ፍትህ ና ፍርድ

ፍትህ ና ፍርድ

ፍትህ ና ፍርድ

አረመኔ ሲገራ

ሕግና ሥርዓት፣ ደንብና መብት

የግለሰብ መብትና መብቶቹ

እንደ ሥልጣን ደስ የሚል፣ እንደ ሥልጣን የሚያጓጓ፣ እንደ ሥልጣን የሚያባልግና እንደ እሱም የሚያሳብድ፣ አሳብዶም አንድን ሰው „አውሬ“ የሚያደርግ ነገር የለም።

ያን ለመሆን ይህን ለማድረግ ደግሞ የዚያ ሰው ሁኖ በባህሪ መፈጠርንም ይጠይቃል።

አንድ ሰው እንደምንም ብሎ ሥልጣኑን እጁ ከአስገባ ደግሞ ያ ሰው „አረመኔ“ ለመሆን ለእሱ – ምንም የሚከለክለው ነገር ስለሌለ- በሩ ክፍት ነው።

የሥልጣን ኮርቻ ላይ አንዴ ከተወጣ ደግሞ ቦታው እራሱ… አትልቀቅም፣ አትውረድም ብሎ ይገፋፋል።

ሥልጣን ያለው ሰው እንደምናውቀው በሰው ሕይወት ሞትና ሽረት ላይ ይወስናል። ይህ ሰው የፈለገውን ሴትና ከረዳ አስገድዶም ቢሆን ይጠቀልላል። ከሰለቸውም ፈቶም ያባራል። በመቶና በሺህ የሚቆጠሩ ቁባቶቹን ቤተ-መንግሥቱ ውስጥ ይሰበስባል።

ያገኘውን ሐብት ይወርሳል። መሬት ያግበሰብሳል። ማዕድኑን ይቆጣጠራል። ንብረት ለእራሱና ለቤተሰቡ ያፈራል። ይህ አልበቃ ከአለው ደግሞ ይቀማል። ጎረቤቱንም ወሮ የጦር ችሎታ ከአለው ያስገብራል።

እዚያ ለመድረስ እንደዚያ ለመሆን ሦስት መንገዶች አሉ።

አንደኛው ከንጉሥ ዘር መወለድን ይጠይቃል። ሁለተኛው መንገድ በጦር ኃይል፣በኩዴታም በአመጽም ሥልጣንን ነጥቆ ወስዶ እጅ ማስገባት ነው። ሦስተኛው በምርጫ ነው።

ይህኛው ሦስተኛው በምርጫ ስልጣን ላይ የወጣው ገደቡንና የሥልጣን ዘመኑን ውስን መሆኑን በደንብ ያውቃል።

nazi-show-prozessግን ደግሞ ደስ ካለው ሒትለር

እንዳደረገው ሕጉን ሽሮ ሊሽረውም ይችላል እዚያው መሰንበት ነው።

ሁለቱ እላይ የተጠቀሱት አንዴ ሥልጣን ላይ ከወጡ ዕድሜ ልካቸውን ገዝተው ለልጆቻቸው ወይም ለጓደኞቻቸው ሥልጣኑን- ሁሌ ጊዜ ግን እነሱ እንደተመኙት አይሆንም እንጂ- „አውርሰው“ ያልፋሉ።

ስለ ሥልጣን ለመረዳት፣ ስለሥልጣን ለማወቅ፣ ሥልጣን ለማን? ሥልጣን ለምን? ሥልጣን እሰከ መቼ? የሥልጣን አስፈላጊነት? ሥልጣንና ፖለቲካ? ሥልጣንና ሕዝብ? የሚባሉትን ጥያቄዎች ለማንሳትና ለመመለስ ወደ ቀድሞው ታሪክ ወደ ሕግ አመጣጥና ወደ ሕግ ትርጓሜ ወደ ፍርድ አሰጣጥና የሥልጣን ክፍፍል በአንድ አገር ውስጥ መሄድ ያስፈልጋል።

የሰው ልጆች በመጀመሪያ የተሰባሰቡትና በአንድነት የቆሙት እራሳቸውን ከአውሬና ከሌላ ቦታ መጥቶ ወግቶ ማርኮ መሬታቸውንና ንብረታቸውን ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ቀምቶ እነሱን ባሪያ አድረጎ ሊገዛቸው ከሚፈልጋቸው ኃይል ለመከላከል ነው።

praying_hands_albrecht_durer

አብሮ ለመኖር፣ አብረው ሲኖሩ ደግሞ አንድ ሥርዓት አንድ ሕግ እንደሚያስፈልጋቸው የሰው ልጆች ሁሉ ይህን ሰለሚረዱና ስለሚያስቡ አስፈላጊነቱን በደንብ (አንዱ ጋ ጠንከር ይላል ሌላው ጋ ለቀቅ ወይም ጠበቅ) እነሱ ያውቁታል።

