ሦስቱ የፈላስፋው ጥያቄዎች !

ምሁሩ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው ሚናና ተግባሮች

አሳቢው/The Thinker (Photo Wikipedia) by Auguste Rodin – ፈላስፋው!

ሦስቱ የፈላስፋው ጥያቄዎች !

___

የዚህች ዓለም ነገር- የኢትዮጵያ ዓለም ነገር በጣም ይገርማል።
በባዶ ሜዳ ዘለዓለማዊ ይመስል፣ አንዱ ብድግ ብሎ ወደ ግራ – በእሱ እምነት- ወደ እሱ ብቻ እንሂድ ይላል። ሌላው የለም ወደ ቀኝ ብሎ ይመልስለታል። እንደ ሦስተኛ አማራጭ ጥቂቱ ለምን ወደ ፊት አንሄድም ይላል። አራተኛው ወደ ሁዋላ እንጂ ወደፊት የለም ብሎ ይከራከራል። አምስተኛው፣ በተራው አሁንስ በቃ በአለንበት እንቁም፣ እዚያው እንርገጥ፣ከእኔ ወዲህ ማንም የለም ብሎ ሁሉንም ይቆጣል። ስድስተኛው፣ ምን አለበት እንደፈለግነው በሁሉም አቅጣጫ ተበታትነን፣ በሁዋላ በልዩ አዲስ ዘዴ ብንሰባሰብ ሲል፣ ሰባተኛው ደግሞ “እኔ የለሁበትም፣ እናንተው እንደፈለጋችሁት ሁኑ” ብሎ ይሰናበታል። ስምንተኛው ይህ ትውልድ ከአልሞተ ምንም ዕረፍት አናገኝም፣ ይሙቱ! ይለናል። አሁን ደግሞ አንዳንዶች አብደው መሆን አለበት የሃይማኖት ጦርነት፣ ከዚያ በፊት ያዋጣል የሚሉም (አርፍደው) ተነሰተዋል። ወዴት?ወዴት!
የት ለመድረስ? ምን ለመሆን? እምቢ ቢባልስ? በአጭሩ ግን ማለት የሚቻል ነገር ቢኖር -ከዚህ ሁሉ ዓመት በሁዋላ “ሁሉም አብደዋል እንዴ ያሰኛል።” የዕብደት፣ በትክክል የፖለቲካ ዕብደት መነሻው ደግሞ-ሌላ ቦታዎች ታይተዋል- እንደዚህ ነው።
በእኛ መንደር ነገሮች ሁሉ፣ ሰው ማሰብ ና መመራመር አቅቶት፣ አንዱ እንዳለው፣ ይህን ይምሰላሉ እንጂ ፣አስተዋይ አንባቢ እንደሚረዳው እላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች አብዛኛዎቹ አንዳዶቹ እንደሚሉት በዘርና በነገድ ወይም በጎሣ…ሌሎቹ ይህን “…ብሔር -ብሔረሰብ “ላይ የተመሰረቱ የድርጅት መሪዎች አቋም ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ከአሉትም ድርጅቶች ውስጥ አብዛኛው፣ እነሱ ናቸው። ዕውነት?
በሌላው ዓለም የሚገኙት ምሁሮች፣ ጊዜአቸውንም፣ የሕይወት ዘመናቸውንም፣ጉልበቱንም፣ እንደምናውቀው የሚያሳልፉት፣ ሐብቱንንና ጭንቅላታቸውንም የሚያውሉት፣ በሌሎች ከባድ፣ የአገርና የሕዝብ ጉዳዮች ላይ ነው።
ለዚህ ደግሞ -ይህ የታወቀ ነው-ሌላ ሚሥጢር የለውም።
በመመራመርና አዲስ ነገር በመፍጠር(በዓይናችን በየሦስት ወሩ እናያለን) ባህልንና ሥልጣኔን በማስፋትና በማሳደግ፣ግሩም ድርሰቶችን በመጻፍ ፣ጥሩ ፊልሞችን በመቅረጽ፣ ቆንጆ ቤቶችንና አስደሳች መናፈሻዎችን በመሥራት፣ የሥራ ዕድል ለወጣቱ የሚከፈትበትን መንገድ በማሰላሰል፣ ጡረታ ለአዛውንቶች፣ ዋስትና ለደካማዎች፣ ለመጪው ትውልድ እንዴት ? በሚለው ሐሳብ ዙሪያ በመወያየት በመመካከር (ዞር ብላችሁ አካባቢአችሁን ቃኙ )፤ ሰዎች ጊዜአቸውን የሚያጠፉት በዚያ ላይ ነው። አውሮፕላን ሰርተዋል። አዳዲስ አይሮፕላኖችም ከመፍረጠርና ከመሥራት አልተቆጠቡም። መርከብ ሰርተዋል፣ ያውም ውስጥ ለውስጥ ውቅያኖስን የሚያቋርጥ…. ፋክስ፣ …የንፋስ ስልክ፣ኮምቲውተር፣…ሳተላይት…እኛ በዚያው ፣አንዱ እንደለው “ሞኝ በያዛቸው ነገር ላይ ጥዋት ማታ ስንነታረክ” ፣ ያውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተማራቸው ጎበዝ ልጆች ተሳትፈውበት፣ምዕራቦቹ በየጊዜው ሰርተው አውጥተዋል። አሁንም በዚህች ሰዓት፣በያዝነው ዘመን አዳዲስ ነገሮችን እየፈለፈሉልን ነው።
ፖለቲከኞቹማ በሥነ-ሥርዓቱ ሽንጎ ገብተው እዚያ ውስጥ የምዕራቡ ዓለም ውስጥ እንደምናየው፣ጋዜጠኞች በየጊዜው እንደሚዘግቡት መድረኩ ላይ ወጥተው “ይዋጣላቸዋል።” በጋራ የነደፉት ሥርዓቱም ፣ ለነዚህ እላይ ለተነሱት ጉዳዮች ሁሉ ፣ ጥሩ አድረጎ እንደምናውቀው መብታቸውን አክብሮ ይፈቅድላቸዋል።
ያ ! ሥርዓት ፣ ይህ ሥርዓት ምንድነው?…ምን ዓይነት ሥርዓት ነው፣በዚህቺ ዓለም ውስጥ የሰው ልጆችን ነጻነት ፣መብት የሚያከብረው? ዋና ጥያቄውም እሱ ነው።

