ኢትዮጵያ በ21ኛው ክፍለ ዘመን_!?
„….ቤት ሠርታችሁ፣ ተቀመጡ፣ አታክልትም፣ ተክላችሁ፣ ፍሬዋንም ብሉ። ተጋቡ።ወንዶችናሴቶች ልጆችንም ውለዱ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁንም አጋቡ። እነርሱም ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች፣ ይውለዱ።…. ተባዙ። ጥቂቶችም አትሁኑ። በአላችሁበት ቦታና ከተማ፣ መልካምና ጥሩ ነገር ለእሱዋ ፈልጋችሁ ሥሩ። ….በመካከላችሁ ያሉት ነቢያቶችና ሆኑ ምዋርተኞች፣ አያታሉአችሁ። እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ። …እናንተ እኔን ትሹኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁም ካሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ከእናንተም ዘንድ፣እገኛለሁ። ….እናንተንም፣ ከተበተናችሁበት …እሰበስባለሁ።“
ትንቢተ ኤርምያስ። ም.29 ቁ. 4-10.
20ኛው ክፍለ-ዘመን፣ ሐሰተኛ ነብያት፣ አታላይ ምዋርተኞች የነገሡበት፣ ኢትዮጵያን ፣የሚበትን፣ የበተናትም፣ ፍልስፍና የዘሩበት… የክፍፍልና የልዩነት፣ የመደብና የብሔር ጦርነት፣ የበተኑበት ዘመን፣ ነበር። በተቃራኒው፣ 21ኘውን፣ ክፍለ-ዘመን፣ በእግዚአብሔር ኃይል፣ ፍቅርና አንድነት በኢትዮጵያ ተመልሶ፣ የሚያብብበት፣ ወርቃማ ጊዜ፣ ከአወቅንበት፣ ይመጣል። ቁም ነገሩ: – የአገሬ ሰዎች- ያለው፣ እንዴት? ለሚለው ጥያቄ ፣ ግሩም መልስ መስጠቱ ላይ ነው። (ከማስታወሻ ማህደሬ)
ለካስ፣ ነብዮቹ፣ ገና ዱሮ፣ አሰጠንቅቀውን ነበር!
አሁን እኔ ፣ ተመልሼ ዛሬ የማነሳው ነገር፣ (….መልካምና ጥሩ ነገር፣ ለእሱዋ፣ ለአገራችሁ፣… ለከተማችሁ፣ …አስባችሁና ፈልጋችሁ:- ነብዩ ኤርምያስ- ሥሩ….ይለናል፣… ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ ይለናል፣ …ተጋቡ፣…..ልጆቻችሁንም አጋቡ፣ ….ከምዋርተኞችም እንዳያታልሉአችሁ ተጠንቀቁ፣ ይላል…)….አሁን እኔ ተመልሼ፣ የማነሳው የነብዩ ቃል፣ ….እርግጠኛ ነኝ፣
…ማርክሲስቱንም፣…. ኮሚኒስቱንም ፣…. ተራማጁንም፣….. ግራውንም፣ ሊበራሉንም፣ ዲሞክራቱንም (ዘንድሮ ይክበር፣ይመስገን፣ ዲሞክራቶች በዝተዋል… እነሱንም!) በተለይ ነጻ-አውጪውንማ፣ ይህ ነገር….የማይጥማቸው፣ በመሆኑ፣ እነሱን፣ እንዲያውም፣ ነገሩ፣ ባያስቆጣቸው፣ ቢያንስ: – ሳስበው- ሊያስቀይማቸውም፣ ይችላል። የሚችልም፣ጉዳይ ነው።
የፈለገው ይሳለቅ፣…. የፈለገውም ይቆጣ – ሌላ ምርጫ፣ ግን ዘንድሮ የለንም ። መነገር፣ ያለበት፣ ነገር ደግሞ የግድ ፣ አሁን ተበታትነን ሳንጠፋ፣ መነገር፣ የአለበት፣ጉዳይ ነው። አለበለዚያ ከገባንበትና ከቆምንበት፣ የውድቀት፣ አፋፍ፣ ፈጽሞ፣ አናመልጥም።
ወጣም ወረደ ፣ –ይህን መደበቅ፣ አይቻልም–፤ ለአለፉት፣ አርባና ሃምሣ አመታት፣በመደብና በዘር፣ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ጭምር፣ „አንተ ኢትዮጵያዊ ሳትሆን ፣… ትግሬ ነህ፣…አንተ ደግሞ፣ የለም… ኦሮሞ ነህ፤ ወይም፣ ኤርትራዊ…ወይም አፋር፣ ኦጋዴን…አማራ፣ወይም ጉራጌ…“ ተብሎ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ፣ ኢትዮጵያኖች፣ እንዲገቡ፣ በተለያዩ ድርጅቶች፣ ፊታውራሪነት፣ ይህ ነው የማይባል፣ አጸያፊና፣ አሳዛኝ፣ ሥራዎች በዓይናችን፣ ሥር፣ በአገራችን፣ ተካሂደዋል። ጥላቻን ብቻ የሚያውቀውን ሕዝብና ትውልድ ደግሞ፣ ምንድነው፣ እሱን መልሶ „አንድ“ የሚያደርገው ነገር? ለሚለው የቆየ፣የእኔ ጥያቄ፣ የምሰጠው መልስ፣ እላይ የተጠቀሱትን ቡድኖችና ሰዎችን፣ ከአስቀየመ፣ከአስቆጣም ምንም ማድረግ እኔ አልችልም። ቢፈልጉ፣ ከእንግዲህ ይሳለቁ …..ይንከትከቱ… ከአልፈለጉም፣…. ይቆጡ! ዕውነቱ ግን ተደብቆ የትም አይደረስም። ዕዉነት ሳይደበቅ መነገር ያለበት ጉዳይ ነው። ዛሬ ባይነገር፣ ሌላ ጊዜ፣ እውነት መውጣቱም የማይቀር ነው።
በዚህ በያዝነው በ21ኛው ክፍለ-ዘመንና በ20ኛው መጨረሻ፣ ላይ፣ ሌላም፣ ሌላም፣…ቲዎሪዎችና ልዩ-ልዩ ኣሳዛኝ ትምህርቶች፣ ኢትዮጵያ አገራችንን የሚበትኑ አስተሳሰቦች፣ አገሪቱ ውስጥ ሰተት ብለው፣ ሠርገው እንደገቡም እናውቃለን። ግን ስለ እነሱ፣ አሁን ሳይሆን፣ በሌላ ጊዜና በሌላ ቦታ፣ አንድ ቀን ማንሳቴ የማይቀር ነገር ነውና፣ አሁን ወደ ጀመርኩት አርዕስት በቀጥታ ልለፍ።
፩
ልጅነት ይሁን አለማወቅ፣ የተለያዩ ቲዎሪዎችና ትምህርቶች የወጣቱን ልብ በቀላሉ ማርከው፣ አገሪቱንም ሕዝቡንም በአለፉት አመታት ደህና አድርገው አወናብደዋል። አንድ ያልታወቀ፣ ማንም ሰው የማያውቀው፣ „ምሥጢራዊ“ የሆነ ነገር፣ እነዚህ ትምህርቶች በጀርባቸው ላይ አዝለው የመጡልንም የመሰላቸው ጥቂት አይደሉም። መገመት እንደሚቻለው:- ብዙ ናቸው። ግን፣ በመጨረሻው ምን ይደረጋል፣ ጉድ ተሠራን!