ይህ ለነጮች ብቻ የተሰጠ ተሰጥኦ አይደለም።

ሰዎች ከዚያም ተነስተው እንደ ጊዜውና ዘመኑም የራሳቸውን ሥርዓት መስርተዋል። ያ ሥርዓት ደግሞ ቆሞ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ – ይህ የትም ቦታ የሚታይ ነው – አንድ ( የረቀቀ ይሁን አይሁን ሌላ ነገር ነው) „የመተዳደሪያ ሕግ“ ሃይማኖትም ሊሆን ይችላል፣በመጀመሪያም እሱ ነበር የሰው ልጆች የሃይማኖት አባቶች ደንግገው አውጥተዋል።

ያን ሕግ ወይም ያን ደንብ ወይ የሃይማኖት አባቱ ወይ ጠንቋዩ ወይ ጅግናው ወታደር ወይም መሪው ንጉሥ መከበሩን፣ በሥራ መተርጎሙን በጋራ ወይም በየፊና ይቆጣጠራሉ።

ሕግ ወይም ደንብ የመጣው ሕግም የተነደፈው ሕግ የተዘረጋው ሕግ በሥራ ላይ እኩል እንዲተረጎም የተደረገው ሕግንም ሁሉም እኩል እንዲያከብር የተደነገገው አንዱ ጉልበተኛ ከመካከላቸው ተነስቶ ሌላውን ባሪያው እንዳያደርገው ነው። ከዚያም አልፎ አንዱም ከእነሱ መካከል ተነስቶ „አውሬ ሁኖ“ ሌላውን „አርዶምእንዳይበላውም“ ነው። china-hitlበአጭሩ ሕግ የወጣው የጠንካራውን የአረመኔዎች ድርግት ለማጠናከር ሳይሆን የሕይወት ነገር ስለሆነ እነሱን ለመቆጣጠር ነው። ከዚህም ተገላግሎ በሰላም ከመኖር ፍላጎትም የመነጨ ነው።

ስለ ሕግና ስለ መብት ስለ ዳኝነትና ስለ ፍርድ ሲነሳ ብዙ ነገሮችን ለአየና ለቀመሰ ለአንድ ኢትዮጵያዊ እንግዲህ ብዙ ነገሮች ከተፍ ብለው ዓይኑን መተውት ትዝ ይሉታል።

አንደኛው ከዚህ ሁሉ መካከል የታወቀው የሰለሞን ፍርድ ነው።ከእሱም ጋር በአገራችን የሚታወቀው የንጉሥ ችሎት ነው።

በሁዋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል። ጠበቃዎች ተምረው ወጥተዋል። የወንጀለኛ እና የፍትሓ ብሔር ሕጎች ረቀው ወጥተዋል።

ሁለተኛው ደርግ የሚባለው ፍጡር ከመሬት ተነስቶ አለፍርድ የወሰደው„አብዮታዊ እርምጃ“ የሚባለው ነገር ነው።

ሦስተኛው „ዲሲፕሊን አጎደላችሁ“ በሚለው ሳቢያ፣ በየድርጅቱና ነጻ አውጪ ነኝ እያለ በየተነሱት ኃይሎች፣ እንደዚሁ ጫካ ውስጥ በጥይት የተደበደቡ ወጣቶች ሕይወት ጉዳይ ነው።

አራተኛው አለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደዚሁ በአዋጅ የተወረሱ ቤቶች፣ መሬቶች፣ መኪናዎች፣ የባንክ ገንዘብና የግል ንብረቶች ቅሚያ ጉዳይ ነው።

አምስተኛው ከአለማዘዣ በማንም „የቀበሌ በአለሥልጣን“ የሚፈተሹ ቤቶች ሁኔታ ነው። ስድሰተኛው ጥፋታቸው ሳይመረመር አለፍርድና አለአንዳች ችሎት፣ አለጠበቃና አለ ማስረጃ እሥር ቤት ገብተው የሚማቅቁ ሰዎች ሕይወት ነው። ሰባተኛው…ለምን ጻፍክ፣ ለምን ተናገርክ፣ ለምን ተሰበሰብክ ተቸህ… ተብሎ አንድ ሰው በአገሩ እንደ አውሬ የሚታደንበት ሁኔታ ነው። ስምተኛው… ዘጠነኛው፣አሥረኛው ወዘተ እያለ ይሄዳል። አሁን ፍርድና ፍትሕ በኢትዮጵያ በአፍሪካ አለ?

