ትችት እነደ መብት፣ ትችት እንደ ሙያ
ጋዜጣና ጋዜጠኛነት፣የፕሬስ ነጻነት
“የሰው ልጆች በሙሉ ፣ በትውልድ ነጻ እና አኩል መብት በሕግ ፊት አላቸው።” 1789 የፈረንሣይ ሽንጎ አዋጅ።
እንዴት ደሰ ይላል ቅዳሜና እሁድ ወይም ከሥራ መልስ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ ከቤተሰብ ጋር እየተወያዩ የዕለቱን አንድ ሳይሆን የተለያዩ ጋዜጣዎችን ሲያገላብጡ።
እጅግ ደስ ይላል ቡና ቤት በረንዳ ላይ ጋዜጣዎችን፣ ከቢራ፣ ወይም ከሻይ፣ ወይም ደግሞ ከአፕሬቲፍ ጋር፣የተለያዩ ሐሳቦችንና አመለካከቶችን አምዱ ላይ እየመተሩ አብረው ሲያጣጥሙ።
እኔን ማንንም በጣም ደስ ይላል አውሮፓና አሜሪካ መጽሔትና ጋዜጣ እቤት ድረስ በፖስታ መጥቶ የቁርስ ጠረጴዛ ላይ ሲዘረገፍ። የለመዱት ጽሑፍም ተከትሎ ያደሩበት ሆቴል ከተፍ ሲል። እንዴት ደስ ይላል፣ እየተዝናኑ፣ እየተንጠራሩ ሁሉነም ሲፈትሹት።
ግን ደግሞ እንደምናቀወቀው፣ይህን የመሰለ ሁኔታ ሁሉም ቦታ አይታይም።
አንዱ “ጉልበተኛ አምባገነን” ባልታወቀና በአልተሰማ ስም ከየትም መጥቶ፣ ሁሉንም ጋዜጠኞችን እሥር ቤት ወርውሮ ቢሮአቸውን ዘግቶ „…ከዛሬ ጀምሮ የቡርጃ የአደሃሪዎች ቅጠሎች ፣ እንዳይታተሙ በአዋጅ “ከልክዬዋለወ ሲል። በእጁም አንድ ጽሑፍ የተገኘውን ሰው አብሮም እዚያው እሱን ሲቀጣው፣ሲያባረው፣ ሲያስፈራራው።
የለም እንዳይባል ብዙ ቦታም እንደዚህ ተደርጎአል። ብዙ ቦታም የጋዜጠኞች ብዕር እንደ ወንጄል ተቆጥሮ ታስረዋል። ተደብድበዋል ። ቆስለዋል። ተገድለዋል። በአጋጣሚ ያመለጡትም ተሰደዋል።
በጣም ደስ ይላል ፣ ሱቅ ተገብቶ ከአንድ ሺህ ጋዜጣና መጽሓፍት ውስጥ ከእነሱም መካከል አንዱን ደስ ያለውን ሳብ አድረጎ ገንዘቡን ከፍሎ፣ አለፍርሃት ከእዚያ ሲወጣ!
አእምሮን እንዴት ደስ ይለዋል፣ መንፈስም እንዴት ይረካል፣ ከሃያና ከመቶ ሺህ መጻሕፍት ውስጥ አሥሩን ሃያውን ከአንድ መጽሓፍት ቤት ተውሶ ወደ መኖሪያ ቤት ማታ ሲገባ!
ግን እዚያም፣እዚህም ከታሪክ እንደምናውቀው፣ አንዱ መጥቶ፣ „…አንጎል የሚያበላሹ ድርሰቶች “ብሎ በአደባባይ ላይ መጽሓፍቶቸን ሰብስቦ ቤንዚን አርከፍክፎ በክብሪት ሲያቀጥል።
ሒትለርና ሞሶሊኒ፣ ስታሊኒንና ሌኒንን፣ ማኦና ፖልፖት፣ሞኝ አንሁን ከእንግዲህ ቀንድ አናበቅልም ….ካስትሮና፣ ኪም ኢልሱንግ ፣ ኢሳያስና ….ዝርዝራቸው ረጅም ነው፣…ጋዜጦች እንዳይሰራጩ ፣ መጽሓፍቶች እንዳይታተሙ፣ ቲያትር መድረክ ላይ አለ እነሱ ፈቃድ ሰዎች እንዳይጫወቱ፣ ፊልሞች እንደገና ከአለእነሱ ፈቃድ እንደይቀረጹ፣ እላይ የተጠቀሱ ሰዎችና ሌሎቸ ግብረ አበሮቻቸው፣ ከልክለዋል፣ ደምስሰዋል፣ ከመጽሓፍት ቤትም ግሩም መጽሓፍቶች አውጥተው አቃጥለዋል። በአዋጅም አንዱም ደፍሮ እንዳይጽፍም ፣ ሥዕልእንዳይስልም፣ ዘፈን እንዳይዘፈንም፣ እነሱ አግደዋል።
እንዴት ደስ ይላል፤ እቤት ተገብቶ ከሁለት መቶ ፣ ሦስት መቶ የራዲዮና የቴለቪዢን ፕሮግራሞች ውስጥ እያማረጡና እያወዳደሩ፣ የፈለጉትን፣አንዱን ወይም ሁለቱን ፣እያፈራረቁ ሲመለከቱት። እረ! እንዴት ደስ ይላል ከግል የመጽሓፍት መደርደሪያ ውስጥ አንዱን መጽሓፍ ሳብ አድረገው ሲያገላብጡት። ዘንድሮማ ኢንተርኔት ውስጥ ተገብቶ ከአንዱ ውቅያኖስ ወደ ሌላው ጠረፍ አለፍርሃት ሲዋኙ፣ ጽሑፍ ሲሰበስቡ እንዴት ደስ ይላል።
ግን እንደምናውቀው፣ አንዱ አምባገነን መጥቶ፣ ሁሉንም የመገናኛ መስመር ከስልኩ ጋር ጥርቅም አድርጎ ብዙ ቦታ በጉልበቱ ዘግቶአል።
የት ነው ? ከመሆኑ ያለነው? በስንተኛ ክፍለ-ዘመን ውስጥ ነው አሁን እኛ የምንገኘው? ለማገድ ማን ፈቀደለት? ማን አይዞህ አለው?
