ሊበርቲ፣…ዲሞክራሲ
„የሰው ልጆች ነጻ ናቸው። ግን እጅና እግራቸው በብዙ ሰንሰለት ተተብትቦ ታስሮአል።“ ጃን ጃክ ሩሶ
„ነጻነት ማንም የማይቀማኝ፣የማይሸጥ የማይለወጥ፣ የግል ሐብቴ ነው።“ ማርቲን ሐይድገር
ስዕል፥ ፔሪክለስ ለአቴን ዲሞክራሲ ሲታገሉ ለወደቁ ወታደሮች መታሰቢያ ንግግር ሲያደርግ /wikipedia
በምን ተዓምር ነው አምባገነኖች በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ በአራቱም ማዕዘን በአንዴ እንደ አሸን የፈሉት?
ማነው እነሱን የላከብን?… ለቅጣት፣… የእግዚአብሔር ቁጣ ነው ? ወይስ የሰይጣን ሥራ? ወይስ ሟርተኞች ተደብቀው የተበተቡልን መኣት?…አምባገነኖች ከየት መጡ? እነሱስ እነማን ናቸው?
አምባገነኖች ብቅ ለማለት፣ ለመሰፋፋት፣ ሥር ሰደው እግራቸውን በአካባቢው ለመትከል፣ ሜዳውም አየሩም አፈሩም ወሃውም፣…የሚያመች መሆን አለበት። አለበለዚያ ጠውልገው ደርቀው እዚያው ክችች ብለው ንፋስ ይዞአቸው እንደመጣው ሁሉ ነፋሱ እነሱን እያዋከበ ይዞአቸው ይሄዳል።
ሰሜን አሜሪካ ለአንድ አምባገነን መነሳት አመቺ ቦታ አይደለም። አውሮፓም እንደዚሁ።
ላቲን አሜሪካ በተቃራኒ ተደጋግሞ እንደታየው አመቺ መንደር ነው። ግነ እነሱ ከዚያ ከደቡብ አሜሪካ ብቅ እንዳሉ ወዲያው ተባረው ሄደዋል። ከምሥራቅ አውሮፓም ተነቅለዋል። አረብ አገሮች፣ ለቀሩትና ለተረፉት ማስጠንቀቂያ ትሰጥቶአቸዋል።አፍሪካስ?
ከደቡብ አፍሪካ፣ ከጋና እና ከናይጄሪያ፣ ከጎረቤት አገር ከኬንያ ጭምር፣ ሁለተኛ እዚህ እንዳትደርሱ ተብለው፣ በጅራፍ፣ በምርጫ ቅጣት ተባረዋል።
A
አምባገነኖች እና የአምባገነን ትምህርት፣ በአጭሩ የቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር- ኤርትራንም ያጠቃልላል- የእኛ ብቻ „ልዩ በሽታ“ አይደለም።
እርግጥ የኢትዮጵያ ምድር ከሌሎቹ እብዛኛዎቹ ቦታዎችና አካባቢዎች ለአምባገነን አስተሳሰብ መስፋፋት ያመቸ ሥፍራ ነው። ግን ከሩሲያና ከጀርመን፣ ከጣሊያንና ከእስፔን፣ ከቻይና፣ ወይም ከቬትናምና ከኪዩባ ….አይለይም።
ግን ለምንድነው? በሕንድ የቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ እዚያ ያልነገሰው?…እሩቅ ምሥራቅ፣ ጃፓንንስ እንዴት ናት? …..ኮሪያስ?… የትኛው ኮሪያ?
