ምኒልክ – በጎታ / Gotha

ምኒልክ- በጎታ

menelikatgotha

እንደ ዳግማዊ ምኒልክ በዓለም የተደነቀ እንደ እሳቸው ደግሞ በአንዳንድ የአገሪቱ ልጆች ዘንድ የተናቀ የአፍሪካ ንጉሥ የለም።

ደፍረው -ይህ ይገርማል- ሐውልታቸው እንዲፈርስ አዲስ አበባ ላይ አንዳንዶቹ ጠይቀዋል። ብዙዎቹም ይህ የመታሰቢያ ሐውልቱ እንዳይነካ ታግለዋል። ለምልክትም ቀለም ጥቂቶቹ ቀብተዋል።

በጀርመን አገር ጎታ በሚባለው ከተማ የመቶኛ የሙት አመታቸውን ምክንያት በማድረግና እሱንም በማስታወስ አሥራ ስድስተኛ „የውርሰ ኢትዮጵያ የሳይንስና የምርምር ጥናት ማህበር“ አመታዊ ጉባዔውን እዚያ አካሂዶ በንጉሠ ነገሥቱ በአጼ ምኒልክ ሥራና ገድላቸው ላይ ሦስት ቀን የፈጀ አተኩሮ ለእሳቸው ሰብሰባው ሰጥቶአል።

ጎታ ታሪካዊ ከተማ ናት።

እዚህ ነው የጀርመኑ የሲሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የመጀመሪያውን የድርጅቱን ፕሮግራም ነድፎ ለጀርመን ሕዝብ ያስተዋወቀው።

እዚህ ነው ከአምስት መቶ አመት በፊት እነ ዶክትር ማርቲን ሉተር የፕሮቴስታንትን ሃይማኖት እንቅስቃሴ በዘመናቸው ለኩሰው ይህን እምነት ሊያስፋፉ፣ሊያራምዱት የቻሉት።

እዚሁ ነው ከሦስት መቶ ሃምሣ አመት በፊት ኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ እና የጀርመኑ ተወላጅ ሒዮብ ሉዶልፍ በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደገና የተገናኙት።

እንግዲህ እዚሁ  የቤተ-መንግሥቱ አንደኛውና ትልቁ አዳራሽ- የመስተዋትአዳራሽ ውስጥ-  ነው ከጥቅምት 11 እሰከ ጥቅምት 13 2013 ዓ.ም (እአአ) „ውርሰ ኢትዮጵያ“ የተባለው ድርጅት አሥራ ስድስተኛውን አመታዊ ጉባዔውን ጠርቶ፣ንጉሠ ነገሥቱን አጼ ምኒልክን ከሞቱ ከአንድ መቶ አመት በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የእኝህን ትልቅ ሰው ሥራና ገድል ያስታወሰው።

ጉባዔውን የከፈቱት የከተማው ከንቲባ ሚስተር ክኑት ክሮይች እና የውርሰ ኢትዮጵያ ድርጅት የቦርዱ ሊቀመንበር ልጅ ዶ/ር አስፋ ወሰን አሥራተ ሁለቱም አንድ ላይ ሁነው እየተፈራረቁ ተራ በተራ በአደረጉት ረጅም ንግግራቸው ነው።

ወደፊት እንዲታሰብበትም ስለ የእህት ከተማዎች ጉዳይም እዚያው አብሮ ተያይዞ በልጅ ዶ/ር አስፋ ወሰን አሥራተ ይህ ሐሳብ ለከንቲባው ቀርቦ ቤቱ ውስጥ ጉዳዩ ተሰምቶአል። ጎንደርና ጎታ እህትማማቾች ቢሆኑ ከጊዜውና ከታሪኩም ጋር አብሮ ስለሚሄድ  መልካም ነው ተብሎአል።

ተራ በተራ ከዚያ በሁዋላ፣ አንድ በአንድ – ተናጋሪ ምሁራኖቹ አትራኖሱንና መድረኩን፣ዘመናዊ መግለጫ ቢመሩንም እየተቀባበሉ፣ለረጅም አመታት ብቻቸውን ተቀምጠው ከአካሄዱት ጥናቶችና ምርምሮች ለእኛ – መገመት እንደሚቻለው- ሁሉንም ሳይሆን „ቀንጥበው!“ በትንሹም ከዚያ ላይ „ቦጭቀው“ ማለት እንችላልን“…ስለ አጼ ምኒልክ ገድልና ሥራ፣ ትልቅነትም ሦስት ቀን በፈጀው ስብሰባ ላይ ምሁሮቹ ለተሳታፊ እንግዶቹ ፣ በጭብጭባ እየታጀቡ -ከደረሱበት ጥናቶቻቸው ጋር እኛን አስተዋዉቀዋል።