ከአለስ ምን ይመስላል?

በሰለሞን ፍርድ እንጀምር።

የንጉሥ ሰለሞን ፍርድ ከእዚያ በፊት ከነበረው „…ዓይን ለዓይን ጥርስ ለጥርስ „ ከሚለው ከሓሙራቢ የፍርድ አሰጣጥ የፍርድ ፍጻሜና እርምጃ ይለያል።

በአጠቃላይ „… አትስረቅ፣ አትግደል፣ አታመንዝር፣ በሐሰት አትመስክር፣ የሰው ሐብት አትመኝ…“ከሚለውም ከሙሴ አሥርቱ ቃላት፣ ከታቦቱም ሕግጋት ይህኛው ተጨማሪ „አሥራ አንደኛ“ ስለሆነ ከእነሱም ለየት ይላል።

ያኛው የላይኛው የሙሴ ጽላት „የአኗኗር ዘይቤን“ በሰው ልጆች ዘንድ የሚደነግገው የሞራል ደንብ ነው። የኦሪት ህጎች በጥቅሉ፣ ይህን አታደርግ ያን ከአደርክ በሚሉ „በመከልከልና በቅጣት“ ላይ የተመሰረቱ ደንቦች ናቸው።

በጥበብ ላይ የተመሰረተው የሰለሞን ፍርድ ለአንድ ወገን ሳያዳላ ወይም በጭፍኑ እንደ „ሓሙራቢ ሕግም“ ነገር ሳያመዛዝን፣ ጊዜ ወስዶ ጉዳዩንና ችግሩን ጠለቅ ብሎ ሳይመረምርና ሳይመለከት „በጠፋው ጥፋት ልክ…ዓይን ከሆነ ዓይን እንዲጠፋ…“ በጥድፊያ ውሳኔ ላይ የሚደርስ ዳኝነት አይደለም።

የሰለሞን ፍርድ „ዕውነትን“ ፈልጎ፣ ዕውነትን አሽትቶ ለተነሳው ችግር፣ ዕውነትን ተመርኩዞ በጥበባዊ ዘዴ መፍትሔ የሚሰጥ ብየና ነው።

ዕውነትን ፈልጎ ማግኘት ደግሞ እንደዚሁ ቀላል አይደለም።

„ዕውነት“ ፍለጋ አስቸጋሪ ስለሆነ፣ እሱን ለመረዳት „ወንጄልን“ ለጊዜው ትተን ሃይማኖትን እንውሰድ።

በተለይ ሃይማኖትን አስታኮ ለሚወረወር ችግር „እርግጠኛና ዕውነተኛ“ መልስ ለመስጠት መሞከር በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ እናውቃለን። የጠለቀም ዕውቀት ቢኖረን (ሃይማኖት የለሽ ሃይማኖት ናቂ አቴኢስት ካልሆን በስተቀር እሱም ያጠራጥራል) ችግር ውስጥ እንገባለን።

ለመሆኑ የትኛው ሃይማኖት ነው በዓለም ላይ ከአሉት አምስቱ (ከዚያም ሊበልጡ ይችላሉ) ትላልቅ ሃይማኖቶች ውስጥ ዕውነተኛውና ትክክለኛው መንገድ የያዘው? ብለን እራሳችንን ብንጠየቅ መልሱ ከባድ እንደሆነ ለማንኛችንም ግልጽ እና አስቸጋሪ ፈተናም ነው። እላይ እንደተባለው አቴኢስቱ መልሱን አውቃለሁ ብሎ ሊነሳ ይችላል።

ግን ትክክለኛው – ቡዲዚም ነው ወይስ ሒንዱ? እስላም ነው ወይስ ክርስቲያን? ወይስ ደግሞ የአይሁድ ሃይማኖት?… ሃይማኖት የለሹ አቴኢስት እሱስ ትክክለኛ መንገድ የያዘ ሰው ነው? ወይስ አግኖስቲከሩ? ምናልባት ጴንጤው? ወይስ…ሺኢቱ? ወይስ ሱኒቱ?

