ዘመነ፥ብርሃን / Enlightenment

ዘመነ፥ብርሃን / Enlightenment

ዘመነ፥ብርሃን / Enlightenment

አእምሮ መጽሔት፥ አዲሱ እትም – I-05/08-7

ዘመነ፥ብርሃን / Enlightenment

ማንም ሊያግደው የማይችለውየተፈጥሮ ጸጋ! የተፈጥሮ መብት!

በትክክል ስለ ነጻ ሰውና ስለነጻነት፣ስለ ማሰብና ስለ አለ ፍረሃት መነጋገር፣ ስለ እነሱም መጻፍና መመራመር የተጀመረው:- እንደገና በትክክል ነገሩን ለማስቀመጥ “ ስለ ባሪያ ሳይሆን ስለ ነጻ ሰውና ስለነጻነት“ (ይህ መነገር ያለበት አስፈላጊ ቦታ ነው) ስለዚህ ጉዳይ ማሰብና መነጋገር የተጀመረው በጥቂት ሰዎች የጥናት ክበብና የጽሕፈት ቢሮ ውስጥ ነው።

የደረሱበት ውጤትና ተመክሮዎች፣ ታትሞና ተባዝቶ፣ለሰዎች መበትን በአውሮፓ የተጀመረው በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ነው።

የዚህ ጥናት ውጤት የዩኒቨርስቲ አስተማሪዎች እጅ ይገባል።ቆየት ብሎ ተማሪዎቻቸው ቀበል አድርገውት በየአለበት፣በመጀመሪያ በዘመዶቻቸውና በጓደኞቻቸው መካከል አሰራጭተውታል።

እንደሚባለውና ብዙዎቹ እንደሚገምቱት የጀርመኑ ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት አይደለም „ስለ ዘመነ- ብርሃን፣ስለ ጸጋና ስለ ጧፍ ልጆች፣… ስለ ጨለማው ዓለም „ የመጀመሪያውን የአካዳሚ ጽሑፍ የጻፈው።ያስተማረው። የተነተነው።

ለካንት አስተማሪዎቹና የቅርብ ጓደኞቹ ናቸው፣ አርዕስቱንም፣ሁኔታውንም ለእሱ የእንግሊዘኛ ቋንቋ በደንብ ለማያውቀው ፈላስፋ በሁዋላ ያስተዋወቁት።

ካንት ግን አለጥርጥር ትላልቅ ጽሑፎች አውጥቶ የዘመኑን ሰዎችና ከዚያ በሁዋላ የተወለዱትን ትውልዶች፣ ስለ ሞራልና ስለ ኤትክ፣ስለ የሰው ልጆች አብሮ የመኖር ዘይቤ፣ ስለ የዓለም ሰላም፣ ስለፍትህና ፍርድ ብዙ ነገሮች አስተምሮአል።

እንግዲህ የኢንላይትሜንት :- የዘመነ- ብርሃን ትምህርት ፣ ዋና አባት ካንት ሳይሆን የእንግሊዙ ፈላስፋው ጆን ሎክ ነው።

ሎክ ይህን ዕውቀት የሰበሰበው፣ከቡዙ ጊዜ ጥናት በሁዋላና እሱ እራሱ ከአየውና ከአገኘው ተመክሮ ተነስቶ ነው። ግሩም ጥያቄዎችን ለእራሱና ለሌቹም በማቅረቡና ለእሱም ጊዜ ወስዶ ከፍተኛ አተኩሮስ ሰጥቶ፣ በመልስ ፍለጋውም ላይ በመጠንከሩም ነው።

ከጓደኞቹ ጋር አብሮ እየተገናኘ በአደረገው የረጅም አመታት የጥናት ጊዜ በሁዋላ እሱ እንደሚለው „…የተሳሳተ አቅጣጫ ይዘው ሁሉም ብዙ ተንከራተው“ እንደ ነበር በተወልን ማስታወሻው ላይ ያስታውሳል።

