እራስህን እወቅ (ርዕስ አንቀጽ/Editorial)

spiegelbildእራስህን እወቅ (ርዕስ አንቀጽ/Editorial)

ውድ አንባቢዎች !

የዛሬውን ሕትመታችንን የከፈትነው ለየት በአለ ጥያቄና መልስ ነው። ለዚህም ነው „ርዕተ፥ዓለም /አይዲኦሎጂ ወይስ እሴት/ ቫሊዩስ“ ያልነው።

መጽሔቱ በአጠቃላይ በርካታ ነጥቦችን አቅፎአል።

ሁሉም ጉዳዮች የሚሸከረከሩትደግሞ እግዚአብሔር በሰጠን መብት – አንዳዶቹ ይህን ነገር ተፈጥሮ ነው ይሉታል – „በኢንላይትመንትና በሊበርቲ“ ዙሪያ ነው:- እኔም አንተም ሁላችንም ነጻ-ሰው ነን።

አንደኛው -ከወዲሁ ግልጽ ለማድረግ-ሁለት ፍልስፍናዎችና ትምህርቶች ከጀርመን ተነስተው „የዓለም ሕዝብ ሁሉ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የግድ መኖር አለበት“ ብለው አገሩቱንም ሕዝቡንም ምድርንም በየአለበት አተረማምሰው በሃያኛው ክፍለ ዘመን እንደሄዱ የሚታወቅ ነው።

በብዙዎቹ ዘንድ የማይታወቀው ጀርመን እነዚህን ትምህርቶችና ፍልስፍናዎችን በምን ብልሃትና ዘዴ አራግፋ ከእነሱም ተገላግላ ወደ ነጻ-ሕብረተሰብ ተሸጋግራ በኢኮኖሚያዋ በልጽጋ ሁሉን ቀድማ ሕዝቦቹዋን አስደስታ እዚህ አሁን የምናየው ደረጃ ላይ ደረሰች ለሚለው ጥያቄ የሰጠቺው መልስ ነው።

ይህንንም እኛ በዚህች ሕትመታችን ላይ ከሞላ ጎደል ብልሃቱንና ጥበቡን አንስተን እናንተ እንድትመለከቱት አድርገናል።

ወረድ ብለን በዚህ በኩል አሸነፍናት ብለው ገና እፎይ ሳይሉ በሌላ በኩል ብቅ ስለምትልባቸው ኢትዮጵያ እናነሳለን። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ በኩዋክብት ተመስላ ስሙዋን ቀየር አድርጋ „ካሲዮጵያ „ ተብላ እንዴት ብቅ እንዳለች እንመለከታለን።

ስለዚህች የኢትዮጵያ ንግሥት ማንም የማይደርስባት ሰማይ ላይ ዘለዓለማዊ ሁና ስለቀረቺው ኮከብ-„ካሲዮጵያ“ እግረ መንገዳችንን አንስተን እናልፋለን።

ከዚሁ ጋር እንደ „ማስቲካ“ ጥዋት ማታ ስለሚታኘከው ስለ አማራና ስለ ብሔር ብሔረሰብ እሰከ መገንጠል ድረስ ጥያቄም መለስ ብለን አንስተን ገደቡና ልኩ የት ድረስ ነው ብለን እረራሳችንን ጠይቀን አንድ ግንዛቤ ሰንዝረን ወደ ሌላ ጉዳይ እንሸጋግረናል።

በሦስተኛ ደረጃ ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያን አውሮፓ ውስጥ ተገንጥሎ የራሱን መንገድ ሂዶ አሁን የመንፈስ ቀውስ ገብቶ ቤተ ክርስቲያኑን በበርካታ ከተማዎች ለመሸጥ ስለተገደደው የሉተር ኢቫንጀልስት/ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን እናነሳለን።

ተሸጠውም ቤተ-ክርስቲያኖቹ ምግብ ቤትና መሸታ ቤት ሁነዋል። የወጣቶች ዳንኪራ መርገጫና መጨፈሪያ ጋለሪና የብስክሌት ማቆሚያ ወይም መቃብር ቤት ተደርገዋል። ይህ ጉዳይም ጀርመን ውስጥ ያስነሳውን ውይይት መጽሔቱ ገረፍ አድርጎ ያልፋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለባህሉዋ ለሃይማኖቱዋና ለታሪኩዋ ፍጹም እንግደ የሆነውን የማርክስና የስታሊን ትምህርትና ቲዎሪ እጃቸውን ዘርግተው ልባቸውን ከፍተው „የተቀበሉ ሰዎች“ ለምን አሁን አገሪቱ ማለት ሕዝቡ „…ሰበአዊና ዲሞክራሲ መብቱን ተጠቅሞ አብሮ በሰላም በእኩልነትና በአንድነት ለመኖርና የፈለገውን ዓይነት ሓሳቦቹን ተሰብስቦ ተደራጅቶ ተናግሮ ጽፎና መክሮ መርጦ መኖር የማይችልበት ደረጃ ላይ ነው „ የሚሉበት ምክንያት አይገባንም። ይህንንም ጉዳይ በተዘዋዋሪ አንስተንም በጽሑፋችን ላይ እንመላለስበታለን።