ሁሉ ነገር – ምን ይደረግ- አዲስ ስለሆነና ከባሕር ማዶም ስለመጣ፣ ሲይዙትና ሲጨብጡት፣ ደስ ይላል። አብሮ መሰለፍም አብሮም መሮጥም፣ ያኔ ያስጎመጃል። አዲስ አለምም በመሆኑም፣ …. አዲስ ጓደኛ፣ አዲስ ወንድም፣ አዲስ እህት፣ ከነዚያ ከጨቅጫቃ ኣባትና እናት የተሻለ፣ አዲስ ቤተሰብም፣ ወጣቱም ያገኘ ይመስለዋል። ሰው ሁሉ የራሱን የግል ቤት፣ ድርጅት ማለት ነው፣ ከሕግ ውጭ መሥርቶም:- የሚመጣውን ችግር ሳይመለከት- እንደልቡ ቡዋርቆአል። ከንፎአል። አብዶአል። አብዶም፣ ሌላውንም ሰው አብሮ አሳብዶአል።
በሁለት ትምህርቶች፣ – በትክክል ለመናገር- በሁለት ርዕዮተ-ዓለሞች፣ ወጣቱ የኢትዮጵያ ትወልድ፣ ከአለፈው፣ ከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ በዚያ አስተሳሰብ፣ ተለክፎ፣ ተጠምቆም፣ ማለት እንችላለን፣ ረዘም ላሉ ጊዜያት፣ እራሱን አወናብዶ፣ ሌላውንም ይዞ አወናብዶ፣ ወርቃማ ዘመኑን አበላሽቶ፣ ይኸው አገሪቱን፣ አሁን የምናየው ችግር ውስጥ ከቶአታል።
ከዚያ በሁዋላ፣ ሁለቱን ርዕዮተ-ዓለሞች፣ ማን ይቻላቸው! እንዳለ አዋከቡን። እኛም አብረን ተዋከብን። አበዱ፣ እኛም አብረን አበድን። ሰው ሁሉ ጨርቁን ጣለ። …ቄሱም፣ መነኩሴውም፣ ሓጂውም፣ ወታደሩም፣ ሴቱም፣ ወንዱም፣ ፖሊሱም…. አስተማሪውም ተማሪውም፣ ….ሓኪሙም፣ ….ገበሬውም….አብሮ፣ ሮጦ፣ ምን ቀረ? …ሁሉም፣ አደባባይ ወጣ።
የንጉሠ-ነገሥቱ፣ ዘውድና ዙፋን ይውደቅ፤ ብለውም፣ ሁሉም ተነሱ። እሳቸውም ወደቁ።ቀጥሎ…. መሬት ለኣራሹ፤ ተባለ። መሬት፣ (ዛሬ፣ ወያኔ እንደ-ግል-ሓብቱ የሚቸበችበውም) ያኔ ….ተወረሰ። …ሥር-ነቀል ለውጥ ተባለ፣ ….አብዮታዊ እርምጃ፤ …እናቸንፋለን፣ … እናሸንፋለን፣ ….የላብ አደሩ፣ ወይም…የወዝ አደሩ፣ አምባገነን መንግሥትም፣ መምጣት አለበት፣ ተብሎም በአደባባይ፣ ተጠራ። ያም! አምባገንን መንግሥት ከተፍ ብሎ መጣ። ….የመደብ ትግል እና ፣ የብሔር/ ብሔረሰብ እኩልነት እሰከ መገንጠል ድረስ፣ ….ተባለ። ግባችን፣ … ሶሻለዚም፣ ….ከዚያም፣ አልፎ፣ …ኮምኒዝም፣ ተብሎ ተተለመ። እሱም፣ እንደፈለግነውና እነደ ተመኘነው፣ ከተፍ አለልን። ከዚያ በሁዋላ፣ ማጅራታችንን፣ … ቀበሌውም፣ … ደህንነቱም፣ …ካድሬውም፣ አነቆልን ያዘ።
ይህ ጉዞ፣ ….ይህ ነገር፣ በአንዳች ምክንያት ከከሸፈስ፣ ወለም ብሎት መስመሩን ከለቀቀ፣ አረ-ወዴት ይወስደናል? የሚለው ጥያቄ፣ ፈጽሞ አልተነሳም። ….እኛ እና አገራችን ኢትዮጵያስ ምን ትሆናለች? ….ምንስ ይመጣል?… ምን ሊሆን ይችላል? በዚህ „ትምህርት አገራቸውን የገነቡ፣ የምሥራቅ አውሮፓ አካባቢዎች፣ በሕዝባቸው ላይ የአመጡት ደስታና መከራ ምንድነው“?
….ለመሆኑ ስንት ሰው „አደሃሪ„ ብለው፣ “በእጃቸው ፈጁ“? …በቻይና፣ በካምቦድያ፣ በአልባኒያ…ስንት ሚሊዮን ሰው ጨረሱ? ….ነጻ-ፕሬስ፣ … ነጻ -ፍርድ ቤት፣ …በእነሱ ሠፈር፣ በእነሱ ቤት፣ እንዴት ነው? የሸንጎ ምርጫቸውስ ምን ይመስላል? ብሎ የጠየቀ ሰውም የለም። አንዲያው፣ የመጣው ይምጣ – አሁን እንደሚባለው- „እኛ ለሕዝቡ የሚስማማውን እናውቃለን“ ተብሎ የተጀመረ፣ የተገባበትም፣ „ጨዋታ“ ነበር።
፪
እንግዲህ ብዙዎቹ (?)ወይስ ጥቀቶቹ (?) የተመኙትም ሥርዓት ከተፍ አለ።
ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምና ግብረ-አበሮቹ፣ እነዚያ „ደርግ „ የሚባሉት ፍጡሮች፣ ብቅ ብለው፣ ያ! እንዲመጣ የተተለመው፣ „የሠራተኛው አምባገነን መንግሥትና ሶሻለዝም“ ምን ዓይነት መንግሥት እንደሆነ፣ እነሱ በትክክሉ በሥራ ላይ ተርጉመው ኣሳዩን። ያኔ የወጣው ሕገ-መንግሥት፣ ከአልተረሳ፣ „ኢሠፓን የተቃወመ፣ ግለሰብ ሆነ ድርጅት፣ በሞት ፍርድ ወይም በ20 አመት እሥራት…“ ይቀጣል የሚል አንቀጽም አዝሎ ብቅ ብሎም ነበር። ግን- ምን ይደረግ! ከዚያም መማር እንኳን አልቻልንም? እሱ አልበቃ ብሎን፣ ሻቢዕያና ወያኔ፣… ኦነግ ጭምር፣ መልሰው እዚያው ወጥመድ ውስጥ ደግመው፣ እኛን ዘፈቁን። „ገና ምን አይታችሁ! ልጆቻችን“ እነሱ እንዳሉት፣ „ሥልጣኑን ወርሰው፣ ይገዙአችሁዋል“ ብለውም አረፉት።
ለመሆኑ ከእነሱ እና ከአለፈው የአርባ አመት ስህተት፣ በቂ ትምህርቶችን ቀስመናልን?… ምንስ ዓይነት ተመክሮ አሰከ አሁን ድረስ ሰብስበናል?… ምንድነው ለመሆኑ ከአለፈው ትርምስ የተሰበሰበው ዕውቀት? …ምን ዓይነት ዕውቀት? …. ምንስ ተገኘ? …..ምን አግኝተናል?
