አይዲዮሎጂ ና ፋቡላ ?

አይዲዮሎጂ ና ፋቡላ ?

አይዲሎጂና ፋቡላ ?

ወይስ

ሥ ል ጣ ኔ ና እ ሴ ት?

Sokrates-Gift

ንድንነው እነሱ ያላቸው ችሎታና ብልሃት እኛ ደግሞ የሌለን ነገር?“ ብሎ አንድ ውሻ እሱ እራሱ የሚያውቃቸውን ጋብዞና ጠርቶ ዛፍ ሥር እነሱንም ሰብስቦ አጠገቡ የቆሙትን የመንደር ውሾች „…አንዲት መልስ ብቻ ከየትም አምጥተው ለጥያቄው እንዲሰጡት“ ያፋጥጣቸዋል።

ከፊሉ ውሻ -እዚያ ከነበሩት ውስጥ- ብዙውን ክፉና ደጉን በአለፉት ቀናትና ረጅሙ አመታት ከእሱ ጋር አብረው የተካፈሉ የዕድሜ አኩዮቹ ናቸው። ሌሎቹ አብሮ አደጎቹ ናቸው። የተቀሩት ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ናቸው። ሁሉም ጠባዩን ስለሚያውቁት መልስ ለመስጠት ተጨንቀዋል። ብዥ ብሎበት አይኑን ከጎለጎለና ክራንቻ ጥርሱን አሳይቶ የጀርባው ጠጉር ከተነሳ ማንም አይችለውም። ይቦጫጭቃቸዋል።

ከእነሱም ጋር በዚያን ዕለት ከተገኙት ውስጥ የቆየ መንደራቸውን ጥለው – ስለፈረሰ የተቀላቀሉ ወዶ ገብ አዲስ መጤዎችም አሉበት። ትናንሽ ቡችሎች ራቅ ብለው -የዚህች ዓለም ነገር ወዴት እንደምታመረ ገና ያልገባቸው፣ ጮርቃ ምኑንም የማያውቁት እዚያ አፈሩ ላይ እነሱ ይተረማመሳሉ፣ በሆዳቸውም ይገለባበጣሉ።

ፍቅረኞቹም ሲተያዩ ይሽኮረመማሉ። መጪውን ቀን ክፉ ይሁን ወይም በአለው ይቀጥል ወይም ደግሞ ደህና ይሁን የሚያውቅ ከእነሱ መካከል የለም።

አውራው ግን የገባው ይመስላል።

„…ምንድነው እነሱ የተካኑበት ጸጋ ለእኛ ደግሞ ሥውር ሁኖ የማይታየን ነገር? „ እስቲ ንገሩኝ እያለ ውሻ ይንጎራደዳል።

የእንስሶችንና የአውሬዎች ፋቡላ ታሪክ በደንብ ለተከታተለ አንድ ሰው ከእነሱ ብዙም ባይሆን ትንሽ ትምህርት ይገኝበታል ይባላል ።

ታሪክ የማይረሳቸውና የሚያስታውሳቸው አሉ።

አንደኛው የጆርጅ ኦርቭል ድርሰት ነው። የእሱ „…የእንስሳት እርሻ „ የሚለው አጭር ልበ ወለድ ድርሰቱ ግሩምና ድንቅ ጽሑፍ ነው።

„…አያ ጅቦ ሳታመከኝ ብላኝ“ ያላቸው የአህያዋ አነጋገር ከነተረቱ እንደanimal_farmዚሁ ሌላው የሚጠቀስ ምሳሌ ነው ።

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት የመጀመሪያ ድርሰታቸውን በቲያትር መልክ ጽፈውና አዘጋጅተው አዲስ አበባ ላይ በዘመናቸው መድረክ ላይ ያቀረቡት ጨዋታ በዚሁ በፋቡላ በእንስሶች ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው።

ልችቶት ይመስላል ወይም ተናዶ ወይም ደግሞ ድክመትና ጥንካሬአቸውን በሁለቱም ወገን መካከል ያለውን ለማወቅ ከአለው ፍላጎትና ጉግት ተነስቶ ሊሆን ይችላል ይህኛው አውራ ውሻ ስብሰባ የጠራበት ዋናው ምክንያት የትኛው እንደሆነ አይታወቅም። ወይስ ውሸትና እውነት ተለይቶና ተበጥሮ እንዲወጣ ፈልጎ ይሆን?

ያ ውሻ የመንደሩን ውሾች ሁሉ ጠርቶ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ „…እስቲ ንገሩኝ …ምንድነው እነሱ ያላቸው ጥንካሬ እኛ ደግሞ የሌለን?“ ማለቱ ከዚህ ሁሉ አመት በሁዋላ -አጥንት ከአዩ ብዙ አመታቸው ነው- የገርማል።

አጥንቱ ትዝ እያለው-

„…እነሱ ያላቸው ትልቅ አብሮ የመኖር ፍልስፍና እና እኛ ደግሞ በእጃችን የሌለን ነገር እስቲ እባካችሁ ፈልጋችሁ መልስ ስጡኝ? ብሎ፤ ቢጤዎቹን ሰልችቶት ወደ መጨረሻ ላይ እየተለመማመጠ ይጠይቃል።

በዚያች አንዳዶቹ ትክ ብለው መልስ ለመስጠት በሚያስቡበትና በሚያሳስሉበት ሰዓትና ደቂቃ ከየት እነደመጣች የማይታወቅ አንዲት ጥንቸል ሽው ብላ ታልፋለች። ስታልፍ ከሩቁ ያዩ ሁለት የስብሰባው ተሳታፊዎች ተጠቃቅሰው ብድግ ብለው በዚያ በረጃጅም እግሮቻቸው ወደፊት እየተሳቡና እየተገፋተሩ „…እሱዋማ የእኔ ናት። የለም የአንተ“ እየተባባሉ ማሳደድ ይጀምራሉ። የት እንደገቡ ሳይታወቅ:- ቢጠበቁ እነሱ ሳይመለሱ በዚያው ጭልጥ ብለው ጠፍተው ቀርተዋል። እነሱ ተረስተው:-

