ውርሰ፥ቅርስ

header-limimid
ውርሰ፥ቅርስ
በየቤቱ ብዙ ሰነዶች እንደአሉ መገመት ከባድ አይደለም። የተማረው ክፍል በሕብረተሰቡ ውስጥ ብዙሃኑን አይያዝ እንጂ፣የጽሑፍ ፊደል ከጥንት ጀምሮ በሚታወቀውና በሚገለገልበት በኢትዮጵያ ምድር፣ ወረቀት ላይ ሳይሰፍሩ ተረስተው የቀሩ ነገሮች አሉ ብሎ መገመት በጣም ይከብዳል። ቢያንስ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ፣ የገበሬ ቤትም ቢሆን አንድ ልጅ ለቤተ-ክርስቲያን አገልጋይነት ይሰጣል። በዚያውም ያ ልጅ (ቁጥሩን በደንብ አናውቅም እንጂ)… ድቁናና ቅስና ባይቀበልም ፊደል ቢያንስ እንዲቆጥር ይደረጋል።
በጥንታዊ ገዳሞቻችን እና በየቤተክርስቲያኑ አድባራት፣ ረዥም ዕድሜ ያላቸው ጥንታዊ ጽሑፎች፣እንደ ጥንታዊው ዛፎች፣ ተደርድረው እንደሚገኙ እናውቃለን።
ዘራቸው ሌላ ቦታ የማይገኝ፣ በቅጥር ግቢው ውስጥ የቆሙትን ጥንታዊ የአገራችንን ዛፎች፣ እንኳን ከቅርቡ ከሩቁም አፋፍ ላይ ስለሆኑ በደንብ እናያቸዋለን። በሌላ በኩል መጻሕፍት፣ በየአለበት አሉ ይባላል እንጂ እነዚህ መጻሕፍት ምን እንደአዘሉ፣ ምን እንደተሸከሙ ምን ዓይነት ምስጢራዊ መልዕክቶች ለትውልዱ እንደያዙ ምንም የምናውቀው ነገር የለም።… አናውቅም።
እንደዚሁ የአገራችን ሥዕሎች፣ ድርሰቶች፣ግጥሞች፣ እራሱ የምግብ ዝግጅትና አሰራር፣ ስንት እንደሆኑ? የት እንዳሉ? በማን እጅ እንደሚገኙ- የተመዘገበ፣የተጻፈ ነገር ስለ ሌለ፣ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። እንዲያው ብቻ „…የባላበት፣የፊውዳል፣የአቆርቋዥ…ባህል…“ ጥራዝ ነጠቆች እያሉ ሁሉን ነገር አጥላልተውት ዞር ብሎ የአገሩን ቅርስ የት ደረሰ? ምን ሆነ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ጠፍቶአል።
በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ብዙ ተማሪዎች ለትምህርት ወደ አውሮፓና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ፣ወደ ሰሜን አሜሪካም እንደሄዱ እናውቃለን። እነዚህ ሰዎች በወጣትነት ዘመናቸው ምን እንደጻፉ፣ ምን እንዳጠኑ፣ ለየትኛው የጥበብና የዕውቀት ክፍል ልባቸውንና አእምሮአቸውን ሰጥተው በዚያ እንደተሳቡ –አንዳንዶቹ በእርግጥ ጽፈዋል- ስለሌሎቹ ብዙም የምናውቀው፣ምንም ነገር የለም።
ጳውሎስ ኞኞ- ነፍሱን ይማረውና- አንዴ በርሊን መጥቶ ሲያጫውተን፣ ትልቁ ቤተ-መንግሥት ውስጥ፣ ስለ አጼ ምኒልክ ታሪክ ለመጻፍ ሰነዶች ለመሰብሰብ በደርግ ዘመን በተፈቀደለት ጊዜ ፣በቤተ-መንግሥቱ ምድር ቤቱ ውስጥ ያየውን ነገር እንደዚህ አድርጎ ተርኮልን ነበር። መዝገቦቹ ሁሉ ተበትነዋል። በእጅ የተጻፉ ወረቀቶች ጣውላው ላይ ወድቀዋል። ከውጭ ክረምት ስለሆነ የዝናብ ወሃ ይገባል። አንዳንድ ብጣሽ ወረቀቶች ወሃ ላይ ይንሳፈፋሉ።አንዲት ወረቀት ብድግ አድርጌ ስለመለከት፣የሚንስትሮች ስብሰባ ቃለ-ጉባዔ ይዘት የያዘች የንጉሡ (የቀ.ኃ.ሥ.) ማስታወሻ ነበረች። „…እምሩ ጥሩ ብሎአል።…አበበ ተሳስቶአል።…“

