ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት –የኢትዮጵያ ባህልና ሥልጣኔ አነሳሱና አመጣጡ (PDF)
Some remarks on Ethiopian civilization….
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት
የኢትዮጵያ ባህልና ሥልጣኔ አነሳሱና አመጣጡ
….. እኛ ማን ነን?
፩
አንድ ጊዜ ፣ከጥቂት ወራት በፊት፣ የአገሬ ልጆች፣ ቀለል በአለ ቋንቋና አቀራረብ፣ ማንም ሰው ሊረዳው በሚችለው ዘዴና መንገድ፣ ኢትዮጵያን፣ ከሌሎቹ የአፍሪካ መንግሥታትና ከአካባቢ ፣ የአረብ አገሮች ልዩ የሚያደርጋትን ነገር ፈልገህ፣ ፈልፍለህ፣ ሰብስብ አድርገህ፣… ከየት ኢትዮጵያ እንደመጣች? ….እኛ ማን እንደሆን? ባህላችንና ታሪካችንን፣ ሥልጣኔአችን ጭምር፣ በምን ላይ እንደተመሰረተ፣ ቅልብጭ ያለች ነገር፣ በጽሑፍ አዘጋጅተህ፣ ለነጮቹም፣ ለእኛም ፣ ንግግር አድርግልን፣ ብለው ጠይቀውኝ ነበር።
እኔም በደስታ ጥያቄውን ተቀብዬ፣ የሚከተለውን ጽሑፍ ፣ ያኔ አቀረቤላቸው ነበር። ይህን ጽሑፍና፣የዚያን ጊዜ ንግግሬን ያዳመጡ ሰዎች፣ “ምን አለበት ከቻልክ በአማርኛ ተርጉመህ፣ ለእኛም፣ለሌሎቹም፣ እንዲያውቁት፣… እንዲዳረስ፣ ብታደርግ ደግ ነው” ብለው እንደገና እነሱም፣ ጠይቀውኝ ነበር።
ስመለከተው ጥያቄአቸው፣ ትክክል ነው።ሌላውም ሰው ቢያውቀው ጥሩ ነው ብዬ ይኸው፣ ተርጉሜ፣ ማንም ሰው እንዲመለከተው፣ አሁን፣ በደስታ አቅርቤላችሁዋለሁ።
“ባህልና ሥልጣኔ”፣ በተለያዩ አገሮች የተለያዩ ትርጉም፣ ቢኖራቸውም ፣ እኔ ለጊዜው፣ ሁለቱን ስያሜዎች፣ ማለት፣ቃላቶች፣ አንድ አድርጌ ወስጄአለሁና፣በዚህ አጠቃቀሜ፣ ግራ እንዳትጋቡ፣ተ-ወዲሁ ይቅርታ እናንተን እጠይቃለሁ።
፪
የቆየና የኖረ፣ በብዙ ሽህ አመታቶች የሚቆጠሩ፣ ባህልሎቹዋንና፣ ሥልጣኔዋን፣ …የሕዝቦቹዋንም ልማድና ወግ፣ ሥርዓትና ደንቡዋን ፣ የእሱዋንም፣ አሁን አሉ፣ ከሚባሉት ፣ ምናልባት ፣ ትላንት ከተመሰረቱት፣ ኃያላን መንግሥታት፣የታሪክ ቆጠራ ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር፣ በስንትና ስንት ዘመናት አጣፍቶ የሚሄደውን ታሪኩዋን ጠለቅ አድርጎ ለማቅረብ መሞከሩ ቀርቶ፣ ገረፍ፣ገረፍ አድርጎ እንኳን፣ በችኮላም መሄዱም፣ ቀላል እንዳልሆነ፣እናንተም አንባቢዎቹ፣ በደንብ ታውቃላችሁ። ይህን ጉዳይ ለእናንተ አሁን ማንሳቱ አሰፈላጊ አይደለም። የሆነው ሁኖ፣ ከብዙ በጥቂቱ፣ የእኔ ሙከራ ይህን ይመስላል።
እንደምናውቀው፣ ኢትዮጵያ አገራችን፣ያኔ እነደተማርነውም:- የዛሬን አያድርገውና- የሦስት ሺህ አመት ታሪክ የአላት አገር ናት። አንድንድ ጸሓፊዎች፣ ከዚህም አልፈው፣ ወደፊትም ተራምደው፣ ይህቺ አገር፣ከአምስት ሽህ አመት በላይ እንደኖረችና እንደቆየችም፣ይናገራሉ፣ እነሱም ፣ይጽፋሉ። ሌሎቹ፣ ደግሞ ረጋ ብለው፣ ሰባት ሽህ አመት የሚለውን አሃዝ፣ ለእኛ ይመርጣሉ።
ተመራማሪ ጠበብቶች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ቆፍረው ከአገኙት ጥንታዊ ቅርሳ-ቅርሶች ተነስተው፣ ከአርባ ሽህ አመት በፊት፣ የሰው ልጆች ፣ አሁን ኢትዮጵያ ተብሎ በሚታወቀው ግዛት ውስጥ፣ ይኖሩ እንደነበርም ፣በደረሱበት ጥናታቸው፣ ሁሉም ተስማምተው ይህን ሐቅ በአንድነት ያረጋግጣሉ።
ትልቁዋ አዛውንት ባልቴት፣ የሰው ልጆች ሁሉ “እናት” የምትባለውም “ድንቅነሽም”፣ –ይህቺ ሴትዮ፣ምናልባት፣ ሔዋን ትሆን?- ከ3.5 ሚሊዮን አመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ትኖር እንደነበር፣ ከእነማሥረጃው ለዓለም ሕዝብ፣ ታሪኩን፣– ይኸው፣ ቢያንስ አጽሙዋ ከተገኘ አሁን አርባ አመት ይሆነዋል፣–በንግግርም፣በመጽሐፍም መልክ፣ ተመራማሪዎቹ አቅርበውልን ፣ እኛንም፣ ሌሎቹንም በሥራቸው ውጤት አስገረመዋል።
፫
የሚያሳዝነው ግን፣ ወይም የሚገርመው፣ዘንድሮ ማለት እንችላለን፣ ይህን ሁሉ ነገር እያወቁ፣ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ በተለይ የተወሰነ የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው ፣አገሪቱን ማተረማመስ የሚፈልጉ ኃይሎች፣ የዚህችን አገር ዕድሜና ታሪክ በእነሱ ዓይን ወደታች ጎትተው፣ “አንድ መቶ አመት ብቻ ነው”፣ ብለው ደፍረው፣ እኛንም ሆነ የተቀረውን ዓለም ለማሳመን በኃይል ጭምር፣ ብዙ፣እነዚህ ሰዎች ደክመዋል። የእንደዚህ ዓይነቱ አቀራረብና የታሪክ አጻጻፍ፣ ግንባር ቀደሞቹ ደግሞ:- ይህ ሓሜት አይደለም፣ማንም ሰው ያውቀዋል- እራሳቸውን “ነጻ-አውጪ” ብለው የሰየሙ በርካታ የተገንጣይ በድን፣ ድርጅቶችና መሪዎች ናቸው። የካድሬውን ቅስቀሳ ግን ለጊዜው ፣ጥቅም ስለሌለው፣ ወደ ጎን እንተወው። እሱ እራሱን የቻለ ሌላ ታሪክ ነው!