አንዱ የኢትዮጵያ መንግሥት „የኮራበት“፣ አንደኛው መንግሥት ደግሞ ማንም ሳይመርጠው ፣ ማንም ሳይጠይቀው„ዝቅ ብሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ይቅርታ“ የጠየቀበት፣ የአገራችን ዘማች ሠራዊት ደማቸውን ያፈሰሱበት የኮርያ ግማሽ-ደሴት፣ ለእኛ ለኢትዮጵያኖች “….አምባገነን ከየት ይመጣል?… አምባገነንስ ምንድነው? …አምባገነን ለዕድገት ያመቻል? ወይስ ያደናቅፋል?.. አምባገነን እሥር ቤት ነው? ወይስ አይደለም? „ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥሩ የትምህርት ቦታ ይመስለናል።
ጀርመንም፣ ዋና ከተማዋ በርሊንም ስለ አምባገነን ሥርዓቶች፣ ስለ ኮሙኒዝምና ስለ ፋሺዝም፣ ስለ ቶታሊቴሪያን አስተሳሰብና ሥርዓት፣ ጥናት ለመውሰድ ፈቃደኛ ለሆነ ሰው፣ ከኮሪያ ቀጥሎ ግሩም ሜዳ ነው።
ኮሪያ እንደምናየው፣ ተቃዋሚ፣ ጠያቂና ተቺ በሌለበት አገር፣ አንድ ቡድን ከመሬት ተነስቶ ሥልጣን ላይ ጉብ ብሎ፣ እንደ የዘውድ አገዛዝ፣… ሥልጣኑንና ወንበሩን፣ አባት ለልጁ፣ እሱ ደግሞ ሲደክም ለበኩር ልጁ፣ ያኛው ደግሞ ለልጅ ልጁ፣ አገሩንም ሐብቱንም፣ በአለሙሉ ሥልጣኑንም እንደሚያስተላልፍ ለማየትና ለመገንዘብ አመች ሥፍራ ነው። በአዋጅ፣ አልፈው ተርፈው ሰውን በትዕዛዝ የሚያስለቅሱም ናቸው።
„ንጉሡ ሊቀመንበር“ በሰሜን ኮሪያ ያደረጉትን፣ ጄኔራሎቹንንና የጦር መኮንኖቹን፣ ካድሬዎቹንና የፖሊት ቢሮ አባሎቹን ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ምንም እነሱን የሚያግዳቸው፣ ነገር የለም። እንግዲህ እዚያ የምናየው ነገር ሌላም ቦታ ተቆጣጣሪ አካልና ክፍል ከሌለ፣ የማይደገምበት ምንም ምክንያት የለም።
B
በሌላ በኩል፣ ደቡብ ኮሪያና ምዕራብ ጀርመን፣ ሌሎቹ „ወንድሞቻቸው“ በቴክኒክ ዕድገት ወደሁዋላ ሲቀሩ በምን ታአምር ይኸው እንደምናየው፣ እነሱ አምልጠው ለሄዱ ቻሉ? የሚለውን የብዙዎቻችንን ጥያቄም እነዚህ ሁለት አገሮችን ማየት ለሚፈልግ ሰው ደህና መልስ ይሰጡናል።
በአጭሩ አንደኛው ወገን የስታሊን እና የሌኒንን፣ የማርክስና የኤንግልስን ፣ የኪሚ እና የሆኔከርን „ዕብድ“ የሚያክሉ ፎቶግራፎች በየአጋጣሚው አደባባይ ላይ፣ አንድም ጥያቄ ሳያነሱ እየተሸከሙ „ሲንቀዋለሉ“፣ ነጻነት ያለበት የምዕራብ ጀርመን ና የደቡብ ኮሪያ ሰዎች፣ እየተመራመሩ፣ እየጠየቁ፣ እየተቹ፣ ጎበዙን የአዋቂዎቹን ፓረቲ እየመሩጡ እዚህ፣ ዛሬ የምናየው የቴክኒክ ደረጃ ላይ እነሱ ሊደርሱ ችለዋል።
