ፖለካቲካ ምንድን ነው?
ስለ ባርነት ምንም ነገር የማያውቅ ሰው ስለ ነጻነት ጥዋት ማታ ቢነግሩት ምንም አይገባውም። እንዲያውም አትጨቅጭቀኝ ብሎ፣ በመጀመሪይ ይሳደባል። ከአልሆነም በዱላ ወይም በድንጋይ ያባርራል። ቢቻለው እና እጁ ላይ ያ ሰው ከወደቀ ደግሞ፣ መሣሪያ አንስቶ አስፈራርቶ፣ ያስረዋል። ወይም በጠበንጃ ረሽኖት ይገድለዋል። ሌኒን አንድ ቦታ ጥሩ አድርጎ አሰቀምጦታል። አብዮቱን፣ የሩሲያን ኦክቶበር ሪቮሊሲዮን ለመጠበቅና ለመከላከል፣ አስፈላጊ ከሆነ „ በመደዳ፣ ሁሉንም ጸረ-አብዮተኛ አቁሞ መረሸን“ በእሱ እምነት፣“ ተገቢ ነው „ ብሎአል።
በቶሎ ለመግባባትና አንድ ነጥብ ላይ ለመድረስ፣ በቅርቡ በእኛው ላይ፣ ዓይናችን እያየ በደረሰው፣ ታሪክ ላይ፣ በእሱ እንጀምር። በኤርትራና በኢትዮጵያ ፣ „ሁለቱን አገሮች፣ እኛ እንወክላለን „ በሚሉና እራሳቸውን በሰየሙ፣ ወገኖች መካከል የሆነውን ነገር፣ እናንሳ። ምን ሆነ?
ከዚያ በፊት አንድ ሐቅ አለ።
እሱም ፣ „ በእኩልነት ስም“ –ይህ የአኔ ቋንቋ አይደለም፣ በታሪክ የትም ቦታ ብትሄዱ የምታዩት ነው– „በእኩልነት ስም በጌቶቻቸው ላይ የሚየምጹ፣ ያመጹ ባሪያዎች“ –ፈላስፎች ናቸው ይህን ያሉት–„ ሥልጣኑን ነጥቀው እነሱ ቤተ-መንግሥት የገቡ ቀን፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚያውጁት፣ አወጅ፣ የጌቶችና የባሪያዎች እኩልነትን ሳይሆን፣ ነገሩን ሁሉ ቀያይረው እነሱ `ጌታ ሁነው፣ የቀድሞ ጌቶቹን ባሪያ አድርገው` ለመግዛት ነው።
ለመረዳት:- „የኢትዮጵያ አብዮት“ በቂ ነው። በንጉሱ ፋንታ ማን ነው፣ ታላቁ ቤተ ምንግሥት፣ ስድስት ወር በአልሞላ ጊዜ „ፈላጭ ቆራጭ ሁኖ“ በአናታችን ላይ ገብ ያለው?
ማን ነው ከኮነሬል መንግሥቱ ኃያለማሪያም በሁዋላ፣ ኢትዮጵያን ለሁለት ተካፍሎ፣ በአሥመራና በአዲስ አበባ፣ በቤተ- መንግሥቱ ውሰጥ ተንደላቆ ተቀምጦ፣ „የእራሱን ሕግ“ ያወጣው?
ደርግና ሻቢያ፣ ወያኔና ሻቢያ፣ የያዙትን ሥልጣን ከኑጉሠ -ነገሥቱ፣ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ሥልጣን፣ የሚለየው ምንድነው?
ሌላም ጥያቄ አከታትለን እናንሳ።
ምንድ ነው፣ ሻቢያና ጀበሃን፣ ወያኔና ኦነግን፣ የኦጋዴንና የደቡብ ሕዝቦችን፣ መኢሶንና ኢህአፓን፣ ወዝና ሰደድ፣ ኢጭአትንና፣ ማሌሪድን፣…የአማራንና፣ የጉራጌን ድርጅት፣ አንዱን ከሌላው የሚለየው?
ከዚህ ሁሉ ትርምስ በሁዋላ ውጤቱ ደግሞ ምንድነው? ምን ሆነ?
በቀጥታ ማሰብ የሚችሉበት እንግለዞች፣ አንድ ነገር ይላሉ። „ከምግብ በሁዋላ የሚቀርበውን ጣፋጩን ፑዲንግ፣ ፑዲንግ ነው ወይስ አይደለም ብሎ፣ ዝም ብሎ ከመነታረክ፣ (ምክንያቱም ክርክር የፈለገ ሰው የማያገላብጠው ድንጋይ የለም) በዕውነት ያ ነገር „ፑዲንግ“ መሆኑን የምታውቀው፣ ስትበላው ብቻ ነው፣… በል ብላው“ ይላሉ።
እንግዲህ ይኸው ፣ ያ ! ስንት ሰው፣ ከአርባ አመት በላይ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ ፣… ከኤርትራ እሰከ ኦጋዴን፣ ….ከኢሉባቦር እስከ ጅቡቲ ጠረፍ፤… የታገለለት፣…የሞተለት፣ የቆሰለበት፣ አካለ ስንኩል የሆነበት፣… ቤትና ትዳር የተበተነበት፣ ያ አንድ ቀን ይመጣላችሁዋል ተብሎ በሁሉም ድርጅቶች የተነገረለት „ልዩ የሆነው የኢትዮጵያ የሶሻሊዝም ፣….ፑዲንግን“ ቀምሰነው ስንመለከተው፣ በመጨረሻም ተንከራተን ያገኘነውና ያተረፍነው፣—መለስ ብለን ብንመለከተው— በአንድ በኩል–ግልጽ እንሁን– እልቂትና ትርምስ ብቻ ነው። በሌላ በኩል፣ የሸመትነው፣ ሁለት ትላልቅ ግዙፍ አምባገነኖችን ነው።
ይህ አንደኛው ገጽታ ነው። በሌላው አቅጣጫ ደግሞ ስንመለከተው፣ ያተረፍነው የኢትዮጵያን ጥፋትና፣ በመካከላችን አለመደማመጥን፣ ብቻ ነው።
እንዴት?
