የምን ነጻነት? ለምን፣ ለማን ወይስ… ?

ርዕሰ እንቀጽ

የምን ነጻነት? ለምን፣ ለማን ወይስ… ?

Cicerone/1*

ሁሉም ይናገር! የመናገር መብት ለሁሉም…

„ዝምታው ምንድነው? የፈለክኸውን የልብህን ተናገር እንጂ…“ ይላል አንደኛው ጥሪ። “…እባክህን እየደጋገምክ የልብህን ጻፍ እንጂ ወዳጄ…ፈረሃቻው ለምንድነው!“ ይላል ሌላው። „…ኑ እኔ ጋ ተሰብሰቡ! በሩም አዳራሹም ለእናንተ ለልጆቼ ክፍት ነው።“ ይላል ሦስተኛው። „…የልብህን ትርታ ተከትለህ፣ ሰምተህ ወይ ተቃወም! ወይም ደግሞ ደግፈን እንጂ“ ብሎ ይጣራል አራተኛው።

እንደዚህ ዓይነቱን ጥሪ ሕገ-መንግሥቱን መሰረት አደርገው በሕዝቡ መካከል እዚህ የሚያናፍሱት፣ ተቃዋሚ ፖቲከኞች ሳይሆኑ (ቢያደርጉ የሚከለክላቸው የለም) የጀርመን የግል የቴሌፎን ኩባኒያ ድርጅቶች፣ የፖስፓና እዚህ ባዶ እየሆነ የመጣው የጀርመን ቤተክርስቲያን ቄሶች ናቸው። ማስታወቂያውም „ ነጻነትን“ ፈልጎ አግኝቶአል።

አንድ የሰውነት ማጠናከሪያ የጅምናስቲክ ማሰልጠኛ ሰቱዲዮማ „…አትፍራ ቆርጠህ ተነስተህ ፣ ሐሳብህን፣ ፍላጎትህን ዛሬውኑ በሥራ ተርጉመው!… ጎበዝ አይደለህም እንዴ!…“ የሚለውን የለውጥ ጥሪ ፣ ከተማው ውስጥ በያለበት ለጥፎ፣ ወኔ ለመቀስቅስ ሙከራ –የተከተለው ሰው ምንያህል እንደሆነ ባይታወቅም– አድርጎአል።

አንዲት ልጅማ „ አሥራ ስምንተኛውን የልደት በዓሌን ብቻዬን ማክበር ስለማልፈልግ፣…አንተም፣ አንቺም፣ እሱም እሱዋም….ሁላችሁም ተጋብዛችሁዋል፣ ኑ! ብሉልኝ ጠጡልኝ…“ ብላ ትዊተሩዋን ልካ ወደ አምስት ሺህ ሰዎች ተጠራርተው መጥተው የመንደሩን ሰዎች፣… ፖሊሶቹንም ግራ አጋብተው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተጠይቀዋል። እንግዲህ ሐሳብን መግለጽ ወንጀል አይደለም።

„ሳላንዛዛው” ሐሳቤን ዛሬ በአንድ ግንዛቤ ሸብ ላድርገው።

ብዙ መንገዶችን በታሪካችን ፣ ሌሎቹ ሲወድቁና ሲነሱ፣ እኛ ኢትዮጵያኖች፣ ብቻችንን ተጉዘናል። አንድ ትልቅ ቁም ነገር ላይ ግን ሳንደርስ የጀመርነውን መልካም መንገድ እራሳችን ባልሆነ ትምህርትና ፍልስፍና ሳናውቅበት ቀጭተነው፣ ይኸው ዛሬ ተበታትነን፣ የአውሬ፣… የተኩላ፣… የጅቦች ራት ለመሆን በጨለማ ዓለም ውስጥ ፣ መውጫና መግብያው በማይታወቀው ጫካ ውስጥ፣ ሁላችንም ወድቀን ፣ ተዘርተን፣ እንገኛለን።

ለአገራችን ነጻነት፣…. የባዕድ ሰው ጥገኛ አሽከር፣ ….ባርነትን፣ጨርሶ የማንወድ ኢትዮጵያኖች፣ አገር አቋርጠው ሊይዙን የመጡትን ጠላቶች ሁሉ የፈለገውን ያህል መስዋዕትንተ ከፍለን ፣ የአገራችንን ፣ የባነዲራችንን ነጻነት ጠብቀን እስከ ዛሬ ድረስ (ይህ የእኛ ሳይሆን የአባቶቻችን ሥራ ነው ) ቆይተናል።

