ጃንሆይና ነጻ-ዜጋ፣ ፓርቲና ዲስፕሊን

ጃንሆይና ነጻ-ዜጋ

Advertisements

ጃንሆይና ነጻ-ዜጋ

ፓርቲና ዲስፕሊን

ለምንድነው የታወቀውን ነገር እንደገና ለማብራራት የምንሞክረው? አሁን ምን ይጠቅማል? ምን ያደርጋል በንጉሥና በተራ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ደግመን የምናነሳው?

መልሱን የምንረዳው አሁን ሳይሆን ከጥቂት አረፍተ ነገር በሁዋላ ነው። በትክክል የምንገዘበው ደግሞ ወደ መጨረሻው ላይ ነው።

ከንጉሠ-ነገሥቱ የተላለፈልን (አብዛኛዎቹ ዕድሜአቸው ቢያንስ ከሃምሣ አመት በላይ የሆኑት አዛውንቶች የማይረሱት) አንድ የቆየ አነጋገር አለ።

እሱም „…የምንወደው ሕዝባችንና የሚወደን ሕዝባችን…!“ የሚለው የ ቀ ኃ ሥ ግሩም አነጋገር ነው። እሳቸው „ሕዝባቸውን እንደሚወዱ“ ጥርጥር የለም። ሕዝቡ ደግሞ „እንደሚወዳቸው…“ መገመት ይቻላል።

ግን አንድ ችግር አለ።

በዚያውም መጠን የማይታወቀው ምን ያህል ሕዝብ እሳቸውን ጸሓዩን ንጉሥ„እንደሚወዳቸው“? ምን ያህልስ ሰው እንደ „ሚጠላቸው“ አንዳችም ጥናት እንደ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ይህን ነገር የሚከታተል የምርመራ ጣቢያ በአገራችን ስለሌለ፣ ስለአልነበረም፣ በትክክል ለመናገርና ይህን ያህል ነው ብሎ ማስቀመጥ አይቻልም።

የአገራችን የኢትዮጵያ ነገር የሚያስገርም ነውና አሁንም ቢሆን„…የምንወደው ሕዝባችንና የሚወደን ሕዝባችን…“ የሚሉ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እንዳሉ እንዲያው ከነገረ ሥራቸው ተነስተን ስንመለከተው፣ መገመት ይቻላል።

ግን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሁለቱም ፖሊተከኞች ሆኑ ሌሎቹ „የኢትዮጵያ ንጉሥና የነጉሠ-ነገሥቱ ዙፋን ላይ አልተቀመጡም። “ ንጉሥም አይደሉም።

በሌላ ቋንቋ አቶ ኃይለ ማሪያም እንደ ሳውዲው ንጉሥ ፣ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂም እንደ ሞሮኮ ንጉሥ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ሊገዙ „ቅባ ቅዱሱን“ የተቀቡ የዕድሜ ልክ „ንጉሦች“ የሚታወቀውን ለመድገም፣ እነሱ “የተነሱ አይደሉም።”

እነሱም -እኛ እሰከ ምናውቀው ድረስ- አንድም ቦታ ንጉሥ ነን አላሉም። እነሱም ይህን አይክዱም። ከአፋቸውም አንድ ቀን አልወጣም።

አመጣጣቸውንም ክደው „የሰለሞን ዘርን ነን“ ስለዚህ ሥልጣኑም ቤተ-ምንግሥቱም „ዕድሜ ልካችን ድረስ ይገባናል“ እሰከ አሁን አላሉም።

ሁለቱም እንደ እኔና እንደ አንተ፣ እንደ እሷና እንደ እሱ፣ አንደ እከሌና እከሊት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ተራ ሰዎች ናቸው።

ንጉሡ ደግሞ እንደምናውቀው „ልዩ – ፍጡር“ ናቸው። እነሱ እንደሚሉት፣ የሃይማኖት አባቶች እንደሚያስተምሩት „…እግዚአብሔር ከሰው ሁሉ የመረጠው“ እሰከ ዕድሜ ልኩ የሚገዛ „…ልዩ ሰው“ ነው። ንጉሥ እንደምናውቀው አይከሰስም። ንጉሥ አይወቀስም፣ አይተችም። ከሥልጣንህም በቃህ ውረድ አይባልም። በዘልማድ የኢትዮጵያ ሕዝብ „…ሰማይ አይታረስም ንጉሥ አይከሰስም …“ ብሎ ጨርሶታል።

ታዲያ ለምንድነው ንጉሡ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለምም አንድ በአንድ ተራ በተራ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ የተደረገው?

በምንስ ብልሃት ነው እነሱ ከዙፋናቸው የወርዱትስ?