„ደቡብ ኮሪያ ያደገችው በአምባገነኖቹ ወታደር፣ በጄነራሎቹ ክንድና አገዛዝ ነው፣ ስለዚህ በኢትዮጵያም፣ በኤርትራም እንደዚህ ዓይነቱ ሥርዓት፣ እግሩን ተክሎ ቢቆይ መልካም ነው። ይህ ሥርዓት እንዳይነካም መታገል ተገቢ ነው „ የሚሉ ብልጣብልጦች ድምጽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአንዳንድ አካባቢ ተሰምቶአል። ይህ ግን የመጨረሻው መንፈራገጫ ምልክት እንጂ ከጀርባው ምንም አሳማኝ ነገር እንደሌለውም የሚታወቅ ነው።
„የዓለም ዕድገት፣ የታሪክ ጉዞ፣ …ከዝቅተኛው፣ ከጋሪዮሽ ሕብረተሰብ ተነስቶ፣ በፊውዳል አድርጎ፣ ካፒታሊዝምን ይዞ ወይም ይህን ሥርዓት ዘሎ፣ ወደሶሻሊዝም ዘልቆ የማይቀረውን የኮሚኒስት ሕብረተሰብ፣ ወደፊት ይመሰርታል፣ አሰከዚያ ጊዜ ድረስን ጭቆናውንም፣ የአምባገነኑን ዱላ እንደምንም ብለህ ተቀበል ፣ ቻለው፣ አንተ ባትደርስበት ልጆችህ፣ እነሱም ካአልሆነላቸው፣ የልጅ ልጆችህ፣ የሁዋላ ሁዋላ ከጣፋጩዋ የምድር ላይ ገነት፣ እሱዋ ከምትሰጠው መልካሙዋ ፍሬ፣ እነሱ ቁጭ ብለው ይለቅማሉ፣…እሰከዚያ ጊዜ ድረስ፣ ግን ዝም ብለህ ተገዛ!“ የሚለው የአፍዝ አደንግዝ ቅስቀሳ፣ የሰው ልጆችን ሙሉ ነጻነት፣ የሰበአዊ መብቶችን መከበር ጉዳይ፣ ብዙዎቹ፣ ዞር ብለው እንዳይመለከቱት፣ መለስ ብለውም እንደይጠይቁና እንዳያስቡበትም፣ እነሱን አድርጎአቸዋል።
„አደሃሪ ቡርጃ፣… ሁዋላ ቀር፣ አቆርቋዠ፣ …ፊውዳል፣…ሰው በላ….“ በሚባሉ ቅጽሎችም ሌላውን ዝም አሰኝተው፣ አምባገነኖቹ እግራቸውን፣ ቤተ-ምንግሥቱ ውስጥ ዘርግተው፣ በሕዝቡ ላይ እንዲቀልዱም እነሱን በዓለም ዙሪያ ረድቶአቸዋል። ወደ „አልጋና ዘውድ“ ውርስ የሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስቶችም የሄዱበት ምክንያትም (ሌላ ነገር ሳይሆን) ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።
የምዕራቡ ፖለቲከኛ እንደገና ለመመረጥ ተቀናቃኙ አርፎ ስለማይተኛለት፣ ከብዙ ነገሮች ተቆጥቦ (አሉ ከእነሱም ውስጥ የበግ ደበሎ የለበሱ ተኩላዎች፣ ግን በፕሬሱ ይጋለጣሉ) ለአገሪቱ ችግር መፍትሔ ይፈልጋል፣ ዕውቀቱን ያሻሽላል፣ ከሕዝቡ ጋር ይውላል፣ ችግራቸውንም ያዳምጣል…። የግዛት ዘመኑም እድሜ ልኩን ሳይሆን ገደብ እንዳለውም ያውቃል። …በሕግ ፊትም ከማንም እኩል እንደሆን እሱም ሕዝቡም፣ ስለሚያውቁ እንደ ላይኞቹ ቀብጦ እድሜ ልኬን ልግዛችሁ ብሎ አፉንም አያበላሽም።
C
አሁን ብዙውን ሰውና አብዛኛውን ሕዝብና መንግሥታት እየሳበና እየማረከ የመጣው የዓለም አቀፉ የሳበአዊ መብቶች መከበርና መጠበቅ፣… የዲሞክራቲክ ሥርዓትና የሕግ በላይንት፣…ነጻ-ጋዜጣና ነጻ-የሸንጎ ምርጫ፣ አስተሳሰብ…ከየት መጣ?