ወይይቱ እንደገና በሌላ ጥያቄ ይከፈታል። ያም ገና በደንብ ሳይደመጥ በመካከሉ አንዲት ተንኮለኛ እነሱን ውሾቹን በማነደድ ብቻ ደስታውን የምታገኝ ቅምጥ የሳሎን ድመት ተደብቃ ቀስ ብላ ጠጋ ብላ በጭረዋ የአንዱን ውሻ ጀርባ ገረፍ አድርጋ ፈትለክ ብላ ትሰወራለች።

እሱና አጠገቡ የነበሩት ውሾች ተደፈርን ብለው ብድግ ብለው ዘለው በተራቸው እሱዋን ድራሹዋን ለመጥፈት ሲዘሉ -ሥራዋን በደንብ ታውቃለች- አፈትልካ በመጀመሪያ ዘላ ግንቡ ላይ ከግንቡ ጣራው ላይ ጉብ ብላ „ሚያው“ እያለች እየተንጎራደደች እነሱ የተሰበሰቡበትን ዓላማ ረስተው የተለመደው ጩኸት ውስጥ ይገባሉ። በጩኸት ቅላጼ በእሱዋ ምክንያት ስብሰባው ሊፈርስ ጥቂት ይቀረዋል።

እንደተለመደው ጮኸው ሲሰለቻቸው ይረጋጋሉ ብላ ንቃቸው ግቢዋ ውስጥ ዘላ ገብታ እመቤትዋ እግር ሥር በረንዳው ላይ ጋደም ትላለች።

ደፍሮ ከመካከላቸው አንድ ጎልማሳ ውሻ ብድግ ይልና „…እኔ ከእናንተ በዕድሜ ወጣት በመሆኔ እምብዛም ብዙ ነገር አላውቅም። አሳዳጊዎቼ ፈረንጆቹ እኔን እዚህ ሜዳ ላይ ጥለው ወደ አገራቸው ከመመለሳቸውና ከመሄዳቸው በፊት እንደአየሁትና እንደተገነዘብኩት እነሱም በደጉ ዘመን እንዳሳደጉኝ እኔም በደንብ እንደአዳመጥኩት የፈረንጅ ውሾች ትምህርት ቤት ተልከው እዚያ ‚ሁሉን ዓይነት የአብሮ መኖር ሥርዓት‘ እነሱ እንዲማሩ ይደረጋል።… የማናውቀው እንግዳ እንኳን ወደ ቤታችንfabula-cat-and-dog ሲመጣ -ብዙም ሊሆኑ ይችላሉ – ወጣ ብለን ከጌቶቻችን ጋር ሁነን ሳንጮህና ሳናስፈራራቸው እግራቸ ሥር እየተሽከረከርን በደስታ እንቀበላቸዋለን።

„ከሌላም ከማናቀው ውሻም ጋር እንደዚሁ ገበያ ላይ ወይም ንፋስ ለመቀበል ለሽርሽር ስንወጣ ሜዳ ላይ ከተገናኘን ተጠያይቀን ትንሽ ‚እመቤትሽ የለበሸቺው ቀሚስ ጌታህ የያዘው ከዘራ ወይም ክራቫት ብለን ተቀላልደን‘ መንገዳችንን እንቀጥላለን እንጅ እዚህ እንደማየው አንዱን ሰብሰብን ብለን አሳደን አንቦጫጭቀውም። እናንተ እኔ ይህ ሳጫውታችሁ ‚አውሬነትህን ረሳኸው’ ብላችሁ እንደምትስቁብኝ አውቃለሁ።

„ምግባችንን ከሳህናችን ላይ እንበላለን እንጅ ጌቶች ሲበሉ ሆነ ልጆች ዳቦአቸውን አስቀምጠው ሲጫወቱ ቦጭቀን እናንተ እንደምታደርጉት አንሮጥም። በዚያም ሳቢያ ጥዋት ማታ በድንጋይ አንደበደብም።

fabula-dogcatአሁን ያቺ ድመት በዚህ ስታልፍ የሆነውን አይቼአለሁ። ከቤት ድመቶችም ጋር አብረን እንውላለን እንጅ አንጣላም። ምንም የሚያጣላን ምክንያት የለም። እሱዋ እራሱዋ አይጥ አይታ ስትፈራና እኔ ጋ መጥታ ስትወሸቅ አብረን እንስቃለን እንጅ እሱዋን አሳደን ጊዜአችንን በዚህ አናጠፋም…በጊዜአችን ሌላ ስንት የሚሰራ ነገር አለ። እኔ ለምሳሌ አስተማሪ ተቀጥሮልኝ ጋዜጣ ጥዋት ጥዋት ለጌታዬ ለማምጣት ትምህርት ወስጄ ነበር። ሌሎቹ ሲማሩም አ…“ እያለ እላይ የተሰነዘሩትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሙከራ በሚያደርግበት ደቂቃ አንዱ ዕድሜው ጠና ያለ ውሻ ተነስቶ „…ምን ይደረግ አንተ ‚ችሎ ማደር‘፣ አንተ እኮ ነህ በዚህ ውርጋጥ ዛሬ የምታሰድበን። እንተ እንደዚህ እኛ እንደዚያ እያለ …ይህ ትላንት የመጣ ጥጋበኛ ውሻ እኛን እየሰደበን ነው። የልብህን እየተናገርክ የስድብ ናዳ አወረድክብን …። እግዚሔር ይስጥህ። ጥፋተኛው አንተ ሳትሆን አንተ ስብሰባውን የጠራኸው አቶ ‚ችሎ ማደር ነህ!“ ብሎ ጋባዡንም ተናጋሪውንም በወቀሳ ያዋክባል።

