ክፍል ሁለት
ፖለቲካ ምንድነው?
/1*
ፖለቲካ ምንድነው?…ለምንድነው የፖለቲካ ሰዎች ሥልጣን ላይ አንዴ ከወጡ በገዛ ፈቃዳቸው የማይለቁት?….ሥልጣን ምንድነው?
ሀ
በሙያ ከሆነ እንደ ገበሬ አዋቂ ሰው የለም። ዘንድሮ ምን መዝራት እንዳለበት ያውቃል።መሬቱ ምን እነደሚሰጠው በደንብ ያውቃል። እሩቅ ሳንሄድ የጉዋሮው አትክልቱ፣ ጥሩ ሥዕል ስለእሱ ይሰጠናል።…. ከተሳሳተ፣ …ዞሮበት የተሳሳተ ውሳኔ ላይ ደርሶ ያልሆነ ነገር፣ይህ ሰው ከሰራ፣… እሱና ሚስቱ፣ ልጆቹና ዘመዶቹ ፣ ከብቱና ቤቱ የሚጠብቀው ውሻው ጭምር፣ ከድቶት፣ሁሉም እንደሚበተኑበት፣ እነደሚሞቱበት በደንብ ያውቃል።
ከገባበት ችግር እንደምንም ቢያመልጥም፣በጎረቤቶቹ ዘንድ መሳቂያ መሳለቂያ ፣ ለዘመናት እንደሚሆነም፣ ይህ ወጣት ገበሬም ፣ በደንብ ያውቃል። ስለዚህ ነው ፣ስንት ኃላፊነት ስለአለበት፣ የአባቱም የአያቱም ምክርና ተመክሮም ከልጅነቱ ጀምሮ፣ እሱን ስለገነባው፣ የት ቦታ፣… በምን ወራት፣ ምን ዓይነት አዝመራ፣ ዘንድሮ እንደሚዘራ፣ እሱ ተጠንቅቆ እጁን ይዘረጋል። አለበለዚያ ጉድ ይፈላል።
አንድ ፖለቲከኛ ግን –ያውም የእኛ አገር ፖለቲከኛ- ከገበሬው ጋር ሲተያይና ሲነጻጸር ፍጹም ሌላ ነው። ረጋ ብሎ አያስብም። ቀዥቀዥ ያደርገዋል። ቀዥቃዣም ነው። ወፈፍ ያደርገዋል። ሳያመዛዝን ትክክለኛ ነው ብሎ የጨበጠውን በየአለበት ይዘራዋል። ያ ነገርም አንድ ቀን እራሱን ጭምር ያዋክባል ወይ ብሎም አይጠይቅም። ደግሞ ሲያዋክበው አይደነግጥም። ግን ያዋክበዋል። አርፎ ስለማይቀመጥም ብድግ ብሎ ያልሆነ ነገር ከመሬት ተነስቶ፣… አፈሩ ይቀበለዋል ፣… አገሩ ያዳምጠዋል …አየሩ ይስማማዋል ወይ ብሎ …ሳይጠይቅ ና ሳይጨነቅ፣ በሁሉም አቅጣጫ ያገኘውን ዘር ከንፋሱ ጋር አብሮ እንደገና ይዘራዋል።
በተለይ „ የጥላቻ ዘሩን በጭፍን ዓይኑ“ ይኸው „ቀዥቃዣ፣ የሆነ ፖለቲከኛ“ በአራቱም ማዕዘን ይለቀዋል። በመጨረሻም እሱንም ሌላውንም ይህ ሥራው ዓይኑን ስለሚያሳውር ገደል ይዞት ይገባል። በመጀመሪያ አጃቢዎቹና ደጋፊዎቹ ይሸሹታል። በሁዋላ ጓደኞቹ። በመጨረሻ እሱ ብቻውን ይቀራል።ያኔ ደግሞ ጊዜውም፣ ሰዓቱም፣ ትውልዱም ተቀይሮ አውላላ ሜዳ ላይ „ ቅራኔው አንድ ቀን ከሮ ወደኔ ይመጣሉ ብሎ „ እራሱን ያታልላል።
ግን ስለ የትኛው የፖለቲካ ሰው ነው፣ አሁን የምናወራው?
