ግብፅ / ምን ሊያስተምረን መጣ ?

ግብፅ / ምን ሊያስተምረን መጣ ?

ግብፅ / ምን ሊያስተምረን መጣ ?

Advertisements

አእምሮ መጽሔት፥ አዲሱ እትም – I-05/08-7

„ጠላት“? አንድ ግራ የሚያጋባ ቃል!

„አብዮት“– ፈረንሣይ አገር አንዴ እንዳደረገቸው- በኢትዮጵያ ልጆቹዋን ቅርጥፍ አድርጋ በልታለች። ግብጽ ላይ ደግሞ -አንዱ የጀርመን ጋዜጣ እንደ ጻፈው- ይህቺ ጨካኝ አብዮት ብቅ ብላ „ወንድሞቹዋን“ ከእህቶቹዋ ጋር ጠብሳ፣ ዋጥ አደርጋችዋለች።“

ነገ ደግሞ – ይህን ዛሬ ማን ያውቃል- አንዱን ቀቅላ እንደ ልማዱዋ ትበላለች።ምናልባት -ይህን ማሰቡ ያስፈራል- እናትና አባትዋን አሳዳ…ትጨርስም ይሆናል።

ወሬው እንደተሰማ፣ ዜናው ከካይሮ እንደተስፋፋ(-የአገሬን ልጆች መቼም በዚህቺ ድፍረታቸው እወደቸዋለሁ፣ በዚህችም ችሎታቸው አደንቃቸዋለሁ -) ቶሎ ብለው “… ሙርሲ ይህን ቢያደርግ፣ የእስላም ወንድማማቾች ያን ቢያደርጉ፣ ወታደሩ ለአገሩና ለሕዝቡ ቢያስብ፣ አንድ ላይ ተቀምጠው ቢነጋገሩ ኑሮ፣….ሁለቱም ሦስቱም፣አራቱም ወገኖች የጋራ መንገድ ቢፈልጉ፣እረ ቢያንስ በትንሹ ቢከባበሩ፣… አስታራቂ ሽማጋሌዎች እንኳን መኻላቸው ቢገቡ…ይህ ሁሉ እነሱ እነደሚሉት ትርምስና ደም መፍሰስ፣ሞትም ላይ በአልደረሱም ነበር…“ይላሉ።

እንደዚህ ዓይነቱን ቀና ሐሳብ ከሚሰነዝሩት ሰዎች መካከል፣መገመት እንደሚቻለው ኢህአዴግን የሚደግፉ ሰዎችም (ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን ሌላ ነገር ያነሳሉ) እንደ ተደመጠው እነሱም ይገኙበታል።

አዲስ የተፈጠረው የግብጹ ውስጣዊ የፓለቲካ ሁኔታ ግልጽ አድርጎ የሚያሳየን አንድ ነገር ቢኖር (ምን ግብጽ ብቻ!… ጠቅላላው መካከለኛው ምሥራቅ)እንዴት አድርጎ አለመደማመጥ፣ በጠላት አይን ከመሬት ተነስቶ መተያየት፣…የሁዋላ ሁዋላ፣ ቀስ እያለ፣ ከባድ ችግር ውስጥ አንድን ሀገርና አንድን ሕዝብ እንደሚከት ቁልጭ አድረጎ፣ያስተምረናል።ያሳየናል።

እንዴት አድርጎም ስለ „ሀገር አስሰዳደር ብልሃትና ዘዴ ምንም ነገር አለማወቅ“ ምን ያህል መመለሻ የሌለው እሳት ውስጥ አንድን ሕዝብና እንድን ሀገር፣ በጥቂት ሰዓታት፣በትንሽ ጊዜ፣ በቅጽበት፣ እነሱንጨምሮ እንደሚበታትን ማተዋየሚችል ሰው ቢኖር፣ የግብጽ ሁኔታቁልጭ አድርጎ ያሳያል።ያስተምራል።