እንደዚህ ዓይነቱ አቀራረብና የታሪክ አጻጻፍ:– ተጨባጩ ሁኔታ፣ዛሬ ምስክር ሁኖ እንደሚያሳየን– ለአለፉት አመታት አገሪቱን ኢትዮጵያን… የጦርነትና የቀውስ፣የፍጅትና እንዲሁም የትርምሰ ሜዳ እንድትሆንና፣ እዚያም ውስጥ አገሪቱ እንድትገባ፣ ይህ፣ አሳዛኝ ሥራና ትምህርት ፣ የተቻለውን አሰተዋጽኦ፣ጥሩ አድርጎ በአለፉት ጊዜ አበርክቶአል። …ረሃቡ፣… ድህነቱ፣ የበሽታ የመስፋፋቱ፣… ስደቱ፣… ለየት ያለ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ክትትሉና ግድያውም፣….እሥራቱም…ይህ ሁሉ መኣት የመጣው ደግሞ፣ ከሌላ ነገር ሳይሆን፣ ከዚሁ የተሳሳተ፣ ወይም አውቆ ከተነደፈ አጀንዳም የመነጨ ነው። ጊዜዋንም:- አገሪቱ- ሐብቱዋንም፣….ጉልበቱንም ፣… ሕይወቱንም ፣ ልጁንም፣ ሰው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ን ጭምር ፣ ያጣችውና፣ ወላጆች ያጡት፣ በዚሁ፣ መሰረት በሌለው፣ በከንቱ ውዳሴአቸውና አንዴ በጀመሩት ቅጀት ሳቢያ ነው።
ለመሆኑ ምን አተረፍን? ….ምንስ ተገኘ? ማነው ዛሬ የዚህ ሁሉ ትረምስ ተጠቃሚ?…ማነውስ ዛሬ ተጠያቂው?…የሚለው ጥያቄ ሲነሳ፣ዞሮ ዞሮ መልሱ፣በአንድ ነጥብ ላይ የሚያነጣጥር ነው።እሱም ያ ሁሉ ነገር፣በመጨረሻ የጠቀመው፣አምባገነኖችንና፣ከድሮም ጀምሮ ኢትዮጵያ ተበትና እንድትጠፋ የሚፈልጉትን ኃይሎችን ነው።
ዛሬ፣ በዓለም ዙሪያ፣ ቤታቸው፣መንደራቸው፣ አገራቸው፣ በዚህ የእርስ በእርስ ጦርነት ፈርሶ፣ የኢትዮጵያ ስደተኞች፣ ሰብሳቢ አጥተው፣ የትም ቦታ ሲንከራተቱ እናያለን።ብዙ ቦታም እነደ ዕቃ፣በየበረሃው አሸዋ ውስጥና በየባሕሩ የትም ወድቀው፣ የአሞራ፣ወይም የአሣ-ነባሪ ምሣና ራት ሁነው ቀርተዋል።
….አሽከርና ገረድ፣ ሴተኛ አዳሪና፣…በር ጠባቂ ዘበኛ፣የሆኑ ኢትዮጵያኖች … በአረቦች ቤት:- በመካከለኛው ምሥራቅ፣ዛሬ ሲረገጡ፣ሲደበደቡ፣…የሞት ፍርድም ሲፈረድባቸው እንሰማለን። በዩቱብ እናያለን። ሌላው ቀርቶ፣የእናታቸውን ጡት ያልጨረሱ ሕጻናት ልጆች ሳይቀሩ ለጉዲፈቻ ወደ አሜሪካንና ወደ አውሮፓ፣ከቅርብ ጊዜ፣ እነዲጎርፉም ተደርጎአል።ስንት ልጆች አገራቸውን ጥለው ወጥተዋል!
ይህ ሁሉ መአትና ጉድ ያሳፈራቸውና የሚያሳፍራቸው ኢትዮጵያኖች ቁጥር፣ጥቂት አይደለም። ብዙ ናቸው። በውጭ አገር ፣በደረሱበት ቦታ፣ ከየት መጣችሁ ተብለው እነሱ፣ በፈረንጆች ሲጠየቁም፣ መልሳቸው፣የእነሱ፣ከጥቂት ጊዜ ወዲህ፣ የሚደንቅም የሚገርምም፣ ሁኖአል። ያ ! ዱሮ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ፣ማንነቱን የማይደብቀው ሰው፣ ዛሬ ….ከጃማይካ፣ ከሓይቲ፣ ከኬንያ፣….የሚሉ:- እንደምንሰማው- ሁነዋል። ቁጥራቸውም ዘንድሮ ትንሽ አይደለም።
እንደምናውቀው፣ ብዙዎቹ የካሪቢክ አገር ሰዎች፣በተቃራኒው፣ ሲጠየቁ፣ የአመጣጥ ዘራቸውን እየቆጠሩ፣ የዘር- ግንዳቸውን እየሳቡ ከኢትዮጵያ እንደሆነና እነሱም “የራስ-ተፈሪያን” ወገን እንደሆኑ እሰከ ዛሬ ድረስ ሳይደብቁ በዚህቺ አገር ይመኩባታል። እራሳቸው አብዛኛው የአፍሪካ አገር ሰዎችም ከናይጄሪያ ይሁኑ ከማሊ ከሀሩዋንዳ ይሁኑ ከብሩንዲ ከኬንያ ይሁኑ ከማደጋስካር፣ከሱማሌ ይሁኑ ከሱዳን፣- ዝርዝሩ ብዙ ነው- …ዘራቸው ፣…. ወላጆቻቸው፣ዘመዶቻቸው፣ አንዴ፣ ከኢትዮጵያ ፈልሰው እንደወጡ፣ እነሱም፣ ሳያፍሩ፣ ይህን ታሪካቸውን መለስ ብለው ያስታውሱታል። ኮርተውም፣ – ይህ አይካድም፣ስታገኙአቸው፣ ጠይቁአቸው- ይናገራሉ።
፬
ግን፣ በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ፣ ልዩ የሆነ፣የእራሱን ታሪክና ነጻነቱን ጠብቆ፣ በማንም ሳይደፈር የኖረ ሕዝብና አገር የለም ቢባል፣ ማጋነን አይደለም።
በአውሮፓ ሆነ በሌላ አካባቢ ያሉ አገሮችና ሕዝቦችን፣ታሪካቸውን ጠጋ ብለን ብንመለከት፣ ሁሉም በተለያዩ ጊዜያትና ዘመናት፣ በሌላው፣ በዘመኑ ኃያልና ጠንካራ በነበረው ጦር ተወረው፣ እንዲያውም ባሪያ ሁነው ተሸጠው፣ …የተጋዙ ሕዝቦች ብዙ ናቸው።