ስለ „የመሸታ ቤቱ ፖለቲከኛ?“ ….ስለቀማኛው የጫካ ሽፍታ?..በአውሮፓና በአሜሪካ፣…በእሲያና በላቲን አገር ስለተነሱት የደፈጣና የከተማ ሽብር ፈጣሪዎች? ስለኮሚኒስቶቹ? ወይስ ስለ አናርኪስቶቹ? ስለ ሶሻል ዲሞክራቶቹ፣ ወይስ ስለ ሊበራሎቹ?
ወይስ ስለ ትግሬ?… ስለ ኦሮሞ?…አማራ፣ ስለ ኤርትራ ፣ ኦጋዴን…አፋርና …ስለ ….ነጻ-አውጪዎቹ ፖለቲከኛ?… ለመሆኑ ስለማንኛው ፖለቲከኛ ክፍል ነው የምናወራው?
ለ
የተለያዩ ድርጅቶች ታሪክ ውስጥ ገብተን ፣ ልዩነቶቻቸውን አንድ በአንድ ዘርዝረን፣ ከመዳረቃችን በፊት፣ እንዳው፣ በቀላሉ ለመግባባት አንድ ነገር እናንሳና እሱን እንመልከት። እሱም ገበሬው የሚዘራውን ያውቃል፣ በተቃራኒው ቀዥቃዣው ፖለቲከኛው ግን የጥላቻ ዘሩን በሁሉም አቅጣጫ ከንፋሱ ጋር አብሮ ይዘራል ብለናል።
ግልጽ እንዲሆንልን በኢትዮጵያ ላይ ከአንዴም ሁለቴ የወረደውን ትራጀዲ፣ያ! ትምህርት ሰጪ፣ ጥሩ ምሳሌ ስለሆነም እሱን እንመርምር ።
እህአዴግና ሻቢያን፣ እነሱን እናስቀድማቸው። ኦነግን አሁን ለጊዜ እንተወው። መኢሶንና አህአፓን ደርግንም ልንወስድ እነችላለን። ግን እላይ በተጠቀሱት በሁለቱ ላይ እንቆይ። እነሱ ናቸው አሸናፊ ሁነው የወጡት።
ወጣ ወረደ ሁሉም በቂ ትምህርት ይሰጣሉ።
ብቻ! ይህኛው፣ እነሱ ለዘመናት ያራመዱት ፖለቲካ „ፖለቲካ „ ከአልነው፣ „…ስለ ስታሊን የመገንጠል ፖለቲካ“ ስለሆነ ፣ ደህና ትምህርት፣ ለሁላችንም ይሰጠናል። ….ሻቢያ በሚከተለው ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ከአልተገነጠልኩ ይላል። አለ። ለብዙ አመትም „ታገለ“። ሕዝባዊ ወያኔ ተገንጠሉ ብሎ ደብዳቤ ለተባበሩት መንገሥታት ድርጅት፣በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ወደ ኒዎርክ ጻፈ። እነሱም፣እያወቁ ተቀበሉት። እንደ ልጆች ጨዋታ፣ ሁለቱን አካባቢ፣ሁለቱም፣ ድርጅቶች፣ እነደተመኙት ተከፋፍለው ይዘው „ተገነጣጠሉ“። ድግስ ተደገሰ፣ ተጨፈረ…ተበላ፣ ተጠጣ።
እስከዚህ ድረስ ፣እንግዲህ ምንም „ችግር“ በዚያ አካባቢ አልታየም። ግን ከዚህ በሁዋላ ትንሽ ቆይቶ የሆነው ነገር፣ ደጋፊዎቹም ተቃዋሚዎቹም፣ ሌሎቹም ይደርስብናል ብለው ያልገመቱት ጉዳይ ሆነ።