ቀጥሎም:-
ለመሆኑ ሕይወታችንን እንዳለ፣ በሥራችን አበላሽተናል? …ወይስ አላበላሸንም? እኛም በዚህች ዓለም ላይ፣ በሙሉ አፋችን፣ ኖረናል ማለት እንችላለን?
ከዚህ ሁሉ በሁዋላ አሁን፣ ዛሬስ፣ „ኢትዮጵያ፣….ኢትዮጵያ፣“ ማለት፣ ለምንድነው? …ማነውስ አሁን ኢትዮጵያዊ ?
ኧረ! ለአረቡ ሕዝብ ፣- ለአላሙዲ ጭምር- አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ሲባል ለእሱ ይህ ሰው፣ ምንድነው? በምን ዓይኑ ነው፣ እሱ፣ እነሱ እኛን አሁን የሚያዩት?
ለሕንዱና ለቻይናው፣ …..ለአውሮፓና ለአሜሪካን፣ …ለድፍን ዓለም እኛ ምንድነን? ….ለመሆኑ በምን ዓይን ነው፣ እኛን / ኢትዮጵያዊያንን፣ እነሱ አሁን የሚያዩት?
….ለማኝ ነን? …ደሃ ነን? እራሳችንን ማስተዳደር የማንችል ሰዎች ነን? ወይስ የወደፊት ባሪያዎቻቸው?
ሌላው ቀርቶ፣ አሁንም፣ ከዚህ ሁሉ ዓመት በሁዋላ፣ ከመካከላችን ተነስተው፣ „…እኔ ኦሮሞ እንጂ ….ኢትዮጵያዊ አይደለሁም። …..እኔ ትግሬ እንጂ፣…. ኤርትራዊ እንጂ ….ኢትዮጵያዊ፣ አይደለሁም የሚለው ሰው፣ ቁጥሩ ትንሽ እንዳልሆነ እናውቃለን። አዎ! ቁጥራቸውም ተበራክቶአል። ለእነሱስ፣ ያዘጋጀነው መልስ አለ?… ለመሆኑ መልሳችን ምንድነው?
ደግሞ፣ እዚሁ ላይ አንድ ነገር መርሳት የለብንም። ….እሰከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሌላ አቅጣጫ „እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ….ትግሬ እንጂ፣ … ኤርትራ፣ …ኦሮሞ …ነን“ እያሉ ሲቀልዱብንና ሲያሾፉብን፣ የከረሙት „የነጻ-አውጪ ፖለቲከኞች ሁሉ“ ዛሬ፣ ዞር ብለው ቤተ- መንግሥት ገብተው፣ „በኢትዮጵያ መንግሥት“ ስም ፣ የአገሪቱን መሬት ለባዕድ ይሸጣሉ። ለእነሱስ ያዘጋጀነው መልስ አለ? …ለመሆኑ መልሳችንስ ምንድነው? …ምንስ፣ ይመስላል?
ሌሎችም ጉዳዮች አለ። እነሱንም ዝም ብለን ማለፍ የለብንም። ዱሮ „….እኛ እኮ ት፣ኦ …እንጂ ኢትዮጵያዊ፣ አይደለንም… „ይሉ የነበሩ ሰዎች፣ ዛሬ፣ እነሱ፣ የተቃዋሚ ቡድኖች መሪ በየአለበት ሁነዋል። እነሱንስ ዝም ብለን እንቀበላቸው? ወይስ እንጠይቃቸው? ወይስ እንደ ተለመደው ፣ አድበስብሰን እንለፈው?
ትላንት ሕዝብ የፈጀው፣ ያ! መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም፣ ሳይቀር፣ በተራው፣ እሱም መጽሓፍ ጸሓፊ ሁኖ „ለምን በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮታዊ እርምጃ ለመውሰድ፣ እነደተገደደ“፤ ማለት ሰው ለመግደል በኢትዮጵያ እንደቻለና እንደተነሳ፣ አንደአተረማመሰ „ትምህርት“ ከአርባ አመት በሁዋላ፣ ለእኛ ለመስጠት፣ ይኸው ሰው፣ ብቅ ብሎአል። … እሱንም፣ ግብረ አበሮቹንም፣ ዝም ብለን፣ እናዳምጥ? …ይህ መንገድ፣ ለመሆኑ፣ ያዋጣል?
ሌላም ነጥብ አለ። “ፖለቲከኞች“ አሥመራ ወርደው በኢሳያስ አፈወርቂ ተደግፈው፣ እኛን እና አገራችንን ከወያኔ መዳፍ፣ እነሱ እንደሚሉት „ነጻ – ለማውጣት“ ይደክሙልናል፣ ይባላል። እነሱንስ፣ እንደተለመደው „በርቱ“ እንበላቸው? ወይስ፣ አትቀልዱ፣ አርፋችሁ ተቀመጡ?
ወይስ፣ በእራሳችሁም ላይ ሆነ በሌላውም፣ እንዳለፈው ጊዜ፣ እንደ አቶ መለሰ፣ አትቀልዱብን፣ ብለን፣ እነሱንስ እንቆጣቸው ወይ? እንደምናውቀው፣ የሕዝባዊ ወያኔ፣የክርስትና አባት፣ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ነበር። ይህ ተረሳና፣ አሁን፣ እናም …አሥመራ፣ይውረዱ?
፫
የት ነው ለመሆኑ ያለነው? … ምንድነው እኛን የነካን ነገር?…. ናላችንን ያዞረው በሽታ ስሙ ምን ይባላል?…. ምን ዓይነትስ በሽታ ነው የለከፈን? ለመሆኑስ፣ ይህ በሸታ፣ መድሓኒትስ አለው ወይ?
እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ደግሞ፣ በትክክል ለመመለስ፣ መደማመጥ፣ በመካከላችን በመጀመሪያ መኖር አለበት። ግን ዕውነቱን ለመናገር፣ የመደማመጥ መንፈስ በመካከላችንስ በእርግጥ አለ ?
የአለመደማመጡ፣ የነአንደማመጡ ሠፈር ደግሞ፣ „ፓልቶክ“ እንደሚባለው መንደር ዓይነቱ፣ እንደ አሸን ፈልቷል። ምክንያቱም፣ አንዱ የሚለውን፣ ሌላው አያዳምጠውምና !
ሌላው „የማንደማመጥበት መድረክ“፣ ሁላችንም፣ የምንጠቀምበት፣ የምንጽፍበት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ እንደሆነም፣ እናውቃለን ። ምክንያቱም፣ በዚህም ቢሆን፣ ሺ ነገሮች ከመደጋገማቸው ሌላ፣ „ ቢያንስ፣ “የአቀራረብ ሲስተም“ የሌለው የዝላይ ሜዳ ሆኗል።
ይህን ስል፣ ጨርሶ አትናገሩ አትተንፍሱ፣ ምንም ነገር አትጻፉ ማለቴ፣ እነዳልሆነ ግልጽ ነው።…. ….መናገር፣ ….መጻፍ፣ …መተቸት፣ ….መውቀስ፣ …ሓሳቦችን መደገፍና፣ መጣል ፣…. ተገቢና፣ እንዲያውም ይህ ባህል፣ በእኛ መካከል መበረታታት ያለበት፣ ባህላችንም እንዲሆን ወደፊት፣ የበለጠ በዚህ መስክ መሥራት አለብን ከሚሉት ሰዎች መካከል አንደኛው ነኝ።
ግን ችግሩ ያለው እዚያ ላይ አይደለም። ችግሩ ያለው፣ ዱሮም አሁንም፣ በአንድ የአስተሳሰብ አቅጣጫ፣ ለጊዜው ሰውን ሁሉ በሚያሰባስብ መርሓ-ግብር ዙሪያ፣ ተሰባስበን፣ ኢትዮጵያ ላይ የአምባገነን ሥርዓታቸውን ዘርግተው፣ የሚገዙንን መዓቶች እንዴት እንጣላቸው? እንዴትስ? ወደፊት እነሱን በሕግ እንቆጣጠራቸው? እንዴትስ? ነጻ-ሕብረተሰብ በጋራ እንመስርት? በሚለው ጉዳይ ላይ አተኩሮ ሰጥተን፣ ጊዜ ወስደን፣ እኛ ለመነጋገር በአለመቻላችን ላይ ነው።
„ንግግር: – በቂ ንግግር አለ እኮ “ አንዳዶቻችሁ፣ ልትሉኝ ትችላላችሁ።
የት ቦታ? … ምን- ዓይነት ተጨባጭ ንግግር? ….እስካሁን ድረስ ምን ተካሄደ?
ለመሆኑ ሠልፍ ለመውጣት፣ ተወሰነ? …..እምቢ ባይ አመጽ ለማስነሳት፣ ስምምነት ላይ ተደርሶ ተጠራ?… የት ቦታ? ብዬ ሰው ብጠይቅ፣ መልስ፣ እሰከ አሁን ድረስ፣ በቂ መልስ፣ ከማንም፣ አላገኘሁም።
…..እኔ ያየሁትን ለእናንተም አንዳልተሰወረ፣… (እንደምታዩት) እርግጠኛ ነኝ። እኔ ያዳመጥኩትን እናተም እንደአዳመጣችሁት፣ ተስፋ አደርጋለሁ። አንዱ (ለምሳሌ) ስለ አንድ ነገር ሲያወራና ሲጽፍ፣ ሌላው፣ ያ! ነገር ገና መቋጠሪያ ሳያገኝ፣ ስለ ልዩ የሆነ አዲስ ነገር ያወራል። ምናልባት፣ እንደዚህ ዓይነቱን ነገር፣ መብቱ ነው፣ ብለን ልናልፈው፣ እንችላለን። አዎ ! መብቱ ነው። ማንም ሰው፣ ስለፈለገው ነገር፣ ሊጽፍ፣ ሊያነሳ፣ ዘሎም ማለፍ… ይችላል። ግን ተገንዝባችሁት እንደሆነ፣ በአንድ ጊዜ፣ ሰላሣ የተለያዩ አርዕስቶች፣ ይነሳሉ። አንዱንም ነገር በቅጡ ሳይያዝ፣ ሳናብላላው፣ ጊዜው መሽቶ፣ ሌላ አዲስ ነገር ተጨምሮበት፣ ይነጋል። መቋጠሪያ ሳይደረግለት፣ እንዳውም የተቋጠረውም ይፈታል። እንደገና በሌላ ቀን አስር አርዕስቶች፣ በአናቱ ላይ፣ ይጨመርበታል።
በሰለጠነው ዓለም፣ ጥዋት ጥዋት፣ የተለያዩ ጋዜጣዎችን፣ ገዝተን እናነባለን። የተለያዩ የራዲዮና የቴሌቭዠን ጣቢያዎችን ከፍተን እናያለን፣ እንሰማለን። ግን እንደምናውቀው፣ „አቀራረባቸው፣ የተዘበራረቀና፣ ውጥቅንጡም የጠፋ አይደለም“። እንደምናውቀው፣ መልክ፣ መልክ፣ አላቸው:- ሥርዓትም ይገኝባቸዋል!
እኛ እኮ፣ የምናደርገው ነገር….(ይህ ማለት) በሌላ ቋንቋ፣ መርከቡን ወይንም ጀልባውን ሠራዊቱ ሁሉ በእጁ፣ በጨበጠው መቅዘፊያ፣ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች፣ የመቅዘፍ ነገር አድርገነዋል። በተለያዩ አቀጣጫ ከተቀዘፈ ወይም ደግሞ፣ መርከቡን፣ በአራቱም ማዕዘን ሰው ሁሉ በገመድ ከጎተተው፣ …..ወደፊትም ሆነ ወደ ሁዋላ፣ ያ! መርከብ መንቀሳቀስ አይችልም። ስመለከተው ፣ እኛም የገባንበትም ሁኔታ ከዚህ አይለይም። በዚህ ጉዞ ደግሞ እነኩዋን ኢህአዴግን መጣል ቀርቶ፣ ገፍተር አድርጎም፣ ማለፍ አይቻልም።
፬
ሁለት ትምህርቶች፣ ሁለት አስተሳሰቦች፣ ገና መጀመሪይ እላይ እንዳልኩት፣ ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን ኣጋማሽ ላይ ጀምሮ፣ የኢትዮጵያን ወጣቶች ልብ ስበውና ማርከው፣ ያልሆነ ነገር ውስጥ ከተው፣ አገሪቱን አተረማምሰው ዞር ብለዋል። ማን ይሙት፣ አሁን ፈረንጆቹ ይህ ነገር፣ አንድ ቀን እኛን እንደሚበትን፣ ያጡት ይመስላችሁዋል? አረቦቹስ ይህቺን ዘለው የሚያልፉ፣ ይመስላችሁዋል?