መጽሔቱ በአራተኛ ደረጃ „በብሔርና በመደብ ትግል እሰከ መገንጠል…“ በሚባለው ፍቅርን ሳይሆን አምባጓሮን አንድነትን ሳይሆን መበታተንን ተቻችሎ ተከባብሮ በመልካም ጉርብትና አብሮ ተረዳድቶ መኖርን ሳይሆን ጥላችን እንዲያውም – ማርክስና እስታሊን እንደሚሉት- „አንዱ መደብ ሌላውን መደምሰስ አለበት“ ብሎ የሚለውንም ነገር እንደገና ተመልሶ ይመለከታል።

ይህን ዓይነቱን ጥላቻ በሚያስተምረውም ጽንሰ ሓሳብ ዙሪያም ላይ ተሽከርክሮ -መጽሓፍ አይደለም የምንጽፈው- አይዲኦሎጂውን ይተቻል።

የአለፈው ሃምሣ አመት ታሪካችን ለምን በከንቱ በዚህ ጉዳይ ላይ አለፈ? ብሎም በተዘዋዋሪ ይጠይቃል።

„ትግል“ የሚለው ቃል ብዙ ትርጉም አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ቀስ ብሎ እየተንሸራተተ የገባው ይህ „የብሔርና የመደብ ትግል“ ቃል (መንግሥቱ ኃይለማሪያም „ጥሩ“ አድረጎ „በከርሰ መቃብራቸው ላይ እንቀመጣለን „ ብሎ አስቀምጦታል) ገፍትሮ አሁንም ቢሆን የት እንደከተተን በዓይናችን ጥዋት ማታ እናያለን። ከሩቅም ሆነን እንሰማለንም።

እሱንም አንስተን እዚያና እዚህ ነስንሰን – ወረድ ብላችሁ እንደምትመለከቱት እናልፋለን።

እንግዲህ ለዚህም ነው ይህን ጉዳይ ግልጽ ለማድረግ የውሾችን ታሪክ መርጠንም ያስቀደምነው። የአንበሳ ወይም የነብሮች ወይም ደግሞ የድመቶች ታሪክ ልንለውም እነችላለን። ይህን ያህል „ልዪነት“ የላቸውም አንድ ናቸው።

ውሻ ግን ከነብር ታማኝ ነው። ንቁ ነው። ውሻ ከአስተማሩት -እስከ መቶ የተለያዩ ቃላቶችን መያዝ ይችላል። እነሱንም አቀነባብሮ ምን እንደ ተባለ መላ መምታትም ይችልበታል። በዚህም የሚሰማቸውን ነገሮች አዳምጦ-ትዕዛዝ ይቀበላል።

እንደምናውቀው ደግሞ በጋራ የሚኖሩና አጥቂአውሬ ሲመጣባቸው ለጋራም ጩኸት የሚተባበሩ ናቸው። በዚያው መጠን አጥንት ከአዩ የሚቦጫጨቁእነሱናቸው።

ርዕዮተ-ዓለም ወይስ እሴት ? ከማለት ይልቅ „አይዲኦሎጂ ወይስ ትሩፋት/ ቨርቺውስ?“ ብለን እሱን ማስቀድና መመልከት ምርጫችን በሆነ ነበር።

„ስለህሊና ስለልቦና ስለ ፍቅር ስለ ርህሩህነት ስለ መከባበር ስለ ተግሳጽና ምክር …“ ስለነዚህ ሁሉ ለማንሳትና ታሪክና ምሳሌን ተደግፎ ለማብራራት የሚፈልግ ሰው ቨርቺውስ/ትሩፋት ውስጥ ገብቶ ዋኝቶ ከዚያ ወጥቶ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ሰብስቦ ለማሳየት ከዚህ የበለጠ ሜዳ የትም እሱ አያገኝም።

የኢትዮጵያ ባህልና ትውፊት (ካልቸርና ትራዲሽን) የተመሰረቱት በዚህ እላይ በአነሳነው በትሩፋትና አገሪቱ ከጥንት ጀምሮ በምትመራበት ሥነ-ምግባርና ግብረገብም (ሞራልና ኤትክስም) ነው። እነዚህ ሁሉ አብረየተያያዙ ናቸው።

