ከ -ካ ሲ ዮ ጵ ያ እስከ መ ገ ነ ጣ ጠ ል !

ከ -ካ ሲ ዮ ጵ ያ እስከ መ ገ ነ ጣ ጠ ል /

ከ – ዮጵ ያ እስከ መ ገ ነ ጣ ጠ ል/[1]

ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት እንደ ማስቲካ መልሰው መላልሰው የሚታኘኩ አርዕስቶች አሉ።

ይህ ደግሞ ዛሬ አይደለም የተጀመረው። ቆይቶአል። እንዲያውም የሺህ አመታት ዕድሜ አለው።

አረቦች ሃይማኖትን ሰበብ አድርገው ይህቺን አገር በትነው ለመያዝ በተዳጋጋሚ ሞክረዋል። ግብጾች ከጥንት ከፈርኦን ዘመናት ጀምረው የካሄዱት ተንኮል አንዴም ሳይሳካላቸው ቀርቶአል።

ፋርስብዙ ደክማለች። ግን አልሆነላትም። ታላቁ እስክንድር ብቻ ነው ዓለምን ለመግዛት ሲነሳ እኛን ሳይነካን አክብሮ በድንበሩዋ ላይ በማለፉ „ቅዱስ“ የሚባለውን ስም እሱም ሊያተርፍ የቻለው።

የሮማው ቄሳሮች-ኃይለኛው የዩሊዮስ ሴዛር እንኳን ያልደፈረውን በሁዋላ አርፍዳ የተቋቋመቺው የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን ቅኝ አድርጋ ልትገዛ ሁለት ጊዜ መጥታ ሁለት ጊዜ ድል ተመታ ወደ መንደሩዋ ተመልሳለች።

Cassiopea-Poeticon_astronomicon_cas

እነዚህ ሁሉ ያልቻሉትን አሁን አንዳንድ ልጆቹዋ በተለያዩ ስሞች „ኢትዮጵያ“ የሚባል ነገር የለም ብለው አድመው ተነስተውባታል። ጥያቄው እነሱ ስንት ናቸው የሚለው ነው?

አንድ መቶ? አምስት መቶ? አንድ ሺህ? ወይስ እነደሚፎክሩት ሁለትና አምስት ሺህ?

እነሱስ በየጊዜው ምን ይላሉ? የሚለው ቀጣዩ ጥያቄ ነው።

ምንድነው ሁል ጊዜ እንደ አዲስ ነገር የሚነሳው? የትኛውን አይዲኦሎጂ ነው የሚከተሉት?

አንደኛው „የብሔር /ብሔረሰብ እኩልነት?“ የሚለው ተገቢ የሆነ ጥያቄ ነው።

ሁለተኛው „…. እሰከ መገንጠል „ የሚለው ቅጥ ያጣ ጣጣ ነገር ነው።

ይህ አመለካከት እንደዚህ ዓይነቱ ጥያቄ ከየት መጣ? የት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ መፈክር የተሰማው? ማነው የዚህ „ግሩም „ቲዎሪ አባቱ? ስንት ሰዎች ናቸው የዚህ ጥያቄ አራማጆቹ ? የት ቦታ ነው ይህ አይዲኦሎጂ በሥራ ተተርጉሞ ሰውን የስደሰተው?-በኤርትራ?

ይህን አንስተን -የነገር ቋንጣ የለውም – መልስ እንሰጥበታለን።

ሁለተኛው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተወረወረውና ግራ የሚያጋበው „በአማራው ላይ ብቻ የሚወረወረው ቅኝ ገዢዎች“ የሚባለው ክስ ነው።

ለመሆኑ ማን ነው ዛሬ? ማንን ዛሬ የሚገዛው? የኦሮም ክልል ተብሎአል። የትግራይ ክልል ተብሎአል። የኦጋዴን… የአፋር የደቡብ ሕዝቦች…ተብሎ ማን ነው ማንን አሁን የሚያስተዳድረው? የሚገዛውስ? ለዚህ የሚሰጠው መልስ በቂ ነው።

ሦስተኛው ኢትዮጵያ ከተመሰረተች ቢበዛ „ አንድ መቶ ዓመት ነው“ የሚለው የሕዝባዊ ወያኔና የኦነግ – በቅርቡ እንደተነበበው ደግሞ አቶ ኢሳያስ ወደ ታች ቀንስው ከእራሳቸው ዕድሜ በታች አድረገው „65 አመቱዋ ነው“ የሚለው ትንተና ነው።

ለምን 50 አይሉም?- ለምን 25 አመት ብቻ ነው? „ታሪክ“ ጸሓፊዎቻችን አይሉንም?

