ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት
የኢትዮጵያ ባህልና ሥልጣኔ አነሳሱና አመጣጡ
….. እኛ ማን ነን?
የኢትዮጵያ ባህልና ሥልጣኔ አነሳሱና አመጣጡ (PDF)
ክፍል ሁለት
፩
በአዋጅ የክርስትና ሃይማኖት የአገሪቱ የኢትዮጵያ ዋና መመሪያ ሃይማኖት ሁኖ ለአራት መቶ አመታት፣ በተከታታይ በአገለገለበት በክርስቲያኑ ንጉሥ፣ በአሸማ ዘመን፣ የመጀመሪያው የነብዩ መሐመድ ተከታዮች፣ነፍሳቸውን ለማዳን ፣ በነብዩ ምክር ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው፣ ስደትና ጠለላን፣ እንክብካቤም ጭምር ጠይቀው ፣ የመጀመሩያውን የሞስሊሞች መንደር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይቆረቁራሉ። ቁጥራቸው ትንሽ ነበር።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ፣ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ደግሞ፣ መንደራቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ የዘረጉት፣ የቆረቆሩት ማለት እንችላለን፣ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን፣ ብዙም ሳይቆይ በቀጥታ ከክርስቶስ ልደት በሁዋላ ነው።
የክርስትና ሃይማኖት፣ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ የገባው በሁለት መንገድ ነው። እምነቱን አምጥቶ ያስተዋወቀው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደሰፈረውና አሁንም ድረስ ማንበብ እንደሚቻለው፣ የንግሥቲቱ የእቴጌ ካንዳኬ የግምጃ ቤት ኃላፊ የነበረው፣ እየሩሳሌም ላይ በዲዯቆኑ በፊሊፖስ ከተጠመቀ ወዲህ ነው። ይህ ሰው፣ ሠረገላ ውስጥ ተቀምጦ፣ የነቢዩ ኢሳያስ መጽሐፉ ላይ እንደሰፈረው፣ ትንቢት ሲያነብ፣ መልአኩ ወርዶ ፊሊፖስን እንዲያነጋግረው ያዘዋል።…..እሱም ጃንደረባው የክርስቶስን ቃል ተቀብሎ እዚያው ተጠምቆ ክሪስተያን ይሆናል። „…የአመነ የተጠመቀ፣ የእግዚአብሔርን ቃል የተቀበለ“፣ ይህ እራሱ፣ እንደዚህ ዓይነቱ፣ እርምጃ ምን አይነት ሕብረትና አንድነት፣ ከዚያም አልፎ መተሣሰርን በሰው ልጆች ዘንድ፣ በእነሱ መካከል እንደሚያመጣ፣ መገመቱ ከባድ አይደለም ።
ይህ ሃይማኖት፣ ኢትዮጵያ ደርሶ፣ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ፣ በየመንደሩ ተስፋፍቶ፣ አገሪቱን ሁሉ አዳርሶ በመጨረሻው የሕዝቡ እና የንጉሠ ነገሥቱ ፣ በሰላም የአገሪቱም፣ ልዩ መለያ ሃይማኖት ሁኖ የወጣው፣ በንጉሥ ኢዛና ዘመን መንግሥት፣ በ330 ዓመተ ምህረት ላይ ነው። በዚህም የምዕራቡን ዓለም –ሌሎቹማ ትላንትና ነው ተጠምቀው ክርሰቲያን የሆኑት – በተለይ የሮምን መንግሥት ቀድመን እኛ የክርስትና ሃይማኖት ተቀብለን፣ የዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ ብቻችንን ብቅ ብለናል።
ሮም የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበለቸው፣ የሕዝቡዋም ሃይማኖት ያደረገቺው፣ አርፍዳ፣ በ391 ዓመተ ምህረት ላይ ነው።
ይህ ሁኔታ ደግሞ፣ አውሮፓያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ይዘው ሌሎቹን የአፍሪካና የእሲያን ወንድሞቻችንን „አጥመቀው“፣…አታለው፣ አገራቸውን ወረው ባሪያ ሲያደርጉ፣ እኛን ለመያዝ፣ የምናውቀውን የክርስቲያና ትምህርት፣ መልሶ ለማስተማር፣ ፈጽሞ ሰሚ ጆሮ ኢጥዮጵያ ውስጥ አጡ። እንዲያውም ፈልገው አላገኙም። ሰውም ሰብስበው ለመያዝ አልቻሉም። ጥርስ ግን፣ አንዳዶቹ ነክሰውብን፣ ኢትዮጵያን ለመያዝ በጦር ታጅበው መጥተዋል።