በኢትዮጵያ ግን ይህ ፣እላይ የተቆጠሩት የአለመግባባት፣ ያለመደማመጥ “ታሪክ” የተጀመረው፣ ከዕለታት አንድ ቀን ፣ በትክክል፣ ለመናገር ከጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ በሁዋላ ነው።
ጊዜው መሽቶአል። በአዲስ አበባም ላይ ጸሓይ ጠልቃ ጨለማ ነግሶአል።
አንድ ወጣት፣ ከዕለታት አንድ ቀን፣ በዚያን ዘመንና ሰዓት በሩን በርግዶ ገብቶ፣ በጥድፊያ፣ያንን የመኝታ ክፍል በር ፣ቀስ ብሎ ግራና ቀኙን ቃኝቶ ከዘጋው በሁዋላ ፣ ትንሹ ጠረጴዛ ላይ በእጁ ሞነጫጭሮ የጻፈውን ባለ አራት አምስት፣ ስድስትና ሰባት ገጽ ወረቀት፣ አመልካች ጣቱን ከንፈሩ ላይ ጥሎ፣ ዝምም… እሽ…በሉ ብሎ፣ ጓደኞቹን አስጠንቅቆ፣ እንዲመለከቱት፣ ትልቅ ነገር ስለሆነም – ሰሞኑን ይበተናል ብሎ-አዚያ ክፍል ውስጥ የነበሩ፣ የተወሰኑ የተመረጡ “ምርጥ ልጆች ብቻ” እንዲመለከቱት፣ እንዲወያዩበትና እንግሊዘኛውንም አብረው እንዲያርሙት ይዘረግፍላቸዋል።
በዚያን ሰዓት የባቡር መንገዱን ተሻግሮ የሚገኘው የአልጋ ወራሹ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ፣ከራዲዮ ዜና በሁዋላ ወፍራም የሆሊውድ ፊልም ተለቆ አዳራሹ ውስጥ፣ ልጆች እየተንጫጩ ፣…የእነ ክለርክ ጋብል፣የእነ ሶፊያ ሎሬን፣ በርትና ዶሪስ ዴይ…ማሊሪነረ ሞንሮና ቶኒ ከርተስ ፣ምኑ ይታወቀል አንደኛው ፊልም ተመርጦ ይታያል።
በጥቂቱ ቢገመት ስድስት ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ በሚገኘው የኢዮቤሊዩ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ደግሞ ንጉሱ ከልጅና ከየልጅ ልጆቻቸው ጋር ራታቸውን በልተው፣ሁሉ ጊዜ እንደሚያደርጉት ውሾቻቸውን ተመልክተው፣ ቀዝቀዝ ያለውን አየር ለመተንፈስ ሰገነቱ ላይ ወዲያና ወዲህ ይላሉ።
ከጥቂት ሰዓታት በፊት ፈረሶቻቸውንና እዚያው ቅጥር ግቢ የሚገኙ አንበሶቻቸውንና አጋዘኖቸንም፣በእግራቸው ተዘዋውረው አይተዋል።
የዚያኑ ምሽት ወጣቱ ተማሪ ያን በሁዋላ “አገሪቱን የሚያነጋ” ብሎ የሰየመው ፓምፍሌት በዘረጋበት ሰዓት የዕድሜ እኩዮቸ ፣ ከ ቀ ኃ ሥ ዩኒቨርሲት ቅጥር ግቢ ዝቅ ብሎ አፍንጮ በርን አቋርጦ አፋፉ ላይ የሚገኘው በዘልማድ በጎልማሣ የከተሜ ልጆች ዘንድ “የውቤ በረሃ” የሚባለውን ስም ያተረፈውና በዚህም የሚታወቀው፣ ባለቀያዩ መብራት የመሸታ ቤቶች፣ “…ማንጎና ማሪንጌ አብረን የደነስንባቸው” የሚለው የጥላሁን ገሰስ ዘፈን ከእነ ሳም ኩክ እና ከነ ናትኪንግ ኮል ጋር አብሮ ይደመጣል። በቢትልስ ሙዚቃም ይጨፈራል። አረቄ ይጠጣል። የኤልቪስም ሸክላ ይቀየራል።… የዪኒቨርስቲ ተማሪዎች “አዲሲቱን ኢትዮጵያ ለመመስረት ነገሮች ሲያውጠነጥኑ፣ ሌላው ጎረምሳው ፣ እኩዮቻቸው “አንድ ወደ ግራ አንድ ወደ ቀኝ ” እያለ ጣውላውን፣ ከመልከ መልካም ወጣት ሴቶች ጋር አብሮ ይርግጣል።…አንድ ወደ ግራ አንድ ወደ ቀኝ!
ይህ ነገር የተጠነሰሰልን የጥፋት መንገድ መሰናክል፣ ጉድጓድ ይሆን? ብሎ እራሱን የጠየቀ ሰው የለም። መራራ ነገር መራራ መሆኑን የምታውቀው ስትቀምሰውና ከቀመስከኸው በሁዋላ ነው ይባላል። ከሁለት ቀን በፊት ዓለምን በኢትዮጵያ የጦር መርከብ አሜሪካ ደርሰው፣ አውሮፓ ዙረው፣ወደ ምጽዋ ተመልሰው ከዚያ በአይሮፕላን አዲስ አበባ ለዕረፍት የገቡት የባህር ኃይል ልጆች፣ የደብረ ዘይቱ የአየር ኃይል ወጣት መኮንንኖች፣ የአየር መንገድ አብራሪዎች፣…አንዳንድ ፈተና የጨረሱ የዩኒቨርሲት ተማሪዎች፣ የከተማ ነጋዴዎችና ደላላዎች ቢራውን እየተጎነጩ፣ ውስኪውን እያጣጣሙ፣ አብረው ሜዳውወውስጥ ገብተው ይጨፍራሉ። አንዳንዱ የጨዋ ልጅ እንደ ዛሬው የገዢዎች ልጅ ብቻውን የሚሽከረከርበት ጥሩ ግልጽ መኪና አለው። አንዳንዱ ላንድ ሮቨር፣ ይዞአል። ሌላው ኦፔል፣ የአባቱን ወይም የእናቱን ወይም ደግሞ የወንድሙን ጃጉዋር፣ ፔጆ…ደርድሮአል።
ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ዱሮም እንደ አሁኑ ሰዎች ታሥረዋል። እዚያው ቀኑን ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ደጃፍ የዋሉ ለማኞች በግንቡ ግድግዳው ዙሪያ ጥግ ጥጉን ይዘው ድሪቶአቸውን ደርበው በዚያች ሰዓት ተጋድመዋል።
የፒያሳ ሱቆች ተዘግተዋል። ከተማው ከአላንድንድ ቡና ቤቶች በስተቀር እረጭ ብሎአል። ከሲነማ ኢትዮጵያ የማታ ፊልም ባለትዳሮችና ትኩስ እጮኛ የያዙ ወጣቶች ተቃቅፈው ወጥተው ወደ መኪናቸው ይገባሉ። ወይም ታክሲ ይፈልጋሉ።
ቀኑ የትኛው ቀን እንደሆን አይታወቅም። ምናልባት አርብ ወይም ቅዳሜ ማታ፣ ብቻ ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ላይ፣ እንደተሰማው ይሆናል።
ዋላልኝ መኮንን በዚያን ምሽት በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች መኝታ ክፍል ለጥቂት ጓደኞቹ እንዲመለከቱትና በሁዋላም ትንሽ ቆይተው አብረውት እንዲያርሙት የዘረገፈው ጽሑፍ ከየት እንደ መጣ አይታወቅም። በዚያኑ ዕለት “ዓለም ጤና ነው” ብለው፣ አልጋቸው ውስጥ ገብተው እንቅልፋቸውን የለጠጡት “የጸጥታ ሰዎች” በሁዋላ እነሱ እንዳሉት የዚህ ጽሑፍ ዋና ምንጭ የሆነው፣ ያኔ የተከለከለውን የኮሚኒስቶች ጽሑፍ ለወጣቱ ተማሪ ያስጨበጡት አለጥርጥር “የሩሲያ ኢምባሲ ሰራተኞች” ናቸው ተብለው ውስጥ ውስጡን ተከሰዋል። ሌሎች ከዚህ ሁሉ ተንኮል ጀርባ የተቀመጡት ንጉሱን ከመጣል የማይመለሱት “እንግሊዞች ናቸው፣ በመሆኑም በአስተማሪዎቻቸው በኩል፣ ይህን የስታሊንን በራሪ ፓምፍሌት፣ በሁዋላ ዋለልኝ የተረጎመውን አቀበሉት” ብለው እነሱን ጠርጥረዋል።

እስከ አሁን ድረስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የታወቀ ነገር ። ግልጽ ሁኖም የወጣ “ምሥጢር “የለም። ግን በዚያን ዘመን ከተባረሩት፣ሰባት የራሺያ ኢምባሲ ሰራተኞች ውስጥ አንዱን ሚስተር ሻራዬቭን በሁዋላ የሞስኮ የኮሚኒስት ፓርቲ ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና የብሬዠኔቭና የመንግሥቱ የአማርኛ አሰተረጓሚ የሆኑትን ሰው እንደ አጋጣሚ አግኝቼ እሳችው ይህ ነገር “ዕውነት”ነው ብለው አላጫወቱኝም።

ወጣ ወረደ፣ ዋለልኝ “ትንሽ ውይይት እንዲከፈት ፕሮቮክ ላድርግ” ብሎ የጀመረው ጽሑፉ፣ ምንም ዓይነት ብዙ ድካምና ምርምር የሚጠይቅ ሰፋ ያለ ፣የሚያሳምን አንዳች ጥናት ሳያቀርብ፣ ብድግ ብሎ እንደ የምድር ዝላይ፣ ስፖርተኛ ተንደርድሮ፣ ፈንጠር ብሎ እንደሚዘል ሰው፣ ከጥቂት መስመር በሁዋላ በሁለተኛው ገጹ ላይ “ኢትዮጵያ አንድ ብሔር ሳትሆን ትላንት እንዲያው በአጋጣሚ የተገናኙ ይመስል ” የተለያዩ ብሔር ….አገር ናት…” ስለዚህ ብሎ በዚያችው በጥቂት ገጾቸ ላይ ፣ ስለመጪው “አዲሲቱ ሶሻሊስት ኢትዮጵያ፣ ምሥረታም” -እሱ ብቻውን አይደለም- ንድፈ ሐሳቡን ይለቀዋል።
እንግዲህ ይህ ነው፣ “በታሪክ ሂደት የማይቀር ነው ተብሎ የተነገረለት የኮሚኒስት ሥርዓት” የኢትዮጵያ ተማሪዎችን፣ ወታደሩን ፣ ሰራተኛውን ፣ ትውልዱንም ጭምር፣ “ቀዩ መስፍንንም “እነ ራስ እምሩን፣እነ ደጃች ከበደን፣…. ሳይቀር፣ማርኮ“የትርምስ መነሻም የትርምስም መጨረሻም አገሪቱን ያደረገው። “
ከዚሁ ጋር በአውሮፓና በአዲስ አበባ የማርክስና የሌኒን ጽሑፎች ማንበብም ያኔ ተጀምሮም ነበር። ስለ አዲስ አበባው ብዙ ባይታወቅም በአውሮፓ፣ በተለይ ….በበርሊንና በፍራንክፈርት፣ በፓሪስ ና በለንድን፣ ሞስኮ የለየለት ነው፣…በዩነቨርሲቲ ደረጃም ይህ ትምህርት መንግሥት በቀጠራቸው አስተማሪዎች በኩል ይሰጥም ነበር።

“ሶሻሊዝምና የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ትክክል ነው? ወይስ አይደለም”፣ “ዲሞክራሲና የሰበአዊ መብቶች መከበር አስፈላጊ ናቸው ወይስ አስፈላጊ አይደሉም” “የቡርዣ ዲሞክራሲ ምንድነው?… አምባገነን ሥርዓትስ ምንድነው? ” የሚሉ ውይይትና ክርክር ተከፍቶ፣ ተማሪዎች፣ ከአስተማሪአቸውም ጋር –ለዚህ ግን ያኔ ቁም ነገር የሰጠው የተወሰነ ክፍል ጥቂት ተማሪዎች ብቻ ነበሩ– ወጣቱም በዩኒቨርሰቲው የትምህርት አዳራሽ ውስጥ ከሌላ የፖለቲካ አቋም አራማጆች ጋር ተያይዘው ፣ይፋጩ ነበር።
እንግዲህ እንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ እዚያ አዲስ አበባ ውስጥ ውስጡን “ይኑር አይኑር “ምንም የምናውቀው ነገር የለም።
ፕሮፌሰር ባህሩ በአደረጉት ” የጥያቄና መልስ” ጥናታቸው፣ በዚያን ዘመን ተዋንያን የነበሩ ምሁሮችም፣ ያነሱአቸው የቃል ኑዛዜ (ኦራል ሂስትሪ ) ላይ ፈልገን ምንም ፍንጭ አላገኘንም።

የምናውቀው ነገር ቢኖር ፣አሥር የማይሞሉ መጻሕፍት ( አንድ ከሌኒን አንድ ከስታሊን፣ አንደ ከማርክስ አንድ ከኤንግሊስ፣ አንድ ከኮለንታይን፣ ትሮትሰኪና ፕሌካኖቭ፣ እንዲሁም ማኦ፣ ፍራንስ ፋኖንና ቼ፣ ሆቺ ሚን) ከእነሱ በተሰበሰቡና በተገኙ ዕውቀቶች ወደ አምባገነኑ የአንድ ፓርቲ ወደ ሶሻሊዚም ሥርዓት ጉዞው ተጀመረ ።