ሌላው ተነስቶ „…አወቂ ሲጫወት ልጆች እየተነሱ ጣልቃ እንዳይገቡ ቁጥጥር ይደረግ „ ብሎ ማሳሰቢያውን ለቤቱ ያቀርባል። እሱም ማሰሪያ ሳያገኝ እንደገና አንድ ያልታሰበ ነገር ስብሰባውን እንዳለ ገልብጦ በሰከንድ ውስጥ በጭንቅላቱ ያቆመዋል።

አንድ ተንኮለኛ ዘበኛ- እነሱ ሲቦጫጨFabulaቁ ቁጭ ብሎ ማየቱን ይወዳል- የውሾቹን ስም አንድ በአንድ „ አንተ …ውስኪ…ቦቢ ዘብ ይደሩ የት ነህ?…እነነብሮ እነ ግሥላ እነ ፑሺኪን እነ ሉሉ የትናችሁ…ተመልከቱ…“እያለ እየተጣራ እንደተለመደው እነሱ ሲቦጫጨቁ ቁጭ ብሎ እግሩን ዘርግቶ ለመሳቅ አንድ አጥንት እያሽከረከረ ያ ተንኮለኛ ዘበኛ መሓላቸው ይጥላል።

ግልጽ ነው። ያችን አጥንት ለብቻው ቀምቶ ለመብላት ወንዱም ሴቱም ብድግ ብለው ተያያዙ። በቅጽበት በትንሽ ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ያ በሰላም የተጠራው ስብሰባ ወደ ጦር ሜዳ ተቀየረ። ሁሉም አፈር ለበሱ። እንደፈለገው ተቦጫጨቁለት።

ምን መጣ ብለው ቡችሎቹም ሸሽተው አፋፍ ላይ ቆመው ይህን ጉድ – እነሱም ነፍስ ሲገዙ የሚገቡበትን ነገር- ትንሽ ኮረብታ ላይ ሁነው መመልከት ጀመሩ።

ሁለተኛው አጥንት በሌላ ዘበኛ ተወርውሮ እፎይ ሳይሉ መሓላቸው ወደቀ። እንደገና የይገባኛል/አይገባህም ግብግቡ በመካከላቸው ተከፈተ። አጥንቱዋም አፈር ትለብሳለች። በጥቂት ደቂቃ ከፊሉ ውሻ ቆስሎ በዚያች ትንሽ ጊዜ ውስጥ ያነክሳል። ሌላው ቁስሉን መላስ ጀምሮአል። አፍንጫው የደማ አለ… ቆዳው የተቀደደ። ጭንቅላቱንና ጆሮውን የሚነቀንቅ አለ። ቁና ቁናቸውን ይተነፍሳሉ።

ያ ፈረንጆች ቤት „ለጥቂት ጊዜያት በልጅነቴ አሳልፌ ነበር“ ያለው ውሻ ቡችሎቹን ሰብስቦ „ ከዚህ የውሻ መብት ከማይከበርበት አገር ጠፍቶ ሌላ አገር መብታችን የሚከበርበት ቦታ ሄዶ መኖር ያስፈልጋል እያለ…“ ሰበካውን ጀመረ።

„… ታውቃላችሁ በአውሮፓ ለእንስሶች መብትና ክብር የሚሟገቱ ሰዎች አሉ፣ እነሱ ጋ በረሃውንም ባህሩንም አቋርጠን ተሻግረን እንሄዳለን።… ከዚያም ሰላም እናገኛለን። …ልንገራችሁ ውሻውን የሚደበድብ ቀርቶ የሚገላምጥ ሰው እንኳን እንደሰማሁት ይቀጣል… ይህን በጆሮዬ ነጮቹ ሲናገሩ ሰምቼአለሁ“ እያለ ይዞአቸው ከዚያ ከማያምር ግርግር በወሬው እየሳበ ዞር አለ።

ታሪኩን እንግዲህ እንፍታው ።

ለቱ የተወረወሩት አጥንቶች „ሁለቱ እኛ የምናውቃቸው አይዲኦሎጂዎች“ ናቸው።

ideology

አይዲኦሎጅ በአንድ በኩል ያሰባስባል በሌላ በኩል ያከፋፍላል። በአንድ በኩል ብቻዬን አሸንፌ ልውጣ ብሎ ሌሎቹን ከፊቱ የቆሞትን ደፍጥጦ ይሄዳል። በሌላ በኩል የሚያንገራግሩትን ያታልላል። ይሸነግላል። ያባብላል። የሌለ ያልነበረ የውሸት ታሪክ ፕሮፓጋንዳውን ለቆ አእምሮም ይሰልባል። ለመስለብም ይጥራል።

ርዕዮተ- ዓለም ጥቂቶቹን ደጋፊዎቹን የመሰብሰቡን ያህል ከአላወቁበት ሁሉንም ሕዝብ አሳክሮ አጋጭቶ ያጣላል። አገርንም ያተረማምሳል። ደስ ከአለውም ያሸጣል።

ይኸው ርዕዮተ ዓለም እንደገና በደንብ ከአልያዙት አሳብዶ ጎልጉለው ቆፍረው ያመጡትንም ሰዎች ሳይቀር ይዞ አያይዞ እነሱንም ገደል ይከታል። ቢቀር ቢቀር እነሱን አጠፋችሁ ብሎ እሥር ቤት ያስወረውራል።

ትልቁንም ትንሹንም አመሰቃቅሎ አንዱን በአንዱ ላይ አስነስቶ ያጨራርሳል። ምንም የማያውቀውንም እሳት ውስጥ ከቶ ያስጨርሳል። የዞረበት አይዲኦሎጂ ደግሞ አንድን ሰው እላይ ሰቅሎ መላ ሕብረተሰቡን ወደ የግል ሐብት ወደ እሥር ቤትም እንዳለ ይቀይራል።

