እኛ ማን ነን !

images-ID

እኛ ማን ነን !

የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ሁነው ሚስተር ባራክ ሁሴን ኦባማ፣ በአሜሪካን አገር ተመርጠው የዋይት ሐውስ ቤተ-መንግሥት ገቡ የሚለው ዜና እንደተሰማ፣ የዓለም መንግሥታት መሪዎች በሌሎች ሳይቀደሙ በጥድፊያ የደስታ መልእክታቸውን ለፕሬዚዳንቱ፣ያኔ ተጽፎ እንደተነበበው፣ ልከውላቸው ነበር።
ከደስታ ተካፋዮቹም ውስጥ ያኔ እዚህ በሹክሹክታ ተናፍሶ የደረሰው ወሬ እንደ ሚጠቁመው (ከየት እንደ መጣ ታሪኩ አይታወቅም) አሁን ከሥልጣናቸው ላይ የተባረሩት አንዳንድ የአረብ መሪዎች ፣…እንደ ኮነሬል ጋዳፊ ያሉ፣ እንደ ጄነራል ሙባራክ፣ እንደ ቤን አሊና የየመኑ ፕሬዚዳንትና አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት የሳውዲ ንጉሥም…ይገኙበታል።

መጥፎ ምላሶች እንደሚሉት ከሆነ፣ ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምና ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ተመካክረው አንድ ደብዳቤ ለሁለት፣አንድ ላይ ሁነው ጽፈዋል።
አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና አቶ መለሰ ዜናዊም፣ የሱዳኑ አልባሽርና፣ የሩዋንዳው ፓውል ካጋሜም፣ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንትም፣ በየፊናቸው ከደስታ ተካፋዮች ውስጥ አሉበት ይባላል።
ከሰላምታው ባሻግር…መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምና ሮበርት ሙጋቤ ወደ ምክሩ ዘልቀው እንደዚህ የሚለውን ቃል አያይዘው ፣ያኔ እንደተወራው፣ ለፕሬዚዳንቱ ልከዋል።
መነሻው ምክንያት የዛሬ መቶ አመት ገደማ ፕሬዚዳንት ሩስቬልት የሥልጣን ዘመናቸውን አገባደው ለአደን በዚያን ጊዜ የእንግሊዝ ቅኝ አገር የነበረችውን ኬንያን ጎብኝተው፣ አቃለው የተናገሩት ቃል እንደሆነ እንደሆነ አንዳዶቹ ገምተዋል። ሩስቬልት በዚያን ዘመን የነበረውን የጥቁር ሕዝብ “ሰነፍነው፣…ምንም ጊዜም ሰርቶ ጥሮ ከአለበት ችግር ከአለነጮች ዕርዳታ አይወጣም “የሚለውን ፍልስፍና ተከትለው፣ “…ኬንያን እንደአየሁት ከአለ እንግሊዝ ድጋፍ ብቻዋን እራሱዋን ችላ ልትኖር አትችልም” ብለው ፣እኚሁ ፕሬዚዳንት ስለ ጉብኝታቸው ሲጠየቁ መልስው ነበር።
ፐሬዚዳንት ኦባማ እንደተምረጡ አንድ የኬንያ ምሁር እዚህ በርሊን መጥቶ በአደረገው ንግግር፣ ይህን “አነጋገር” አስታውሶና ጠቅሶ እንደዚህም ብሎ ነበር። “…እነ ሊነከንና እነ ቶማስ ጄፈርሰን፣ …ይህን በአሉት በዋይት ሃውስ ውስጥ እነ ሩስቬልት በተኙበት አልጋ ላይ የኬንያ ደም ያለው ጥቁር ልጅ የአሜሪካን አገር ፕሬዚዳንት ሁኖ ተመርጦ እዚያ አልጋ ላይ ሲጋደምበትና ከኦቫል ሠገነት የአሜሪካንን የጦር ኃይል ዛሬ ሲያዝ እነሱ የቀድሞዎቹ መሪዎች ይህን ቢሰሙ ፣ መቃብራቸው ውስጥ ፣ ምሁሩ ኮርቶ እንዳለው፣እነሱ ወዲያና ወዲህ ይገላበጡ ነበር ” ብሎእል።
