*ዕ ን ቁ ጣ ጣ ሽ *(ርዕሰ አንቀጽ)

*ዕ ን ቁ ጣ ጣ ሽ*

 newyearjpg

አንድ የሚያደርገንና አንድ ያደረጉን ነገሮች ብዙ ናቸው።

አንደኛው አለጥርጥር ዕንቁጣጣሽ ነው። ይህን የሚክድ ሰው ከአለ ኢትዮጵየዊ እሱ/እሱዋ አይደሉም። ቀልዱ እዚህ ላይ ያቆማል። 

ኢትዮጵያን በዚያውም እኛን አንድ የሚያደርግ ነገር ቢኖር ይህ ዛሬ ሁላችንም የምናከብረው አዲሱ አመት ነው።  

ሁለተኛው የሰዓት አቆጣጠራችን ነው።  ሶስተኛው ልዩ የሆነው የምግብ አሰራራችን ነው። አራተኛው የዘመን መቁጠሪያችን ነው።  ቅርጫና በመሶብ ዙሪያ አብሮ መብላትም አለ።  

አምስተኛው ምርቃቱም ነው።  ከሁሉም የምናምንበት አሃዱ አምላከችንም አንደኛውና መዚጊያው ነው።  

ስድሰተኛውና ሰባተኛው፣ ስምንተኛውና….ዘጠነኛው….

የቡሄና የገና ጫዋታ፣ …አበባዬ ሆይ፣ ሙዚቃው፣  ትዝታና ሰርጋችን፣ ዕድር ዕቁባችን (…በአንዳንድ ነገር የተበሳጩ ልጆች፣ ሌላ ጊዜ ፈልገው በአገኙት ነገር ተደስተው ያናደዱአቸውን ጓደኞቻቸውን መልስው በተራቸው ሲያበሽቁ „ኤቺ ቤቺ…ይኸው እየው፣ ተመልከተው፣ … እኔም አለኝ…“ ልጆች ተንኮለኛ ናቸው እዚህ ይላሉ) እነዚህ ሁሉ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ናቸው።  በዚህ አያቆምም ሌሎቹም አሉ።  

የሆነው ሁኖ፣ እነዚህ ሁሉ ባህሎቻችን እኛን ከሌሎቹ እንደለ „ፍጹም ልዩ“ ያደርጉናል።

አዋቅረው አያይዘው አንድ አድርገው የያዙን ብዙ ናቸው።  ይህ ደግሞ ቢሉት ቢገፉት፣ ለመፋቅ ቢሞክሩት  አይፈቅም። ይህ በቀላሉ አይሰረዝም። ይህ ከአእምሮ አይጠፋም። ይህ ወደዱም ጠሉም ሕያው ሁኖ ለመጪው ትውልድም የሚተላለፍ ባህል ነው።

አንድ ጊዜ ከጸሎት በሁዋላ አዲሱን አመት ለማክረበር ወደ አንድ አዳራሽ ተያይዘን ስነገባ አንድ እንግዳ ፈረንጅ እኛን አይቶ የማያውቅ (ይመስለኛል ከሴት ጓደኛው ጋር አብሮ የመጣ) ሲተዋወቀን የአንዱን ጓደኛችንን ስም መሓመድ መሆኑን ሰምቶ ተገርሞ „…እንዴ እርሶም እዚህ ይመጣሉ እንዴ?“ ብሎ ሲጠይቀው“ እኔ እኮ ጌታዬ ሞስሊም እንጂ አረብ አይደለሁም „ ያለው መልሱ አይረሳም።

በሁዋላ በደመራ በመስቀል በዓል ላይ ይኸው ሰው፣  ሌላውን „ሐሰን“ የሚባለውን አንዱን ኢትዮጵያዊ ያገኘዋል።  ምን እንደተባባሉ መገመት ለአንባቢው መተው በቂ ነው።  