በእርግጥም ጆን ሎክ ከጓደኞቹ ጋር በየጊዜው እየተገናኘ በጋራ በሚያካሄደው የጥናትና የምርምር ድካም ፣ እሱ እንደሚለው፣ የተሳሳተ መንገድና የተሳሳተ ፍንጭና ዱካ ተከትለው የማይሆን ቦታ ደርሰው ነበር።

ግን አስተዋዩ ሎክ፣እሱ እራሱ እንደሚለው፣ ያን ጎዳና ጥሎ በ1689 ዓ.ም(እ.አ.አ) „አንዳንድ አመለካከቶች፣ በፖለቲካና በሃይማኖት፣እንዲሁም በአስሰተዳደር ላይ…“በሚለው አርዕስት ሥር የራሱን አመለካከቶች ጽፎ አደባባይ ላይ ሳያወጣው ለተወሰኑ አመታት ሐሳቦቹን አስቀምጦታል።

ሎክ እሱን በሚያበረታተውና መልሶም በሚጠይቀው በፖለቲከኛው በሁዋላ የመኳንት ማዕርግ አግኝቶ ግራዝማች የተባለው አንቶኒ ኤሽሌ ኩፐር፣በእሱ ምክንያት የአመለካከት አቅጣጫውን ሊቀይር ችሎአል።

ግራዝማቹ የኤርል ኦፍ ሻፍትስበሪ”.. እስቲ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ አሰበህ ጻፍልኝ..“ ብሎ ይጠይቀው እንደነበር ይጠቀሳል። ትውውቃቸው በሰኔ/ሐምሌ 1666 አካባቢ ነው።

የእሱና የአብዛኛው የጧፍና የብርሃን ልጆች የትግል አቅጣጫም „ …የሰውን ልጆች፣ በሙሉ በዚያውም የእንግሊዝን ኑዋሪዎች“ እነሱ እንደሚሉት“… ከሮማው ሊቃነጳጳስ የባርነት ዘመን ነጻ -ለማውጣት ምን እናድርግ ?“ የሚለው „ጥያቄና የትግል ብልሃት“ የጉዞአቸውን አቅጣጫ እነደወሰነውና እንደቀየረው እነሱም፣አረጋግጠው ተናግረውታል ።

በአጭሩ ሎክ የሮማውን ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳስ የበላይነት፣ እንደሌሎቹ እንግሊዞችና የሰሜን አውሮፓ ተወላጆች እሱ የማይቀበል ሰው ነበር።

እንዲያውም „በቫቲካን ሥር ሁኖ የካቶሊክን ሃይማኖት ተከትሎ መኖርን እንደባርነት“ የሚያይ ሰው ነበር። በዚህ አመለካከቱም ብቻውን አልነበረም።

ዘግየት ብለን እነደምናየው የሎክ ትምህርቶችና አመለካከቶች በፈረንሣይ እና በአሜሪካን አብዮት፣ከዚያም በሁዋላ እነሱ እራሳቸው ወደው በነደፉትና በተቀበሉት መንግሥት ላይ እንዲሰፍር ተደርጎአል።

በጀርመኑ በ1848 እና እንደገና ከዘውድ አገዛዝ በሁዋላ ተነድፎ በወጣው በ1918 የጀርመኑ የቫይመር ሕገ-መንግሥት ላይ የጆን ሎክ መሰረታዊ አስተሳሰቦች አብሮ ተጠቃሎ እንዲቀመጥም ተደርጎአል።

