ከኔልሰን ማንዴላ፥
ዲሞክራቱ
ከዴሞክራቱ ጋር
መቼም ስለዚህ ሰው በአለፉት ሁለትና ሦስት፣…አራትና አምስት ቀናት፣ ሌላው ቀርቶ በአንድ ቀን ብቻ በዓለም ዙሪያ ታትመው የወጡትን ዕለታዊ ጋዜጣዎች እነሱን ብቻ አንድ ሰው ጠርዞ ቢያወጣው ረጅምና ብዙ ገጽ የያዘ ጥሩ መጽሓፍ ሊወጣው ይችላል።
ይህ ከሆነ ለምን አሁን እንደገና ስለ ኔልሰን ማንዴላ?
የተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች አንዲት ጋዜጠኛ ተገርማ ከዚያ ሁና እንደዘገበቺው ስብሰባቸውን አቁመው – ይህ የትም አልታየም የትም አልተደረገም እሱዋም እንደዚህ ዓይነቱ ክብር የትም አልተሰማም ትላለች- የሕሊና ጸሎት መሞታቸው እንደተሰማ እነሱ ብድግ ብለው አድርገዋል።
ከቶኪዮ እስከ ኦስሎ፣ከብራዚል እስከ ቻይና ከሎንዶን እስከ ሞስኮ፣ ከዋሽንግተን እስከ ሓቫና …አፍሪካማ አንዲት ቅንጣት ታህል የማንዴላን ሓሳብና መንፈስ የማይከተሉ መሪዎች እነሱም ቢሆኑ – ብድግ ብለው አጠቃላይ የሆነውን መግለጫቸውን፣ ከእነ ባራክ ኦባማ ጋር ተጋርተው ሁሉም ሰጥተዋል።
የሚገርመው ትላልቅ የዓለም የዜና አውታሮችና የቴሌቪዢን ጣቢያዎች ሁሉም ለሰውዬው ዕረፍት ትልቅ ቦታ ስጥተው ቀኑን በመሉ ለኔልሰን ማንዴላ ታሪክና ሥራ ላይ ተመላልሰውበታል።
ምንድነው ነገሩ? ማንዴላን ከሌሎቹ ከምናውቃቸው ከእነ ሮበርት ሙጋቤ እና ከእነ አልባሽር፣ ከእነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እና ከእነ መለሰ ዜናዊ፣ ከእነእሳያስና ከእነሙባራክ፣ ከእነ ጋዳፊና ከእነ ቤን ዓሊ…ከካውንዳና ከነኡሁሩ ኬንያታ ከእነ ፖል ካጋሜና ከነካቢላ …ከፖልፖትና ከማኦ… መዘርዘሩ ይሰለቻል እሱን የሚለየው?
ምንድነው እሱን ማንዴላን ፍጹም ልዩ የሚያደርገው? ልዩ አድርጎትስ „ዓለም“ ስለ እሱ እንደዚህ የሚያወራው? የቻይምፕዮንስ ሊግ የኳስ ሜዳ ጨዋታ ላይም ሳይቀር ፎቶግራፉ ሰሞኑን ታይቶአል። ምክንይቱ ምንድነው?
ሰማይና ምድር ናቸው፣ ማንዴላ ሌላ ሰው፣ እነሱ የተቀሩት የአፍሪካ መሪዎች ሌላ። ለምንድነው ሁለቱን ፍጡሮችን የምታወዳድረው ? የምትሉ አላችሁ።
“የለም …ማንዴላ እኮ የእነሱ ሰው ስለሆነ የእነሱ በመሆኑ ነው…“ የምትሉም ሰዎች አትጠፉም።
የፈለገ ሰው ብዙ ነገር ሊጽፍ ይችላል። ብዙም በቃላት የተዋበ አስተያየቱን ስለ ማንዴላ – በሥልጣን ዘመኑ የእራሱን ሕዝብ የፈጀውም የበደለውም ሰው ሁሉ ሳይቀር ስም መጥቀስ ይቻላል- የሚሰጥበት ሰዓት ሁኖአል። የት ነበሩ አነሱ ማንዴላ በገዛ ፈቃዱ ጀሥልጣኑ ሲውርድ? ዲሞክራሲን ሲያውጅ? የት ነበሩ እሱ የበደሉትን ይቅር ሲል?