እንዲያው ሳይታሰብ ከሰማይ ላይ ዱብ ያለ ነገር አይደለም። ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በተለይ በፋሺሺቶቹ፣ በሒትለርና በሞሶሊኒ በሁለቱ አምባገነኖች በተጫረው ጦርነቶች በእነሱም ሳቢያ ከመጣው ፍጅት የተገኘ ተመክሮ ነው።
ይህ የብዙ ሚሊዮንን ሰው ሕይወት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያና በሌሎች አካባቢዎች ይዞ የሄደው ጦርነት፣ እንደገናም በዚህቺ ዓለም ላይ ተመልሶ እንዳይመጣና እንዳይነሳም፣ ለማገድ ነው።
ይህ አንደኛው ማብራሪያ ነው። ሁለተኛው ምክንያት፣ የላብ-አደሩ ወይም የወዝ-አደሩ አምባገነን ሥርዓት እተስፋፋ መምጣቱ ነው።
ለዚህ ነው በ1948 ዓ.ም ኢትዮጵያ እራሱዋ በቦታው ተገኝታ በፈረመቺው የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ ላይ የሚቀጥለው አረፈተ ነገርም እንዲሰፍር የተደረገው። በመግቢያው ላይ አዋጁ “…. ሰበአዊ መብቶችን ችላ ማለትና መናቅ የሰውን ልጅ ሒሊናን የአስጨነቁ አረመኔያዊ ተግባሮችን አሰከትለዋል…“ ይላል።
ይህም የአረመኔዎች ሥራ በቆዳ ቀለምና በዘር ጥላቻ ላይ ተመስርቶ፣ እነደምናውቀው አይሁዶችን በአውሮፓ፣ ጥቁሮችን በኢትዮጵያ፣ ቻይናንና ኮሪያኖችን በእሲያ በመርዝ ጢስና በጋዝ፣ በቦንብና በእሳት፣ እነዲፈጁ አድርጎአል።
በሃይማኖት ጥላቻም ላይ ተመስርቶ ሰዎች ለፈለጉት አምላካቸው እንዳይጸለዩ፣ የጸሎት ቤታቸውም እንዲፈርስ እና እንዲቃጠልም ተደርጎአል።
ይኸው መግለጫ፣ ቀጠል አድርጎ እዚሁ መግብያው ላይ „….ዋነኛው የሰው ልጆች ሁሉ ጉጉት፣ የንግግርና የእምነት ነጻነት የሚጎናጸፉበት ፣ ከፍርሃትና ከችግር ነጻ የሚወጡበት ዓለም እንዲመጣ ነው“ ብሎ ይህ አዋጅ ተውጆአል፣ ይለናል።
„…ሰዎች በክፉ አገዛዝና በጭቆና ተማረው ያላቸው የመጨረሻ ምርጫም አመጽ ለማካሄድ እንዳይገደዱም፣ (እነዚህን) የሰበአዊ መብቶችን በሕግ እንዲከበሩ ማድረጉ አሰፈላጊ…ነው“ ብሎ የ1948 ዓ.ም መግለጫ፣ መንግሥታትን ሁሉ እንዲያስቡበት ይመክራል።
እንግዲህ ወረድ ብሎም ይህ ኢትዮጵያ ወዳ የተቀበለቺው፣ የዓለም አቀፉ የሰበአዊ መብቶች አዋጅ፣ የእያንዳንዱን ሰው፣ ትልቅም ይሁን ትንሽ ፣ ሐብታም ይሁን ደሃ፣ በአለሥልጣንም ይሁን ዝቅተኛ ተራ ሰው፣“…. ሙሉ ነጻነቱን“ በዝርዝር እንደዚህ አድረጎ አንቀጽ፣ በአንቀጽ፣ ከፋፍሎ አሰቀምጦልናል።
እያንዳንዱ ሰው — አንቀጽ ሦስት ላይ እንደሰፈረው — ነጻ ሰው ነው ይላል። አንቀጽ አራት–አዋጁ ላይ እንደሚነበበው– ባርንትን ይከለክላል። አንቀጽ አምስት ፣ ማንንም ሰው ማሰቃየት ወይም በጭካኔ ና ኢሰበአዊ በሆነ መንገድ ማጉላላት ወይም ማዋረድ ወይም መቅጣት አይቻልም፣ ይላል። ዘጠኝ ላይ፣ ማንም ሰው በዘፈቃድ በሆነ መንገድ ሊያዝ፣ ሊታሰር ወይም ሊጋዝ አይችልም፣ የሚለውን አረፍተ ነገር መግለጫው አንስቶ ይህን ወንጄል፣ ያግዳል። ይከለክላል።