፩
„…ነፃነትና ባርነት፤ ዲሞክራሲና አምባገነንነት፤ ሰብአዊ መብትና ጭቆና፤ ፍትህና ፈላጭ ቆራጥነት፤ ሌለው ቀርቶ የፓርላማ ሥርዓትና የአንድ ፓርቲ አገዛዝ … ነፃ ጋዜጣና ያንድ ፓርቲ ልሳን፤ … መለአክና ሰይጣን፤… እነዚህን ሁሉ አምታተውና አንድ አድረገው፤ ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች በብዙ አካባቢ ታይተዎል። ብዙ ቦታም፤ አንድ ናቸው ተብሎ፤ ተፅፎአል።
እንደ ኢትዮጵያ ግን፤ ይህ ነገር ተምታቶና በማር ተቀብቶ፤ ለገበያ የቀረበበት ቦታ የለም። የሚገርመው ደግሞ ከሁሉም ነገር፤ ይህ ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ፤ ከሌሎች ቦታዎች ሁሉ፤ ሥር ሰዶ ከሰው አእምሮ አልወጣ ብሎ፤ እስከአሁን ድረስ አስቸግሮአል።
አንድ፤ በቅርቡ የተከሰተ፤ ግን ያልተረሳ ታሪክ ፤ – ግልጽ ለመሆን- ለምሳሌ፤ እዚህ ላይ፣ እናንሳ፤ እሱም:- “…ነፃነት ወይም ባርነት!” የሚለውን፤ ኤርትራ የተገነጠለችበትን ጥያቄ ነው። መለስ ብለን እንመልከት። መቼም እላይ እንዳልነው፣ ባርነትን የማያውቅ ስለነጻነት ሊናፍቅና በአግባቡ ሊያውቅ የማይችለውን ያህል፣ ባርነትን የሚያውቅም ስለነጻነትም የሚያውቀው የለውም፣ ሁለቱም “ፑዲንጉን” ሲቀምሱት ነው፣ ጉዱ የሚገለጥላቸው!
የኤርትራ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን፤ አሁን ያሉት፤ “በባርነት ሥር ነው“ ወይስ „የነፃነትን“ አየርን እየተነፈሱ ነው? … ማነው? ለመሆኑ ከማን ጭቆና፤ እነሱን ነፃ ያወጣው? …ማነው? ለመሆኑ ዛሬ የማን ባርያ ሆኖ የሚያለቅሰው? ነፃነት፤ በእውነት በኤርትራ፤ አሁን አለ ወይ? ጌታውስ ማን ነዉ? ባርያውስ ማነው… እዝያ?“
ይህን ነጥብ ወይዘሮ ወለተ ማሪያም፣ በኢትዮ ሚዲያ ላይ አንዴ አንስተውታል።
ግን ደግሞ ከዚሁ፣ ራመድ ብለን እንሂድና አንድ ጥያቄም በቶሎ ለመግባባት፣ እናንስ። እንደገና! …ለመሆኑ፣ በኮነሬል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምና በእሳያስ አፈወርቂ መካከል፣ በእሱና በአቶ መለሰ ዜናዊ፣…. በኦነግና በሻቢያ፣ በሕዝባዊ ወያኔና ፣… ወይም በኦጋዴን፣ በጀብሃና… በሌሎቹም፣ በኢትዮጵያ፣ ውስጥ በአለፉት አርባና ሃምሳ አመታት በበቀሉት ድርጅቶች መካከል ምን ዓይነት „ትልቅ ልዩነት“ አለ?
በእርግጥ ሁለቱም ሦስቱም፣ ኢትዮጵያን፣ ወይም ኤርትራን፣ ለአለፉት ረጅም አመታት፣ በጋራ ሆነ በተናጠል ገዝተዋል። ወይም፣ሌሎቹ እንደ አቅማቸው፣ ያቺን አገር አተራምሰው ሄደዋል። ወይም ደግሞ፣ አንዳዶቹ እንደገና ጫካ ገብተዋል። ከአልሆነም በስወር ትግል፣ ላይ ከአንዳነድ፣ ጽሑፎች ላይ እንደምናነበው፣ ተሰማርተዋል ።
ግን ይህ ሁሉ ሆኖ፣ እነዚህ ድርጅቶች፣ በመጨረሻ አላማቸው፣ „ እነሱ፣ ለእኛ ለኢትዮጵያ፣ ለማምጣት በተለሙት በሶሻሊዝም፣ አምባገነን ሥርዓታቸው“ ላይ፣ ይለያያሉ? አዎ ! አምባገነን ሥርዓታቸው ላይ፣ ይለያያሉ?