ይህን ታሪክ መንግሥቱ ኃይለማሪያምና ሮበረት ሙጋቤ “ወደ ዋሽንግተን ደብዳቤአቸውን ቁጭ ብለው ተመካክረው ሲጽፉ ” ያውቁ ነበር ለማለት ያስቸግራል። ግን እንደ ተወራው እንደዚህ ብለው ደብዳቤአቸውን ጀምረዋል።
“…. አሁን አንተ በስንት መከራ ከእዚህ ሁሉ የጭቆና አመት በሁዋላ የተገኘውን የጥቁር አሜሪካኖች ድል በቀላሉ ላለማስነጠቅ አንድ የቆረጠ፣ቁርጥና ቆፍጣና ሐሳብ ከአለህ፣ እኛ ታላላቆችህ የምንሰጠውን ምክር በጥሞና እንድታዳምጠው፣በመጀመሪያ ዝቅ ብለን እንጠይቀሃለን።
እንደሚታወቀው ድል አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚገኘው። እጅ የገባ ድል ደግሞ እንደ ነብር ጭራ ነው። ሳታውቅበት ሳት ብሎብህ ከለቀቀኸው፣ ነገ አንተ ብቻ ሳትሆን ድፍን የጥቁር ሕዝብ በዓለም ዙሪያ ጉድ ይሆናል።
ስለዚህ አሁን ቶሎ ብለህ ይህን “የዲሞክራቲክ ድርጅትህን አባሎች” በአስቸኳይ ለአንድ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተህ (እኛ እንደዚህ ያደርግነው) ወደ ብቸኛና ተቀናቃኝ ወደማይኖረው ሠራተኛው ፓርቲ (ኮሚኒስት እንኳን ብሎ መሰየም አሁን ያስቸግራል) ቶሎ ብለህ ቀይረው። የሊቀመንበሩን ቦታም አንተው ያዝ። የገባዔው ሰብሳቢ አንተው ሁን።ቶሎ ብለህ ሹም ሽር አድርግ። ትዕዛዝ አልቀበልም የሚለውን ክፍል ደግሞ በብልሁት ሰብሰብ አድርገህ፣እኛ ከአንዴም ሁለቴም ፣ደጋግመን እንዳደረግነው እምድር ቤት ውስጥ ነድተህ ግድግዳ አስይዘህ አለርህራሄ ረሽናቸው።
ቢቻልህ ምርጫ እንዳይደረግ ፣ሁል ጊዜ ያልታሰበ መሰናክል አዘጋጅ። አብጅ። ከአልሆነም “ለይስሙላ ፈቅደህ” መልሰህ ተቀናቃኞችህን ወይ እሰራቸው፣ ወይም አሰፈራርተህ እንዲሰደዱ አድርጋቸው።…ፊደል ካስትሮም አንዳንድ ነገሮችን ፣በዚህ የተካነ ስለሆነ ሊጨምርበት ይችላል። ችግር ሲያጋጥምህ ለእኛም ለእሱም ለካስትሮ ደውል። ከልምምዳችን ለማከፈል ዝግጁ ነን። ” ወዘተ፣ወዘተ፣ የሚለውነ ሐሳባቸውን ጽፈው፣ የአሁኑና ቀድሞው ፕሬዚዳነት ብለው ፈርመው (አያፍሩም ወሬውን ያወራው ልጅ ነው ያለው) ልከውላቸዋል።
“….ስማ ያልሆኑ ሰዎች ያለሆኑ ነገሮችን መናገር ይወዳሉ። ጆሮህን አትስጣቸው።….አሁን ላንተ ዋናው ቁም ነገር፣ መግቢያ መውጫ የሆነውን የኒዮርክን በርና ወደብ ይዘህ …” አቶ ኢሳያስ የላኩትን ደብዳቤ አየን የሚሉ ሰዎች ወሬውን እንዳናፈሱት”…ከአሜሪካን ግዛት ተገንጥለህ ፣ያን ያህል፣ አሜሪካንን የሚያክል አገር ለአንድ ሰው ተቆጣጥሮ ለመግዛት ከባድ ነውና ( በትግል ዘመኔ ችግሩን አይቼዋለሁ፣ በደንብ አውቃለሁ) የራስህን ትንሽ መንግሥት በመጀመሪያ እዚያው አቋቁም። ኒዮርክ ያለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤትም ፣ለእኛ እንዳደረገው አንተንም ይተባበራል። ከዚያ በሁዋላ እንደ እኔ የጠዳ ቤተ-መንግሥት ቁጭ ብለህ ( አምስት ሳንቲም አላወጣሁበትም ደርግ የወረሰው ነው)ኮኛክህን እግርህን ዘርግተህ፣እንደ እኔ እየጠጣህ፣ የተቀረቺውን ጊዜ በደስታ በሳቅና በፌዝ እንደ ማሳለፍ ትልቅ ነገር በዚህቺ ዓለም ላይ ፣ሞኝ አትሁን ፣ የለም።