ለመሆኑ ከእነዚህ ሁሉ መካከል ትክክለኛው ማነው ቢባል መገመት እንደሚቻለው „መልሱን“ አግኝቶ ለአንድ ሰው ማስረዳቱ በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደ እምነታቸውና እንደ አስተዳደጋቸው ከተለያዩ ሰዎች የተለያዩ መልሶችን በእርግጥ እንሰማ ይሆናል።

እነዚህ የተለያዩ መልሶች ደግሞ በሥነ-ሥርዓቱ ከአልተያዙ „ፍቅርን ሳይሆን ጠብን በሰው ልጆች መካከል እንደሚጭሩ“ መገመቱ ከባድ አይደለም።

ኢራክን ና ሶሪያን፣ አፍጋኒስታን ና ናይጄሪያን፣ …ኬንያን፣ …ማየቱ በቂ ነው።

እኔ ነኝ ትክክለኛ ተባብለው በየቀኑ እንደምንሰማው እነሱ ይገዳደላሉ።

እንግዲህ ለዚህ ነው እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ውስጥ ገብቶ „ፍርድ“ መስጠቱ አስቸጋሪ ነው የሚባለውም። በዚያው መጠን „የማይከባበሩና የሚናናቁ“ ሃይማኖቶችም ተከታይ አማኝ ለማፍራት „ የእኔ አምላክ ከአንተ አምላክ ይበጣል አትድከም…“ ብለው በያለበት እንደሚቀሰቅሱ ሁላችንም እናውቃለን።

ትልቁ ችግሩ የሚነሳው ደግሞ – እላይ የአንዳንድ አገሮችን ስም ጠቅሰናል- „ በእኔ ሃይማኖት ሥር እሱ በሚፈቅድልህ ሕግና ሥርዓት በዚያ ደንብ ብቻ መኖር አለብህ…“ የሚለው አዋጅ ሲታወጅ ነው። ያ አዋጅ የታወጀ ዕለት ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ሰክኖ የኖረ ሰላም „ደፈረሰ…ያኔ ተበላሸ“ ማለት ይቻላል።

በሻሪያን ሕግ ወይስ በኦሪት

ሕግ?በክርስቲያን ሕግ teheran-schauprozessወይስ በቡዲዚም? በሂስና በግለሒስ ወይስ በአብዮታዊ እርምጃ? በቡርዡዋ ሕግ (እንደዚህ የሚባል ሕግ የለም) ወይስ በሶሻሊስት ሕግ?…የትኛው ሥርዓት ነው ለሰው ልጆች ትክክለኛው? በየትኛው ሥርዓትና ሕግ ሥር መኖር ትፈልጋለህ? ቢባል ይህ የሚያጣላ፣ ይህ የሚያከራክር ነጥብ መሆኑ ከአለፉት ዘመናት ከአገኘነው ተመክሮ በደንብ እናውቃለን።

ታዲያ ለመሆኑ ሕግ ምንድነው?

ምንድነው ሰለሞን ያደረገው?

ሁለት አንድ ላይ ያደጉ አንድ ላይ የሚኖሩ እንደአጋጠሚም አንድ ላይ አርግዘው በአንድ ጊዜ የወለዱ ወጣት ልጃገረዶች – ታሪኩን ታውቃላችሁ- ነበሩ።

የአንደኛዋ ልጅ – አብዛኛዎቻችን የምናውቀው ታሪክ ነው በእሱ እንጀምር – በድንገት ታሞ ጡት እያጠባችው ደረቱዋ ላይ ይሞትባታል።

በዚያን ሰዓት ጓደኛዋ የእራሱዋን ልጅ አስተኝታ ወሃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ ወርዳለች። ተመልሳ ስትመጣ ትርምስና ጩኸት፣ ሁካታና ግርግር በእዚያ አካባቢ ያሉ ጎረቤቶች ይሰማሉ። ሲደርሱ ለቅሶ ነው። አንዱ ልጅ ሞቶ አልጋው ውስጥ ተጋድሞአል። ሁለቱ ሴቶች „የእኔ ልጅ ሞተ የለም የአንቺ“ እየተባባሉ ይጣላሉ።

ሁለተኛው ልጅ እቤት በቀረቺው ሴትዮ ክንድ ተጋድሞ „የእናቱን ጡት“ ይፈልጋል። አሁን የሞተው ልጅ የማን ነው የሚለው ጥያቄ ይነሳል።

ችግሩን ለመፍታት ጥበበኛው ንጉሥ ሰለሞን ፊት ይቀርባሉ።

የሚታወቀውን ታሪክ እናሳጥረው። ዳኛው አዝኖና ተክዞ ሁለቱም „የእኔ ነው የለም የእኔ ነው“ ብለው ስለ አስቸገሩና ስለ አስጨነቁት በመጨረሻው „በሰለሞናዊ ፍርዱ“ ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ በል „ ልጁን በሰይፍህ ለሁለት እኩል ሰንጥቀህ ለሁለቱም አከፋፍላቸው…“ ሲል ያቺ ልጅዋ የሞተባት ሴትዮ እጅ ነስታ፣ የንጉሱን ፍርዱን አመስግና ስትቀበል፣ የእናት ሆድ አላስችል ብሎአት ልጅዋ በሰይፍ ለሁለት ተሰንጥቆ ከሚሞትባት „… አትግደሉት! የሞተው ልጅ የእኔ ነው ይህኛው ልጅ ግን የእሱዋ ነው። ስጥዋት ጥፋተኛውም፣ ውሸታሙም እኔ ነኝ“ ብላ ትማጸናለች።