አይመስለኝም።
በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ላይ፣ በተለያዩ ጊዜያት የተጻፉትን አላማዎችና ግባቸውን እንደገና፣ በተጨማሪ፣ በቀላሉ ለመግባባት፣ ከፈለግን፣ መለስ ብሎ፣ መመልከት በቂ ነው። እንግዲህ እነሱ፣ ፕሮግራማቸው ላይ ያሰፈሩት ነጥቦች ሁሉ፣ ስለ እነሱ ማንነት በደንብ ያስረዳል።
የዕለት ተዕለት ፅሑፋቸውንም እንደገና ፈልጎ፣ መመልከትም፣ በቀላሉ ለመግባባት፣ ይረዳል። እነሱም፣ በጊዜያቸው፣ በልሣናቸው ላይ ያስቀመጡአቸው ፣ ቃላቶች፣ ስለ እነሱ፣ ማንነት፣ ግልጽ አድርጎ ያብራራል። አፈ ቀላጤዎ ቻቸውም፣ ባደባባይ አንድ ሁለትቃሎች ሲሰነዝሩ አዋቂ ያውቃቸዋል።
፪
ማንም ሰው አይደለም ፣ ወዳጆቼ (እዚህ ላይ፣ ለዚህ ሰው እግዚአብሔር ይስጠው እንዳይባል በዚህ ስም የተካሄደው በደል ቀላል አይደለም፣) እሱ እራሱ ቪላዲሚር ኢሊች ሌኒን ነው፣ በጽሑፉ ላይ አንድ ቦታ ከዚህ በታች ያለውን ቃል፣ ለማስታወስ ያህል፣ ያሰፈረው። „…ፖለቲካ ሲባል ምን ያህል ትንሽና ቀላል ነገር እንደሆን“ ለማስረዳት፣ እሱ ሌኒን የተጠቀመውን፣ አነጋገር መልስ ብለን ተመልክተን እናንሳ።
„…ማንም ተራ ሰው፣…አንዲት ወጥ ቀቃይ ሠራተኛም ብትሆን፣ የአገዛዝ ማንቀሳቀሻ ፣ የመኪናውን መሪ እንደምንም ብለው እሱዋን፣ አንዴ ከአሰጨበጡዋት፣ እሱዋ፣ ያኔ መኪናውን፣…የፖሊት ቢሮውን ይዛ የፈለገችበት ቦታ አሽከርክራ፣ ልታደርሰው፣ ትችላለች…“ ብሎ፣ይህ የሩሲያ አብዮት አርቺቴክት፣ „መሪ“ በጊዜው፣ ፖለቲካ ቀላል ነገር መሆኑን አስተምሮ ነበር። ከዚሁም ጋር አንድ የኢትዮጵያን ምሁሮች አእምሮ የሰለበ፣ ምሳሌም አብሮ ወርውሮ ነበር። ከአልተረሳ፣ ሌኒንና ግብረ አበሮቹ ስለመገንጠል ሲያውሩ ሲያስረዱ፣ ይህን ምሳሌ ይጠቅሱ ነበር።
„ባልና ሚስት ከአልተግባቡ፣ ይፋታሉ። ሊፋቱም ይችላሉ።… የብሔሮችም አንድነት እንደ ጋብቻ እንደዚሁ ነው።… ከአልተግባቡ፣ ብድግ ብለው ሊገነጠሉ ይችላሉ። ይህ ስለተባለ ግን ሁሉም ፣ ይፋቱ፣ ሁሉም ይገንጠሉ ማለት አይደለም።… የላብ አደሩ አላማ፣ የመጨረሻ ግቡ ለሶሻሊዝም ስለሆነ፣ …የሚቆመው ለአንድነት ነው። ወዘተ…ወዘተ…“
ግሩም ዳይሌክትክ ነው። እላይ እንደተባለው፣ በፖለቲካ „ የፑዲንጉ መፈተኛው፣ መብላት ነው።“
…. እንግዲህ ይህን ያዳመጡ ሰዎች፣ ምክሩን ፣ ትምህርቱን፣ ተከትለው፣ አገራቸውን እያሽከረከሩ፣ ዛሬ የት እንዳደረሱ፣ በተለያዩ አህጉሮች ተዘዋውሮ መመልከት ከባድ አይደለም። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዩጎዝለቪያም ምሳሌ ናት። እሱዋ ብቻ ሳትሆን፣ ሶቪየትም እራሱዋ። …
ጀርመን ተዋህዳለች። ኮሪያ ልትዋሃድ ትፈልጋለች። አውሮፓ ከለውህደትና አንድነት፣ ተስፋ የለንም ብለው፣ ድንበራቸውን፣ ገንዘባቸውን፣….ሸንጎአቸውን፣ አንድ አድርገዋል።
ካርል ማርክስ ሌላ ቦታ ላይ፣ ከሌኒን በፊት፣ የጥበበኛዋን የንብ ሥራንና፣ የአንድ ሰነፍ አናጢን፣ የግንባታ ሥራ አወዳድሮ፣ የሚከተለውን ነገር ያነሳል።
ጥበብ የተሞላው፣ ንቦች ተጠንቅቀው የሚሰሩት የማር ቂጣ፣ በማርክስ አመለካከት፣ አንድ ሰነፍና ደካማ አናጢ ከሚሰራው የቤት ጣራ ጋር ሲወዳደር፣ የንቦቹ፣ በዲዛይን ደረጃ የትና የት አጣፍቶ የሚሄድ ነው ይለናል። በእርግጥም፣ እነሱ የሚሰሩት ሥራ የሚያስቀና ነው። ግሩም ሕብረትና የሥራ ክፍፍል አላቸው። እሱ ግን አሁን የጨዋታችን አርእሰት አይደለም።