ሱማሌና…ሩዋንዳ ብሩንዲና ኬንያ፣ ሱዳናና ደቡብ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና የመን፣ ኮንጎ እና መካከለኛው አፍሪካ፣ ግብጽ ሊቢያ ማሊና ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ ኡጋንዳ ኢትዮጵያና ኤርትራ …ኢራክ፣ ሶሪያ ሊባኖስ አፍጋኒስታን … እነዚህ ሁሉ አገሮች የሚተረማመሱት እርስ በራሳቸው የሚፋጁት በሌላ ነገር ሳይሆን ከውስጥ ሆነ ከውጭ በተወረወረላቸው በማያስማማ አደገኛ አይዶሎጂ ነው።

ያንን ያዝን ብለው በሚያምኑት ርዕዮተ ዓለምም በእሱ ሳቢያ በተቆሰቆሰው እሳት አንዱ ተነስቶ በሌላው ላይ ጦር አውጆል። ያኛው በዚህኛው ይህኛው በዚያኛው ላይ ተነስቶአል። ሁሉም በአንዱ ላይ። አንዱ ብቻውን በሌላው ላይ! በመጨረሻውም ተናንቀዋል። አሸናፊ ደግሞ በመካከላቸው የለም። አይኖርም። የዛሬው ድል አድራጊ ነገ በተራው በሌላው ድል የሚመታ ነው።

„…የማን ቤት ፈርሶ የማን ቤት ሊበጅ የአውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ…“ ይህ በኢትዮጵያ የተለመደ አነጋገር ሌላም ቦታ በጎረቤት አገሮችም አለ። ሱማሌዎች እርስ በራሳቸው የሚገዳደሉት፣ ኬንያ የተራረደው፣ ሴንትራል አፍሪካ… ዛሬ ጎረቤቱን ቤንዚን አርከፍክፎ የሚገድለው በዚሁ በተጫረው የጥላቻ አይዲኦሎጂ ነው። አፍሪካን ያሳበደው ይኸው ትምህርት ነው።

በእርግጥ አይዶኦሎጂ የጠላትና የወዳጅ እንደ ጎራአቸው መሰባሰቢያ አዳራሽና መገናኛ ቤት ነው። እንደ መጠለያ ድንኳንና ጎጆም ያገለግላቸዋል። ለአንዳዶቹማ እንደ „ቤተሰብም“ ነው። እንደ ዔሊ ቀፎ ጠንካራ ምሽግ በቀላሉ የማይሰበር ዛጎል ይመስላቸዋል። እንደ ጃንጥላም ሁኖ ከሚርከፈከፈው ዝናብና በትንሹ ከሚፈነጥቀው የጸሓይ ጮራ ለጊዜው ይከላከላል።ideology-02

ከአልተጠነቀቁ አዲዮሎጂ አእምሮን ሰልቦ „ባሪያ“ አድርጎ የሕልም ዓለም ውስጥ ከቶ አፍዝዞ ጦር ሜዳ ድረስ ይነዳል። አውሎ ንፋስ ሲመጣ ኃይለኛ ማዕበል ሲነሳ ደግሞ በቀላሉ ተኖ በመጣው ፍጥነት ተመልሶ ይጠፋል። ያ ሲሆን ደግሞ በኤርትራና በጠቅላላው ምሥራቅ አፍሪካ እንደምናየው ሰው ሁሉ ግራ ተጋብቶ ለካስ ያ ሁሉ ድካም ለዚህ ነው ብሎ ለስደት ይዳረጋል። ወይም ጆሮውን ዘግቶ ጀርባውን አዙሮ ይተኛል።

በደንብ ለመመልከት ሁለቱን ጀርመኖች እንውሰድ: – ምዕራቡንና ምሥራቁን ጀርመን!

ለምንደው ጀርመኖች የዛሬ ዘጠና አምስት ገደማ ንጉሡን አባረው የቫይመሩን ሪፓብሊክ አውጀው „…እኔ ልግዛ እኔ ልምራ“ በሚባለው የፓለቲካ ድርጅቶች ንትርክ ውስጥ ገብተው ያ እፎይ ብሎ ለመኖር የሚፈልገውን ሕዝብ በአንዴ በነገር አሳክረው በቀላሉ ሊያወናብዱት የቻሉት?

ለምንድነው አብዛኛው የጀርመን የፖለቲካ ድርጅት በዚሁ በቫይመር ሪፓብሊክ ዘመን የራሱን ተደባዳቢና ተዋጊ ጦር ልዩ መለዮ የወታደር ልብስ የማዕከላዊ ኮሚቴ የስለላ ድርጅት የቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ክፍል ፈጥሮና መሥርቶ መንገድ ላይ እርስ በእራሱ መፋለጥ የጀመረው?

እንግዲህ እንዴት ነው ሒትለር በጀርመን አገር አሸናፊ ሁኖ ሊወጣ የቻለው?

ለምንድነው ከፋሽሽቱ ሒትለር አገዛዝ በሁዋላ ጀርመን ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በሁዋላ፣ ለሁለት ይህች አንድ አገር የተከፈለቸው?

ለምንድን ነው – አንደኛው ኮሚኒስት ሁለተኛው ነጻ -የዲሞክራቲክ ሕብረተሰብ ሁነው- በዓለም ፖለቲካ ምድር ላይ ብቅ ያሉት?

እንግዲህ በመጨረሻውም :-

ለምንድን ነው የምዕራብ ጀርመን የዛሬ ሃያ አምስት አመት አሸናፊ ሁኖ የወጣው? ለምንድነውስ የምሥራቅ ጀርመኑ የኮሚኒስቶች ሥርዓት ተንኮታኩቶ የወደቀው?

በሌላ አነጋገር ለምንድን ነው የኮሚኒስቶቹ ሥርዓት ብቻዬን ልግዛ ብሎ አጥር አጥሮ በጠበንጃ አፈ ሙዝ ሲገዛ ከርሞ በሁዋላ ሳይታሰብ በሰላማዊ የሕዝብ አመጽ ሊወድቅ የቻለው? እንዴትስ ወደቁ ?