ያኔ ! እንደ ቁም ነገርም ፣ እንደ ጌጥም ፣ ተይዞ የነበረው አንደኛው ጉዞ — ይህ ለማንም ሰው ምስጢር አይደለም፣ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ተነግሮአል— የመደብ ጦርነትን፣ በሕዝብ መካካል፣ የሚያስተምረው፣ የስተማረው፣ „የመደብ ትግል“ የሚባለው ፈሊጥ ነው።
ሁለተኛው፣ „የብሔር/ ብሔረሰብ እኩልነት እሰከ መገንጠል“ የሚባለው፣ ይ እላይ ላይዩን ሲያዩት፣ „የዲሞክራሲና የነጻነት መብት፣ የሚያመጣ„ የሚመስለው፣ ግን፣ አሁን እንደምናየው፣ የአንድ አገርን ሕዝብ፣ የሚበትነው፣ የዕብድ ልጆች „የፖለቲካ ጨዋታ“ ነው። አሁን ማን ይሙት፣ የማርክስ ሆነ የስታሊን ትምህርት „መንግሥት ለማጠንከር፣ ሕዝብ ለመሰበሰብ፣ ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ ጠቃሚ ቢሆን“ ፈረነረጆቹ ለእራሳቸው፣ ሳይጠቀሙበት ዝም ብለው፣ ለእኛ ኣሳልፈው፣ ውሰዱት፣ ብለው መርቀው ይሰጡን ነበር?
ማርክስ እኮ የበኩር ልጃቸው ነው። ስታሊንም፣ የእነሱ፣ ዲቃላ ነው። ታዲያ! የሁለቱ ትምህርት ጥሩ፣ ቢሆን፣ ዝም ብለው፣ እኛን አስተምረው፣ ተጠቀሙበት ብለው ይሸኙን ነበር? …..ሞኝ አፍሪካ! …ሞኝ እና ተላላው ኧረ የአገሬ ልጅ ሆይ! መች ይሆን ዓይንህ / ዓይንሽ የሚገለጠው !?
ሁለቱም ትምህርቶች፣ ለረጅም ሺህ አመታት ተሳስረውና ተጋብተው፣ ተዋህደውና ነጻነታቸውን ጠብቀው፣ ይኖሩ በነበሩት በአንድ ሕዝብና በአንድ አገር ውስጥ ገብተው፣ አንዴት፣ ያንን ባህልና ሥርዓት እንደሚያናጉት፣ እንደአተረማምሱት፣ ነጮቹ አጥብቀው፣ በደንብ ያውቃሉ። ይህን ለመረዳት፣ ሩቅ ሳይኬድ መጽሃፍም ሳያገላብጡ፣ መንፈስም ሳያማክሩ፣ በየሙዝየማቸው እንኳን ጎራ ማለት ይበቃል!
የቅርብ ጊዜው ታሪካችንም፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ለመረዳት ለሚፈልግ ሰውና ለተረዳው ሰው፣ ትልቅ ምስክር ነው። ይህን በደንብ ለመረዳት ሁለተኛ መወለድ ኣያሰፈልግም።…
የመደብ ሆነ የብሔሩ ትግሉ፣ ሁለቱም፣ በመጨረሻ፣ እኛን ኢትዮጵያኖችን፣ እርስ በራሳችን አፋጅቶ፣ አንድ ቀን እንደሚበትነን ጠላቶቻችን፣ ይህን ፣ የተደገሰልን ድግስና በእራሳችን እግር ሥር፣ የተቀበረው ቦንብ ፣ ጥንካሬው ምን ያህል እንደሆነ ፣ ከእኛ ይልቅ፣ እነሱ በደንብ አውቀውልናል። ለዚህም ነው „በርቱ“ ብለው፣ ምዕራቦቹም ሆነ፣ ምሥራቆቹም፣ እኩል ከመሣሪያ እስከ ገንዘብ ድረስ በጆንያ እየሞሉ፣ እያስታጠቁ፣ ሁለቱንም፣ ሦስቱንም ወገኖች፣ …..ኢትዮጵያ! በሚባለው ባዶ ሜዳ ውስጥ „እነሱንም ሆነ፣ እኛን ለቀው“፣ ሰውን ሁሉ፣ ያኔም ሆነ ዛሬም ፣ ሊያፋጁት የቻሉት።
„…….እናንተ ኢትዮጵያውያኖች፣ ሳይቸግራችሁ፣ ለአለፉት ሺህ ዓመታት፣ የአንድነት ምልክት ሁኖ ያገለግል የነበረውን፣ ዘዉዱን“ አንዱ፣ እየቀለደብኝ እንዳለው፣ “…..ሳይቸግራችሁ፣ ጥላችሁት፣ ንጉሡንም አባራችሁ፣ ቀፎው ወድቆ፣ ንገሥቲቱዋ ሞታ፣ አለመሪ፣ አንደ ቀረ፣ የተበተነ ንብ፣ ሆናችሁ አይደለም እንዴ!“
ያለኝን፣ የአንድ አሜሪካዊ አነጋገር እሰከ አሁን ድረስ እኔ አልረሳሁም።
„…ንጉሥና፣ ዘውድ፣ ወዳጄ! እኛ ብቻ! ሳንሆን፣ እናንተም፣ አሜሪካኖቹ፣ …ፈረንሳዩም፣… ሩሲያም፣ ቻይናም… ጥላችሁታል “
እያልኩ፣ ስቆጥር፣ አቋርጦ ያለኝን ነገር ደግሞ፣ አሁንም፣ እኔ አልረሳሁም።
„…..አትርሳ! ዲሞክራሲ በአበበበት በታላቁዋ ብርታኒየም ሆነ በስውዲን፣ በዴንማርክ ሆነ በሆላንድ፣ በኖርዌይ ሆነ በስፔን፣ በቤልጂግ ሆነ…በሞናኮ….በጃፓን፣ አሁንም ቢሆን „ እሱ እንዳለው፣ „ዘውድ የአንድነት ምልክት ነው።“
እኔም ከዘውድ እኩል እንዲያውም ከዚያ የሚበልጡ፣ ሌሎች ጠንካራ የአንድነት ምልክቶች፣ እኛ ኢትዮጵያውያኖች አለን አልኩት።
„ምንድናቸው? እስቲ ቁጠርልኝ?“
አለ።
እኔም፣ አንድ፣…ሁለት ፣ …ሦስት…እያልኩ፣ መቁጠሩን፣ ተያያዝኩት።
ተገርሞ፣ ምን አልክ….እስቲ ፣ ድገምልኝ፣ አለ!