ግን ይላል ይህ ፈላስፋ፣ „ጥራት የሌለውን ሥራ የሚሰራው ግንበኛና አናጢ፣ ከንቡዋ የሚለየው ነገር ቢኖር፣ ያ ሰውዬ ግንቡን ከመገንባቱና ከመሥራቱ፣ በፊት ጠቅላላውን፣ የቤቱን ሥራ ፕላን፣ በመጀመሪያ በጭንቅላቱ ውስጥ፣ ነድፎ፣ ሰርቶ፣ የጨረሰው ነገር ነው „ ይለናል። በእርግጥ፣ የቤቱ ቅርጽ፣ ሥዕሉ በአዕምሮ ውስጥ ተነድፎ ተሰርቶ ያለቀ ነገር ነው።
የንቡዋን የጭንቅላት ሥራ፣ ከምን እንደመጣ፣ እንዴት ከትውልድ ወደ ትውልድ፣ ይህ ጥበብ በትክክል እንደሚተላለፍ፣ እኔ ባላውቅም፣ አንድ ደራሲ፣ …አንድ ሰዓሊ፣ አንድ ጸሐፊ፣ እንድ የመኪና ይሁን የልብስ ዲዛይን አውጭ…ወይም አንድ የፊልም ዳይሬክተር፣…ሥራውን ከመጀመሩ በፊት፣ ፕላኑን በአእምሮው ውስጥ ነድፎ፣ የሚያስቀምጠው ነገር መሆኑን እኔ በደንብ አውቃለሁ። ደግሞም መሆን ያለበት ነገር ነው። አለበለዚያ ትርፉ ከወረቀት ጋር ፍጥጫ ነው ። በእርግጥ በሥራ ሂደቱም ውስጥ፣ ያ …ሰው ያን የነደፈውን ፕላን፣ ወዲያና ወዲህ እየጎተተው፣ ሊቀይረው ይችላል። ግን ያለ ፕላን ምንም ነገር ወረቀት ላይ አይሞነጫጨርም።
ለምንድነው ይህን ጉዳይ አሁን ያነሳሁት? ፖለቲከኛም፣ እንደ አናጢው የሚሰራውን ሥራ በመጀመሪያ (ጀሌ ተከታይ እስካልሆነ ድረስ) በደንብ በጭንቅላቱ ውሰጥ ነድፎ ያስቀመጠው፣ ወይም የደበቀው፣ ነገር በኪሱ፣ ሁል ጊዜ አለው።
ይህም ማለት፣ በሌላ ቋንቋ፣ በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደረው ዲሞክራቱም ይሁን ከሕግ በላይ እራሱን የሰየመው አንድ አምባገነኑም፣ ሁለቱም፣ የፖለቲካ ሰዎችና „መደቦች“፣ አንዱ ከሌላው ሳይለይ፣ የሚጓዙበት፣ አዲስ አይደለም፣ መንገድ ነው። በተለይ የአምባገነን ሥርዓት ዲዛይን አውጪዎች፣ ይህን ነገር በደንብ ስለሚያውቁበት፣ ሁሉን ነገር በሕብረተሰቡ ውስጥ ተብትበው፣ ቆልፈውና አስረው፣… ባል ሚስቱን፣ ሚስት ባሉዋን፣ ልጆች ወላጆቻቸውን፣ ጎረቤት ጎረቤቱን፣ ….አንዱ ሌለውን፣ እንደ ማፊያ ድርጅት፣ በአይነ-ቁራኛ እንዲከታተለውም፣ የሚያደርጉት፣ ለዚሁ ነው።
„ፑዲንጉን ቀምሰን“ እንዳየነው፣ እንደዚህ ዓይነቱ ሥርዓት፣ ደግሞ የሰውን መብቱን ገፎ፣ እንዳይናገር፣… እንዳይጽፍ፣ እንዳይተች፣ ከመደገፍ ሌላ፣ ትንፍሽ ብሎ እንዳይቃወም፣….እንዳይጠይቅ፣ እንዳይመራመር፣ የሚያግድ የአምባገነን ሥርዓት ነው። ኮሚኒስቶች ይሁኑ ፋሽሽቶች፣ በነገረ ሥራቸው፣ የስውን ልጆች መብት በመርገጥ „አንድ ናቸው“ የሚባሉትም፣ ለዚሁ ነው።
እነዚህ ኃይሎች፣ ከአውሮፓና ከሌሎች አህጉሮች፣ ተራ በተራ እየወደቁ ጠፍተዋል። በቀድሞው የሶቭየት ሪፓብሊክ፣ በቤላ ሩሲያና በካውሼያን፣ አለፍ ብሎ በቻይናና በበርማ…በቬትናምና በሰሜን ኮሪያ፣ አሁንም ይታያሉ። እንደገና እያገረሸባቸው የመጡ አገሮችም አሉ። አንደኛው፣ ሐንጋሪ ነው።