ዋለልኝ ከዚህ ተነስቶ “ከእንግዲህ አይዲኦሎጂአችን ሶሻሊዝም ነው…” (ከሌሎች ጋር ሁኖ) ይለናል። ይህን ብሎም የብሔር ትግልን አያይዞ ጠቁሞ  (እሱ ብቻውን አይደለም )”ያወጀው አዋጅ” ከእዚሁ ከዘመኑ ጋር ብቅ ከአለው “የዮሴፍ ስታሊን ዕውቀት” የመነጨ ነው ። የጀርመኑ ዜዲኤፍ/ZDF/ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ጥላሁን ግዛው ፣እነደተቀረጸውና ድምጹ እንደ ተቀዳው “ከእንግዲህ ትግላችን ፕሮትራክትድ ዎር” ነው፣ ብሎም እሱም፣በተራው የጊዜውን የማኦ አዋጅ፣ ከጀበሃና ሻብያ ጋር አብሮ፣ አዲስ አበባ ላይ አውጆአል።
“ለአዋጁ አዋጅ” ብለው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም እሩጫቸው ወዴት እንደሆን ትንሽ ቆይተው ግልጽ አድርገዋል። የአውሮፓ ማህበር ፣የሰሜን አሜሪካ፣ …የሱዳንና የመካከለኛው ምሥራቅ አገር የኢትዮጵያ ተማሪዎች ውሳኔ በውሳኔ በየአመቱ፣ወደዚያው ወደ ሶሻሊዝምና ወደ ኮሚኒዚም በሚወስደው መንገድ ላይ ያተኩራል።

እንግዲህ በዚያን ጊዜ የተጀመረ የሶሻሊስት ኮሚኒስት ፍልስፍና እና አስተሳሰብ፣ ይኸው “…አንደኛ ቅራኔ፣ ሁለተኛ ቅራኔ፣ሦስትና አራተኛው ቅራኔ ፣…እያለ የሚነጉደው “ትምህርት” ትንሽ ቆይቶ ” አንደኛው ቅራኔ ቦታውን ለሁለተኛ ቅራኔ ለቆ፣ ወደታች ወረደ…” ይለናል።
ይህ የማኦ ሴቱንግ “ዲያሌክቲክስ” ቀስ ብሎ የወጣቱን አንጎል ይዞ ባሪያው ከአደረገ ወዲህ፣ ሁሉ ነገር ተጓቶና ተደበላልቆ ማሰሪያ ሳያገኝ አሁን ያለንበት 21ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ተከትሎን መጥቶአል።

ግን ደግሞ አንድም ቦታ ላይ ጠንክረው የኢትዮጵያ ምሁሮች “…ስለ ነጻ ሕብረተሰብ፣ ስለ ነጻ-ፕሬስ፣ ስለ ሰባዊ መብቶች መከበር፣ ስለ ፓርላማ ሥርዓት፣ ስለ ብዙ ፓርቲዎች በአንድ አገር መኖር ፣… ስለ መንግሥትና አስተዳደር ምሥረታ፣ እስከ መጨረሻው ይህ ምን ይመስላል? ” ብለው በግልጽ ተከራክረው ሲለያዩ የትም ቦታ ላይ አልታዩም። ወይም አላስተማሩም። ወይም ደግሞ በግልጽ ደፍረው ከዱሮ ትምህርት አልተላቀቁም።

በእሱ ፋንታ “አምባገነን መንግሥት ” የትም ይሁን የት በአፍሪካ ” ትክክለኛ መፍትሔ ነው” ተብሎ፣(ይህ እኮ በእራስ ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ነው) ይህን ሐሳብ ብዙዎቸ ታቅፈውት ቁጭ ብለዋል።
በመጨረሻው “የአልባኒያው ሞዴል” የሚሉት በኢትዮጵያም በኤርትራም አሸናፊ ሁነው ይወጣሉ።

በእንግሊዘኛ ተናጋሪ አገሮች ውስጥ፣በእነሱ ዘንድ የአንድ ቲዎሪ ትክክለኛነት መፈተኛው (ልክ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው) በፕራክሲስ፣ በተግባር ተተርጉሞ ሲታይ ነው፣ ይባላል። በአለፉት አመታት ምን አየን?
እንደምናውቀው አብዛኛው የኢትዮጵያ ምሁሮች “ለአገሪቱ ለኢትዮጵያ ያዋጣል ብለው የነደፉት የአምባገነን የኮሚኒስቶች ሥርዓትና ጉዞ” ይህም የስታሊንን የብሔር ጥያቄ ያካትታል፣ ተፈትኖ፣ታይቶ እንደማይሰራ በዓለም ደረጃ ግልጽ ሁኖአል። ታዲያ ድካሙ አሁን ለምንድነው?

የእኛም ትችት (ሰው የፈለገውን ይዞ –የግድ ተቀበለኝ ፣ተከተለኝ ብሎ እስከ አላስገደደ ድረስ–የፈለገውን ቲዎሪ ይዞ ሊቀመጥ ይችላል) የእኛም ትችት፣ የዚህ የአምባገነን አምልኮ ለጂትመሲ በኢትዮጵያ ከየት መጣ? እንዴትስ አድረጎ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥር ሰደዶ እስከ አሁን ጊዜ ድረስ አብዛኛውን ምሁር፣ ሕዝቡንም ጭምር “ባሪያው” አድርጎ ያዘ ? …ሊይዝም ቻለ? የሚለውን ነጥብ አጉልቶ በማሳየት ላይ ያተኮረ ነው።

(በነገራችን እንደምታዩት በዚህ ጉዞ ፣ የኢትዮጵያ ምድር ለምን ለአምባገነኖች አመቺ ሆነች? ለሚለውም ቀደም ሲል ለወረወርነው፣ አንጠልጥለንም ለሄድነው ጥያቄያችን መልስም ነው።)

በነገራችን ይህ ነጥብ “እንዴት እንኑር? “ለሚለውም የፈላስፋው ጥያቄም በተዘዋዋሪ መልስም ነው።

እላይ ከተዘረዘሩት መልሶች፣ አንዱ ወደ ግራ ሌላው ወደ ቀኝ (ሌሎችንም መቁጠር ይቻላል) ከነዚህ ሁሉ “መልሶች” የማንኛው ወገን፣ አመለካከትና መልስ አሁን ትክክልኛ እና የሚያዋጣው መንገድ የትኛው ነው? ብለን ብንጠይቅ፣ መልሱ ፣ከዚህ ሁሉ የትርምስ ዘመን በሁዋላ አስቸጋሪ አይደለም።

የፖለቲከኞች የነገር ጥልቀታቸውና መልሶቻቸው-ዕውነቱን ለመናገር – እንደየቅላቸው ነው። መልሶቹ የሚሰነዘሩት እንደ የፖለቲካ አመለካከታቸውና እንደ ዝንባሌአቸውም ነው ።እንደተጠመቁበት ጠበልና እንደጠጡትም ወሃ ነው። እንደ አስተማሪአቸውና እንደ የነፍስ አባታቸው ምክርና፣ እንዲሁም እንደአነበቡትም መጽሓፍቶች ብዛት ነው። ነገሩም ከዚያ አልፎ ይሄዳል።

እሱም፣ እነሱ እራሳቸው እንደ ነደፉት ፕላንና፣ ምናልባት እንዳወቀሩት ድብቅ አጀንዳቸው ነው። ወይም ደግሞ ሌላው በርቱ ብሎ እንደነደፈላቸው፣ አላማና ግብም ነው። የእያንዳንዱ መልስ ከሌላው የሚለየውም፣ እነሱ እራሳቸው ወደው በመረጡትና በሚከተሉት አይዶሎጂም ነው። ይህም፣ ማንም እንደሚያውቀው እንደ ቅላቸው የተለያዩ ያደርጋቸዋል። አንድ አይዶሎጂም ቢከተሉም እንኳን፣ ተከትለውም የሚለያዩ አሉ- “ይለያያሉ።” ታዲያ የትኛው አይዲኦሎጂ ነው ትክክለኛው? ስንት ዓይነት አይዲኦሎጆዋች፣ በዚህቺ ዓለም ላይ አሉ? የኢትዮጵያ አዋቂዎችስ በየትኛው ትምህርት ነው የተጠመቁት?
ለመሆኑ የነዚህ የተለያዩ – አሉ ከተባለ- አይዲኦሎጂዎች ሁሉ አራማጆች የነፍስ ኣባቶች እነሱ እነማናቸው? ከየት ነው የመጡት? ምንድነው ምክንያቱ ፣ ትውልዱን በሙሉ(?)እንደዚህ ያደረገው? …ያሳበደው? ያንቀጀቀጀው? እንዳይስማማ ያደረገው? ለመሆኑ ምንድነው ዛሬ አብዛኛዎቹ የሚያስቡት? ምንድነው በመጨረሻው እነሱ በነፍስ ወከፍ የሚፈልጉት ሥርዓት?
ከየት መጣን? …ወዴት እንሄዳለን? …እንዴትስ እንኖራለን? በትክክል ጥያቄዉን ለማስቀመጥ “እንዴት አብረን እንኖራለን?” እነዚህን – ሦስቱ የፈላስፋው ጥያቄዎች ቀላል ቢመስሉም ፣ ጠጋ ብለው ሲመለከቱአቸው፣ መልሶቹ አሁንም ቢሆን ቀላል አይደሉም ። ቢያንስ ትንሽ ከባድም ናቸው።
ይህ ፈላስፋው ያንሳቸው ጥያቄዎች፣ የእሱ ብቻ አይደሉም። ይህን ጥያቄ ሌሎቹም ክፍሎች፣ ወይም ቡድኖች በማንሳት፣ እኩል እሱን ይጋሩታል።
“እንዴት እንኖራለን?” “እንዴትስ አብረን እንኑር?” ብለው፣ የተለያዩ ምሁሮች፣ እራሳቸው ፈላስፋዎች ጭምር፣ ከብዙ አሳሳች ነቢዮችና አምባገነኖች ጋር ሁነው፣ ድርጅት መሥርተው ፣በያለበት ተነስተው፣ ሕዝቡን በነገር አስክረው፣ ዓለምን አተረማምሰዋል።
የአንዳንዱማ አላማዎችና መልሶቻቸው አደገኛና ኃይለኛ ነበር።
ግን በ20ኛው ክፍለ ዘመን እንዳየነውና እንደምናውቀው፣ የአንዱም የሕልም እሩጯ፣ ሳይሳካ አብዛኛዎቹ፣ወድቀው ተንኮታኩተው፣ ከፖለቲካው መድረክ ተሰናብተዋል። ያም ሁኖ ግን የሚያሳዝነው፣ እነሱ፣ ተሰባስበው የነደፉትን “የሕልም ዓለም” ከግቡ ለማድረስ አንድንዶቹ በሬሣ ላይ ሳይከብዳቸው ተራምደዋል። ሌሎቹ በደም ላይ ዋኝተዋል፣ የተቀረው በረሃ ላይ ወድቆ ቀርቶአል። የተረፈው ተሰዶአል። ሌላው አካለ ጎዶሌ ድኩማን ሁኖ የትም ወድቆአል። በጠቅላለው ሲቆጠር ከአንድ መቶ ሚሊዮን ሰው በላይ ሕይወቱን በአለፈው ክፍለ-ዘመን በዓለም ዙሪያ አጥቶአል።