የሰው ልጆች በተፈጥሮአቸውና በባህሪያቸው፤ እንደ መላእክት ከክፉ ነገር የራቁ ፣ ንጹህና የተባረኩ ርህሩህ ፍጡሮች አይደሉም። በዚህ አትታለሉ።
ግን ደግሞ ይህ ስለተባለ እንደ ሰይጣንም እርኩስና አረመኔዎች አይደሉም። በሁለቱም መካከል የሚገኙ፣ ግን በጥቅሉ እንደዚህ ናቸው ተብለው ፣ በድፍኑ፣ በጅምላው ፣ „የማይያዙና የማይጨበጡ ፍጡሮች“ ናቸው።
” እንደዚህ ዓይነት አረመኔዎች” በየአለበት አሉ ስንል፣ ደግሞ” ደህና ሰው ” በዚህች ዓለም የለም ማለት አይደለም።ድህና ሰዎች ብዙ ቦታ አሉ። በሌላ አካባቢም እናገኛለን። ሁሉም ደህና ናቸው ብለን ስናምናቸውና ልባችንን ገልጠን ስንሰጣቸው ደግሞ “ቀጣፊ ሌቦች” ሁነው እስርቤት ሲወርዱ እናያቸዋለን።
„ቁጥጥር“ ከአልተደረገባቸው ፣ብዙ ሰዎቹ፣ ከአረመኔ ድርጊታቸው አይመለሱም ። እርግጥ በመልካም ቤተሰብ በጥሩ እንክብካቤ ተኮትኩተው ከአደጉ ደግሞ ደግና ርህሩይ ሰው ስለሚወጣአቸው፣እንደነሱ አይነት ሰዎች አረአያ ናቸው። ያም ቢሆን ምንም እርግጠኛ የሚያደርገን ነገር የለም። ጤነኛ ያልነው ሰው “ነገ አውሬ”ነው። ሰው “ዛሬም ሰይጣንም” ነው።
ለዚህም የአለፉት ዘመናት ብቻ ሳይሆኑ የቅርቡም ጊዜ የሰው ልጆች ታሪኮች በቂ ምስክሮች ናቸው። በሥልጣኔ ስም፣ ስንት በደል፣በዓለም ላይ ተፈጽሞአል። በሃይማኖት ስም የስንት ሰው ደም ፈሷል። በኮሙኒዝምና በሶሻሊዝም ስም የስንት ሰው ሕይወት፣ በከንቱ አልፎአል። „በነጻነት ትግል“ ስም ደግሞ የስንት ሰው ንብረት፤ የስንት ሰው ሕይወት ወድሞ ጠፍቶ፣ እናቶች መካን ሁነው ቀርተዋል። በፋሺዝም ስም ሰዎች በመርዝ ጢስ አልቀዋል።
„ሰው አረመኔም፣ ሰይጣንም፣ ርህሩህም ፣ ደግም ሰው:- ሁለቱንም፣ሦስቱንም ነው።“ ምን አልን? በተለያዩ ስሞች፣ የሰው ልጆች ሕይወት ጠፍቶአል። ለምን? ማን ናቸው እነሱ ይህን ለማድረግ?
ሰው ማለት በአንድ በኩል እላይ እንደቆጠርናቸው …. እነ ሒትለርና ሞሶሊኒ ፣ ስታሊንእና …ኢዲ አሚንን፣ ሞቡቱንና ፖል ፖትን፣ ፒኖቼ እና ማኦ ሴቱንግ፣… መንግሥቱ ኃይለማሪያምንና…ሌሎች ብዙ መሰሎቻቸውን ያካተተ ነው። አብረሃምና ሣራ፣ አቡነ ጴጥሮስንና፣ ማሪያ ቴሬዛን… በርካታ ….ሰማዕታትና ጻድቃን፣ በሌላ በኩልም ማለት ነው።
ለምንድነው አንደኛው „የአረመኔ ባህሪ ያለው? ሌላው በተቃራኒው ቅዱስ የሆነ ነገር የሚሰራው?“ለምንድነው በምዕራቡ ዓለም ነጻ-ጋዜጣ፣ ራዲዮን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች መክፈት፣ ማውጣት የሚቻለው? ለምንድነው በኮሚኒሰትና በሌሎች ቶታሊቴሪያን ሥርዓት በሕግ የሚከለከለው?