ግን ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ከክርስትና ሃይማኖት ጋር ተዋወቀች እንላለን እነጂ፣ እራሱ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ማሪያምና ከዮሴፍ ጋር ተሰዶ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከርሞ ፣ እንደሄደም ቤተ-ክርስቲያናችን፣ ኮርታ በደንብ፣ ታስተምራለች።
ይህን አሁን እናንሳ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ከአንዱ ኃያል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር የተዋወቀችው፣ አንድ ሺህ ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። እሱም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተጻፈውና ኢትዮጵያም ከተቆረቆረችበት፣ ከተመሰረተችበት አፈ-ታሪክ፣ እሱም ላይ በትክክል እንደሰፈረው፣ (አይዞአችሁ!… ሁሉም ሕዝብና ሁሉም መንግሥታት የእራሱ የሆነ አፈ ታሪክ አለው፣ …. ሮምን የቆረቆሩት ሁለቱ ወንድማማቾች፣ ሮሚዎስንና ሮሙለስን፣ አንዲት ተኩላ ናት ይባላል ጡዋት ማታ ጡትዋን ሰጥታ አጥብታ ያሰደገቻቸው፤ ይህንንም ጣለያኖች ኮርተው ይተርካሉ፣… የሌሎቹንም የአመጣጥ ታሪክ ጊዜ ከአላችሁ፣ አገላብጣችሁ ተመልከቱ…) በንግሥት ሳባ ዘመን፣ በንጉሥ ሰለሞን ጊዜ ነው።
፪
በዕውቀቱ ተደንቃ ይላል መጽሐፉ፣ በጥበቡ ችሎታ ተገርማ ይላል፣ ይኸው ማንም የማይደርስበት የኢትዮጵያ ሚቶሎጂ፣ በሥነስርዓቱ የሰፈረበት „ ክብረ ነገሥት“ የሚባለው፣ መጽሐፋችን፣ ያቺ ወጣት ንግሥት፣ ብድግ ብላ ወደ እየሩሳሌም ወረደች ይለናል።።
ንግሥት ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም ወርዳ እዚያ ሰንብታ ስትመለስ፣ ዕውቀት ና ጥበብ ብቻ ሳይሆን ወንድ ልጅም ጸንሳ ትመለሳለች። ስሙንም ምንልክ ቀዳማዊ ትለዋለች። ምንልክ አድጎ አባቱን ሰለሞንን ለማየት፣ በሃያ አመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይወርዳል። ከዚያ ይዞልን የመጣው — ይህ ነው ወሳኙ ቦታ–ኢትዮጵያ አገራችንን ከሌሎች ሕዝቦች ታሪክ ሁሉ፣ እንደገና ፍጽም ልዩ የሚያደርጋት፣ አድርጎአትም እስከ አሁን ጊዜ ድረስ ያቆያትን ( ይህን ከአውቀንበት ደግሞ፣ እንደ ዓይን ብሌናችን ከጠበቅነው፣ እስከ ዘለዓለሙም ድረስ፣ ልዩ አድርጎ የሚያቆያትን) የትም የማይገኝ ምርጥ ሐብት፣ ይህ ወጣት ምንሊክ ከኢየሩሳሌም ይዞልን ተመልሶአል።
ዛሬ ዋናው ታቦቱ፣ ምንልክ ያኔ ይዞት የመጣው የሙሴ ጽላቱ፣ አክሱም ጽዮን ተቀምጦ ከ50 ሺህ የሚበልጡ የተባረኩ ቅጂ ታቦቶች፣ ደግሞ በኢትዮጵያ ምድር፣… በኤርትራም በሁሉም ቦታ በአገራችንን ሜዳና ሸንተረር (ዕብዶች እየተሳለቁ የሚሉትን ጨርሶ አትስሙ) ተተክለው፣ ተበትነው ይገኛሉ። እንደሸረሪት ድር፣ እንደ አጥር እንደ ማግና ድር፣ አንድ ላይ ሰብስቦ እኛን ያኖረን።
ኢትዮጵያ ብቻ ናት በንግሥት ሳባና በቀዳማዊ ምንልክ ጊዜ አገራችን ከገባው ከአይሁድ ሃይማኖት በቀጥታ፣ መጽሐፉ ላይ እንደሰፈረው፣ ወደ ክርስትና ሃይማኖት የተሸጋገረቺው።
ከአራት መቶ የክርስትና ሃይማኖት ዘመን በሁዋላ ነው፣ እንግዲህ፣ ነቢዩ መሐመድ „እኔ እስከምጠራችሁ ድረስ ወደ ኢትዮጵያው ርህሩህ ንጉሥ ሂዱ፣ እሱ እናንተን ተቀብሎ እምነታችሁና አስተሳሰባችሁ ሳይረብሸው፣ ያስተናግዳችሁዋል፣ ይጠብቃችሁዋልም፣“ ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ያኔ ሚስቱንና ልጁን፣ ከእነሱም ጋር ወጣት ተከታዮቹን የላካቸው።
ተቻችሎና ተከባብሮ ፣ ተደማምጦና ተነጋግሮ አብሮ መኖርን፣ ለየት፥ያለ አመለካከትና ለየት፥ያለ እምነትን ማንም ሰው፣ እንደ መብቱ እንደፈለገው መከተልና ማምለክን አንደሚችል፣ ከኢትዮጵያው ንጉስ … ከእሱ፣ ስደተኞችን ተቀብሎ ከማስተናገድ እርምጃ፣እኛ ዛሬ መመልከት እንችላለን። እንደዚህ ዓይነቱን አብሮ የመኖር ጥበብ ንጉሡ ከየት አመጣው? እንደዚህ ዓይነቱን የአስተዳደር ብልሃትና ዘዴ ማን አስተማረው?
