Monthly Archives: December 2013

እምዬ እንደገና

እምዬ እንደገና

menelik-horse

ም ኒ ል ክ

 

በብረት ቅርጫት ቀፎ የሮም ጎዳና ላይ ያንን የኢትዮጵያ ንጉሥ ነኝ የሚለውን ሰው ይዤ እየጎተትኩ -ጥንታዊት ሮም በዚህ የታወቀች ናት- አመጥቼ አሳይችሁዋላሁ…” ብሎ የፎከረው ጄኔራል አደዋ ላይ ተቀጥቶ ወታደሩን በትኖ ሸሽቶ ነፍሱን ለማዳን አሥመራ ይህ ሰው  ገብቶአል። የአደዋን ጦርነት ለሚያውቁ ሰዎች ይህ አዲስ ታሪክ አይደለም።

አዲሱ ታሪክ አዲስ መሆን ያለበት እንዴት አድረገው ኢትዮጵያኖች ተስማምተው በጋራ አንድላይ መላ-መተው የጣሊያንን ጦር አታለው ከምሽጉ አስወጥተው አውላላ ሜዳ ላይ ደበደቡት የሚለው ብልሃት ነው። ለዚህም ነው የአደዋ ጦርነት በትክክል መቼ እና በስንት  ሰዓት ተጀመረ፣ ንጉሠነገሥቱስ በዚያን ሰዓት የት ነበሩ የሚለውን  ነገር በደንብ ለማስፈር አስቸጋሪ የሆነው። ሰሚንም ነገሩ ግራ የሚያጋባው በዚህ ምክንያት ነው ።

እሱንም ሁኔታ ወረድ ብላችሁ ትመለከቱታላችሁ።

ጣሊያኖች ሳይሆኑ በሁዋላ የተወለዱትና በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ ወጣት „ኢትዮጵያኖች“ የምኒልክን ሓውልት ከራስ መኮንን ጋር እናፍርስ ብለው ተነስተው እንደ  ነበር አይረሳም።ይህም ነገር ሳይሳካላቸው፣ እንደምናውቀው ቀርቶአል። ይህንንም በምኒልክ ላይ የተጀመረውን ዘመቻ(መቼ አቆመ) ከብዙ በጥቂቱ ትንሽ ቆይታችሁ ዘለቅ ስትሉ ትደርሱበታላችሁ።

ምኒልክ እንግሊዝ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ በ1900 ዓመተ-ምህረት መጀመሪያ ላይ የተካሄደውን የፓን አፍሪካ ጉባዔን በበላይ ጠባቂና በሊቀመንበርነት እንዲመሩመጠየቃቸውን ዘግየት ብላችሁ እሱንም ዜና  ታገኙታላችሁ።

የምኒልክን መቶኛውን የሙት አመት ስናስታው ስለዚህ ንጉሥ ታሪካዊ ቦታውን ለመስጠትና ሙታንን የማስታወስ ባህል በአገራችንም እንደገና ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ-በማሰብነው።

 

በእርግጥ „የሰማዕታት ቀን“ የሚባል በዓል ነበረን። ግን ስንቶቻችን ነን የሞቱትን ዘመዶቻችንን አፈር ከለበሱ ወዲህ ዞር ብለን የምናስታውሰው?

ስለምኒልክ ዛሬ ስናነሳ “…ቅባቅ ዱሱን የተቀባ አንድ ንጉሥ ብድግ ብሎ አሁን ከገባንበት ጣጣ መጣጣ እሱ መጥቶ ያወጣናልለማለት አይደለም።

እሱማ! እንኳን እሱና በአንድ በዞረበት ያልታወቀ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችም ለብቻቸው በ21ኛው ክፍለ ዘመን „ዕድሜ ልካቸውን የሚገዙበት“ የብልጣ ብልጥነት የአታላዮች የአምባገነን ሥርዓት  የማይሆን የማይደረግ ነገር እንደሆነ ሁላችንም ገብቶናል። የጠፋው ዕወቀትና ብልሃት -እንዴት? የሚለው ላይ ነው።

ምኒልክ  „አገሬንና ሕዝቤን ለነጮች አሳልፌ ለባርነት አልሰጥም“ ያለ የዘመኑ ጀግና ሰው ነበር። ከአሁኑ ዘመን ከእኛ ትውልድ ደግሞ የሚጠበቀው ሌላ ነገር ሳይሆን እንደዚህ ዓይነቱን አመለካከትና  የዲሞክራሲ መብቶችን ከዚሁ ጋር አብሮ የማስጠበቅ ቆራጥነት ነው።