በባድሜ ድንበር፣ በናፍቃ ብር፣… በቡና እና በቅቤ ንግድ፣በእንጨት፣ በጤፍና በስንዴ …ሁለቱ ድርጅቶች ሲጣሉ( ምንም የሚያጣላቸው ምንም ምክንያት የላቸውም፣ ባድሜም ኤርትራም የኢትዮጵያም የአፍሪካም ግዛት ነው) የአዲስ አበባው ገዢ በያለበት ተሰማርተው ትዳር መስርተው ፣ ተቀላቅለውና ተጋብተው ለብዙ መቶ አመታት የሚኖሩትን በሺህና በመቶሺህ የሚቆጠሩ „ኤርትራውያኖች“„ ለቃቅሞና ስብስቦ ወደ ኤርትራ ሲልካቸው፣ የአሥመረው ገዢ በተራው ተመሳሳይ እርምጃ፣ቀደም ሲል እነደ ጀመረው ቀጥሎበት፣ እሱም በተራው ትግሬዎችንም ጭምር ለቃቅሞ ከኤርትራ አባረረ።
የደቡቡ ሕዝቡም „እኛ ትግሬና ኤርትራ መለየት ስለማንችል እንተው ለዩአቸው ብሎም …“ የገዛ ጎረቤቱን ወደ አዲስ አበባ ላከ። ነገሩ በጊዜው ሰውን ሁሉ፣ ይህ የሚያሳዝን ሥራ፣ „አስቆአል“ ። ሌላው የኢትዮጵያ ጠላት „ ሰዎቹ አብደው ይኸው ተበታተኑ“ ብሎ ደስ ብሎታል። ይህ አሁን የጤነኛ „ፖለቲከኛ ሥራ ነው?“
ሐ
ማክስ ቬበር ( ለዚህ ነው ይህን ሁሉ ታሪክ መልሼ ያነሳሁት) ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት ለሚፈልጉ የዩኒቨርሲት ተማሪዎች ያኔ በአደረገው ንግግሩ፣ሦስት ነገሮችን ሁልጊዜ ሳይረሱ እንዲመለከቱት፣ እንዲያገናዝቡት፣ እነሱን አደራ ብሎ ለቆአቸዋል። ይህን አደራ „ከእንግዲህ ከኢትዮጵያ እንገንጠል፣ከአልተገነጠልን፣ ሞተን እንገኛለን“ የሚሉት ኃይሎች ይህ ነገር -ለዚህ ነው የማነሳው- ዞር ብለው ማየት አለባቸው። በተለይ ስንቱ „ኦሮሞ“ ስንቱ „ኦጋዴን“ ስንቱ „ትግሬ“… ከሌላው ዜጋው ጋር እንደተጋባ አለማየቱ፣ የላይኛውን ዓይነት ስህተት እንደገና መድገም ይሆናል። … እሱስ ነገ ምን ይሆናል?… የት ይደርሳል? ስንት ትዳርስ፣ ስንት ቤተሰብስ፣ይበተናል?… ይፈርሳል። ይህን የማያይ ፖለቲከኛ፣ ጤነኛ ሳይሆን፣ „ቀዠቃዣ ዕብድ“ ነው።
„ፖለቲካ እንደ ሙያ“ በሚለው ንግግሩ ላይ ቬበር እንዳስቀመጠውና ፣እሱ እንደጻፈው አንደኛ፣ ዝም ብሎ አንድን ነገር ሳያመዛዝኑ ይዞና ጨብጦ „ከመጋለብ“፣ አንደኛ:- አንድ ፖለቲከኛ „ሚዛናዊ የሆነ ፍርድን መውሰድ ይገባዋል ይለናል“። ምንድነው ሚዛናዊ ፍርድ?