ደርግ ከወደቀ በሁዋላም አንዱ ያዳመጠውን እንደዚህ አድርጎ ሁኔታውን አስቀምጦታል።
ሥልጣኑን በምርጫ ሳይሆን ያኔ በጠበንጃ ለሦስት የተረከቡት ድርጅቶች ( … ሻብያም ፣ኦነግም፣ከሕዝባዊ ወያኔ ጋር አብረው አዲስ አበባ ገብተዋል) የእነሱ ወታደሮች በዚያን ጊዜ ትልቁን ቤተ-መንግሥት የሚጠብቁት ዘበኞች፣ያለ የሌለውን ጥንታዊ ሰነዶች፣ ለሻይ ጀበናቸው የከሰል ማቀጣጠያ እንዳደረጉት በርከት ያሉ ሰዎች አይተዋል።
ምክንያቱ ግልጽ ነው። አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ያው „የአደሃሪ፣ የፊውዳል…የበዝባዣ…ታሪክ ከሚለው ጥላቻ ተነስተው ነው።“ እነዚያ የከሰል ማቀጣጠያ የሆኑ ሰነዶች ስለ ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነቶች ሊሆን ይችላል።ወይም ስለ ሌላ ጉዳይ። ግን ዛሬ ብንፈልጋቸው የማናገኛቸው ሰነዶች ናቸው።

አንድ ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ለረጅም አመታት ጥናት የሚያደርጉ አዛውንት፣ ፕሮፌሰር ሆህናዚ የሚባሉ ምሁር „ገንዘብ ከአለህ ኢትዮጵያ ስትወርድ ያገኘኸውን ቅርሳ ቅርስ ዝም ብለህ ግዛ፣ ወደፊት በቀላሉ የማታገኙት የአገሪቱ ንብረታችሁ እየተዘረፈ ነው“ ብለው መክረውኝ ነበር። ይህን ለማድረግ (ሮከፌለር ወይም ቢል ጌት መሆን ያስፈልጋል) የአንድ ሰው ሥራ አይደለም። ይህን ማድረግ የሚችለው መንግሥት ወይም ብዙ ሰዎች ሰብሰብ ብለው የሚያቋቁሙት „ትራንስፓረንት“ ግልጽ የሆነ አባሎቹ በየጊዜው የሚቆጣጠሩት የበጎ አድራጎት፣ የሽልማትም ድርጅት ሲመሰረት ነው። ለዚህ ደግሞ በወር አንድ ዶለርም በነፍስ ወከፍ ማዋጣቱ በቂ ነው።
ለምንድነው ይህን ጉዳይ የምናነሳው?
ለትውልድ የሚተላለፉ ጽሑፎች የት እንዳሉ አናውቅም ብለናል። የሚታወቁትም ምን እንዳዘሉ እነደዚሁ ስለእነሱ የምናውቀው ነገር የለም ብለናል። የአገራችን ሰዓሊዎች የሳሉት ሥዕሎች ተሸጠው በዓለም ዙሪያ ተበትነዋል። አንደ ቤተ መንግሥቱም ሰነዶች እነሱም አልተመዘገቡም ብለናል።
የትምህርትና ሥነ-ጥበብ ሚኒስትር ተመራቂ ተማሪዎች ብዙ ናቸው። ሥራቸው የት ገባ? የትይገኛል?… ቢያንስ በምዝገባ ሥራ አንዳንድ ነገሮችን መጀመር ይቻላል።

*

እንዳው ለመነሻ ያህል፣

አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፣  እአአ 1965፣ ለንጉሠ፥ነገሥቱ

የጻፉትን አቤቱታ  እዚህ እትም ውስጥ  አካተነዋል።

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s