እንደምናውቀው በዚህ ሰለሞናዊ ፍርዱ ንጉሡ ልጁን ለወላጅ እናቱ መልሶ ሰጥቶ ያቺኛዋን ቀጥቶአታል።

ከሦስት ሺህ አመት በሁዋላ ዛሬ እንደዚህ ዓይነቱ ችግር ቢከሰት እዚያ ላይ ሁለቱን ሴቶች የሚያዳርስ ሙግት አይኖርም። በ ዲ ኔ ኤ ምርምራ በቀላሉ በትንሽ ደቂቃ እናትና ልጅን መለየትና ጥፋተኛዋ ማን እንደሆነች አጣርቶ አውቆ „መቅጣት“ ወይም „መገሰጽ“ ይቻላል። ያኔ ግን ይህ እንደዚህ ዓይነት ብልሃት አይታወቅም ነበር።

ከሰው ልጆች የፍርድ አሰጣጥ ታሪክ እንደምናውቀው በሁለቱ ዘመን መካከል – እላይ ከተጠቀሱት በዲ ኔ ኤ ምርመራና በሰለሞን ፍርድ – ብዙ ዓይነት አስፈሪ የሆነ የፍርድ አሰጣጥና አካሄዶች አይተናል። ሰምተናል። እንዴት እንደነበሩም አንብበናል።

በሰለሞን ፋንታ ፍርድ ሰጪው ሒትለር ቢሆን ኑሮ አለጥርጥር „ገና አሥር አሥር ልጆች ሁለታችሁም ትወልዱልኛላችሁ“ ብሎ እሱ ለዚሁ ሲል አስቀምጦ ወደ ሚቀልባቸው ጎረምሶች/መኮንኖች መንደር ( እንደዚህ ዓይነት የማረፊያና የመዝናኛ የልጆችም መፈልፈያ መንደር ያኔ ነበር) አታልቅሱብኝ ጥፉ ከፊቴ ብሎ ወደዚያ በየአመቱ ሕጻናት እንዲቀፈቅፉለት ይሸኛቸው ነበር። ወይም በመርዝ ጋዝ አይሁዶች ከሆኑ ደግሞ ፈጅቶ እንዲቃጠሉም ያደርግ ነበር።

rotkhmer

ለስታሊን ሆነ ለፖልፖት መልሱ ለእነሱም ቀላል ነው። stalin-process „… እኛ ሶሻሊዝምን ለመገንባት ስንጣጣር እናንተ ከማንም ጋር ትዳራላችሁ“ ብለው ከእነ ባሎቻቸው ወይም ከእነ ወዳጆቻቸው ወደ ሳይቤሪያ ወይም ወደ አንድ ገደል ለድንጋይ ፈለጣ ያሳናብቱአቸው ነበር።

„አለፈቃድ አረገዛችሁ“ ተብለው „አብዮታዊ እርምጃ“ የሚወስዱባቸው ኃይሎችም እንዳሉ፣ ከመውሰድ የማይመለሱ እንዳሉ እናውቃለን።

ሕግ ያለበትና ሕግ የሌለበትን ቦታዎች ለማሳየት ነው የሞተውን ልጅ ታሪክ ያነሳነው።

የተለያዩ ሃይማኖቶች ባሉበት በአንድ አገር፣ በሃምሳና በሰማንያ ሚሊዮን ከዚያም የሚበልጡ ሰዎች በአንድ ግዛት ውስጥ በሚኖሩበት አገር፣ የተለያዩ የሚፎካከሩና የሚቃረኑ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉንም እኩል የሚያስተናግድ አንድ ሕግ የግድ ያስፈልጋል።

ለምን ያስፈልጋል?