የእነሱን „ታሪክ“ አጻጻፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አንስተን ማየት- ዕድሜ ልክ ስለ አንድ ነገር ዝም ተብሎ እንደ ሞኝ አይወራም- ነገር ለመቋጨት አስፈላጊ ነው።

ምናልባት ለማዘናጋት አውቆ የተወረወረ ነገር ይሆን? የልባቸውን እየሰሩ ሰውን በዚህ ጥያቄ ጠምዶ ለመያዝ ይሆን?

ነጮች እንደዚህ ዓይነቱን ጉዳይ -ነገር ለማዘናጋት የሚደረገውን ያፍዝ፥አደንግዝ የፖለቲካ ጨዋታ – በዚህ አሳይቶ በዚያ ለመሮጥ „ፊንታ“ ይሉታል። በእርግጥም ብዙ ሰው እንደዚህ ዓይነቱ „የተማሰ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ“ ጊዜውን በከንቱ ያጠፋል።

አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ „ታሪክ“ ቢያንስ በሌሎቹ ሒሳብ አርባ ሺህ ሲደርስ አንቹም ጠበብቶችቢያንስ „የአሥር ሺህ አመት ዕድሜ አላት“ ለማሳመን ተነስተዋል። ለቀስቃሽ ፖለቲከኞች ሳይሆን ለምን ጉዳዩን ለታሪክ ጸሓፊዎች አንተውም። ኢሳያስ አፈወርቂና ሌሎ የታሪክ ሰው እንዳልሆኑ እናውቃለን።

„ኢትዮጵያኖች ተጋብተው ተዋልደው ተካልሰዋል ወይስ ሳይነካኩ በጉርብትና ብቻ ከሩቁ እየተያዩ ሳይካለሱ ኑረዋል ወይ?“ የሚለው ጥያቄ ወደፊት አራተኛውን ቦታ ይይዛል።

የጋራ መገበያያና መግባቢያ መማሪያም ቋንቋ ሊንጉዋ ፍራንካ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም? የሚለውም ጥያቄ አብሮ ወደፊት ይታያል። ይህም አምስተኛውን ቦታ ይዞአል።

በስድስተኛ ደረጃ ደግሞ ደጋግሞ እንደ አዲስ ነገር ስለ ዜጎች መብት (በዘር ላይ የተመሰረተ ሳይሆን) ስለ እያንዳንዱ ኢትዮጵያው ግለሰብ መብት መከበርና መጠበቅ በኢትዮጵያ እንደዚሁ እናነሳለን።

እንግዲህ በሰባተኛ ደረጃ ስለ „ዲሞክራሲና ስለ ዲሞክራሲ የምርጫ ሥርዓት „ ስለ እነሱም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜም ባይባልም፣ ቢያንስ ግልጽነት ሰፍኖ„ የወሃ ቅዳ የወሃ መልስ“ ጨዋታና ፌዝ በአገራችን ፖለቲከኞች መካከል ማሳረጊያውን እንዲያገኝ – ማሲቲካም ታኝኮ የዚያኑ ቀን ይጣላል- ይህ እንዲሆን ወደፊት ጥረት እናደርጋለን።

„ለመሆኑ በድርጅቱ አመራር ውስጥ ማነው ከሌሎቹ እጩዎች ጋር በይፋ ተወዳድሮ በአባለቶቹ በድምጽ ብልጫ የተመረጠ?“ብለንም ሁሉንም ፓርቲ እንጠይቃለን።

ስለብሔር እኩልነት እሰከ መገንጠል ድረስ የሚለውን ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች እዚያ ላይ ከመድረሳችሁ በፊት በእራሳችሁ ቤት በመጀመሪያ በእኩልነት ደረጃ ከሌሎች አባሎች ጋር አብራችሁ ቆማችሁ በድርጅታችሁ ውስጥ ምርጫ አካሁዳችሁ ተመረጡ እንላለን። እንደዚህ ዓይነቱን አሰራር በእያንዳንዱ ድርጅት ውስጥ መኖር አለበት ብለንም ይህ የድርጅት ውስጥ ዲሞክራሲ እናነሳለን።

ይህን ለማለት በቂ ምክንያት አለን።

አንዳቸውም ቢሆኑ በገዛ ቤታቸው ጋዜጠኞችን ጠርተው በይፋ ከሌሎቹ ጋር ተወዳድረው በአባሎቹ በብዙሃኑ ድምጽ የተመረጡ ሕጋዊ ማንዴት ያላቸው የድርጅት መሪዎች አይደሉም። ለምን ሰለእሱ አንስተው ሰዎች አይከራከሩም?