ለዚህ ሁሉ ጥያቄ ከፊሉን ሳያኮሎጂስቶች ከፊሉን ደግሞ የፖለቲካ ፈላስፋዎችና የሕብረተሰብ ተመራማሪዎች፣ የባህል ልዩነት ጠበበቶች በቂ መልስ( ትክክል ይሁን አይሁን መመራመሩ የሁሉም ፋንታ ነው) ሰጥተውበታል። ሁለቱም፣ ሶስቱም፣ እላይ የተጠቀሱት ክፍሎች የደረሱበት የሰው ልጅ በእራሱና በሌላው ላይ አደጋ ከማድረሱ በፊት “ቁጥጥር „ ይደረግበት በሚለው ሐሳብና ተመክሮ ላይ ሁሉም ይስማማሉ።
ጋዜጣና ጋዜጠኞች፣ ደራሲና ጸሓፊዎች፣ ተቺና የፖለቲካ ተንታኞች፣ ፈላስፋና የሕብረተሰብ ተመራማሪዎች….የሥልጣን ባለቤቶች፣ የሆኑትን ገዢዎች ( ይመረጡ አይመረጡ፣ ዘውዱን ይውረሱ ወይም ይንጠቁ፣…አይዉረሱ፣ ከየትም ይምጡ) እነሱን “የሚቆጣጠሩ ሰዎች“ ናቸው። ማን ፈቀደላቸው? ልንል እንችላልን። ተገቢ ጥያቄ ነው።
„ቁጥጥር „ የምትለውን ቃል ደግሞ ከአረመኔ ሥራ የማይመለሱት አምባገነኖቹ፣ ለተንኮል አላማቸው፣ በአንድ በኩል ስለምታመች፣ በሌላ በኩል “ጀሌውን ተከታይ ለማሳመን ” ስለሚያመች ፣ በጣም አድረገው ይህቺን ቃል እነሱ ይወዷታል።
„…እሱን አይደለም እንዴ! እሱን እኮ ነው፣ እኛ ለእናንተ የምንመኘው“ ብለው አንዴ እነሱ ሥልጣኑን ከነከሱ፣ ጠበቅ አድርገው፣ቀጥጥሩን ይይዟታል። በዚያም ስም ያገኙትን ደፍጥጠው ፣እድሜአቸውን ለማራዛም ይህቺን ቃል እንደፈለጉት ያንከባልሉዋታል። በሌላ በኩል ሥልጣን ላይ እስከሚወጡ ድረስ፣ እንደ እነሱ የግንባር ቀደም ቦታ ይዞ „…ለዲሞክራሲ፣ ለነጻ-ጋዜጣ፣ ለነጻ- ንግግር ፣መብቶች በሙሉ መከበር „ የሚታገል ሰው የለም።
ሁሉም አምባገነኖች ፣….ሒትለርና ሞሰሊኒ፣ ሌኒንና ስታሊን፣ ማርክስ፣ ማኦ ፖልፖት…. ዮሴፍ ጎብልስ ፣ ያውም እነሱ ግንባር ቀደም ሁነው፣ ለዚህ መብት መከበር፣ መታወቅ፣በሥራ ላይ መተርጎም፣ (ታሪካቸውን አንብቡ) እነሱ እንደ ሌሎቸ ዲሞክራቶች አብረው ፣ እነሱ ጎን ቆመው ታግለዋል።
በሁዋላ ግን አንደምናውቀው ዞር ብለው ሁሉም „የቡርጃው ዲሞክራሲ“ “የበዝባዦች ፕሮፓጋንዳ ጋዜጣ ” ብለው ጥለውት በቦት ጫማቸው እነሱ ፕሬሱን አፍነው፣ ረግጠው፣ ዘግተው ይዘዋል።
„ቁጥጥር „ ሲባል ምን ማለት ነው? ምን ዓይነት ቁጥጥር?ማን ነው ተቆጣጣሪው? ቁጥጥርስ እንዴት?