„ …ጭቆና እና ብዝበዛ የሌለበትን ገነተ – ሰማይን፣ በኢትዮጵያ ላይ፣ በምድሩቱ፣ በቅርቡ እናመጣላችሁዋለን` የሚለውም፣ ´የወጣት ኢትዮጵያኖች“ ቅዠት፣ ይኸው ዛሬ ያችን አገር ጎትቶ፣ ምን ዓይነት „ሲኦል“ ውስጥ፣ ሕዝቡን ጭምር እንደ ጣለ እና እነደሚያሰቃይ መገመቱ፣ ለአንተ፣ ከባድ አይደለም። “
ስል፣ ለአሜሪካኑ፣ ወደ መጨረሻው፣ ተናዘዝኩና አረፍኩ።
„የሚገርመው፣ ከዚህ ሁሉ መከራ በሁዋላ፣ አሁንም፣ ይህንኑ ጉዳይ ፣ እንደ ትልቅ ቁም ነገር፣ እነደ አዋቂ ሥራ፣ ስለ አለፈው „የመደብ ትግልና የብሔር ትግል ጀብዱ፣ ተራራ ያንቀጠቀጠ፣ ትግል፣ ራዕይ“ እያሉ፣ መጽሃፍ እየጻፉ፣ ፕሮግራም እየቀየሩ :- ከዚህ ሁሉ ዓመት በሁዋላ በእኛና በአራሳቸው ላይ መቀለዱ፣ የሚደንቅ፣ ነገር ነው፣“
ብዬ፣ ከሰውዬው ተሰናበትኩኝ። ለመሆኑ፣ ለምን አሜሪካኖቹም፣ እነሱን እንደሚረዱ፣ ጠየኩት። መልሱ ግን፣ የሚያስተዛዝብና ደካማ ነው።
፭
አሰከ አሁን ድረስ፣ በኢትዮጵያ ላይ የተዘሩት፣ የተነሰነሱት፣ ትምህርቶች ሁሉ፣ „በመካከላችን አሉ የሚባሉትን ልዩነቶቻችን“ የሚቀርፉ ሰይሆን፣ የሚያጠናክሩ፣ በዚያውም እኛን የሚበትኑ፣ አደገኛ ርዕዮተ-ዓለሞች ናቸው። አሁን ግን ጊዜው: – እንግዲህ በሥነ-ሥርዓቱ እንነጋገር ከኣላችሁ – ከአዋቂውም፣ ከተራ- ሕዝብም፣ የሚያሰተሳስረንን ትምህርቶች፣ ጥበቦችና ዕውቀቶችን፣ ፈልጋችሁ፣ አምጡልኝ፣ ብሎ፣የሚጣራበት፣ ዘመን ነው።
„የመደብ ትግል“ የሚባለው ነገር፣ ለመድገም፣ የመደብ ጦርነትን፣ የሚያስተምር ትምህርት ነው። የብሔር ትግል ደግሞ፣ ይባስ ብሎ፣ (የአለፈው ጊዜ ምሥክር ነው) ለዘርና ለጎሣ ጦርነት ሕዝቦችን የሚጋብዝና እነሱንም የሚበትን፣ ርዕዮተ-ዓለም ነው ። ከዚያም በላይ፣ሁለቱም ትምህርቶች፣ አምባገነኖች ሥልጣን ላይ፣ አጭበርብረው የሚወጡበት፣አልወርድም ብለውም የሚቆዩበት፣ የማጭበርበሪያ መሣሪያ፣ እርካን ነወ።
በአጭሩ እላይ የተባለውን ሰብሰብ አድርጎ ለማስቀመጥና ለመናገር፣ የአለፉትን ሃምሳና ስድሳ ዓመታት፣ ፊደል የቆጠሩና ተማሩ የተባሉት፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ወርቃማውን ጊዜአቸውን፣ ያጠፉበትና የሳለፉበት፣ ጉዳይ እሱ ምንድነው? ተብሎ፣ ዛሬ ተጠይቆ፣ ምርመራ ቢካሄድበት፣ ከዚያ የሚገኘው መልስ፣ ግልጽና አንድ ነገር ብቻ ነው። እሱም ሕዝቡንና አገሪቱን አንድ በሚያደርግ ጠቃሚ ነገር ላይ ሳይሆን፣ አገሪቱን በሚበትን ፣ ሕዝቡን በሚያፋጅ፣ ርዕዮተ-ዓለም፣ በእሱም „ትምህርት“ ላይ፣ ብቻ አተኩረው፣ ሰዎቹ የእራሳቸውንና የሌሎቹን ሕይወት አበለሰሽተዋል፤ ነው !!!
እንግዲህ አሁን ጊዜው፣ ለአገራቸው ማሰብ ከሚችሉት ሰዎች፣ የሚጠብቀው፣ አንድ ነገር ብቻ ነው።
እሱም፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያኖችን የሚያስተሳስር፣ አዲስ ጥበብና ብልሃት ፈልጎ ማስቀመጥ ነው። ምንድ ነው ያ እኛን መልሶ የሚያሰተሳስር ነገር? …..ይህን የሚነግረን ሰው ከመካከላችንስ አሁን አለ?
ለመሆኑ እኛን ኢትዮጵያኖችን ከእንግዲህ፣ ከእዚህ ሁሉ ዓመት በሁዋላ መልሶ አንድ፣ የሚያደርገን ነገር፣ የሚሰበስበን ትምህርት፣ ከአለስ….. እሱ ምንድነው?
ለዚህ ፣ ከባድ ጥያቄ፣ የምንሰጠው፣ መልስ፣ እሱ ብቻውን፣ ወደፊት…. መንገድም ነው፣ ….ግብም ሁኖ የሚያገለግል ነው።
ታዲያ እህቶቼና ወንድሞቼ፣ እሱ ምን ይመስላችሁዋል?… ከዚህ ሁሉ ደም መፋሰስ በሁዋላ፣ ከዚህ ሁሉ፣ የዕብደት ዘመንና ትርምስ ጊዜ፣…. የመወናበድ አመታት፣ ከዚህ ሁሉ ጥፋትና መኣት፣ ከዚህ በሁዋላ፣ እኛን ሁላችንን፣ መልሶ፣… እንደ አንድ ቤተ ሰብ ልጆች፣ አንድ አድርጎ የሚያፋቅረን፣ …..የሚየሰተሳስረን፣ ሰንሰለት አለ ብላችሁ ትገምታላችሁ? ታዲያ! እሱ …..እኛን የሚያቀራርበን፣ ጥበብና ዕውቀት፣ ምንድነው? …..ምንስ? ይመስላችሁዋል?
አንድን ሕብረተሰብ – ነጭ ይሁን ጥቁር ፣ ቢጫ ይሁን ቀይ፣ የተካለሰ ይሁን የተቀየጠ፣የተደበላለቀ፣ እነሱን ሁሉ ….ሕብረተሰቡን፣ …..እዚያም ሕብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩትን የተለያዩ ሰዎችን፣ ዜጎቹን፣ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ። ….ግን ይሄ ነገር – ይህ ምስጢር ምንድነው?