በሦስት ሽህ ወይም ከዚያ በላይ በሚቆጠረው ረጅሙ ታሪካችን አንድ ጊዜም፣ አንዱም፣ ጉልበተኛ ፣ኃያል መንግሥት፣ ከመሬት ተነስቶ እኛን በጦር ወግቶ፣ ቅኝ-ተገዢ ባሪያው አድርጎ አልሸጠንም። የኢትዮጵያ ልጆችም ፣ይህን ዓይነቱን መከራ ፈጽሞ አላዩም።
ይህ ማለት፣አገሪቱን ለመያዝ የሞከረ መንግሥት የለም ማለት አይደለም። ብዙዎቹ፣ሐብቱዋን አይተው፣ሌሎቹ፣ አየሩዋን ተመኝተው፣ የተቀሩት፣”ባሪያና መሥፈሪያ ቦታ፣ ፈልገው” እሱዋን ለመያዝ ከአንዴም ሁለቴ፣ እየተፈራረቁ ሞክረዋል። ግን እነሱ፣ይህን ዓይነቱን ሙከራ ሲያደርጉ፣ተይዘው፣ አይቀጡ ቅጣት፣በሕዝቡ ክንድ፣በአባቶቻችን ጦር ተቀጥተው አርፈው ሁሉም ተቀምጠዋል።
….ጣሊያን ዱሮ፣ በግሪክ ተይዛለች። እንግሊዝ በሮም …ግሪክ በቱርክ አሜሪካን በስቴን በፖርቱጋል በእንግለዝና በፈረንሣይ እንደ ገና እነዚህ ሁሉ አገሮች ጥንት በሮም መንግሥት ተይዘው ባሪያ ሁነው ተሸጠው በተለያዩ ጊዜያት በእነሱ ተገዝተዋል።በኢትዮጵያ ላይ ግን ይህ ነገር አልደረሰም ሲባል፣ተአምር የሚመስላቸው አሉ። ታላቁ እስክንድር፣ግብጽን፣ ሲይዝ፣ኢትዮጵያን አልነካትም። ዩለየስ ሴዛር፣ አፍሪካ ሲወርድ፣በመርከብ አባይ ላይ፣ ከቂሊዮፓጥራ ጋር ሲንሸራሸር እንደዚሁ ኢትዮጵያን አልደፈረም። የንግድ ልውውጥ ግን ነበር። ወርቁን፣የዝሆን፣ ጥርሱን፣ዝባዱን…የአንበሳና የአነር ቡችላውን፣ ከእኛ ይገዙ ነበር። ለምን ወርደው አልያዙንም?
ድፍን የአፍሪካና የእሲያ አገሮችም፣…ቻይና፣…. ሕንድ፣…. ኢንዶ ቻይና፣ ኮሪያ፣ መካከለኛው ሥራቅና አረቦች በሙሉ፣ የቅኝ ገዢዎች መዳፍ ውስጥ ገብተው ፣ ፍዳቸውን፣ በአሥራ ዘጠነኛውና በሃያኛው ክፍለ-ዘመን ሲያዩ፣ ኢትዮጵያ፣በተቃራኒው፣ ለእነሱ፣ ለነዚህ ፣ በብዙ ቢሊዮን፣ ለሚቆጠሩ ሕዝቦች፣ የነጻነት ችቦ ሁና፣ እንደ ምሳሌም፣ተጠርታ፣ እንደ ነጻነትም ተስፋ ፣ ተጠቅሳ፣ ለእነሱም ቆማ፣… ትታግል እንደነበረች፣ እነሱ እራሳቸው ፣ ሳይደብቁም ብዙ ቦታ ደጋግመው ጽፈዋል። ጋንዲ ና ማኦ ሴቱንግ፣ከእነሱ ውስጥ አሉበት።
፭
የእንግሊዞች የመንፈሳዊ ትምህርት፣ አስተማሪ ሚሲዮኖች ናቸው፣ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን፣ በሰሜን አሜሪካና በካሪቢክ አገሮች፣ እሁድ እሁድ፣ በቤተክርስቲያን የጸሎትና የሰበካ ሰዓቶቻቸው፣ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል፣ከመጽሐፍ ቅዱሱ፣ እየጠቀሱ በዘመኑ በጥቀሮች ላይ ነግሰው ለነበሩት ነጮችና፣ በትላልቅ እርሻዎች ላይ ተሰማርተው፣ ለነበሩ ለአፍሪካውያኖቹ:- ለባሪያዎቻቸው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ይህቺን፣ሁሉን ቀድማ፣ የክርስቲያን አገር፣ የሆነቺውን:– ኢትዮጵያን– ያኔ ብድግ ብለው ያስተዋወቁት።
“የሰው ልጆች ሁሉ፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ፣ ጥቁር ይሁን ነጭ፣ ቢጫ ይሁን ቀይ፣…ክልስ ይሁን፣ ለምጣም….የእሱ የፈጣሪ ልጆች ስለሆኑ እኩል ናቸው” ፣ ብለው፣ የእንግሊዙ ቄሶች፣ ቢያንስ፣ በቤተ ክርስቲያኑ መቅደስ ውስጥ፣ ጥቁሮቹ ወንበራቸውን ይዘው፣ አብረው ከነጮቹ እኩል፣ ወንበር ላይ ተቀምጠው፣ ለአምላካቸው፣እንዲጸልዩም ገዠዎቹን፣ያኔ ፣ እነሱ፣ ጠይቀወ፣ ሥርዓቱን አናግተዋል። በሁዋላ ወጣቱ መሥፍን፣ ተፈሪ መኮንን ብቅ ይላሉ።
ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን፣ የጎንደር ንጉሥ ተብለው፣ ዘውዱን፣በንግሥት ዘውዲቱ ሥር ሲደፉ፣ ትንሽ ቆይቶም፣ እኝሁ መስፍን፣ “ ቅባ ቅዱሱን ተቀብተው፣ ዙፋኑ ላይ ተቀምጠው፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ- ነገሥት “ሲባሉ፣ በመላው ዓለም፣ ተበትነው ፣ የሚገኙ ጥቁሮች ሁሉ፣ ያኔ ፣ ታትመው ይወጡ የነበሩት ጋዜጣዎች ላይ ተጽፎ የነበሩትን ቃላቶች፣ አሁን መለስ ብለን ስንመለከተው፣ የደስታው ተካፋይ ብቻ ሳይሆኑ፣ የእነሱም የነጻነት ቀን ፣ እንደተቃረበ አድርገውት፣ ሁኔታውን እንደተቀበሉት፣ እንደቆጠሩትም፣ ከእነሱ ውስጣዊ ስሜት እንመለከታለን።