ለምንድን ነው ምዕራብ ጀርመን በሸንጎ ምርጫ ከፖለቲከኞቹ ለመገላገል ይህኛውን ሰላማዊ መንገድ እንደ መፍትሔ የመረጠው? የተለያዩ የፖለቲከ ድርጅት መሪዎችና አባሎቻቸው በነጻ-የፓርላማ ምርጫ ውድድር ውስጥ ገብተው ለመሳተፍ ለምን ተስማሙ?

የጀርመን ኢኮኖሚንስ (የምዕራቡ) እንዴትና በምን ብልሃት ነው ከወደቀበትና አመድ ከለበሰበት ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በሁዋላ ( ኢትዮጵያ የዛሬን አያድርገውና ስንዴና የብርድ ልብስ እንዲሁም ቡና ለጀርመን፣ ለእንግሊዚ ለጃፓን በጊዜው ዕርዳታ ሰጥታለች) አሥራ ሁለት አመት በአልሞላ አጭር ጊዜ ውስጥ በልዩ ተአምር ከመቀመቅ ተነስቶ በአንዴ -በስድሳው አመተ ምህረት – ዓለምን ሊያስገርም የቻለው?… እረ ብልሃቱ፣ የእነሱ ብልሃታቸው ምንድነው? ምን ነበር?

በመጨረሻው እንደገና በምን ብልሃትና ዘዴ ነው? በየትኛው መንገድ ነው? የጀርመኑ የፖለቲካና የኢኮነሚ ሥርዓት አሁን ሌሎቹ አገሮችና መንግሥታት በኢኮኖሚና በፊናንስ ቀውስ ውስጥ ገብተው ሲማቅቁ እነሱ በአውሮፓ/በዓለምም ውስጥ ጠንካራ ሁነው ሊወጡ የቻሉት?

ልሱ አጭር ነው። menschenwuerde

እንደማመጥ ከተባለ!

ምዕራብ ጀርመን አሸናፊ ሁና ሊትወጣ የቻለቺው በሚቀጥሉት አብይ ምክንያቶች ነው።

መንገዳቸውን የቀየሱት ድርቅ በአለ የአምባገነን አይዲዎሎጂ አይደለም። በእሱ ሳይሆን በቫሊውስ- በእሴት ላይ በአተኮረና በእሱም ላይ በተመሰረተ አመለካከትና አሠራር ነው።

እሴት ምንድነው? ምንድናቸው እነዚህ እሴቶች? የትኛው እሴት ነው ከሁሉም ወሳኝ?

አንደኛው እሴት -ይህንንም ሕገ-መንግሥታቸው ላይ ገና -ሀ- ብለው ሲጀምሩ ጥሩ አድርገው አስቀምጠውታል- የሰው ልጆች በአጠቃላይ ከሕይወት ልምምዳቸውና ተመክሮአቸው ከሁሉም በላይ ከአምላካቸው በተፈጥሮ በእሱ አምሳል በመፈጠራቸው ያገኙት ትምህርት ነው- „የማንም ሰው ሰበአዊ መብቱና ክብሩ በማንም አይረገጥም አይደፈርም „የሚለው አንቀጻቸው ነው።

ይህም አብሮ ተከባብሮ ተቻችሎና ተደጋግፎ ለመኖር የሰው ልጆች ያገኙት ጥበብና ጸጋ ነው።

እርግጥ በዚህች አጭር ጽሑፍ ከድንጋይ ዳቦ ዘመን ተነስተን ወደ 1948ቱ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ መግለጫ ድረስ አሁን መጥተን ሁሉን ነገር ገበታው ላይ ዘርግተን ማሳየት አንችልም። በአጠቃላይ የሰው ልጆች ከጠብ ይልቅ ፍቅርን እንደሚመርጡ ማንኛችንም በደንብ እናውቃለን።

በጦርነት ፋንታ ሰላምን ከመበታተን አንድነትን፣ ከሥራዓተ አልባነት ይልቅ መልካም አስተዳደርን፣ ከቀማኛነት መልካም ሥነ ምግባርን ከተንኮል መረዳዳትን ከበደል ፍርድን….እነዚህን ሁሉ የሰው ልጆች እንደሚያስቀድሙና እንደሚመርጡ ይህን ስለምናውቅ ስለምንረዳ መድገሙ አስፈላጊ አይደለም።

ታዲያ የነገሮች አቀማመጥ እንደዚህ ከሆነ የሰው ልጆች ሁሉ ችግር ከየት መጣ?

ለጀርመኑ ፈላስፋ ለማርክሲ እና ለእሱ ተከታዮች ለኮሚኒስቶቹ መልሱ ቀላልና አጭር ነው።

በእነሱ ዕምነት „በዝባዡ ክፍል-አደሃሪ“ የሚሉት መደብ ስለ አለ „ይህን ሁሉ መዓት በሰው ልጆች ላይ ያመጣውና ያወረደው እሱ ወይም እነሱ ስለሆኑ „እነሱን ደምስሰን የላብ አደሩን አምባገነን ሥርዓት ከዘረጋን ይህች ዓለም በአንዴ ወደ ገነት ትቀየራለች“ ባይ ናቸው።

ኢትዮጵያም -የሚያሳዝነው ታሪካችን ይህ ነው-የመረጠቺው መንገድ ይህኛውን ነው።

ሓይማኖተኛውና የሃይማኖት አስተማሪው ከዚህ ለየት ያለ አመለካከት አለው። „ሰይጣንና መጥፎ መናፍስት በዓለም ላይ ስለተበተኑ እነሱ ናቸው የችግሮቻችን ሁሉ መነሻ „ ብለው ያስተምራሉ።

ለአክራሪ ፋናቲከሮች ደግሞ ሌላው ሕዝብ ተቀብሎ የሚከተለው ከእነሱ የተለየ „ እምነትና ሃይማኖት ያለው ሰው ለዓለም ሁሉ ችግር ተጠያቂ እሱ“ ነው ባይ ናቸው። እንደዚህ ዓይነቱ አደገኛ አመለካከትዘንድሮአፍሪካ ገብቶአል።