ስለ የተለያዩ የሰው ልጆች በህሪና ተፈጥሮ ቅንጣት ያህል እነኳን ደክሞ ለመረዳት አለመቻል፣ አለመሞከርም ገፍትሮ መጨረሻ ወደ ሌለው የማይታወቅ ሁኔታም ውስጥ እነደሚከት፣ የግብጽ ግርግር ያስተምራል።ተጠንቀቁም ብሎ ይመክራል።

ግብጽ አብዮቱን በአካሄደች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ትሆናለች ብሎ የገመተ ሰው የለም።

ግብጽ የገባችበት ሁኔታና ችግር ደግሞ ማንኛውም አገር -የአስተዳደር ብልሃትን ከአላወቀበትምክንያቱ እላይ ተገልጸአል- ዓይኑ እያየ፣ ነገ ሰተት ብሎ፣ ያ! ሀገርና ሕዝብ ሊገባ ይችላል።

ሌላም ትምህርት የግብጹ ሁኔታ ጥሎልን ሄዶአል።

እሱም „ወታደሩ“ በግብፅ ሀገር (በሌላው ዓለም እንደምናውቀው)„ በፖለቲካ ር የሚተዳደር የሀገር መከላከያ ተቋም „ ሳይሆን፣ ይህ የጦር ሠራዊቱ እራሱን የቻለ(እስከ ዛሬ የምናውቀው አራት ተቋሞችን ብቻ ነው፣እሱም…የሕግ ማውጫ፣የሕግ መወሰኛ፣ ነጻ-ፍርድ ቤትና ነጻ- ጋዜጣን/ሜድያ…) „አምስተኛው፣የሕብረተሰቡ በዚያውም ፖለቲከኞቹንና የፖለቲካ አቅጣጫን የሚቆጣጣሪ ኃያል ኃይል“ ሁኖ ዘንድሮ ብቅ ብሎአል።

እንደሚባለው የግብጽ የጦር ኃይል፣ ዱሮንም ቢሆን „በአገሪቱ ውስጥ፣ በመንግሥት ር የራሱ የሆነ “ልዩ መንግሥት“ ገና ዱሮ እንደ አቋቋመ፣የአደባባይ ምሥጢር ሁኖ ይነገርለታል።

የእራሱም የሆነ የተለያዩ እንዱስትሪምርት የሚያመርቱ የግል ፋብሪካዎች፣ የንግድ ድርጅቶች፣የሕንጻ ተቋራጮች፣ የጉዞ ወኪሎችና የቱርስት ድርጅቶች፣ ከእነሱ ጋር በየቀኑገንዘብ„የሚያትምበት“ ሆቴሎች፣ባንኮች፣ሠራዊቱ አሉት።

„ሲሶ መንግሥት ነው“ ማለት፣አንድ ተመልካች እንዳለው ይቻላል። ይህ በግብጽ እንደሆነም እርግጠኛ ሁነው ብዙዎቹ ይናገራሉ።

እንደዚህ ዓይነቱ የአሰራር ዘይቤምና ሐሳቡም ተስፋፍቶ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ግዛቶችም እንደዘለቀና አንዳንዶቹ የአፍሪካ የጦር ኃይሎች፣ ባንክ ቤቶች ለመክፍት፣ ፋብሪካ ለመመስረት፣ የሕንፃ ተቋራጭ ለመሆን ዝግጅት ላይ እንደሆኑ የአውሮፓ ጋዜጣዎች ይጽፋሉ።

ምን ይታወቃል፣ በዚህ በያዝነው በ21ኛው ክፍለ-ዘመን የግብጽ ጉዞ ተከታይ አግኝቶ፣ እኛም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገርና መንግሥታት ጋር ወደዚያው(ደርግ እንዳልገዛን ሁሉ) እንደገና ተመልሰን እናመራ ይሆናል።

በርካሽ የወር ደመወዝ የጦር ፋብሪካውን፣ሆቴሉን … በጉልበት ሥራ የሚያንቀሳቅሱለት፣ነገሩ ከተነሳ ላይቀር „…ወጣት ወታደር እና ሰላይ ሁነው የሚቀጠሩት ልጆች“ እንደሆኑም ይጠቀሳል።

ሐሳቡ ከየት መጣ? ማነው የዚህ ዓይነቱ አሰራር አባቱ?