በእርግጥም ኢትዮጵያ ፣ ለእራሱዋ ነጻነት ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎቹም ቅኝ ተገዢ ሕዝቦች፣ለእነሱ ነጻነት፣ በግንባር ቀደምነት፣ ቆማም፣ይህቺ አገር ለሕዝቦች፣ እኩልነት ታግላለች። በሃያኛው፣ ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ላይም፣ በኢትዮጵያ ጥረትና ድክመት፣ ብዙ የአፍሪካና የእስያ አገሮች፣ከቅኝ ግዛት አገዛዝ ነጻም ሊወጡም ችለዋል።
እንግሊዝና ፈረንሣይ፣ ጣሊያንና ስፔን፣ እንዱሁም ፖርቱጋል፣ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው በየተራ እየተዘዋወሩ፣…እየሄዱ፣ባንዲራቸውን እያወረዱ፣ እየጠቀለሉ ሲሰናበቱና፣ያን አገር ለቀዉ ሲወጡ፣ በቦታው ፣አፍሪካውያኖቹ፣ ያውለበለቡት፣ አዲሱ ሰንደቅ አላማቸው፣ (በተለያዩ ቅደም ተከተሎች ያሸበረቁ፣ እነዚህ ሰንደቅ አለማዎች) ሦስቱን፣ ቀለም ፣ – እዚህ ላይ፣ መናገር አያስፈልግም- አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ፣ነው።
ምንድነው፣ ለአገራቸው፣ መለያ ምልክት፣ ከሌሎቹ፣ ሁሉ ቀለሞች እሱን፣ብቻ መርጠው የተቀበሉት?
በዓለም ላይ፣( ይህን ለማያውቁት፣ጮክ ብላችሁ ንገሩአቸው፣) እንደ ነጻነት ምልክታቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ባንዲራ፣ በቁጥሩም በብዛቱም ፣ ብዙ መንግሥታት የተቀበሉት ሰንደቅ አላማ የለም። ከኢትዮጵያ ሌላ አንድም መንግሥት፣ባንዲራው ብዙ ቦታ አይታይም። የአሜሪካንን ወይም የእንግለዚን ባንዲራን የሚመስል ሰንደቅ አላማ፣ ብዙ አገሮች፣ ተቀብለው አያውለበልቡም!
ይህን ለመረዳት፣ የተባበሩት መንግሥታት በር ላይ፣ ትንሽ ደቂቃን ማሳለፍ ይበቃል። ይህም፣ዝም ብሎ ከሰማይ ላይ ዱብ ያለ፣ የአፍሪካውያኖች ውሳኔ አይደለም። ከኢትዮጵያ፣ነጻነትና ከእሱዋም ጋር የተያያዘ መተሣሰርን ያረጋግጣል።
፮
በአውሮፓ ምሁሮች ዘንድ፣ በአውሮፓ ገዳምና በቤተ ክርስቲያን አካባቢዎች፣ እንዲሁም ቀስ እያሉ እየተጠናከሩ፣ያኔ በመጡት ፣በዪኒቨርስቲዎች ቅጥር ግቢም ውስጥም፣ ይህቺ አገር ኢትዮጵያ፣ የምትታወቀው፣ ከመካከለኛ ክፍለ-ዘመን ጊዜ ጀምሮ ነው። ከዚህም አልፎም ወደ ሁዋላም ዘመን ይሄዳል።
የመስቀል ጦረኞች ዘመን ፣ያኔ ! ኢየሩሳሌምን ከአረብና ከቱርክ፣ እጅ እናስወጣ የሚሉ አውሮፓውያኖች፣በወዳጅ ፍለጋ፣ አንድ መላ ሲመቱ፣ ዞረው፣ ዞረው፣እነዚህ ሰዎች፣ የኔ ያገኙት አንድ ወዳጅ፣ቢኖር፣ ጻዲቁ ዮሐንስ የሚባለውን ስመጥሩውን የኢትዮጵያን ንጉሥ ነው።
ከጥንት ጀምሮ የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበለቺውን ኢትዮጵያ፣በጦርነቱ ላይ ማሳተፍ፣ ለእነሱ ለአውሮፓውያኖቹ፣ ቱርክንና አረቦቹን፣በሁለት አቅጣቻ ፣እንደ ጉጠት ነክሶ፣ ከዚያም፣ ከኢየሩሳሌም፣ እነሱን ማባረር ይቻላል፣የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰው ነበር።ይህም የማይገኝ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነም ተረድተው ነበር።
በጥንታዊ ሮምና በግሪክ ጸሓፊዎችም ዘንድ፣… በእራሳቸው፣ በፋርስና በአረብ ደራሲዎች፣ አካባቢ ፣ ኢትዮጵያን ከሁለትና ከሦስት ሺህ አመት በፊት በደንብ፣እነሱ ያውቁአታል። በተለይ ሆሜርና ሔሮዶት ፣በሁዋላም የተነሳው፣ ፔቶሌሜዮስ፣ እነዚህ ሰዎች፣ጥሩ አድርገው ፣ ስለዚህቺ አገር ጽፈዋል። ከሁሉም ጥንታዊው፣የግሪክና የሮም፣ኢትዮጵያን የሚያሳየው ካርታ ትልቅ፣ ምስክር፣ነው።
ትልቁ የጀርመን ፈላስፋ፣ ኢማኑኤል፣ ካንት፣በጽሑፉ የሚያወራላት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያኖች፣ እነሱ፣… እነማንናቸው?…. ለመሆኑ፣ ምንድናቸው?… ከየት ነው፣የመጡት?….መጥተውስ፤ የዓለም ፖለተካ መድረክ ላይ ብቅ ያሉት፣ በምን ብልሃትና ዘዴ ነው?
ለመሆኑ፣እነሱ በምን ጭንቅላታቸውና ችሎታቸው ነው፣ የአደዋ ጦርነት ላይ፣ ያኔ፣ ይፈራ የነበረውን ፣ ታላቁን የጣሊያን ጦር ሠራዊት ድል፣እነሱ ሊመቱት የቻሉት?