ሁለተኛ እንዲያው በዘልማድ „…እሰከ መገንጠል ድረስ „ ይባላል እንጂ ያንን ጥያቄ በተግባር በሥራ ለመተርጎም በሚደረገው ጉዞ „የሚወራረደው ሒሳብ“ ማለት ከመስዋዕትነት እሰከ ጥፋትና ፍጅት ከዚያም አልፎ በደርግ እና በእህአዴግ የግዛት ዘመን በኤርትራ ላይ እንዳየነው ያ ሁሉ ትርምስ በመጨረሻው ወዴት ያመራል የሚለው ጥያቄ በደንብ የታሰበበት -ከላይኛውም መራራ ጉዞ ትምህርት ያልተገኘበት ታሪክ ነው። ለምን ስለዚህ ጉዳይ አይነሳም?

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው የተካለሰው ቤተ ሰብ ምን ይሆናል? እነዚህንና ሌሎቹን ጥያቄዎች ያልመለሰ ሰው -አንዴ እጃችን ተፈጅቶአል- ይህን „የመገንጠል“ ጥያቄ ዝም ብሎ ወርውሮ አውላላ ሜዳ ላይ ሊንጎራደድ አይችልም ። ሕዝቡም አይቀበለውም። እንግዲህ ይህን እናነሳለን።

አብዛኛውን የኢትዮጵያን „ፖለቲከኞች“ አእምሮና ልብ እሰከ ዛሬ ድረስ አሸንፈው የሳቡትና የማረኩት „የእነ ማርክስና የእነ ኤንግልስ የእነ ሌኒንና የእነስታሊን የነማኦና…የነ ምንትስ “ትምህርቶች በአጠቃላይ የኮሚንዝም ቲዎሪ – እነሱ ናቸው(በጀርመን ምሳሌ እንዳየነው) አገሪቱን አተረማምሰው እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሱ ፍልስፍናዎች- ስለሆነ፣ስለዚህ የእነሱ ትምህርትና ፍልስፍና ለአገሪቱ ችግር መፍትሔ እንዳልሆኑ ወደፊት ሳንታክት መልሰን መላልሰን እናነሳለን። የኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር ማሰሪያ ያላገኘው፣ደርጅቶችም በአገሪቱ ውስጥ የማይስማሙት አብዛኛው የፖለቲካ ደርጅት ይህን ፍልስፍና በመከተሉ ነው። ችግሩም ያለው እዚያ ላይ ነው። መቁጠር ይቻላል…

የፈለገ ሰው እንደሌላው ዓለም (በጀርመን አገር ሕገ-መንግሥቱን እሰከ አከበሩ ድረስ ኒዎ ናዚዎቹ ሆነ ኮሚኒስቶቹ መደራጀት ይችላሉ) በዚያ አይዲኦሎጂ በዚያ ትምህርት ሥር መንቀሳቀሱ መብታቸው ስለሆነ ይችላሉ- ግን እሱ ብቻ ነው ለኢትዮጵያ መፍትሔው ወይም እኔ ብቻ ነኝ መፍትሔውን የማውቃው ብለው ሲሟገቱ ከአገኘን- እንደዚህ እያሉ የሚተናነቁ ናቸው – ( ለአገሪቱ ለኢትዮጵያ ችግር ስታሊን ሆነ ማርክስ እሰከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት መፍትሔ አላመጡም)- ተገቢውን ትችታችንን እንሰነዝራለን ።

የኤርትራ፣ የኦሮሞ የትግሬ፣ የኦጋዴን ….ጥያቄ ያለ ስታሊን ቲዎሪና ያለ ማርክስ እና ሌኒን ያለ ማኦ ትምህርትና አይዲኦሎጂ ስማቸውን እየቀያየሩ መጥተው ደጋፊ አባልና ተከታይ ጀሌ መሰብሰብ እንደማይችሉ አንስተን በየጊዜው እንደዚህ ዓይነቱ ጨዋታ ወደፊት መልክ እንዲይዝም እንጥራለን።

በስታሊን ቲዎሪ በማርክስ ትምህርት በሌኒን እና በማኦ አይዲኦሎጂ የትም ቦታ የትም አገር-የታወቀውን ለመድገም- የትም አህጉር ጤነኛ መንግሥት እንዳልተገነባ በየጊዜው እናነሳለን።

ቻይናንን የሚጠቅሱልን አሉ። ኪዩባን የሚጠሩ። ወይም እስከነካቴአንዴውኑ ሰሜን ኮሪያን የሚጠቅሱም ከመካከላችን አይጠፉም። ግን በእነዚያ መንግሥታት ሥር ሰበአዊ መብቶች ይከበራሉ? ለመሆኑ ሕዝቡ መሪዎቹን መምረጥ ይችላል? ነጻ-ጋዜጣ ነጻ ኢንተርኔት አለ? ሰው በሰላም ያለሰላይ የልቡን መናገር ይችላል?