የዓለም ሕዝብ በፋሺዚምና በኮሚኒዚም ተዋክቦና በሚሊዮን የሚቄጠሩ ሰዎች በዚያ ጦስ ተጨፍጭፈው ከአለቁ ወዲህም፣ ከዚያ በተገኘው ተመክሮም “አረመኔዎች ተመልሰው እንዳይመጡ በተነደፈው የጋራ ሐሳብም ላይ” የጆን ሎክ መሰረታዊ ሐሳቦች መነሻ ሁነው „ዓለም አቀፋዊው የሰባአዊ መብት አዋጅ“ ሊታወጅም ችሎአል። ንቁ የሕግ አዋቂ የኢትዮጵያ ልጆችም አብረው የጥቁሩን ሕዝብ ወክለው የ1948ቱን አዋጅ ነድፈዋል። እንደሚባለው “የነጮች አዋጅ” ሳይሆን አብረው እንደአባልነታቸው አጽድቀዋል። “የአረመኔዎች አገዛዝ ተመልሶ እንዳይመጣ” -ይህ ነው የዓለም አቀፉ አዋጅ- ይህ ነው የጀርመኖች ከሒትለር በሁዋላ የወጣው አዲሱ ሕገ-መንግሥት ይዘት “…የሰው ልጆች ሁሉ በተፈጥሮአቸውና በሕግ ፊት እኩል ናቸው የሚለውን መሰረተ ሐሳብ ተንተርሶ፣… ማንም ሰው የሌላውን ሰው መብትና ሰበአዊ ክብሩን ሊደፍረውም ሊረግጠውም አይችልም …”ብሎ ያግደዋል። ከዚያም ስለ መብቱ፣ከግል ሀብት እስከ የግል እምነቱ፣ ስለ መናገርና መጻፍ ነጻነቱ፣…ፍርድና ፍትህ፣ ስለ ተቃውሞ መብቱ… ይዘረዝራል።

ሎክ በምርምር ዘመኑ „ ብዙ የተለያዩ አስተሳሰቦችና እምነቶች በአሉበት በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ እንዴት ተቻችሎና ተከባብሮ መኖር ይቻላል?“ የሚለውን ጥሩ መጣጥፉን (በ1667እ.አ.አ) ጽፎ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን፣ አብሮ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦችን አስፍሮልናል።

ሰውዬው ” ባለ ግርማው አብዮት Glorious Revolution” የሚባለው የእንግሊዞች አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት የስደት ዓለምን በነጻው ሆላንድ ቀምሶአል።

በጽሑፉም የአንድ መንግሥት ወይም የአንድ አስተዳደር ዋና „ዓላማና ኃላፊነቱ፣ ጸጥታና ሰላም በዜጎቹ መካካል ማረጋገጥ፣ ሰው የፈለገውን ሃይማኖት እንዲከተል መልቀቅ እንጂ ከዚያ አልፎ ያ አስተዳደር በመንፈሳዊ ዓለም ውስ ገብቶ ሰዎች እንዴት መኖር እንዳለባቸው፣ማንን ማምለክ እንዳለባቸው፣… በማን ሃይማኖታዊ አባት ሥር መተዳደር እንዳለባቸው መወሰን ቀርቶ፣ እዚያ ውስጥ አልፎ ተርፎ ገብቶ ማብኳት አንድ መንግሥት የለበትም „ ይላል።

በእሱ እምነት „መንግሥት በዚህ ጉዳይ አያገባውም“ባይ ነው። ከዚሁ ጋር ፈላስፋው ሎክ አንድ ሰው፣አንድ ሕዝብ የፈለገውን የተለያዩ ሃይማኖቶች፣እራሱ መርጦ ሊከተል ይችላል።”

ይህን ማድረግ በእሱ እምነት „ሀገር እንዳይበታተን ይጠቅማል“ ባይ ነው። ንጉሡ ግን የእንግሊካን እንጅ የካቶሊክ ሃማኖት ተከታይ ፍጹም መሆን የለበትም ይላል። ቅራኔ ይታይበታል? አይደለም።

የጆን ሎክ ጉዞ በዚህ አቅጣጫ ጀርመኖችም ከሮማው የቫቲካን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለመላቀቅ ከአደረጉት ከማርቲን ሉተር የፕሮቴስታን እንቅስቃሴም ጋር በጥብቅ ይመሳሰላል ።