እኔም ሥልጣኑን ስጨብጥ ዕድሜዬ እንዳተው ነበር።
….ምርጫ የሚባለውን ነገር እነዚህ አውሮፓያኖች እንዳያነሱብህ እንደ እኔ –ይኽው እኔ ይህን ያህል አመት ዕረፍት አግኝቼ እኖራለሁ- የምርጫ ሥነ-ሥርዓቱን የሚያብራራ ሕገ-ምንግሥቱ አልተነደፈም:- ጊዜ ስጡኝ ብለህ ሲጠይቁህ ይህቺን ብቻ መልስላቸው።ይህን ሲሰሙ ደስታውን በእኔ ይሁንብህ ደስታውን አይችሉትም።
እነሱ፣ በእኔ ይሁንብህ ይህን ሲሰሙ ዝም ብለው እንደ ተለመደው ትንሽ አጉረምርመው ያልፉሃል። በደንብ አውቃቸዋለሁ ።አያስቸግሩህም ።የሞስሊም ሃይማኖት ተከታዮችንም አበረታታ። ያ! እኔ ያሳደኩትን ልጅ ግን ፣አለሁ አለሁ ማለቱ አይቀርም ከቁም ነገር አደራህን እሱን ምንጊዜም አትቁጠረው። ያንተው ኢ…”
የዋይት ሐውስ ሰዎች ተገርመው ይህን ሲመለከቱ፣ ሌላ ደብዳቤ ከምሥራቅ አፍሪካ ፣ ከአቶ መለሰ ዘንድ በአናቱ ላይ ከተፍ ይላል።
“…ውድ ኦባማ! በስንት መከራ የተገኘው “የጭቁኖች መንግሥት”፣ አንተም ፣አማካሪዎችህም ይህን በደንብ ታውቁታላችሁ፣ በሰላማዊ ምርጫ በማግኘትህ እኛን ደስ ብሎናል። ታውቀዋለህ እኛ በስንት መስዋዕትነት በጠበንጃ እነዳገኘነው። ለዚህ ነው ደግሞ ለማንም በምርጫ ተሸንፈን መልሰን የማንለቀው። ሥልጣን ላይ እንደ እኔና እንደ ድርጅቶቼ ለረጅም አመታት በገዢነትህ ለመቆየት ከፈለግ፣ መንገዱም፣ብልሃቱና ዘዴውም በጣም ቀላል ነው።
በዘር ከፋፍላቸው። እንዲያውም ከእኔ ይልቅ ለአንተ ሁኔታው በደንብ ያመቻል። ጀርመኑን፣ አየርላንዱን፣ ጣሊያኑን፣ ፈሪሣይውን፣ ዌልሱን፣ ሕንዱን፣ናይጄሪያውን ፣ኮንጎውን፣ሱማሌውን ፣ ኬንያውን፣አይሁዱን፣ ላቲኑን፣ ጃፓንና ቻይናውን፣ ሩሲያና ጆርጂያውን፣ አርመኑንና ግሪኩን፣ እራሱን ሐበሻውን፣ አማረ፣ትግሬ፣ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ሐማሴን አካለጉዛዬ ፣..ጎንደሬ እያልክ የአሜሪካንን ሕብረተሰብ (ለአንተማ ሁሉ ነገር የሰጠነው) ሽንሽነህ፣ ተብትበህ፣ እንደ እኔ ቤተ-መንግሥት ገብተህ፣ ሸንጎ ውስጥ ሰዎችህን ሰግስገህ፣ ዕድሜ ልክህን በቀላሉ መግዛት ትችላለህ። ያኔ ነው የጭቁን ሕዝቦች መብት ታላቁ ሖጅያ እንደሚለው ዘለዓለማዊ ሁኖ የሚቆዩት። እንግሊዞችም ደህና አድርገው በዚህ ዘዴ ፣ምሥጢር አይደለም ዓለምን ገዝተዋል።