በድፍኑ „ትችት እንደ ሙያ“ ያልነው በጋዜጣ ሚና እና በጸሓፊ- ጋዜጠኞች ላይ ያተኩራል። ይህ ሙያም ደራሲና የፖለቲካ ጸሐፊዎችን፣ የታሪክና የሕብረተሰብ ተንተኞችን፣ ፈላስፋዎችንም ይጨምራል።
የሓሳብ ነጻነት፣ የመናገርና የመጻፍ ነጻነት፣ በአጭሩ የፕሬስ ነጻነት፣ በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን በስንት መከራ በትግል የተገኘ መብት ነው። ለዚህም የፈረንሣይና የአሜሪካን አብዮት ምስክር ናቸው።
በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን አንዳንድ የአውሮፓ መንግሥታት፣ የፕሬስ ሕግ በይፋ ሳያውጁ የፈረንሳዩ አብዮት ፣ያ አለፍርድ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ይዞ የሄደው፣ ዓይነት የሞት ጽዋ ለእነሱም በድንገት መጥቶ እንዳይቀምሱት፣ እንደይጨርሳቸው፣ ጋዜጠኞች የተወሰነ ነገር (በገደብ)በቅጠሎቻቸው ላይ አንስተው እንዲጽፉ “ገዢዎቸች” ፈቅደዋል።
በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ላይና በሃያኛው ክፍለ-ዘመን የፕሬስ ነጻነት በአብዛኛው የአውሮፓ አገሮች ታውጆ ብዙ ጋዜጣዎች፣በያለበት ታትመው መውጣት ይጀምራሉ።
ግን አረመኔ አምባገነኖች በፋሺዚምና በኮሚኒዝም ስም ፣በስታሊንም ስም ብቅ ብለው እላይ እንዳልነው፣ ጋዜጠኞችን አባረው፣ ሐብታቸውን ወርሰው፣ ከአለ እነሱ ጽሑፍ የሌሎቹን ማተሚያ ቤቶች ዘግተው፣ ድራሻቸውንም እንዳለ አጥፍተው “ዘለዓለማዊ መረባቸውን” መስሎአቸው በዓለም ላይ ለመዘርጋት ተፍጨርጭረዋል። ሒትለርና ሞሲሊን በሁለተኛው አለም ጦርነት ድል ተመተው ፕሬስ በአውሮፓ እጅና እግሩን ታስሮ ከነበረበት እሥርቤት ነጻ ይወጣል። ይህም እንደምናውቀው የምዕራቡን ዓለም ብቻ ያጠቃልላል።
ከሰባና ሰማንያ አመት በሁዋላ ደግሞ ኮሚኒስቶቹ አምባገነኖች ሳይታሰብ በተራቸው ተንኮታኩተው ሲወድቁ፣ ነጻ -ጋዜጠና ጋዜጠኞች እንደገና አሸናፊ ሁነው በምሥራቅ አውሮፓ ከተቀበሩበት መቃብር ብድግ ብለዋል። ከእነሱም ጋር የኮሚኒስቶቹም ጋዜጠኞች ሳይከለከሉ እዚህ አውሮፓ- ይህ ነው ዲሞክራሲ- እነሱም ዕለታዊ ሥራቸውን እንዲቀጥሉበት ተደርገዋል።
መ
ፕሬስና የፕሬስ ነጻነት እነሱንም የሚያጅበው ሳንሱር ግን መለስ ብለን ስንመለከተው በጣም ረጅም እድሜ ፣ ይህ ነገር አለው።
“ሳንሱር” የሚባለው ነገር ይፋ ሁኖ የወጣው ዮሓን ጉትንበርግ የሚባለው የጀርመኑ ተወላጅ1 ( 1450) አስቸጋሪውን በእጅ እየተገለበጠ ለንባብ የሚቀርቡትን ጥቂት መጻሕፍቶች፣ ከኒኬል ተሰርተው በወጡ „ዘመናዊ ፊደሎች“ እሱ ከተካቸው በሁዋላ ነው።
እነዚህ በእጅ ተለቅመው የተገጣጠሙ ፊደሎች በአንድ ጊዜ በእንድ ቀን ውስጥ፣ ከአንድ የበለጡ መጻሕፍቶችን አንድ ሰው አትሞ ማውጣት መቻሉን የተመለከቱ የቤተክርስቲያን ሃይማኖት አባቶችና ትላልቅ የመንግሥት በአለሥልጣኖች „ማንም ሰው አለ ልዩ ፈቃድ „ (መጪውን የጥብብና የዕውቀት መስፋፋት አይተው ) “አለ እነሱ ፈቃድ እንዳይገለገልበት” – ዛሬ ከእንተርኔት ጋር ማወዳደር ይቻላል – እነሱ ከልክለዋል። ይህ የሳንሱር ቁጥጥርም በህትመት ላይ በሕግ ተከልክሎ እስከ ፈረንሣይ አብዮት ድረስ ይፋ ሁኖም (ሁሉም) “ሲገለገልበት” ቈይቶአል።
የፈረንሣይ አብዮት ለመጀመሪያ ጊዜ የሳንሱር መጋረጃውን ገርስሶ ጥሎ የፕሬስ ነጻነትን ያውጃል። ይህ ፣ እንግዲህ በአውሮፓ ነው።
የ ደሴቱዋ የእንግለዚና የአሜሪካ ሁኔታ ደግሞ ለየት ያለ ነበር።