በአጭሩ እሱም ከአገር ነጻነት ጋር እኩል አብሮ የሚሄድ የግለስብ ነጻነትና የግለሰብ መብቶች መከበር ከሁሉም ነገር በፊት ይህን ጉዳይ በሥራ ላይ ማዋል ነው።

እሱ ደግሞ ምን እንደሆነ በትክክል ያሳየው “…ዲሞክራሲ እኮ ! በአፍሪካ አይሰራም… ” የሚሉትን ሰዎች አፋቸውን አንዴ ያስያዘው የአፍሪካው ልጅ የማንዴላ ሥራና ገድል ነው።

እንግዲህ ስለማንዴላም አለፍ ስትሉ እዚሁ ቅጠሉ ላይ ታገኛላችሁ።

 

ለጊዜው መልካም ቀን

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

ምኒልክ – በጎታ / Gotha

ምኒልክ- በጎታ

menelikatgotha

እንደ ዳግማዊ ምኒልክ በዓለም የተደነቀ እንደ እሳቸው ደግሞ በአንዳንድ የአገሪቱ ልጆች ዘንድ የተናቀ የአፍሪካ ንጉሥ የለም።

ደፍረው -ይህ ይገርማል- ሐውልታቸው እንዲፈርስ አዲስ አበባ ላይ አንዳንዶቹ ጠይቀዋል። ብዙዎቹም ይህ የመታሰቢያ ሐውልቱ እንዳይነካ ታግለዋል። ለምልክትም ቀለም ጥቂቶቹ ቀብተዋል።

በጀርመን አገር ጎታ በሚባለው ከተማ የመቶኛ የሙት አመታቸውን ምክንያት በማድረግና እሱንም በማስታወስ አሥራ ስድስተኛ „የውርሰ ኢትዮጵያ የሳይንስና የምርምር ጥናት ማህበር“ አመታዊ ጉባዔውን እዚያ አካሂዶ በንጉሠ ነገሥቱ በአጼ ምኒልክ ሥራና ገድላቸው ላይ ሦስት ቀን የፈጀ አተኩሮ ለእሳቸው ሰብሰባው ሰጥቶአል።

ጎታ ታሪካዊ ከተማ ናት።

እዚህ ነው የጀርመኑ የሲሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የመጀመሪያውን የድርጅቱን ፕሮግራም ነድፎ ለጀርመን ሕዝብ ያስተዋወቀው።

እዚህ ነው ከአምስት መቶ አመት በፊት እነ ዶክትር ማርቲን ሉተር የፕሮቴስታንትን ሃይማኖት እንቅስቃሴ በዘመናቸው ለኩሰው ይህን እምነት ሊያስፋፉ፣ሊያራምዱት የቻሉት።

እዚሁ ነው ከሦስት መቶ ሃምሣ አመት በፊት ኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ እና የጀርመኑ ተወላጅ ሒዮብ ሉዶልፍ በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደገና የተገናኙት።

እንግዲህ እዚሁ  የቤተ-መንግሥቱ አንደኛውና ትልቁ አዳራሽ- የመስተዋትአዳራሽ ውስጥ-  ነው ከጥቅምት 11 እሰከ ጥቅምት 13 2013 ዓ.ም (እአአ) „ውርሰ ኢትዮጵያ“ የተባለው ድርጅት አሥራ ስድስተኛውን አመታዊ ጉባዔውን ጠርቶ፣ንጉሠ ነገሥቱን አጼ ምኒልክን ከሞቱ ከአንድ መቶ አመት በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የእኝህን ትልቅ ሰው ሥራና ገድል ያስታወሰው።

ጉባዔውን የከፈቱት የከተማው ከንቲባ ሚስተር ክኑት ክሮይች እና የውርሰ ኢትዮጵያ ድርጅት የቦርዱ ሊቀመንበር ልጅ ዶ/ር አስፋ ወሰን አሥራተ ሁለቱም አንድ ላይ ሁነው እየተፈራረቁ ተራ በተራ በአደረጉት ረጅም ንግግራቸው ነው።