ሁለተኛው፣ „ፖለቲካ „ በሙሉ ልብና በቀና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ (እሱ ፓሺን በእንግሊዘኛ ይለዋል) አካሄዱ መመስረት አለበት ብሎ ያስተምራል።
በመጨረሻ ደግሞ ሦስተኛው፣ ለሰሩት ሥራ ሁሉ በሕዝብ ፊትም ሆነ በታሪክ ወይም በፈጣሪም ዘንድ ኃላፊነቱን ተቀብሎ መቆም፣ እንዳለም መረሳት የለበትም፣ ይላል። ይህም ማለት ልጆችም፣ ዘመዶችም፣ አባቶታቸው፣ ወንድሞቻቸው በሰሩት ሥራ ወደፊት ማፈር የለባቸውም ማለት ነው ።
ከዚያ እንግዲህ ምሁሩ በቀጥታ ወደ ኤቲክና ወደ ሞራል፣ ወደ መልካም ሥነ ምግባርም በሰው ልጆች መካካል ወደ ማስተማር ይሸጋገራል።
ግን አዚህ ላይ የገዛ የአገሩን ልጅ…“ በለው፣ እረገጠው፣ ደምስሰው፣ እናሸንፋልን፣ እናቸንፋልን፣ አብዮቱ እስከ መጨረሻው የደም ጠብታ፣… ከርሰ- መቃብራቸው ላይ እንቆማለን….“ እያለ እዚህ ለደረሰው ትውልድ ፣ ስለ ኤቲክ እና ስለሞራል፣ ስለ መልካም አስዳደርና ስለ የአገር ፍቅር… አሁን ብናወራለት ከንቱ መሆኑን እናውቃለን።
በሁዋላ ላይ ተመልሶ ለመምጣት ለጊዜው ይህን ጉዳይ አሁን እንዝለለውና ወደ ማክስ ቬበር ጥያቄዎች፣ ይህም የእኛም ጥያቄዎች ስለሆኑ ፣ ወደ እነሱ አሁን ጎራ እንላለን።
ለምንድነው ሰው ሁሉ በአገራችን ፣ ከአልጠፋ ነገር ፖለቲከኛ የሆነው? „… ሰው ሁሉ፣ ማለት ባንችልም „አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቢያንስ አንድ ደርጅት ውስጥ የገባው?…ወይም ደግሞ አብዛኛው ከቢጤዎቹ ጋር ሁኖ የራሱን ድርጅት መሥርቶ ሰውን ሁሉ በሆነውና ባልሆነው „ትምህርቱ፣ በሚከተለው አላማው የሚያዋክበው“?
ለምንድነው በኢትዮጵያ ውስጥ የተመሰረቱት አብዛኛዎቹ ድርጅቶች „በብሔር – ብሔረሰብ ፣በጎሳና በዘር ላይ ብቻ ተምርኩዘው፣ የተመሰረቱት“? ለምንድነው ሌላው ዓለም በዘር ላይ ሳይሆን „በፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ“ ፓሪቲውን አቋቁሞ ለሽንጎ ምርጫ በሰላም ሕዝብ እንዲመርጠው፣ ብቅ ብሎ የሚወዳደረው?