እንደዚህ ዓይነቱ የአስተዳደር ጥበብና ዕውቀት፣ የግድ ከውጭ መምጣት የለበትም። የሚያስቡ የሰው ልጆች ከተንቀሰቃሽ ሕይወት ከዚያም፣ ከሚያገኙት ተመክሮና ልምምዶች እራሳቸው፣ በቂ ትምህርት ቤቶች፣ እነሱ፣ ስለሆኑ፣ ብዙ ዕውቀቶችን አባቶቻችን እንደሰበስቡ መገመት ይቻላል።
፫
ግን በአባቶቻቸው ሥራ የማይተማመኑትን ጠርጣሪዎች ለማረጋጋት፣ ከሁለት ቦታ፣ ይህ ዕውቀት ከውጭም መጥቶአል ብሎም መናገር ይቻላል።
አንደኛው ፣ ጽላቱ ላይ ፣ እኛ ዝቅ ብለን የምንሰግድለት ታቦቱ ላይ፣ እንደተጻፈው፣ „ ….አትግደል፣ አትስረቅ፣…እናትና አባትህን አክብር…“ይላል። ይህን ቃል፣ ይህን ሕግ፣ ሕግ- አክባሪዉ (የዛሬውን ካድሬ ድርጊት ለጊዜው እንርሳ) የኢትዮጵያ ሕዝብና ነገሥታት፣ ያከብራሉ፣ የፈጣሪያቸውም ትዕዛዝ ስለሆነ ይከተላሉ።። በማክበራቸውም፣ ለየት ያለ ሐሳብና እምነት የሚከተለውን፣ እንግዳም ቢሆን ጥሩ አድርገው፣ ያስተናግዳሉ።
ሁለተኛው ፣ አማኙ የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ ነገሥታቶች፣ ተቀብለውት የሚተዳደሩበት፣ እንደ መመሪያቸውም አድርገውም ለረጅም አመታት የሚመሩበት ነገር አለ። እሱም፣ ረፈድ ያለው፣ የጥንታዊው ቤተክርሰቲያን አስተማሪ ፣ አጉስቲኖስ ስለ መልካም አስተዳደር ከማስተማሩ በፊትና ፣ ይህን የሚቀጥለውን ቃል ከመናገሩ በፊትም ፣ የአስተዳደር ሰዎች በኢትዮጵያ የተቀበሉትም ትምህርት አለ። አሱም፣ በአጭሩ ንጉሥ ሰለሞን የአባቱን ዙፋን ወርሶ ቅባ ቅዱሱን ከመቀባቱ በፊት እግዚአብሔርን ለምኖት፣ ያገኘውም፣ እንደተጻፈው፣ ጸጋ ነው።
የአጉስቲኖስ ቃልና ትምህርትን እናስቀድመው። „….የአንድ ሕዝብና መንግሥት፣ የሁሉም መተዳደሪያ ደንብ የሆነውን ሕግ፣ አንድ ሰው፣ ወይም አንድ ቡድን ያንን ሕገ-መንግሥት ሸሮ፣ የእራሱን፣ ለእራሱ ብቻ የቀደደውን ሕግ ተክሎ፣ የነበረውን ሥርዓቱን እንዳለ አጥፍቶ፣ የእራሱን አዲስ ሕገ ወጥ አዋጅ በአገሪቱ ላይ ከአወጀ፣ ይህ መንግሥት፣ ከዘራፊ ሽፍቶች፣ ሥርዓት ከሌላቸው ወረበሌች፣ ከጨረባ ተዝካር ምንም የምለየው ነገር የለም…“
ያለው አነጋገር ፣ አገራችን ኢትዮጵያም፣ እንደዚህ ዓይነቱ፣ አስተሳሰብ ሰርጎ እንደገባም መገመት ይቻላል። እንዴት?
አንደኛው መንገድ በግሪክ አስተማሪዎች- ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው- ወደ ኢትዮጵያ መግባትና እና ግሪክ አገር ወርደው፣ ፍልስፍና ታሪክ፣ ሒሳብና የሕንጻ ሥራ፣… በተማሩ ተምረውም በተመለሱ፣ ኢትዮጵያኖች በኩል ነው።
ሁለተኛው ከአይሁድ ሃይማኖት ትምህርት ጋር ወደ አገራችን የገባው የዳዊት መዝሙር፣ የነብያት ጽሑፍ፣ ኦሪት ዘፍጥረት፣ እንበለው፣ እነዚህ ሁሉ ቀላል ነገሮች አይደሉም። መልካም ሥነ-ምግባር፣ ኤቲክና ቀና አመለካከት የሚመነጩት አፍልስፍና ትምህርት ብቻ ሳይሆን፣ ከሃይማኖት ትምህርትም ነው።
ንጉስ ሰለሞን፣ የቀዳመዊ ምንልክ አባት፣ ቅባ ቅዱሱን ተቀብቶ ዘውዱን ከመድፋቱ በፊት፣ መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ ፫ ላይ እንደምናነበው –ይህ የሚከተለው አረፍተ ነገር ቀላል አይደለም– እግዚአብሔር በሕልሙ ተገልጦለት“…ምን ዓይነት ነገር መርቄ እነድሰጥህ ትገልጋለህ?“ ሲለው ወጣቱ ሰለሞን ከፈጣሪው ከአምላኩ የተመኘው፣
ትምህርት፣ ትልቅ ትምህርት፣ ፖለቲከኛ ለመሆን ለሚፈልግ አንድ ሰው ፣ ወይም ደግሞ ነኝ ብሎ ለቆመ ሰው፣ ግሩም ትምህርት የሚሰጥ ስለሆነ፣ እንዳለ መልሼ እዚህ ላይ አነሳለሁ። እጠቅሳለሁ።
ሰለሞን፣… ሐብትን፣ ዝናን፣ ረጅም እድሜን፣ ጠላቶቹን የሚያጠፋበት ጠንካራ ክንድና ጠንካራ ጦር እግዚአብሔር፣ እንዲሰጠው አልተመኘም።
ይልቅስ: የጠየቀው ይህን ነው። እንደዚህ አለው:-
