ዓለም እንዴት ሰነበተች

ዓለም እንዴት ሰነበተች

ውድ አባቢ

የሚያበረታቱና ተስፋ የሚሰጡ ዜናዎችን ከአፍሪካ እንሰማለን። በእዚያው መጠን የሚያስደነግጡና የሚያሳዝኑ ወሬዎችንም እናዳምጣለን።

አሰዛኙን አቆይተን፣ በጥሩ ዜና እንጀምር።

አምባገነኑ የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ቻርልስ ቴለር በሰራውና በአደረገው ጥፋት የተፈረደበትን የሃምሳ አመት እሥራት ቅጣት “አለልክ በዛብኝ” ብሎ “ጉዳዩ እንደገና እንዲታይለት ያቀረበው የይግባኝ ማመልከቻ ውድቅ ሆነ“ የሚለውን ዜና እናስቀድማለን።

„ሞገደኛው ቻርልስ ቴለር“ እንደ ኬንያው ኡሁሩ ኬንያታና እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የዴንሃጉ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ኢሰበአዊ ሥራ በአገራችሁ ሰራችሁ ተብለው ከተከሰሱት የአፍሪካ መሪዎች አንደኛው ናቸው።

ሁለተኛው ዜና “ድርጅት መስረታችሁ በኮንጎ ውስጥ ጦርነት ከፍታችሁ ሴቶች ትደፍራላችሁ፣ ንብረት ታወድማላችሁ፣ ሕዝብ ታፈጃላችሁ፣ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ወጣት ሕጻናት አስገድዳችሁ ታዋጋላችሁ፣ ባንክ ትዘርፋላችሁ፣ … ” ተብለው እዚህ ጀርመን አገር ስለተከሰሱት ቡድኖች እናነሳለን።

በሦስተኛ ደረጃ በቻይና እንደትልቅ የሕብረተሰቡ ማስተካከያ ሜካኒዝም እንደ ትልቅ ቁም ነገር በአገሪቱ ከማኦ ጊዜ ጀምሮ ስለተስፋፋው „ የሒስና የግለሒስ ዘመቻም“ አንስተን ይህ ነገር አንድን ሕዝብ አንድን አገር ወዴት እነደሚወስድ እንመለከታልን።

„አሁን እኛን ምን አግብቶን የቻይና ፖለቲካ ውስጥ ገብተን እንፈተፍታለን? …ምንስ አገባን ?“ ሊባል ይቻላል።

ቻይና እንደሚታወቀው የብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች አረያና ሞዴል ናት። በመሆኑዋም „ሙስናን ለመዋጋትና በሥልጣን መባለግን ለመቆጣጠር“ አብዛኛው የአፍሪካ መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች “በነጻ-ፍርድ ቤትና በነጻ-ጋዜጣ” ይህን ችግር ከመቆጣጠር ጊዜአቸውን እንደ ቻይና የኮሚኒስት ፓርቲ “በሒስና በግለሒስ፣ በሴሚናርና በውይይት” እንደሚያጠፉ አብዛኛዎቻችን እናውቃለን።

አራተኛው – ይህ ነው የሚያሳዝነው ዜና- ዱሮ „በደጉ ዘመን፣ በንጉሡ ጊዜ“ በኢትዮጵያ ፓስፖርት ኮርተው የትም መንቀሳቀስ የሚችሉ ኢትዮጵያውያኖች (ዛሬ ኤርትራውያኖች) ያ የተመኙትና ያ የአለሙት የዲሞክራሲ ሕልም ሳይሳካላቸው ቀርቶ በስደት ጉዞ ላምፔዱሳ ላይ መሞታቸው አንድ ሐተታ እንድንጽፍ ገፋፍቶናል።

ዓለም እንዴት ሰነበተች እንጀምር።

ዓለም እንዴት ሰነበተች

አዲስ ሰው ምንም የማያውቅ ባልሆነ አስተሳሰብ ያልተበከለ „ንጽህ ሰው እንፈጥራለን“ የሚለው የአንዳንድ „አብዮተኞች በሽታ“ ረጅም ዕድሜ አለው።

ከአለባበስ በአንዳንዶቹ ይጀምራል።ከአነጋገር፣ ከአጠራር፣ ከሰላምታና እራሱ የእጅ አነሳስንም ያካትታል።

ኮሊታ የለው የማኦና የስታሊን አለባበስ፣ የሌኒን ኮፊያ፣ የሒትለርና የሞሰሊን ሰላምታን እነዚህን ሁሉ ያጠቃልላል።

የሰሜን ኮሪያ የጠጉር አቆራረጥ፣ የኡልብርሽትና የእነሆኔከር የድምጽ አጣጣልና አነጋገር፣ የታሊባን ጢም፣ የአራፋትና የክሜር ሩጅ የአንገት ልብሶች እነዚህ ሁሉ:- አንዳዶቹን ለመጥቀስ በዓይን የሚታዩ ነገሮች ናቸው። በእኛም ሀገር አንዳዶቹ ትልቅ ዲስኩር ሲያደረጉ የእጅ አወራወሩ ወደዚያው ተጠግቶአል!