ለመሆኑ በመጨረሻው “እንዴት አብረን እንኑር” ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ማንኛው ወገን ነው ያቀረበው?

በአጠቃላይ ሲታይ “እንዴት እንኑር ” የሚለው ጥያቄ የሁሉም ሰው፣ “ፊደል” የቆጠረ ሰው ሁሉ ጥያቄ ነው።

ደራሲውም ይህን ጉዳይ በእራሱ መልክ አንስቶ ስለፍቅርም፣ ስለጠብ፣ ስለቅናትና ስለ ስግብግብነት፣ በአጭሩ ስለ ሰው ልጆች፣ የተለያ ባሕሪዎችና ጠባዮች፣ ተንኮሎችና ድብቅ ወንጄሎች በልብ ወለድ ትረካው፣ (ከአእምሮው ያመነጨው ለሆን ይችላል፣ ወይም በጆሮው የሰማውን፣ ወይም በዓይኑ ያየውን) ለእኛ አጫውቶአል። ገና ተጽፎም ያላለቁ ታሪኮች አሉ።

“ፖለቲከኛው”፣ እንደ አቅሙ፣ ይህንኑ ጥያቄ ያነሳል። ትንሽ ቆይቶ ያን የመጀመሪያውን መልሶ ጥሎ (ቅራኔዎች ቦታቸውን ተቀያየሩ እያለ) ሌላ አዲስ ነገር ጨብጦ ናላችንን ያዞረዋል።
ከቢጤው ጋር ፣ ለጥቂት ሰዎች አዳዲስ ነገሮችን ጠፍጥፎ፣ አቀነባብሮ ፣የሚከተለው ከአገኘ ማቅረቡ፣ ለእሱ ለምሁሩ አይከብደውም። ግን የማታለያውና የመሳቢያው ፎርሙላው፣ብዙ ስለአልሆነ አሁን ያለቀባቸው ይመስላል።
ምስራቅ አውሮፓ ጥሩ ምሳሌ ነው። ምሥራቅ ጀርመን ትምህርት ለመሰብሰብ ግሩም መድረክ ነው። የዱሮ ኮሚኒስቶች የሚየዙትንና የሚጨብጡትን (በጊዜው ደህና ነገር ለሕዝባቸው ሳይሰሩ) አጥተው አሁን ሰው ማሰባሰቢያ ብልሃት (ፎርሙላዋ ውስን ነው፣ብዙ አይደለም) ጠፍቶአቸው ግራ ተጋብተዋል።

ካህናቶችና ሊቃውንቶች፣ እነሱም ተመሳሳይ ጥያቄዎች “፣እንዴት እንኑር? ብለው ጉዳዩን አንስተዋል። እንደ ደራሲዎቹም እነሱም በተራቸው ብዙ ነገሮችን ጥለውልን ሄደዋል። ነብያትና የሃይማኖት አባቶች መልስ ሰጥተውበታል። ግን እነሱን “ከድርጊት ” ሰዎች የሚለያቸው አንድ ነገር ቢኖር፣ አላማቸውን በሰይፍ በሥራ ለመተርጎም፣በሕዝቡ ላይ አልሞከሩም።

በእርግጥ፣ በተለይ የተለያዩ የሃይማኖቶች፣”እንዴት እንኑር?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ፣ እነሱ የሚሰጡት መልስ (ሁሌ አይደለም) ለውዝግቦች መነሻ ምክንያት ሁነው ወደ ግጭት አምርተዋል። ምን ይታወቃል! ገና ዕድሜ ይስጠን እነጂ ብዙ ደግ ነገሮችን ወይም ጉዶችን በሕይወት ዘመናችን እንሰማም ይሆናል።

ልጆችም፣ ሳይቀሩ ይህን፣ “እንዴት አብረን እንኑር ? እኛስ ከየት መጣን ?…ወዴትስ በመጨረሻው እነሄዳለን ?” የሚለውንም የሰው ልጆች ጥያቄዎችም፣ እነሱም በልጅነት አእምሮአቸው ያነሱታል።
አባቶችም፣ እናቶችም ተመሳሳይ ነገር ወርውረዋል። ግን ክፋትና ጥላቻ ውስጥ ገብተው ግን እኛ እስቀምናውቀው ድረስ አገር አላቃጠሉም። ትዳር አላፋለሱም። ቤተሰብ አልበተኑም። ገበሬውም፣ መሣፍንቱም፣ መኳንንቱም እነዚህን ጥያቄዎች (በዘመናቸው) ከማንሳት እነሱም አልተመለሱም።

ማነው ለዚህ ሁሉ ጥያቄ ጥሩ መልስ የሰጠው? ትክክለኛውን መልስ እላይ ከተጠቀሱት፣ ክፍሎች ይዞ ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የቀረበው ቡድን ማን ነው? የትኛው “መደብ “ነው፣ድርጅት ነው፣ የቡድኖች ስብስብ ነው “ዕውነትን” የጨበጠው?
ግን ደግሞ መርሳት የሌለብን አንድ ሀቅ ቢኖር፣ እንደ ሒትለርና እንደ ሞሰሊኒ ያሉ ዕብዶች፣ እንደ ስታሊንንና ፖልፖት የመሰሉ አደገኛ ሰዎች፣ እንደ ፍራንኮና ፒኖቼ ፣እንደ ቻውቼስኮና እንደ ኢዲአሚን….ኪም አሊሱንግ፣ ቢን-ላዲን …ያሉ ደም የጠማቸው ሰዎች፣ “እንዴት እንኑር?” ብቻ ሳይሆን “እንደዚህ፣ እኔ በአልኩት ትክክለኛ መንገድ ኑር” ብለው ተነስተው (ተቆጣጣሪ በሌለበት አገር ሁሉ) የፈለጉትን ሊያዙ፣ሊገርፉ፣ ሊያስሩ፣ ሊረሽኑ፣ ወይም ወጣቱን ትውልድ ወደ ጦር ሜዳ ለሞት ሊሸኙ ችለዋል።
ተቆጣጣሪ ስለሌላቸው!
 ለምንድነው የምዕራቡ ዓለም “የተለያዩ የቁጥጥር ተቋሞች ” አዘጋጅተው የተከሉት?…ያላቸው? ለምንድነው የምሥራቅ ዓለምና ድፍን አፍሪካ፣ ከአረብ አገሮች ጋር እንደዚህ ዓይነቱን ነገር እንደ ጠበል የሚፈሩት? እንዳይፈጠርም በሩን ጥርቅም አድርገው የዘጉት?
ይህን ለመረዳት፣ለጥያቄዎቹም መልስ ለመስጠት (ይቅርታ መነገር ያለበት ጉዳይ ነው) “የስቴት አፌርን” እንግሊዞች እንደሚሉት፣ ወይም “የመንግሥት አስተዳደርን” ጀርመኖች እንደ ጠሩት ፣ ወይም ደግሞ ተዘዋውሮ የተለያዩ ” የፖለቲካ ፍልስፍናዎችን”፣ ያጠና፣ የተከታተለ ሰው ብቻ ነው፣” እንዴት መኖር አለብን? “ለሚለው ጥያቄ ጥሩ መልስ መስጠት የሚችለው።
እሱ ብቻ ነው፣ ማንም ከመሬት ተነስቶ “….ማርክስና ኤንግልስ፣ ሌኒንና ስታሊን፣ ሆድጃ እና ማኦ ሴቱንግ እንዳሉት፣ አንደ አስተማሩት “ብሎ ሲቀባጥር “አሁንስ አበዛችሁት” ብሎ እንዲታረሙ፣ይቅርታ “ማስተካከያ መልስ ሊሰጥ የሚችለው።”

                                            ፭
ዓለም ደስ የምትለውና ከእንስሳና ከከብት ኑሮ፣ ከእነሱም ሕይወት የሰውን ልጆች ፍጹም ልዩ የሚያደርገው፣ አንድ ነገር ቢኖር (ከብት ሜዳ ላይ ቆሞ ብዙም ስለ መጪው ሕይወቱ ሳይጨነቅ ሣሩን ይግጣል፣ …አደጋ ሲመጣበት ደግሞ ተፈጥሮው ነው፣ በኢንስቲንክት ደንግጦ ይፈረጥጣል) እነዚህን፣እንዴት እንኖራለን? ወዴት እንሄዳለን? የሚሉ ጥያቄዎች በማነሳቱና በማሰላሰሉ፣ በመመራመሩና ከሁሉም ይህን በአንደበቱ በንግግርና በመደማመጥ፣ በመወያየትና በመከራከር፣ በተለይ ደግሞ ይህን በጽሑፍ መልክ ፣ በመጽሐፍና በጋዜጣ ላይ አውጥቶ፣ ሌላው እንዲመለከተው መልስም ለመስጠት ዝግጁም፣ ችሎታውም፣ መብቱንም መጠቀም ስለ ሚችል ነው።