„….አቤቱ አምላኬ ሆይ ፣ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኽኛል። እኔም መውጫዬንና መግብያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ። ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ፣ ስለ ብዛቱም ይቆጠር ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው። ስለዚህም ሰምቶ በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው። አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ ማን ይችላል?“
መጽሐፉ በዚህ ጥሩ ምሳሌ ኃላፊነት ተቀብለው አንድን ሕዝብ፣ አንድን የቆየ ጥንታዊ አገር ለመምራት ለሚፈልጉ ፖለቲከኞች ለማስተማር የፈለገው፣ የአንድ ፖለቲከኛ ፣ ዋና ዓላማ በሥልጣን ባልጎ የግል ሐብትን ማካባት፣ ዝናና እን ሹመትን ማዳበር፣ ተንኮልና ጥላአቻን በሰው ልጆች ዘንድ መዝራትን ….ሳይሆን፣ ክፉና ደግን ለይቶ፣ ሕዝብና አገር አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ ፍትህንና ፍርድን አምጥቶ፣ ሰላምን ማስፈንና ማሽጸዳደር እንደሆነ፣ እላይ ከጸጸረከ ታሪክ እንመለከታለን።
አንድ ሺህ አመት ከንጉሥ ሰለሞን ዘመን በሁዋላ ደግሞ፣ ወደ አገራችን የመጣው የክርስትና ሃይማኖት ደግሞ፣ ስለ ፍቅር፣ ስለወንድማማችነት፣ ስለአንድነት፣ ስለሰላም፣ ስለ ነጻ ሰውና ስለነጻነት፣ እነዚህ ሁሉ ምን እነደሆኑ፣ በሰፊው ያስተምራል። ከዚያም አልፎ፣ ጠላትህን ሳይቀር ውደደው ይላል። ከዚያም ትምህርት ኢትዮጵያ ብዙ ወስዳለች።
ሕግና ሥርዓት፣ ሰብአዊ መብት የማይከበርበት፣ ነጻነት የሌለበት፣ ሃይማኖት የጠፋበት ቦታ፣ ምን ዓይነት አሰቃቂ ወንጄሎች በሰው ልጆች ላይ እንደተፈጸሙ፣ እሩቅ መሄድ አያስፈልግም፤ የ20 ኛውን ክፍለ-ዘመን ወንጀልን፣ መለስ ብሎ በተለያይ አገሮች መመልከት በቂ ነው።
በግሪክ ፍልስፍና፣ በአይሁድ ሃይማኖት፣ በክርስትና ትምህርት አገራችን ኢትዮጵያ እነዘህን ሶስቱን፣ የተለያዩ ግን ደግሞ የተወራረሱ፣ አመለካከቶች ጨፍልቃ በአእምሮ ደረጃ የእራሱዋ አድርጋ ትመራ ነበር። በሁዋላ እንዳየነው የእስልምና ሃይማኖት ቀስ እያለ እየተስፋፋ ከአገሪቱ ሁኔታ ጋር እራሱን ያስተዋውቃል።
ይህም ሃይማኖት ልክ እንደ ክርስትናውና እንደ አይሁዱ ሃይማኖት፣ ኢትዮጵያ ሲደርስ ከአርብ አገሮች የተለየ – ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው አካሄዱን ይዞአል። አለባበሳቸውን ማየት ይበቃል። አመጋገባቸውን፣ እራሱ መጠጣቸውን፣ ከዚያም አልፎ ትዳራቸውን፣ ልጆች አሰተዳደጋቸውን…እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ከአረቦቹ ጋር ማነጻጸር ያስፈልጋል።
ልክ በኢትዮጵያ ክርስቲያንና በአውሮፓ ወይም በአፍሪካ ክርስቲያኖች መካከል ልዩነት እንዳለ ሁሉ፣ በአረብ አገር እስላሞችና በኢትዮጵያ ሞስሊሞች መካከል ትልቅ ልዪነት በሁለቱ መካከል አለ። በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ አይሁዶችና በሌላው ዓለም በሚገኙ አይሁዶች መካከል እንደዚሁ ትልቅ ልዩነት እናያለን። ከአንድ ምንጭ የተቀዱ፣ ከአንድ ቦታ የፈለቁ ባህልና ሥልጣኔ፣ ሌላ አካባቢ ሲደርሱ፣ ከቦታ ቦታ ይለያያሉ፣ የሚባለውም ለዚህ ነው።
፬
እነዚህ ሦስቱም አራቱም ሃይማኖቶችና እምነቶች (አራተኛው የግሪኮች ፍልስፍና ነው፣ የፋርሱ፣ ዛራሁስተስ፣ ኢትዮጵያ ገብቶ ነበር የሚሉ ጸሐፊዎች አሉ) ምንም እነኳን በክርስቲያን ሃይማኖት ሥር ተቻችለውና ተከባብረው ጎን ለጎን ቢኖሩም፣ ሁለት ጊዜ በተለያዩ ዘመናት እነዚህ ሃይማኖቶች፣ እኔ እሻላለሁ፣ እኔ እበልጣለሁ ብለው ጦርነት ከፍተው፣ ተናንቀው ሕዝቡን አፋጅተዋል። ጥንታዊ ቅርሶችን አውድመዋል።