ክርስቲያኑም እስላሙም፣ አይሁዱም ጭምር (እነሱ ቤተ-እሥራኤሎቹ አሁን ወጥተው አልቀዋል ይባላል) አዲሱን አመት አብረው አንድ ላይ ያከብራሉ።  የዶሮ ወጡ አንድ ነው።  የቡና አፈላል ሥርዓቱ ( ሌላ ሳይሆን ) አይለያይም ያው አንድ ነው።  Coffee_Ceremony_1_Ethiopia

 የጠላ አጠማመቁ፣  የጤፍ እንጀራው፣ ፍትፍቱ፣ አገልግሉ፣  (ልጆች ምን ይላሉ እንደዚህ ዓይነቱን ነገር ብለናል…ኤች ቤች!) ድፎ ዳቦው፣ ሽሮው፣ በርበሬው፣ … የሸማ-ልብሱ፣ ጥጡ(ቀለሙ ይለያይ እንጂ) ነጠላው፣ ጋቢው፣ ቡሉኮው፣ ፈትሉና ሸማኔው ያው አንድ ነው።  ቅመሙም አንድ ነው። ኢትዮጵያም የተቀመመችበት ቅመም፣  ምሥጢሩም ይኸው ነው።  ግን ደግሞ የአንድነታችን ምሥጢሩ  ከዚህም አልፎ ይሄዳል።

 

የቤተ-ክርስቲያኑን ቁልፍ እስላሙ በታመኝነት ተረክቦ ይጠብቃል።  አጎቱና አክስቱ እስላም ወይም ክርስቲያኑ የሆኑ ጥቂት አይደሉም።  በጋራ የጉልበት ሥራ በደቦ ድሮም አሁንም ኢትዮጵያኖች ይገናኛሉ። ይረዳዳሉ።  

አብረው ያጭዳሉ።   በጋራ መንገድ ይጠርጋሉ።  በአማርኛ ቋንቋ ይነጋገራሉ።  ይገበያያሉ።  እንቅፋት ሲመታቸው የማይተዋወቁ ሰዎች መንገድ ላይ „ወንድሜን“ ይባባሉ።  ሲያስነጥሰው „ይማርህ/ይማርሽ „መንገድ ላይ ሰላምታ ይለዋወጣሉ።  ይህ የት ቦታ አለ?

በዛሬው ዕለት ደግሞ ልጆች ተሰብስበው፣ ዘር ሳይቆጥሩ ፣ ሐብት ሳያራርቃቸው፣ ሃይማኖት ሳይሉ፣  በአንድነት „አበባዬ ሆይ“ ይላሉ።  

ጎረቤት ጎረቤቱን ያምናል። ጓደኛ በአብሮ አደጉ ይተማመናል።  …በፍቅር ላይ የተመሰረተ የተደበላለቀ ትዳር በብዛት አለ።  ከእነሱም የወጡ ልጆች በያአለበት በየመንደሩና በየአገሩ ተሰማርተዋል።  ተበትነዋል።  

እንግዲህ ኢትዮጵያና ልጆቹዋ ድሮም እነደዚህ ነበሩ።   ዛሬም እንደዚህ ናቸው።  ይህ ነው እኛን ኢትዮጵያቾችን ከሌሎቹ ለይቶ „ልዩ“ የሚያደርገን ነገር።  ቢያንስ በዚህ በመስከረም ወር አዲሱን አመት (2006ዓ.ም)የሚያከብር ሕዝብ እኛ ነን።  

ይህ የት ይገኛል?

ሌሎች እኛን አንድ የሚያደርጉን ነገሮችም አሉ።  

እሱም ለሰበአዊ መብትና ለነጻነት ያለን፣  ወራሪ ነጮች ግን ሊረዱት የማይችሉት፣  የቆየ ጥማታችን እንዳለ ነው።  ለዚህ በማይሸጠውና በማይለወጠው ቀናተኛ የተፈጥሮ ነጻነታችንና መብታችን፣  አገራችንን ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ፣  ከቱርክና አረቦች ሴራ፣  ከፖርቱጋል ሙከራ፣  …አባቶቻችን አድነዋል።  