A

አንድ ዜጋ አንድ ተራ ሰው አንድ ከእኔና ከአንተ ምን ዓይነት ልዩነት የሌለው ሰው ሲያተፋ ከታየ እሱ ይተቻል፣ ይወቀሳል፣ እንዲታረም ይጠየቃል። ከሥልጣንም ከዚህ ሁሉ አመት በሁዋላ በቃህ እስቲ ደግሞ ውረድ ተብሎ ምርጫ ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል።

በአሜሪካን አገር የምናየው ይህን ነው። በፈረንሣይና በጀርመን፣ በጃፓንና በኬንያ በደቡብ አፍሪካ፣ እንዲሁም በናይጄሪያና በጋና የምናየውም ተመሳሳይ አሰራርን ነው። …ምርጫ የሸንጎ ምርጫ እዚያ ይካሄዳል።

በሌላ በኩል እነ ንግሥት ኤልሳቤጥን፣ የጃፓኑን ንጉሠ ነገሥት አይህቶ፣ የስፔኑ ሁዋን ካርሎ፣ የስዉዲኑን፣ የዴንማርኩን፣ የቤልጅጉን፣ የኖረዌውን…ወደው በገዛ ፈቃዳቸው እስከ አለቀቁ ድረስ „በቃችሁ ውረዱ“ ተብለው እነሱ ሕዝቡ አይጠየቁም። ለምን?

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግን እንደ ሌሎቹ ከሁለት ተከታታይ ምርጫ በሁዋላ-ይህ የአሜሪካን ሕግ ነው- ጓዛቸውን ጠቅልለው ከዋይት ሓውስ በሚቀጥሉት አመታት መጨረሻ ላይ እንደሚወጡ ግልጽ ነው። ሌሎቹ የአውሮፓና የላቲን አሜሪካ መሪዎች በየአራት አመቱ አደባባይ ወጥተው ሕዝብ ፊት ቀርበው ወይ እንደገና ይመረጣሉ ወይ ተሸንፈው ከፖለቲካ ዓለሙ ይሰናበታሉ። ይህን ማለት የታወቀውን መድገም ነው።

አቶ ኢሳያስና አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ሚስተር ሮበርት ሙጋቤና የአንጎላው ዶሳንተስ…ቁጥራቸው ረዥም ነው- ዕድሜ ልካቸውን የሚገዙበት ምክንያት ግን ግልጽ አይደለም። ለምን? ምክንያቱ ምንድነው?

ማን ጠየቃቸው እነሱን ይህን ያህል አመት በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ?ማን ለመናቸው? ማን መረጣቸው? ማን ፈቀደላቸው? ለመሆኑ ምን የሚያሳምን ነገር ጨብጠዋል? ለምን እነሱ ብቻ ሥልጣኑ ላይ እንዲሰነብቱ ይደረጋል?….ለምን አንተ ወይም አንቺ በሕዝብ ተመርጣችሁ አገሪቱን አትመሩም? አታስተዳድሩም?…እግዚአብሔር ሥልጣኑን መርቆ ነው የሰጣቸው? ወይስ ሕዝቡ ?

ይህን ለመረዳት ችግሩ ያለው አንድ ቦታ ላይ ነው። ይህም ዕውነቱን እንናገር ከተባለ የተቃዋሚውንም ጎራ ያጠቃልላል።

ምን አጠፉ እነሱ ደግሞ? የሚል ድምጽ ሊሰማም ይችላል።

የተቃዋሚ ቡድኖችን ጎራ ተመልከትን፣ እነሱስ እንዴት ነው የተመሰረቱት? አባሎቻቸውን እንዴት ነው የሰበሰቡት ብለን እራሳችንን እንጠይቅ?

ቀድሞ ድርጅቱን የመሰረተ–ይህ ነው ብልሃቱ–ቀድሞ የድርጅቱን ሕግ የነደፈ፣ ቀድሞ ሮጦ የድርጅቱን አመራር የጨበጠ፣ ተከታይ ደጋፊዎቹን ሰብስቦ ያዋቀረ…እሱ „ቅባ ቅዱሱን ሳይቀባ ንጉሥ“ የሆነ፣ እራሱን በራሱ የሾመ፣ እንደ ናፖሊዮን ዘውዱን ከሚንቀጠቀጠው ጳጳሱ እጅ ቀምቶ አናቱ ላይ የደፋ ሰው ማለት ነው።

ከዚያ በሁዋላ ይህን ሰው አስመልክቶ „ዕውነተኛ ምርጫ“ በድርጅቱም ውስጥ ሆነ ከድርጅቱም ውጭ ሥልጣን ይዞ ብቅ ያለ ቀን „ ሕዝቡ እሱን እንዲመርጠው „ አይደረግም ። ይህ እንዳይሆን ተሟጋቾቹም ብዙ ናቸው።