እሱን እነተውና „አብዮት ልጆቹን የምትበላው ለምንድነው?“ ብለን እንጠይቅ።

ቡዳ ስለሆነች አይደለም። ወይም የአብዮት „ዓይኑዋ „ ከሩቁ ስለሚወጋም አይደለም። ወይም ደግሞ አብዮት „…ደም ማሽተት፣ደም ማፍሰስ“ ስለምትወድም አይደለም።

አብዮት ልጆቹዋን ትበላለች የሚባለው በአንድ ነገር ነው።

እሱም በአንድ ሀገር የሚኖሩ፣ ነገር ግን የተለያዩ አመለካከቶችና አቋሞች የሚያራምዱ፣ኃይሎች፣… እንበል ጥቂት ቡድኖች፣የፖለቲካ ድርጅቶች:- አቋማቸው ሊጻረም ይችላል- „ በጠላትነት በደመኛ ጠላትነት መተያየት „ የጀመሩ ሰዓት“ ያኔ! ነገር ተበላሸቶ፣”አብዮት ልጆቹዋን ለመብላት” ቢላዋን ትስላለች፣ድስቱዋን ትጥዳለች፣ ጠበንጃዋን ትወለውላለች፣ ማለት ነው።

ቀደም ሲል „ሰውን ለመሰብሰብ ሆን ተብሎ የተወረወረ አይዲኦሎጂ የሚዋገው ጠላት“ ያስፈልገዋል ብለናል።

አለበለዚያ ያ ድርጅት እንደ ምትሃት፣ ለአፍዝ አደንግዝ፣ ተከታዮቹን ለመሰብሰብ የቀነጠሰው ቅጠል፣ ያን ቢል ይህን ቢያደርግ የመከተለው “ጀሌ” መሰብሰብ ሰለማይችል፣ድካሙ ሁሉ ከንቱ ሁኖ አይሰራለትም።

ግን የተመኘው ከሰራለት ያኔ ! እነዚህ „በጠላትነት የሚተያዩና የሚፈላለጉ“ ቡድኖች ፊት ለፊት፣ የተገናኙ ቀን ደግሞ „…ደመኛ ጠላቶች“ ስለሆኑ የሚገላግላቸው ነገር (ይህ የታወቀ ነው) አንድ እርማጃ ብቻ ነው። እሱም አንዱ ሌላውን ቀድሞ (ሻለቃ መንግሥቱ ብሎት ጨርሶታል ለምሳ ያሰቡንን ቁርስ አደረግናቸው…እንዳለው) መግደልና መገዳደል ብቻ ነው።

ይህ ብዙ ቦታ ተደጋግሞ ታይቶአል።

እራሱ የቅርቡ የኢትዮጵያ ታሪክም ምስክር ነው።… ለመድገም:- ደረግና የደርግ አባሎች እርስ በራሳቸው፣ ደርግና መሣፍንቱ፣ ኢህአፓና መኢሶን፣ ወያኔና ሻቢያ፣ሻቢያና ጀበሃ፣ ደርግና ወያኔ፣ደርግና ሻቢያ፣ ኦነግና ወያኔ….ወያኔና አባሎቹ…ወዘተ፣እነዚህ ሁሉ እንደ ዕውር ተያይዘው ተናንቆዋል። ይህም ማየት ለሚፈልግ ሰው ቋሚ ምስክሮች ናቸው።

ችግሮቻቸውን፣ በአንድ ዓረፍተ-ነገር ለመናገር ለመፍታት የሞከሩት በኃይል፣ ያውም በጥይት ነው።

ለምንድነው በአውሮፓ ወይም በሰሜን አሜሪካ እንደዚህ ዓይነቱ“ጥላቻና የደም ማፍሰስ ጭካኔ፣ በጠላትነት የመተያየት መንፈስና ሓሰቦች“ በዚያ አካባቢ፣በመካከላቸው ዛሬ የማይታየው?