ለመለዮ ለባሹ ለጠበንጃ ያዢው ወታደር ሳይጠየቅ እሱ እራሱ የራሱ መልስ አለው። ተማሪውም እነደ ተማሪነቱ እንደዚሁ የችኮላ መልስ ታቅፎ ቁጭ ብሎአል። „ነጻ-አውጪው“ ደግሞ በተራው ሌላ ማንም ሰው ከአለ መሪው በስተቀር የማያውቀው የራሱ „ራዕይ“ አለው። አንዴ „አዲሱ ዲሞክራቲ ነው።“ አንዴ „ብሔራዊ ዲሞክራሲ።“ አንዴ „ዲሞክራቲክ አብዮት።“ ሌላ ጊዜ ….ሶሻሊዝም ኮመኒዝምነው። ወይም መገንጠል ተብሎ ፕሮግራማቸው ላይ ተጽፎአል።

የሰው ልጆች ባህሪና አካሄዳቸውን እናውቃለን የሚሉት እነሱ እንደሚሉት ከሆነ (ይህ የታሪክና የፍልስፍና የሳይኮሎጂና የሕግ ሰዎች ምራቃቸውን የዋጡትን ፖለቲከኞች ያካትታል…) ተቆጣጣሪና ተቆጪ ከልካይ ኃይልና ተቋሞች ሕግና ሥርዓት ከሌሉ ነገ „…አንተም እኔም እሱዋም እሱም ማንም አረመኔ“ ከመሆን አትመለሱም ይላሉ።

እንግዲህ ማነው አሁን ትክክለኛው?

መልሱን ለማግኘት ወደ ጀመርንበት ወደ ጀርመን አገር ወደ እነሱ „ወድቆ መነሳት ታሪክ „ እንመለስ። የግድም መመለስ ያስፈልጋል ።

ለጀርመን ችግር ለዚያ ሁሉ ጣጣ መንጣጣ መነሻ ዋና ተጠያቂዎቹ ለአገሪቱ መከፋፈል ሆነ ወደ ጦር ሜዳ ለመጓዝማርክስ በአንድ በኩል ሒትለር በሌላ በኩል እነሱ ናቸው ብለናል። ወደዚያው እንመለስ።

የእሴትና የአይዲኦሎጂ ልዩነት የሚታየውም እዚሁ ላይ ነው።

አንደኛው የጀርመን ግዛት – በኮሚኒስቶቹ ይመራ የነበረው የምሥራቁ በርሊን ከ„እሴት“ ይልቅ -እዚህ ላይ ትሩፋት እና ትውፊትን መጨመር ያስፈልጋል- በእነሱ ፋንታ የዚያ አካባቢ መሪዎች ያተኮሩትና ዕድሜአቸውን የገፉት አደባባይ ተወጥቶ ቢጮህ ምንም ነገር በማያመጣው የአይዲኦሎጂ መፍክርና እነሱን የሚቃወሙትንና የሚተቹትን ጭንቅላቶች- ሓሳባቸውን ወስዶ እንደማስተካከልና እንደመታረም – እነሱን አሳዶ በመያዝና በማሰር ላይ ነው። አይረሳም ምን የሚያካክሉ- ዕብድ የሚያክሉ የማርክስና የኤንግልስ የሌኒንና የስታሊን የብርጄኔቭና የሆኔከር ፎቶግራፎች አሥር ሰው አንዱን ፎቶ እንደ ሞኝ አውራ ጎዳናው ላይ „እንደ ታቦት „ተሸክመው እየዘመሩ (ወደው ሳይሆን ) ሲጓዙ።

በዘመናቸው እነዚህ ሰዎች ኮሚኒስቶቹለአገራቸው አልሰሩም ማለት አይቻልም።

ቤቶችና ሕንጻዎች በበቂ ሰርተዋል። ግን ምን ዓይነት ቤት ነው የሰሩት?

ሐኪም ቤቶች በየአለበት ከፍተዋል። ግን ምን አይነት መድሓኒትና የሕክምና መሣሪያ ሰርተው አውጥተዋል?

ትምህርት ቤትና ዩኒቨርስቲ ቆርቁረዋል። ግን ምን ዓይነት ትምህርት ሰጥተው ልጆቻቸውን በዚያ ኮትኩተው አስመርቀዋል?

… መንገድ ጠርገዋል። ድልድይ ዘርግተዋል። ሓውልትና ሓዲዲ ሆቴልና ምግብ ቤት የመኪና ፋብሪካ ሳይቀር ተክለው ሊሞዚን ተሽከርካሪ መኪናዎችና ካሚዮኖችም ሰርተው አውጥተዋል። ጥያቄው ግን ምን ምን ዓይነቱን ሠሩ፣ ምን ግሩም መtrabiኪና ሰሩ የሚለው ነው?

የምሥራቁ መኪና እነ ትራቢና እነቫርተቡርግ…ከማርቼዲስ እና ከቢኤም ደብሊዩ ከፖርሸና ከአውዲ ከቮልስባገንና ከኦፔል…ጋር በምንም ዓይነት አይወዳደርም።

የቤትና የመንገድ የድልድይና የሓዲዲ አሰራራቸውን ምሥራቅ ጀርመን ምናልባት ከአፍሪካውይኖቹ ሊበልጥ ይችላል- የምዕራቡን ግን በምንም ዓይነት ተወዳድሮ አይደርስበትም።

የሁለቱ ጀርመኖች የምርመራና የአዳዲስ ነገሮች ፈጠራ ትምህርት ቤቶቻቸውም አንድ አይደሉም። የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አላቸው።

እንዴት ነው ? በምን ብልሃት ነው? ምዕራቡ ምሥራቁን ሊበልጠው የቻለው?