እላይ በተጠቀሱት ሰዎች ትምህርትና ፍልስፍና ሥር „ሰበአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ በእነሱ አይዲኦሎጂ ሥር የትም አገር -እንደገና የታወቀውን ለመድገም- በሥራ ተተርጉሞ እንዳልታየ፣ እንዳልመጣ ፈጽሞ እንዳልተከበሩ ወደፊት በተከታታይ በሚወጡት „የካሲዮጵያ ማህደር“ ላይ እንመላለስበታለን።

ከሃምሳ አመት በላይ ሁለት ትውልድ ያንኑ መልሶ መላልሶ (ገዢዎ እነማን እንደሆኑ ግልጽ በሆነበት ዘመን) እንደ ማስቲካ መፈክሮችን ማኘክ- ነጮቹ እንደሚሉት በያፍዝ አደንግዝ የመንደር ጨዋታ – ጊዜአችን ማጥፋት ጨርሶ ተገቢ አይደለም። ነገሮች መቋጠር አለባቸው።

እንግዲህ በዚሁ ወደ ተነሳንበት በአለፉት ሃምሳ አመታት ትልቁን ቦታ ይዘ ስለነበሩት ጥያቄዎች እንመለስ።

የመደብ ትግል /የብሔር ትግል

ለአርባና ሃምሣ አመታት እንዲያውም ለአለፉት ስድሳ አመታት በተከታታይ እንደ ወሃ መውቀጥ በየጊዜው (ሌላ አማራጭ መፍትሔ የሚሰጡ ቲዎሪና ትምህርቶች በዓለም ላይ የሌሉ ይመስል) መልሰው መላልሰው የኢትዮጵያ „ፖለቲከኞች“ ያንኑ „ የመደብ ወይም ደግሞ እሱ አላዋጣ ሲል የብሔር ትግል“ የሚባለውን መፈክር ሲወቅጡልን ከርመዋል።

በአገራችን አነጋገር የነገር ቋንጣ የለውም ይባላል።

እንደ ሌላው የሠለጠኑ ሕዝቦችና መንግሥታት ከጊዜው ጋር አብረን እየተራመድን እኛም ለአለንበትና ለገባንበት ችግሮች መፍትሔ እየሰጠን እንሂድ ከአልን ከረጅም አመታት ጀምሮ የተከፈቱት አንዳንድ አጀንዳዎች ተዘግተው ወደፊት መራመድ ይኖርብናል።

ተንዛዛ እኮ ! ከዚህ ሌላ ምንም የሚታወቅ መፈክር የለም እንዴ!

„…አንዴ መገንጠል ሌላ ጊዜ አለመገንጠል። አንዴ „ለዲሞክራሲ ሌላ ጊዜ እዚያ ላይ ለመድረስ ጊዜ ስጡን። አንዴ አንድነት ሌላ ጊዜ መበታተን…“ ምንድነው የተያዘው ነገር?…ሃይማኖት ነው ወይስ ፖለቲካ?

ኤርትራም -ዓይናችን ከፍተን እንመልከት- ተገንጥላ ያገኘቺው ትርፍ ስታሊን እንደተለመው „ ያንኑ የአንድ ሰው አንድ አምባገነን ሥርዓትን ነው።“ መገመት እንደሚቻለው እንደ ኢሳያስ ዓይነቱ አምባገነኖች ደግሞ በኢትዮጵያ „እነሱን የሚቆጣጣር ሕግና ሕገ – መንግሥት ….ተቋምና ተቋሞች የምርጫ ሥርዓትና ነጻ-ጋዜጠዎች ከሌሉ“…. ቁጥራቸው ነገ ብቻ ሳይሆን አሁንም ቢሆን „ብዙ“ ነው።

ሰለዚህም ጉዳይ ቀደም ብለን እንደአነሳናቸው ወደፊትም እናነሳለን።

የምንጀምረው „በብሔር ጥያቄ …እሰከ መገንጠል „ በሚለው ፍልስፍና ነው።

ከየት መጣ? ማን ነው የዚህ ጥያቄ አባቱ?