ለምንድነው የምሥራቅ አውሮፓው፣ ጸረ-ኮሚኒስትና ጸረ-አምባገነኖች የሕዝብ እንቅስቃሴ – ከአለ የሩሜኒያው ቻውቼስኮ የሞት ፍርድ በስተቀር – አንዲት ጥይት ሳትተኮስ በሰላም ያለቀው?ለምንድነው ለሁለት ተከፍለው ከአርባ አመት በላይ ይኖሩ የነበሩ የጀርመን ወታደሮች ጠበንጃቸውን ጥለው በውህደቱ ቀን የተቃቀፉት?

ከ500 ሺህ በላይ የሆኑ በደንብ የታጠቁ የራሺያ ወታደሮች ጓናቸውን አንዲት ጥይት ሳይተኩሱ ጠቅልለው የጀርመንን መሬት የለቀቁት?

ይህን መረዳት የምንችለው“ጠላት“ የሚለውን ቃል አውሮፓያኖቹና አረቦቹ፣ኢትዮጵያና አሜሪካኞቹ፣ ቻይናና ሕንዱ፣ እሥራኤልና ኢራኩ፣… እነዚህ ሁሉ አገሮች የሚያዩበት ዓይንና ግምት፣ ጠጋ ብሎ መመልከት አስፈላጊ ነው።

የሚያዩበት ዓይናቸው የተለያዩ ናቸው። ፍጹም ሌላ በመሆኑም ችግራቸውን የሚፈቱት በተለያዩ መንገድ ነው።

በአውሮፓና በአሜሪካን የፖለቲካ ፍልስፍና „ጠላት“ ተብሎ የሚታየው፣እነደ ጠላትም የሚቆጠረው „ ሀገር አቋርጦ፣ድንበር ሰብሮ፣ ጦር መዞ፣ ወታደር አሰልፎ የሁሉም እናት ሀገር የሆነቺውን መሬት ይዞ ባሪያ ለማድረግ የተነሳውን፣የሚነሳውን ወራሪ ኃይል ብቻ ነው።

ሌላውስ ? ለየት ያለ የፖለቲካ አቋም የሚያራምደውስ? ሥልጣን ላይ ለመውጣት ተቀናቃኝ ሁኖ የፖለቲካው መድረክ ላይ ብቅ የሚለውስ ቡድን?… ድረጅት?…ተቺውስ?ጸሓፊ ጋዜጠኛውስ?… እነሱ በአውሮፓና በአሜሪካ „ጠላት“ አይደሉም። በጠላት ዓይንም፣ እርስ በእራሳቸው አይተያዩም።

ሥልጣን ላይ ያለውን፣በሌላ በኩል እንበል አንድ የገዢን መደብ፣ ሕዝቡ በምን ዓይን እነሱን ያያቸዋል?

እሱም ቢሆን፣ ይህኛው ገዢው ክፍል በምንም ዓይነት፣ በምዕራብ አውሮፓ ሆነ በአሜሪካ „ተቃዋሚ“ እንጂ „ጠላት፣ ደመኛ ጠላት“ አይደለም።

ይህን የመሰለ የፖለቲካ ጥበብና ዕውቀት አውሮፓውያኖች ፈልገው ያገኙት ደግሞ ወደ ታሪክ መለስ እንበል፣ ከጥንታዊ ግሪክ ከአቴንስ ፍልስፍና እን ከእነሱም ሥልጣኔ ነው።