ይህም ነገር ኢትዮጵያና ኢራን፣ኒካራጉዋና ቦሊቪያ፣ ሌላም አካባቢና ቦታ (ይኸው ሠላሣም አርባም አመት ይሆነዋል) ዘልቆ ገብቶአል። ከእሱም ጋር „ሒስና ግለሒስ“ (ደግሞም፣ ግምገማ እራስን ማጋለጥ በሚባል ስምም እኛ ዘንድ በአዲስ ስም ተጠምቋል) የሚባለው ነገር፣ እነማኦ ሴቱንግ በነጻ-ፍርድ ቤትና በነጻ-ዳኛ ፋንታ ለቻይና (ለዓለምም) ያስተዋወቁት የችሎት ፍርድም ከዚያም ተንደርድሮ፣ ዳኞችን ሥራ ፈት ለማድረግ አፍሪካ ገብቶአል።

ሃሳቡን ያፈለቀው „ ጸረ-ኮሚኒስቶቹን” እሱ እንደሚለው ” ከፓርቲው ለማጽዳት“ በዚያም ሳቢያ ብቻውን ለመግዛት የተነሳው ዮሴፍ ስታሊን ነው። ስታሊን በዚህ ሥራው በሚሊዮን የሚቆጠሩ „ጓደኞቹን“ በጅምላ በአደባባይና በራዲዮ እያስለፈለፈ ፈጅቶአል።

የማኦ „ሒስና ግለ ሒስ“ ለማታለል ለየት ያለ ይመስላል። ግን እሱም ቢሆን አብረው ከጎኑ ሁነው ጃፓንን የታገሉትን ጓደኞቹን ሳይቀር በግለ-ሒስ ስም „አምናችሁ ጥፋታችሁን ከተቀበላችሁ ትፈታለችሁ፣ ድርጅቱም ይቅርታ ያደርግላችሁዋል „ እየተባሉ፣ እንደተመዘገበው „በብዙበሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናዎች በፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሳይታይ፣ ጥፋታቸው ሳይመረመር በጥይት ተደብድበው አልቀዋል።“

ሌሎቹ በአደባባይ ተወግረው እዚያው ወድቀው ቀርተዋል። ማኦ በዚህ በዚያ በታሪክ „የካልቸራል አብዮት“ የሚባለውን ስም ባተረፈው ዘዴ ከሚስቱና ከጓደኞቹ „ተገላግሎ“ ሥልጣኑን አጠናክሮ ወጥቶአል። አይረሳም ደረታቸው ላይ “እኔ ጸረ-አብዮተኛ ነኝ ” የሚል ሰሌዳ አሸክሞ እንደ ከብት ሰውን መንገድ ላይ ማኦና ተከታዮቹ ነድተው መሳቂያ መሳለቂያ አድርገው በሁዋላ ረሽነዋቸዋል።

እሱ ማኦ ከሞተ በሁዋላ በሩሲያ ኩሩቾብ ስታሊንን እንደተቸው፣ በአደረገው ድርጊቱ በኮምኒስት ፓርቲው ማኦም ተተችቶአል። ግን ሁሉም እንደተመኙት በዚያ አላቆመም።

ለዘመናት ይህ „ሒስና ግለሒስ „ የሚባለው የአሰራር ዘዴ ተረስቶ ከከረመ በሁዋላ አሁን ከፔኪንግ እንደምንሰማው፣ እዚህ የሚጻፉትም ጋዜጣዎች እንደሚመሰክሩት „በዚህ ወራት በትልቁ በቻይና የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በሊቀመንበሩ በሺ ጂንፒንግ ሰብሳቢነት ሥር ትላልቅ መሪ የአገሪቱ ካድሬዎች የተለመደውን የሒስና ግለሒስ ለቅሶ ማዥጎድጎድ „ ጀምረዋል።

የቻይና አመራር የተረሳውን እንደተለመደው „የጥፋት ሙሾ በቴሌቭዢን ለማውረድ ተሰባስቦአል“ በሚለው አርዕሰቱ ሥር „ሱድ ዶቸ ሳይቱንግ“ የተባለው የጀርመኑ ዕለታዊ ጋዜጣ የሚከተለውን ቁም ነገር ለአንባቢዎቹ አምዱ ላይ እንዲመለከቱት አስፍሮአል።

„አንደኛው አገረ ገዢ የእራሱን ገደብ ባለማወቅ“ ይኸው ጋዜጣ እንደሚለው እሱ በሰጠው ግለ-ሒስ ሙሾው „…ልቡን አሳብጦ፣ ሌላውን የሚንቅ ጥጋበኛ ፖለቲከኛ እራሱን አድርጎ፣ ያይ እንደነበረ“ አትቶ፣ ወደ ሌለው ዞር ብሎ፣ የቅስቀሳና የፕሮፓጋንዳው ኃላፊ ደግሞ „በመንግሥትና በሕዝብ ሐብት ምን የመሰለ ቅልጥ ያለ ድግስ እየደገሰ ገንዘብ እንደሚያባክን ተጸጽቶ፣ እራሱን እሰከማጋለጥ ድረስ ሄድዋል…“ ይኸውጋዜጣ ይለናል።