ዋናው የአምባገነኖች፣ መሰባሰቢያ መንደር፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ደግሞ፣ እንዲያውም መናኸሪያቸው፣ አፍሪካ ሁኖአል። በመካከለኛው ምሥራቅም አሉ። ልክ እነሱም፣ እንደ አፍሪካውያኖቹ፣ ሥልጣኑን ለልጆቻቸው፣ ወይም ለትግል ጓደኛቻቸው፣ እንደ ዕቃ፣ ማውረስ ከጀመሩ ቆይተዋል።… ያወርሳሉ። አፍሪካውያኖቹ፣ አንዳዶቹ፣ ለሚስቶቻቸው ሥልጣኑን ሲያውርሱ፣ አረቦቹ ብቻ ይህቺን ነገር ደፍረው፣ እስከ ዛሬ ድረስ አላደረጉም።
የሚያሳዝነው በአፍሪካም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ:- በአረቦች አገር፣ አምባገነኖችን ሥልጣን ላይ የሚያወጡት፣ እንዲቆይም የሚያደርጉት፣ ይህ ሚሥጢር አይደለም ምዕራቦቹ ናቸው።
ግን ቀደም ሲባል እንደተባለው፣ ስለ ባርነት የማየውቅን ሰው ስለነጻነት ጥዋት ማታ ቢነግሩት፣ ምንም አይገባውም። ወይም ደግሞ እራሱ ማርክስ፣ አንዴ፣ አንድ ቦታ፣ በወጣትነት ዘመኑ፣ እንደአለው፣ „…አንድ አይዶሎጂ፣… አንድ ርዕዮተ-ዓለም ጭንቅላቱን ስቦ፣ ያንን ሰው ባሪያው ያደረገው ትምህርት፣ ምንም ቢሉት ምንም፣ ልክ እንደ ሃይማኖት፣ በቀላሉ፣ ያንን ሰው፣ ያ አስተሳሰብ፣ ዝም ብሎ፣ — ከመሬት ጋር ሳያዳፋው–እሱን በቀላሉ አይለቀውም።“ ብሎ ፣ እራሱ ማርክስ ቀልዶ ጽፎአል። ይገርማል! ይህ አመለካከትና ግንዛቤ በጣም ይደንቃል!
ግን ደግሞ ከሃይማኖትም፣ „ሃይማኖት“ አለው። አንዳንዱ ሃይማኖት፣ ለነጻ-አስተሳሰብ ክፍት ቦታ ይሰጣል። …ጠይቁ፣… ተመራመሩ፣ …ጥሩውን ነገር ፈልጋችሁ አግኙም ይላል። አንዳንዱ ደግሞ ፣ „ነጻ-አስተሳሰብንና አመለካከትን፣ ምርመራና ጥያቄዎችን እንደ፣ አንድ አምባገነን ሥርዓት“ ጨርሶ ፣ ለተከታዮቹ፣ ምዕመናኑ፣ ፈጽሞ አይፈቅድላቸውም።
(ተመራመሩ፣ ጠይቁም፣ ከሚሉት ሃይማኖቶች ውስጥ የክርስትና ሃይማኖት ይገኛል። በተለይ ጳውሎስ፣ ስለ ነጻ ሰውና፣ ስለ ነጻነት አስተሳሰብ፣ በትክክል ስለ አርነት፣ እሱ ያነሳል። እሱን ግን ሌላ ጊዜ፣ እንመጣበታለን። አሁን ወደ ተነሳንበት አርዕስት፣ ወደ ፖለቲካ ምንድነው? ወደሚለው ጥያቄአችን እንመለስ)
፫
ፖለቲካ የሰውን፣ መብት መግፈፍና መርገጥ አይደለም። ፖለቲካ እንደሚባለው „…አሰቀያሚና አሳዛኝ፣…አሰፈሪም፣ የብልጦች ቆሻሻ ጨዋታም“ አይደለም። „ፖለቲካ“ እስከ አሁን ጊዜ ድረስ እንደምናውቀው፣ „ወዳጅና ጠላትን“ በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ ለይቶ አሰቀምጦ፣ አንዱን አሳዶ ማጥፋት አይደለም። መዋሸትም፣ አይደለም። ማተረማመስ፣ ከፋፍሎ መግዛት፣ ማስፈራራት፣ ዛሬ ይህን ነገ ያን ማለት፣ ማወናበድ፣ ግራ ማጋባት፣ ሕግና ሥርዓትን ለእራስ ኢንዲያመች አመቻቻቶ ማስቀመጥም አይደለም።
ፖለቲካ እንዱን ማራቅ፣ሌላውን ማቅረብ፣ ያቀረቡትን ሰው ተጠቅሞ፣ እንደ ሎሚ መጦ መጣል፣ በሰው ነፍስም ላይ መቀለድ አይደለም።
ታዲያ ፖለቲካ ምንድነው? የፖለቲካ ጥበብ ማለት፣ ምኑ ላይ ነው? ምንድነው ፖለቲካ? የፖለቲካ ሳይንስ፣ አረ ለመሆኑ እሱ ምንድነው? የፖለቲካ ፍልስፍናስ? የፖለቲካ ቲዎሪዎችስ?
ማንም ከመሬት ተነስቶ ሌኒን እንዳለው፣ „ የፖሊቲ ቢሮውን የመኪና መሪ ጨብጦ፣ አገሪቱንና ድርጅቱን ወደ ፈለገው አቅጣጫ፣ ሊያሽከረክረው ይችላል?“
አንድን ሕዝብ ጠበንጃ ደግኖ፣ ጥይቱን አቀባብሎ፣ አፈ- ሙዙን „ምርኮኛው ላይ አነጣጥሮ“… ምን ያህል ጊዜ መግዛት ይቻላል?
እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ለመመለስ፣ ከፕላቶ እሰከ አርስጣጥለስ፣ ከሲሲሮ እሰከ ማይካቬሊ ድረስ፣ ከ…. መሄድ ያስፈልጋል።
እኔ ግን በማክስ ቬበር፣ በጀርመኑ የሕብረተሰብ ተመራማሪ፣ በእሱ ሁለት ትናንሽ ጽሑፎች መጀመሩን እመርጣለሁ። በሁለት ምክንያቶች ብቻ ነው፣ ምርጫዬ እነሱ ላይ የወደቀው። እንደኛው ጽሑፎቹ አጫጭር ና በቀላሉ ስብሰብ ተደርገው የተጻፉ ጽሑፎች በመሆናቸው።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ ልክ እንደ እኛው „ለተወናበደ ትውልድ“፣ ያ ጽሑፍ የተጻፈ በመሆኑ ነው።
ጀርመን በአንደኛው ዓለም ጦርነት ተሸንፋ ነበር። ሕዝቡም ተነስቶ ንጉሡን አባሮ፣ አዲሱን ሪፓብሊክን አውጆአል። የተለያዩ ግን የማይደማመጡ የፖለቲካ ድርጅቶችና ቡድኖች እንደአሸን በአገሪቱ በጀርመን፣ ፈልተዋል። በሌላ በኩል እዚያ፣ የትርምስ ዘመን ውስጥ ገብተው፣ የተወናበዱ፣ ነገር ግን ወደፊት ኃላፊነታቸውን ለመረከብ፣ የተዘጋጁ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም፣ ከፊቱ እነደቆሙ፣ ማክስ ቬበር ተመልክቶአል።
ቬበር ፣ አንድ ጊዜ በ1917 ሌላ ጊዜ በ1919 ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ይህን የመሰለ ንግግር ሲያደርግ፣ ሒትለር፣ ወይም ኮሚኒስቶቹ፣ ሥልጣን ላይ አልወጡም ነበር። ለመውጣት፣ ግን ሁለቱም፣ ወገኖች ይዘጋጁም ነበር።
ግን ከዚያ በፊት አንድ ነገር መለስ ብዬ ላንሳ ።
በዓለም ላይ የአገሪቱ መሪዎች ( የምታውቁ ከአላችሁ አርሙኝ) ሥልጣን ላይ ወጥተው፣ „የአስተዳደር ትምህርት ቤት“ የሄዱበት አገር፣ ኢትዮጵያ ብቻ ነው። በአርባ አመት ጊዜ ውስጥ፣ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ሁለት ጊዜ ተፈራርቀው ሥልጣኑን፣ በችሎታና በሕዝብ ምርጫ ሳይሆን በጠበንጃ የነጠቁትና የተነጣጠቁት ኃይሎች፣ (ይህ የተመዘገበ ታሪክ ነው) ሥልጣኑን ይዘው ቤተ-መንግሥት ገብተው፣ „እንዴት እንደሚያስተዳድሩ፣ ትምህርት ያገኙት“፣ አስተማሪ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካን ከተላከላቸው ወዲህ፣ ወይም ከእሱም በሁዋላ ነው። ምን ዓይነት ተአምር ነው።
የደርግ አባሎች በሞስኮና በምሥራቅ በርሊን ፣ ኢህዴግ፣ ሻቢያና ኦነግ ደግሞ ከለንድንና ከአሜሪካን እየተነሱ በሚመላለሱ አስተማሪዎች ሰልጥነው፣ አገሪቱን፣ እንዲገዙ ተደርገዋል። እነሱም፣ ገዝተዋል።
የአውሮፓ አንድነት ማህበር እንዳለው፣ „ለመጨረሻዎቹ ተማሪዎች፣ ወደ ሃያ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ“ ተደርጎአል። አንዳዶቹም በጥሩ ውጤት ትምህርታቸውን ሲያገባድዱ፣ ሌሎቹ ጊዜ የለንም ብለው ትምህርታቸውን አቋርጠው „በአስተዳደሩ ሥራ ላይ፣ በገዢነቱ“ ላይ ቀጥለዋል።
ለምን ተማሩ አይደለም አሁን የውይይቱ አርዕስት ። መማር ጥሩ ነው። መማር ገደብ የለውም። ግን የተማሩ ሰዎች በአገራችን እያሉ፣… ተወዳድረው፣ ሕዝብ ፊት ቀርበው፣ ችሎታቸውን አሳይተው፣ተመርጠው ኢትዮጵያን ማስተዳደር የሚችሉ ሰዎች፣ በአልጠፉበት አገር፣ ለምን እነዚህ „የዲምክራሲ ሥርዓትና የሰበአዊ መብቶች መከበር በዓለም ዙሪያ ያሳስበናል „ የሚሉ የምዕራብ መንግሥታት፣ ይህን ዓይነቱን እርምጃ ለመውሰድ ተገደዱ?
ግን ወደ ተነሳሁበት፣ አርዕስት ልመለስ።
የለም ! ከዚያም በፊት አንድ የተረሣ : – ሰው ሁሉ የሚያነሳው ጥያቄም አለ።
እሱም፣ „ኢትዮጵያንም ሆነ ኤርትራን ከደርግ አገዛዝ ነጻ -አውጥተን፣ ሕዝቡን ፣ … ፣ በብልጽግናና በዕድገት፣… በትምህርትና በምርምር፣ በድርሰትና በኪነጥበብ፣ …የማህበራዊ ኑሮአቸውን ሁኔታም አሻሽለን፣…. በሽታና ረሃብን፣ ከአገሪቱ አጥፍተን ፣ በሰላምና በደስታ፣ እነሱ እንደሚሉት በዲሞክራቲክ ሥርዓት፣ ሕዝቡ እንዴት እንደሚኖር፣ እኛ እናውቃለን“ ይሉ የነበሩ „የነጻ-አውጪ“ ድርጅት መሪዎች፣ ሥልጣን ከያዙ በሁዋላ ለምን የእነሱ „ትምህርት ቤት“ መግባቱን፣ መረጡ?