ግን የዚያኑ ያህል ፣ እኛ የዛሬው ትውልድ (አባቶቻችንን ብቻ መክሰስ እንወዳለን፣ እንጂ ) ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ „ከባርነት“ ወደ ሙሉ ነጻነት፣ ሰበአዊ ክብሩና መብቱ የማንም ሰው፣ ትልቅ ይሁን ትንሽ፣ በማንም ( ኮሚኒስት ይሁን ነጻ- አውጪ፣ ሽፍታ ይሁን፣ ተገንጣይ፣ ዲሞክራት ይሁን ሶሻሊስት፣ ወታደር ይሁን፣…ቄስ ወይም ኢማም….) እንዳይረገጥ፣ እንዳይደፈር፣ የፈለግነውን ፣ ማድረግና መተው፣….መጻፍና መናገር፣ መመራመርና መጠየቅ…መተቸትና መቃወም ፣ በሕግ ለተረጋገጠብት የፓርላማ ሥርዓት፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ፣ ብድግ ብለን ተነስተን አለመታገላችን፣ የሚያሳዝን ስለሆነ መጠቀስ ያለበት ፣ይቅርታ አድርጉልኝ ፣ጉዳይ ነው። ይህም ስለሆነ፣ ይህቺን ነገር አነሳለሁ።

የእያነዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሙሉ ነጻነት ጉዳይ፣ ደግሞ፣ በቀጠሮ ገና ሃምሳና መቶ አመት የሚሰጠው፣ የአራዳ ልጆች ጨዋታ አይደለም። ይህ መብት፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነው። ከፍጡሮች ሁሉ ፣ ከእንስሶችና ከአራዊቶች ሁሉ፣ ለእኛ በአምሳሉ የሰጠን መብት፣ በምላሳችንን እነድንናገርበት፣ በአእምሮአችን እንድናስብበት፣ በእጃችንን እንድንጽፍበት ነው።…. መናገር መጻፍ፣ ማመዛዘን፣ ክፉን ደጉን ለይቶ፣ መመልከት፣ ዱሮም የነበረ፣ አሁንም ያለ መብት ነው።“

አሁን እንግዲህ ጊዜው፣ ይህን ሐቅ በእርግጥም የምናይበት ጊዜ፣ የደረሰ ይመስላል። እዚያ ላይ የሚደረሰው ግን በአሁኑ ሰዓት ፣ በዚህ በያዝነው በ21ኛው ክፍለ-ዘመን አንዱ „ሰለመገነጠል“ ሲያወራ፤ ሌላው „ለኢትዮጵያ አንድነት“ ሲጮህ አይደለም።

ወይም አንዱ ሥልጣን ላይ የወጣው ኢህአዴግ፣ ስለ „አምባገነን ሥርዓት“ መኖርና መጠናከር በኢትዮጵያ ሲከራከር፣ ሌላው „ለዲሞክራቲክ መብቶች መከበር“ ሲታገሉም ብቻ አይደለም።

ሁለቱ እላይ የተጠቀሱት ኢትዮጵያን ለማተረማመስ በአገሪቱ ላይ የተወረወሩት ፍልስፍናዎች፣ ማለት „የመገንጠልና የአምባገነን ሥርዓት አስተሳሰብ“ ይኸው እንደምናየው ሌሎቹ አገሮችና መንግሥታት ፣ ከሁዋላችን ተነስተው እኛን በሥልጣኔ እርምጃቸው፣ ወደ ኋላ ጥለውን እንዲሄዱ አድርገዋል።

በአለፉት አርባና ሃምሳ አመታት በእነዚህ „ትምህርቶች ተሳክረን“ ምንስ ያመጣነው አዲስ ነገር አለ? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ።… ምንስ ለአገሪቱና ለሕዝቡ የሚጠቅም አዲስ ነገር ፈጠርን? በዓይን የሚታይ አዲስ ዕውቀትና ጥበብ፣ ልዩ የሆነ ፣ የዓለም ሕዝብ ከእኛ ሊማር የሚችል ነገር ለዓለም ሥልጣኔ፣ ለመሆኑ በአለፉት አመታት አበረከትን ወይ?… አቀረብን እንዴ? ….እስቲ ምን?

ዞር ብለን ከተመለከትን ትርፉ፣….ሞት፣…ስደት፣ ለቅሶ፣…እሥራትና ግርፋት፣ በሽታና ረሃብ፣ ሁዋላ ቀርነትና ድንቁርና እና ጦርነትን ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ ዱሮ ማንም ያልደፈረውን መሬታችንን በኢንቨስትሜንት ስም ፣ ቤልጅግና ማዮርካን የሚያካክሉ አገሮች፣ ለሃምሳ፣ ስድሳና ዘጠና አመታት ለባዕድ መንግሥታትና ቱጃሮች፣ በሊዝ ስም „ ይሸጣሉ“። ነገ ከሃምሳ አመት በሁዋላ ምን እንደሚመጣ እናውቃለን?