ለምንድ ነው፣ ያኔ በደንብ የታጠቀውና በሕንድ ተዋጊ ጦር፣ በዝሆኖች ጭምር፣ የታጀበው፣ የእንግሊዝ ሠራዊት፣ ቴዎድሮስን፣ እራሱን ኢንዲገድል፣እዚያ ሁኔታ ውስጥ ከተውት፣ የሁዋላ ሁዋላ፣ አገሪቱን ፣ኢትዮጵያን ሳይዙና የቅኝ-ግዛታቸው ሳያደርጉአት ፣ዝም ብለው፣ያ ጦራቸው፣ ልጅ ዓለማየሁን ብቻ ወስዶ የተመለሰው?
የኢትዮጵያ፣ ባህል?… የእሱዋም፣ሥልጣኔ ስንል፣ ምን ማለታችን ነው? ምንድነው፣ይህቺን አገርና ሕዝቡዋን፣ አንድ አድርጎ እስከ አሁን፣ ድረስ፣ ያቆየው? ምንድነው እነሱን፣ኢትዮጵያኖች፣ እንደሌሎቹ፣ሕዝቦች ሳይበታተኑ፣ አንድ፣ አድርጎ ያስማማቸው ምሥጥር?
፯
በምርምር ዓለም ፣የአንድን ሕዝብ ውስጣዊ ፣ተንቀሳቃሽ ነፍስ፣ እነሱን ሁሉ፣ አንድ የሚያደርግ መንፈስ፣…. የአንድነታቸውን የልብ ትርታ፣ እንዲያውም፣ አለፎ ተርፎ፣ እነሱን፣ እንደ አንድ ሰው ሰብስቦና አስተባብሮ፣ለብዙ ዘመናት፣…. በመቶና፣ በሁለት መቶ፣ በአምስትና በሰባት መቶ፣… ለሽህና፣ ለሦስት ሺህ አመታት፣ የሚያቆያቸውን ፣ አንዳች፣ያ! በዓይን የማይታይ ምሥጢራዊ የሆነውን ነገር፣ ፈልጎና ፈልፍሎ፣ እንደ ማግኘት ያለ፣ ከባድ ነገር ፣ በሳይንስ ዓለም፣ ውስጥ፣ ፈጽሞ የለም።
ለየትኛው ነገር፣….ነው? በየትኛውስ ፣ ብልሃት ነው? የአገሪቱ ባህልና ሥልጣኔ፣ ወግና ሥርዓቱ፣ ደንቡና ትምህርቱ ፣ ቅድሚያ ፣ በተለያዩ ዘመናት ሰጥቶ …አውጥቶና አውርዶ ተመካክሮም ያን ያገኘውን ነገር ጨብጦ እሱንም ለሰው ሁሉ ለዜጎቹ እንዲከተሉት አቅርቦ … አገሪቱንና ሕዝቡን አንድ አድርጎ ሊያዋቀረው የቻለው?
የአንድን ሕዝብ፣ ባህልና ሥልጣኔውን፣ አስተሳሰቡና አመለካከቱን፣ ለመረዳት፣ ያ ሕዝብ፣የተገነባበትን፣ ድርና ማጉን፣ አጥንትና ሥጋውን፣ ልቦናውንና፣ መንፈሱን፣ አሰከ የደም ጠብታውና የአጥንቱ፣ውስጣዊ መረቁ ድረስ፣ እሰከዚያ፣ ታች ድረስ፣ ወርዶ ፣ መመልከትን ይጠይቃል።ከዚያም፣ ወደሁዋላ፣ ተመልሶ፣ እስከ ፣ እያንዳንዱ ፣… ሰው በየፊናው፣ የቆመበትን፣መድረክ፣መቃኝትን ይጠይቃል። ከዚያም አልፎ፣ በጋራ እንደ ችቦ አንድ ላይ ዜጋው ሁሉ፣ ሰብሰብ ብሎ የቆመበትን አስተሳሰብ፣ መመልከትንም፣መምርመርንም፣ ያጠቃልላል።
በዚያው ላይ ፣ ሳይቆሙም፣ ከዚያም አልፎ፣ የሚሄድ፣ጠቅላላውን፣ አገሪቱንና ሕዝቡን ፣ አንድ አድርጎ፣ የተሸከመውን ፣ መሠረትና ምሶሶ፣ ምንድነው? ብሎ ጠይቆ፣ ያንንም፣ሥዕል አዕምሮ ውስጥ፣አስገብቶ፣ እሱን፣ ለመረዳት፣ የጠለቀ፣ ምርምርን፣ ማካሄድ ይጠይቃል።
የአንድን ሕዝብ፣ታሪክ፣ የዚያንም ሕዝብ ፍልስፍና፣ ቁጭ ብሎ፣መጽሓፍት፣ቤት፣ ተቀምጦ ማጥናት፣ ይቻላል። ግን ፣እሱ ብቻውን፣ በቂ አይደለም። ወግና ሥርዓቱን፣ ልማድና፣ሕግጋቶቹን፣ለኣማልክቶቹም፣በየፊና የሚያቀርበውን መስዋዕት፣ መቁጠርም፣ይቻላል። ግን ፣ እሱ ብቻውን፣ አሁንም፣ቢሆን፣ በቂ አይደለም። ወይም፣ደግሞ፣ የምጣኔ ሐብቱን፣ የእርሻ ምርቱን፣ የቴክንክ ችሎታውን፣ መዝግቦ ፣እነዚህን ሁሉ፣በእያለበት፣ ተዘዋውሮ፣ መመልከትን፣ይጠይቃል። እሱም ብቻውን አንድ ሕዝብ ለምን ይህን መንገድ ትቶ፣ ያኛውን እንደተከተለ፣ መልሱን፣በበቂ፣ እዚያ ውስጥ፣ አናገኝም። እሱም አይሰጠንም። በዚህ ዘዴና በእዚህ ጉዞ፣ በተለያዩ፣ ሳይንሳዊ፣ ጥበቦችና ምርምሮች፣ተንቀሳቃሹን፣ ሕይወት፣ ያለውን የአንድን ሕዝብ፣ መንፈስና ነፍሱን፣ የልብ፣ትርታውን ፣ ጭምር፣ ዋና እምብርቱን፣ማለት፣ እንችላለን፣ በዚህ ዘዴ፣…በዚህ፣የምርምር ጉዞ፣ በቀላሉ፣ ፈልጎ ፣ ማግኘት –የሚቻል ይመስላል እንጂ– ጨርሶ፣ አይቻልም።
የአንድ ህዝብ ባህልና ሥልጣኔ፣ በምሳሌ ለመናገር፣ እንክብካቤ፣ እንደሚያስፈልገው ፣ እንደ ትንሽ ቡቃያ፣ አታክልት፣ነው። ከጊዜ በሁዋላም፣ያ! ትንሽ ችግኝ …ደርቶ፣ አድጎ፣ አብቦ፣ጥላውን፣ ለአላፊ አግዳሚው፣ …ለአራዊቱም፣ ለሰውም፣ ለአዕወፋትም፣ይሰጣል። ይህ ትልቅ ዛፍ፣ ጥድ ወይም ፣ የግራር ዛፍ፣ አይነትም፣ ነው።