ወደፊት እንዲታሰብበትም ስለ የእህት ከተማዎች ጉዳይም እዚያው አብሮ ተያይዞ በልጅ ዶ/ር አስፋ ወሰን አሥራተ ይህ ሐሳብ ለከንቲባው ቀርቦ ቤቱ ውስጥ ጉዳዩ ተሰምቶአል። ጎንደርና ጎታ እህትማማቾች ቢሆኑ ከጊዜውና ከታሪኩም ጋር አብሮ ስለሚሄድ  መልካም ነው ተብሎአል።

ተራ በተራ ከዚያ በሁዋላ፣ አንድ በአንድ – ተናጋሪ ምሁራኖቹ አትራኖሱንና መድረኩን፣ዘመናዊ መግለጫ ቢመሩንም እየተቀባበሉ፣ለረጅም አመታት ብቻቸውን ተቀምጠው ከአካሄዱት ጥናቶችና ምርምሮች ለእኛ – መገመት እንደሚቻለው- ሁሉንም ሳይሆን „ቀንጥበው!“ በትንሹም ከዚያ ላይ „ቦጭቀው“ ማለት እንችላልን“…ስለ አጼ ምኒልክ ገድልና ሥራ፣ ትልቅነትም ሦስት ቀን በፈጀው ስብሰባ ላይ ምሁሮቹ ለተሳታፊ እንግዶቹ ፣ በጭብጭባ እየታጀቡ -ከደረሱበት ጥናቶቻቸው ጋር እኛን አስተዋዉቀዋል።

ረፈድ ሲል በስብሰባው ላይ ለመገኘት ያልቻሉት የታሪክ ጸሓፊውና የምሁሩ የፕሮፌሰር ባይሩ ተላ አጭር ጥናት ቤቱ ውስጥ ተነቦአል።

ጳውሎስ ኞኞን ጋዜጠኛውን እያመሰገኑ (ከላኩት ደብዳቤ ላይ እንደተሰማው) የአሜሪካኑን ጸሓፊ ሚስተር ቡርጋርድን እየጠቀሱ „…እንደ ምኒልክ በደጋፊዎቻቸው የሚደነቁ የዚያኑ ያህል ደግሞ በተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ የሚናቁና -አሜሪካኑ እንደ አለው- እንደ እሳቸው የሚከሰሱ መሪ የለም „ ብሎ ያስቀመጠውን አመለካከት በላኩት ደብዳቤ ላይ ይህን ቃል አስቀምጠው ወደ ተነሱበት አርዕስት ፕሮፌሰር ባይሩ ዘልቀወል።

ቀደም ሲል ሌላው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴም -በአቀረቡት ጥናት ላይ ተመሣሣይ ነገር በኢትዮጵያ እንደተመለከቱ እሳቸውም ወርወር  አድረገው ለመናገር በተነሱበት አርዕስት ላይ ወደፊት በተራቸው ገፍተዋል።

„አባቶቻችን በጋራ አንድ ላይ ተነስተው አደዋ ላይ ጣሊያንን ድል ያደረጉበትንና ያሸነፉበትን መቶኛ አመት አንድ ላይ በጋራ ለማክበር እንኳንመግባባት ከአንዳንዶቹ ጋር እንደ አልተቻለም“  ምሁሩ አስታውሰው „…ምኒልክ ኮትኩተው እኚህ ንጉሥ አሳድገው ወደ ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ ስለአደረሱአቸው፣ የዝቅተኛው መደብ ልጆች „ ፕሮፌሰር ባህሩ በአቀረቡት ጥናት ስለእነሱ በተለይ ስለ ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የጦር ሚኒስትሩ ማተቱን መርጠዋል።

እግረ መንገዳቸውንም ከብዙ በጥቂቱ ስለ ራስ ጎበናም ምሁሩ ጠቅሰዋል። ሁለቱም በኢትዮጵያ ታሪክና በዘመናዊ ኢትዮጵያ አስተዳደር ምሥረታ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ይህን ማን የሚያውቀው ነው።

ፊታውራር ሐብተ ጊዮርጊስ ግን በሥልጣን ሽግግሩ ዘመን ከምኒልክ ወደ ልጅ ኢያሱ፣ ከእያሱ ወደ ዘውዲቱና ወደ አጼ ኃይለሥላሴ በሰገሌም ጦርነት ጊዜ እኝህ ሰው የተጫወቱት ሚና በፕሮፌሰሩ ጥሩ ሁኖ ቀርቦአል። መለስ ብለውም „እንደዚህ ዓይነቱ አሠራር – ብልህንና አስተዋይን ሰው ማቅረብ፣ነገር የገባውንና ነገርን የሚመለከት ሰው መርጦ ወስዶ ኮትኩቶ ለከፍተኛ ኃላፊነትና ማዕርግ ማድረስ …በድሮም የኢትዮጵያ ነገሥታቶች ዘንድ ያለ የቆየ ባህል ነው።“ ብለዋል።

ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አደርገው ያቆዩትም እሴቶች እንደዚህ ዓይነት ተመክሮዎች ናቸው።

ስለ ምኒልክ ትልቅነትና ስለ ምኒልክ ግሩም የረቀቀ የፖለቲካ ጥበብ ፣ስለ አመራር ብልሃታቸውና ሚዛናዊ ፍርዳቸው፣ስለ አመለካከት ስልታቸውና ስለ የፖለቲካ እርምጃቸው፣ የተጠነቀቀምረጋ ያለ አካሄዳቸው -መቼም ይህ ነው የማይባል ንግግር ያደረጉት የጀርመኑ የፖለቲካ ሳይንስ አስተማሪ ፕሮፌሰር ራይነር ቴትዝላፍ የሚባሉ ሰው ናቸው።

„ከፓን አፍሪካኒዝም ማለት ከመላው የጥቁሮች ራዕያና ነጻ ዓለም ኑሮና ሕይወት ጋር አያይዘው“ ሁሉንም ተናጋሪ ቀድመው በጥወቱ ሰዓት ላይ ደህና አድርገው በአቀረቡት ሁፋቸው ላይ የምኒልክን ጉዞ መምህሩ አስቀምጠዋል።

 

„…ምኒልክ ለጥቁር አፍሪካ ምሁሮች ለነዚያ በቅኝ ገዢዎች የበላይነት መከራቸውን ያዩ፣ የተጨቆኑ ጥቁር ሕዝቦች፣ እነሱ ምሁሮቹ አንድ ቀን ተነስተን እናመጣለን ብለው የሚመኙትን ሓሳብ በድርጊትና በተግባር ንጉሡ በሥራ ላይ አውለው በማየታቸው እጅግ አድርገው ሁሉም በምኒልክ ሥራ ተደንቀዋል። እንዲያውም እንግሊዝ አገር በሺህ ዘጠኝ መቶ አመተ ምህረት መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የመጀመሪያው የጥቁር ዘሮች የፓን አፍሪካ ኮንግሬስ ላይም የበላይ ጠባቂ መሪና የስብሰባው ሊቀመንበር አጤ ምኒልክን እንዲሆኑላቸው ጠይቀውም ነበር።  ንጉሡ ግን“ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት „ሌላ ጋላፊነትና ሌላም የመንግሥት ሥራ ስለነበራቸው በስብሰባው ላይ ተገኝተው የፓን አፍሪካን ጥቁሮች ጥያቄ ሊያሟሉ አልቻሉም።“

ምኒልክና ጥንታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለተበደሉትና በጭቆና ሥር ለሚማቅቁት የዓለም  ጥቁር ሕዝቦች ትልቅ አስተዋጾ እንደ አደረጉ ዘርዝረዋል። „ኢትዮጵያን ገንብተው፣አንድ አድርገው፣አመቻችተው ለቀጣዩ ትውልድ አሳልፈው እንደሄዱም …“ አትተዋል።

„ምኒልክ ግን ብቻውን ሳይሆን ከሌሎቹ የአገሪቱ መሣፍንትና መኳንንቶች፣ ካህናትና የሃይማኖት አባቶች፣ ከዝቅተኛው ክፍል ከመጡ ከእነ ራስ ጎበናና ከእነ ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ፣ ከውጭ አማካሪዎቻቸውም ጋር ከእነ አልፍሬድ ኢልግ -አንዳዶቹን ለመጥቀስ እየተማካከሩ ኢትዮጵያን በጋራ ከሁሉም ጋር እንደገነቡና ወድቆ የነበረውን የኢትጵያዊነት መንፈስንም እንደገና እንዳደሱ፣ አድሰውም በዓለም ላይ ተገቢውን ቦታ እንዲይዝም እንዳደረጉ“…የተቀሩት ጠቁመዋል።