B

ከዚህ በሁዋላ በተነደፈው አይዶኦሎጂም ሥር ሁሉንም ሰው ሰካክቶ ሽንሽኖ አስቀምጦ፣ “በዲስፕሊን፣ በሥልጣን ተዋረጅ፣ በበላይና በታች፣ በቅጣትና በዱላ በጥይትና በባሩድ አስፈራርቶ….“ ድርጅትንና የድርጅቱን አባሎች ተብትቦ በመያዝ፣ ሁሉንም ልክ አስገብቶ ሥልጣንን አንድ ቀን በጠበንጃ ኃይል ይዞ ቤተ- መንግሥት መግባት ዋና የትግል ዓላማና ጉዞ ነው።

discipline-party

እንደዚህ ዓይነቱ ነገር በሃይማኖት ድርጅቶችም ውስጥም በደንብ ይታያል። ከዚህ ያለተለየ ጉዞ በአመጣጥ ታሪካቸውም አብዛኛዎቹ አላሳዩም።

እንደ ንብረታቸው ነው እነዚህ ሰዎች ሕዝቡንም እያንዳንዱንም ሰው ሁሉ የሚያዩት። እንደ ሓብታቸው ነው ሁሉንም ከቁጥጥራቸው እንዳይወጣ በዓይነ ቁራኛ የሚጠብቁት። እንደ የግል „ባሪያቸው“ ነው መብቱን ቆይተው የሚገፉት። ከዚያ በሁዋላ መብቱን መርገጥ ቀላል ነው።

የሰው ልጅ ግን የትም ቦታ ይኑር የትም ይወለድ፣ ነጭ ይሁን ጥቁር፣ ቢጫ ይሁን ቀይ…. ቤቱን ዘግቶ ወጥቶ ንጹህ አየር መተንፈስ ይገልጋል። ቡና ቤት ገብቶ ሳይገላመጥ ከጓደኞቹ ጋር የልቡን ተነጋግሮ ወቅሶ ተችቶ ሐሳቡን ከሌላው ጋር ተከፋፍሎ ወደ ቤቱ ማንንም ሳይፈራ መመለስ ይፈልጋል።

የባቡር ወይም የአይሮፕላን ቲኬቱን ገዝቶ፣ መኪናውን ወይም ብስክሌቱን ይዞ፣ ፈረሱ ላይ ወይም አንድ አውቶብስ ላይ ተሳፍሮ፣ ቢፈልግ ዘመዱን፣ መጠየቅ ባይፈልግ ሜዳ ላይ ዱንኳኑን ተክሎ ማደር ይፈልጋል።

የፈለገውን ልብስ፣ የወደዳትን ሴት ልጅ፣ ደስ የሚለውን ሙያ፣ ቢፈልግ ጢሙን ማሳደግ፣ ባይፈልግ መላጨት፣ ማግባትንና መፍታት፣ አንገቱን ሳይደፋ ቀና ብሎ መሄድን የሰው ልጆች ሁሉ እኩል መብት ስለአላቸው፣ ማንንም ሳይፈራ ማድረግ ይፈልጋል።

ፊደል የቆጠረውማ አለ አንዳች ቁጥጥርና ፍረሃቻ በአገሩ መሬት አለ- ሳንሱር መጻፍ ይመኛል። ዕውቀቱን ማከፋልና ትውልዱን ማስተማር፣ ዛፍና አበባ ተክሎ መኮትኮት፣ ግቢውን ማሳመር የግል ቤቱንና የግል እርሻውን መጠበቅ ይፈልጋል።

ገበሬ የግል የእርሻ መሬቱን ይመኛል። ሠራተኛው ሥራውን፣ ተማሪው የትምህርት ዕድሉን፣ እናቶችና አባቶች ጡረታቸውን፣ በሽተኛው ሕክምና እና እንክብካቤን፣ ረሃብተኛው ምግብን፣ ሜዳ አዳሪው ፍራሽና አልጋን አዘጋጁልኝ ይላል። ይህ ለማለት ደግሞ መብቱ ነው።

ጥያቄው ሌሎቹ ነጮቹ በምን ብልሃትና ዘዴ እላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ፈቱ የተቀሩት ደግሞ እዚያው የችግር አዙሪት ውስጥ ገብተው፣ መንገዱ ጠፍቶአቸው ከዚያ ለመውጣት ያልቻሉት? የሚለው ጥያቄ ነው።

መልሱ አርባውንና ሃምሳውን አመታት እንደሚባለው „የብሔር -ብሔረሰብ ትግል፣ እሰከ መገንጠል“ የሚባለው ፍልስፍና በኢትዮጵያ ተገቢውን መልስ ባለ ማግኘቱም አይደለም።እሱማ ለጦር ትግል ሁሉንም ጋብዞ ሰውን አፋጅቶአል። ከዚያም ጦርነት የተገኘው ውጤት ምን እንደሆን ሰው ሁሉ ያውቀዋል።