ሁለተኛው „ጠላትህን እንደ እራስህ አድርገህ ውደደው“ ከሚለው ከክርስትና ትምህርትም ነው። ሶስተኛው በተጨማሪ ከሮማ ሕግ ነው።

አቴናውያን በነበራቸውና በአገኙት የምርምር ነጻነት „..ዓይን ለዓይን፣ጥርስ ለጥርስ „ የሚለውን የሓሙራቢን ሕግ (እስከ አጼ ምኒልክ ድረስ እኛ አገር ይህ ሕግ፣አልፎ አልፎ በአንዳንድ ቦታዎች ይታይ ነበር) ከጥቅሙ ለአንድ ሕብረተሰብ፣ ጉዳቱ ስለሚያመዝን እሱን ጥለውት ለመሄድ፣ ለየት ያለ መንገድ እነሱ ፈልገው ፣ መርጠው ወስደዋል።

ከእሱም ጋር „…በሰው ልጆች ዘንድ ቂም በቀልን ለማስቀረት ፣… ለፈሰሰው የአባት ወይም የወንድም ደም ፤… ልጅ የአባቱን ደም መበቀል አለበት“ የሚለውን ልማድ ( የጣሊያን ማፊያ አሁንም ድረስ ያደርገዋል) እነሱ ገና ዱሮ፣ እንደዚህ ዓይነቱን ልማድ አስቀርተዋል። ለምን? ምን ታይቶአቸው ነው ይህን ያደረጉት?

ይህ አካሄድ “ አንዱ አድፍጦ አንዱን መበቀል…ዞሮ ዞሮ መጨረሻ ወደሌለው የበቀል ኣዙሪት“ ትውልዱን እንደ ሚከት እንደከተተም መለስ ብለው ስለ ተገነዘቡት ነው። ይከታል። ደግሞም ከቶአቸዋል።

ስለሚከትም ከዚያ „ባህልና ልማድ፣እንዲሁም ከጥንታዊ ሕግጋት“ ለመላቀቅ የወሰዱት እርምጃ ወሳኝ እና በጣም የሚደነቅ መንገድ ነው።

ከክርስቶስ ልደት በፊት እነዚህ ግሪኮች የደነገጉት ሕግ „የሁለት ጠበኞችን ጉዳይ በግዲያም ሊሆን ይችላል… ይህን ውዝግብ ችሎት ተቀምጦ፣ የሚመለከተው፣ የተበዳዩ ቤተሰብ ሳይሆን፣…. ዳኛና ፍርድ ቤት ነው ብለው ደንግገዋል።

“ …ያ እሱ በእኔ ዘመድ ላይ ስለአደረገው ወንጄል፣ እኔ አጻፋውን በተመሳሳይ መልኩ፣ በልኩ እሱ እንዳደረገው፣ እኔም በዚያው መልክ መልሼ ልገደለው እችላለሁ“ ብሎ መነሳት እንደማይችል -ይህ ነው እንግዲህ የአቴኖች ችሎታ- በሕግ፣እሱ ይህን ማድረግ እንደማይችል እነሱ ከልክለዋል። „ቂም በቀል እርምጃውንም“ ማንም ከመሬት ተነስቶ እንዳይወስድ አግደውታል።

እንዴት አድርገው ነው ሕዝቡ እንደዚህ ዓይነቱን አዲስ አሰራር፣…የዱሮውን ባህሉና ልማዱን ጥሎ፣ በቀላሉያኔ ጋዜጣና ራዲዮ፣ ቴሌቭዠንም በሌለበት ዘመን እንዲቀበለው ያደረጉት?