እዚያ፣ ለመድረስ፣ ብዙ አመታቶችን፣ ይጠይቃል። ያም ! ሊሆን የሚችለው፣እንደዚሁ በቀላሉ፣ አይደለም። ዛፉ የቆመበት አካባቢ፣መሬቱና አየሩ፣… ከታችም ፣ ከሚመግበው፣ ወሃና ያ ዛፉ የቆመበት፣ ምድረ-ከርስ፣እሱም፣ የሚሰጠው ፣ ጥሩ፣ ጥሩ ፣ንጥረ -ነገሮች፣ ምግቦቹም፣ ወሳኝ፣ ናቸው። በዚያም ተጠናክሮ፣ ሲወጣ፣ ብቻ፣ ነው፣ በሽታውን፣ ቀጠሎውን፣ ምስጡንና፣ አውሬውን፣ መክቶ፣ ለመቶና ሁለት መቶ፣ አመታት፣ ከዚያም አልፎ፣ አንድ ሺህ አመት፣ሊኖር የሚችለው። ስንቱ፣ችግኝ፣ ነው፣ ወሃና፣ ጠቃሚ ንጥረ-ነገሮችን አጥቶ፣በዚያው፣ ከሮ፣… ክቺች ብሎ፣በጸሐይ ደርቆ፣አመድ፣ሁኖ የቀረው።
ይህም ማለት፣ በሌላ ቋንቋ፣ አንድ ባህል፣ልክ እንደ፣ ትንሽ፣ ችግኝ፣ በዚህች ዓለም ላይ ብቅ፣ ሲል እንክብካቤ ያስፈልገዋል። ባህል፣ማለት፣ትልቅ ዛፍ ነው፣የሚባለውም ለዚህ ነው!
የተለያዩ፣ እሴቶችና፣ ሐሳቦች፣ እኛ በምናውቀውና ብዙዎቹንም፣ እኛ በማናውቃቸው፣….. በአጋጣሚም ፣ምክንያቶች ይሁኑ፣ወይም፣ ታስቦበት፣ በተነደፉት፣የተለያዩ አላማዎችና ግቦች፣ላይ የተመሰረቱ ናቸው።ነገሩ ከዚያም አልፎ ይሄዳል። ባህል፣ አንድ ባህል፣ ከሕይወት ከተገኙ ተመክሮዎች ፣ ከተለያዩ ዕውቀቶችና ጥበቦች፣ እንዲሁም በተለይ፣ እሳት የላሱ፣የታሪክ ፣ ተወናዋኞች፣ አውጥተው አውርደው፣ በአቀረቡትና፣ በአዘጋጁት፣የጭንቅላት፣ሥራ ላይ፣ የተመሰረተና፣የተገነባ፣ መሠረት፣ ያለው ቤት፣ ማለት ነው።
ይህ በመሆኑም ነው፣ የአንዱ አገር ባህል፣ ከሌላው፣ ….ልክ እንደ እጽዋትና አታክልቶች፣እንደ ጫካና እንደ አበባዎች፣ ፍጹም፣ ከቦታ ቦታ፣ ይለያያሉ ። እዚህ አውሮፓ የሚበቅሉ፣እጽዋቶች፣ ከአሜሪካኖቹ፣ ይለያሉ። የአፍሪካው ደን፣ከእሲያ ይለያል።
ሰውም፣ አራዊቱም እንደዚሁ፣ ተለያዩ ናቸው።
፰
ይህ ስለተባለ ግን፣ በዓለም ላይ፣የሚታወቁ ትላልቅ፣ ባህሎች፣ እራሳቸውን ከሌላው አግለው፣ የሚኖሩ፣ ባህልና ሥልጣኔዎች አይደሉም። እንዲያውም አንዱ ከሌላው፣ አዳዲስ ሐሳቦችንና እሴቶችን፣ ወስዶና ገልብጦ፣ ለእራሱ ጥቅምና የእራሱን የመጨረሻ አላማ እስከአልተጻረረ ድረሰ፣ አእምሮውን የሚያሰፉ፣ አመለካከቶችን፣ ሕይወቱን የሚያስደስቱ፣ ሥራዎችን፣ ፣ ሐብቱን የሚያዳብሩ ፣ ግሩም የሆኑ ሐሳቦችን፣… ውድድርና፣ ጠንካራ መንፈስን፣ … ወኔን የሚቀሰቅሱ፣ ስልቶችን፣ ከሌላው፣ዓለምና ሕዝብ ወስዶና ገልብጦ፣ ለእራሱ፣ጥቅም ሲል እነሱን፣ ከመጠቀም፣ፈጽሞ፣ አንድ ባህል፣ አይመለስም።
ይህ ማለት ግን እንዳለ፣ሳያወጣና፣ ሳያመዛዝን፣ አንድ አገር፣ የሁሉንም የባዕድ፣ ወይም የጎረቤትን፣አገሮችን እሴት፣ ወይም ደግሞ፣ የውጭን አመለካከቶች፣ እንዳለ፣ “ሰርቆ ፣ ወይም አጥንቶ ፣ ይቀዳል፣ኮቲም አድርጎ ይወስዳል” ማለት፣ አይደለም። መርጦ፣ የሚወስዳቸው፣እላይ እንደተባለው፣ ከጠቅላላው ፕላኑ፣ ከትልቁ አላማው ጋር አብሮ ይሄዳሉ ብሎ የሚያምናቸውን ፣ ነገሮች ብቻ ነው።
ኢትዮጵያም፣አገራችን ደግሞ፣ በዚህ ቀልድ የማታውቅ፣ እንዲያውም፣ በዚህ፣ነገር፣የማትጠረጠር፣ነገር የገባት፣ ይህንንም በደንብ አድርጋ የምታውቅና የምትጠቀም፣እንደገና ፣ እንዲያውም በዚህ፣ብልሃት፣ የተካነች አገር ናት። የሚጠቅማትን ለይታም ታውቃለች።
እሱንም ወስዳ፣ በሥራ ላይ ትተረጉማለች።
ይህን ስታደርግ ግን፣ እሱዋ እራሱዋ ፣ አባቶቹዋ በስንት መከራ ፈልገው ያገኙላትን፣ የእራሱዋን የሆነውን ባህል፣ እነደ ዓይን ብሌን መጠበቁን ትታ፣ እሱን ወርውራ፣የባዕዱን ፣በጭፍን ዝም ብላ ይጠቅመኛል ፣ ብላ እነደ ሞኝ ፣ በትክክል ግልባጭ፣ “አንድ፣…ለአንድ ኮፒ “ሁሉም ነገር ቀድታ፣ የምትወስድ አገር፣ አይደለችም።…ወስዳለችም ፣ ብለን መናገር አንችልም።