„ምኒልክን ምኒልክ እንዲሆን“ ባህሪውንም አመለካከቱንም ረጋ ያለ የፖለቲካ አካሄዱንም ጠርቦ ሞርዶ አስተካክሎ እዚያ ያደረሰውን ነገር „ከሞላ ጎደል „ ለማስረዳት መድረኩን የተረከቡት ዶ/ር አህመድ ሐሰን ናቸው።

አራት ጣቢያዎችን ጠቅሰውልናል።

አንደኛው በልጅነት ዕድሜአቸው በጠምቄ ገዳም ያሳለፉት ጊዜና ከአስተማሪያቸው ከአባ ሸዋ ዘርፍ ያገኙት ተመክሮና ትምህርት ነው።

ሁለተኛው ተማርከው በአጼ ቴዎድሮስ ችሎት እዚያ ላይ ያሳለፉት ጊዜና የቁም እሥር ዘመን ነው።

ሦስተኛው አብሮአቸው ታሥረው የነበሩት የሸዋ መሣፍንቶችና መኳንንቶች „ምክር ነው።“

የመጨረሻው ትምህርት መቅደላ ላይ የተዋወቁአቸው የአውሮፓ „ምሁሮች“ ናቸው።

ምኒልክ በእነዚህና በሌሎች ተመክሮች የኢትዮጵያ ነጻነት ጠብቆና አስከብሮ ለቀጣዩ ትውልድ አስተላልፎ ሄዶአል። „ተማረ፣አወቀ፣ነገር ገብቶታል“ የተባለው ትውልድ ደግሞ እንደምናውቀው „…በተለያዩ ፍልስፍናዎችና የአምባገነን ፖለቲካ አይዶኦሎጂዎች“ አብዶ፣ ቀላሉን …የሰበአዊና የዲሞክራሲዊ መብቶች መከበርን እንኳን፣ የነጻ-ሕብረተሰብን መመሥረትን፣ የግል ሐብትን፣ ነጻ ስብሰባና ነጻ ፕሬስን ሲቃወም  ይህን በ21 ኛው ክፍለ ዘመን በአዲስ አበባና በአሥመራ ማየቱና መሰማቱ ምንድነው።

በምኒልክ ላይ የትችት ናዳቸውን የሚወረውሩ ከአሉ፣ እራሳቸው በመጀመሪያ ኢትዮጵያን ከሚበትነው ከአምባገነን ከቴታሊቴሪያን አስተሳሰብ ማለቀቅ ይኖርባቸዋል።

 እንደዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ግን – ንጉሣዊ አገዛዝንቀደሲል ፣ፈሺዝምን፣ ከእሱም ጋር ፍልስፍናው የተወለደውም እዚህ ነው- ኮምንዝምንበደንብ በያውቀው በጀርመኑ አገር  ስብሰባ ላይ እንደዚህ ዓይነቱ ትችት አልተሰማም።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

 

ዳግማዊ ምኒልክ (ርዕስ አንቀጽ)

ዳግማዊ ምኒልክ (ርዕስ አንቀጽ)

ዳግማዊ ምኒልክ

ዳግማዊ ምኒልክ

 

እኛ ኢትዮጵያኖች ሙታንን በማስታወስ „ዘለዓለማዊ“ ማድረግ ቀርቶ የሰባት አመቱ  -ጥቂቱ ይህን ቀን ይጠብቃል- ተዝካር ሳይወጣ እንኳን አብዛኛዎቻችን ንዳልነበሩ እንረሳቸዋለን።

አፈር ሰውዬው አንዴ ከለበሰ ማን አስታውሶት የእሱን መቃብር መልሶ መላልሶ ይጎበኛል? ማን አታክልት መቃብሩ ላይ ተክሎ አልፎ አልፎ እየወረደ እሱን ይኮተኩታል? አበባውንስ ጥዋት ማታ ወሃ እየቀዳ ማን ያጠጣል? ሜዳውንና አካባቢውንስ ማን ዞር ብሎ ይጠርጋል?