የእስልምና ሃይማኖት ኢትዮጵያ ገብቶ ቀስ እያለ ሰባት መቶ አመት ከተስፋፋ በሁዋላ በመካከለኛው ክፍለ-ዘመን ኢማም አሕመድ ኢብራሂም፣ ግራኝ መሐመድ ወይም አሕመድ ግራኝ ፣ በእሱ መሪነት በቱርኮች ድጋፍና መሣሪያ ብርታት፣ በሠይፍና በእሳት አገሪቱን ወደ እስላም ሃይማኖት ቀይሮ „የሻሪያን ሕግ በሱዳን በሱማሌና በኢትዮጵያ“ ይህ ሰው፣ ለመዘርጋት ተነስቶ ነበር።
ልክ የአይሁድ ሃይማኖትን በኢትዮጵያ መልሶ ለማቋቋም፣ በአሥረኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ተነስታ፣ በደረሰችበት ቦታ ሁሉ ገዳሞችንና ቤተክርስተያንን ፣ መጽሐፍት ቤቶችንና ትላልቅ ቤተ መንግሥቶችን፣ ጥንታዊ ከተማዎችንንና መንደሮችን፣ እሳት ለኩሳ እንዳቀጠለችው „ዮዲት ጉዲት“፣ ግራኝ፣ የነብዩ መሐመድን ቃል ጥሶ፣ ድፍን ኢትዮጵያን እስላም ለማድረግ፣ በደረሰበት ቦታ ሁሉ እሳት እየለቀቀ፣ እንደገና ፈልገን የማናገኛቸውን ታሪካዊ ቅርሶች፣ እነዚህ ሁለት ጦረኞች፣ እኩል አጥፍተዋል። እንኳን እነሱ የእነ መንግሥቱ ኃይለማሪያምም ካድሬዎች አዲስ አበባ ላይ መጽሐፍቶችን – አሁን ከአልተረሳ አቃጥለዋል።
ግን ያ ሁሉ ሁኖ፣ ሁለቱም ሶስቱም ሃይማኖቶች፣ ከዚያ በሁዋላ፣ ለአለፉት አምስት መቶ አመታት ተቻችለው አብረው ኖረዋል።
እስከአሁን ድረስ መለስ ብዬ የኢትዮጵያን ባህልና ሥልጣኔ ወሳኝ ሁነው በአገሪቱ ላይ፣ እስከ 20ኛው ክፍለ – ዘመን አጋማሽ ድረስ፣ ኮሚኒዝም የሚባለው ፍልስፍና እና ትምህርት፣ ይህን የወጣቱ ትውልድ ሃይማኖት ልንለው እንችላልን፣ አገራንችን ገብቶ፣ ከመስፋፋቱ በፊት፣ ማህተማቸውንና አሻራቸውን በኢትዮጵያ ጥለው የሄዱ(!) ምሶሶዎች
ብዬ የአነሳሁአቸው፣ አበይት ነገሮች፣ ሁለት ናቸው።
አንደኛው፣ ለማስታውስ ከሶስት ሺህ አመት በላይ በተከታታይ የአንድነት ምልክት ሁኖ የቆየው ዘውድና፤
ሁለተኛው፣ እንደዚሁ ከሶስት ሺህ አመት በላይ በኢትዮጵያ ሥር ሰዶ ባህላችንን የወሰነው፣ የአንድ አሃዱ አምላክ፣ ሃይማኖት ነው። ይህ ሃይማኖት የሞራል ኮዶችን፣የኤቲክ መስመሮችን፣ ጥሎልን ሄዶአል።
በዚህ አቀራረቤ ከአድማጮቼ ወይም ከአንባቢዎቼ ከመሰናበቴ በፊት፣
ሦሰተኛውን ፣ የኢትዮጵያ፣ ባህልና ሥልጣኔ እንደዚሁ ለረጅም ሺህ አመታቶች ያጀበውን ተጨማሪ ምሶሶ እንዳይረሳ፣ እንደዚሁ አሁን አነሳለሁ።
እሱም፣ ለእናት አገራችን ለኢትዮጵያ ያለን፣ እስከ ሞት መስዋዕትንት የሚያደርሰውን ፍቅር ነው። ይህም ፍቅር ተበጥሶ እንዳይጠፋ፣ በተከታዩም እንዳይረሳ፣ በሥነ – ሥርዓቱ እንድ ልጅ ሲወለድ፣ በተወለደ በአርባ ቀኑ የሚወሰደውን፣ እርምጃ ነው።
ከወላጅ እናቱ ጋር የሚያስተሳስረውን እትብታቡን፣ ከተወለደ በሁዋላ ከእናት አገሩ መሬት ጋር መተሳሰሩን የሚያረጋግጠው፣ ቃል-ኪዳን ነው። ይህም፣ በመጨረሻ እትብታቡ የተቀበረበት ቦታ ሰውዬው/ሴትዮዋ መቀበር አለበት የሚለው ውሳኔ ነው። የልጅ እትብታብ፣ የተወለደበት ቦታ ይቀበራል። ለምን?
ያ ማለት፣ እትብታብህ የተቀበረበት፣….አገርህን ፣ ድንበርህን፣ ግቢህን፣ መሬትህን፣ ዘመድና ቤተሰብህን፣ ደብርና ገዳምህን፣ ቅዱስ የጸሎት ቤትህንም፣ እርሻህንና ከብትህን፣ ዱርና ገደሉን ጫካውንና ሜዳውን፣ ባሪያ አድርጎ ሊሸጥ ከሚመጣ ጠላት ፣ በጦርና በጋሻህ፣ በክንድህና በጭንቅላትህ፣ በደምህ ፣ በሕይወት እስከ አለህ ድረስ፣ ጠብቀው ማለት ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በውጭ አገር በስደት ሆነ በሥራ፣ ትዳር መሥርተው ልጆች ወልደው የሚኖሩ ቤተሰቦች፣ የልጆቻቸውን እትብታብ፣ ኢትዮጵያ ድረስ አምጥተው እንደ አባቶቻቸው ይቀብሩ እንደነበር አውቃለሁ። አሁን ማነው የሚጨነቅላት?