ግን ደግሞ የፈላስፋው አመለካከቶች፣ከዚያም አልፎ ይሄዳል። “መለኮታዊ ነኝ” የሚለውን የአንድ ንጉሥ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን እንደ ሮማው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እሱንም ያቃወማል።

ብረሃን ልጆች፣ የንጉሰ ነገሥቱን ዙፋንና ዘውድን ሳይተቹና ሳይነኩ በዚያ ላይ ያቆማሉ ብሎ መገመት ስህተት ነው። በ1680 „…መለኮታዊው የንጉሡ ሥልጣን…“በሚለው ጽሑፉ ሎክ ስለ የሥልጣን ገደብ በንጉስ ላይ አንስቶ ከዚሁ ጋር ራመድ ብሎ ስለ ነጻነትና ስለ እኩልነት፣ ስለፍትህና ዳኝነት፣ ስለ የፓርላማ መብትና ገደብ በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ፣ ምን መምሰል አለበት? ብሎ ወደ መዘርዘሩ ይራመዳል።

እንግዲህ ይህ ሰው ቆየት ብሎ በቀጥታ እኛን የሰው ልጆችን(የትም እንሁን የት፣ እስላም እንሁን ክርስቲያን፣ አሕዛብ እንሁን፣ኮሚኒስት ወይም ሶሻሊስት…) በቀጥታ ሁላችንም ሰለሚያሳስበውና ስለሚያስጨንቀው በሥራም ላይ ውሎ ሌላ ቦታ ማየት ስለ ምንፈልገው “ …ስለ በነጻ-የመኖር መብት፣…ስለ ነጻ-ሰው መብት፣ ስለ የግል ሀብት፣ በእሱም የሰው ልጅ ስለ አለው መብት…“ ፈላስፋው ጆን ሎክ አንስቶ መልስ ይሰጣል።

ንጉሠ ነገሥቱ ሕግ ከጣሰ? ብሎ ይጠይቃል። ሕዝቡም መብቱን በመንግሥት፣በገዢ መደብ ከተገፈፈ? ምን እናድርግ ይላል። ፈላጭ ቆራጩ ጉልበተኛ ገዢ አልሰማም ከአለ? ….ያኔ ሕዝቡ፣ ሰበአዊ መብቱ ተገፎ ተገዢ ባሪያ እንዳይሆን፣ ፈላስፋው „…እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በተፈጥሮ የሰጠውን መብቱን ለማስከበር፣ላለማስነጠቅ መነሳት“ አለበት ብሎም ያስተምራል።

ካንት በአስተማሪዎቹና በአብሮ አደግ ጓደኞቹ የጆን ሎክን ከእንግሊዘኛ ወደ ጀርመንኛ የተተረጎመውን ጽሑፍ አገላብጦ እላይ እንዳልነው ወፋፍራም መጽሓፍትን በሁዋላ ጽፎልናል።

የአሜሪካንንና የፈረንሣይ አብዮት አባትና አዋላጆች በሕገ-መንግሥታቸው ላይ „ስለ ምርጫ፣ ….“ የሎክን ሓሳቦች መሰረት አድርገው ወደ ዲሞክራቲክ ሥርዓት ከአንድ መቶ አገር የበለጡ መንግሥታት ተሸጋግረዋል። እንደተባለው ከ1948 ቱ የተባበሩት መንግሥታት አዋጅ ወዲህ “ለሰበአዊ መብት መታገል፣ ለነጻ-ፕሬስ መሟገት፣ ለግል ሀብት መቆም፣መምረጥና መመረጥ፣መተቸት፣ፊልም መቅረጽና መጸሕፍቶች ማተም …” እንደ ወንጀል አይቆጠርም። የሎክ ትምህርት ውጤት ይህ ነው።