ከዚያም አልፎ የሰው ልጅ ለመጪው ትውልድ ታሪኩን በጽሑፍ ማስተላለፍ በመቻሉም ነው። ይህን ፍጡር የሰውን ልጅ ከሌሎቹ እንስሳት፣ ከኣራዊትም፣ ከትንኝም፣…. ይህ ችሎታው ፍጹም ልዩ ያደርገዋል። ያለፈውንም የሰው ልጆች ታሪክ በዚሁ ዘዴ መለስ ብሎ መመልከት በመቻሉም ነው። (የግዕዝ ፊደልንም፣ ጎበዝ! እኛ የምነከባከበው፣ ለሌላ ነገር ሳይሆን በዚሁ ምክንያት ብቻ ነው።)
ፖለቲከኛው ግን በየፊናው፣ ለእነዚህ እላይ ለተወረወሩት ሦስት ጥያቄዎች “…ከየት መጣን? ወዴት እንሄዳለን? እንዴትስ እንኑር?” ለሚለው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ፣ምላሱን ያንቀሳቀስበት ዕለት፣ ብዕሩን የጨበጠበት ቀን፣ የሚሰማ ጆሮ ያ! ቡድን፣ ይህ ክፍል ከአገኘ ደግሞ! ይህ “መደብ” …ያኔ ! ከጥራት ይልቅ ውጅንብርን፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን፣ ከፍቅር ይልቅ ጠብን ፣ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን እንደሚጋብዝ፣ የአገራችን የቅርቡ ታሪክ ያሳየን ጉድ፣ እሱ እራሱ ትልቅ ምስክር ነው። ይህ ደግሞ፣ ከታሪክ እንደምናውቀው፣ “የኢትዮጵያ ልጆች” በሽታ ብቻ አይደለም።
የአውሮፓም፣ የእሲያም፣ የአሜሪካም፣ ሌሎች አፍሪካውያኖችም ቢሆኑ እነሱም በ”ዕብደታቸው” ከእኛ ፣ ምንም አይለዩም። ግን እነሱ ችግርን መፍታት ያውቁበታል። ነገር መቋጠር ይችሉበታል። ሕግን ያከብራሉ።ከዚያም አልፎ፣ ይከባበራሉ። ጥሩ መፍትሔ ያቀረበውም በሕዝቡ ዘንድ ተመርጦ (ለዘለዓለም ሳይሆን) ለተወሰነ ጊዜ ኃላፊነቱን ይረከባል። በሚቀጥለውም ዙር በምርጫ ሲሸነፍ፣ የተቃውሞውን ወንበር ይዞ ጊዜውን ይጠብቃል። የእኛ እኮ በዛ።ለዘ አጣ! አርባ አመት ሰው እንደ ሞኝ የነከሰውን ነገር ይዞ ይቀመጣል?
ለምን አውሮፓኖች ችግራቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈቱ?….ለምን እኛ ጋ እንደዚህ ዓይነቱን ሁኔታ ለመግባት እያስቸገረ፣ እየከበደ፣ልቅ እያጣ የመጣው፣የሄደው?
በዚምባቡዌ (እራሱ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ነፍሱን ለማዳን የሸሸበትን አገር) ሰሞኑን እዚያ የሆነውን ነገር አታዩም !። ኬንያን አትመለከቱም ! ስለጋናና ስለናይጄሪያ፣ ስለደቡብ አፍሪካና ስለማሊ…አልሰማችሁም? ቢያንስ በብዙ ነገር እነሱ እኛን ቀድመው ሄደዋል። ተቃዋሚው ቢያንስ ሽንጎ ውስጥ ወንበር አለው። ነጻ የተቃውሞ ሐሳቡን ማሰማት ይችላል። ለምን እዚያ እንደዚህ ሆነ? ለምን በኢትዮጵያና በኤርትራ፣ “ዝምታ ነገሠ”? ለምንድነው የምዕራቡ ዓለም ሌሎቹን እንዲታረሙ ሲያዋክባቸው? ኢትዮጵያንና ኤርትራን ዘለው የሚያልፉት? ለምንድነው ለኬንያ፣ ለግብጽ፣ ለዝምባቡዌ ፣ መሆን አለበት የተባለው የዲሞክራሲ ጥያቄ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ዝም ተብሎ የሚዘለለው?
ቢያንስ (አዲሱን ፈሊጥ ለመጠቀም፣ እነሱም እንደ እኛው ከተለያዩ “ዘሮች” ቢወጣጡም ) ቢያንስ እነሱ፣ እላይ የተቆጠሩት የአፍሪካ መንግሥታት፣ ይደማመጣሉ ። ቢያንስ ቆመው ይከራከራሉ። ቢያንስ “የጨዋታውን” ሕግጋት ያውቃሉ። ቢያንስ እንደ እኛ አላበዱም? ቢያንስ ሰብሰብ ብለው አብረው ይጮኻሉ?
ለምን እነሱ እንደዚህ ሆኑ? ለምን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፣ ሥልጣን ላይ ያለውም ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልገውም ፣ ብልሃት ፈልጎ እርስ በእራሱ የማይነጋገረው? ?
ለመሆኑ እንደገና ለማስታወስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማነው “ትክክለኛውን አቋም ” (አለ ብለን እንገምት) አሁን የሚያራምደው?
“አሥመራና አዲስ አበባ ላይ ሥልጣን ላይ የወጡ ነጻ -አውጪዎች? ….ወይስ ኮሚስትና ሶሻሊስቶች ነን ባዮቹ? ወይስ ዘውድና ዙፋን ከአልተመለሰ (ስንት እንደሆኑ አናውቅም) የሚጠይቁ ክፍሎች? ምናልባት እንገንጠል ባዮቹ? ወይስ በአለፈው ምርጫ በ99.6 % አሸነፍን የሚሉት፣….ወገኖች?…. ከእነዚህ ሁሉ፣ ለመሆኑ ትክክለኛው ማነው?
በኢትዮጵያ የተነሱት የፖለቲካ መደቦች፣ በጥቅሉ ለመናገር በሁለት፣ ግፋ ቢል በሦስት የፖለቲካ ሜዳዎች ብቻ ላይ የተሰማሩ ናቸው። እነሱም ከሁለት፣ ወይም ያው ነው ፣”አንድ አይዲኦሎጂ” ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው።

አይዲኦሎጂ ደግሞ ምሁሮች ጠፍጥፈው አቀነባብረው፣ አዋቅረው፣ ወዳጅ ለመግዛት፣ ተከታይ ለማፍራት፣ የሚወረውሩት “የማሰባሰቢያ ትምህርትና ማሰሪያ መረብ ወይም ማጎሪያ ጎተራ ነው”። ይህን ለማድረግ በተላይ የሃይማኖትና የፖለቲካ ምሁር አንድ ፍልስፍና ወይም አንድ “ትምህርት እራሱ ቀምሞና ፈጥሮ” ለተከታዮ ማቅረብ አለበት።
እነሱ-ምሁሮቹ- አዲስ ነገር መፍጠር ከአልቻሉና ከአላወቁበት ከጎረቤት አገር ትምህርቱን (እንበል አሁን ለኢትዮጵያ) “ይጠቅማል” ብለው ይዋሱታል። ጎረቤት አገር ተፈልጎ በቀላሉ የማይገኝ ከሆነ ከሌለው ቦታ እሩቅ አገር ሄደው ከዚያ “ተሸክመው” አሁንም እንበል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል ብለው ጎትተው ያመጡታል።
አንደኛው አይዲኦሎጂ የኢትዮጵያን ወጣት ትውልድ አዕምሮና ልብ የማረከውና የሳበው፣ ይህ ለማንኛችንም አዲስ አይደለም፣ ” የኮሚኒዝምና የሶሻሊስት” ፍልስፍና ነው። ሁለተኛው፣ እንደገና ለማስታወስና ለመድገም የእሱው ውላጅ የሆነው የስታሊን “የብሔር ብሔረሰብ እስከመገንጠል …”የሚለው ፣ አስገራሚው ለኢትዮጵያ የተነደፈው “የመበታተን እስከ መገንጠል የሚለው መፍትሔ” ነው።
ሦስተኛው ደግሞ፣ ይህ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አብሮ የዛሬ አርባ አመት የተሰናበተው፣ግን የሶስት ሺህ ዘመን ዕድሜ የነበረው ” የዘውድና የዙፋን…የሰለሞን ውርሰ- መንግሥት ” ፍልስፍና የሚለው የቆየው ጥንታዊ አመለካከት ነው።
እንግዲህ እነዚህን ሁለቱን -ሶስት ማለት አንችልም፣ “ፍልስፍና” የኢትዮጵያ ምሁር ጨብጦ ወደፊትም ወደ ሁዋላም ፣እንዳንል፣ እንዳንኖርም እንዳንሽርም እኛን እንደ አንዳች አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ከቶን፣ አላራምድ ብሎ እንደ “ማርኮኛ”የእነሱ እሥረኛ አድርጎን በሕይወታችን የሚቀልደው።
ለምን ከዚህ አመለካከት ውጭ ለአገሪቱ ምሁር ሌላ ነገር፣ አልታያቸውም፣ አይታያቸውም? ለምን ከጊዜው ጋር አብረው አይራመዱም? ለምን እሱ ብቻ ነው ብለው ድርቅ ብለው እንደ “ጨው አምድ” ቆመው የቀሩት?
“አይዲኦሎጂ አይያዝህ እንጂ አንዴ ከያዘህ ወዳጄ! (የሚገርም ነው ይህን የሚለው፣… ወዳጄ! ሌላ ሰው ሳይሆን ወጣቱ ካርል ማርክስ ነው :- እሱ ደግሞ ስለምን እንደሚያወራ በደንብ ያውቃል!) አንዴ ከያዘህ መሬት ላይ ጥሎ፣ እንደ አንዳች አጋንንት ሳያዳፋህና ሳያንደፋድፍህ እንደዚሁ በቀላሉ ፣ ሞኝ አትሁን፣ ያ አይዲኦሎጂ፣ እመኑኝ አይለቅህም”… ብሎ አስተምሮናል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ፣ መገመት እንደሚቻለው ፣እንደዚህ ከሆነ ብዙውን ሰው ባዶ እጁን ስለሚያስቀረውእጅግ አድርጎ ከዚያ መላቀቁ ያስፈራዋል። በእርግጥም የለመዱትን “አጋንንት”ጥሎ ( ከማያቀወቁት መለአክ የሚያውቁት አጋንንት–እኔ ይህ ነገር አይገባኝም– የእኛ ሰው፣ እራሱን ሊያታልል ይሻላል፣ ደጋግሞ ይላል፣ ምናልባት አብዳለሁ ብሎ ስለሚፈራም ይሆናል!) ሁሉን ነገር እርግፍ አድረጎ ባዶ እጅ መቅረት ያስፈራ ይሆናል። ግን ያ! ስለ ተባለ እኛ ለምን ፍዳችንን እንይ? ነጻ ሰው ነን ! ነጻሰው ደግሞ የእራሱን ሕይወት መምራት ይችላል።