ሦስተኛው አገሪቱን አንድ አድርጎ የያዘው ምሶሶ „…መገንጠል፣ ከኢትዮጵያ፣ ግዛትና መንግሥት መገንጠል …“ የሚባለው ፈለጥ ሳይስፋፋ፣ ከዚያ በፊት፣ „ የአገር-ፍቅር“ የሚባለው፣ ትምህርት ደማችን ውስጥ ገብቶ ነበር። ዛሬ ግን በብዙዎቹ፣ ዘንድ ይህ ነገር መቀለጃ ሁኖአል። ለምን? ምን ሆነን?… ምንስ ነክቶን?
ወረድ ብዬ እግረ መንገዴን፣ እናንትን ሳላሰለች የማነሳላችሁ ሌሎቹ ሁለቱ ነጥቦች ደግሞ፣ በኢትዮጵያ መንፈስና በኢትዮጵያ ነፍስ፣ በአእምሮ ጥንካሬአችን ላይ ወሳኝ ቦታ ይዘው እዚህ በአደረሱን ጉዳዮች ላይ ነው። ለመሆኑ ምንድናቸው እነሱ?
አንደኛው ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኮርቶ፣- አሁን እሱም እንደ ሌሎቹ ጉዳዮች ተረስቶአል- ፣ እራሱን በእራሱ ዓይን የሚያይበት፣ መነጽር ፣… ወይም መስተዋት ነው።
ፈጣሪ አምላክ እኛ ልጆቹን (ነብዩ ኢሳያስ እንዳለው) የእሱ ምርጥ ልጆች አደርጎ መርጦ መውሰዱ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር አከታትዬ ማንሳት የምፈልገው፣ ወይም ለጊዜው የመጨረሻው እኛን ኢትዮጵያኖችን፣ አንድ አድርጎ ሰብሰቦ እንደ ችቦ የያዘው፣ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ – እሱም ተረስቶአል መሰለኝ- „ እኔ ጥቁር ነኝ፣ ነገር ግን ውብ ነኝ…“ የሚለው፣ ትልቅ ዓረፍተ ነገር ነው። በኋላም ጥቁር አሜሪካኖችም ዘረኝነት ላይ ትግል በ60 ዎቹ ዘመን ሲያውጁ፣ ይህን ተቀብለው „I am black & Proud“ ይሉ እንደነበር አስታውሳለሁ!
ይህ ዓረፍተ ነገር፣ እንደዚህ ዓይነቱ አመለካከት፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያኖች ይህ ነው የማይባል አንዳች መንፈስ ሰጥቶ እስከ ዛሬ ድረስ አቆይቶናል።
ልጅ ሁኜ የተማርኩትን እንደገና ላንሳው:-
„….እኔ ጥቁር ነኝ፣ ነገር ግን ውብ ነኝ…“ ይላል።
„እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች።
…እኔ የዱር ጽጌረዳ ፣ የቄለም የሱፍ አበባ ነኝ…“ቀጥሎ ይላል።
„በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ…“ ብሎም ይዘልቃል።
(መሓልየ መሓልይ ዘሰሎሞን ተመልከት)
እዚይው ላይ ቀደም ሲል „….እናንተ የእየሩሳሌም ቆነጃጂት ሆይ፣“ – ብሎ ይጀምራል።
በመካከሉም „…ጸሓይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለሆንኩ አትዩኝ…“ ብሎም ይጠይቃል።
በቀጥታ ደግሞ፣ ለመድገም፣ ተመልሶ „…እኔ ጥቁር ነኝ ነገር ግን ውብ ነኝ፣
… የዱር ጽጌረዳ የቄለም የሱፍ አበባ ….
በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ…“ እያለ ኮርቶ ይጣራል።
ይህ አባት ለልጁ የጻፈለት ይሆን? ወይስ ልጅ ከአባቱ ጥበብ ሰብስቦ ለኢትዮጵያ የተናገረው፣ቃል?