ሌሎቹ ግን እንደ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምና ያ ተነኮለኛ ኢሳያስ የሚሉህን (ወደቡን ይዘህ ተገንጠል ሳይልህ አይቀርም መቼ አጣሁት የእሱን ሥራ) ጨርሶ እሱን በእኔ ይሁንብህ አትስማው። አደራህን…ፊርማ መ.ዜ.”
“…ሥልጣን ላይ መቆየት ከባድ ይመስላል እንጂ በጣም ቀላል ነው።የሰው ልጅ በተፈጥሮው ነፍሱን ሰለሚወድ ፣ በደንብ አውቀዋለሁ ፈሪ ነው። ከዚይም በላይ የተራባ ይሁን የጠገበ ሰው፣ በተፈጥርው እንደዚሁ አይግባባም።ሌላው ሰው በቀላሉ ለሆዱ ይገዛል። የሰው ልጅ፣ ምክሬን እኽ ብለህ አዳምጥ አንድ ቀን አምርሮ ከተነሳ ደግሞ አደገኛ ነው። ይገለብጠኻል። እሱ እነንዳይሆን በየጊዜው ያልሆነ ነገር እያነሳህ እንዳያስብ አድርገው። እኔ አንዴ በአቶም ቦንብ አጠፋችሁዋለሁ እያልኩ የምዝተው፣ እንዴ እኔጋ ኑ እያልኩ የምጋብዘው፣ ሌላ ጊዜ የደቡቡን ወንድሞቼን በስልክ የማነጋግረው፣ ዞር ብዬ የኢራን ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የምገባው ለሌላ ነገር አይምሰልህ። ሰው አርፎ በእኔ ላይ ተነኮል እንዳይጠነስስብኝ ነው።ሥልጣንን ላይ ተቀምጦ እነደ ንጉሣዊ ቤተ-ሰብ ፣ አልጋውን ለልጅ ልጆች ማውረስ ደግሞ  እንዴት ያለ ደግ  ነገር ነው አባቴ ይሉኝ ነበር። …
መቼም ጠበኛ ብንሆንም -አትርሳ-ሁለታችንም የሥልጣን ሰዎች ነን። አባቴ ኪም ኢልሱንግ ይህን ሲሉ ያኔ ልጅ ስለነበርኩ፣ (ማርክስና ስታሊን፣ ሌላውም አባቴ ማኦ …እንደዚህ ዓይነቱን ነገር ቢሰሙ ምን ይላሉ ብዬ…) ወራሼ ሌላ ሰው ሳይሆን “አንተ ነህ ” ሲሉኝ ይዘገንነኝ ነበር። ግን አሁን አየሁት ። ሥልጣንን ለልጅ እነደማቆየት ጥሩ ነገር የለም። የእኔም ወራሽ– እወቀው ውዱ ልጄ ነው። እንኳን በዲሞክራሲ ምርጫ ሥልጣን ማስረከብ ቀርቶ ከቤተሰብህ ይህ አንዴ (ተውቃለህ እኔ በእግዚአብሔር አላምንም አቴኢስት ነኝ) እግዚአብሔር የሰጠህን የጥቁር ገዢነት ቦታ ፣ ከዘርህ እንዳይወጣ ከፈለግህ፣ ልጆችህ ገና ጩጬ ስለሆኑ ፣ ሚስትህን ተተኪ አድርጋት።