ጆን ሚሊተን በእንግሊዝ አገር (1644) /2 ሳንሱር እነዲነሳ ከጠየቀ ወዲህና በቨርጂኒያ፣ በአሜሪካን አገር በ1776 በሕገ-መንግሥታቸው ላይ የፕሬስ ነጻነትን ከአውጁ ወዲህ የአውሮፓ ምሁሮች ይህን መብት እነሱ እንዲኖራቸው፣ እንዲፈቀድላቸው ገዢዎቻቸውን፣ መንግሥታቶቻቸውን ጠይቀዋል። መልስ ያላገኙትም በስውር ሐሳባቸውን ወደ ማተሙና ወደ ማሰራጨቱም ተሸጋግረዋል።
በ1865 አውሮፓ ውስጥ ብቅ ያለው አዲሱ ተሽከርካሪው የሕትመት መሣሪያ በሺህና በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ጋዜጣዎች ታትመው አደባባይ ላይ ብቅ ለማለት ይህነው የማይባል ዕድል ይከፍታል። ይህን ያዩ ሁለት ቀልጣፋ ክፍሎች ቶሎ ብለው ሜዳውን ተሻምተው እነሱ ይይዛሉ።
በአንድ በኩል የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በሌላ በኩል ትርፍ ፈላጊ “ነጋዴዎች “ትላልቅ አሳታሚዎች ሁነው ሜዳውን ተካፍለው የፖለቲካ መድረኩ ላይ ብቅ ይላሉ። ይህን ጊዜ በአለሥልጣን ገዢዎች፣ ብዙ ነገሮች ከእጃቸው አፈትልከው ከመውጣታቸው በፊት “ሕግ” ወደማውጣትና በሕግ ወደ መቆጣጠሩ እሰኑም ይሸጋገራሉ።
በአዋጅ በተለያዩ አገርና መንግሥታት በ ሕገ- መንግሥታቸው ላይ “የፕሬስ ነጻነት፣… ምን እንደሆነ?…. ይህ ሕግ ምን እንደሚፈቀድ?… መብትና ግዴታውን፣ የሥራ መስኩና የሥራ አድማሱን ፣… ሥርጭቱና እንቅስቃሴው፣….የሚያሳዩ ፣ዝርዝር ደንቦችን ደንግገው ያወጣሉ። …ማንም ያለፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ (ይህቺን ነገር ሁለት ጊዜ ማንበብ ያስፈልጋል) የማንንም በፈቃድ የሚሰራውን የጋዜጣ ቢሮ መክፈትና መዝጋት እንደማይችልም በሕገ – መንግሥታቸው ላይ ( በተለያዩ ጊዜያት) እያሻሻሉና እየአረሙ ፣ ከጊዜውም ጋር አብረው አየተራመዱ አዳዲስ ሕጎችና ደንቦችን አወጡ። እንግዲህ የጸሐፊው “መደብ” የብዕር ሰው፣ ከደራሲ ጭምር ብቅ ይላሉ። ግን ለማስታወስ የደሪሲና የጸሓፊ ዕድሜ ከዚያም ከፍ ይላል። የአቴንን ታሪክ ተመልከት።
ያም ሁኖ እላይ እንዳልነው በሃያኛው ክፍለ ዘመን በሩሲያና በጣሊያን ፣ በጀርመንና በድፍን ምሥራቅ አውሮፓ አረመኔ አምባገነኖች ተነስተው፤ የፕሬስ ነጻነትና ሕግቹን ሽረው ጋዜጠኞችን እያሳደዱ፣ ማተሚያ ቤቶችን እየዘረፉና እየዘጉ የራሳቸውን /አንድወጥ/ቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ የሚያስፋፉ የእነሱን ጋዜጣዎች ብቻ “ሕይወት” የሚጠብቅ አዲስ ሕግ አውጥተው በያለበት በሕዝቡ ላይ መቀለድ ጀመሩ። እነሱም እዚህ እላይ እንደጠቆምነው በሁለት መንገድ ፣፣ተራ በተራ ከፖለቲካው ዓለም ፣ይክበር ይመስገን ፣ዓይናችን እያየ ተወገዱ።
በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍጻሜ ላይ ፋሺሽቶቹ ድል ሲመቱ ነጻ-ጋዜጣዎች እንደ ገና በብዛት እዚያና እዚህ በምዕራብ አውሮፓ እንደ አሸን ፈሉ። ከበርሊን ግንብ ጋርም ኮሚኒስቶቹ እዚህ አብረው ሲወድቁ ፣ በምሥራቅ አውሮፓ ነጻ-ጋዜጣዎች – አሁንም ይክበር ይመስገን – እንደገና በየአለበት፣ …ከነጻ-ራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር አብረው አበቡ።
አፍሪካስ አሁን እንዴት ናት? ….ኢትዮጵያስ በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ-ዘመን በጋዜጣ ሕትመት የት ትገኛለች?