መ
ሥልጣንና ኃይልን፣ ( ስለ ፖለቲካ ነው የምናወራው)… መንግሥትንና አስተዳደርን፣ የፖለቲካ ድርጅትንና ተከታይ አባሎችን፣ የበላይ አለቃና የበታች ታዛዠን፣ ሕግና ሥርዓትን፣ ገዢው መደብና ተገዢውን ሕዝብ፤ የተለያዩ ተቋሞችንንና የሥልጣን አከፋፈልንና አወራረድ ፣ በዚያች አገር፣ የፖሊስና የጦር ሠራዊትን፣..የባለሥልጣኖች በሥልጣን መባለግና፣ አንድን ሕዝብ አንድ ቡድን በጠበንጃ የቁም ምርኮኛ አድርጎ ፣ እንደ የግል ቤቱ መዝረፍ….ወዘተ፣ ወዘተ… እነዙህን ሁሉ ቀስ በቀስ ወደ ግራና ወደ ቀኝ እየመተርን፣ ማክስ ቬበርን መሰረት አድርገን ፣እነሱን እንመለከታቸዋለን።
እዚሁ ውስጥ …የነጻ- ምርጫና የነጻ -ጋዜጣ ሚናንም እንመለከታልን ። የነጻ- ፍርድቤትና የተለያዩ የሙያ ድርጅቶች ቦታም በሕብረተሰቡ ውስጥ እንመረምራለን። የተለያዩ ሃይማኖት አባቶችና፣ የአገር ሸማግሌችም ሚናም እንዴት ነው ብለን እንጠይቃለን። …ጸሐፊና ደራሲዎችን ፣ የኪነትና የጥበብ ሰዎችን የእነሱንም ሚና ወደፊት እናነሳለን።
„ፖለቲካ እንደ ሙያ… አገዛዝና …አስተዳደር „ በሚለው ጽሑፉ ቬበር እላይ የተነሱትን ነጥቦች በሥነስርዓቱ ለመረዳትና ለመመለስ፣ ሦስት ቁም ነገር ያላቸው ጥያቄዎችን አንስቶአል። እነሱም:-
ሀ) እንድ የገዢ መደብ አገሪቱን ለማስተዳደርና ሕዝቡን ለመግዛት፣ በእጁ ላይ የሚገኙት፣ እሱ የጨበጠው የማስተዳደሪያ መሣሪያዎቹ ምንድናቸው? ብሎ ይጠይቃል።
ለ) ተገዢዎቹን ወይም ሕዝቡን ፣የገዢዎቹን ትዕዛዝና ደንብ እሽ ጌታዬ ብሎ ተቀብሎ ለመገዛት የሚገፋፋው ነገር ምንድነው? ይላል።
ሐ) በየጊዜው ብቅ ብለው የሚፈነዱትን ችግሮች፣ ለመፍታትና ለመቆጣጠር፣ መልክም ለማስያዝ ፣ መንግሥት ምን ዓይነት ተቋሞችን መሥርቶ ነው፣ ሕዝቡን የሚያስተዳድረው? የሚለውንም ጥያቄውንም አብሮ ይሰነዝራል።
ይህን የእሱን ጥያቄ ተራ በተራ -ከብዙ በጥቂቱም ያለፈው ጊዜ መልሰናል። ወደፊትም በበቂም ጊዜ ወስደን እንመልሳለን። ግን ደግሞ እሱ ከቁም ነገር ሳይቆጥራቸው ጥሎአቸው ያለፈውን ሁለት ጥያቄዎች አብረን ማንሳት ኢዚህ ላይ እንፈልጋለን።
ሠ
እነሱም:-
ሀ) አርፎ እንደሌሎቹ ተቀምጦ መኖር ሲቻል ፣ ገዢዉን ቡድን ፣ ወይም አንድ ሰው፣ ያንን አገርና ያንን ሕዝብ ለመግዛት ፣ለመምራት የሚገፋፉት፣ የገፋፉት ነገሮች ምንድናቸው? መግዛት አለብህ ብሎ ያንን ሰው „የሚያሳብደው ነገር“ ለመሆኑ ምንድነው?
ለ) ተገዢው ሕዝብስ ደግሞ መአቱ ሲበዛበት፣ በደሉ ሲጠነክርበት፣ አይ አሁንስ አበዛችሁት ፣ በቃችሁ ብሎ፣እነሱን የሚገስጽበት መድረክ፣ አቤት የሚልበት ሜዳ፣ ከዚያም አልፎ ወይዱ ከዚህ ብሎ የሚያምጽበት „መሣሪያ“ – ጠበንጃ ሳይሆን – ብልሃትና ዘዴ በእጁ ላይ፣ ለመሆኑ ያ! ሕዝብ አለው ወይ?