በአሜሪካን አገር ሴት ፕሬዚዳንት ሆና አታውቅም ይባላል። ስለዚህ ጊዜው ለአንተም ለእኔም አመቺ ነው። ምክሬን ስማ ። ከሚስትህ በሁዋላ ፣እሱዋም ሞግዚት ሁና ልጆችህን ልትመክር ትችላለች–አንዱዋን ብልህ ልጅ እጩ አድርጋት። ኪዚያ በሁዋላ የልጅ ልጆችህ….እንደዚያ እያለ ያንተም የእኔም ውርሰ-መንግሥታችን ለሚመጡት መቶ አመቶች ይቀጥላል። ምን ይታወቃል፣ ማርክስ እንደሚለው የኮሚኒስት ሥርዓት ጊዜውን ጠብቆ ከመምጣቱም በፊት አንተም ወደ እኛ ፣ሠፈር ደስ ብሎህ ጎራ ብለህ ከተደባለክ ልጆቻችንም ይጋቡና ዓለምንም በጋራ ተከፋፍለን እንገዛም ይሆናል። ፊርማ ኪም ኢል ጁ…”

መቼም የአንድን ሕዝብ ታሪክና ባህሉን አለማወቅ፣ ምን ያህል እንደሚያስቀባጥር እላይ የተጠቀሱት ደብዳቤዎች ሕያው ሁነው (ደብዳቤው ይኑር አይኑር…ሌላ ነገር ነው፣ቀልደኞቹ ግን ይህቺን ጨዋታ ከየት እንደ አገኙ እግዚአብሔር ይወቀው) ይመሰክራሉ።
በአሜሪካን አገር አንድ ሰው ብድግ ብሎ “የፈለገውን ነገር በሥራ ተርጉሞ ” ዕድሜ ልኩን እንደ ሰሜን ኮሪያ፣ ወይም እንደ ዚምባቡዌ፣ እንደ ኤርትራና ኢትዮጵያ ፣እነደ ሳውዲና እንደ ጆረዳኒያ ፣ሶሪያ ሊገዛ አይችልም። ለምን?
መላ አማራ ለተሸነፉት የሪፓብሊካን ድርጅት መሪ ፣ አንዳንድ የነጻ -አውጪ ድርጅት ተጠሪዎች ደግሞ በስውር ተደራጅተዋል ተብሎ ለሚነገረው “ለሎሳንጅለስ፣ለካሊፎርኒያ፣ለቴክሳስ ነጻ አውጪዎች ድርጅት ታጋዮች፣ ጊዜው ለመገንጠል አሁን ነው በርቱ…” የሚሉ መልእክቶችን –ይዘቱን አልሰማንም–አስተላልፈዋል ይባላል።
ወይ ጉድ!
“እኛ ማን ነን !” የሚለው፣ በቀላልና በሚገባ ቋንቋ የተጻፈው የፐሮፌሰር ሳሙኤል ፒ.ሐንቲንግተን መጽሓፍ ፣ እላይ የተጠቀሱት ሰዎች ለፕሬዚዳንቱ፣ ለባራክ ኦባማ የሰነዘሩአቸው ሓሳቦችና ምክሮች፣ ምንም እንኳን የኤሜሪካ ሕዝብ “ከአምስት ሺህ በላይ ከሆኑ የዓለም ዘሮች የተውጣጣ ቢሆንም” አንዱንም ”ተንኮለኞቹ ” የሰነዘሩትን ሓሳብ በሥራ ላይ መተርጎም አንደማይቻል ጥሩ አድርጎ ያሳያል።
ይህን አገር እነማን እንደ መሰረቱት በዝርዝር ከማሰቀመጡና ከማስጨበጡ በፊት መጽሓፉ፣አሜሪካን አገር ውስጥ እየተስፋፋ ስለ መጣው “የማንነት፣ማለት የአይደንቲቲ ቀውስም በትውልዱ ዘንድ”እንዴት እነደሆነ ያነሳል።
ወረድ ብሎም ደግሞ ይህን የቆየውና የኖረውን፣አሁን እየወደቀ የመጣውን “የአሜሪካዊነት መንፈስን እንደገና እናድሰው ” ብሎ “አሜሪካንን ፣ አሜሪካ!”ያደረጉትን የነገሮች “አስኳል”-ማወቅ ለሚፈልግ ሰው ጥሩ አድረጎ ምሁሩ አስቀምጦ ግሩምና ሸጋ ትምህርት፣(እንደገና ለማወቅ ለሚፈልግ ሰው) ይሰጣል ።