“ፖለቲካና ዕውነት” ፣ “…ዕውነትና ፖለቲካ ” ከአንድ እናት ሆድ፣ ወይም ከአንድ አባት አእምሮ፣ ወይም ደግሞ “ከአንድ እንጨት የተፈለጡ ” መንታ እህትና ወንድማማቾች –እንወቀው!– አይደሉም።
“ዕውነት” ፍጹም ሌላ ነገር ናት። ፖለቲካም እንደዚሁ ከዕውነት ጋር ያለው ግንኙነት ኩታ ገጠም አይደለም። ሁለቱ የተለያዩ ዓለሞች ናቸው።
ሐና አረንድት፣ ይህን ነገር ግልጽ ለማድረግ አምስት ዓይነት ዕውነት አለ ትላለች። አንደኛው፣በፈላስፋዋ ዓይን የሒሳብ ሕግጋት፣ የአርትሜትክ ዕውነት ነው። ሁለትና ሁለት፣ አራት ነው። ይህን ዕውነት፣ ማንም ሰው በዚህች ዓለም ላይ የፈለገውን ያህል ኃይል ይኑረው፣ ይህ ሰው የፈለገውን ነገር ያደርግ፣ ድንጋይ ያገላብጥ፣ ጥይት ይተኩስ በምንም ዓይነት፣ሁለትና ሁለት አራት የሚለውን ሀቅ፣ ቀይሮ ይህ ሰው አምስት ወይም ስድስት ለያደርገው፣ አስዋ እንደምትለው አይችልም። እንዴት አድርጎስ? አንድ ፖለቲከኛ ግን ሞኝ ከአገኘ ሁለትና ሁለትን ዋሽቶ አንድ መቶም ያደርገዋል። ሁለተኛው ዕውነት፣ ያለው ታሪክ ላይ ነው። በአንድ ቦታ፣ በአንድ አገር የሆነ፣ የነበረ የተደረገ፣ ታሪክ ይህን ዕውነት፣ ሀቅ መካድ፣መሻር፣ ማጭበርበር (ማንም ሊሞክር ይችላል ግን ዕውነቱ፣ አንድ ቀን ይወጣል፣ መውጣቱም አይቀር) ፈጽሞ አይቻልም ።

ሦስተኛውና አራተኛው በእሷ ጥናት፣ የባዮሎጂ፣ የተፈጥሮና የፊዚካል ሳይንስ ዕውነት ነው ብላ፣ አምስተኛው ሀቅ፣ ያው ዕውንትን ያዘለ፣ ሌላው የሀቅ ሜዳ የፍልስፍና ቋሚ አረፍተ ነገር/ነገሮች ናቸው ትለናለች።
ዝርዝር ነገር ውስጥ መግባቱ ሌላ ቦታ ይወስደናልና በዚሁ ወደ ፖለቲካ ፊታችንን እናዙር።
ፖለቲካና በምንም ዕይነት የዕውነት ካታጎሪ ውስጥ ሳይሆን የሚመደበው፣ በአይዶሎጂ ሥር ነው። ፖለቲካ ደግሞ እንደ ገበያው፣ ሰውን ለመሳብ፣ተከታይን ለማፍራት፣ አላማን ከግብ ለማድረስ፣ በማር የተቀባ የአነጋገር ስልት፣የአቀራረበረ ችሎታ፣ በግማሽና በእሩብ “ዕውነት” ላይ የተመሰረተ ውሸትንም ያቀፈ፣ ተቃዋሚን የሚያዋክብ፣ ደጋፊን፣ በብልሃት የሚሰበስብ፣ አብዛኛውን ጊዜ የብልጦችና ብልጣብልጦች ሥራ ነው።
ጥሩ ምሳሌ “ኢትዮጵያ አንድ አይደለችም” የሚለው “ፖለቲካ ቅስቀሳ” ነው። ወይም ኤርትራ “የኢትዮጵያ አካል አልነበረችም” የሚለው ” የሐሰተኞች አይዲኦሎጂ ነው።”
አንድ አይዲኦሎጂ ደግሞ የሚሰራው፣ ረዥም ዕድሜም ይህ አይዲኦሎጂ የሚኖረው ፣ደጋፊዎቹን ለመሰብስብ፣ ተከታዮቹን ለማፍራት የሚችለው “ጠላት” ሲኖረው ነው። እንደምንም ብሎ አንድ አይዶለጂስት “ጠላቱን” ፈልጎ ማግኘት አለበት። ያለ ጠላት የሚንቀሳቀስ፣ሰው አወናብዶ የሚሰበስብ አይዲኦሎጂ፣አንድም አይዲኦሎጂ የትም ቦታ የለም። እንግዲህ የትግል ሜዳው ውስጥ ዘሎ ለመግባት የሚፈልግ “ወጣት አስተሳሰብ ” ጠላት ባይኖረውም ፈልጎ የግድ የውሸት ጠላቱን፣እሱ እንደምንም ብሎ “ጠፍጥፎ” መፍጠር ይኖርበታል። በኢትዮጵያም የሆነው ይኸው ሀቅ ነው።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የከበርቴ ጥያቄ በኢትዮጵያ የሚለው ቅስቀሳ ነው። ፋብሪካ “በሌለበት” በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ፣ የፋብሪካ ሰራተኛው ቁጥር እሚንት በማይገባበት በንጉሡ ዘመንና ከዚያ በሁዋላ በደርግ ጊዜ “ካፒታሊዝምና ከበርቴው–አቀባባይ ከበርቴው መደምሰስ አለበት” ተብሎአል።
ይህ ከአልተባለ ደግሞ እንዴት ወደ ሶሻሊስት ሥርዓት መሄድ ይቻላል። ስለዚህ ሩሲያ ውስጥ ያኔ ስለተባለ (እዚያም አልነበረም) ማኦ ሴቱንግ በቻይና ስለ አለ ( እዚያም ያኔ፣ የከበርቴ ፋብሪካ ፈስፋፍቶ አልነበረም) በባዶ ሜዳ የኢትዮጵያ ምሁር ከመሬት ተነስቶ “ከበርቴው ይወረስ፣ይደምሰስ…ይወገድ…”ተባለ።
ሌላም ጠላት ፈልገው አግኝተዋል። አማራው! ዱሮም አሁንም ባዶ እግሩን የሚሄደውን አማራ፣ እንደ ሌላው የሚበላው እንኳን የሌለውን ” የመሓል አገር ሰው- አማራውን ” ያኔም አሁንም “የዚህ ዘር የበላይነት መደምሰስ ” (ሌኒንና ስታሊን በሩሲያ ስለ አሉ) ያ ተቀድቶ በያለበት፣ በሩሲያ ፋንታ “አማራው” ተተክቶ፣ አሱ “ጠላት ” ነው፣ ተብሎ፣ እንዲደመሰስ ተጠይቆአል።  ያለ ጥያቄም “….ይደምሰስ” ተብሎ፣ ተፈርዶበታል።
“ጠላት” ተጠቁሞ ከተገኘ ደግሞ፣ እሱን “…..በዝባዥ፣ አቆርቋዥ፣ መጅገርና ቅኝ ገዢ ….” ብሎ ፣ ተከታይ ለመሰብሰብ ቅስቀሳውን ለማጦፍ ፣”….የፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳው ክፍል ኃላፊነት፣ የፖሊት ቢሮ ሥራ፣ የፖለቲካ ትምህርት ቤቱ ግዳጅ ነው።”

በዚህ ነው እንግዲህ የአንድ ሀገርን ሕዝብ በነገር አዋክቦ፣ በቀላሉ “…መበተን፣ መከፋፈል ….”የሚቻለው።ይቻላልም።
ይህ ጉዞ ደግሞ ዞሮ ዞሮ፣ “ይህች ለነጮች አልገዛም ብላ ያስቸገረቺውን ኢትዮጵያ” ሞሰሊን እንዳለው “አዳክሞ ማንበርከክ፣ በቀላሉ አሁን ተችሎአል።” “ጠላት” ደግሞ ሳይታሰብ ከመድረኩ ላይ ሲጠፋ፣ እንኳን የእኛዎቹ “እሳት የላሱት” የምዕራቡ አገር አይዶሎጂስቶቹም ሳይቀሩ ግራ ተጋብተዋል። ግራም ይጋባሉ። ሳይታሰብ “ሳይንቲፊክ ሶሻሊዚም” እየተባለ የሚነገርለት፣ የዋርሶ የጦር -ቃል ኪዳን አገሮች፣አንድነትና ሕብረት ተራ በተራ፣ ተፈረካክሶ ሲወድቅ፣ የምዕራቡ ዓለም ፣ “….ጠላቱ ሳይታወቅ በአንዴ ስለጠፋበት ” ለተወሰነ ጊዜ፣… ለአሥር አመታት፣በተከታታይ ግራ ተጋብቶ፣ ያኔ እንደተጻፈው ቁጭ ብሎ ሰንብቶአል። በሁዋላ ግን የእስላም አክራሪዎቸ-እነ ቢንላዲን፣ ብቅ ብለው የዓለምን ፖለቲካ ሌላ መልክ እንዲይዝ አድርገውታል።
የሩሲያ እንዳለ ሁኖ፣ የቻይናም ወዳጅንትና ጠላትነት ለምዕራቡ ዓለም ገና ባይለይለትም….። … ለምዕራቡ አይዶሎጂስቶች ሌላ በቂ ሥራ  መገመት እንደሚቻለው ገና ወደፊት ይጠብቃቸዋል።
ኢትዮጵያስ ውስጥ? አማራው እንደ ሚባለው አሁን ሥልጣኑ ላይ አልተቀመጠም። ማነው አሁን ታዲያ “ዋና ጠላት?”