ይህ ብዙ ሰው ያኔ የጠየቀው፣ እስከ አሁን ድረስ መልስ ያልተሰጠው ጥያቄ ነው።
እንግዲህ እንደገና ወደ ተነሳሁበት አርዕስት ልመለስ።
፬
በ1917 „ሳይንስ እነደ ሙያ“ በሚለው አርዓስቱ ዙሪያ፣ ማክስ ቬበር፣ ግሩም የሆነ ትንትና ለተማሪዎቹ እንዲያዳምጡት አቅርቦላቸዋል። በሳይንስ ዓለም ቆይተው ለእራሳቸውና ለአገራቸው አንድ ነገር ለመሥራት ከፈለጉ፣ ሐሳቡንና ምክሩን እንዲከተሉትም ጠይቆአቸዋል።፣ ውሳኔአቸውን „በሳይንስ እና በምርምር ላይ፣ ብቻ ከጣሉ ደግሞ፣ መጣልም ከፈለጉ፣ „ከፖለቲካው ዓለም ኢንዲርቁ“ ይህን በመሰለ ቃል እነሱን መክሮአቸው፣ ምሁሩ ቬበር፣ ያኔ ከተማሪዎቹ ተሰናብቶአል።
የመረጠው ሰውም፣ ለተማሪዎቹ ፣ ለማስረዳት ለቅሞ የሰነዘረው ቃልም „…ይመሻል ይነጋል፣… ጨለማውም አልፎ፣ ነግቶም ጻሐይ ይወጣል፣ እናንተ ግን አሁን ሂዱ ተኙ…“ አንዴ ያለውን፣ የነብዩ ኢሳያስን ቃል ነው።
የግሪኩ ፈላስፋ ኤፒኩር ተመሳሳይ ምክር ለአገሩ ልጆች „ከአደገኛው የፖለቲካ ዓለም ርቀው በምርመራ ብቻ ላይ እንዲሰማሩ“ ፣ የዛሬ ስንት ሺህ አመት ያነሳውን ምክርም እዚህ ላይ ማስታወስ ይስፈልጋል። ነገሩ በአጭሩ ፖለቲካ „አደገኛ“ ስለሆነ፣ ከእሱም ራቁ ፣ ብሎ ማክስ ቬበርም ፣ ኤፒኩርም ፣ ሁለቱም አስተማሪዎች፣ ተማሪዎቻቸውን፣ መክረዋል ። በምን ምክንያት?… ለምንድነው ፖለቲካ አደገኛ ነው የሚባለው?
ማክስ ቬበር „ሳይንስ እንደ ሙያ“ በሚለው፣ ለተማሪዎች በደረገው ንግግሩ ፣ „ምርምር …የጠለቀ ጥናት፣ በአንድ ጉዳይ ማካሄድና በእሱ ላይ ብቻ አተኩሮ፣ ወደፊት መጓዝ ምን ያህል ትልቅ ትረጉሙ፣ በሕይወት ላይ እንደሚያመጣና ምን፣ ያህል ዝናና ክብር፣ የማይሞት ስምም በዚህች ዓለም ላይ ማፍራት እንደሚቻል ፣ ለተማሪዎቹ፣ እሱ አስረድቶአል። „ሁለት ነገሮች ውስጥ፣ ገብቶ ከመዋኘት ፣ ከአንዱም፣ በመጨረሻ ስለማትሆኑ፣ አትግቡ“ የሚለውን ምክሩን አብሮ አቅርቦላቸዋል።
ያኔ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አደጋ እንዳለውም፣ ቬበር ያውቃል። ምን ዓይነት አደጋ?