የአንድ አገር “መንፈስ፣ የዚያም አገር ነፍስም” እሱ እንደሚለው “ውቃቤው”ምን እነደሆነ ያነሳል።ምንድነው ከዚያና ከዚህ፣ ከዓለም ዙሪያ በተላያዩ ዘመናት አህጉሩን ረግጠው “እዚያ የሰፈሩትን የመጡትን አሜሪካኖች አንድ ያደረገው፣ ነገር?… አንድ የሚያደርጋቸው እርሾ እሱ ምንድነው? ብሎም ይጠይቃል።
… የጋራ ታሪካቸው፣የጋራ ባህላቸው፣ የጋራ ወግና -ሥርዓቱ፣ ልማዱና የኑሮ ዘይቤው፣..በአሱ ላይ፣ ሐንቲንግተን፣ የተመሰረተ ነው ይላል። እንዴት?
 ሁሉም በተለያዩ ጊዜ ተንጠባጥበው የመጡ መጤ “ነፍጠኞች” ናቸው። ታዲያ ያ! እሱ… የጋራ ታሪክ፣የጋራ ባህል፣ወግና ሥርዓት፣ ልማድና የኑሮ ዘይቤ ከየት መጣ? እንዴት አንድ ወጥ ሆኑ? ….ይዋሻል እነዴ ሰውዬ? የሚል ተጠራጣሪ አንባቢም አይጠፋም።
ሐንቲንግተን ለረጅም አመታት የአሜሪካንን መንግሥት አማክሮአል። ግን እሱ እንደተመለከተው፣ ይህ በየፊናው እያንዳንዱ ጎሣ፣ ነገድ ወይም በዘርና በቀለም ላይ የተመሰረተ “ክፍፍል” የሁዋላ ሁዋላ “ታላቁን አሜሪካ ይጎዳል ፣ያዳክማል ” ብሎም ያስጠንቅቅና በቀጥታ ልዩነትን ከመቁጠር፣ከእሱ ይልቅ፣ ሐንቲንግተን ወደ አሜሪካኖች አንድነት፣ አንድ ሰለአደረጋቸው እሴቶችና ታሪኮች፣አመለካከቶችና ትምህርቶች፣ ወደ አሜሪካን ስፒሪት፣ መንፈስ፣… ዝርዝር ሁኔታ ውስጥ በአራት መቶ ሃምሳ ገጽ ጽሑፉ(ዋለለኝ መኮንን የእኛን ታሪክና አንድ እንዳልሆን የሚያትተውን ትንተናውን ፣ ልዩነቶቻችንን በአሥር ገጽ አሱና ሌሎቹ ጨርሰውታል) ሐንቲንግተን ፣ለማስረዳት ሳይታክተው ይመላለሳል ።
ፓትሪዮቱ (የአሜሪካን)ሐንቲንግተን፣ የታወቀው የፖለቲካ መጽሔት “የፎርን አፌርስ” መጋዚን አንደኛው አዘጋጅ ነበር። ከዚያም በላይ እሱ እራሱ እንደሚለው “የአሜሪካ ናሽናሊስትና አገር ወዳድ ቆራጥ ሰው ነው።”በመሆኑም፣ በአገር ጥያቄ ላይ ብዙ ቦታ ደጋግሞ እንደ ጻፈው “…ቀልድ ፣በአገራችን:- በአሜሪካ ላይ የለም!” ይላል።

ሳሙኤል ሐንቲንግትን ይህን መጽሐፍ ከመጻፉ በፊት” የባህልና የሥልጣኔ ጦርነት ” በሚለው መጽሐፉ (ይህ መጽሐፉ ብዙዎቹን አስቆጥቶአል። ሌሎቹን አስደስቶአል) መጪውን የ21ኛውን ክፍለ-ዘመን ችግሮች አንስቶ ተናግሮአል።