የብሔር እኩልነት …እሰከ መገንጠል ድረስ

አልፍሬድ ሮዝንበርግ የሒትለር ችፍ አይዲኦሊጂስት -ይህ ነበር ማዕርጉ- ሶቭየት ኅብረትንና ምሥራቅ አውሮፓን ለመበተንና በቀላሉ ለመያዝ ከአወጣቸው africa-bevor-col-smallእቅዶች ውስጥ አንዱ ያን የሰማይ ስባሪ የሚክለውን „ትልቁን አህጉር“ ከውስጥ ገብቶ ለመበተን ያለው አማራጭ „ሕዝቡን በዘርና በየብሔሩ ከፋፍሎ“ በኮሚኒስቶቹ በነእስታሊን ላይ እንዲነሳ ማድረግ ነው። ከእሱም ጋር „የሃይማኖትን ልዩነት አብሮ አዳምቆ መወርወር ነው።“

በስታሊን ላይ ፋሺሽቶቹ የጠነሰሱትን ተንኮልና ሤራ እነሌኒንና እነስታሊን በሩሲያ ቄሣር በዘውድ አገዛዙ ላይ ከሠላሣ አምስት አመት በፊት ቃል በቃል እነሱ ከነደፉት ፕላን ጋር አንድና ልዩነት የሌለው ኩታ ገጠም ነው። ተመሳሳይ ድርጊት ቀይሰውሁለቱ ሞገደኞች በዘመናቸው በሕዝቡ መካከል አሠራጭተዋል።

ፕላኑ አንድ ነው። አላማቸው አንደኛው ፋሺዝምን ሌላው የኮሚኒስቶችን አምባገነን ሥርዓት በመሆኑ „የተለያዩ“ ናቸው። ውጤቱ ግን ዞሮ ዞሮ የሥልጣን ጉዳይ ስለሆነያውና አንድ ነው ።

ሁለቱም የፈለጉት የሁዋላ ሁዋላ „አምባገነን ሥርዓታቸውን“ በተለያዩ ስሞች በሰው ልጆች ላይ ለመዘርጋት ነው። በሒትለር ወይም በስታሊን ትዕዛዝ የሚተኮሰው የፋሺሺቱ ወይም የኮሚኒስቱ ጥይት የሚገድለው ሰው ወይም ተቃዋሚዎቹ የሚታሰሩበት የእሥር ቤት ሁኔታ አንድ ነው።ያኛው ፍራሽ ላይ ሲያስተኛ ይህኛው እስረኛውን መሬት ላይ ጥሎት አይሄድም። ቅቤ ሁለቱም ለተቃዋሚዎቻቸው አያቀብሉም።

ሌኒንና ስታሊን ያሰቡትን የኦስትሪያ መንግሥት በባልካን፣ ታለቁዋ ብርታኒያ ደግሞ በዘመኑዋ በቅኝ ግዛቶቹዋ ላይ በደንብ ተጠቅመውበታል። አፍሪካም በቀላሉ በኃያላን መንግሥታት በአሥራ -ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን የተያዘቺውም በዚሁ በዘርና በነገድ ከፋፍሎ እና ነጥሎ ተራ በተራ በማጋጨት በተወሰደው ብልሃትና መንገድ ነው።

ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመያዝ የሞከረቺውና ባህረ-ነጋሽ ይባል የነበረውን የሰሜን አካባቢ „ኤርትራ“ ብላ በኁዋላ የያዘቺው በዚሁ ዘዴ ነው።

በመጀመሪያ አሰብ ገዛች። በሁዋላ ምጽዋን ያዘች። ቀጥሎ አሥመራን …

እንዲያውም ከዚያው ከእነሱ ሰዎች ወታደር መልምላ አስታጥቃ ኢትዮጵያን -ምኒልክ ቀድማአቸው እንጂ-

እንዲወጉም ያደረገችውም በዚሁ ቲዎሪ ነው።

 አይዲዮሎጂ ና ፋቡላ ?

አይዲዮሎጂ ና ፋቡላ ?