እንግዲህ ይህ ከሦሰት ሺህ አመት በላይ የኢትዮጵያኖችን ፣ አመለካከት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማንንም ሳይፈሩ፣ ጠብቆ ያቆየውና የጠረበው፣ እምነትና ትምህርት፣ ይህቺን አገር ከሌሎቹ አገሮችና መንግሥታት በታች እራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንዲያዩ፣ ምን ጊዜም አላደረጋቸውም። እንዲያውም፣ ጠንካራ የመንፈስ ብርታት ሰጥቶአቸው፣ እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ድረስ አቆይቶአቸዋል።
አሁንስ፣ ወዳጆቼ እንዴት አድርጋችሁ ነው እረሳችሁን የምታዩት? ….እስቲ እራሳችሁን ጠይቁ ? መልሱ ደግሞ በእጃችሁ ነው።
፭
ሳላንዛዛው ሐሳቤን ዛሬ በአንድ ግንዛቤ ሸብ ላድርገው።
ብዙ መንገዶች በታሪካችን ፣ሌሎቹ ሲወድቁና ሲነሱ፣ እኛ ኢትዮጵያኖች፣ ብቻችንን ተጉዘናል። አንድ ትልቅ ቁም ነገር ላይ፣ ግን ሳንደርስ የጀመርነውን መልካም መንገድ እራሳችን ባልሆነ ትምህርትና ፍልስፍና ሳናውቅበት ቀጭተነው፣ ይኸው ዛሬ ተበታትነን፣ የአውሬ፣… የተኩላ፣… የጅቦች ራት ለመሆን በጨለማ ዓለም ውስጥ፣ መውጫና መግብያው በማይታወቀው ጫካ ውስጥ፣ ሁላችንም ወድቀን ፣ ተዘርተን፣ እንገኛለን።
ለአገራችን ነጻነት፣…. የባዕድ ሰው ጥገኛ አሽከር፣ ….ባርነትን፣ ጨርሶ የማንወድ፣ኢትዮጵያኖች፣ አገር አቋርጠው ሊይዙን የመጡትን ጠላቶች ሁሉ የፈለገውን ያህል መስዋዕትንተ ከፍለን፣ የአገራችንን ፣ የባነዲራችንን ነጻነት ጠብቀን እስከ ዛሬ ድረስ (ይህ የእኛ ሳይሆን የአባቶቻችን ሥራ ነው) ቆይተናል።
ግን የዚያኑ ያህል፣ እኛ የዛሬው ትውልድ (አባቶቻችንን ብቻ መክሰስ እንወዳለን፣ እንጂ ) ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ „ከባርነት“ ወደ ሙሉ ነጻነት፣ ሰበአዊ ክብሩና መብቱ የማንም ሰው፣ ትልቅ ይሁን ትንሽ፣ በማንም ( ኮሚኒስት ይሁን ነጻ- አውጪ፣ ሽፍታ ይሁን፣ ተገንጣይ፣ ዲሞክራት ይሁን ሶሻሊስት፣ ወታደር ይሁን፣…ቄስ ወይም ኢማም….) እንዳይረገጥ፣ እንዳይደፈር፣ የፈለግነውን ፣ ማድረግና መተው፣….መጻፍና መናገር፣ መመራመርና መጠየቅ…መተቸትና መቃወም፣ በሕግ ለተረጋገጠብት የፓርላማ ሥርዓት፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ፣ ብድግ ብለን ተነስተን አለመታገላችን፣ የሚያሳዝን ስለሆነ መጠቀስ ያለበት፣ ይቅርታ አድርጉልኝ፣ ጉዳይ ነው። ይህም ስለሆነ፣ ይህቺን ነገር አነሳለሁ።
የእያነዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሙሉ ነጻነት ጉዳይ፣ ደግሞ፣ በቀጠሮ ገና ሃምሳና መቶ አመት የሚሰጠው፣ የአራዳ፥ልጆች ጨዋታ አይደለም። ይህ መብት፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነው። ከፍጡሮች ሁሉ፣ ከእንስሶችና ከአራዊቶች ሁሉ፣ ለእኛ በአምሳሉ የሰጠን መብት፣በምላሳችን እነድንናገርበት፣ በአእምሮአችን እንድናስብበት፣ በእጃችንን እንድነጽፍበት ነው።…. መናገር መጻፍ፣ ማመዛዘን፣ ክፉን ደጉን ለይቶ፣ መመልከት፣ ዱሮም የነበረ፣ አሁንም ያለ መብት ነው።
ይህን መብት ከጨበጥን፣ የኢትዮጵያ ባህልና ሥልጣኔና እንደሌሎቹ፣ ኃያላን መንግሥታት፣ አድጎ አብቦ ደርቶ የማይታይበት ምንም ምክንየት የለም። ቁም ነገሩ፣ ያለው፣ የነጻነት አዋጁን፣ ሁሉም ሰው በአለበትና በቆመበት ቦታ፣ በቤቱም፣ በደጁም በየሜዳው ማወጅ ላይ ነው።
ለምንድነው አሁን እንደዚህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ወደ መ ጨ ረሻው ላይ ያነሳሁት?
አሁን፣ ጌጥ ስለሆ ነና አላፊው አግዳሚ ው በየአለበት ስለሚ ያነሳው አይደለም ።አይም ሰላችሁ።
ስንት ሰው „ዲሞ ክራሲ እኔ ሥ ልጣ ኑ ላይ ብ ወ ጣ አመ ጣ ላችሁ ዋለሁ!“ ብሎ እንደቀለደብን ሁላችንም እናውቃለን። ስንት ሰው በነጻነት ስም አሳቦ ሥልጣኑ ላይ ጉብ ብሎ እነደቀለደብንና እንዳሾፈብን ሚሥጢር አይደለም።
ያልዋሹንም ሰዎችና ድርጅቶች አሉ። በጊዜው „ የላብ አደሩን እና የገበሬውን ወይም የወዝአደሩን ….አምባ ገነን መንግሥት እናመጣላችሁዋለን „ ብለው፣ በአወጡት ፕሮግራማቸው ላይ፣ በይፋ፣ እነሱ ነግረውናል። ግን እኛ፣ ስንት ሰው እነደሆን ባላውቅም፣ ሞኝ ሁነን፣ ሳይገባን ይህን ሐሳባቸውን ተቀብለናል።
እንግዲህ ኢትዮጵያን ለማ ዳን እንደዚህ ዓይነቱን ቀልድ ቆሞ ወደ ቁም ነገሩ፣ እላይ ወደ አልኩት ወደ ነጻ ዜጋ መ ብ ት ጉዳይ መ መ ለስ ሁላችንም ይኖርብ ናል። ደግሞ ም አለብ ን።
የሚ ቀጥለው ጽሑ ፌ በም ሁርና በፖ ለቲካ፣ ትርጉም ላይ ያተኩ ራል።
ሰለ ትሩፋት፣… ሰለ ምግባረ ሰናይ ፣ ….ስለ መልካም ሥራ፣ …ስለ ተግሣጽና ምክር ፣ ስለ የኢትዮጵያ የትምህርት አሰሳጥ፣…ስለ ሥልጣን ተዋረድ፣ወይም …ስለ ኤቲክና ሞራል፣ ወይም፣… ሰለ ኢትዮጵያ እሴቶች ፣…. ስለነዚህ ሁሉ፣ አላነሳሁም።
አልፌም ሄጄ፣ ስለ የሰው ልጆች ባህሪ ( ኮንዲስዮ ፣ ሁማና ) በሰፊው፣ ለመናገር፣ እኔ አልሞከረኩም።
ምንም የሚያጣድፈን ነገር የለም። ተመልሰን፣ ተራ በተራ፣ እንመጣበታለን። ግን አንድ አስምሬበት ለማለፍ የምፈልገው ነገር ቢኖር፣ ውድ አገራችን ኢትዮጵያ፣ ትላንት፣ እንደ እንግሊዝና አሜሪካ፣… ፈረንሣይና ጀርመን ፣…ሩሲያና ጃፓን፣ የተፈጠረች አይደለችም።
አርግጥ እነሱ ግሩም ፖለቲካ ተከትለው፣ ምን የመሰለች አገር፣ ከእኛ በሁዋላ መሥርተዋል። „ግሩም ፖለቲካ“!… አልኩ?… ምን ማለቴ ነው?