በሁዋላ ግን ሳይታሰብ ብቅ ያሉ አሁንም እየተጠናከሩ የመጡ አዲስ አመለካከቶች የነበረውን ሁሉ እንዳልነበር አድርገዋል።

„ማጭበርበር፣ መዋሸት፣ መስገብገብ አለመደማመጥ …እግዚአብሔርን አለመፍራት …በአጭሩ አብዮታዊ እርምጃ የሚባሉ ነገሮችና….ፍርደ ገምድልነት የሚሊተሪ የጦር ሜዳ ፍርድ “ የሚባሉት ጠበንጃ ለያዙት ብቻ የሚሰራና የሚያገለግል አዲስ ኖርሞችና „ሕግጋት“ …እነዚህ ሁሉ የተጻፉና ያልተጻፉ የአኗኗር ዘዴዎችን ገልብጠውና ገለባብጠው ነገሮችን ሁሉ -ነጮቹ እንደሚሉት-በእግራቸው ሳይሆን በጭንቅላታቸው አገራችንን አቁመው ለቀዋታል።

ይመስላል እንጂ ነገሮች ሁሉ ቀስ እያሉ ከቅጥጥር ውጭ ሁነዋል። ከሆኑም ቆይቶአል። ጨርሶ መደማመጥ መግባባት በማንኛችንም ቤት የሌለው በሌላ ሳይሆን በዚሁ በአገራችን ቀስ ብሎ እግሩን በሰደደው አይዲኦሎጂ ምክንያት ነው።

መጽሔቱ ይህንንም እዚያም እዚህም በገጹ ላይ ያነሳል።

ስለትሩፋት ግን በቀጥታ ብዙ አያነሳም።

ዚህ ቁም ነገር አንዳንድ ነገር ማስተዋል ለፈለገ፣ ጥራዝ ነጠቅነት በአገሪቱ ሳይስፋፋ በኢትዮጵያኖች አስተሳሰብና ባህሪ ላይ ትልቅ ሚናና አስተዋጾ ያደረገውን „ መጽሐፈ ፈላስፋ „ የተባለውን መጽሑፍ ፕሮፌሰር ክሉድ ሰምነር(1 አገላብጠው ወደ አርባ የሚደርሱ የኢትዮጵያ ቨርቺውስን / ትሩፋትን „የኢትዮጵያ ፊሎሶፊ“ በሚለው ጥናታቸው ላይ እንድንመለከተው እሳቸው ቆጥረውልናል።

እዚያም ላይ እንደ „…ችሎታና እንደ ዝምታ… እነደ መልካም አንደበትና እንደ ብልሃተኛነት እንደ ጥበብና እንደ ረጋ ማለት እንደ ታማኝነትና እነደ ይቅርታ… ይቅር ለእግዚአብሔር ብሎ መታረቅና መስማማትን፣ “ምሁሩ አንስተው መጽሓፉ ውስጥ ያገኙትን ምርጥ ቨርቺውስን ቆጥረውልናል።

እዚያው ላይ „ እንደ ደፋርናትና እንደ ተስፋ እንደ ጥንካሬና እንደ ሥራ ወዳድነት እንደ ትህትና እና እንደ ደስታን እንደ ፍርድና ፍትህ…እንደ ጥራትና እነደ ቻይነት- እንደ ልበ-ሰፊነት እንደ መቆጠብና ከስግብግብነት መራቅን እነደ አክብሮት እነደ አርቆ ማየት ….እነደ እምነትና ጠንካራ ሃይማኖታዊነት….“ያሉትን ፕሮፌሰሩ ሰብሰብው ያስቀመጡትን ውድ ሐብቶች እዚያም ውስጥ እናገኛለን።

„ተግሣጽና ምክር „የሚባሉ ጽሑፎች ነበሩ። የሞራልና የግብረገብ ትምህርት በየትምህርት ቤቱ ለወጣቱ ትውልድ ይሰጥ ነበር።

„መልካም ሶሳይት“ የሚባሉ የሥነ -ስርዓት ማስተማሪያ ጽሑፎች ነበሩ።

እዚያም ላይ „የአቀራረብና የአነጋገር የአቋቋምና የአቀባበል ቅደም ተከተል የትህትና እና የአክብሮት ሥነ-ስርዓቶች“ ለልጆች ይተላለፉ ነበር።

ይህ ሁሉ ግን ወይ „አብዮት“ በሚባለው ነገር ወይም“ አብዮታዊ እርምጃ …“ በሚባለው አዲስ „ባህልና ጌጥ“ ድረሻቸው እንዲጠፋም ተደርጎአል።