አንቀጽ አሥራ አንድ፣ ትላንት የተጻፈ፣ ከጊዜው የኢትዮጵያኖች ጥያቄም ጋር አብሮም የሚሄድ ይመስላል፣ …ማንም ሰው በተከሰሰበት ወንጀል በሕጋዊ መንገድ፣ እራሱን የመከላከል መብቱ ተጠብቆለት፣ በሕጋዊና ግልጽ በሆነ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ እነደ ጥፋተኛ አይቆጠርም ይላል።
አንቀጽ 15 ስለ የዜግንት መብት ያነሳል። እዚሁ ላይ ማንም ሰው በዘፍቃድ ንብረቱን በማንም አይነጠቅም ይላል። አንቀጽ 18 እና 19፣ 20 እና 21 ደግሞ ፣ ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የሚይጠይቀውን በቅርቡም አዲስ አበባ ላይ ሠልፍ የወጡት ሰዎች ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ …ስለ የሓሳብና የሒሊና ነጻነት፣… ስለ እምነትና የሃይማኖት ነጻነት፣… ስለ መናገርና ስለ መጻፍ፣ …አስተሳሰብንም ስለ ማስራጨት ነጻነት፣… ስለ መሰብሰብና መደራጀት ስለ መምረጥና መመረጥ ነጻነት፣ ከጊዜው ጋር ይህ አዋጅ መቼም ሳያረጅ አብሮ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ እንዲሰጥ፣ እንዲታወቅ፣ እንዲከበርም ይጠይቃል።
አንቀጽ 23 ስለ ሥራ መብትና ስለ… ከሥራ አጥነት የመዳን መብት፣ ያነሳል ። 25 ደግሞ፣ ማንም ሰው ምግቡን ፣ ልብሱን፣ ቤቱን የሕክምና አገልግሎቱና …ጡረታውን ከመንግሥት የማግኘት መብት እንዳለው ያስታውሳል። አንቀጽ 27 የአእምሮ ሥራ በሕብረተሰቡ ውስጥ ከፈተኛ ቦታ እንዳለው ያነሳል።
በዚህም መንፈስ መግለጫው፣ በቁጥር አንድ፣ በመጀመሪያው አንቀጹ ላይ፣ ግሩምና ድንቅ የሆነ ቃል አናቱ ላይ አስፍሮ፣ የሚከተለውን ያስነብበናል።።
„…የሰው ልጆች ሁሉ“ ይላል መግለጫው „…በነጻነታቸው፣ በክብራቸውና በመብቶቻቸው አንዱ ከአንዱ ሳይበልጥ፣ እኩል ሁነው የተፈጠሩ ናቸው። በማሰብና በሒሊና ችሎታም (ከሌሎች ፍጡሮች ሁሉ እነሱ) ስለ ታደሉ እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ ሊተያዩ ይገባል።“ ይለናል። ከዚያም በአንዳዶቹ ዘንድ አሁን የሚፈራውን የሃማኖት „ግጭትም“፣ እንዳይነሳ መግለጫው፣ ከግምቱ ውስጥ አስገብቶ „ ሰዎች ሁሉ..እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ ሊተያዩ፣“ እላይ እንደሰፈርው „ ይገባል“ ብሎም ስለአንድነት ያነሳል።
D
እንግዲህ ይህን መግለጫ መሰረት አድርገው የምሥራቅ አውሮፓ ሕዝቦች ሳይታሰብ ብድግ ብለው የአንድ ፓርቲ ኮምኒስት አምባገነን ሥርዓቶችን፣ ገርስሰው፣ ጥለው፣ ነጻ-የዲሞክራቲክ ሕብረተሰብ እነሱ ዛሬ መሥርተዋል።
ወደ 1820 አካባቢ እየተስፋፋ የመጣው የዲሞክራቲክ ሥርዓትና የኑሮ ዘይቤ፣ ቀስ እያለ መቶ አመት በማይሞላ አጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሰላሳ በሚደርሱ አገርና መንግሥታት ውስጥ ተስፋፍቶ ሌሎቹን ሕዝቦች፣ ይህ ሥርዓት፣ ይማርካል።