፮
„ተመልሶ ደግሞ በዚህ እኛ „ጥለነው በሄድነው“ ነገር፣ መጣ እነዳትሉኝ“ …አንጂ፣ እኛን መልሶ አንደ ዱሮው አንድ የሚያደርግን አንድ ነገር ቢኖር፣ ሌላ ሳይሆን፣ እራሱ፣ „የኢትዮጵያ አብዮት“ ነው።
ጥያቄው ግን፤ የጥያቄዎቹ ሁሉ ጥያቄም፣ ምን ዓይነት አብዮት ነው? የሚለው ነገር ነው ።
የሚገርመው ነገር፣ ይህ „የዘንድሮው አብዮት“፤ እንደ አለፈው ጊዜ፣ ብቻውን፣ ተመልሶ አልመጣልንም።
„….ደግሞ ማንን ይዞ፣ ማንን፣ አስከትሎ ዘንድሮ ብቅ አለ?“ … ልትሉኝ ትችላላችሁ።
መልሴ አጭርና ግልጽ ነው። የዘንድሮው አብዮት፣ „ፈጣሪ አምላካችንን እግዚአብሔርን“ አስከትሎ ነው የመጣው። „…ተመስጌን አምላኬ፣…ወይም፣ ….አላህ አክበር….“ ብሎ፣ በምስጋና ጥሪ፣ –በደንብ ከአዳመጣችሁ– የሚጀምር፣ የጀመረ፣ አብዮት ነው።
„እግዚአብሔር ሞቶአል! ። ሞተ፣ ተብሎም፣ በአሰተማሪአችን፣…. በአስተማሪዎቻችን፣ አልተወራም እንዴ?“፣ ብላችሁ፣ አንዳዶቻችሁ ፣ ዛሬ፣ ልትቀልዱም ይቃጣችኋል! ልታፌዙም ትችላላችሁ።
አዎ፣ ፍሬደሪክ ኒቼ ፣ አንዴ! በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ፣ „እግዚአብሔር ሞተ“ ብሎ ቀልዶ፣ ያ! ፈላስፋ፣ ለጋ ወጣት ተማሪዎቹን፣ ይህን፣ የመሰለ ሐሳብ ያኔ፣ አስተምሮ፣ እነሱንም፣ አሳስቶ፣ እራሱም በመጨረሻ አብዶ፣ ከዚህቺ ዓለም፣ ተሰናብቶ፣ ፈለስፋው ሄዶአል።
እንደገና የጀርመኑ ካርል ማርክስ ቀበል አድርጎ፣ „ሃይማኖት አደንዛዥ – መርዝ ነው „ ብሎ፣…. የቄሱንም፣ …የጨዋውኑም፣ የሠራተኛውንም፣… ልጅ አሳስስቶ፣ ሰውን ሁሉ በመደብ ከፋፍሎ፣ እነዲፋጁም፣ ምሁሩ፣ ማርክስ፣ እሳት ለኩሶ፣ እሱም ሰውን ሁሉ ለመጨረሻው ጠብ ጋብዞ ፣ ዞር ብሎአል።
ከአንድ መቶ ሃምሳ አመት በሁዋላ ደግሞ፣ ሳሙኤል ሐንቲንግ ተን፣ የሚባል አንድ የአሜሪካ ምሁር ተነስቶ፣ „መጪው የ21ኛው ክፍለ- ዘመን፣ የሃይማኖት ጦርነት ዘመን „ብሎ አውጆ፣ ተንብዮም፣ …እሱም ፣ በተራው ከዚህች ዓለም በሞት፣ ተለይቶአል።
ሳሙኤል ሐንቲንግ ተን፣ ይህን ሲል፣ „የእስላምና የክርስቲያን – የኦሪየንቱ እስላምና፣ የኦክሲደንቱ የምዕራብ ክርስቲያን“- በሌላ ቋንቋ፣ አረቡና ነጩ፣ አንድ ቀን ይዋጣላቸዋል፣ማለቱ እንደሆነም፣ እሱ እራሱ፣ ሲጠየቅ፣ ማስረጃ እያቀረበ፣ በጊዜው መልስ ሰጥቶበታል።
ይህ፣ ጉዞ እንግዲህ፣ ለእነሱ ለምዕራቦቹ ነው። ግን ለእኛ ኢትዮጵያኖቹ፣ አንቀው ከያዙን ከአረመኔዎች አገዛዝ፣ ለመላቀቅ፣ ያለን ምርጫ፣ ፍጹም፣ ሌላ መንገድ ነው።
ለማስታወስ! የካርል ማርክስን እና የነቼን፣ ትምህርት የቀመሱ፣ በትንሹም ቢሆን በእነሱ የተጠመቁ፣ „ነጻ- አውጨዎችና የደፈጣ ተዋጊ ኮሚንስቶች“ ጥሪውን እንደ ትልቅ ነገር ቆጥረው፣ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ – የዓይን ምስክሮች፣ ያኔ እንዳሉት- አቃጥለዋል። ታቦት ሠርቀው ሸጠዋል። ግምጃ ቤቱን ሰብረው፣ ወርቁን፣ ልብሱን፣ አክሊሉን ….ዘርፈው፣ ባህር ማዶ አሸጋግረው፣ ለነጮች፣ እነሱ እራሳቸው አሰረክበዋል። እነዚህ ሰዎች አሁንም አላርፍ ብለው፣ ገዳምና ቤተ-ክርስቲያናችንን፣ ወደ መፈታተኑም ተሸጋግረዋል። የሞስሊም አማኞችንም በኢትዮጵያ ለመበተን ተነስተዋል። መጪው፣ አብዮት፣ ደግሞ ለእንደዚህ ዓይነቱ፣ የአረመኔዎች ተንኮል፣ አንዲት ቀዳዳም፣ እንደምናየው፣ ለእነሱ፣ አልሰጥም ።
፯
ምንድነው፣ ታዲያ እኛን ኢትዮጵያውያኖችን፣ ከዚህ ሁሉ የመከራ ዘመን በሁዋላ ሊያሰባስበን የሚችለው ትምህርት?- ለሚለው ጥይቄዬ፣ መልሴ፣ ሌላ ነገር ሳይሆን፣ አውጥቼ አውርጄ፣ እንደደረስኩበት፣ እሱ፣ የቆየው፣ ሃይማኖታችን፣ ሃይማኖቶቻችን፣ ብቻ ናቸው። … እስላሙም ሆነ ክርስቲያኑም፣ አይሁዱም፣ ጭምር፣ አንድ ላይ ሁነው የሚያመልኩት ፣ አምላካችን፣ የእሱ የእግዚአብሔር፣ ትምህርት ነው።
በአሱ ብርታትም፣ በአሱ ስም፣ …..በዚህ የቀና መንፈሳዊ መንገድም፣ በዚህ፣ በጨበጥነው፣ እምነታችን ፣ በእግዘለአብሔር ኃይልና በእሱ ከንድ፣ እኛን ለመበትንም የመጡትን፣ አረመኔዎች፣ እኛ፣ እሱ፣ ይክበር ይመስገን፣ እያልን፣ ልንበትናቸው እንችላለን። ተደናግጠው፣ የተበተኑትንም፣ ወገኖቻችንንም፣ በአሱ በእግዚአብሔር ፈቃድና ቸርነት፣እንደገና፣ እነሱን ከተሰደዱበትና ከወደቁበት ቦታ፣ ፈልገን፣ እነሰበስባቸዋለን።