ረፈድ ሲል በስብሰባው ላይ ለመገኘት ያልቻሉት የታሪክ ጸሓፊውና የምሁሩ የፕሮፌሰር ባይሩ ተላ አጭር ጥናት ቤቱ ውስጥ ተነቦአል።

ጳውሎስ ኞኞን ጋዜጠኛውን እያመሰገኑ (ከላኩት ደብዳቤ ላይ እንደተሰማው) የአሜሪካኑን ጸሓፊ ሚስተር ቡርጋርድን እየጠቀሱ „…እንደ ምኒልክ በደጋፊዎቻቸው የሚደነቁ የዚያኑ ያህል ደግሞ በተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ የሚናቁና -አሜሪካኑ እንደ አለው- እንደ እሳቸው የሚከሰሱ መሪ የለም „ ብሎ ያስቀመጠውን አመለካከት በላኩት ደብዳቤ ላይ ይህን ቃል አስቀምጠው ወደ ተነሱበት አርዕስት ፕሮፌሰር ባይሩ ዘልቀወል።

ቀደም ሲል ሌላው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴም -በአቀረቡት ጥናት ላይ ተመሣሣይ ነገር በኢትዮጵያ እንደተመለከቱ እሳቸውም ወርወር  አድረገው ለመናገር በተነሱበት አርዕስት ላይ ወደፊት በተራቸው ገፍተዋል።

„አባቶቻችን በጋራ አንድ ላይ ተነስተው አደዋ ላይ ጣሊያንን ድል ያደረጉበትንና ያሸነፉበትን መቶኛ አመት አንድ ላይ በጋራ ለማክበር እንኳንመግባባት ከአንዳንዶቹ ጋር እንደ አልተቻለም“  ምሁሩ አስታውሰው „…ምኒልክ ኮትኩተው እኚህ ንጉሥ አሳድገው ወደ ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ ስለአደረሱአቸው፣ የዝቅተኛው መደብ ልጆች „ ፕሮፌሰር ባህሩ በአቀረቡት ጥናት ስለእነሱ በተለይ ስለ ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የጦር ሚኒስትሩ ማተቱን መርጠዋል።

እግረ መንገዳቸውንም ከብዙ በጥቂቱ ስለ ራስ ጎበናም ምሁሩ ጠቅሰዋል። ሁለቱም በኢትዮጵያ ታሪክና በዘመናዊ ኢትዮጵያ አስተዳደር ምሥረታ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ይህን ማን የሚያውቀው ነው።

ፊታውራር ሐብተ ጊዮርጊስ ግን በሥልጣን ሽግግሩ ዘመን ከምኒልክ ወደ ልጅ ኢያሱ፣ ከእያሱ ወደ ዘውዲቱና ወደ አጼ ኃይለሥላሴ በሰገሌም ጦርነት ጊዜ እኝህ ሰው የተጫወቱት ሚና በፕሮፌሰሩ ጥሩ ሁኖ ቀርቦአል። መለስ ብለውም „እንደዚህ ዓይነቱ አሠራር – ብልህንና አስተዋይን ሰው ማቅረብ፣ነገር የገባውንና ነገርን የሚመለከት ሰው መርጦ ወስዶ ኮትኩቶ ለከፍተኛ ኃላፊነትና ማዕርግ ማድረስ …በድሮም የኢትዮጵያ ነገሥታቶች ዘንድ ያለ የቆየ ባህል ነው።“ ብለዋል።

ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አደርገው ያቆዩትም እሴቶች እንደዚህ ዓይነት ተመክሮዎች ናቸው።

ስለ ምኒልክ ትልቅነትና ስለ ምኒልክ ግሩም የረቀቀ የፖለቲካ ጥበብ ፣ስለ አመራር ብልሃታቸውና ሚዛናዊ ፍርዳቸው፣ስለ አመለካከት ስልታቸውና ስለ የፖለቲካ እርምጃቸው፣ የተጠነቀቀምረጋ ያለ አካሄዳቸው -መቼም ይህ ነው የማይባል ንግግር ያደረጉት የጀርመኑ የፖለቲካ ሳይንስ አስተማሪ ፕሮፌሰር ራይነር ቴትዝላፍ የሚባሉ ሰው ናቸው።

„ከፓን አፍሪካኒዝም ማለት ከመላው የጥቁሮች ራዕያና ነጻ ዓለም ኑሮና ሕይወት ጋር አያይዘው“ ሁሉንም ተናጋሪ ቀድመው በጥወቱ ሰዓት ላይ ደህና አድርገው በአቀረቡት ሁፋቸው ላይ የምኒልክን ጉዞ መምህሩ አስቀምጠዋል።

 