ይህን የሙታን ቀን የሚባለውን ነገር ቤተ- ክርስቲያናችንም  አታውቅም። የሞስሊሙም ማህበረ ሰቡም  እንደዚሁ አያውቀውም። አይንከባከበውም። 

 ለአገራቸው ዳር ድንበር ወይም ለነጻነታቸውና  ለባንዲራቸው የሞቱትንና የወደቁትን ልጆቹዋን የመከላከያ የጦር ሠራዊቱም የጦር ኃይሉም ይህን ቀን በአመት አንዴ የሚያስታውስበት ቀን  እንኳን – ሐውልት መሥራቱን እንተወው የለውም።

ያለውንና የኖረውን ማጥፋት የነበረውን ማቃጠል ከዚያም አልፎ በእሱ ቦታ ደግሞ ለአዲሱ ትውልድ „…እኔም እኮ አዲስ ታሪክ መጻፍ እችላለሁ እንችላለን“ በሚለው ከንቱ ውዳሴ ብቻ ብዙ ትርዕይቶች ማቅረቡን የፖለቲካ መደቡ በተቃራኒው ያውቅበታል። በአለፉት አመታት እነደዚህ ዓይነቱን ቲያትሮች – የተመዘገቡ ናቸው- በተደጋጋሚ አይተናል።

…ምን ለመሆን? ብሎ እነሱን የሚኮረኩር፣ የት ለመድረስ ?…ብሎ እነሱን በጥያቄ የሚያጣድፋቸው፣እሩጫው ወዴት ብሎ እነሱን የሚወቅሳቸው፣ የራሳቸው ሒሊናም ሆነ ሌላ ሰው የለም። በእርሱ ፋንታ በርቱ የሚል ድምጽ ግን እንደገደል ማሚቶ ከሁሉም ቦታ ይሰማል።

ስንቱ ነው የእናቱንና የአባቱን መቃብር የሚጎበኘው? አልፎ አልፎስ ብቅ ብሎ የሚጠርገው? የሚንከባከበው?

ምኒልክ ከሞተ አንድ መቶ አመቱ ነው። ይህን ምክንያት በማድረግ በስሙ የተዘከረበት ስሙ የተነሳበት ፣ጉባዔ በሥነስርዓቱ የተካሄደበት ጊዜ የለም። ቢኖርም ብዙበቦታ አልተሰማም።   

ለቴዎድሮስም፣…ለዮሐንስም፣…ለዘውዲቱም ፣ለኃይለ ሥላሴም …ለንጉሥ ….እገሌና እገሊት ….ጥቂቱን ብቻ ለመቁጠር እነቁጠር ለእነሱም -ይህ ነው የአብዛኛው አስተሳሰብ- ምንም ስለ አልተደረገ „ለምን ለምኒልክ ብቻ ይህን ይህል ቦታ ከአልጠፋ ነገር ትሰጣላችሁ ?“ የሚለን ሰው አይጠፋም።          

ምኒልክ የሚለው ስም በኢትዮጵያ የነገሥታትና የአገሪቱ ታሪክ -የሌሎቹ ስም ይደጋገማል – በአለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት ምክንያቱ ምን እነደሆን በግልጽ አይታወቅም እንጂ-  ሁለት ጊዜ ብቻ ነው በታሪክ ላይ ብቅ ያለው።

አንደኛው በኢትዮጵያ መንግሥትና ግዛት የምሥረታ ሚቶሎጂ [1]፣ የቀዳማዊ ምኒልክ ታሪክ ሲሆን

ሁለተኛው ደግሞ ከስንት ሺህ አመት በሁዋላ ብቅ ያለው የዳግማዊ ምኒልክ ሥራና ገድል ነው።

እኛዚህን ትልቅ ጥቁር ሰው፣ የምኒልክን ታሪክ ዛሬ የምናነሳው መቶኛውን የሙት አመት ለማስታወስ ነው።

የእሳቸውን ታሪክ በጥቂቱ  አስቀምጠን  እንዳለፍን ምኒልክ ከሞቱ ከአምስት አመት በሁዋላ በደቡብ አፍሪካ የተወለዱት የሚስተር ኔልሰን ማንዴላ ዕረፍት –  እኛም በዝግጅት ላይ እንዳለን ደርሶን- ይህ ዜና እኛንም እነደ ሌሎቹ አስደነግጦአል።

በሁለቱም የአፍሪካ መሪዎች መካከል የአንድ መቶ አመት ልዩነት አለ።

አንደኛው ንጉሥ „…አገሬን ሕዝቤን ነጻነቴን ለባዕድ ለቅኝ ገዢ ወራሪ ኃይል አልሰጥም“ ብሎ በዲፕሎማሲውም መንገድ በሁዋላም ወረድ ብለን እንደምናየው፣እሱም አልሆን ሲል  በጦር ሜዳም አደዋ ላይ ተዋግቶ የኢትዮጵያን ስም ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝብን መብት- አሁን የእሱ ሐውልት ይፍረስ የሚሉትንም ሰዎች መብት ጭምር ተከራክሮ- ይህ ጀግና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንድ ላይ አስተባብሮ ከእነሱም ጋር አብሮ አንድ ላይ  ቆሞ  ነጸነታቸውን፣ነጻነታችንን እሱ አስከብሮአል።