እንደ አራስ ነብር፣ ባህሉዋን ፣ ሥርዓቱዋን ፣ የቆየ ወጉዋን….ወለም ዘለም ሳትል፣ የምትጠብቅ አገር፣ ከጃፓን ቀጥላ፣አለ ቢባል(ሌሎችንም መጥራት ይቻላል) ኢትዮጵያ ናት። በባህሉዋ፣…. በአለባበስዋ ሆነ፣ በምግብ አሰራርዋና በቅቀላ ሙያዋ፣… በመዚቃ ጨዋታ ሆነ፣ ….በሠርግ፣ ሰው ከሰው ጋር በአለው ግኑኝነት ሆነ፣ በደሰታና በሐዘን፣ጊዜ፣ ሌላው ቀርቶ፣ በቡና አጠጣጥ ሥነ-ሥርዓቶች ፣ በወንዶች ልጆች ግርዘት፣…. በአስክስታና ጭፈራ፣… በመሶብና በድስት አጠቃቀም፣…እንዲያውም፣ ከኦሪት ጊዜ ከነበረው ሕግጋቶች ጋር -ምግባችንን ፣ ከወሰድን፣… ከእሱ ጋር፣ የዛሬ ሦስት ሸህ፣ ከተነደፈው ሕግጋት ጋር፣ የአሁኑ ሁኔታ፣ ያኔ እንደነበረው፣አንድም ሳይቀየር፣ እስከ አሁን ድረስ፣ ሲወርድ ሲወራረድ፣ እሰከ እኛ ትውልድ ድረስ ተላልፎልናል።
ይህን ፣ እንደ ወደሁዋላ ቀርነት የሚመለከቱ ክፍሎች አይጠፉም። ግን ፣እንደዚህ አይነቱ አመለካከት፣አብዛኛውን ጊዜ የሚመሰረተው፣ የእራስን ባህልንና፣ የአበቶችን ቅርስ በመናቅ ላይ የተገነባነው። ወይም የአገርን ባህል፣ የእያንዳንዱን ሰው፣ መብት፣ በአለማክበርና እሱንም በአለማወቅ ላይ የተመሰረተ ነው።
እኛም እንደ ቻይናዎቹ ፣ እባብ ፣ አሳማ….እንቁራሪት፣ውሻና ድመት፣ ቁንቡርስና ትላትሎች፣ …መብላት አለብን የሚሉ ሰዎች አይጠፉም። ግን የሚረሱት፣ነገር ቢኖር፣ የቻይና ባህልና ታሪክ፣ ሌላ ነው፣ የእኛ የኢትዮጵያኖቹ ደግሞ ፍጹም የተለየ ነው። ስለ የተለያዩ ባህልና /ባህሎችም፣ የምናወራውም በዚሁ፣እላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ነው።
አንዴ ግን ኢትዮጵያ ተሳስታ፣ አብዳ ማለት ይቻላል፣ “የአምባገነኖችን ሪዕዮተ-ዓለም” ሳይቸግራት፣ ጎትታ፣ አንድ በአንድ ኮፒ አድርጋ አገሩዋ አስገብታለች።
ያ ነገር የት እንደከተተን ለመረዳት ከባድ አይደለም።
፱
ዛሬ ፣ ብዙ ታትመው ከወጡትና እጃችን ከገቡት፣ ጥናቶች እንደምናውቀው፣ ትላልቅ ባህሎችና ሥልጣኔዎች የተመሰረቱት፣ በተለያዩ ቦታዎችና አካባቢዎችም ፣ ሳይታሰብ ብቅ ብለው ያበቡት፣ በተለያዩ ጊዜያትና ዘመናት፣ የተለያዩ ዘሮችና ነገዶች ከነበሩበት ቦታ፣( ይህም ብዙ ምክንያት አለው) እየለቀቁና እየፈለሱ ወደ ሌላ አካባቢ በመሄዳቸውና በመሥፈራቸው ነው። ሠፍረውም ፣ እዚያ ቀደም ሲል ይኖሩ ከነበሩት ነገዶችና ጎሣዎችም ጋር በመቀላቀላቸው፣ ነው።
መጤዎቹ አዳዲስ ሐሳብ ና ዕውቀት ይዘው፣ በሰፈሩበት አዲስ መንደር፣ ግዛትም ሊሆን ይችላል፣…እዚያ ከነበረው ጋር ያዳቅላሉ፣… ይከልሳሉ፣ ያዋህዳሉ። ወይም እንዳአለ፣ዱሮ በአዲሱ ይተካሉ።
ሮም የተገነባችው፣…አቴን የተቆረቆረቺው፣… ባቢሎን የተመሰረተችው፣ ግብጽና ሰሜን አሜሪካ ፣ እሥራኤልና ቻይና፣ ሩሲያና ጃፓን፣ ህንድና ቱርክ፣አረብና ፋርስ….ጀርመንና…ሌሎቹ አገሮችም፣ በዓለም ታሪክ ላይ ብቅ ያሉት፣ በዚሁ መንገድና ዘዴ፣ በነገዶችና በጎሣዎች፣ እንቅስቃሴ፣ በፍለሳ ነው።
ከአንድ ድንጋይ – እንዲያው ነጻ- አውጪዎች ከመሬት ተነስተው ይንጫጫሉ እንጂ- ከአንድ ድንጋይ ተፈልጦ የወጣ ሕዝብ የለም። ማለት የምንችለው ነገር፣ ቢኖር፣ ሁሉም የአዳምና ሔዋን ልጆች ናቸው፣ የሚለውን እውነተኛ እምነት መቀበል ብቻ ነው።
ይህን ደግሞ፣ “እኛ፣ የእግአብሔር ፍጡር ሳንሆን፣ ከጦጣና ከዠንጄሮ ነው የመጣነው የሚሉ” ሰዎች ይቃወሙታል።
አንድ ሕዝብ ግን በዓለም ላይ አካባቢውን ሳይለቅ፣ እዚያው የተፈጠረበት፣ ምድር ላይ ቀርቶ ታሪኩንና ባህሉን ለልጅ ልጆቹ አስተላልፎ፣ እሰከ ዛሬ ቆይቶአል።እሱም፣… እሱዋም ኢትዮጵያ ናት።
ወጣ ወረደ፣ የኢትዮጵያ ልጆች ከጥንት -ከሉሲ፣ ወይም ከአዳምና ሄዋን ጊዜ ጀምሮ፣ የተወለዱበትን መንደርና አካባቢ፣ ግዛትና ክልል ሳይለቁ፣ ሕዝቦችዋ እዚያው፣አሁን ያሉበት ቦታ መንግሥት አቋቁመው፣ እዚያው ቀርተዋል። “እኛው፣ ፈልገን ያገኘነውን ባህልና ሥልጣኔ፣ እኛው ተንከባክበን፣ እስከ አሁን ድረስ አቆየነው “ ቢሉ፣ እነሱ ዕውንት አላቸው። ኢትዮጵያኖች፣–ይህን እንድገመው—ጥንታዊ መንደራቸውን ፣ግዛታቸውን ምን ጊዜም ለቀው፣ ነቅለው፣ እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች ፣ ሌላ ቦታ ተሰደው አልሄዱም። ለምን ብለው? አንዳንድ ልጆቹዋ አገሪቱን ለቀው፣ በገዛ ፈቃዳቸው ሄደዋል።