„የቦኑ ሪፓብሊክ“ የወሰደውና የተጓዘበት መንገድ እላይ እንዳየነው ደረቅ አይዶሎጂ ሳይሆን -ትሩፋቱንም ለጊዜው እንተው- በቫሊዩ/በእሴት ላይ በተመሰረተ መፍትሔ ነው።

በምሥራቅ ጀርመን ጋዜጣዎች እየታተሙ ይወጡ ነበር። ግን ምን ዓይነት ጋዜጣ ነበር? ስንት ጋዜጣዎች?…. የተለያዩ አስተሳሰቦችና አመለካከቶችን ይኸው ጋዜጣቸው ያስተናግድ ነበር ወይ? ሰዎች እንዲከራከሩበት ይጋብዝ ነበር?

እንደ ምዕራብ ጀርመን የኮሚስቶቹም ሥርዓት እንደ አቂሚት አልፎ አልፎ ምርጫ አካሂደው በ95% ከመቶ እነሱ እራሳቸው አሸንፈው ሸንጎአቸው ውስጥ የህዝብ እንደራሴዎችን ያስቀምጡ ነበር። ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች መናገርና መጠየቅ ይፈቀድላቸዋል?

በምሥራቅ ጀርመን በተለያዩ ስም የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ። ከእነሱስ ጀርባ እነማን ነበሩ?

ተለጣፊ ድርጅቶች ናቸው ወይስ በነጻ የተደራጁ?

በምሥራቅ ጀርመን እንደ ማንኛውም አገርና መንግሥት ፍርድ ቤትና ጠበቃ፣ ፖሊስና የስለላ ድርጅቶች ወታደርና የጦር ኃይሎች ነበሩ።

ዋና የበላይ አዛዡ ለመሆኑ እነማን ነበሩ? ከኮሚኒስቶቹ ትዕዛዝ ውጭ ያስቡ ነበር? … ዳኞቹስ ተጠሪነታቸውስ ለማን ነው?

ለአንድ ሕዝብ እንዲያስብ እንዲሰራ እንዲናገርና እንዲቃወም መብቱን ስጠው ተአምር በዚህች ምድር ላይ ይሰራልሃል። ይህን ኮሚኒስቶቹ ይቀበሉይፈቅዱ ነበር?

በምሥራቅ ጀርመን ፊልም ይሰራል። መጽሓፍት ይጻፋል። ቲያትር ይደረሳል። መልዕክቱ ግን በመጨረሻ ምን ነበር?

እንደማንኛው አገር በምሥራቅ ጀርመን የቴሌቪዥንና የራዲዮ ፕሮግራሞች ይሰራጩ ነበር። ስለምን ነበር በየቀኑ የሚወሩት?

ምዕራቦቹ ይህን ተገንዝበው ያኔ በሚገበያዩበት በማርካቸው ላይ ሦሰት ቃላቶች ያኔ ጽፈው ማንም ሰው በየቀኑ እንዲያነበውና እንዲገነዘበው አድርገዋል።

እነሱም:- „…አንድነት ነጻነትና ፍትህ-ማለት የሕግ በላይነት“ የሚባሉትን ሦስት መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ሳንቲሞቻቸው ላይ አሥፍረው በጀመሩት ሥራቸው -ሌሎቹን ነገሮች ለታሪክ ጸሓፊዎችና ለጠበብቶች ለቀው- ሳይታክቱ ቀጥለውበታል።

አብራርተው ሕገ -መንግሥታቸው ላይ እሴቶቻቸውን ሲያሰፍሩትም እነሱእንደዚህ ብለው አስቀምጠውታል። ከሁሉም አረፍተ ነገር ቀድሞ በመጀመሪያ!OLYMPUS DIGITAL CAMERA

„…የማንም ሰው መብቱና ክብሩ በማንም ሰው አይደፈርም አይረገጥም „ የሚለው ቃል ሰፍሮአል።

ቀጠል አድርጎ ይኸው ሕገ-መንግሥታቸው „…ማንም ሰው የፈለገውን ሓሳቡን በጽሑፍ ይሁን በቃል በወረቀት ይሁን በፊልም መልክ አቅርቦ መበተን ማሰራጨት ይችላል። …ሣንሱር የሚባል ነገር የለም። „ ብሎ አዲሱን ዘመን ያበስራል።

ይኸው ሕገ መንግሥታቸው „መደራጀት መደገፍና መቃወም መሰብሰብ መምረጥና መመረጥ… መመራመር…ማንም ሰው ይችላል“ ይላል።

እነዚህ እሴቶች እነዚህ ቫሊዩዎች ናቸው የአገርንና የሕዝብ አንድነትን የሕግ በላይነትን ከሁሉም በላይ የግለሰብ ነጻነትን አረጋግጦ ጀርመንን ዛሬ የደረሰችበት የሥልጣኔን ዕድገትና ደረጃ ላይ ያደረሳት።

ይህ ብቻ አይደለም።

የጀርመን ሕገ-መንግሥት የተመሰረተበት እሴት ሰብሰብ አድርገን ስናየነው „…በግለ ሰብ ሙሉ ነጻነት ላይ „የቆመ ነው። እዚያም ውስጥ „ በሕግ ፊት ሁሉም እኩል “ እንደሆነ ያነሳል። „የሕዝብ ውሳኔና ዲሞክራሲም“ በአገሪቱ እንዳለ ያረጋግጣል።

የሕገ- መንግሥቱ እሴት ነጻው ሕብረተሰብ እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ያብራራል።

እዚያም ውስጥ የግል ሕይወትና የግል ኑሮና የመኖሪያ ቤቶች በማንም እንደማይደፈሩ በግልጽ ቋንቋ ያነሳል።

…ሃይማኖትና የፖለቲካ አመለካከት የግል እንደሆነ፣ በዚያውም በንግድ ላይ መሰማራትና በኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ገብቶ መንቀስቃስ፣ በአካባቢና በአገር ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት…ተዘዋዎሮ ሐሳብ በጋራ ጉዳይ ላይ ከሌሎቹ ጋር መለዋወጥና መነጋገር፣ መረዳዳትና መከባበር… ሕገ መንግሥቱ እነዚህን ሁሉ እሴቶች ያረጋግጣል።