የአገር ፍቅርም በዚያው አብሮ በተወሰኑ ሰዎች ዘንድ መሬት ላይ ተጥሎ ተረግጦአል።

እሴት እና አይዲኦሎጂን በመጽሔቱ ላይ ያነሳነውም ከዚህ አንጻር ብቻ ነው።

ሰዎች በዘር ወይም በአጥንት ቆጠራ ላይ ተመስርተው በኢትዮጵያ ከሚደራጁ –ህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው- (እንደ ጤፍ የተደበላለቅን ስለሆን አንዱን ፍሬ ለቅሞ ከሌላው መለያያቱ ከባድ ነው)- በተለያዩ አይዲኦሎጂ ዙሪያና ሥር እንደ ሌላየዓለም ሕዝብ ተሰባስበው ቢደራጁ እኛ የምንቃወመው ሳይሆን የምንደግፈው አካሄድ ነው።

እኛ የምንተቸውና የምንቃወመው፣ መስተካከል አለበት የምንለው ጉዳይ ቢኖር „የራስንና የግል ወታደሮችን ሰብስበው አደራጅተው አስታጥቀው በጠበንጃ አፈ ሙዝ አስገድደው …እኛ ብቻ ለሕዝቡ የሚያስፈልገውን ነገር እናውቃለን እናንተ አርፋችሁ ተቀመጡ…“ የሚሉትን የአሥራ ዘጠነኛውና የሃኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሰዎችን ነው።

እንደዚህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ አሁን በያዝነው በ21ኛ ክፍለ-ዘመን የትም አገር ምንም ቦታ የውም።

ይህንንም ጉዳይ ለማሳየት ጀርመኖቹእንደ ምሳሌ ወስደን ከብዙ በጥቂቱ በዚህ ሕትመታችን -ዘለቅ ስትሉ ታገኙታላችሁ – አንስተነዋል።

እንደሚታወቀው የጀርመን ፋሽሽቶችና የጀርመን ኮሚኒስቶች የእራሳቸውን ሰዎች ሰብስበው የወታደር ልብስ አልብሰው የራሳቸውን የስለላ ድርጅት ዘርግተው የቅስቀሳና የፕሮፓጋንዳ ክፍል ከፍተው፣ በመንግሥት ሥር የራሳቸውን „መንግሥት „ መሥርተው ይህችን አገር አተረማምሰዋል።

የዘር እና የመደብ ጥላቻ ትምህርትና ቲዎሪ -ፋሺዝምም ሆነ ኮሚኒዚም- እነዚህ ዓለምን ያተረማመሱ ሁለቱ አይዲኦሎጂዎች የበቀሉት ቀስ ብለውም ዓለምን ያዳረሱት ከዚሁ ከጀርመን አገር :- ከሒትለርና ከማርክስ ብዕር፣ ከእነሱም ጭንቅላት ነው።

እነሱን አባረው ደግሞ እላይ ገና ከመጀመሪያው እንዳልነው ይኸው ነጻው የጀርመን ሕዝብ ንጹሁን የዲሞክራሲ አየር እተነፈሰ ጋዜጣውንና መጽሓፉን እየጻፈ ድርሰቱን እየደረሰ ምርምሩን በነጻነት እያካሄደ ቲያትሩን እየተጫወተ ፊልሙን እየቀረጸ በዓለም ላይ ምን የመሰለ ምርጥ የእንዱስትሪ ዕቃዎችን እያመረተ ዛሬ ሁሉም የሚቀናበት አገርና ሕዝብ ወጥቶታል ።

እሱንም ትንትና ወረድ ብላችሁ ስትዘልቁት ታገኙታላችሁ።

ከሁሉም እቴጌ ጣይቱ ከዛሬ አንድ መቶ አመት በፊት ስለ „አንድነት“ ትልቅነት ለሃይማኖት አባቶች የጻፉት የቆየ ደብዳቤ አስደናቂና ግሩም ስለ ሆና እሱንም ረጋ ብላችሁት እንድትመለከቱት እንጋብዛችሁዋለን። መልዕክቱ ለሃይማኖት አባቶች ብቻ አይደለም። መልዕክቱ ለአንተና ለአንች ለእሱና ለእኛ ለሁላችንም ነው።

በመጨረሻም በ1969 ዓ. ም. ቀ ኃ ሥ በሰበአዊ መብት ታጋዩ በዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ መቃብር ላይ በአትላንታ የአበበ ጉንጉን ሲያስቀምጡ በዘመኑ ከወጣው ጋዜጣ ላይ ያገኘነውን ሰነድ አብረን እንድትመለከቱት አውጥተናል።

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ።

ዋና አዘጋጁ

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

————————

1) http://en.wikipedia.org/wiki/Claude_Sumner

http://en.wikipedia.org/wiki/Ethiopian_philosophy

 

ለአእምሮ የጥር 2006 / January 2014/ እትም፣ቅጽ 2 ቁጥር 6

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s