ሃይማኖት፣ እመኑኝ፣ አንደኛውና ዋነኛው፣ (ከሌሎች አገሮች፣ ከታሪክ መስተምሮ ሁሉ የምንገነዘበው!) ያችን አገር ኢትዮጵያን ያዋቀረ፣ ያንን ሕዝብ ያስተሳሰረ፣…. አንድ ያደረገንም፣… ድርና ማግ፣ ጣራና ምሶሶ፣ ግንብና መሠረት ነው። አለ-ምክንያት አይደለም፣ ኦሪት ዘ-ፍጥረት፣ የመጀመሪያው ገጽ ላይ፣ „ኢትዮጵያ“ የሚለው ቃል፣ ከአዳምና ሔዋን ጋር አብሮ፣ የሠፈረው። አለ–ምክንያት፣ አይደለም፣ የነቢዩ መሐመድ፣ የመጀመሪያ ተከታዮች፣ ወደ ኢትዮጵያ ተስደው የመጡት። አለ–ምክንያት አይደለም ማርያምና ክርስቶስ፣ ከዮሴፍ ጋር ግብጽን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የዘለቁት። አለ ምክንያት አይደለም፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ፣ ከወሃ ጥፋት በሁዋላ፣ በተሰየመው፣ የቀስተ ደመና ፣ ቃል-ኪዳን፣ ቀለም፣ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት፣ ያሸበረቀው።
ከእንግዲህ ማጭድና መዶሻ፣ ወይም፣ የወያኔ ጠበንጃና ቀለሃ፣ ኢትዮጵያን ይበትናታል እንጂ፣ እነዚህ በኣርማነት፣ እሱዋን፣ እናት አገራችንን፣ ምን ጊዜም አንድ አያደርጉዋትም።
ምልክታችን፣ ኢትዮጵያ እንዳትጠፋ፣ ከፈለግን፣ ቀደም ሲል አንስቼአለሁ፣ የሙሴ ታቦት፣ የክርሰቶስ መሰቀል፣ እና የነቡዩ መሐመድ ጨረቃ-ኮከብ፣ ናቸው። እንደገና ለመድገም፣ በቅዱስ ቁራንና በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ዘጠና ሚሊዮን ሰው አንቀሳቅሶ፣ አረመኔዎቹን ማባረር ይቻላል። ከቅዱስ ቁራንና ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያን ኣንድ ህዝብና አንድ የሚያደርገን፣ እራሱ ታላቁ አንድ እግዚአብሄር ነው!
ሎሎች እኛን ኢትዮጵያኖችን አንድ ያደረጉንን ነገሮች ብዙ ስለሆኑ፣ እነሱንም ወረድ ብሎ ማንሳት፣ ይቻላል። እንዃን ኢትዮጵያ ፣ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የነበረች አገር ቀርቶ፣ „ትላንት በችኮላ፣ የተዋቀሩትም ኃያላን መንግሥታትም“፣ በረካታ አንድ የሚያደርጋቸው፣ንጥረ -ነገሮች፣ በበቂ፣ እነሱም አሉአቸው።
ወንድሞቼና እህቶቼ …አባቶችና እናቶች፣ እኛን፣ ልዩ የሚያደርገንን ታሪክ፣ …. አንድ ….ሁለት፣ ሦስት…. እያልኩ፣ ሌላ ጊዜ፣ በቅርቡ፣ እነሱንም፣ እቆጥርላችሁዋለሁ።
ከሙዚቃው፣ ትዝታን ወስጄ አጫውታችሁዋሉ። የጤፍ እንጀራውንና የዶሮ ፍትፍቱን አነሳለሁ። ጠላውንና ጠጁን፣ ፉከራውንና ቀረርቶውን ፣ አሰታውሳለሁ። ሸማውንና፣ በርኖሱን፣ …ደቦና …ዕድሩን፣ የጉግስ ግጥሚያውንና ፣ የገና ጨዋታውን፣ አደኑንና ጦርነቱን ቡሄንና አበባዬ ሆይን….በትንሹም ቢሆን፣ እቆጥርላችሁዋሁ።….ድርሰት አለ።…ፊደላችን፣አለ። የቅዳሴና የጸሎት ሥነ-ሥርዓተችን ከሁሉም፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለ እምነታችን፣ (ያኔ ሌሎቹ፣ በጣኦት ያመልኩ፣ ወይም፣ ዛፍና ሜዳ ላይ ይዘሉ፣ ነበር) ለአንድነታችን ወሳኝ ነው። …. አዎ ብዙ ሌሎች ሌሎችም አሉን! ብዙ ዝርዝሮች አሉኝ።
ግን እሱ ብቻውን፣ እምነት…. ያለ ፍቅር፣ ሐዋሪያው ጳውሎስ አንዴ ተጠይቆ እንደ አስተማረው፣ ዋጋ የለውም። ….ከሁሉም፣…“ ከተስፋና ከእምነት…“ የሚበልጠውና እኛን ኢትዮጵያኖችን፣ እንደ ገና አንድ አድርጎ የሚያስተሳስረን ነገር ቢኖር፣ እሱም፣ ፍቅር ነው።
እስላሙና ክርስቲያኑ አንድ ላይ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ አደባባይ የወጣ ዕለት፣ ያኔ እኛ ከከአለንበት ማጥና፣ ከገዥዎቻችን – መንጋጋ ነጻ – እንወጣለን። አለበለዚያ፣ ….የኢራክና የአፍጋንስታን፣ የሱዳንና የሶሪያ፣ …የሊቢያና የዩጎዝላቢያ፣ ዕጣ ዕድል ውስጥ፣ (የሃይማኖት ጦርነቶች እዚያ ተንኮለኞቹ እንደፈተፈቱት) እኛንም (- እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባይው፣ ጠላታችን ብዙ ነው።) ከተው ዞር ይላሉ።
ተፈሪ መኮንን
ዛ ሬ ….. መልካም የ2005 ዓ ም የትንሳኤ በዓል፣ ለሁላችንም ይሁንልን እላላሁ!
*********************************************************************
ለዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ አስተያየት ለመላክ / To contact the author: teferimak@gmail.com
********************************************************************************************************
*
ሕግ፥ነክ ማስታወሻዎች / Disclaimer & Legal Statements > Le’Aimero’s Disclaimer