የተመረጠው መንግሥትም አስተዳደርም ኃላፊነትና ግዳጅ እንዳለበትም ያነሳል።…. ሕጉን ለማክበር የሕዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አገሪቱን ከአስከፊና አደገኛ ነገሮች ለመጠበቅ፣ ትምህርትንና ዕውቀትን ለማስፋፋት ሰላምን ለማውረድ ተፈጥሮን ለመጠበቅና ለመንከባከብ…ባህልናና ትውፈትን /ትራዲሽን ቋንቋንና ቅርሳቅርሶችን ለማዳበር ለመጠበቅ እንደዚሁ መንግሥትም ሕዝብም ኃላፊነት እንደአለባቸው ይገልጻል።

ከዚሁ ጋር ማንም ሰው የሸንጎ አባልም ይሁን ወይም ሚኒስትር የሕሊና ነጻነት እንዳለውና ይህን ነጻነቱን ተጠቅሞ መደገፍ መቃወም እንደሚችል የሕጉ እሴት ያረጋግጥለታል።

… ማታለልና ማጫበርበር ሥልጣንን መከታ አደርጎ አገርንና ሕዝብን አደጋ ላይማንም ፖለቲከኛ መጣል እንደማይቻል ሕጉ ያግዳል ። ለዚህም ነው የመሓላ ቃል በአደባባይ የሚሰጠውም!

ከሁሉም በላይ የግል ሐብትን ያረጋግጣል። የጀርመን ኢኮኖሚም ያደገው በግለሰቦች ድካምና በተመራመሪ ጠበብቶች ጥረት በሠራተኛው ሙሉ ተሳትፎና በእሱ አገርና ሥራ ወዳድነት በሦስቱ ሕብረት ነው።

የአይዲኦሎጂ ዕብደት -በታሪክ እንደምናውቀው- ከዚህ በፊት በተለያዩ ዘመናት ይህችን አገር (ድፍን አውሮፓንም ጭምር) ጦርነት ውስጥ ከቶ አመድ አልብሶአት ለሁለት በመጨረሻም ከፍሎአት ሕዝቡን ችግር ላይ ጥሎም ሲጨፍርባት ከርሞአል።

ይኸው የአይዲኦሎጂ ዕብደትም የምዕራብ ጀርመኑን ተወላጅ ኤርሽ ሆኔከርን -ዛር-ላንድ የተወለደውን- ምሥራቅ በርሊን ገብቶ „ዲዲአርን“ ከሠላሳ አመት በላይ እንዲገዛ አድርጎታአል።

በርካታ የምዕራብ ጀርመን ፖለቲከኞችም – የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐንስ ዲትሪሽ ጌንሸርና ሌሎቸ ከምሥራቅ ጀርመን መጥተው ነጻው የምዕራቡ ሕብረተሰብ ውስጥ ተሳትፈው መርተው የአገሪቱን አንድነት በዲፕሎማቲክ መንገድና በፖለቲካ ትግል መልሰው እነሱም አቋቁመዋል።

በመጨረሻው እንደምናየው በበርሊን ግንብ ውድቆ:-የነጻ ሕብረተሰብ ቫሊዩ በአሸናፊነት ወጥቶአል። mercede

እንዲያውም ፍራንሲስ ፉክያማ እንደአላው ይህ ሥርዓት ትክክለኛነቱን አሳይቶአል።

ቫሊዩና አይዲኦሎጂ ይለያያሉ።

በእርግጥ በሌላ በኩል ቫሊዩና አይዲኦሎጂም ይያዛሉ። -ይህ ደግሞ ሌላ እራሱን የቻለ ሰፊ አርዕስት ነው።

ለጊዜው ከዕብደት ዓለም ለመውጣት ከአይዲኦሎጂ ይልቅ እሴቱ ላይ ማተኮሩ ለአንድ ሕዝብና ለአንድ አገር ለፖለቲከኛም ጠቃሚ ነው።

እሱም ብቻውን አይበቃም።

ከቫሊዩስ ጋር ቨርቺውስን/ ትሩፋትን አብሮ ማንሳት የበለጠ ጠቃሚ ነው። ሞራልና ኤትክስንም፣ ትራዲሽንም ሲጨመሩበት ደግሞ ውሽት ጥራዝነጠቅነትና ጥላቻ ከፖለቲካ ትግል-እንዳለ ማጥፋት ባይቻልም- ቢያንስ ይርቃል።

ይህ ደግሞ ከሆነ በነጻነት አንድ ሰው ቀና ነገር ለአገሩና ለሕዝቡ ማሰብ ይችላል። እኛ ነጻ-ሰው ነን !

እዚህ ደረጃ ላይ – ጉዳዩን እንዝጋው- ያደረሳቸው „የጀርመን ሕገ- መንግሥት“ የተነደፈው ከሦስት ገብተውበት ከነበረበት መኣትና ጣጣ እንደገና ተመልሰው እንዳይገቡ ለመትረፍ ነው።

አንደኛው ንጉሡን አባረው ከገቡበት ከቫይመር የአይዲኦሎጂ ትርምስ ለመሸሽ ነው።

ሁለተኛው ከዘረኛው ከሒትለር ፋሺዚም የጠበንጃ ክክትል ሥርዓት ለመራቅ ነው። ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ከኮሚንስቶቹ አምባገነን የጠበንጃ አገዛዝ ለመትረፍም ነው።

ከዚያ አልፈው አሁን የአውሮፓ አንድነት ሞተሩም አንቀሳቃሽ ሹፌሩም እነሱ ሁነዋል። ለምን እና እንዴት?

ምርጫው ከዚህ በሁዋላ የአንተ ነው።…. ነጻነት ወይስ ባርነት?

*

ተፈሪ መኮንን

አእምሮ የጥር 2006 / January 2014/ እትም፣ቅጽ 2 ቁጥር 6

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s