ሠ
ወደዚያ ከመዝለቃችን በፊት ሁለት “አዋጆቸን ” እንመለከት።እነዚህ አዋጆች በሁለተኛው ዓለም ጦርንት ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ዓለም አቀፋዊ አዋጆች ናቸው።
ኪዚህ ሁሉ የመከራ የጋዜጠኞች ዘመን በሁዋላ አንዱ አዋጅ ታሪክን መሰረት አድርጎ እንደዚህ ብሎ ይጀምራል። “…ሰበአዊ መብቶችን ችላ ማለትና መናቅ የሰውን ሒሊና የአስጨነቁ አረመኔያዊ ተግባሮችን በማስከተላቸውና የተራ ሰዎችም ሁሉ ፣ ዋነኛው ጉጉት የሰው ልጆች ሁሉ የንግግርና የእምነት ነጻነት የሚጎናጸፍበት ፣ ከፍርሃትና ከችግር ነጻ የሚወጣበት ዓለም እንዲመጣ ….በመሆኑ
ሰዎችም በክፉ አገዛዝና በጭቆና የተነሳ ያላቸው የመጨረሻ ምርጫቸው አመጽ እንዲሆን እንዳይገደዱ፣ ሰበአዊ መብቶች በሕግ እንዲከበሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት…” ይህን ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች መግለጫ በ1948 በጋራ አውጀናል ይልና፣ ይህ ትልቁ ሰነድ። የሚታወቀውና ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮች ደግሞ በፊርማቸው ያረጋገጡት (የፈረሙት) ሰላሳ አንቀጾችን ያዘለው አዋጅ ወረድ ብሎ የሚከተሉትን ፍሬ ሐሳቦች ይደረድራል። ።
ሁለቱንም የአምባገነኖች ሥርዓት ፣ የፋሺስቱንም የኮሚኒስቱንም ፣ተራ በተራ የቀመሰው የጀርመን ሕዝብ ሕገ-መንግሥትም፣ ከአንድ አመት በሁዋላ በ1949 ተመካክሮ በአወጣውና በአወጀው አዋጁ ላይ፣ በአንቀጽ አምስት ላይ ስለ ነጻ – ዜና መሰራጨት፣ ስለ ነጻ-አስተሳሰብ በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ መስፋፋት፣ በአጠቃላይ ስለ የፕሬስ ነጻነት የሚከተለውን አረፍተ ነገር ፣በሕገ-መንግሥቱ ላይ፣ መከራም ያስተምራል ፣ እንዲሰፍርም አድርጎአል።
“…ማንም ሰው” ይላል ደንቡ” ሓሳቡንና አስተያየቱን በድምጽ፣ በቃላትና በጽሑፍ፣ በሥዕል ጭምር ፣ በማንም ሳይታገድ የማስፋፋትና የማሰራጨት መብት አለው። እነዚህንም ለእሱ አስፈላጊ ናቸው ብሎ የሚገምታቸውን ዜናዎችና መረጃዎች ለመሰብሰብ መብት አለው። የፕሬስ ነጻነትና ሓሳብን አለ አንዳች ገደብ በሙሉ ነጻነት በራዲዮና በፊልም አዘጋጅቶና አቀነባብሮ ማሰራጨት በሕግ የተፈቀደ ነው። የሳንሱር ቁጥጥር ( ቁም ነገሩ ላይ ደረስን ፣ አምባገነኖች ይህቺን ቃል ይወዳሉም/ ይፈራሉም ) በምንም ዓይነት አይኖርም ” የጀርመን ሕገ- መንግሥት ይላል።
ረ
ትችትና ነጻ አስስተሳሰብ ፣ ጋዜጣና ጋዜጠኛነት ትላንት የተጀመረ ሙያ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ። ወይም ይህ መብት ለነጮች እንጂ ለጥቁር አፍሪካ ለእነዚያ የራሳቸው የሆነ ፊደል እንኳን ለሌላቸው”ፍጡሮች! ለእነሱ አይገባም የሚሉም ኃይሎች አሉ።
ሌሎቸ ማርክስና ሌኒንን ፣ማኦ ሴቱንግንና ስታሊንን እየጠቀሱ፣ ይህ መብት፣ “ለላብ አደሩ መደብ እንጅ ለማንም ፣ከበርቴና አቆርቋዥ መደብ ፣ ለኢትዮጵያዊ፣ ለኢትዮጵያኖች አይገባቸውም” የሚሉም አሉ። ይህን ከሚሉት መካከል አንደኛው “ማሌሊት- ሕዝባዊ ወያኔ” ነው።
“…የመዝባሪዎችም የተመዝባሪዎችም መብትና ጥቅም” በሚለው “ትንተናው”ሁለቱን ” ባንድ ላይ አስጠብቆ መሄድ አይቻልም። የሁለቱ መብቶችና ጥቅሞች ተጻራሪ ናቸው። አንደኛውን ለመጠበቅ የግድ ሌላኛውን መርገጥ ያስፈልጋል። ስለዚህ ዲሞክራሲን ከጠባብ ክልል አውጥቶ ለማስፋት የመጠቀ ዲሞክራሲን ተግባራዊ ለማድረግ ዲሞክራሲ የሕ/ሰቡ አብዛኛው ክፍል ሃቀኛ ተግባራዊ መብት እንዲሆን ለማድረግ ከተፈለገ ገደብ የለሽ ዲሞክራሲ ማወጅ አይቻልም። እንደዚህ ዓይነቱ የመጠቀና የሰፋ ዲሞክራሲ ተግባራዊ ለማድረግ ከተፈለገ መዝባሪ መደቦችን ከዲሞክራሲ ማግለል በነሱ ላይ ገደብ ማስቀመጥ የግድ አስፈላጊ ነው። ዲሞክራሲ ከጠባብ የቡርዠዋ ክልል ለማውጣት የላብ አደሩ አምባገነንነት መስርቶ ቡርዡዋውን ከዲሞክራሲ ማግልለ ያስፈልጋል።” ማሌሊት ማርክስ- ሌኒን ሊግ ትግራይ ገጽ 39. 1984 ዓ.ም
እንግዲህ ይህ ነው ያኔ ለአገሪቱ ፕሬስ ለኢትዮጵያ የተነደፈው የውስጥ ፕሮግራማቸው። ይህ ፕሮግራም ደግሞ አሁንም አልተሰረዘም። እንዲያውም በሥራ እየተተረጎመ ነው።
የሚያሳዝነው ከወታደሩ መንግሥት ከደርግ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለአለፉት አርባ አመታት በተከታታይ የፕሬስ ነጻነት አለምንም ገደብ በአገሪቱ ፣እንደ ኬኒያና እንደ ጋና እንደ ናይጄሪያና እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽና ቱኒዚያ አለመኖሩ ነው የችግሮች ሁሉ መነሻ ነው። ለምን?