በቲያትር ጫዋታ ነው። መድረኩ ላይ በሚታየው ድራማ ነው። „….ትረጀዲ-አሳዛኝ ጨዋታዎችን“ በመጫወትና እሱንም ሰው አይቶ እንዲነጋገርበት፣እንዲከራከርበት በማድረግም ነው። ቀስ እያሉ ሕዝቡን በዚህ ዘዴ ማስተማር ችለዋል።

በየአደባባዩ ቀንም ሆነ ማታ ማታ መድረክ ላይ በሚጫወቱት የቲያትር ትራጀዲ “ሚስቱን ስለገደለ፣ አንድ የልጆች አባት” ይተረካል። ይነሳል። ሚስት ባሉዋን… ወንድም በወንድሙ ላይ ያካሄደውን የግዲያ ሙከራ፣ በመድረኩ ላይ ተመልካቹ ፍርዱን በሁዋላ እንዲሰጥ ይደረጋል። የወንድሙዋ ገዳይ ፍቅረኛዋ ሆኖም ይገኛል።

እንግዲህ ቤተሰብ እንዳይበትን፣ ሰው በቂም በቀል ተናንቆ እንዳያልቅ፣ ጉዳዩን የሚከታተሉ ዳኞች ተቀምጠው፣ ችሎት፣ ጉዳዩን የሚመለከት፣ መድረኩ ላይ፣ በትራጀዲ ጨዋታው ላይ ይጠራል።

አማልክቶቹ በፍርድ አሰጣጡ ላይ እንዲሳተፉበት ይደረጋል። ጎረቤቶች አስተያየታቸውን እንዲሰነዝሩበት ይጠየቃል።…

የግድያው መነሻ ምክንያት ምንድነው? ተብሎ እዚያው መድረኩ ላይ ይመረመራል። ሲወድቅ ነው የሞተው ወይስ በተሰነዘረበት ጩቤ፣ ተብሎ ይጠየቃል። ባሉዋን የገደለቺው ሴትዮ እሱዋ ብትገደል (ልጁዋ ነው የአባቱን ደም መበቀል ያለበት) ሌሎቹን ማን ያሳድጋል ተብሎ ጉዳዩ ይታያል። ልጁስ ውድ እናቱን ለመግደል ፈቃደኛ ነው ወይ? ተብሎም ይጠየቃል።

ይህንንና ይህን የመሳሰሉ ኃይለኛ የትራጀዲ ድራማዎች „ ፍርድ መስጠት“ የነጻ ፍርድ ቤት ኃላፊነት እንጂ ማንም ከመሬት ተነስቶ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ መፍረድ እንደማይችል፣ አቴኖች አስተምረውበታል።

ይህም ታሪካዊ የሆነ -በሁዋላ ዓለም አቀፋዊ እርምጃ – በሕግ በደንብ ተደንግጎ እንዲወጣም ተደርጎአል።

እንግዲህ በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ በፖለቲካ ጥያቄ ሆነ፣ በምርጫ “ማጭበርበር”…ሌላም ነገር ለሆን ይችላል- ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ሸንጎ ውስጥ ሆነ ከሸንጎ ውጭ ከአልተግባቡ ፣ „ጉዳያቸውን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው ዳኞች እንዲያዩትና ፍርዳቸውን እንዲሰጡ – እዚህ ይደረጋል።“

በግብጽና በኢትዮጵያ፣ወይም ሌላ ቦታ… በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ውዝግብ ሲነሳ፣ በተለይ አንድ መሪ ሕገ-መንግሥቱን ጥሶ፣ ሰውን ሁሉ ከሥራው አባሮ በእራሱ ሰዎች ሲተካ (ፕሬዚዳንት ሙርሲ ይህን አደረገዋል ኢትዮጵያም ውስጥ ተካሂዶአል) ያኔ እንደዚህ ዓይነቱን፣ ሰው ከሥራው ሲባረር፣ ይህን እርምጃ፣ በሠለጠነው ዓለም፣ይህን እርምጃ የሚያግደው „ችሎት የተቀመጠው ነጻ- ፍርድ ቤት“ ነው እንጅ ወታደሩ፣ፖሊሱና የአየር ኃይሉ ባለደረቦች አይደሉም።