እኛ ደግሞ በሦስት የሰው ልጆች በዚህች ዓለም ላይ ለመኖርና ለአለመኖር በሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ የተመሰረተ ሥራ በማካሄዱ ብቻ – አዚህ ሥራው ደግሞ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንደገኘ አስምረን ለማለፍ እንፈልጋልን።
እነሱም:- አንደኛ ማንዴላ በመሓላ ቃሉ ሥልጣኑን እንደተረከበ በቂም በቀል ፋንታ ይቅር ለእግዚአብሔርን፣ በጥላቻ ፋንታ ፍቅርን፣ የቀድሞ ጠላቶቹን፣ የእሥር ቤት ጠባቂ ፖሊሶቹን ሳይቀር (አሳዶእንደማንኛውም በመግደል፣ ሊያስገድላቸውም ይችላል)በዚያ ፋንታ ጋብዞ ማነጋገርንና አብሮ መብላትን ይህ ሰው መርጦአል።
ሁለተኛው ይህ ሰው „አሸንፍኩ እኛ አሸንፈናል!“ ብሎ አገሪቱን በጥቁርና በነጭ፣በክልስና በሕንድ፣በአረብና በተለያዩ ዘሮች፣ በጎሣና በሃይማኖት፣ ከፋፍሎና ሰንጥቆ ደቡብ አፍሪካን እሱና ድርጅቱ፣እነሱ ብቻ በጠበንጃ አፈ ሙዝ ጸጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት አልተነሳም።
ይልቅስ ይህ ሰው ቀስተ ደመና በሚባለው አዲሱ ፍስፍናቸው ሁሉንም ድልድይ ሁኖ አቀራርቦ ሁሉንም ሰብስቦ እኩል የዜጋ መብቱን ለሁሉም እኩል ሰጥቶ አንድ አድረጎአቸዋል።
ሦሰተኛው:- እንደዚሁ አፍሪካ አይታም ሰምታም የማታውቀውን ነገር ይህ ሰው አድረጎ ዓለምን አሰደንቆአል። አለ ጠበንጃ ወይም አለተቃውሞ፣ አለ አመጽ በገዛ ፈቃዱ ማንም ከሥልጣኑ በአፍሪካ በማይወርድበት ዘመን ኔልሰን ማንዴላ በገዛ ፈቃዱ- ዕድሜ ልኩን እሰከ የሞት ቀኑ ድረስ ደቡብ አፍሪካን ሊገዛ ይችል ነበር- ከሥልጣኑ ወርዶአል።
እንግዲህ ይህ ሥራው ነው ሕያው አድረጎት በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ለዘለዓለም የሚያቆየው።
ትንሽ ከእሱ ሥራዎች ውስጥ አንዱዋን ጫፍ ብቻ የአፍሪካ መሪዎች፣ተቃዋሚ ፖለቲከኞች… ጎትተው አውጥተው እሱዋን በሥራ ቢተረጉሙ የትና የት ይህችአ ህጉር በደረሰች ነበር።
ይህን እንደማድረግ ማንዴላ እንደዚህ ማንዴላ የእኛ ነው ብለው ሲመጻደቁ እነሱን መስማቱ ጆሮንም ይቀፋል።
ለመሆኑ ያኔ የት ነበርክ አንተም ሥልጣን ላይ የነበርክ ጊዜም የማንዴላን ዓይነት ሥራና አስተሳሰብ ለመከተል ምን አገደህ? ምንስ እጅህን ያዘህ? ምንስ ታደርግ ነበር ያሰኛል።
ዛሬስ አሁንስ በዚህች ሰዓት አመለካከትህን ለመቀየር አሰራርህን ለመለወጥ ማን ከለከለህ ማንስ አገደህም ያሰኛል።
ማንዴላ ተሰናብቶአል። ትቶት የሄደው ሥራ ሕያው ነው። አስተሳሰቡም ድንቅ ነው። እንደዚህ ዓይነቱን የጥላቻ ሳይሆን የፍቅር አስተሳሰቡን ከየት አመጣው? ለመሆኑ ማን አስተማረው? ዕውነት ዲሞክራት ለመሆን መንገዱ ከባድ ነው? አይመስለንም።