ሰ
በኢትዮጵያ የጋዜጣና የመጽሓፍት ማተሚያ መኪና አዲስ አበባ የገባው በ1879 ዓ.ም ነው። “ዳግማዊ ምኒልክ በሙሴ ሽፋኔ በኩል አንድ ትንሽ የጽሕፈት ማተሚያ መኪና ከአውሮፓ አስመጥተው በጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ጽሕፈት ቤት አጠገብ አቆሙት። ከዚያም በሁዋላ ሥራው በሹሙ በአቶ ደኀኔ ወልደ ማርያም ሥር ሁኖ፣ አንዳንድ መንግሥታዊ ጉዳይ በአማርኛ ፊደል ይታተምበት ነበር። አንድ ትንሽ ጋዜጣም በተወሰነ ጊዜ ሳይሆን፣ አልፎ አልፎ እየቆየ በነአቶ ደስታ ምትኬና በነሙሴ እንድርያስ ከዋዲያ አዘጋጅነት ይታተምበት ነበር። በዚህ ጊዜ ዳግማዊ ምኒልክ ጋዜጣውን “አእምሮ” ብለው ሲሰይሙት ማተሚያ ቤቱንም “መርሐ ጥበብ” ብለውት ነበር።
አጼ ምኒልክ ታመው እቤት ከዋሉ በሁዋላ ግን ሥራው ተቋርጦና ማተሚያው ሥራ ፈትቶ እንደ ተቀመጠ ትዝ ይለኛል።”
አቶ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ እዚሁ ላይ ረመድ ብለው ስለ በ1900ዓ.ም በፈረንረሳዊው በሙሴ ደባዥ አዲስ አበባ ስለ ገባው ሌላው የላቲን ፊደል መምቻው (አሳቸው የፈረንጅ ፊደል ይሉታል) የማተሚያ መኪና ፣ በታሪክ ደብተራቸው ላይ አትተዋል። በሁዋላም በ1904 ዓ.ም የንግድ ማተሚያ ቤትን ስለ አቋቋሙት፣ ስለ እነ ሙሴ ሽፋኔና ስለ እነ ሙሴ ባልደሣሪያ ፣ ሙሴ አትናቴዎስም ቀጥለውም አንስተው ተርከዋል። ።
የተላያዩ የጸሎት መጽሓፍት፣ የንግድ ካረርኒዎች፣ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ አጫጭር ድርሰቶችና ግጥሞች እየታተሙ ይወጡ እንደነበርም ጸሓፉው ዘርዝረዋል። የሐማሴኑ ተወላጅ ብላታ ገብረ እግዚአብሔር “ስለ አገር ፍቅር ” የተጻፈውን ግጥማቸውንም እዚያ ማተሚያ ቤት እያሳተሙ ያወጡ እንደ ነበረም አቶ መርስዔ ኀዘን ጠቅሰዋል።
በልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ጊዜ ደግሞ እንደ እነ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወልደ ሥላሴ ያሉ ጸሐፊዎች ድርሰታቸውን የሚያሳትሙበት ፣ ጋዜጣዎች የሚወጡበት ” ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት “ይቋቋማል።
አንዳነድ ጸሓፊዎችም በርትተው፣ ትችት፣ሐተታና አስተያየት፣ በአስተዳደርና በቤተ ክህነት ላይ፣ አልፈውም በመንግሥት ሰራተኞችም ላይ ጉድለት ሲያዩ ፣እነሱ እንዲታረሙ ይሰነዝሩም እንደ ነበር፣ እዚሁ የአቶ መርስዔ ኀዘን መጽሐፍና/3 ሎሎች ቦታዎች ላይም እንመለከታለን። “ቄሣሩ ንጉስ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይም አቶ ብርሃኑ ድንቄም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አንዳንድ ጉድለቶችን ይተቹ እንደ ነበረና ንጉሱም ይህን አይተው እንደ አቀረቡአቸውም የቀድሞው አምባሳደር አስታውሰው ጽፈዋል።