„…ምኒልክ ለጥቁር አፍሪካ ምሁሮች ለነዚያ በቅኝ ገዢዎች የበላይነት መከራቸውን ያዩ፣ የተጨቆኑ ጥቁር ሕዝቦች፣ እነሱ ምሁሮቹ አንድ ቀን ተነስተን እናመጣለን ብለው የሚመኙትን ሓሳብ በድርጊትና በተግባር ንጉሡ በሥራ ላይ አውለው በማየታቸው እጅግ አድርገው ሁሉም በምኒልክ ሥራ ተደንቀዋል። እንዲያውም እንግሊዝ አገር በሺህ ዘጠኝ መቶ አመተ ምህረት መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የመጀመሪያው የጥቁር ዘሮች የፓን አፍሪካ ኮንግሬስ ላይም የበላይ ጠባቂ መሪና የስብሰባው ሊቀመንበር አጤ ምኒልክን እንዲሆኑላቸው ጠይቀውም ነበር።  ንጉሡ ግን“ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት „ሌላ ጋላፊነትና ሌላም የመንግሥት ሥራ ስለነበራቸው በስብሰባው ላይ ተገኝተው የፓን አፍሪካን ጥቁሮች ጥያቄ ሊያሟሉ አልቻሉም።“

ምኒልክና ጥንታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለተበደሉትና በጭቆና ሥር ለሚማቅቁት የዓለም  ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ አስተዋጾ እንደ አደረጉ ዘርዝረዋል። „ኢትዮጵያን ገንብተው፣አንድ አድርገው፣አመቻችተው ለቀጣዩ ትውልድ አሳልፈው እንደሄዱም …“ አትተዋል።

„ምኒልክ ግን ብቻውን ሳይሆን ከሌሎቹ የአገሪቱ መሣፍንትና መኳንንቶች፣ ካህናትና የሃይማኖት አባቶች፣ ከዝቅተኛው ክፍል ከመጡ ከእነ ራስ ጎበናና ከእነ ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ፣ ከውጭ አማካሪዎቻቸውም ጋር ከእነ አልፍሬድ ኢልግ -አንዳዶቹን ለመጥቀስ እየተማካከሩ ኢትዮጵያን በጋራ ከሁሉም ጋር እንደገነቡና ወድቆ የነበረውን የኢትጵያዊነት መንፈስንም እንደገና እንዳደሱ፣ አድሰውም በዓለም ላይ ተገቢውን ቦታ እንዲይዝም እንዳደረጉ“…የተቀሩት ጠቁመዋል።

„ምኒልክን ምኒልክ እንዲሆን“ ባህሪውንም አመለካከቱንም ረጋ ያለ የፖለቲካ አካሄዱንም ጠርቦ ሞርዶ አስተካክሎ እዚያ ያደረሰውን ነገር „ከሞላ ጎደል „ ለማስረዳት መድረኩን የተረከቡት ዶ/ር አህመድ ሐሰን ናቸው።

አራት ጣቢያዎችን ጠቅሰውልናል።

አንደኛው በልጅነት ዕድሜአቸው በጠምቄ ገዳም ያሳለፉት ጊዜና ከአስተማሪያቸው ከአባ ሸዋ ዘርፍ ያገኙት ተመክሮና ትምህርት ነው።

ሁለተኛው ተማርከው በአጼ ቴዎድሮስ ችሎት እዚያ ላይ ያሳለፉት ጊዜና የቁም እሥር ዘመን ነው።

ሦስተኛው አብሮአቸው ታሥረው የነበሩት የሸዋ መሣፍንቶችና መኳንንቶች „ምክር ነው።“

የመጨረሻው ትምህርት መቅደላ ላይ የተዋወቁአቸው የአውሮፓ „ምሁሮች“ ናቸው።

ምኒልክ በእነዚህና በሌሎች ተመክሮች የኢትዮጵያ ነጻነት ጠብቆና አስከብሮ ለቀጣዩ ትውልድ አስተላልፎ ሄዶአል። „ተማረ፣አወቀ፣ነገር ገብቶታል“ የተባለው ትውልድ ደግሞ እንደምናውቀው „…በተለያዩ ፍልስፍናዎችና የአምባገነን ፖለቲካ አይዶኦሎጂዎች“ አብዶ፣ ቀላሉን …የሰበአዊና የዲሞክራሲዊ መብቶች መከበርን እንኳን፣ የነጻ-ሕብረተሰብን መመሥረትን፣ የግል ሐብትን፣ ነጻ ስብሰባና ነጻ ፕሬስን ሲቃወም  ይህን በ21 ኛው ክፍለ ዘመን በአዲስ አበባና በአሥመራ ማየቱና መሰማቱ ምንድነው።

በምኒልክ ላይ የትችት ናዳቸውን የሚወረውሩ ከአሉ፣ እራሳቸው በመጀመሪያ ኢትዮጵያን ከሚበትነው ከአምባገነን ከቴታሊቴሪያን አስተሳሰብ ማለቀቅ ይኖርባቸዋል።

 እንደዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ግን – ንጉሣዊ አገዛዝንቀደሲል ፣ፈሺዝምን፣ ከእሱም ጋር ፍልስፍናው የተወለደውም እዚህ ነው- ኮምንዝምንበደንብ በያውቀው በጀርመኑ አገር  ስብሰባ ላይ እንደዚህ ዓይነቱ ትችት አልተሰማም።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

 

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s