የባንክ ዘረፋ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን!
ወንበዴዎቹ የመጡት፣ ፖሊስ እነዳለው፣ እንደተለመደው፣ ጨለማን ተገን አድርገው አይደለም። … በጠራራ ጸሓይ በቀን ነው።
እንደዱሮ፣ ፊታቸውን ተሸፋፍነው „በሽጉጥ እጅ ወደላይ፣ ብለው አስፈራርተው …ገንዘቡን፣ አንዲት ኮሮጆ ውስጥ እንዲጨምሩ የባንክ ሠራተኞቹን አላስጨነቁም። እንገላለን ብለውም፣ እነሱን አላስፈራሩም።“
እነደ ሃያኛው ክፍለ-ዘመን ሌቦች እንደ ፍልፈል ግማሽ አመት የፈጀ ረጅም ቱቦ ውስጥ ውስጡን ቆፍረው፣ ከታች የባንኩን ካዝና ስብረው ገብተው በጥቁር መኪና አላመለጡም።
እነዚህ እሳት የላሱ ሌቦች፣ (ቁጥራቸው በደንብ አይታወቅም) የሰሩት ሥራ ቀላል ነው። እንደ የሆቴል ቤት በር መክፈቻ ፣ ዘመናዊ ካርድ፣ የማግኔት መስመር ካርዳቸው ላይ፣ ለጥፈው፣ በየባንኩ መግቢያ በር ግድግዳ ላይ፣ ተገትረው ፣ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው፣ ብር የሚተፉትን ቁም ሳጥኖች፣ ፖሊስ እንዳለው፣ ጠቅጠቅ እያደረጉ፣ እንደ ከረሜላ ጎርፍ፣ አንድ በእንድ፣ ያስነጥሱአቸው ጀመር።
ከአንዱ የባንክ ግድግዳ ወደ ሌላው እየተሳሳቁ፣ የጀርባ ሻንጣቸውን እየከፈቱና እየዘጉ የሚሄዱትን ጎረምሳዎች የተማለከቱ ሰዎች እንዳሉት ከሆነ፣ በኒዮርክ ከተማ ብቻ፣ ወደ ሦስት ሺህ ከሚጠጉ የገንዘብ አውቶማቶች፣ ወረበሎቹ፣ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ሺህ ዶላር ፣ እየቆጠሩ፣ ኪሳቸው ውስጥ አስገብተዋል።
አሁን እንደተደረሰበት፣ እነሱ ብቻቸውን አልነበሩም። በሃያ ስድስት የተለያዩ አገሮችና ከተማዎች ፣ ግብረ አበሮቻቸው ተሰማርተው፣ በአደረጉት ተመሳሳይ የባንክ አዉቶማት ዘረፋ፣ አርባ አምስት ሚሊዮን ዶላር፣ ጠራርገው፣ ሊሰወሩ ችለዋል። ይህም፣ዝርፊያ „ትልቁ የሳይብር ባንክ ዘረፋ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን „ የሚባለውን ስም አትርፎአል።
በጠቅላላው እየተዝናኑ፣ ወደ 36 ሺህ የሚጠጉ ካዝናዎችን ለመጠራረግ፣ አሥር ሰዓት ብቻ እንደፈጀባቸው፣ ፖሊሶች ተናግረዋል።
የጥጋባቸው ብዛት፣ አንድ ካርድ፣ በቀን ማውጣት የሚፈቀድለትን ገደብ ሰብረው፣ ጭንቅላቱን አዙረው፣ እንደፈለጉት እንዲታዘዝ፣ አድርገዋል።
ታሪኩ ረጅም ነው። የታሪኩ ሞራል ምኑ ላይ ነው?
እኛ መልሰን እንደገና የምንተርክበት ምክንያት፣ እንኳን ፖለተከኛ፣ ሌባውም የስርቆት ብልሃቱን ቀይሮአል ለማለት ነው። ጊዜው አ እምሮ ይጠይቃል! እንዳው ለማስታወስ ያህል፣ አጤ ምንልክና አባቶቻችንም የጣልያን ጦርን ያሸነፉት ጦር ሜዳ ላይ፣ በጋሻና ጦር ብቻም አልነበረም። ዘመናዊ አውሮፓ ውስጥ ዓይነተኛ ሚና መጫወት የጀመረውን፣ የሚዲያ /Medial power/ ሃይልንና የህዝብ ግንኙነትንም በመገልገል ነበር።
አዎ ! ጊዜው ለአ እምሮ ነው! ጊዜው እንዳው ሃይ በለው ሳይሆን፣ ጥበብን ብልህነትን፣ አዙሮና አገለባብጦ ማስተዋልን፤ አዎ ! የሚያገናዝብ አእምሮን ይጠይቃል። ካንባ ባሻገር፣ አንባ፥ገነን እስካልሆኑ ድረስ!
———————