ይህች ዓለም፣ በሌላ በኩል የተለያዩ “አንድ አገር ሕዝቦች አብሮ በሰላምና በደስታ” ሊኖሩበት የሚችሉበትን – የሕብረተሰብ ሥርዓትና ሞዴሎች፣ እነሱ ምን እንደሚመስሉ፣ አሁን በያዝነው በ21ኛው ክፍለ- ዘመን :- እንደ 20ኛው አይደለም- በደንብ ታውቃለች።
እነዚህ ሞዴሎች ከየት መጡ? እነዚህ ሞዴሎች በቁጥር ስንት ናቸው? እነማን ፈጠሩአቸው? እነሱስ ከአምባገነን ሥርዓቶች በምን ይለያሉ?
የእነዚህ ሁሉ፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ሥርዓቶችና ሞዴሎች ወላጅ አባትና እናት ደግሞ ሌላ ፍጡር ሳይሆን እንደ አይዲኦሎጂ አባትነቱ እራሱ፣ “ምሁሩ ” ነው።
 ምናልባት እነዚህና ሌሎቹን ቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ የሚያራምዱትን ምሁሮች ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ደግሞ ፣ ሁሉም በጋራና በተናጠል “የቀመሱት ትምህርት” ነው።

ትምህርት ግን በየፊናውና በየቅሉ ነው። ይህ ክፍል “ምሁሩ” በጅምላ ሲታይ፣ መናገርና መጻፍ፣ ማደራጀትና መቆጣጠር፣ተከታዮቹን መሰብሰብና ሲያጠፉ መቅጣት ማስፈራራት በደንብ ይችልበታል። አሳክቶ መናገርና መጻፍ፣ ማሰብና መመራመር፣ ለችግሮችና ለመሰናክሎች መልስ መስጠት የሚችለው ክፍል ደግሞ ፣ የተማረው ወገን፣ ይኸው ክፍል ብቻ ነው። እሱም ፣እኛ “ምሁር” የምንለው ” መደብ” ነው። ይህ ምሁርም ሁሉም ባይሆኑ “የተወሰነው ክፍል ፣ ጭልጥ ያለ ተንኮለኛ ነው።”
 እንግዲህ ማነው ምሁር? ምሁር፣ ምንድነው? ምሁሩ ከየት መጣ ? የምሁር ችሎታው እስከ ምንድነው? ሁሉም ፊደል የቆጠረ ሰው ሁሉ አንድ ወጥ የሚያስብ የምሁር ክፍል ነው ወይ? ስንት ዓይነት ምሁር / ምሁሮች አሉ? የምሁር ቦታውና “መደቡ” ከየትኛው ክፍል ነው? ወገናዊነቱስ ለማን ነው? የፖለቲካ ትግል ውስጥ ሲገባ ለማን ነው የሚታገለው? ለእራሱ ጥቅም ነው ወይስ ዕውነት እንደሚለው ለጭቁኑ መደብ ለገበሬው ነው? ለገበሬው መደብ ከሆነ ለምን ሥልጣኑን ለገበሬው አስረክቦ እሱ ወደ መጣበት ቦታ ሙያው አይመለስም?
እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ደግሞ ቀስ እያልን፣ “ሳንቅበጠበጥና ሳንቸኩል”፣ ወደፊት ጊዜ ወስድን፣ ረጋ ብለን እንመልሳቸዋለን። ምሁር ስለተባለ ግን “ምሁር” ሁሉ “አደገኛ አረመኔ” ወይም ደግሞ “ጤነኛ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ሕግን የሚያከብር ቀና-ሰው ነው “፣ ማለት እንችልንም።

ለምንድነው የተወሰነው ክፍል አደገኛ የሚሆነው? ሌሎቹስ ለምን፣ እንደ እሱ አደገኛ አይደሉም፣የሚባለው? ይህን ጥያቄ ማንሳቱ  አስፈላጊ ነው።
ምንድነው አንደኛውን የምሁር ወገን ከመሬት ተነስቶ የሚያሳብደው? አንቀጅቅጆት የእሳት ራት እሱን የሚያደርገው? ሌላውንስ ረጋ ያለ “ቀናና ደግ ነገር ለሕዝቡና ለወገኑ፣ ለአገሩም እንደሌላው አገር ፖለቲከኞች እንዲያስብ የሚያደርገው?

አንድ ሥዕል የሚሲል ሰዓሊ፣ እሱ ምሁር ነው ወይ? …ሙዚቃ ተጫዋቹስ ምንድ ነው? ፊልም ቀራጩስ? ሐውልት ጠራቢውስ? የትያትር ተዋኒያን? ዳንሰኛውስ ? ስፖርትና ግጥም ገጣሚው?….ጋዜጠኛና ጸሓፊው፣ ፈላስፋና ፖለቲከኛው፣ እነዚህ ሁሉ “የምሁሩ መደብ ውስጥ” የሚመደቡ ሰዎች ናቸው?
  ምሁር ከሆኑ ምን፣ እነሱን እሰከዚህ የሚለያያቸው ነገር በመካከላቸው አለ? ለምንስ አይስማሙም? የዚህን መልሱን ቀስ ብለን ወደፊት እንደርስበታለን።
ስለ ምሁር ስናነሳ ለአባዛኛዎቻችን የሚታየን “የፖለቲካው ምሁር” ብቻ ነው።
በእርግጥ እነሱ በአለፉት አርባና ሃማሣ አመታት በኢትዮጵያ በተካሄደው “የፖለቲካ ግርግር” ከሌሎች ክፍሎች በልጠው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙ፣ የጮሁ ወገኖች ናቸው። በመሆናቸውም እነሱ ብቻ ናቸው ብሎ መገመቱ እምብዛም አያስገርምም። ይህም ከዚያም የመጣ አመለካከት ነው። አሁንም እነሱ ናቸው በዱሮ አስተሳሰቦች፣ ጊዜው ጥሎአቸው በሄደ ትምህርቶች ሜዳውን የያዙት።

ለመሆኑ እነ ገርማሜና እነ ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ከምሁሩ ክፍል የሚመደቡ ናቸው? ወደ አንድ መቶ ሃያ የሚጠጉ የደርግ አባሎችስ ምንድናቸው? እነሱም ምሁሮች ናቸው ልንል እንችላልን? ወይስ አይደሉም? የአገሪቱ ቀሳውስቱና ካህናቶች ከምሁሩ ክፍል ሊመደቡ ይችላሉ? የእስላም ሃይማኖት አባቶችና አስተማሪዎች እነሱም ምሁሮች ናቸው? እነሱና “የሙያ አብዮተኛ-ፕሮፌሽናል ሪቮሉሽነሪ” የሚባሉት ክፍሎች፣ ሁሉም እላይ ከተጠቀሱት ጋር አንድ ላይ የሚታዩ “ምሁሮች” ናቸው? የጠበቃና የዳኛው ሰፈራቸው ከየት ነው?….እነሱስ የት ይመደባሉ?…ምንድናቸው እነሱ? ለመሆኑ የቢሮ ሰራተኛ ሁሉ ምሁር ነው?
 …ጸሓፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሐብተወልድ፣ ልጅ ሚካኤል እምሩ፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ፣ አቶ ከተማ ይፍሩ? …አቶ አክሊሊሉ ሐብቴ፣ ልጅ ካሣ ወልደማሪያም፣…አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ፣ ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ፣ ራስ ጎበና፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ፣ የኢትዮጵያ ኦርኬስትራ፣ አስተማሪዎች፣…..አንዳንዶችን ብቻ ለመጥቀስ ፣ እነሱስ ከምሁሩ ክፍል የሚመደቡ ናቸው? ሳይኮሌጂስቱስ የት ይግባ? ሐኪሙንስ ከማን ጋር እናሰልፈው? እኒጂነሩስ? እርቺቴክቱስ? መሐንዲሱስ? ከበርቴውስ? ካድሬውስ? የት ይግቡ? የት ውስጥ እንመድባቸው?