„በልዩነት ጥያቄ“ በአጭሩ በዘርና በቋንቋ ልዩነት፣ በሃይማኖትና በጾታ፣ በቀለምና በቆዳ ፣ ሩዋንዳ እንደ ታየው …በአፍንጫ ልዩነት…አንድን ሕዝብ ያውም ለብዙ መቶ አመታት በሰላም የኖረን ሕዝብ ከውስጥ ገብቶ እንደ ቦንብ የዘር ጥያቄን አፈንድቶ እነሱን የሚሰማ ከተገኘ

መበተን ይቻላል።

መንግሥታትና ሕዝቦች ደግሞ በዚህ ጥያቄ ሳቢያብዙ ቦታ ተበትነዋል።

እነ ሌኒንና እነስታሊን ደጋፊዎቻቸውን ሲያባብሉና ሕዝቡን ሲሸነግሉ ይህን ነገር „በሁለት ፍቅራቸውን በጨረሱ በተሰላቹ በባልና በሚስት ፍቺ“ በእነሱ ሁኔታ ነገሩን አስቀምጠው በዘመናቸው ምንም አትሆኑም ብትፈልጉ ትታረቃላችሁ ከአልሆነም…ትለያያላችሁ እያሉ „ግሩምና ጥሩ ትምህርት“ – መርዝ ብንለው ይሻላል – ሰጥተው የሩሲያን ሕዝብ አዋክበዋል።

የሚሰሩትን በደንብ የሚያውቁት ሁለቱ አምባገነኖች ቄሣሩን ጥለው ግን ቤተ-መንገሥቱን ሲይዙ „…ወይዱ ከዚህ ብለው ተገንጣዩን በሙሉ ሰብስበው አንድ ሞቆጫ ውስጥ ከተው ወቅጠዋቸዋል።“

እሱን ትምህርት ነው የኢትዮጵያ „ነጻ- አውጪ ድርጅቶች“፣ ስማቸው ብዙ ነው- ጎትተው ኢትዮጵያ አስገብተው „የብሔር እኩልነት….እሰከ መገንጠል ድረስ „ መብት ነው ብለው፣ እሰከ አሁን ድረስ የሚያነታረከው ፍልሰፍና እንደ ትልቅ ቁም ነገር ታይቶና ተሰምቶ፣ እንደማይታወቅ መፍትሔ ተሽሞንሙኖ አገሩን እንዳለ ይህ ትምህርት እንዲያተረማምስ የተደረገው! !

ይህ ጥያቄ ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምን ሁኖአል?

ይህን የሚክድ የለም….በዚህ ጥያቄ ሳቢያ ሰው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። ንብረት ወድሞአል። መግባባት ጠፍቶአል። ዕድገትና መሻሻል ተረስቶ አንዳንዱ አካባቢ – ኤርትራ ጥሩ ምሳሌ ናት- በመጨረሻው ዛሬ ወደ እሥር ቤት ተቀይሮአል። በየወሩ ሦስት ሺህ ሰው አገሩን ለቆ ይወጣል ወይም ሊወጣ ሲሞክር ይያዛል ይባላል።

ይህ ነው ሥልጣኔ? ይህ ነው „የእኩልነት„ ጥያቄ መጨረሻው?ትርፉ አምባገነንነት ነው? ሶሻሊዝም?

የብሔር ጥያቄ የሕዝብ ጥያቄ አይደለም።

የብሔር ጥያቄ አንሽዎቹ ቀስቀሰሾቹ አደራጆቹ (የትም አገር) ተማሪና ምሁራን ከእነሱም ጋር ኢትዮጵያን ለመበተን ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች የእነዚህ የሦስቱ ጥምር ሥራ ነው።

ከብሔር ጥያቄ በፊት የመደብ ጥያቄ -በኢትዮጵያ ተማሪዎችና ምሁራን ዘንድ- ትልቁን ቦታ ይህ ጉዳይ ይዞ ነበር። ይህን እናውቃለን።

እሱ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የወጡ የተለያዩ ጽሑፎች እንደሚመሰክሩት „ከአንደኛ ቅራኔነት ቦታውን ለቆ ወደ ሁለተኛ ሲወርድ ሁለተኛው ቅራኔ የብሔር ትግል (ይህንንም ትንትና ዲያሌክቲክስ ይሉታል) የአንደኛውን ቦታ እንዲይዝ ተደርጎአል።“

ደርግ /ኢሠፓ የመደብ ትግሉን አራማጅ ሠፈር -እየፈጀና እየገደለ ለብቻው ይህን ቦታ ይይዛል። ነጻ-አውጪዎቹ „ የብሔር ትግሉን እሰከ መገንጠል“ ይዘው ያቺን አገር – ዛሬ መለስ ብለን ስንመለከተው የትም አገር በአልሰራ ዕውቀትና ጥበብ ትምህርት- ሁለቱ ወገኖች ተነስተው ያን አካባቢ እንዳልነበር አድርገው እነሱ -የቫይመርን ታሪክ ተመልከት- በይገባኛል ጥያቄ አተረማምሰዋል።

የሚደንቀው ከዚህ ሁሉ ትርምስና ሕይወት መጥፋት በሁዋላ ደግሞ አሁንም ቢሆን እነሱው ናቸው መጽሐፍ እየጻፉ ወረቀት እያወጡ የፖለቲካ ሜዳውን ለብቻቸው የያዙት!

