ርዕስ አንቀጽ
ከጣረ፥ሞት እስከ „ቅዱስ ነገር“፤ አፍሪቃም! ሃምሳ ሆነን!
5 0
አንዳች ጣረ፥ሞት፣ አንድ አጋንንት፣ ጭራቅ መሳይ አስፈሪ ፍጡር፣ በአውሮፓ ላይ ያንጃብባል። የዚያ!አስፈሪ ጭራቅ ስሙ ደግሞ– ካርል ማርክስና ፍሬደሪሽ ኤንግልስ፣ ሁለቱ ተስማምተው፣ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን፣ እንደሰየሙትና ያኔ የዓለምን ሕዝብ፣ በዚህ ትምህርታቸው፣ ሁለቱ ምሁሮች፣ ለማስደንግጥ፣ እንደ ሞከሩት– ስሙን “ኮምኒዝም“ ብለው፣ ሰይመውታል።
በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ፣–የበርሊን ግንብ ከወደቀ ወዲህ፣ “ሊበርቲ”፣ ነጻ-ሕዝብ፣ ነጻ -ዜጋ፣ ነጻ ሕብረተሰብ የሚባለው፣ „ቅዱስ ነገር“፣ እየተስፋፋ መጥቶአል።
ካርል ማርክስና ፍሬደሪሽ ኤንግልስ ስለሚሉት፣ አንቀጥልበት።
ያሉትም ይደርሳል። በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በጥቂት አመታት፣ ይህ አዲስ ትምህርት፣ ኮሚኒዝም፣ ከጀርመን ተነስቶ ሩሲያ ይገባል። እዚያም የአምባገነን ሥርዓቱን ዘርግቶ፣ በደንብ…ገንብቶ፣ የብዙ ሰውን ሕይወት አጥፍቶ ወደ ቻይና ይወርዳል። ከዚያም ወደ ቬትናም፣ ወደ ካምቦጂያ፣ ላኦስና ፔቲት ኢንዶቺና፣ ራመድ ብሎም ወደ ኢንዶኔዠያና ወደ ፊሊፒን ይዘልቃል።
ፊቱን አዙሮም፣ ውቅያኖስ አቋርጦ ላቲን አሜሪካም፣ ሳይታሰብ ገብቶ፣ እዚያም አተረማምሶ ኪዩባ ላይ ቤቱን ሰርቶ ጉብ ይላል። አፍሪካም በአልታወቀ መንገድ አቆራርጦ፣ ከተፍ ይላል። መካከለኛውን ምሥራቅም ይጎበኛል።
ከቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ነጻ -የወጡና ለመውጣት የሚፈልጉ አገርና መሪዎቻቸው፣ ተማሪና አስተማሪዎች፣ ይህን አዲስ ሐሳብ፣ አዲስ ፍልስፍና እና ትምህርት፣ የኮሙኒዝምን ሥርዓት፣ ሳይጠይቁ፣ ሳያመዛዝኑ፣ ሌላው ዓለም እንዴት በሥራ ተተረጎመው? ብለው ሳይመረምሩ፣ ዝም ብለው ቀድተው፣ የእኛዎቹ፣ አፍሪካውያኖቹ፣ እንዳለ ገልብጠው፣ ቤተ መንግሥት ሰተት ብለው፣ መጽሓፉን እያገላበጡ፣ እዚያ ይገባሉ።
ገብተውም፣ ትምህርቱ፣ የአምባገነን ሥርዓት ዘርግቶ፣ አንድን ሕዝብ፣ በጥይትና በጅራፍ አስፈራርቶ ለመግዛት አመች፣ ሰለሆነ፣ ይኼው አሥር – አመት( እሱዋማ ምን አላት) የለም፣ ሃያና ሰላሳ፣ አርባና…ከዚያም በላይ „እንደ ገል ቀጥቅጦ፣ እንደ አፈር ፈጭቶ“፣ እኛን አፍሪካውያኖቹን፣ ለመግዛት፣ የሰጠ ስለሆነ፣ “ተራማጅ „እራሳቸውን እያሉ፣ „አብዮተኛና ነጻ-አውጭ“ እያሉ፣ እራሳቸውን፣ ተራውን ሕዝብ እየደለሉ፣ ከንጉስ ያላነሰ፣ሥልጣን ይዘው፣ ለልጅ ልጆቻቸውም፣ ማውረሳቸውን ቀጠሉበት ።
ልቀቁ ቢባል አይለቁም። እነሱን እንደምንም ብለው ያስለቀቁት „ድርጅቶች“ ደግሞ በተራቸው፣ ዙፋኑ ላይ ጉብ ብለው፣ አሁንም ትምህርቱ፣ ለአምባገነን ሥርዓት፣ መቼም የሰጠ ስለሆነ፣ እየገረፉ፣ እያዋከቡ፣ እያሰሩና እያሳደዱ፣ ሃያ ሰላሳ፣ አርባ ማለታቸውን ቀጥለውበታል።
የዓለም ሁኔታም ለእነሱ አመችቶአል።