ሕግ አንድን ሕዝብ ያስተሳስራል። ሕግ አገርን አንድ ያደርጋል። ሕግ ሰላምንና ጸጥታን ፍቅርንና ወንድማማችነትን መተማመንንና መከባበርን፣ መረዳዳትና በሰው ልጆች መካከል ያመጣል። እራስን ችሎም መኖርን ለግለሰቦች ያስተምራል። ከዚያም ጋር ሕግ አንዱን ከአንዱ ሳይለይ ለግለሰቦች እኩል መብትና ነጻነታቸውን እኩል ደንግጎ የበላይና የበታች ሳይል ያስቀምጣል።

ለመሆኑ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው አንድ በአለሥልጣን ሚኒስትርና አንድ ተራ ሰው በሕግ ፊት ሁለቱ እኩል ናቸው? የጦር መኮንኑ እና አንድ ጋዜጠኛ፣ አንድ ደራሲና አንድ የአገር መሪ ፕሬዚዳንት እነዚህ ሁለቱ እኩል ናቸው?

መለዮ የለበሰው ወታደርና ተማሪ፣ አንድ ለማኝና አንድ የባንክ ገዢ፣ አንድ አስተማሪና እንዲት ተማሪ በሕግ ፊት እኩል ናቸው? ጄነራሉና ተራ ወታደሩ፣ የቢሮ ጸሓፊና ሥራ አስከያጁ፣ አሰሪና ሰራተኛው፣ አባትና ልጅ በሕግ ፊት እኩል ናቸው?

ጠቅላይ ሚኒስተሩና ሚኒስትሮቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ታክሲ ነጂው፣ ኩሊውና እህል አስፈጪው፣ ንግሥቲቱና አትክልት ኮትኳቹ፣ ጳጳሱና ሹፌራቸው፣ እነዚህ ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ናቸው?

ሁሉም በሕግ ፊት አዎን አንዱ አንዱን የማይበልጠው እኩል ሰዎች ናቸው።

በሰለሞን የጀመረው ጥበብ በሔለኒስቲክ ዘመን የተስፋፋው ዕውቀትና ፍልስፍና በሮም የግዛት ዘመን መልክ የያዘው ሕግና ሥርዓት በሁዋላ “በጨለማ ዘመን” በዳርክ ኤጅ ያ ሁሉ በጥቂት የሰው ልጆች ድካም የተደረሰበት የዕውቀት ደረጃ እንዳነበር ሁኖ ይዳፈናል። ለምን ተዳፈነ?

ምክንያቱ ምንድነው? ይህ እራሱን የቻለ የምርምር ክፍል ነው። ብቻ ችግሩ የመጣው “ከሃይማኖት ጠንክሮ መውጣት ነው” የሚሉ አሉ። ወይም የትላልቅ መንግሥታት መውደቅና የሽፍቶች በአውሮፓና በሌለው ዓለም እንደ አሸን መፍላትና ብቅ ማለት ነው የሚሉም አሉ።

ቀስ በቀስ ተራ በተራ ጠፍተው የነበሩ ጽሑፎች በመካከለኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ይሉና በአውሮፓ ገዳማት ይተረጎማሉ። ሳይንስና ምርምር ዳዴ እያሉ ከወደቁበት ቦታ እየፈሩና እየቸሩ አንገታቸውን ያውም በጥንቃቄ ያነሳሉ። ሲመራመሩም ነበልባል እሳትም የበላቸውም ጭንቅላቶች አሉ።

ትምህርት ተስፋፍቶ፣ አንጎልም ክፍት ሁኖ….ጥያቄዎችም በዝቶ “ነገሥታትንና መሣፍንትን፣ የሃይማኖት አባቶችንና የቤተ-ክርስቲያን አለቆችን፣ ወግና ልማድን፣ ሥርዓትና ደንብን፣ አስተዳደግን፣ አስተሳሰብን የሚተቹ፣ የሚቃወሙ፣ እንዲታረሙ የሚጠይቁ፣ ይቀየር” የሚሉ ምሁሮች በያለበት ይነሳሉ።

ምሁሮች የነጻነትንና የሰው ልጅ የእኩልነትን ጥያቄ፣ የዲሞክራሲና የግለሰብ ሰበአዊ መብቶችን ጉዳይ አንስተው መከራከር ይጀምራሉ።

ይህን የግለሰቦችን ነጻነት ጥያቄ ለማንሳት ሆነ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት አንዳንዶቹ አሁን እንደሚሉት „ከልማትና ከዕድገት፣ ከእንዱስትሪ ፋብሪካ ቤቶች መስፋፋትና እሱም ከፈጠረው የሠራተኛው መደብ ጋር „ ምንም የሚያያይዘው ነገር የለም።

ለመናገር ለመተቸት፣ ለመቃወምና ለመደገፍ ለመምረጥና ለመመረጥ፣ የእኩልነት መብትን ጥያቄ ለማንሳት፣ ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ ለመኖር „በመጀመሪያ የፋብሪካ የኢንዱስትሪና የሠራተኛ መደብ ዕድገት “ የሚባል ቲዎሪም ያኔ አልነበረም። እንደዚህ የሚባል ነገር የለም።