ግን ደግሞ ሞሶሊን በጣሊያን፣ ፍራንኮ በስፔን፣ ሌንንእና ስታሊን በሩሲያ፣ ሒትለር በጀርመን ፣ ማኦ ደግሞ በቻይና… ተነስተው፣ ነጻና በዲሞክራቲክ ሥርዓት የሚተዳደሩ አገሮች ቁጥር ወደ ታች ዝቅ ብሎ፣ በአንዴ አሥራ ሁለት ይገባል።
እንደገናም ይህ ቁጥር ከፍ ይላል። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በሁዋላ በተፈጠረው አዲስ ሁኔታም በፓርላማ ሥርዓት የሚያምኑና የሰበአዊ መብቶችን የሚያከብሩ መንግሥታት ቁጥር በ1960 ዓ.ም አካባቢ (እ.አ.አ.) ከፍ ብሎ ሠላሣ ስድስት ይደርሳል።
ቀስ በቀስ በሦስተኛው ዙር ላይ የበርሊን ግንብ ፈርሶ ብዙ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ከትከሻቸው ላይ አምባገነኖቹን ተራ በተራ አራግፈው፣ በዚህ በያዘነው 21ኛው ክፍለ ዘመን የዲሞክራቲክ ሥርዓትን „የተቀበሉ“ አገሮች ቁጥር፣ እንደ ሩሲያ ያሉትን አካቶ፣ (ወደ ሁዋላ ላይ በዝርዝር እንሄድበታለን) በጠቅላላው አንድ መቶ ሃያ ይሆናል።
„ዲሞክራሲ“ የሚለው ቃልና ሥርዓት፣ ከየት እንደመጣ ፣ አዋቂዎች ቢከራከሩም፣ ለእኛ የአገራችንን ስምና የእኛን የኢትዮጵያኖችን መልካምና ጥሩ፣ ሸጋ፣… ማንም በዚያን ዘመን ላልደረሰበት ሥነ-ምግባራችንን፣ ከዚያም አልፎ እኛ ኢትዮጵያኖች ማን እንደሆን? ተዘዋውሮ ፣ አይቶ፣ ሰምቶም ለዓለም ጽፎ ለአስተዋወቀው፣ ለታሪኩ ጸሐፊ ለሔሮዶቱስ (484-425 B.C.) እንግዳ ለአልሆነው ሰው፣ ይህ ቃል „ዲሞክራሲና የዲሞክራሲ ሥርዓት“ ክላይስቴነስ የተባሉ ነገዶች፣ በአቴን ይህን የአኗኗር ዘይቤና ሥርዓት እንደአስተዋወቁ፣ እሱ ሔሮዶቱስ በመጽሐፉ ላይ ዘግቦአል።
በጥንታዊ ዘመን ከ508 እስከ 322 ድረስ ከክርስቶስ ልደት በፊት አብቦና ደርቶ ይህ ሥርዓት ብዙ ጭንቅላቶችን አፍርቶ ዓለምን እንደቀየረ ዛሬ መጽሐፍ ላይ እናነባለን።
ስለ ግሪኮች ጥበብ፣ ስለ ክርስቶስ ትምህርት፣ ስለ ሮማውያን ሕጎች፣ ስለ 18ተኛውና 19ነኛው ዘመን ፍልስፍና፣ ስለ ሰላምና ብርሃን ስለ ኢላይትመንት፣ ከመሸጋገራችን በፊት፣ በ1215 በእንግሊዝ አገር ስለ ታወጀው ማግና ካርታና ኮንስትትውሽናል ሞናሪኪም፣ አንድ ቀን እናነሳለን።
ከዚያ በፊት፣ ሔርደቱስ ስለ ኢትዮጵያ (ይህ ለወጣቱ ትውልድ ነው) በመጽሐፉ ላይ ያሰፈረውን ጠቅሰን „ ስለ ሊበርቲ“ የሚያትተውን ጽሑፍ፣ እዚህ ላይ እናሳድራለን።
„…በስተደቡብ ምዕራብ በኩል በጣም ራቅ ብሎ የሚገኝ፣ ሰዎች የሚኖሩበት አገር ኢትዮጵያ ነው። በዙህም አገር ውስጥ በጣም ትላልቅ የሆኑ ዝሆኖች አሉበት። ዞጲና ሁሉም ዓይነት ዛፎች በያለበት በቅለው ይገኛሉ። ሰዎቹም ከዓለም ሕዝብ ሁሉ ቁመታቸው የረዘመ ውበታቸው የበለጠና ዕድሜአቸውም ረጅም ነው።…“ ብሎ ሔሮዶቱስ ስለ እኛ ማንነት የዛሬ ሁለት ሺህ አራት መቶ አመት ጽፎአል።