እሱን ወደ በሁዋላ ላይ አነሳለሁ። ወደ ፖለቲካው እንደ ሙያ እንሂድ።
„ፖለቲካ እንደ ሙያ“ የሚለው እንደዚሁ ለሙኒክ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ቬበር ያደረገው ንግግር፣ „መጪውን ትውልድ፣ ከጊዜው ጥያቄ ጋር ነገር ግን“ በ1920 ጽሑፉን አሳትመው ያወጡት፣ ባለቤታቸው፣ በመግብያው ላይ እንደአስቀመጡት“ ጊዜ ሳይሽረው ወደፊት ለብዙ ትውልድ ለሚተላለፈው ለዘላቂው፣የፖለቲካ አሰራርና አስተሳሰብ፣ መሰረት፣ ምሁሩ፣ ለመጣል፣ አስቦም ነው።“
ይህ ጽሑፍ ለብዙ አመታት ተረስቶ የትም ወድቆ ነበር። ጥያቄው አሁን እኛን ከዘጠና አመት በሁዋላ ፣ ያ ጽሑፍ ዛሬ ምን ያስተምረናል? የሚለው ላይ ነው።
ቀደም ሲል፣ እንዳልኩት የ1917 እና የ1920 የጀርመን ሁኔታ፣ ከዛሬው ኢትዮጵያ ጋር በአንዳንድ ነገር „ተመሳሳይ ነው።“ … እነሱም ተወናብደው ነበር፣ እኛም፣ ስንወናበድ፣ ተወናብደናል…ይኸው ከአርባ አመት በላይ ነው። “
አንዱ የእሱ ተማሪ እንደዚህ አድረጎ፣ ጥሩ አድርጎ፣ የሰውዬውን ትምህርት ጠቃሚነት ደህና አሰቀምጦታል።
„በዚህ ሰውዬ አስተሳሰብ ሥር፣ ሾልኮ የሄደ ሰው፣ እሱ መጪውን፣ ጤናማና ጥርት ያለውን ጊዜ ፣ በደንብ ለማየት፣ አመች ዕድል ያገኛል። „ ብሎ ዮሴፍ ሹምፔተር ተደንቆ፣ ይህቺን ነገር ጣል አድርጎ አልፎአል። ዮሴፍ ሹምፔተር አንዱ የእሱ፣ የቬበር ተማሪ የነበር ሰው ነው።
ማክስ ቬበር በዚህች ትንሽ ንግግሩ፣ „….ፖለቲካ ማለት፣ ሌላ ነገር ሳይሆን፣ በአንድ ሥርዓትና መንግሥት ውስጥ፣ …መፍትሔ አቅርቦ፣ በዚያ ሐሳብ፣ ዙሪያ ሰውን አሳምኖ እነሱን መምራት ነው …“ይላል። ይህም ማለት እሱ፣ እራሱ ደጋግሞ እንደሚያነሳው፣ „…የሰዎች በሰዎች ላይ፣ ያላቸው የበላይነት ሁኔታ፣ እንዴት ይመሰረታል ? …እንዴትስ ይመጣል? „የሚለውን ጥያቄ በመጀመሪያ ለመፍታት ነው።።
አንድ መንግሥት ሳይፈረካከስ ቆሞ እንዲቆይ ከተፈለገም፣ ከጽሑፉ ላይ እንደምናነበው „ገዢው ክፍል፣ ተገዢዎቹን፣ …ተገዢዎቹ ደግሞ፣ በተራቸው ገዢዎቻቸውን፣ ፈቅደውና ወደው ተቀብለው፣ ´በእነሱ መገዛት ሲፈልጉ ነው፣`… „ ይላል።
መቼና እንዴት ነው?… ተገዢዎቹ ወደው፣ ፈቅደው፣ የገዢዎቻቸውን የበላይነት „አሜን“ ብለው የሚቀበሉት? ….ዕድሜ ልካቸውን ድረስ?… ወይስ ለተወሰነ አመት ብቻ?
…ለአጭር ጊዜ?
እንግዲህ በዚህ ጥያቄ በቀጥታ ወደ “ሌጋሲ”/legacy፣ ወደ „…የገዢዎቹን መደብ፣ ፓርቲ፣ ድርጅት፣ ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ፣ ግዙን ብሎ፣ ወደሚቀበላቸው ሁኔታ ውሰጥ….“ መልስ ፍለጋ ስንሄድደግሞ፣ እዚያ ውስጥ፣ የሚከተለውን ነገር እናገኛለን።
በቬበር ንግግር „ ገዢውም መደብ ሆነ ተገዢውም“፣ ሁለቱም ፣ ወገኖች„ አሜን“ ብለው ተቀብለው የሚተዳደሩበት– በማንኛውም ፣ ሕብረተሰብ ውስጥ– ሦስት የሌጋሲ፣ የሊጂትሜሽን/legitimation፣ መንገዶች አሉ ይለናል።
አንደኛው ፣ ሲውርድ ሲዋረድ፣ በዘልማድ ይሁን ወይም በተጻፈ ሕግ „በክብረ – ነገሥት“ ላይ እንደሰፈረው፣ የገዢው መደብ በውርስ መንግሥት፣ …ዘውዱና ዙፋኑን ከንጉሱ ወደ አልጋ ወራሹ፣ እሱ በተራው ለልጁ፣ የሚያስተላለፍበት፣ የዘውድ አገዛዝ ሥርዓት ነው።
ሁለተኛው፣ ጊዜ የወለደው፣ ጊዜ የሚወልደው፣ ባለ-ግርማ ሞገሱ፣… ጀግና አርበኛ፣ ወይም ጦረኛ፣ ወይም ደግሞ ተናጋሪ ነብይ፣… ብቅ የሚልበት ሥርዓት ነው።
ሦሰተኛውና የመጨረሻው ሥርዓት ደግሞ ፣ ሁሉም እኩል በሚቀበለው ሕግ ላይ የተመሰረተው፣ ከዲሞክራሲ የምርጫ ሥርዓት በአሸናፊነት ተመርጦ የሚወጣው፣ የሥልጣን ዘመኑ የተገደበ፣ መሪ ነው።
ባለግርማ ሞገሱ፣ በአንደኛውም፣ ሆነ በሦስተኛውም ሥርዓት ውሰጥ፣ ብቅ የሚል „ልዩ ስጦታ ያለው ሰው“ ሊሆንም ይችላል። ይህ ፍጡር ሰፋ ያለ ጥናትና ቦታ የሚወስድ፣ ፖለቲከኛ ነው። ግን አንድ ማለት የምንችለው ነገር ቢኖር፣ ይህ ሰው፣ በትልቅ አድናቆት የመጣውን ያህል፣ ተዋርዶም ከሥልጣኑ የሚባረር ሰው ነው። እሱን ለጊዜው እንደገና፣ እዚህ ላይ እናሳድረው።
*
———————————————————
ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements > Le’Aimero’s Disclaimer