እነቶማስ ጄፈርሰን ናቸው ከእንግሊዝ ንጉሥ የዘውድ ቅኝ ግዛት እነሱ እነደአሉት “ነጻ ለመውጣት” የፈላስፋውን የጆን ሎክን የሰበአዊ መብት ትምህርት (1632-1704) ለቀም አድርገው አሜሪካን አገር ትግላቸውን የጀመሩት።በሁዋላ ሕገ-መንግሥታቸውን ነድፈው ቋሚ አድርገው ያስፋፉት።

ሎክን ተከትለው እነቮልቴር፣እነ ዴኒስ ዲደሮ እነ ጃን ጃክሩሶ…(እንመጣባቸዋልን) ይቀጥሉበታል።

የፈረንሣይ አብዮት ነው „አንድ ንጉሥ፣ አንድ ሕግ፣ አንድ ሃይማኖት“ ብለው አገሪቱን ይገዙ የነበሩ ነገሥታትን ሽሮ ሰበአዊ መብትን ያወጀው።

ሌሎች አብዮቶችም አለምን ይወራሉ።

ሌሎቹ አብዮቶች የሩሲያ ሆነ የቻይና የኪዩባ ሆነ የኢትዮጵያ፣ የቬትናም የካምቦጂያ፣ የሰሜን ኮሪያ ወይም የሊቢያ፣ የግብጽ፤የሱዳን፣ …ብቅ ይላሉ።

እነሱ ግን በተቃራኒ ያመጡት የተገላቢጦሹን ነው። በዲሞክራሲ ፋንታ አምባገነንነት ነው።

“በአንድ ንጉሥ ቦታ” ይህ ነው ሓቁ የአንድ ሰው፣ የአንድ ቡድን፣ የአንድ ፓርቲና የአንድ ድርጅት አምባገነን ሥርዓትን ነው።

ይህ ደግሞ የማርክስና የኤንግልስ፣የሌኒ እና የስታሊን ሥራ ነው።

ለምንድነው በምዕራቡ ዓለም ሰበአዊ መብቶች የተከበሩትእላይ በቆጠርናቸው በምሥራቁና በአፍሪካ አገሮች የማይከበሩት?

ለምንድነው በሕግ ፊት በምዕራቡ ዓለም የሰው ልጆች እኩል የሆኑትለምንድነው በአፍሪካና በቻይና በሩሲያና በኮሪያ…በኪዩባ የሰው ልጆች በሕግ ፊት እኩል ያልሆኑት?

china-kultrevo

ለምንድነው መተቸት መቃወም መምረጥና መመረጥ፣ መደራጀትና መወዳደር በአንዳንድ አገሮች የተፈቀደው በሌሎቹ የተከለከለው? ወይም ለምድነው አንደኛው ወገን ሳይመረጥ ተመረጥኩ ብሎ የሚያጭበረብረው?

ለምንድነው በአንዳንድ አካባቢ ስለ የግለሰቦች ሰበአዊ መብት ሳይነሳ፣ እሱ ሳይከበር ስለ ብሔር /ብሔረሰቦች መብትና እኩልነት ብቻ የሚወራው? በሌላው አካባቢ ለግለሰብ መብቶች ቅድሚያ የሚሰጠው?

መልሱ ቀላል ነው። ሥልጣን ለመውጣት፣ ሥልጣን ላይ ለብዙ አመታት እስከ ዕድሜ ልክ ለመቆየት፣ ሥልጣንን ለማውረስ፣ ሥልጣንን ይዞ ሰውን ለመቆጣጠር፣ የዲሞክራሲና የግለሰቦችን ሰበአዊ መብቶች ማወቅ፣ በሥራም ተርጉሞ ማክበር፣ ለገዢው መደብ አደገኛ እንደሆነ እንደሚሆን ያውቃሉ።

አስተዋይ አንባቢ እንደሚረዳው ፣ ኢንላይትመንት ከጨለማ ወደ ብርሃን የሰው ልጆች እንደገና በአደረጉት ጉዞ ሁለት መንገዶችን ነው የተከተሉት። አንደኛው የእነሎክ፣የእነ ቮልቴር፣የእነ ቶማስ ጄፈርሰን…የአሜረካንና የፈረንሣይን የእንግሊዝን መንገድ ነው። ሁለተኛው የማርክስና የሌኒን የስታሊንና የማኦ …የእነፓልፖትን መንገድ ነው። ሦስተኛው በሃያኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያለው የሒትለርና የሞሶሊን የፋሽሽቶች አምባገነን ሞዴል ነው።

ለምንድነው ምዕራቦቹ የመጀመሪያውን መንገድ መርጠው የተከተሉት? ለምንድነው የዲሞክራሲመብቶችን ለእራሰቸውም፣ ለሕዝቡም፣ ለሁሉም እኩል የሰጡት መብቱን የሰጡት? መብቱን እኩል የተጋሩት አለ ሕግ አይደለም። መብት ገደብ አለው። ምን ዓይነት ገደብ?