ይህም ማለት ፣ አገሪቱን በተለያዩ ጊዜያት፣ በቡድንና በቡድን ሰባስበው፣ በአናሳ ቁጥር፣ ትንሽ ሁነው ፣ እናት አገራቸውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ የሄዱ የሉሲና የአዳም ልጆች (ሩቅ አገርና አካባቢውን ለማቅናት ይሆናል፣ ወይም ጠላትን አሳዶ ለመቅጣት፣ ለወረራ፣ ወይም ዓለምን ለማየት) ኢትዮጵያን ለቀው የወጡና “የተሰደዱ”፣ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም። እንዲያውም፣ የሰው ልጆች ከኢትዮጵያ ተነስተው፣ ዓለምን ወረሩ የሚለው፣ የጠበብቶች፣ የሳይንቲስቶች ቲዎሪ፣ እላይ የተባለውን ሐሳብ ያጠናክራል።
በሌላ በኩል፣ ቀደም ብለው አገሪቱን ለቀው የወጡ፣የሉሲ- ልጆቹዋ፣ ከስንት ትውልድ በሁዋላ፣ ቀይ ባሕርን ተሻግረው፣ …ከየመንና፣ ከዛሬይቱ ሳውዲ፣ ወይም ከሰሜን ግብጽ፣….ከሱዳን፣… ከእሥራኤልና፣.. ከማደጋስካር፣ ከኬንያና ከኮንጎ፣…. ተነስተው፣ ወደ እናት አገራቸው፣ “አዳዲስ ዕወቀቶችና ጥበቦችን ቀስመው፣ሰብስበው ፣ተማልሰውም ገብተዋል።”
እንደዚሁ መረሳት የሌለበት ነገር ቢኖር፣ የኢትዮጵያ ግዛት፣ በቆዳ ስፋቱና በትልቅነቱ፣ ከዛሬው፣ የትና የት አልፎ እንደሚሄድም መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህቺ አገር፣ በምሥረቅ በሰሜን በኩል፣ እስከ ፋርሰ ፣እስከ ግሪክ ፣…አረብ አገሮችን ይዞ… እስከ ፍልስጤም ድረስ አካባቢውን ተቆጣጥራ፣ ቅኝ ግዛትም አድርጋ ትገዛ ነበር። የሰሜን የአፍሪካ ድንበሩዋም ከግብጽ ጋር ይዋሰን ነበር። የዛሬው፣ ሱዳን ፣… ኑቢያ የኢትዮጵያ ፣ ግዛትም ነበር። የዛሬው ሱማሌያ፣ …ጅቡቲ፣ …ኬንያና ኡጋንዳ፣… ታንዛኒያ፣… ብሩንዲ፣ ሩዋንዳም፣ ወደ ታች እስከ ማደጋስካር ድረስ…..ከኢትዮጵያ ጋር ተቀላቅለው ነበር። የአጤ ካሌብ የጦርና የንግድ፣ መርከብ ፣ በህንድ ውቅያኖስ ላይ ይንሣፈፍ ነበር።
እንግዲህ በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ፣መንግሥትና ግዛት፣ ከጥንታዊ ሮም፣(ግብጽን ስለ ያዙ) ከእነሱ ጋር ትጎራበት ነበር። ከጥንታዊ ግሪኮችም ጋር፣ የግዛት ድንበሩዋ እስከ ፋርስ በነበረበት ጊዜ፣ ቅርበትና ግንኙነት ይህች አገር ነበራት። እንዲያውም፣ የግሪክ አስተማሪዎች አክሱም ድረስ መጥተው፣ የኢትዮጵያን ነገሥታቶችን ያማክሩም፣ የስተምሩም፣ወታደሮቹዋን ያሰለጥኑም ነበር። በርካታ ተማሪዎች፣ ለትምህርት ወደ አቴን ተልከው፣ እዚያ ታሪክና ፍልስፍና፣ የህንጻና የእጅ ሥራም ተምረው ተመልሰዋል።
የግሪክ ቋንቋ፣ በአክሱም ቤተ- መንግሥት፣ ይነገር፣ይጻፍበትም፣ ነበር። የግዕዙ፣ መጽሐፍ ቅዱሳችን ከእብራዕይስጥና ከግሪክ፣ በቀጥታ እንደተተረጎመ፣ ሌላው ጠፍተው የማይገኙ፣ በገዳማችን የሚገኙ ጽሑፎች ይመሰክራሉ። ብዙ የአማርኛና የግዕዝ ቃላቶች፣ ከግሪክ የተወሰዱ ናቸው። “ውቅያኖስ”፣ የሚለው ቃል አንደኛው ነው።
እንግድህ ከዚህ ተነስተን፣ የኢትዮጵያን ባህልና ሥልጣኔ ለመረዳት፣ ከፈለግን ሁለት ወሳኝና አብይ የሆኑ ነገሮችን፣ በቀጥታ እናነሳለን። አንደኛው፣ “የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት መንግሥት”፣ -ነጮች ኢምፓየር- የሚሉት ነገር ነው።
ሁለተኛው፣ “ክርስቲያን ኢትዮጵያ “ ! የሚባለው፣ ጉዳይ ነው።
(አትቸኩሉ፣ ሌሎቹን ፣ አብይ ነገሮች ፈጽሞ አልረሳሁም….ይቀጥላል)
*

© ለ አእምሮ 2005 / © Le’Aimero Copyright 2013