ጓዙን ፣…ኮተቱን፣ ቅራቅንቦውን፣ ዘመዱንና ጠባቂ ወታደሩን ከባህር ማዶ አምጥቶ፣ ከፍዬበታለሁ ብሎ ቢሰፍርበት ማን ያግደዋል? ደግሞም ይህን ማድረግ ይችላል። ከታሪክ እንደምናውቀው ቀላል ነው።

አሰብ የተያዘችው፣ በሁዋላም ይህች የኢትዮጵያ አካል „ኤርትራ“ ሚባለውን አዲስ ስም ይዛ ጣሊያኖች እጅ የገባችው፣ ጅቡቲ…. ኬንያና ኮንጎ፣ ደቡብ አፍሪካና ሮዴይዢያ፣ ጋናና ናይጄሪያ፣…ሱማሊያ፣ ታንዛኒያ….የትም ቦታ ወረድ ብላችሁ፣ ተዘዋዉራችሁ ተመልከቱ፣ እነዚህ ሁሉ አገሮች በአውሮፓ ተይዘው በሁዋላ ባሪያና የቅኝ ግዛት የሆኑት፣ በቀላል ዘዴ ነው።

በመጀመሪያ አንድ ሰው መጥቶ ባንዲራውን ይሰቅላል። በሁዋላ ጓደኛው መጥቶ ድንኳኑን ይተክላል። ከዚያስ? ወታደር መጥቶ ይሰፍርበታል። አሰብ ጥሩ ምሳሌ ናት። የሆነውም ልክ እነደዚሁ ነው። እንደምናውቀው በዘርና በጎሣ አውሮፓውያኖቹ፣ አፍሪካን ከፋፍለው፣ ጠበንጃና ጦር አቅርበው፣ እርስ በራስ፣ አዋግተውና አፋጅተው፣ በሁዋላ አስታራቂ ሁነው አካባቢውን፣ ድፍን አፍሪካን መቆጣጠር ችለዋል። ተቆጣጥረዋል። ሰውንም ቀስ ብለው ባሪያ አድርገው ሸጠዋል።… ተግባባን?

እሩቅ አይደለም ፣ በቅርቡ የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሚስተር ሔንሪ ኪስንገር እንደጻፉት፣….አንዴ ኒክሰንና ማኦ ሴቱንግ „የሰበአዊ መብትን፣ መከበር ጉዳይ አንስተው ሁለቱ መሪዎች ይከራከራሉ።… ኒክሰን፣ በትክክል፣ አንድ የቻይና ተወላጅ አገሩን ለቆ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ መሥራት፣ መጎብኘት አይችልም።…ይህ አሰራራችሁ መቀየር አለበት፣… የሰው ልጅ አገሩንም ለቆ በነጻ መንቀሳቀስ አለበት፣ ይህ መብቱ እኮ….ነው፣ ሲሉ ማኦ ሴቱንግ ጨዋታውን አቋርጠው“ ኪስንገር ታሪኩን እንደ ተረኩልን “….ለመሆኑ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት… በአሁኑ ሰዓት ስንት ሰው? …ስንት የቻይና ተወላጅ ፣ አሜሪካን መሬት ላይ ተቀብሎ እነሱን ለማስተናገድ ተዘጋጅቶአል? ….ስንት ሰው አዘጋጅቼ ልላክሎት፣ …20 ሚሊዮን ቻይናዊ ፣ 50 ወይስ 70 ፣ ወይስ… 90 ሚሊዮን ? እርሶ ነገ ኒዎርክ ላይ ፣ እነዚህን ሁሉ ሰዎች በትልቅ ክብር ሊቀበሉ ይችላሉ?…“ ብለው፣ „ታላቁ ሊቀመንበር“ ማኦ፣ ኪስንገር፣ አስደነገጡን ይላሉ።

ሕንድና ቻይና ፣ ነገ በቀላሉ …ወደ ኢትዮጵያና ወደ አፍሪካ ፣ መቶና ሁለት መቶ፣ ሦስትና አራት ሚሊዮን ሰው ብድግ አድረገው፣ አንጠልጥለው መላክ ይችላሉ። ለእነሱ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ አገሮች፣ ሁለት መቶ ሚሊዮን ቻይናዊ አገሩን ለቆ ቢሄድ ደስታውንም አይችሉም። ባጀቱም ለዚህ ተመድቦአል። ይህ፣ በሌለ ነገር „…አማራው ወረረን“ ስለዚህ „ የመገንጠል መብት- ነጻነት“ በሚሉ ሰዎች ዘንድ፣ ከግምት ውስጥ ለመሆኑ ገብቶ፣ በደንብ ታስቦበታል? እንግሊዝ ዓለምን ያኔ የያዘቺው በዚሁ መንገድ ነበር።