እንግዲህ እነዚህ፣ ሁለቱ ተጨማሪ ጥያቄዎች ፣ በቀጥታ ዞረው ዞረው የሚወስዱን ሔልሙት ሼልስኪ የሚባለው የጀርመኑ ጸሐፊ እንደአለው ፣ ወደ አስተዳደር ውሰጥ ተሣትፎ ወይም ወደ ተቃውሞ ትግል፣ ወይም ደግሞ ወደ አብዮታዊ ለወጥ ወደ አመጽ፣ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በቀጥታ ይወስዱናል።
ከሁሉም ለአንዱ ጥያቄ ብቻ — እሱ ነው እኛን፣ እስከ አሁን ድረስ ተብትቦ የያዘን– መልስ ለመስጠት ሙከራ እናድርጋለን።
ለምንድነው „እኔ ብቻዬን“ አገሪቱንም፣ ሕዝቡንም እስከ ዕድሜ ልክ ድረስ ከአልገዛሁ ብሎ የፖለቲከውን መደብ ሁሉ፣ በጅምላ በአገሪቱ ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሳበደው፣ያሳበዳቸው ነገር?… ይህ በሽታ ነው ወይስ ጤነኛ አመለካከት?
ይህ ፣ዕውነቱን ለመናገር፣ የኢትዮጵያኖች ብቻ በሽታ አይደለም። የሁሉም ፖለቲከኛ በሽታ ነው። ታዲያ ለምንድነው ሌሎቹ በሰላማዊ ትግል በፓርላማ ምርጫ፣ በጊዜ ገደብ ተገደው መድረኩ ላይ ለመውጣት የቻሉት? ለምንድነው እነሱ „የጨዋታውን ሕግ የሚያከብሩት? ለምንድነው የእኛዎቹ አንዴ እንደምንም ብለው ያውም አወናብደው ሥልጣኑን ከነከሱ፣ አንለቅም ብለው መከራቸውን የሚያዩት? ….እኛንም የሚያሳዩት?
(ካንትና ፣ሖብስ፣ ጆን ሎክና ቦዲን፣…ሌሎቹም…በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በበቂ ጽፈዋል።)
ረ
የሰው ልጆች በተፈጥሮአቸው፣ ሙሉ ነጻነትን ይፈልጋሉ። እንዲያውም ይህን ነጻነቱን ያገኘ ወይም ያወጀ ሰው– ይህ በጣም የሚገርም ነው– የእራሱን ነጻነት እጁ ከአስገባ በሁዋላ „የፈለኩትን ነገር ለማድረግ አሁን ሙሉ ነጻነትአለኝ ብሎ“ የሌላውን ነጻነት ወደ መግፈፍ ይሸጋገራል። በጉልበትም ተጋፍቶ የሌላውን መብት ይነጥቃል። እንግዲህ ኢማኑኤል ካንት ይህን አይቶ፣ „መልካም አመለካከት“ በሚለው የፖለቲካ ፍልስፍናው „ ከፍርደ ገምድሎችንና ከአረመኔዎች መንጋጋና መድፍ ለመትረፍ“ የሕግ በላይነት፣ በአንድ ሕብረተስብ ውስጥ ያስፈልጋል ብሎ፣ ይህን ዕውቀቱን ለተማሪዎቹ እሱ በተራው አሰተምሮአል። እሱ ብቻ አይደለም።
በተለይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሥነ- ጽሑፍ፣ በድርሰትና በቲያትር ዓለም ፣ብዙ ነገሮችን መለስ ብለን ከተመለከትን እዚያ ውስጥ በርካታ ትምህርቶችን እናገኛለን። ሁሉም ሰው ፣ እኔም ፣ እራሴም ብሆን „ቁጥጥር ከአልተደረገብኝ፣ የሚቆጣጠር ኃይል በአጠገቤ ከሌለ“፣ ነገ ብድግ ብዬ ባንኩንም ባልዘርፍ አዝበታለሁ፣ የፈለኩትን እሾማለሁ እሽራለሁ፣ ዙፋኑም ላይ እድሜ ልኬን ብቀመጥበት ደስ ይለኛል። ከዚያም አልፎ ሚስቴም ልጆቼም፣ ዘመዶቼም፣ ጓደኞቼም እንደኔው ቢደሰቱ፣ በአገሪቱ ላይ ቢጨፍሩ ደስ ይለኛል። ይህ እነዳይሆን ካንት ከሁሉም በላይ የሆነ ሕግ ያስፈልጋል ይላል። እሱ ብቻ አይደለም። ሌሎች ነገሮችም ለአንድ ሕብረተሰብ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችም አሉ።
ብቻ! ለጊዜው መንግሥት ፣… መንግሥት ነው ብለን የምንቀበለው፣ አንድ መንግሥት ቢያንስ ቢያንስ ሦስት ነገሮችን ሟሙዋላት አለበት። ለዚህ ነው ሕዝብ ፊት ቀርበው ሥልጣኑን ፖለቲከኞች ሲቀበሉ በመሓላ ቃላቸው፣ „በአገሬና በሕዝቤ ላይ የሚመጣውን አደጋ…“ ለመከላከል፣ ቃል ኪዳን እገባለሁ“ ብለው የሚምሉት። ቃሉን ባያሟላስ? ይጠየቅበታል።
አንደኛው ፣ የመንግሥት አላማ፣ ወደ ፖለቲካ ፍልስፍና እንመለስ:- ለአገሪቱና ለሕዝቡ ፣ ትርምስን አጥፍቶ፣ በደልን አስወግዶ፣ በሥልጣን መባለግን ተቆጣጥሮ፣ ቀማኛን እና አረመኔ ሰውን ከመካከላቸው፣ከሕብረተሰቡ አርቆ ፣ ሰላምን ፣ በአንድ አገር ውስጥ መምጣት ነው። ይህም ማለት፣ የማንም ሰው ቤት አይዘረፍም። ይህ ማለት የድሆች ቤት በአናታቸው ላይ አይፈርስም።… ስልክ አይጠለፍም። ሰው አለምክንያት ተይዞ አይታሰርም።
ሁለተኛው ፣ የመንግሥት አላማና ሥራ:– ረሃብን አጥፍቶ፣ በሽታን አስወገዶ፣ የሥራ ዕድል ለሁሉም ዜጋ ከፍቶ፤ የማህራዊ ኑሮ ሁኔታን አሻሽሎ፣ ደካማውን ረድቶ፣ ሀብታሙን አበረታቶ፣ ዕወቀትና ጥበብን አስፋፍቶ፣ ለአገሪቱ ብልጽግና እን ዕድገትን ማምጣት ነው። እንግዲህ ይህ የአንድ መንግሥት ሁለተኛው ሥራ ነው።
ሥስተኛው የመንግሥት ሥራ ፣ በህ- መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን ፣በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ላይ አገሪቱ (ኢትዮጵያ ) ፈርማ የተቀበለችውን የሰበአዊና የዲሞክራሲያው ፣ የዜጎችን መብቶችን በሙሉ አንዱም ሳይጣል ሁሉንም፣ ነጻነቱን ማክበር፣ ማስከበር፣ የመንገሥት ዋና ሥራ ነው።
ይህንንም በሥራ ለማገድ የሚምክሩትን ኃይሎች ሁሉ፣ ሕጉን ስሚጻረሩና ስለሚያደናቅፉ፣ የሌላውንም መብት ሰለሚገፉ፣ መንግሥት ይህን የመቆጣጠር፣ ግዴታም አለበት።
በአጭሩ „የመንግሥት ተግባር፣ የመንግሥት ግዳጅ እና ዋና አላማውም ይህ ነው።“
ይህም መሆን አለበት። ከሌለስ?