አሁን የሚቀረው ደግሞ  (ደግመን ደጋግመን የምናነሳው) ዕውነተኛው የግለሰብ መብቶች እንደገና፣  ለመናገር ያ! አምላክ  የሰጠንን የተፈጥሮ ጸጋ ሙሉ ሰበአዊ መብታችንና ነጻነታችንን አለአንዳች አምባገነን ፍርሃቻ እሱን ማስከበር ነው።  

ይህ ደግሞ አንዱን ከሌላው ሳይል አንድ የሚደርገን የ21ኛው ክፍለ-ዘመን፣  ግዳጅም ኃላፊነትም፣  መድረሻናግብም፣  የጉዞ መንገድም፣ የጋራ እሴትም ነው።  

ይህን አስመልክተን ስለ ፓርላማ ሥርዓት (ስለ ሸንጎ) አንድ ጽሑፍ እንድትመለከቱት አቅርበናል።  እዚያም ላይ ስለ ሶሰት ሥርዓቶች አንስተናል።

ስለ ሃይማኖት አክራሪዎች መንግሥት፣  ስለጠበንጃ አንጋቢዎች ሥርዓትና ስለ ዲሞክራቲክ ሕብረተሰብ፣  ከብዙ በጥቂቱ ዘርዝረን አልፈናል።  

 „አንድ ሕልም አለን“ ያ የእኛ የዘንድሮው ምኞትና ሕልማችን (እሱን እንናገር ከተባለ) እዚያ የሸንጎ አዳራሽ ውስጥ የተለያዩ ስምና ቀለም ያላቸው ድርጅት ተወካዮች ወንበሮቹን በምርጫ በአገኙት ድምጽ ተከፋፍለው ቦታቸውን ሲይዙና፣  ተዝናንተው አዳራሹ ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ ማየት ነው።

የተለያዩ ድርጅት ተወካዮች ከተከራከሩ በሁዋላ ቢራቸውንና ቡናቸውን አብረው ተገባብዘው ሲጠጡ ማየት ነው።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ወረድ ብላችሁ ደግሞ ሌላውን ጽሑፋችንን ተመልከቱት።

እንደምናውቀው ፣  ሃይማኖትና ባህል፣  ልማዶችና የኑሮ ዘይቤዎች፣  ታሪክና ምሳሌዎች….አንድን ሕዝብ አንድ የሚያደርጉ ክስተቶች ናቸው።  ከእነሱ ጋር የጋራ እሴትም/እሴቶችም የሰውን ልጆች አንድ ያደርጋሉ።  አለበለዚያ የአውሮፓን አንድነት፣  የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት፣  የሰሜን አትላንቲኩን የጦር ቃል-ኪዳን…ወዘተ መረዳት አይቻልም።

ከዚያ ውስጥ አንዱ እሴት ፓርላማና የነጻ ሰው መብት የሚለው ፍልስፍና ነው።

እንግዲህ ይህን እሴት አንስተን መልካም አዲስ አመት እንመኝላችሁዋለን።  መልካም አዲስ አመት ለእናንተም 364 ቀናቱን በሙሉ  በተከታታይ „እኛ“ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ለምትሉትም ወገኖቻችን ሁሉ አብረን እንመኛለን።  

ምክንያቱም ቢያንስ-ይህ ነው መነሻ ሐሳባችን- የዛሬው የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ቀን ሁላችንንም አንድ ያደርገናል።

አንድ ሕልም አለን ያ ሕልምም ለመድገም „ማንም…ፖለቲከኛ „ነን የሚለው ሰው ሁሉ አደባባይ ወጥቶ ተወዳድሮ በአገኘው ውጤት ፓርላማ ገብቶ ወንበሩን ሲይዝ ማየት ነው።  

ጠበንጃ እና ድርጅት ግን ከሁሉ በፊት፣  በመጀመሪያ፣  ልክ እንደ መንግሥትና ሃይማኖት፣ ሁለቱ መለያየት ይኖርባቸዋል።  መለያየትም አለባቸው።

 

የሰላም የጤና እና የዲሞክራሲ መት።

 

——

የመከረም 2006/September 2013 ልዩ እትም * ዕንቁጣጣሽ *

 

 

  

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s