በሦስተኛ ደረጃ የፓርቲውን ዋና ጸሓፊ ጠቅሶ የሚከተለውን አረፍተ ነገር አስቀምጦአል።

„…ጥርሱን እየነከሰ ተጸጽቶ” በአደረገው ንግግር ” በዚያ ትልቁና ምቾት በአለው ላንድክሩዘር አውራጎዳናውን እየሰነጠቀ ሲከንፍ ምንኛ ደስታ ይሰማው እንደነበረ ካድሬው አስታውሶ አሁን ግን በሥራው አፍሮ…ተናዞአል…“ በሚለው አመለካከቱ አዚያ ያየውንና እዚያም የሰማውን „ቲያትር“ ለአንባቢዎቹ አቅርቦአል። ወደው ይሆን ተገደው?

ወረድ ብሎ ነገሩ በዚያ ተጀመረ እንጂ አላለቀም ይለናል።

በቴሌቭዢን የተጀመረው የኮሚኒስቶቹ ሙሾ ማውረድ ወደ ዕለታዊ ጋዜጣ ተሸጋግሮ፣ “ ከሁናንና ከዩናን እንዲሁም ከቾንግቺንግ ከተማዎች“ የሚከተሉትን አረፍተነገሮች ጸሃፊው አነበብኩ ይለናል።

„እንባ እየተናነቃቸው፣ በሰሩት ሥራዎቻቸው አፍረው ሁሉም ካድሬዎች ድርጊታቸውን፣ የቻይና ሕዝብ ጋዜጣ እንደጻፈው፣ ዘክዝከው አውጥተዋል።“

ዓላማው በአንድ በኩል በሕዝብ ዘንድ እየተጠላ የመጣውን የኮሚኒስት ፓርቲና አባሎቹን አንዴ ሊቀመንበር ማኦ እንደአደረጉት ሊቀመንበር xi Jinpingም ደግመው ከተነጣጠረባቸው ኢላማ „በሥልጣን መባላግ፣ በሙስና መጨማለቅ፣ …ጦር አውጄአለሁ ብለው“ ለማምለጥ ነው።

ሌላው ማኦ እንደደረገው -ይኸው ጋዜጣ እንደጻፈው- እግረመንገዳቸውንም ተቃዋሚዎቻቸውን በዚህ ዘመቻ ሳቢያ፣ አለፍርድ ቤት ክስ፣ አለ በቂ ምርመራና አለ ማስረጃ፣አለ ጠበቃ “ጥፈተኛ ናችሁ” ተብለው ተጠራርገው እንዲወጡ ለማድረግና ከእነሱም በዚህ ዘዴ በአጭሩ ለመገላገል ነው።

ሙስና ሆነ በሥልጣን መባለግን፣ ለመቆጣጠር፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲን ለማምጣት ይህ ነው የታሪኩ ሞራል „…ሂስና ግለ -ሂስ“ እንደ ሙሾ በቴሌቪዥን ላይ እያለቀሱ ማውረድ ሳይሆን መድሐኒቱ „…ነጻ-ፍርድ ቤት፣ ነጻ-ጋዜጣ ፣ ነጻ ሕዝብና ነጻ ውይይት፣ ነጻ- ምርጫና…ነጻ-ትችት…“ በአንድ አገር ማካሄድ ሲቻል ብቻ ነው።

“ጥፋተኛ ተብሎ የተጠረጠረውም ሰው” ጥፋቱ በነጻ-ዳኛ በፍርድ ቤት ታይቶ ፍርዱን እሰከሚቀበል ድረስ-የተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፍ የሰበአዊ መብት አዋጅ እንደሚለው-ይህ ሰው “ጥፋተኛ አይደለም።”

ሙስናንና በሥልጣን መባለግን ለመቆጣጠር (ሌላ ነገር ከጀርባው እስከሌለ ድረስ) እንደሚባለው “በሒስና በግለ ሒስ” አገር የቀናበት ቦታ የለም። የነፍስ አባት ጋ አለጠበቃ ተኪዶ “ንሰሃ መግባት”ይቻላል። እሱ ግን ሌላ ዓለም ነው።

እኛ የምንኖርበት ዓለም አለ ነጻ ጠበቃ አለ ነጻ-ዳኛና ፍርድ ቤት አለ ግልጽ የሆነ የዲሞክራቲክ ጨዋታና ሕጎች፣አለ ነጻፕሬስ እና አለ ነጻ ዜጋ ትርፉ የጥቂት አምባገነኖች “ራት” መሆን ነው።

የታሪኩም ሞራል የተባለውን ለመድገም ይህ ነው።

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s