አሜሪካንን አሜሪካ እንድትሆን ያደረጉትን “አንኳር ነገሮች” ምሁሩ ሳይጣደፍ ረጋ ብሎ በዚህኛው መጽሓፉ ላይ አንስቶአል።
 ስለ መጤ የአውሮፓ የመጀመሪያው ሠፋሪዎች፣አንስቶም “የአንግሎ ፕሮቴስታንቶች ባህልና ሥልጣኔ አሜሪካንና አሜሪካዊነት በዚያ ምድር ላይ እነደአቆመና፣መሰረት እንደ ጣለ፣ አሜሪካዊነትም በዚያ ላይ እንደተመሰረተም” ሰውዬ ይገልጻል። ሌሎቸን መጤዎችን ደግሞ ሰይረሳ ስለ እነሱም ያነሳል።
ግን ቁም ነገሩ እዚህ ላይ ነው:-
አሜሪካ የቆመችበት መሠረትና ምሶሶ ፣ወይም አስኳል፣ በሚለው አንቀጹ — የተቀረውን ፍላጎት ያለው ሰው አገላብጦ ጽሑፉን ለያየው ይችላል–የሚከተሉትን ቃላቶች፣ አስፍሮአል።
“….አብዛኛው አገሮች የተገነቡበትና የቆሙበት ፣ ብዙሃኑም ሕዝብ አምኖ የተቀበለው አንድ ነገር፣ምንጊዜም፣ ሁሉም ቦታ አለ። እንደዚህ ዓይነቱን ነገር ደግሞ ሁሉም የቆዩ መንግሥታት በየፊናቸው፣ በየቅላቸው አሉአቸው። ከዚሁ ጋርም ሌሎች ዝቅተኛ የሆኑ ግን ደግሞ አብረው ጎን ለጎን እና እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚሄዱ ሌሎችም፣ስፋትና ጥልቀታቸው ግን ከዋነኛው ምሶሶ ፣ ዝቅተኛ የሆነ ፣ ባህሎች፣ ..ሃይማኖቶች፣ ዘሮች፣ስብስብና ግኑኝነቶችም… አሉ።
አንድ ግን ፣በዓይን የሚታይ የአሜሪካን ባህልንና ሥልጣኔ፣ከማንኛውም በልጦ የወሰነ፣ ቁዋሚ የሆነ ምሶሶ፣ወይም አገሪቱ የተገነባችበት መሠረት አለ።….እሱም የአንግሎ ፕሮቴስታኞች ባህል የሚባለው ንጥረ-ነገር ነው። ይህን ባህል ሁሉም እኩል አዚያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ፣ አገሪቱ አሜሪካ በዚህ ላይ ስለተገነባችና ስለተመሰረተች፣ ሁሉም ይህን እሴት እኩል ይጋሩታል። ይህ ደግሞ ለአለፉት አራት መቶ አመታት ይህቺን አገር ባህር አቋርጠው ምድሪቱዋ ላይ የሠፈሩትና የቆረቆሩት የመጀመሪያው አባት ነፍጠኞች መሬቱ ላይ የቸከሉት፣የማይናወጠው፣የማይሻረው ባህል ነው። የአሜሪካ አይደንቲቲ ፣ ማንንነታቸውም የሁሉም አዚሁ ላይ የተገነባ ነው።” ብሎ ቀጠል አድርጎ ግሩም የሆነ ጥያቄ አንስቶ እሱ እራሱ እንደዚህ አድርጎ ይመልሰዋል።
“…እስቲ እራሳችን እንደዚህ ብለን እንጠይቅ። አሜሪካ በ17ኛውና በ18ተኛው ክፍለ-ዘመን በብሪቲሽ ፕሮቴስታንቶች እጅ ሳትያዝ በእሱዋም ሥር ሳይሆን ፣ በ ፈረንሣይ ወይም በእስፔን ወይም ደግሞ በፖርቱጊዝ ካቶሊኮች መዳፍ ውስጥ ብትወድቅ ኑሮ ፣ ይህቺ አገር አሜሪካ ዛሬ ምንትመስል ነብር? ምንስ ዓይነት አሜሪካ ይወጣት ነበር?… ወጤቱ ግልጽ ነው።
ዛሬ የምናውቃት አሜሪካ ሳትሆን ይህቺ አገር :-ውጤቱ ፣ በተቃሪኒው፣ ኪዩቤክ፣ ወይም ሜክስኮ ወይም ደግሞ የዛሬው ዓይነት ብራዚል በሆነች ነበር።
የአሜሪካ አንግሎፕሮቴስታንት ባህልና ሥልጣኔ ፣….የፖለቲካ አካሄዱ፣ የሕብረተሰብ አወቃቀሩ፣ ወግና ሥርዓቱ፣ የኑሮ ዘይቤው፣ …ሁሉም ነገር ከእራሱ ከቋንቋው ጀምሮ ፣ በአጭሩ እንግሊዛዊነት ማለት ነው። …የብሪቲሽ ባህል ነው።” እያለ ለምን እላይ ከተቆጠሩት ፣ከሜክሲኮና ከፖርቱጋል፣ከእስፔንም መዳፍ እንዳመለጡ ምሁሩ አመጣጣቸውን ይቆጥርልናል።