ሥልጣን ላይ እስከሚወጣ ድረስ ሁሉም በአለ ሥልጣን እንደ ችሎታውና እንደ ፍላጎቱ፣ እንደ አቅሙም “የፕሬስ ነጻነትን” – ወታደሪዊ ደርግም ለትንሽ ወራት ፈቅዶአል ። ወያኔና ሻቢያም እስከሚጠናከሩ ድረስ፣ ሜዳውን ለጥቂት ጊዜ ለቀዋል። ሁሉም ትንሽ ቆይቶ ይህን የፕሬስ ነጻነት ገፈው እጫማቸው ሥር ወርውረውታል።
ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚንስተር ሲሆኑ ለፕሬስ ነጻነት ቅድሚያ ሰጥተዋል። ግን ትንሽ ቆይቶ ብቅ ያሉት ኃይሎች “ዲሞክራሲ በገደብ/አለገደብ…” ብለው ተበጣብጠው ሥልጣኑን ለሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማሪያም አሳልፈው ሰጥተው ፣ያ የኢትዮጵያ ደራሲ፣ …ጸሓፊ፣ ተቺ፣ ነጻ አስተሳሰብና አመለካከት በአገሪቱ ማስፋፋት የሚፈልገው ምሁር፣ ፈላስፋ፣ ፖለቲከኛ፣ አፉ ተለጉሞ እንዲቀር ተደርጎአል። እንግዲህ በእሱ ፋንታ በአገሪቱ ምን ዓይነት ፍልስፍና ነገሠ?
ከዚያስ?
አረ ለመሆኑ የፕሬስ ነጻነት ምንድነው? የሐሳብ አገላለጽ በኢትዮጵያ እንዴት ነው? ማነው መናገር መጻፍ፣ሐሳቡን ማሰራጨት የተፈቀደለት? ለመረመረድነው የግራው ክንፍ በስታሊን ትምህርት ዓይኑ የታወረ ሰው “የፕሬስ ነጻነነትን” የሚፈራው ? ወይም ደግሞ ግፋ ቢል እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ ብቻ “ሥልጣን እስከ የሚይዝ ድረስ የሚደግፈው”?
ኦ ያገሬ ልጆች ! “…አጋንንቶቹ ከገሃነም እሳት አምልጠው” ዊልያም ሼክስፒር እንዳለው “… እኛው መካከል ነው ፣ ተሰግስገው ያሉት!”
ይቀጥላል፣ ወዳጄ ገና ይቀጥላል….
“ሚዲያ ፣…ፕሬስ፣ ጋዜጣና ጋዜጠኛነት አላማቸውና የሥራ መስካቸው ሰፊ ነው። የተለያዩ ዜናዎችን ማቅረብ አንደኛው ነው። የተለያዩ አስተሳሰቦችንና ሐሳቦችን ማስተናገድ ሌላው ነው። ስህተትን ጉድለትን ፈልፍሎ አውጥቶ ማጋለጥ ሌላው ሦስተኛ የሥራቸው መስክ ነው። ከእዚሁ ጋር በሥልጣን መባለግን ፣ ሙስናንና ሌብነትን፣ የዘመድ ሥራና አገር ዘረፋን፣ … ፍርድና ፍትህ ሲጓደል ማጋለጥና አደባባይ አውጥቶ ሰው እንዲነጋገርበት ማድረግ የጋዜጣና የጋዜጠኞች ኃላፊነት ነው። ዓይኑም ሥልጣን ላይ በተቀመጡት ሰዎች ላይ እንደ አነጣጠረ ሁሉ፣ ተቃዋሚዎቹም ሲያጠፉ ዝም ብሎ አያያቸውም፤ እነሱም የትችቱ ኢላማዎቹ ናቸው። ዕውንተኛ ጋዜጣና ጋዜጠኛ ፣ ነጻ ፕሬስ ዋና ሥራው ትችት ነው።
እግረ መንገዱን አንባቢዎቹንና አድመጮቹን ፣ተመልካቾቹን ያዝናናል። ያስተምራል። ምክር ይሰጣል። ያስጠነቅቃል። …ዲሞክራሲ ሥረዓት በአንድ አገር የሚገነባውም በዚሁና በሌሎቸ መሰረት ላይ ብቻ ነው።” (ከጸሐፊው የማስታወሻ ደብተር)
ከሁለት ዓለም አስተሳሰቦች ፣ ከሁለቱ ዓለም አመለካከቶች አንደኛው በኢትዮጵያ ከነገሰ ይኸው ከአርባ አመት በላይ አልፎአል። አንደኛው ከሁለት መቶ አመት በላይ ዕድሜ ያለው የነጻው ሕዝብ አስተሳሰብ ነው። ሁለተኛው ገና ትላንት የተፈጠረ ግን ደግሞ ወድቆ የተንኮታኮት የዕብዶች ሥራና ቅጀት ፣ የተባበሩት መንግሥታት ሰነድ እንደሚለው “የአረመኔዎች ” አስተሳሰብ ነው። ነው።
——-
2/ John Milton