ሌኒን እና ስታሊን በጀርመን ንጉሥ ዕርዳታ ነው ሥልጣን ላይ የወጡት። አብዮት ካለውጭ ዕርዳታ የማይሳካ ይመስል ደርግ በሶቭየት እሱን የተኩት „ነጻ-አውጪዎቹ“ ደግሞ በጎረቤት አገሮችና በምዕራቡ ዓለም በእነሱ ብርታት ሥልጣን ላይ ወጥተዋል።

ደርግና እነ ኮነሬል ምንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ሥልጣን ላይ ለ17 አመታት የቆዩት በሶቪየት ገንዘብና በእነሱ መሣሪያ፣ በምሥራቅ ጀርመን የስለላ ድርጅት ድጋፍና በሁዋላ በመጣችው ኪዩባ ነው።

ደርግ በተራው-በሩ አሁን ለማንም ክፍት ነው- በውጭ ኃይሎች ትብብር ከሥልጣኑ ይወርዳል። መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በእነሱ ምክር፣ ንዋይና ድጋፍ አገሪቱን ለቆ ይወጣል።

በብሔር ትግል ስም ሥልጣኑን የተረከቡት ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍለው የያዙት ሕዝባዊ ወያኔና ሻቢያ ለአጭር ጊዜ ኦነግ -ሦስቱም ድርጅቶች ተመካክረው -ዩጎዚላቪያ እየተገነጣጠለች ሶቪየት ኅብረት እንደዚሁ እየተፈረካከሰች እያዩ፣ – ሕገ- መንግሥቱ ላይ „…እሰከ መገንጠል „ የሚለውን የስታሊን መፍትሔ ለኢትዮጵያ ይተልማሉ።

Ethnic-ethiopian-map

ምሳሌ ሲሰጡ ሌኒን እና ስታሊን አንዴ የሰጡትን የባልና ሚስት የፍች ወረቀት ጉዳይ መልሰው መላልሰው እነሱ ያነሳሉ።

ኢትዮጵያኖች ተካልሰው ተደባቀልው በሃይማኖታቸውና በባህላቸው ተሳስረው ይኖሩ እንደ ነበረ በደንብ የታወቀው የባድሜ ጦርነትን አስታኮ የተነሳው አገር ልቀቁ የሚለው አዋጅ ከታወጀ በሁዋላ ነው።

በዚህ ሳቢያ ስንቱ „ኤርትራዊ“ ኢትዮጵያን ለቆ እንዲወጣ ተደርጎአል። ስንቱ ኢትዮጵያዊ „ኤርትራን“ ለቆ እንዲሸሽ ተገዶአል።

በሁዋላ እንደምንሰማው አቶ ኢሳያስ እና ሌሎች የአሥመራው የአመራር ሰዎች በአንድ በኩል አቶ መለሰና እንደዚሁ የእህአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎች በሌላ በኩል „የትግሬና የሐማሴን፣ የአከለጉዛዬና የሰራዬ …የወልቃይትና….ተወላጆች-የኢትዮጵያ ልጆች ሁነው ይገኛሉ።“

ይህ ነው የብሔር እኩልነት ጥያቄ መጨረሻው?

ፖለቲካ ማለት-ከፖለቲካ ፍልስፍና አንዳንድ ነገር እንማር ከአልን- ነገና ከነገ ወዲያ ምን ይመጣል ብሎ አርቆ ማሰብ ማለት ነው። ፖለቲከኛ ማለት ችግር ፈቺ መፍትሔ አቅራቢ እንጂ በችግር ላይ ችግር ቀፍቃፊና ፈልፋይ መከራም ጠሪ ማለት አይደለም።

ፖለቲካኛ በአንድ በሠለጠነ ሕብረተስብ ውስጥ ሰው ሁሉ ተቻችሎ ተከባብሮ የሚኖርበትን መንገድና ዘዴ ፈላጊ እንጂ እሳት ጫሪ ቤንዚን አርከፍካፊ ማለት አይደልም።