ሦስት አይነት ምሁሮች አሉ። አንደኛው “የአካዳሚው ክፍል” የሚባለው ነው። ሁለተኛው “በአለውና በተማረው ጥበቡ” ላይ የትርፍ ጊዜውን ወስዶ እራሱን በእራሱ ያስተማረውና ዕውቀቱን ያዳበረው፣ ጀርመኖች እዚህ “ገቢልዲተ/ኢዱኬትድ” የሚሉት ፊደል የቆጠረው ክፍል ነው። ሦስተኛው “ኢንተለጄንሳ” የሚባለው አንዳንድ ተመራማሪዎች እኛ ከምናውቀው “ከኢንተለክችዋሎች”የሚለዩዋቸው ክፍሎች ናቸው።

እነዚህ ሁሉ በአንድ አገር፣ ወይም ለአንድ አገር – ይህ የትም ሊሆን ይችላል- አዳዲስ ሐሳቦችንና አሰራሮችን ፈልገውም ፈጥረውም ሆነ ወይም ከውጭ ቀድተው፣ ለዚያ የጋራ አገራቸው፣ ይህን አዲሱን ብልሃት በተለያዩ መንገዶች አስተዋውቀው፣ የቆየውንና የነበረውን “ባህላቸውንና ሥልጣኔአቸውን” ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው።

የሚደነቁ ግሩም የሕንጻ ሥራዎች፣ የሙዚቃ ድርሰቶች፣ የሳይንስ ፈጠራዎች፣ አዲስ የፋብሪካና የእርሻ መሣሪያዎች፣ ድንቅ የሥነ- ጽሑፍ ልብ ወለድ ሥራዎች…የሕክምና ጥበብ፣ አዳዲስ መድሐኒቶች፣….ልዩ ልዩ መንኮራኩሮችና ሮኬቶች፣ አይሮፕላንና መርከቦች፣ የቴክኒክ ጥበቦች፣….. እነዚህን ሁሉ ሊያጠቃልልም ይችላል።

እንግዲህ የምሁር ዋና አላማውና ተግባሩ፣በአንድ አገር፣ የሰውን የኑሮ ሁኔታ፣ የሰው ልጅ ሕይወቱን በቀላሉ አሰተካክሎና አመቻችቶ ሊመራ የሚችልበትን መንገድ ማዘጋጀት ነው። ይህም በሌላ ቋንቋ፣ ትንሽ ቢዘረዘር፣ በሽታን የምንከላከልበትን መድሓኒቶች መፍጠር፣ ሊንቀሳቀስ የሚችልበትን መንኮራኩር ቀጥቅጦ መሥራት፣ የሰው ልጅ እንዳይራብ የሚበላውና የሚጠጣውን፣ የሚለብሰውንና የሚተኛበትን ቤት የሚዘጋጅበትን ዘዴ ተማራምሮ መድረስና በቀላሉ ማዘጋጀት፣ ይህም ዘመናዊ የከብት እርባታን፣ የምርት ዕድገትን (ቆጥረን አንጨርሰውም ) ይጠቀልላል።
… ሳይንስና ጥበብን፣ አዲስ ዕውቀትና አዲስ ፈጠራን …ያካትታል። በሌላ በኩል ምሁሩ፣ የአእምሮንና የመንፈስን ምግብን ለሰውነታችን ያዘጋጃል።

በአንድ በኩል “ቴክኒክን ዕድገትን ማፋጠን” በሌላ በኩል “ጥበብና ዕውቀትን” ማስፋፋት ይህ የምሁሩ ዋና የሥራ መስኩና ተግባሩ ነው።

ሌላው፣ የምሁሩ አንዱ ክፍል፣ ከሳይንስ ዓለም የተገኘውንም ዕውቀትና ጥበብ ለሕዝቡ በሚረዳውና በሚገባው ቋንቋም “ተርጉሞም” የሚያቀርብ ነው። እዚህ ላይ ፕሬስና ጋዜጠኛዎች አሉ። እዚህ ላይ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች አሉ። ፈላሳፋና ተቺዎችም ይጨመሩበታል።

ከሁሉም በላይ “ምሁሩ” የነፍስንም ጉዳይ፣ ከሕይወት በሁዋላ ብሎ መልስ ሰጥቶ መንፈሳችንን ይንከባከባል። መጽሓፉንም እየጠቀሰ ወዴት እንደምንሄድ? እንዴት በሥነ-ምግባር ታንጸን መኖር እንዳለብን ከጥፋት እንድንርቅ ፣ ነስሃ እንድንገባ ሕብረተሰቡን ያስተምራል።
አሁን ስለ ምሁር በድፍኑ ስናወራ ትንሽ ቆይቶ ሳይታሰብ በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ ብቅ ብሎ “ትርምሱንና ድብልቅልቁን” የሚወጣውን፣ ስለ “ፖለቲካኛ መደብ፣… ስለ ቀበጥባጣዎቹ የሙያ አብዮተኞች” ስለ እነሱም የግድ፣ የእነሱ ጩሐት ብቻ ነው በየጊዜው የሚሰማው ማንሳት ይኖርብናል።
 “የሙያ አብዮተኞች” ምንድናቸው እነሱ? ከየትስ መጡ? ማን ሕብረተሰቡን እንዲያተረማምሱና እንደፈለጉት ድብልቅልቁን እንዲያውጡ ፈቀደላቸው? ወዴት ነው የሚሮጡት? የት ለመድረስ ነው የሚጋልቡት? ቀስ እያልን ለነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ እንሰጥበታለን።
ግን ለመግባባት”…እንዴት እንኑር” የሚለውን የፈላስፋውን ጥያቄ ብዙ ፈላስፋዎች እንደ ዕውቀታቸው፣ እንደችሎታቸው፣ በተለያዩ መንገዶች፣ የተለያዩ ደግሞ እርስበራሳቸው የሚጻረሩ በርካታ መልሶች ወርወር አድርገው ሄደዋል።
ሔግል፣ ፊቺቴ፣ ኒቼና ማርክስን፣ ካንትንና ጀን ሎክን፣ ፕላቶንና …አርስጣጥለስን መጥቀስ ይቻላል።
ማርክስ መጥቶ ግን የዓለም “…ፈላስፋዎች ይህቺን እኛ የምንኖርበትን ዓለም በተለያዩ መንገዶች ተርጉመዋል። ትርጉም ሳይሆን ቁም ነገር ያለው፣ ይህችን ዓለም ቀያይሮና ደበላልቆ ፣ ትርምስ ውሰጥ ከቶ እንዳለ ገለባብጦ ድብልቅልቁን ማውጣቱ ላይ ነው።” ብሎ በግራው ክንፍ ውስጥ እሳት ለኩሶ የምሥራቁን ዓለም መሥርቶ (ልብ እንበል ልብ በሉ የምዕራብ ዓለም አይደለም) ይህ ሰው ሄዶአል።

ቀኞቹ ተነስተው እላይ ከተጠቀሱት ፈላስፋዎች የተወሰኑትን ጨብጠው፣ የዳርዊንን ትምህርት አክለውበት፣ በምዕራቡ ዓለም፣ በተለይ በጀርመን፣ በስፔን፣ በጣሊያንና በሩቅ ምሥራቅ በጃፓን፣ ዘረኛ ሥርዓት መስርተው ሄደዋል። እንደምናውቀው እንደኛው ሥርዓት የፋሽሽቱ ሞሰሊን እና የሒትለሩ የናሽናል /ብሔራዊ ሶሻሊዝም ነው። ሁለተኛው ሌኒንና ስታሊን የፈጠሩት የኮሚኒስቶች ሕብረተሰብ ነው።
ሁለቱም ደግሞ ሰላም የማይሰጡ፣ ሰባአዊ መብትን የማያውቁ፣ የማያከብሩ፣ ነጻ አስተሳሰብንና አመለከካከትን የማያስተናግዱ፣ የፕሬስ ነጻነትን ፣የሚያግዱ የሚፈሩ፣ ሃይማኖትን የሚንቁ፣እንዲያውም የእነሱ ካልሆነ የዘመቻ ጦርነት የሚከፍቱ ሥርዓቶች ናቸው።

ለምንድነው፣ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት አምባገነን አስተሳሰብ አራማጆች በድፍን ምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ ፣በእሲያ አገሮችና በላቲን አሜሪካ ሥር ሊተክሉ የቻሉት? ለምንድነው በምዕራብ አውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ያሉ መንግሥታት፣ ሰበአዊ መብቶችን የሚከበሩት? ለምንድነው ብዙ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ፉክክር በምዕራብ አውሮፓ ብቻ የምናየው? ….የፓርላማ ሥርዓትና ነጻ ጋዜጣዎች ፣ የተለያዩ የቴሌቪዥንና የራዲዮ ጣቢያዎችን በምዕራቡ ዓለሞች ብቻ በብዛት የምናገኘው?

ለምንድነው በአረብ አገሮችና ሕዝቦች ዘንድ ለአንድ ጉልበተኛ አምባገነን ለዘመናት፣ እስከ የሞት ዘመኑ ድረስ ለእሱ ብቻ የሚሰግደው? ለምንድነው፣ አንድ ማንንነቱ ያልታወቀ ሰው በመንግሥት ግልበጣ ቤተ-መንግሥት ሰተት ብሎ ሲጋባ በአፍሪካ ሕዝብ ዘንድ የሚደነቀው?

ለምንድነው አንድ አምባገነን ቡድን በ99% በሕዝብ ተመርጬአለሁ ብሎ ሲዋሽና ከሥልጣኑም ላይ አልወርድም ብሎ አንድን አገር ለ 10 ፣ለ20፣ 30 ና 40 አመታት በተከታታይ ሲገዛ ሰው ሁሉ ዝም ብሎ የሚመለከተው?

ለመሆኑ አምባገነኖችን ከአውሮፓ እንደተባረሩት ከአፍሪካም እነሱን አንድ ቀን ይባረሩ ይሆን?… በምን ዘዴ ይባረራሉ? …እንዴት? …ይህስ ከአልተቻለ?… ለምንስ አይቻልም?
በአፍሪካ የተነሱት የአምባገነኖች አይዲኦለጂአቸው ምን ይመስላል? ኢትዮጵያሰ ውስጥ አሁንስ የነገሰው የገዢው መደብ አይዶኦሎጂ ምንድነው? …የተቃዋሚዎች አይዶሎጂ በተቃራኒው የእነሱ በምን ላይ የተመሰረተ ነው ? ሁለቱ ሞዴሎች በምን በምን ላይ ይለያያሉ?

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

___

—————————————————-

https://leaimero.files.wordpress.com/2013/04/a_schreibfeder.gif

አስተያየት ለመስጠት / Comments

——————————–

——————–

leaimero-reg-logo © ለ አእምሮ 2005 / © Le’Aimero Copyright 2013

ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements

Le’Aimero’s Disclaimer

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s