በግብጽ እንዳየነው ወታደሩ መሳሪያውን ይዞ አደባባይ ወጥቶ የእራሱን ፍርድ ሰጥቶ፣ሰልፈኞች ላይ ተኩሶአል። ፕሬዚዳንቱንም አስሮአል። ሌሎቹን አርፋችሁ ተቀመጡ ብሎአል።

እንግዲህ ከዚህ አንጻር ነው የግብጽን ውስጣዊ ፖለቲካ፣ በዚያውም የሌሎቹን አፍሪካ ሀገሮች፣ የኢትዮጵያንም ውስጣዊ ውዝግቦችና ችግሮች ማየት የሚቻለው።

„የጠላትን፣… የደመኛ ጠላትን ትርጉም በአንድ ሕብረተሰብ“በደንብ አለመረዳት ያንን ሀገር፣…አንድን ሕዝብ፣ ሳይታሰብ መጨረሻ ወደ ሌለው እልቂት እንዴት እንደሚወስደው፣ የግብጽም፣ የኢትዮጵያም፣ የኮንጎም፣ የሱማሌም የናይጄሪያም፣ ውስጣዊ ሁኔታዎች ሕያው ምክሮች ናቸው።

በሌላ በኩል የኔልሰን ማንዴላ የፖለቲካ እርምጃ „ዘረኛ የነበሩ ነጮቹን ማንከባከብና ማቀፍ“ እራሱን የቻለ ትልቅ (በጠላት ትርጉም ላይ)ትምህርት ይሰጣል።

„ጠላት“ ማለት እንድገመው፣ ባሪያ አድርጎ ለመግዛት ከውጭ የሚመጣ ወራሪ ኃይል ብቻ ነው። የፖለቲካ ተቃዋሚና ተቀናቃኝ ድርጅቶች „ጠላት „ ሳይሆኑ የሀገር ልጆች ናቸው። ሕገ -መንግሥቱም በትክክል በሥራ ቢውል የመቃወም መብታቸውን ያረጋግጥላቸዋል።

ከጠላት ጋር የሚደረገው ፍሊሚያ ጦር ሜዳ ይለይለታል። ለየት ያለ የፖለቲካ አቋምና የፖለቲካ ፕሮግራም ከሚያራምደው ጋር ያለውን ልዩነት የሚፈታው ደግሞ፣ እኛ እዚህ እንደምናውቀው፣ ሕዝብ ፊት ቀርቦ በሚካሄደው፣ በክርክር፣ በውይይት፣ በመጨረሻም፣በምርጫ ሂደት፣ በወረቀት ነው። ወይም ደግሞ ውዝግብ ሲነሳ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው።

„ገዢው መደብ፣ አልሰማም ብሎ እምቢ ከአለ ደግሞ፣ (በጦርነት ሳይሆን) በሕዝብ አመጽ በተቃውሞ ሰልፍ፣ ከቦታው እንዲነሳ የደረጋል። ወጣ ወረደ ወሳኙ ሰበአዊ መብቶች ፣በሁሉም ወገኖች ዘንድ ይከበራሉ ወይስ አይከበሩም ነው። የግለሰብ ሰበአዊ መብቶችን አምባገነኖች ለምን እንደማይቀበሉት (ሌላውን ነገር ሁሉ ፣የብሔር እኩልነትና የሃይማኖትን እኩልነት እንቀበላለን ይላሉ) የሚያጠያይቅ ነገረ ነው።

ታቦታችን ላይ የሙሴ ጽላት ላይ “አትግደል” ይላል።

ከግብጽ የምንማረውም እሱኑ ነው።

ከሣቴ ብረሃን ሣልሳዊ

—————————————————-

https://leaimero.files.wordpress.com/2013/04/a_schreibfeder.gif

አስተያየት ለመስጠት / Comments

——————————–

——————–

leaimero-reg-logo © ለ አእምሮ 2005 / © Le’Aimero Copyright 2013

ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements

Le’Aimero’s Disclaimer

——————–

አእምሮ መጽሔት፥ አዲሱ እትም – I-05/08-7

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s