ዞረን ዞረን እኛ ኢትዮጵያኖች ዛሬ “ ማሰብና፣… የማሰብ ነጻነት“ያስፈልጋል የሚል ደረጃ ላይ ደረሰናል። ግን ለመሆኑ ….ነጻነት፣ ….ሊበርቲ፣… ሰበአዊ መብቶች፣ የሚባሉ ነገሮች፣….ምንድንናቸው? ምንድነው? ያስፈልጉናል እንዴ አሁን? „ለጥቁር ሕዝብ ለአፍሪካ፣ ለደሃዋ ለኢትዮጵያ ደግሞ፣ ሊበርቲ ምን ያደርግላታል?“ „ዲሞክራሲ እኮ የሠለጠኑ ሕዝቦች የነጮች ጨዋታ ነው።“ ይህን የሚሉ አሉ።

„…አንድ ሰው ፣ አንድ ቡድን ያንን አካባቢ ጸጥ ለጥ አድርጎ፣ (አንድ ድርጅት) በጠበንጃ ያን ሕዝብ ለ20፣ለ30፣..40 አመትና አመታት በተከታታይ ቢገዛቸው፣ ምን ይሆናሉ“? „እንደ ቻይና፣ እንደ ሰሜን ኮሪያ አንድ ቀን ለኢትዮጵያም ዕድገት ያመጣላቸዋል።“

„ንጉሱም ይህን ያህል አመት ገዝተዋል። …ለምን „ትግሬዎቹ“ ገዙ ብለን አሁን እንቃወማለን“? …ይህማ ምቀኝነት ነው!.. ለሌቹም ተራው ያልደረሳቸው፣ ኦሮሞዎቹ፣ ጉራጌዎቹ፣ ሱማሌዎቹም፣… እነሱም ተራውን ጠብቀው ሥልጣኑን ተቀብለው 20፣30…40 አመት፣ ያቺን አገር መግዛት አለባቸው።“ የሚሉ ቅዠቶችን ከብዙ አቅጣጫና አካባቢዎች እንሰማለን። ግሩም አስተሳሰብ ነው።

ግን ማን ነው በኢትዮጵያ ሕዝብና በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ መወሰን የሚችለው? ሕዝባዊ ወያኔ? ወይስ ኢህአዴግ? ጥቂት የፖሊት ቢሮ አባሎች? „ነጻ-አውጪ“ ነን ባዮች? እዚያና እዚህ ብቅ ያሉ ድርጅቶች? የአውሮፓ ማህበር? የእንግለዚና የአሜሪካ መንግሥታት? ቻይና እና ሕንድ? ወይስ የኢትዮጵያ ሕዝብ? ሕዝቡስ እንዴት ድምጹን ያሰማ?

ለመሆኑ „ነጻነት“ ምንድነው? ….የእኔ ነጻነት፣ የአንተ፣ የእሱዋ፣ የእሱ? የጎረቤት ነጻነትና ነጻነታችን ምን ያህል ነው?

ማነው ዛሬ መናገር የተፈቀደለት? ማነው የተከለከለው? ከልካዩስ ማነው? መከልከሉንስ ለእሱና ለእሱዋ ማን ፈቀደላቸው?

እንደ ጠበልና እንደ መስቀል በዚህች ዓለም ላይ የሚገኙ አምባገነኖች የሚፈሩት አንድ ነገር ቢኖር፣ ሌላ ነገር ሳይሆን ( ጦርነትማ እንጀራቸው ነው! ጦር አይፈሩም!) ያቺን ፣ … የሕዝብን ነጻ -ንግግር ፣ ነጻ – ሐሳብን፣ ነጻ- ውይይትንን፣…. ነጻ-ጽሑፍንና፣… የሚጠይቅ፣ የሚጠራጠር፤…የሚተች ነጻ- አእምሮን ፣ (… ዕውነት፣ ዕውነት ፣ እላችሁዋለሁ) ፣ እሱዋን ብቻ ነው። ሥልጣኔ የተመሰረተው ደግሞ በዓለም ላይ በነጻ-አስተሳሰብ፣ በነጻ- ምርምር፣ በነጻ- ትምህርትና….በነጻነት፣… በአርነት፣ (በሌላ ቋንቋ) በሊበርቲ፣ አለጥርጥር፣ በትክክል ለመናገር ፣ በአእምሮ ነጻነት ላይ ነው።

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s