራቡ ጀርመን መካከል ያለውና የነበረው „ልዩነቶች“ ተወግደው የበርሊን ግንብ የሁዋላ ሁዋላ ተገርስሶ ሊወደቅ የቻለው።የወደቀውም።

በእነሆኔከር ፍልስፍና እና ፍላጎትማ ቢሆን የበርሊን ግንብ ገና መቶ ወይም ሁለት መቶ ወይም ደግሞ ከአንድ ሺህ አመት በላይ ተገትሮ በቆመላቸው ነበር። ግን የተመኙት አልሆነም።ከእነሱም ጋር የአንድ ፓርቲ አምባገነን ሥርዓት አብሮ ተበትናአል።

በዘር ልዩነት በኢትዮጵያኖች መካከል ግንብ ማጠር የሚፈልጉ አሉ።በኤርትራና በኢትዮጵያ በኦሮሞና በአማራ….መካከልም የጥላቻ መርዝ የሚረጩ። እርስ በእርስ ከመተማመን ይልቅ „የውጩን ባዕድን“ የሚያምኑና የሚያቀርቡም አሉ። ግን የሁዋላ ሁዋላ አሸናፊው ተንኮልና ጥላቻ ንቀትና ቅናት ክፋትና ውሽት አይደለም። አሸናፊው ዕውነትና ፍቅር የወንድማማችነት መንፈስ ነው።ሌሎች ቦታዎችና አካባቢዎች የምናየውም ይህንኑ ሓቅ ነው። ኢትዮጵያም አይቀርላትም።

ከአገር ልጅ ባዕድን ማመን ደግሞ አንድ ቀን ባሪያ ያደርጋል። ባርነት የዓለም አቀፉ አዋጅ ይጥፋ ይላል።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

አእምሮ የካቲት 2006 / February 2014/ እትም፣ቅጽ 2 ቁጥር-7

Advertisements

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s