የሰው ጉዳ ጉድ ድንቅ ቢላቸው
አያዩ አይሰሙ ትንፋሽ የላቸው
እኒን ጦጣዎች ምን ገጠማቸው ?
ትንሽ ራቅ ብሎ እነዚህ ጦጣዎች ፊት ምን እንደሚደርግ… ምን ተደርጎ እነሱን እንደዚህ እንዳስደነገጣቸው የሚታወቅ ነገር የለም።
ጥሩ ነገር እንዳልሆነ ግን መገመት ይቻላል።
በግልጽ የሚታየው፣ አንደኛው ጦጣ ይህን ሁሉ አልሰማም ብሎ ጆሮውን መያዙን ብቻ ነው። ሌላው ዓይኑን መጨፈኑን ነው።ሶስተኛው ደግሞ አፉን ይዞ አለመናገር መምረጡን ነው።
ምናልባት እናታቸው በአንዱ ትደበደብ ይሆን? ስትደበደብ እዚያ መኖሩ እንዳይታወቅ ደንግጦ ይሆን፣ እንደኛው ደርቆ አፉን ይዞ የተቀመጠው? ለመሆኑ ማንን ፈርቶ ነው እንደዚህ አፍጦ የሚያየው?
ምን ይታወቃል፣ ምንአልባት አባታቸውን አንዱ ሲገድለው ወይም ሲገርፈው አይተው ይሆናል ኮሽ እንደይል ጸጥ ለጥ ብለው የሚያዩት። ከአሁን አሁን እንዳይታዩ ዝም ብለው እየተንቀጠቀጡ የሚመለከቱት።
… ቤታቸው፣ መንደራቸው፣ ወይም ዛፋቸው ተቃጥሎም ይሆናል።አንዱ ተንኮለኛ በለኮሰው እሳትም አካባቢው እየጋየም ሊሆን ይችላል።
ወይስ ሌላ ወንድማቸውን አንዱ አውሬ ሊበላው ማጅራቱን ይዞ እየጎተተው ነው። ይህም ሊሆን ይችላል። እህታቸውን አንዱ ጠልፎአትስ ቢሆን? ሕግ በሌለበት ጫካ ውስጥ የማይሆን ነገር የለም።
አንድ የድርሰት ወይም አንድ የኪነት ሰው፣ ወይም ደግሞ አንድ የጽሑፍ ወይም የጋዜጣ ሰው፣ እነዚህን ሶስቱን ጦጣዎች አይቶ ብዙ ልብ ወለድ ነገሮችን ማንቆርቆር፣ መዘርገፍ፣… ማሳየት ይቻላል። ግጥሞችም መግጠም አይከብድም።
ጃፓኖች ይሁኑ ቻይናዎች (እሰከ አሁን ድረስ ማን እንደሆን አይታወቅም ሁለቱ ናቸው የእነዚህ አሻንጉሊቶች ታሪክና ምሳሌ፣ ጠፍጣፊና ፈጣሪ) ይህን ነገር ሲያስቡ ከአንድ „የሰው ልጆች“ መጥፎ ሥራ ተነስተው እንደሆን አለጥርጥር ዛሬ ሁላችንም መገመት እንችላል።
ምን ይታወቃል፣ ጎረምሶች ጦርነት ከፍተው ይከታከቱ ይሆናል። አምባገነኖች መንደሩን ይዘው፣ ሽፍቶች አካባቢውን ተቆጣጥረው፣ አክራሪዎች አዲስ አዋጅ አውጀው፣… አዲስ ትምህርትና ፍልስፍና ተስፋፍቶ፣…ፈላጭ ቆራጭ ቶታሊቴሪያን አገዛዝ ሰፍኖ፣ ሕዝቡንም፣ አገሩንም ሲያሰፈራራ ሊሆንም ይችላል።
ቅርጾቹ:- የእነዚህ የጦጣዎቹ፣ በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ-ዘመን ብዙ ትርጉም ያዘሉ ናቸው።