ሰ
በዚህ አቀራረብ ምንድነው እኛን፣ ኢትዮጵያኖችን አንድ የሚያደርገን ነገር? የሚለውን ጥያቄ ፣ ከብዙ በጥቂቱ፣ ከተከታተላችሁን በዚህ የመለስን ይመስለኛል።
እዚያው በእዚያው መንግስት እነዚህን እላይ የተጠቀሱትን ሦስት ነገሮች ከአላሟላ ደግሞ ምን ማድረግ ይገባል ? የሚለውን፣ የአብዛኛውን ኢትዮጵያኖች ጥያቄ፣ ነገሩ የእኛ ብቻ አይደለም፣ የዓለም ሕዝቦች ጥያቄ ነው፣ ወደ መመለሱ፣ ቀስ ብለን አሁን እንሸጋገር።
እንደምናውቀውና እንደተማርነው፣ የኢትዮጵያም ሕገ-መንግሥት ላይ እንዳነበብነው፣ አዚያ ላይ ስለ ነጻ -ፍርድ ቤትና ስለነጻ-ዳኛ ያወራል። ስለ ነጻ-ጋዜጣና፣ ስለ ነጻ-ማህበር ምሥረታ ያነሳል። ስለ ነጻ-ምርጫና ስለ ነጻ -ድርጅቶች ምሥረታና ውድድር ያብራራል። ግን ይህ ሁሉ ወረቀት ላይ ሰፍሮ በሥራ ከአልተተሮጎመ፣ ሥልጣን ላይ የወጣውን ሰው፣ ወይም በድን ፣ ሥልጣን ከሕዝብ የሚወጣ ስለሆነ ፣ ይህን ዓይነቱን አሰራር የማይቀበል ድረጅት ወይም ግለሰብ፣ ዓለም አቀፉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የሰው ልጆች መብት አዋጅ፣ እንደሚለውና እንደሚፈቅደው፣ እነዚህ ሰዎች፣ አገሪቱንና ሕዝቡን ሳያጠፉ፣ እነሱ በሰላማዊ መንገድ ተወገደው፣ በሌላ አምባገነን ባልሆኑ ነገር ግን ፣ በምርጫ ሥነ ስርዓት ላይ በሚያምኑ ዲሞክራቶች መተካት አለባቸው ይላል።
የፖለቲካ ትግል እና የፖለቲካ አላማና ግቡም በመጨረሻው፣ ፈላስፋዋ ሐና አረንድት ካንትና ቬበርን ተከትላ እንደምትለው፣ የነጻነትን አየር፣… ሊበርቲን፣ ወይም አርነትን፣ ይህን ጥሩ አየር፣ መተንፈስ ብቻ ነው፣ ትለናለች።
ግን ደግሞ ይህን የነጻነትን ጥሩ አየር፣ ሊበርቲን…. እናመጣላችሁዋለን ብለው ሥልጣኑ ላይ ጉብ ብለው፣ ከእንግዲህ „ አፍንጫችሁን ላሱ ያሉ ኃይሎች“ ቁጥር በዓለም ላይ ጥቂት አይደሉም። ለዚህ ሁሉ መድኀኒቱ፣ ሰይጣን ጠበልና መስቀል እንደሚፈራው ሁሉ፣ እንደገና ለነጻ ምርጫ እና ለነጻ- ፕሬስ፣ ለነጻ- ሕብረተሰብ፣ ለሕግ በላይነት እንደገና፣ ያው ለሰባዊ መብቶች መከበር፣… ለነጻነት ተነስቶ መታገል፣ የሰው ልጆች የማይቀርላቸው፣ „እዳ“ ነው። አንድን ሕዝብ ከገባበት መከራ የሚያወጣው፣ ደግሞ እራሱ ነው።
ፖለቲካ ማለት ነጻነት ነው።
ከሣቴ ብርሃን
————————