አለ ምክንያት አይደልም ኔልሰን ማንዴላ በሁዋላ የመሩት „የደቡብ አፍሪካ ናሺናል ኮንግሬስ ድርጅት „…ሃይማኖቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣…የነጻነት ጥማቱን እንደ ኢትዮጵያ፣… የማንነታቸውን ኩራታቸውንና አርበኝነታቸውን፣ ….ከነጮች ጋር የእኩልነትና መብታቸውን ትግል እንደ ኢትዮጵያ አድርገው…“ (-ለዚህ ደግሞ የማንዴላን ባዮግራፊ ተመልከት-) „ ለመታገል እነሱ አውጥተው አውርደው የተነሱት።

ኔልሰን ማንዴላ በብዙ ትላልቅ የሽንጎ አዳራሽ፣ የፓርላማ  ሕንጻ ውስጥ በበርካታ የዓለም ከተማዎች ተጋብዘው ግሩም ንግግር ስለ የሰው ልጆች እኩልነት፣ስለ ነጻነትና ስለ ሰባአዊ መብቶች ስለ ዲሞክራሲና ስለ ዘረኛነት መጥፎ ጠንቅነት ንግግር እንዳደረጉ ሁላችንም እናስታውሳለን።

በኢትዮጵያ እንኚህ ሰውንና ድርጅታቸውን በረዳው  በዋና ከተማው በአዲስ አበባው የሸንጎ መድረክ ላይ ግን ብቅ ብለው አንድ ጊዜም ንግግር እኚህ ሰው አላደረጉም። ለምን አዲስ አበባ የሽንጎ አዳራሽ ውስጥ ንግግር ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ  ምክንያቱ – እኚህ ሰው ኪዩባ ሳይቀር እዚያ ድረስ ወርደዋል- ለእኛ ግልጽ አይደለም። ለምን አሥመራ ሄደው እዚያም የሽንጎው አዳራሽ ውስጥ ሌላ ቦታዎች እንደአደረጉት እንደአልተናገሩ ምንም የምናውቀው ነገር የለም።

በተባለው ግል የታሪካቸው በባዮግራፊአቸውወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የኢትዮጵያን የአይሮፕላን አስተናጋጆች ተመልክተው እንደተገረሙ ጽፈዋል።ቆየት ብለው አይሮፕላን አብራሪውን ሲመለከቱና ጥቁር ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያኔ በዓይናቸው ሲያዩ መደነቃቸውን እኝህ ሰው ጠቅሰዋል።

„ፖሊሱን፣የክብር ዘበኛውን፣ንጉሡን….ሲቃኙ ደግሞ  „ለካስ ይህም አለ ወይ…“  ብለው ሳይደብቁ በመጸሓፋቸው ላይ አሥፍረዋል። በሁዋላም  „በጦር ትግል ሥልት“  በኢትዮጵያኖች እንዲሰለጥኑ በንጉሡ ትዕዛዝ ተደርጎአል።

 ማንዴላ ከንጉሡ የተሸለሙት ሽጉጥ በሁዋላ ጋርዲያን እንደ ጻፈው (ለኃይሌ ቦታ የሰጠው አንድም ትውልድ የለም) ሁለት ሚሊዮን ፓውንድ እሰከ ማውጣት ድረስ እነደሄደ ጋዜጣው ተገርሞ ጽፎአል።

ምኒልክ በነጻነት ትግል፣ማንዴላም በነጻነት ትግል ሕያው ሁነው ሁለቱም ይኖራሉ። አንደኛው የተረሳውን ለመድገም የቅኝ ግዛት ወራሪዎችን በመከላከል ነው። ሌላው የቅኝ ገዢዎችን የበላይነት በመቃወም ነው።