በዚህ መልኩ „የብሔር እኩልነት ጥያቄ“ ልክ እንደ ሃይማኖት እኩልነት -እንደ እስላሙና እንደ ክርስቲያኑ ወይም እንደ አቴኢስቱ….- ሁሉም ሰው እንደ እምነቱና እንደ ዘሩ በሕብረተሰቡ ውስጥ ተቻችሎና ተከባብሮ ተረዳድቶና ተሳስቦ፣ ተሰባስቦም አንድ ላይ የሚኖርበትን ሥርዓት በጋራ ማዘጋጀት ማለት እንጂ -አንዱ በአንዱ ላይ ተነስቶ ወይም አንዱ ከሌላው ተገንጥሎ በሌላ አነጋገር „ ክርስቲያኑ ከእስላሙ ተለይቶ የራሱን ሪፓብሊክ መስርቶ ይኑር „ ማለት አይደልም።

ይህ እንዳይሆን የዓለም አቀፍ ሕግም ይከለክላል።

በጎረቤት አገር በኬንያ 40 ብሔር ብሔረሰቦች አብረው ይኖራሉ። በቱርክ 80 በናይጄሪያ 380 በአሜሪካን ደግሞ ከዓለም ዙሪያ የመጡ በሺህና ሁለት ሦስት ሺህየሚቆጠሩ ብሔር /ብሔረ ሰቦች አብረው አንድ ላይ ይኖራሉ።

እነዚህ ሁሉ ቢገነጠሉና ቢገነጣጠሉ በተለይ በአፍሪካ – እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛነሽ እንደሚባለው እራሳቸውን፣ በመድሓኒትና በልብስ ….ወታደሮቻቸውን ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ አስተማሪዎችን ……እነዚህን ሁሉ የሚያስተዳድሩበት የቀለብ ገንዘብ የሌላቸው- አለ የውጭ ዕርዳታ- አንድ ቀን ብቻቸውን መቆም የማይችሉ አገሮች መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።

ነገ ተበታትነው ሦስት ሺህ መንግሥታት መሥርተው መጥተው የእህል መግዣ ብርና የምንኖርበትየዕርዳታ ገንዘብጡን ብለው ቢለምኑም (እንደምናውቃው ሁሉም ደሃ ነው) ከእንዱስትሪ አገሮች ውስጥ እነሱን ዞር ብሎ የሚያያቸውና እጁን የሚዘረጋላቸው ቢቆጠሩ „ትንሽ“ ናቸው።

ኤርትራ እንድትገነጠልም በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም የተጻፈው ደብዳቤም አንድ ቀን Ethnic-Ethio-eritreaየሚያጠያይቅ ነው።

የብሔር እኩልነት ጥያቄ እንደ ሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ ተገቢ ጥያቄና መልስ ማግኘት ያለበትም የዲሞክራቲክ ጥያቄ ነው። ግን ለምንድነው የብሔር ጥያቄን የሚያነሱ „ነጻ-አውጪ“ ነን ብለው እራሳቸውን የሚጠሩ ድርጅት መሪዎችና ደጋፊዎች ስለ ሰበአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጉዳይ ጮክ ብለው ሲናገሩ ሲጽፉ ሲቀሰቅሱ የማይታየው የማይሰማው?ወይም በኤርትራና በኢትዮጵያ -ሁለቱም ነጻ-አውጪዎች ናቸው- ሰበአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው የማናየው? ለምንድነው „አማራ አማራ…ጨቆነን „ ይሉ የነበሩ ሰዎች አሁን በይፋ ስለ ሰበአዊ መብቶች መከበር በኢትዮጵያ በይፋ የማይናገሩት?

ትልቁ ጥያቄ እሱ ነው።

የተራው ሕዝብ ችግር የሚበላው ዳቦ የሚጠጣው ንጹህ ወሃየሥራ እድልና የቀን ልብሱ የማታ ብርድ ልብሱ የውጋት ማሰታገሻ መድሐኒቱና ጡረታው የዓይን ብርሃኑና የልጆቹ ሆድና ትምህርት ጉዳይየቤቱ ጣራና ቀዳዳ የበዛው የግድግዳው የምሶሶው የማሳው ጉዳይ ነው።

ይህም ሌላው አብይና ዋና አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄ ነው።

የብሔር ጥያቄ መልስ የሚያገኘው የግለሰብ ሰበአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በይፋ ሲታወቁ ነው። ዜጋው መምረጥና መመረጥ ሲችል መጻፍና መተቸት መሰብሰብና መደራጀት መናገርና መቃወም በአገሪቱ መብቱ ታውቆ ሲቻል ብቻ ነው። …ሕግና የሕግ በላይነት ሲሰፍን ብቻ ነው።

[1]The Queen Cassiopeia, wife of kingCepheus of Æthiopia

—-

ለአእምሮ የጥር 2006 / January 2014/ እትም፣ቅጽ 2 ቁጥር 6

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s