እዚህ ላይ፣ አስተዋይ አንባቢ ” ኢትዮጵያ በሰይፍ በአረቦች ብትሸነፍ፣ በቱርኮች ብትያዝ፣ የጣሊያን ቅኝ ብትሆን፣ ፖርቲጊዞች በመካከለኛው ክፍል እንደተመኙት ቢጨፈልቁንና መዳፋቸው ውስጥ ገብትን ቢሆን፣ …ምን እነሆን ነበር ብሎ? አንድ ኢትዮጵያዊ ሐንቲንግተንና እራሱን ቢጠይቅ መልሱ ምን እንደሚመስል መገመት ከባድ አይደልም ።
የመጀመሪያውና የሁለተኛው አማራጭ ቢከሰት ኑሮ ልክ እንደ ጎረቤት አገሮች እንደ ግብጽና እንደ ሱዳን እንደ ሱማሌና እንደ የመን እኛም …አረብ እንሆን ነበር። የግዕዝን ፊደል ትረሳለህ። እሱ ከአልሆንም፣ የጣሊያንና የፖርቱጋል ቅኝ ተገዢ ብንሆን ኑሮ ፣እሰከ “ሁለተኛ ክፍል ብቻ የሚማር ፣አገልጋይ ባሪያቸው” ሆነን በቀረን ነበር።… ሃይማኖታችንም ሐንቲንግተን እነደ አለው ፖርቱጋል እንደ አሰበችው” ካቶሊክ” እንሆን ነበር።
መቼም ሐንቲንግተን የጻፈው መጽሐፍ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “ጥቁር ባሪያቸውን ጣለው ብለው በጅራፍ የሚገርፉ” አንዱ እንዳለው ” የአሜሪካን ነጮች” እንዴት አድረገው “…ነጻነትና ነጻ -ሕብረተሰብን ፣ ሰበአዊ መብቶችን …” እንደ “የሕይወት እሴት አስኳላቸው አድርገው” ያቺን አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ኃያል አንዳደረጉዋት ከጽሑፉ ከሞላ ጎደል ብዙ ትምህርቶችን ታታሪ አንባቢ እዚያ ውስጥ ፈልጎም ያገኛል።
የሙጋቤና የመንግሥቱን ደብዳቤ ዕውነት ከሆነ፣ የመለሰና የኢሳያስ ጻፉ የተባለው ምክር፣ እንደዚሁ እርግጠኛ ከሆነ፣ አዎን የኮሚኒስቱ የኪም-ዳይናስቲ ፣የውርሰ መንግሥቱ ነገር ለኦባማና ለቤተሰቡ እላይ እንደተባለው፣”ለጥቁሮች የባላይነት በአሜሪካን፣ አመቺ ነው” የተባለው የኪም ትንትና እንደዚሁ ሓቅ ከሆነ ፣ ይህ ነገር በምንም ዓይነት እዚያ አህጉር፣በአሜሪካን በሥራ፣ በማንም ሰው መጽሓፉ ላይ እንደሰፈረው ሊተረጎም አይችልም።
አምባገነኖችን በአሜሪካ አስፈላጊ ከሆነ –ለዚህ ነው አሜሪካኖች ጠበንጃን የሚወዱት- በጥይት እስከ ማባረር ድረስ ሕጉም ለሕዝቡ፣ተነስቶ እንዲዋጋ በደንብ (የአሜሪካን ሕግ )ይፈቅድለታል።
 መጽሓፉን አንብቦ (እኛ ማን ነን !) የሆሊውድን የካው ቦይ የእረኛ ፊልሞችን እንደገና በሌላ ዓይኑ ቢመልከት ፣ አንድንድ ነገሮች እዚያ ውስጥ ያገኛል። መንበቡ ግን የበለጠ ይጠቅማል።
በሶስት ነገሮች አሜሪካኖች መጥቀው ሄደዋል። በሰይንስና በቴክኖሎጂ፣ በሆሊውድ ፊልምና በለበርቲ፣በሰበአዊ መብቶች መከበር ጥያቄ ፣ የማይነጠቁ ሜዳዎችን እነሱ ይዘዋል። ይህን የምትለው ደግሞ ከሐንቲንግተን ጋር ኮነደሊዛ ራይስ ናት።
ሰውዬው ሐንቲግተን የአሜሪካ ወደፊት ዕጣ ዕድል እንደአሳሰባቸው ፣ ከእነ መፍትሔው ጥሩ አድርገው በዚህች መጽሓፋቸው:- “እኛ ማን ነን” ላይ አስፍረዋል። አሜሪካንን ለመረዳት መነበብ ያለበት መጽሓፍ ነው።

___

—————————————————-

https://leaimero.files.wordpress.com/2013/04/a_schreibfeder.gif

አስተያየት ለመስጠት / Comments

——————————–

——————–

leaimero-reg-logo © ለ አእምሮ 2005 / © Le’Aimero Copyright 2013

ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements

Le’Aimero’s Disclaimer

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s