ይህን ሐሳብ ግን :- ይህ ነጥብ ሲነሳ የሚቆጡ ደግሞ የሚበሳጩ አይጠፉም- እነ ሌኒንና እነ ስታሊን፣ ማኦና ሖዲጃ፣ ፖልፖትና ካስትሮ፣ ኢሳያስና መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም…ቆጥረን አንጨርሰውም፣ ተነስተው ….ይህን ሐሳብ ውድቅ አድረገው „አምባገነን ሥርዓታቸውን“ (መውደቃቸው ላይቀር) በገዛ ወገኖቻቸው ላይ መስርተዋል።

እዚሁ “የቶታሊቴሪያንና የአምባገነኖች የአስተሳሰብ” ማጥ ውስጥ ገብቶ አልወጣ ያለው ሰው ቁጥር ሌላ ቦታ እየቀነሰ ሲመጣ እኛ ጋ ተበራክቶአል። ይህ ዕውነት ነው?

ጆን ሎክ ፈላስፋው „ስለ አእምሮ ነጻነት አመጣጥ „ ጽፎአል። ወዳጄ!

በአንዴ ሁሉን ነገር ዘርግፎ ማስቀመጥ አይቻልም። በቂ ጊዜ ወደፊት ስለ አለን ቀስ ብለን እንመለስበታለን። ቀስ ብለን እንደርስበታለን።

አንድ ጥያቄ ግን አንስ ጉዳዩን እዚህ ላይ ለጊዜው እናሳድራለን። ለምንድነው የኢትዮጵያ ምሁር እንደዚህ ዓይነቱ፣ እነደ ሎክ ያሉ ፈላስፋዎች ላይ አተኩሮአቸውን ሳይጥሉ እንዲያው „…በላብ አደሩ አምባገነን ሥርዓት፣በዚያ ፍልስፍና ተማርከው….“ ” …በሌኒን እና በስታሊን ፣… በማርክስና በማኦ ትምህርት” ላይ ዓይናቸውን ጥለው እሰከ አሁን ድረስ እዚያው ላይ ብዙዎች የቀሩት? ለመሆኑ እነሱስ ዛሬ ስንት ናቸው?

…የሰው ልጆች:-ሁለተኛው ጥያቄ- ዕድሜ ልካቸውን ሊገዛቸው የሚፈልገውን “አንድ አምባገነን ሥርዓት” ምን ያህል ጊዜ ዝም ብለው ይቀበሉታል?… ይሸከሙታል?

በሌላ በኩል „ በተፈጥሮ ያገኘነውን የነጻነት መብት“ እሱን ማን ሊያግደው ይችላል? ለምን ድነው “ስለሃይማኖት ነጻነት፣… ስለየተለያዩ ሃይማኖቶች በኢትዮጵያ ተቻችለው መኖር” በየጊዜው እያስታወሱ መናገር የሚያዘወትሩ ሰዎች፣ ለምን ስለ የተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች እንደዚሁ ተቻችሎ መኖር የማይናገሩት?

ለምንድነው ስለ “ብሔር/ብሔረሰቦች እኩልነት በኢትዮጵያ አለ” ብለው የሚናገሩ ሰዎች፣ ስለ “ሰበአዊ መበት፣ ስለ ግለሰብ ነጻነት፣ ስለ ነጻ-ፕሬስ አስፈላጊነት ግልጽ በሆነ ቋንቋ የማይናገሩት?

መልሱንም እንግዲህ ቢቻል ወደፊት በጋራ መልስ ብለን እንመለከተዋለን።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

—————————————————-

https://leaimero.files.wordpress.com/2013/04/a_schreibfeder.gif

አስተያየት ለመስጠት / Comments

——————————–

——————–

leaimero-reg-logo © ለ አእምሮ 2005 / © Le’Aimero Copyright 2013

ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements

Le’Aimero’s Disclaimer

——————–

አእምሮ መጽሔት፥ አዲሱ እትም – I-05/08-7

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s