የሰው ልጆች አንድ ወጥ ሳይሆኑ የተለያዩ መሆናቸውን ስለሚያውቁ ነው። የሰው ልጅ ቁጥጥር ከአልተደረገበት አውሬ መሆኑን ስለተገነዘቡም ነው።

እላይ እንደተጠቀሰው ዲሞክራሲና የዲሞክራሲ ሥርዓት፣ የግለሰቦች ሰበአዊ መብቶች መከበር ሕግ የመጣውና የወጣው ፈላጭ ቆራጩን ንጉሣዊ አገዛዝን ከመቃወም ነው። ይህ አንደኛው ምክንያት ነው።

ሁለተኛው፣ ዓለም አቀፋዊው የሰበአዊ መብት አዋጅ የታወጀው አረመኔውን የሒትለርንና የሞሰለኒን ሥርዓት ተመልሶ እንዳይመጣ ለማገድ ነው።

ሌላው ምክንይት ያኔ በሥነ-ሥርዓቱ የአዋጁን መልዕክት ያዳመጠው ሰው የለም እንጂ የሚፈራውን „የኮሚኒስቶቹን አምባገነን ሥርዓት“ በዓለም ላይ እንዳይስፋፋም ለማገድ ነው።

ቁጥጥር የሌለው፣ ቁጥጥር የማይደረግበት ሥርዓትና ገዢ የፈለገውን ስም ይያዝ አደገኛ ነው። ስለዚህ አንዱ ክፍል ሌላውን ክፍል እንዲቆጣጠረው ተደርጎአል። የሥልጣን ክፍፍል፣ የሥልጣን ሽንሸና፣ የሥልጣን ተዋረድ፣ የሥልጣን ገደብ፣ የሥልጣን ተቆጣጣሪ፣ ክፍሎች ወደላይና ወደታች፣ ወደጎንና በዙሪያ ጥምጥም ተዘርግተዋል።

ብዙ ቦታ እንደምናየው ሁሉም መንግሥታት “ሸንጎ-ፓርላማ” የሚባል ሕንጻ አላቸው። ግን ሁሉም ሸንጎ አንድ አይደለም።

በምዕራቡ ዓለም ሽንጎውን የሚቆጣጠረው ክፍል አለ። ሕግ አውጪ እና የሕግ መምሪያ የሕግ አስፈጻሚም ክፍሎች አሉ። እዚሁ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሽንጎ ውስጥ ወንበር አላቸው። ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ የሆኑ የሙያ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋሞች፣ የሲቢል ድርጅቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ደራሲና ጸሓፊዎች፣ ሠልፍና አቤቱታዎች፣ የሴቶችና የወጣቶች፣ የአሰሪና የባለጸጋዎች፣ የአዛውንትና የስፖርት…እነዚህ ሁሉ ዓይናቸውን በባለሥልጣኖች ላይ ጥለው በቁራኛ የሚከታተሉ ክፍሎች ናቸው።

ይህን ማድረግ ሁሉም ቦታ ይቻላል? አዎን ይቻላል። ሥልጣን ላይ የተቀመጠው መንግሥት አሻፈረኝ ከአለስ?

Rule-of-law

በአደባባይ ጩኸት፣ በተቃውሞ አመጽ ሕገ-መንግሥቱን እንዲያከብር አለበለዚያም ቦታውን በሕዝብ በተመረጠ ለሌላ ችሎታ ላለው ለሚሰራ ኃይል እንዲለቅ ይደረጋል። ሥልጣን በየአራት አመቱ በምርጫ እንዲወሰን ይደረጋል። ለዕድሜ ልክ የሚሰጥ የሚታደል ሥልጣን በ21ኛው ክፍለ-ዘመን የለም።

ለዚህ ደግሞ በቂ ምሳሌዎች አሉ።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

———

[1] ሔሊኒስቶች ከሰለሞን በሁዋላ ብቅ ይላሉ። የእነሱ ትምህርትም ብርሃንን ይገልጣል።

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s