እንደ ተባለው ኤርትራና ኢትዮጵያ (ያኔ እንደተባለው) „የአፍሪካ ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና …“በአሥርና በሃያ ሦስት አመታት ጊዜ ውስጥ ሆነው የአውሮፓን ገበያ በእንዱስትሪ ምርታቸው አላጥለቀለቁም ።

C

ብዙዎቹ የተመኙት “የመደብ ትግሉም ሶሻሊዚምም የላብ አደሩ አምባገነን መንግሥት በኢትዮጵያ”ያም ቢሆን መፍትሔ አልነበረም። አይደለምም።

አንድ ድርጅት ሓብትና ንብረት በአዋጅ ወረሶ እንድን አገር „ሌኒን እንዳለው፣ ማርክስ እንዳስተማረው፣ ስታሊን በተግባር እንዳሳየው…“ እያሉ ያንን ሕዝብና ያንን አገር እንደ የግል ሐብት እሱን „በሶሻሊዝም ስም“ እጅ አስገብቶ እሱን ቁጭ ብሎ መሸጥና መለወጥ ያ አገሪቱ ከገባችበት ችግር እንደማያወጣት አሁን ያለንበት ሁኔታ እራሱ ምስክር ነው።

የኢትዮጵያ ችግርና የኢትዮጵያ መፍትሔ ያለው ሌላ ቦታ ነው።

እንደሚባለውም የአገራችን ችግር፣ አሁን ያለንበትና የገባንበት መከራ ትላንትና ብቅ ያለው ግሎባላይዜሽን የሚባለው ነገር ይዞልን የመጣ ችግርም አይደለም። ወይም ሌሎች እንደሚሉት የቅኝ ገዢዎች ተንኮል የለቀቁብን በሽታ አይደለም።

ችግሩ ያለው በእኛው መካከል ነው።

እንደ ሰንሰለት ተብትቦ ከያዘን የድርጅት „የዲስፕሊን እሥር ቤት“ መውጣት አለብን። እንደ ባሪያ ፣ እንደ ሎሌ አሽከር ወዲያና ወዲህ ከሚያዋክብን „ፍልስፍናና ትምህርት እምነትና… „ እንዲያውም ወደ ሃይማኖት ከተቀየረው „የፖለቲካ አስተሳሰብ“ ከእሱ ነጻ- መውጣት አለብን።

እንደዚህ ከአልን ደግሞ ከጨለማ ወደ ብረሃን፣ እንወጣለን። ከገባንበት ዋሻ ወጥተን ዓለምን በሌላ ዓይን እናያለን። ፍረሃትን አስወግደን በጠራ አንደበታችንን ግሩም ውይይትን በመካከላችን እንከፍታለን። የተለጎመውን አፋችንን ከፍተን „ለመሆኑ አንተ ማን ነህ? ምን ትፈልጋለህ? ምን ለአገርህ ሰራህ? ምን መስራት ትፈልጋለህ? ችሎታህ ምንድነው? አሁን ደግሞ ይበቃሃል ቦታውን ለሌላው ልቀቅ…“ማለት እንጀምራለን።

እንደዚህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ወደ ጦር ሜዳ አይወስደንም። ጦር ክፈቱ ብሎም አይጋብዘንም። እንዲያውም ጦርነት ምን ይህል የሰው ነፍስና ሐብት ያወጣል? ስንት መስዋዕትነትን ይጠይቃል? ስንት አመት ይፈጃል? ወደሚለው ጥራት ወደ አለው ጥያቄና መልስ ይወስደናል?

ከጦርነት ሌላ ሌላ ብልሃቶችና ዘዴዎች አሉ ወይ ወደሚለው የፖለቲካ አመለካት ይወስደናል።

የነጻ-ዜጋ ኮንሰፕት፣ የነጻ ሰው ሕብረተሰብ ምሥረታ ያም አስተሳሰብ -እናሳጥረው- ኢትዮጵያንና ልጆቹዋን አንድ ያደርጋል።

እንዴት?

መልሱን እዚሁ እኛ አብዛኛዎቻችን የምንኖርበት የአውሮፓና የአሜሪካን ሕብረተሰብ ሰጥቶናል። አብዛኛው የእሲያና የላቲን አሜሪካ አገሮችም እንደኛው ብዙ አመታት ተንከራተው እነሱም በመጨረሻው መልሱን አግኝተው ደርሰውበታል።

ጃፓንና ደቡብ ኮሪያም አውቀውበታል። እሱም የነጻ -ዜጋ የግለሰብ መብት፣ የሚለው ፍልስፍና ነው።

ለመሆኑ ይህ ምን ይመስላል? እላይ እኮ የአገሮች ስም ጠቅሰናል።

ከሣቴ ብርሃን

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s