ምኒልክ ነጻነታችንአስክብሮ መንግሥቱን አመቻችቶ ለአጼ ኃይለሥላሴ እና ለእኛ ለአለነው ትውልድ አገሪቱን አስተላልፎ ሄዶአል። ማንዴላም ኢትዮጵያን አረአያ አድርጎ ሁሉም የደቡብ አፍሪካ ኑዋሪዎችና ተወላጆች ነጩም ጥቁሩም፣ክልሱም ሕንዱም …ቻይናው አረቡም… የአገሪቱ ዜጎቹ ሁሉ እኩል በነጻ  የሚኖሩበት ዲሞክራቲክ  ሕብረተሰብ መሥርቶ አልፎአል።

በሁለቱ ሰዎች መካከል የአንድ መቶ አመት ልዩነት አለ። ለምን ምኒልክ የዲሞክራቲክ ሥርዓት ለኢትዮጵያ አላመጣም ብለን ልንከሰው አንችልም።

የምኒልክን የነጻነት ትግልና የፖለቲካ ጥበብ ከእሱም ጋር  የኔልሰን ማንዴላን „ለዲሞክራሲና ለሰበአዊ መብቶች መከበር- ጥቁር ይሁን ነጭ፣ክልስ ይሁን ሕንድ- የእነሱን የዜጎች መብት መጠበቅና ማወቅ ማክበርም“…  እነዚህን ሁለቱን አስተሳሰቦች አጣምሮ፣አዳቅሎ ለአገሬ እሰራለሁ፣ እንደዚህ  ዓይነቱን ፖለቲካም በኢትዮጵያ አራምዳለሁ ለሚል ሰው፣ ሁለቱ የሰሩት ሥራ ሕያው ሁኖ የሚቆም ግሩምና መልካም፣እጅግም ደስ የሚያሰኝ  ጥሩ ትምህርት  ነው።  ከዚህ ውጭ መጀመሪያ ልማት በሁዋላ ዲምክራሲና ሰበአዊ መበት  የሚለው ራዕይ „ …ዕብደትና ምኞት“ ነው።

በ„ዕብደት“ ደግሞ የሚመጣውና የሚሆነው ነገር ስለ ማይታወቅ ይህም ነገር አደገኛ ስለሆነ ከዚህ ነገር ራቁ ይባላል። “…ምኞት“ ግን ምኞትደግሞ የሌላውን መብት እስከአልተጋፈ ድረስ „ይፈቀዳል።“ 

 መድሓኒት ቀማሚ ነጋዴዎች እንደሚሉት”…ከዚህ ለየት ያለ ሓሳብ ያላችሁ ሰዎች ….ብዙ ቦታ ሳትደርሱ ሐኪማችሁን ለማንኛውም ነገር ጥርጣሬ ከአላችሁ እነሱን እባካችሁ አነጋግሩ…።“ 

እኛም ይህን ማለቱን ለዛሬ – ይቅርታ አድርጉልን-እንመርጣለን።

መልካም ንባብ! መልካም ትካዜ! መልካም ግንዛቤና ምናልባት ደግሞ መልካም  ጥያቄና አስተያየት !

እንደ ምኒልክ በዓለም ላይ የተከበረ፣ እንደ እሱም በአንዳንድ በገዛ ልጆቹ አልአግባብ የተጠላ – ሰው የለም!

 

 ዋናው አዘጋጅ ይልማ ኃይለ ሚካኤል    

 


[1](ይህን ደግሞ በሌሎች ትላልቅ የዓለም ሕዝብ ታሪክ የምናየው ነው- ሌላው ቀርቶ በተኩላ ሞግዚትነትና ከእሱዋም  „የእናት ወተት“( እርቦአት ልትበላቸው፣አውሬ ስለሆነች ትችላለችግን ታሪካቸው ላይ ይህን አላደረገችም) የእሱዋን ወተት ጠብተው ያደጉት- ይህን አልነበረም ብሎ መከራከር የአንባቢው ፋንታ ነው- ሁለቱ የሮም መንግሥት መሥራች ወንድማማቾች ሮሚውሲና ሮሙሎስ፣  እዚህ ላይ ይህን ማስታወሱ በቂ ነው፣…. ግሪኮችም፣ጀርመኖችም፣…ሩሲያና ቻይናዎችም ጃፓኖችም በየፊናቸው እረ ስንቱ ሥልጣኔ… ተመሣሣይ ታሪክ አሉአቸው)

 

ጣ ይ ቱ / TAITU / ንግሥቲቱ / መሪይቱ

የኛዓለም ሲያየው ! THE GIRL EFFECT