ለመሆኑ፣“…ግሩም ፖለቲካ“ የሚለውን ነገር ለጊዜው እንተውና በጅምላ ለመሆኑ፣ „ፖለቲካ“… ምንድነው?ብለን እንጠይቅ።
ፖለቲካ!… ሰውን ማጋጭት፣ አገር ማናጋት፣ ቀዶ እና ሰነጣጥቆ እንደ ገና መልሶ መስፋት? ….ወይስ ፖለቲካ ማለት …የመደብ ትግል ማወጅ፣ የነበረና የቆን ነገር ደምስሶ በአዲስ ( ከአለፈጣሪውና አድራጊው በስተቀር) ማንም ሰው በማያውቀው መተካት? ለመሆኑ ፣ ከብሔርና ከመደብ ትግል ሌላ ለየት ያለ ፖለቲካ በኢትዮጵያ አለ ወይ?
ከአለስ እሱ ምን ይባላል?
ዕውነትም፣ „ፖለቲካ“ የጀርመኑ ኦቶ ቮን ቢስማርክ እንደሚለው „ ቆሻሻ“ ነገር ነው? ወይስ ፖለቲካ „ዕጹብ ድንቅ ዕንቁ“ የሆነ ነገር ነው?
ፖለቲካ ! ሕዝብን አሰባስቦ ለዚያ ሕዝብና ለዚያች አገር ጥሩ ነገር መሥራት ነው? ወይስ፣ የእራስን ጥቅም ብቻ አሳዶ የተቀረውን መርሣት?…. ፖለቲካ ፣ ለመሆኑ ምንድ ነው?
ማነው አሁን ፖለቲከኛ ከእኛ መካከል? ምን ዓይነት ፖለቲከኛ …ለመሆኑ፣ ፖለቲከኞች ከየት መጡ?…እነሱ ማን ናቸው ? የፖለቲከኛ መመዘኛ ሚዛኑ ምንድነው? ፖለቲከኞች ለጠብና ለነገር ነው ፣ የተፈጠሩት? ወይስ ጥሩ አማራጭ መንገድ ለአገሩቱም ለሕዝቡም ለማቅረብ? ለመሆኑ ፖለቲከኛ ያስፈልጋልናል ወይ?…. ምን ያህል ዘመን በሥልጣን ላይ መቆየት አለባቸው? ዕድሜ ልካቸውን? ወይስ አራት አመት?… እንክርዳዱን ከስንዴ እንዴት መለየት ይቻላል?
ስለፖለቲከኞች እና ስለ ምሁሮች ፣ በአጠቃላይ ረብሻ ስለአነሱ ረብሻ፣ ከእናካቴው ስለ ማንም ሳይጠይቃቸውና ሳይለምናቸው ፣ „ልምራ“ ስለሚሉት „ፍጡሮች“ የሚቀጥለው ጽሑፍ፣ ያተኩራል።
አዚህ ውሰጥ ስለ መንግሥት አመሰራረትም አነሳለሁ። ከእሱም ጋር ሌሎቹን ጉዳዮች ሁሉ ወደፊት እጠቅሳለሁ።
አንድ የረሣሁት ነገር ቢኖር ይህ ነው። እሱም:- ” የክርስቲያን ሃይማኖት፣ በገባበት አገር ሁሉ ( ይህ ትልቅ ቁም ነገር ነው) እያንዳንዱን ሕዝብ የአኗኗር ባህልና ዘዴ ሳቀይር እንደፈለጉት (በዚህ ከሌሎቹ ሃይማኖቶች ይለያል)ኢንዲኖሩ የሚፈቅድ ሃይማኖት ነው።” በዚህ ምክንያት፣ “የደቡቡ፣ ሕዝቦች አኗኗር ከሰሜኑ የተለየ ” የሚመስለ። ይህ ስለሆነ ግን እነዚህም ሆኑ እነዚያ የሰሜኑም ሆነ የደቡቡ፣ የምስራቁም ሆነ የምዕራቡ፣ የመሃል ሃገሩም ሆነ የዳርዮሹና የጠረፉ ፤ አንዱ ከሌላው ያነሰ ወይንም የላቀ “ኢትዮጵያዊ” አይደለም፣ አይደሉም። ለመሆኑ የሰውልጅስ የተፈጠረው ከየትስ ሆነና!
ይልማ ኃይለ ሚካኤል
——————————-