ከእነሱ ጎን የቆሙት ኃያላን መንግሥታትም፣ በፈለገው ስም ያ ! አምባገነን መሪ፣ ጀሌዎቹን አሰልፎ፣ ድርጅቱን ጭምር አዋቅሮ፣ እጉያቸው እስከሆነ ድረስ፣ ያንን ሕዝብና አገር እንደፈለገው ይግዛው፣( ይህ ለእነሱ ምንም የራስ ምታት አያመጣባቸውም፣ „ትንሽ ያሳስበናል“ ማለት ይችሉበታል፣ እሱንም ማለት ያውቁበታል) የእነሱን ጥቅም እስከ ጠበቀ ድረስ እነሱ፣ የዱሮ ሰው እንደሚለው፣ ምንም „ዴንታም“ የላቸውም።
አፍሪካ „እንደ አህያ እርስ በእራሱ ቢራገጥ፣ ጥርሱ፣ ምንጊዜም አይረግፍም „ የሚሉ ናቸው። ተፈረካክሶ ቢወድቅ ደግሞ፣ አይጨንቃቸውም። መፍትሔ ፥ መድሐኒት ያላቸው ይመስላል።
ይኸው እንግዲህ አፍሪካን ቅኝ ገዢዎቻቸውን ጥለው ከወጡ ስድሳ አመቱ ነው። ብዙም ነገር ለአህጉሪቱ ያመጣላታል ተብሎ የተመሰረተውም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ከተቋቋመ ሃምሳ አመቱ ነው።
ኢትዮጵያም „ነጻነቱዋን“ ጠብቃ ከኖረች፣ ሦስት ወይም አራት አምስት ሺህ አመቱዋ ነው።
ኤርትራም፣ ከኢትዮጵያ „ቀንበር ነጻ-ከወጣች“ እነሱ እንደሚሉት ይኸው፣ ከሃያ ሦስት አመት በላይ ነው። ሁሉም የአፍሪካ መሪዎች፣ በግዛት ዘመናቸው ለመሆኑ ምን አመጡልን?
በአለፉት ሃምሳ አመታት ሰባዊ መብቶችን እንዲከበሩልን አደረጉልን? ዳቦና ሥራ አዘጋጅተው አቀረቡልን? ለአባቶቻችንና ለእናቶቻችን የጡረታ መብታቸውን አሰከበሩልን?….ትምህርትና ዕወቀትን አሰፋፉልን? ሕክምና እንዴት ነው? ሐሳብ መግለጽ ይፈቀዳል? በአገራችን መጻፍ፣ መናገር፣ መስብሰብ፣ መደራጀት፣ መቃወም፣ መምረጥና መመረጥ፣ ለአንድ ሰው ፣ በገዛ አገሩ ይፈቀድለታል?…. ስደቱስ፣ በሰው ሃገር ባገልጋይነትና ብግርድና እንዳውም ይበላችሁ ተብለን፣ እንድከብት የባለጸጋዎቹ የህክምና ሆድእቃ መለዋወጫ መሆኑስ፣ ኧረ ምኑ ቅጡ!
ማነው የመሥራት፣ የመነገድ፣ የመሸጥና መለወጥ መብትና ዕድል ያለው? የግል ሐብትስ ለሁሉም ይፈቀዳል?
ይህን ሁሉ ጥያቄ እናንሳ እንጂ፣ በጋና እና በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካና በናይጄሪያ ፣ በግብጽና በቦትስዋና፣….ጋዜጣዎች፣ ይታተማሉ፣ ሐሳቦች በነጻ ይንሸራሸራሉ፣ ነጻ -ምርጫ በእነዚያ አካባቢ ይካሄዳል፣ ጠበቃ ገዝቶ መከራከር ይቻላል። በዘር፣ በጎሣ፣በመደብ፣…በጂኒጃንካ እነሱ እንደኛ አልተከፋፈሉም። ለምን?
እኛን ግን ምን ነካን?
ጊዜው እንደሚባለው የእስታሊን „ብሔር-ብሔረሰብ እሰከመገንጠል ድረስ“ ሳይሆን፣ ጊዜው፣ የበርሊን ግንብ ከፈረሰ ወዲህ፣ የነጻ እና የግለሰብ፣ የሰብዓዊና የዲሞክራቲኪ፣መብቶቹ ሁሉ የተከበሩበት፣ ሥርዓት የሚመሰረትበት ጊዜ ነው። የስታሊን የኮሚኒዝም ዘመን፣ በዓለም ደረጃ አልፎበታል።
——-
© ለ አእምሮ 2005 / © Le’Aimero Copyright 2013
*
———————————————————
ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements > Le’Aimero’s Disclaimer